በሕይወትህ ትልቁን ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው?
“የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።”—መዝሙር 143:8
1. ንጉሥ ሰሎሞን ሰዎች ስለሚያሳድዷቸው ነገሮችና ስለሚያገኟቸው ውጤቶች ምን ብሎ ደምድሟል?
እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ አንተም ሕይወት በተለያዩ የሥራ እንቅስቃሴዎችና በሚያሳስቡ ነገሮች የተሞላ መሆኑን ሳትገነዘብ አትቀርም። ስለ ጉዳዩ ስታስብ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የግድ አስፈላጊ ሆነው ታገኛቸዋለህ። ሌሎቹ የሥራ እንቅስቃሴዎችና የሚያሳስቡ ነገሮች ደግሞ እምብዛም አስፈላጊ አይደሉም ወይም ከንቱ ናቸው። ይህን ቁም ነገር ተገነዘብክ ማለት እስከ ዛሬ ከተነሡት እጅግ ጠቢብ የሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ ከሆነው ከንጉሥ ሰሎሞን አባባል ጋር ትስማማለህ ማለት ነው። በሕይወት ዙሪያ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ሁሉ በጥሞና ካስተዋለ በኋላ “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” በማለት ደምድሟል። (መክብብ 2:4-9, 11፤ 12:13) ይህ ዛሬ ላለነው ሰዎች ምን ቁም ነገር ይዞልናል?
2. ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ሊጠይቁት የሚገባው መሠረታዊ ጥያቄ ምንድን ነው? ይህስ ወደ የትኞቹ ተዛማጅ ጥያቄዎች ይመራል?
2 ‘እውነተኛውን አምላክ ለመፍራትና ትእዛዙንም ለመጠበቅ’ የምትፈልግ ከሆነ የሚከተለውን ፈታኝ ጥያቄ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ነገር ምንድን ነው?’ በየዕለቱ ስለዚህ ጥያቄ እንደማታስብ የታወቀ ነው፤ ታዲያ አሁን ለምን አትመረምረውም? እንዲያውም እንደሚከተሉት ያሉትን ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎችም ያስታውሰናል፦ ‘ለሥራዬ ወይም ለሙያዬ አለዚያም ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ትኩረት እየሰጠሁ ይሆንን? ትዳሬ፣ ቤተሰቤና ወዳጆቼ በሕይወቴ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምንድን ነው?’ አንድ ወጣትም እንዲህ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል፦ ‘ትምህርት ትኩረቴንና ጊዜዬን የሚወስድብኝ ምን ያህል ነው? የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ፣ ስፖርት፣ አንድ ዓይነት መዝናኛ ወይም የቴክኖሎጂ ውጤት በእርግጥ ዋነኛ ፍላጎቶቼ ሆነዋልን?’ ዕድሜያችን ወይም ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ ለአምላክ አገልግሎት የሰጠሁት ቦታ ምንድን ነው?’ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች መወሰን አስፈላጊ መሆኑን ሳትስማማበት አትቀርም። ይሁን እንጂ ይህንን በጥበብ ለመወሰን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴትና ከየት ነው?
3. ለክርስቲያኖች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች መወሰን ምን ማድረግን ይጨምራል?
3 ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ተብሎ የተተረጎመው “ፓራማውንት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ የሚቀድም ወይም በአንደኛ ደረጃ ሊታይ የሚገባው ነገር ማለት ነው። ከይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ ከእነርሱ ጋር ከሚተባበሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው የአምላክ ቃል ተማሪዎች አንዱ ከሆንክ ቀጥሎ የሠፈረውን ሐቅ ልብ በል፦ “ለሁሉ ዘመን አለው፣ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1) ይህ ለቤተሰብህ ጉዳይ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየትን የሚያካትት መሆኑ የተገባ ነው። (ቆላስይስ 3:18-21) ሰብዓዊ ሥራ እየሠራህ ቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ነገር በሚገባ ማሟላትን ይጨምራል። (2 ተሰሎንቄ 3:10-12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) ለለውጥ ያህል ደግሞ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች ወይም አልፎ አልፎ በሚደረጉ መዝናኛዎች ለመደሰት ጊዜ ልትመድብ ትችላለህ። (ከማርቆስ 6:31 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ነገሩን በቁም ነገር ካሰብክበት ከእነዚህ መካከል ማንኛቸውም ቢሆኑ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳልሆኑ አትገነዘብምን? ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሌላ ነገር አለ።
4. ፊልጵስዩስ 1:9, 10 ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ከመወሰን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት መመሪያ የሚሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች በመወሰንና የጥበብ ውሳኔ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖራቸው ሳትገነዘብ አትቀርም። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያኖች በፊልጵስዩስ 1:9, 10 ላይ “በትክክለኛ እውቀትና፣ በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ” እንዲያድጉ ተመክረዋል። ለምን ዓላማ? ሐዋርያው ጳውሎስ በመቀጠል “ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ” [አዓት] በማለት ተናግሯል። ይህ ትክክል አይመስልህም? አንድ አስተዋይ ክርስቲያን በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመርኩዞ በአንደኛ ቦታ ሊቀመጥ ወይም በሌላ አባባል ቀዳሚ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ መወሰን ይችላል።
ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ምን እንደሆነ የሚጠቁም ምሳሌ
5. ቅዱሳን ጽሑፎች ለክርስቲያኖች ስለተተወላቸው ምሳሌ በሚገልጹበት ጊዜ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የያዘው ነገር ምን እንደነበር የሚያሳዩት እንዴት ነው?
