ይሖዋን ታወድሰዋለህን?
“አምላክ ሆይ፣ እንደ ስምህ እንዲሁም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስጋናህ ነው።” እነዚህ የቆሬ ልጆች ከዘመሩት ትንቢታዊ መዝሙር መካከል የሚገኙ ቃላት ናቸው። (መዝሙር 48:10) ዛሬም በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንድ ታላቅ የመዘምራን ቡድን በመሆን የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ አምላክን በማወደስና ስሙን በሰፊው በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ። ይህንንም በ232 አገሮችና የባሕር ደሴቶች እንዲሁም ከ300 በሚበልጡ ቋንቋዎች በማከናወን ቃል በቃል “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” እየደረሱ ናቸው።
ከተለያየ ዓይነት ባሕል፣ ኅብረተሰብና ቋንቋ የመጡ ሕዝቦች ይሖዋን በአንድነት እንዲያወድሱ የሚገፋፋቸው ነገር ምንድን ነው? አንዱና ዋነኛው ምክንያት የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላገኙት ትክክለኛ እውቀት ያላቸው አመስጋኝነት ነው። መንፈሳዊ እውነት ከመናፍስትነትና እንደ ዘላለማዊ ሥቃይ ከመሰሉ ባሪያ ከሚያደርጉ ሃይማኖታዊ እምነቶች ነፃ አውጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 8:32) በተጨማሪም እውነት እንደ ፍቅር፣ ኃይል፣ ጥበብ እንዲሁም በምህረት ላይ የተመሠረተውን ፍትህ ያሉትን የአምላክን ግሩም ባሕርያት እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። አምላክ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ዘር ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ መስጠቱን ማወቃቸው ቅን የሆኑ ሰዎች ይሖዋን እንዲያወድሱትና እንዲያገለግሉት ከልብ ያነሳሳቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” በማለት በሰማይ ያሉት የመዘምራን ቡድን አባላት ከፍ ባለ ድምፅ ያስተጋባሉ። (ራእይ 4:11) እንዲህ ያለው የውዳሴ ድምፅ እንዲያው ከመገደድ ስሜት የመጣ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ካላቸው አድናቆት የመነጨ ነው።
ምሥራቹን በማወጅ አምላክን አወድስ
አንድ ሰው ይሖዋን ማወደሱ ዋነኛ የአምላክ አወዳሽ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ግሩም ምሳሌ መከተሉ ነው። የኢየሱስን ፈለግ መከተል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ተካፋይ መሆንን ይጨምራል። (ማቴዎስ 4:17, 23፤ 24:14) ይህ የስብከት እንቅስቃሴ ይሖዋን በማወደስ ረገድ በዓለም ዙሪያ ከሁሉ የላቀውን ድርሻ የያዘ ሥራ ሆኗል።
ይህ የስብከት ሥራ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስ ከመዳን ጋር በግልጽ ያያይዘዋል። ሮሜ 10:13–15 እንዲህ ይነበባል፦ “የጌታን [“የይሖዋን” አዓት] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?”
ባለፈው ዓመት ብቻ የይሖዋ ምሥክሮች ለስብከቱ ሥራ ከአንድ ቢልዮን ሰዓት በላይ አውለዋል። ከዚህ አምላክን የማወደስ እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ውጤቶች ተገኝተዋል። 314,000 የሚያህሉ ሰዎች ለይሖዋ ራሳቸውን መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት በማሳየት ከዚህ ውዳሴ አቅራቢ ከሆነው ታላቅ የመዘምራን ቡድን ጋር ተቀላቅለዋል።
ይሁን እንጂ በ1994 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ስለ ተገኙት ወደ 12, 288, 917 የሚያህሉ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ከእነዚህ ውስጥ ከ7,000,000 የሚበልጡት የምሥራቹ ሰባኪ በመሆን ይሖዋን በማወደሱ ሥራ ገና ያልተካፈሉ ናቸው። ይሁን እንጂ በዚህ በጣም አስፈላጊ በሆነው በዓል ላይ መገኘታቸው ውሎ አድሮ በታላቁ የአወዳሾች ቡድን ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሊጨመሩ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። እነዚህ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ይሖዋን የሚያወድሱ እንዲሆኑ ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል?
