ሰዎችን ደስተኛ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
አንድ ዓለም አቀፋዊ የተመራማሪዎች ቡድን ለሁለት አሥርተ ዓመታት ስለ ደስታ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል። የጥናቱ ውጤት ምን ሆነ? ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለው መጽሔት “ደስታ በአብዛኛው በውጪያዊ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ሆኖ አልተገኘም” ብሏል።
በተጨማሪም ይኸው ሳይንሳዊ መጽሔት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሀብትም ቢሆን ደስታ አያስገኝም። ሰዎች የኑሮ ደረጃቸው እየተሻሻለ ሲሄድ ይበልጥ ደስተኞች ሆነው አልተገኙም። . . . በብዙ አገሮች በገቢ መጠንና በደስታ መካከል ያለው ዝምድና ከቁጥር የሚገባ አይደለም።”
ደስተኛ ሰዎች አራት የጋራ ባሕርይ እንዳላቸው ጥናቶቹ አመልክተዋል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የማይጠሉ ከመሆናቸውም በላይ ለራሳቸው ከፍተኛ አክብሮት አላቸው፣ የግል ሕይወታቸው በራሳቸው ቁጥጥር ሥር ያለ እንደሆነ ይሰማቸዋል፣ ይሆናል የሚል አመለካከት አላቸው እንዲሁም በገዛ ራሳቸው ላይ ብቻ አያተኩሩም። በተጨማሪም ለደስተኛ ኑሮ ጥሩ ትዳርና ከሌሎች ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት አስተዋጽኦ ያደርጋል። እነዚህ ነገሮች ጥሩ ጤንነትና ረዥም ዕድሜም እንደሚያስገኙ ተደርሶበታል።
ሳይንቲፊክ አሜሪካን ያቀረበው የሚከተለው ሪፖርት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው:- “በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ይበልጥ ደስተኞች እንደሆኑ ተደርሶበታል። አንድ የሕዝባዊ አስተያየት ጥናት እንዳመለከተው በጣም ሃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች፣ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ግድየለሽ ከሆኑ ሰዎች በሁለት እጥፍ ደስተኞች ናቸው። አሥራ ስድስት አገሮች በ14 አገሮች በሚገኙ 166,000 ሰዎች ላይ ያካሄዱት ጥምር ጥናት ጨምሮ በሌሎች ጥናቶችም እንደታየው ደስታና የኑሮ እርካታ ማግኘት ከሃይማኖተኛነትና በአምልኮ ሥርዓቶች ላይ አዘውትሮ ከመገኘት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው።”
መዝሙራዊው ዳዊት ከረዥም ዘመናት በፊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” ብሎ በመጻፍ ደስታ ይሖዋ አምላክን በኅብረት ከማምለክ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለው አመልክቷል።—መዝሙር 122:1
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልደረቦቹን “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . መሰብሰባችንን አንተው” በማለት በጥብቅ ማሳሰቡ አያስደንቅም! (ዕብራውያን 10:24, 25፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሚያፈቅሩ ሁሉ መሰል እምነት ካላቸው ጋር ተሰብስቦ አምላክን ማምለክ በጣም ያስደስታል። በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የዚህን እውነተኝነት ተገንዝበዋል። እናንተም በአቅራቢያችሁ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ተገኝታችሁ ይህንን ደስታ እንድትቀምሱ ይጋብዟችኋል።