እርዳታ መስጠት
ፍላጎት ያሳዩ ብዙ ሰዎች ይሖዋን የማወደስ ምኞት ይኖራቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚፈለጉትን ብቃቶች ሊያሟሉ እንደማይችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል። “ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” ሲል መዝሙራዊው የተናገራቸውን ቃላት ቢያስታውሱ ጥሩ ነው። (መዝሙር 121:1, 2) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዳዊት የይሖዋ ቤተ መቅደስና የቲኦክራሲያዊው መስተዳድር ምድራዊ መቀመጫ ወደሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ተራራ ለማየት ዓይኑን አንስቷል። አምላክን ለማወደስና የመንግሥቱን መልእክት ለማወጅ የሚያስፈልገው እርዳታ ከይሖዋና ከድርጅቱ ብቻ እንደሚገኝ ከዚህ ለመደምደም እንችላለን።—መዝሙር 3:4፤ ዳንኤል 6:10
ዛሬ ይሖዋን ለማወደስ የሚፈልጉ ሰዎች ከአምላክ ምድራዊ ድርጅት ፍቅራዊ እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር ያለ ክፍያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማድረግ እርዳታ ይለግሳሉ። ይህ የትምህርት መርሐ ግብር የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ከማስተማር የበለጠ ነገርን ያጠቃልላል። ተማሪው እየተማረው ላለው ነገርና ይሖዋ እየተጠቀመበት ላለው ድርጅት አድናቆት እንዲያድርበት ይረዳዋል።
ከዚህ ጋር በመስማማት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን የሚመራው ምሥክር አዲስ የተገኘው እውነት ወደ ተማሪው ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ወደ ልቡ ጠልቆ እንዲገባ ለማድረግ ይጥራል። አስተማሪው ይሖዋ ዓላማውን በምድር ላይ ለማስፈጸም ድርጅቱን እንዴት አድርጎ እየተጠቀመበት እንዳለ ለተማሪው በግልጽ ከማስረዳት ወደ ኋላ ማለት የለበትም። እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ብሮሹርና የይሖዋ ምሥክሮች ከስሙ በስተ ጀርባ ያለው ድርጅት የተባለው የቪዲዮ ካሴት እንዲህ ያለውን ሥራ ለማከናወን ብዙ ጊዜ ጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋለ።
ይሖዋን ለማወደስ በጉዞ ላይ ያሉ ሰዎችን በመርዳት በኩል ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ተማሪው ገና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደ ጀመረ በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ ሊጋበዝ ይችላል። በዚህ ጊዜም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ የመሰብሰብንና ተሳትፎ የማድረግን አስፈላጊነት ይማራል። (ዕብራውያን 10:24, 25) የበላይ ተመልካቾች የእምነት ወንድሞቻቸውንና ይሖዋን ለማወደስ በጉዞ ላይ የሚገኙትን ሰዎች በመንፈሳዊ የሚያንጹና ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ስብሰባዎች በማዘጋጀት ተወዳዳሪ የሌለው እርዳታ ማበርከት ይችላሉ።
ልጆች ይሖዋን እንዲያወድሱ እርዷቸው
ልጆች በቅርብ ጊዜ ውስጥ የምሥራቹ አስፋፊ መሆን ከሚችሉ ብዙ ቁጥር ካላቸው ሰዎች መካከል የሚገኙ ናቸው። በተለይ አባቶች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” የማሳደግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኃላፊነት አለባቸው። (ኤፌሶን 6:4) አምላካዊ ፍርሃት ባላቸው ወላጆች በሚገባ የሠለጠኑ ልጆች ምንም እንኳን ትንንሽ ቢሆኑም ይሖዋን የማወደስ ምኞት በውስጣቸው ሊያሳድጉ ይችላሉ።
በአርጀንቲና የምትገኝ አንዲት ትንሽ ልጅ የመንግሥቱ አስፋፊ ለመሆን ብቁ የሚያደርጋትን እርዳታ እንዲሰጧት የጉባኤ ሽማግሌዎችን ቀርባ ለብዙ ወራት ደጋግማ ወተወተቻቸው። ከጊዜ በኋላም ወላጆቿና ሽማግሌዎቹ ያልተጠመቀች አስፋፊ ለመሆን እንዲፈቀድላት ተስማሙ። ከበር ወደ በር እየሄደች የመንግሥቱን መልእክት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ አስቀድማ ችላ ነበር። ምንም እንኳን ይህች ትንሽ ልጅ ማንበብ የማትችል ገና የአምስት ዓመት ልጅ ብትሆንም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የት ቦታ እንደሚገኙ በአእምሮዋ ይዛቸዋለች። አንድ ጥቅስ ፈልጋ ካገኘች በኋላ የቤቱ ባለቤት እንዲያነበው ትጠይቀዋለች፤ ከዚያም እርሷ ማብራሪያ ታክልበታለች።
ይሖዋን ለማወደስ ብቁ ለመሆን እድገት እያደረጉ ያሉትን ሰዎች በማበረታታትና በመርዳት ሽማግሌዎችና ወላጆች ሊያከናውኑ የሚችሉት ብዙ ጥሩ ነገር እንዳላቸው ግልጽ ነው።—ምሳሌ 3:27
ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ ዝምድና መመሥረት
አንተ ራስህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ረዘም ላለ ጊዜ መተባበር ጀምረህ በስብከቱ ሥራ ግን ገና አብረሃቸው ያልተካፈልክ ከሆንክስ? የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ብትጠይቅ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፦ ‘እውነትን እንዳገኘሁና ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አምናለሁን? ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛ መፍትሄ የአምላክ መንግሥት እንደሆነች አምኜ ተቀብያለሁን? ይሖዋን የሚያስከፋውን ጠቅላላ የሐሰት ሃይማኖትንና ዓለማዊ ወጎችን እንዲሁም ልማዶችን ጭራሽ ትቻለሁን? ለአምላክና ለጽድቅ ብቃቶቹ የጠለቀ ፍቅር አለኝን?’ (መዝሙር 97:10) ለእነዚህ ጥያቄዎች በሐቀኝነት አዎን የሚል መልስ መስጠት ከቻልክ ይሖዋን ከማወደስ ምን ይከለክልሃል?—ከሥራ 8:36 ጋር አወዳድር።
ይሖዋን ማወደስ ምሥራቹን በመስበክ ብቻ አያበቃም። ትክክለኛ እውቀት ካካበትክ፣ እውተኛ እምነት ካለህና ሕይወትህን ከመለኮታዊ ብቃቶች ጋር እያስማማህ ከሆንክ ከአምላክ ጋር ያለህን የግል ዝምድና ማጠናከር ያስፈልግሃል። እንዴት? በጸሎት ራስህን ለእርሱ በመወሰንና ይህንንም ውስንነትህን በውኃ ጥምቀት በማሳየት ነው። የዘላለም ሕይወት የማግኘትህ ጉዳይ ውሳኔ የሚጠይቅ ነው። ስለዚህ የሚከተለውን የኢየሱስን ምክር አሁኑኑ ሥራበት፦ “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”—ማቴዎስ 7:13, 14
አሁን ያለው የነገሮች ሥርዓት ወደ መጨረሻ ውድመቱ እየተቃረበ ስለሆነ ይህ የምናመነታበት ጊዜ አይደለም። ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ ዝምድና ለመመሥረት አፋጣኝ እርምጃ ውሰድ። በእርግጥም ይሖዋን ታወድሰዋለህን ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ የሚሰጥበት ጊዜ አሁን ነው።