5 ሐዋርያው ጴጥሮስ ከተናገራቸው ቃላት እውቀት ስላለው አንድ ውድ ገጽታ እንማራለን፦ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።” (1 ጴጥሮስ 2:21) አዎን፣ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ምን ስለመሆኑ ፍንጭ ለማግኘት እንዲረዳን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረውን ሐሳብ መመርመር እንችላለን። መዝሙር 40:8 ስለ እርሱ ትንቢት ሲናገር “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ይላል። ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል፦ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።”—ዮሐንስ 4:34፤ ዕብራውያን 12:2
6. የአምላክን ፈቃድ በማስቀደም ረገድ የኢየሱስን ዓይነት ውጤት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
6 ቁልፍ የሆነው ነገር የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደሆነ ልብ በል። ኢየሱስ ‘ፈጽሞ የተማረ ሁሉ እንደ መምህሩ ይሆናል’ በማለት ስለተናገረ እርሱ ያሳየው ምሳሌ ደቀ መዛሙርቱ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር። (ሉቃስ 6:40) እንዲሁም ኢየሱስ አባቱ ለሱ ባሰበው መንገድ በመመላለስ ለአምላክ ፈቃድ ትልቁን ቦታ መስጠት ‘ደስታን እንደሚያጠግብ’ አሳይቷል። (መዝሙር 16:11፤ ሥራ 2:28) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተገንዝበሃልን? የኢየሱስ ተከታዮች በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን ትልቅ ቦታ ሲሰጡት ‘ደስታ ከመጥገባቸውም’ ሌላ እውነተኛ ሕይወት ያገኛሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) እንግዲያው የአምላክን ፈቃድ ማድረግን በሕይወታችን ውስጥ የምናስቀድምባቸው ከአንድ በላይ ምክንያቶች አሉን ማለት ነው።
7, 8. ኢየሱስ ምን ፈተናዎች አጋጥመውት ነበር? ከዚህስ ምን እንማራለን?
7 ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን በጥምቀት እንዳሳየ ዲያብሎስ ወዲያውኑ እርሱን ከአቋሙ ፈቀቅ ለማድረግ ሞክሯል። እንዴት? ከሦስት አቅጣጫ ፈተና በማቅረብ ነበር። ኢየሱስ በሦስቱም ወቅት ቢሆን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 4:1-10) ይሁን እንጂ ሌሎች ፈተናዎች ማለትም ስቃይ፣ መዘባበቻ መሆን፣ በአስቆሮቱ ይሁዳ አልፎ መሰጠት፣ በሐሰት መወንጀል እና በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞት ይጠብቀው ነበር። ያም ሆኖ ግን የትኛውም ፈተና ቢሆን ታማኝ የሆነውን የአምላክ ልጅ ከአቋሙ ፈቀቅ አላደረገውም። ኢየሱስ በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ “አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን። . . . ፈቃድህ ትሁን” ብሎ ጸልዮአል። (ማቴዎስ 26:39, 42) ይህ ኢየሱስ የተወልን ምሳሌ በጥልቅ ሊነካንና ‘በጸሎት እንድንጸና’ ሊያደርገን አይገባምን?—ሮሜ 12:12
8 አዎን፣ በሕይወታችን ውስጥ በተለይ ደግሞ የእውነት ጠላት የሆኑና የአምላክን ፈቃድ የሚቃወሙ ሰዎች ሲገጥሙን ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለመወሰን መለኮታዊውን አመራር ማግኘታችን በጣም ጠቃሚ ነው። የታመነ የአምላክ አገልጋይ የነበረው ንጉሥ ዳዊት ከጠላቶቹ ተቃውሞ በገጠመው ጊዜ መመሪያ ለማግኘት ያቀረበውን ልመና አስታውስ። ይህ መዝሙር 143ን በከፊል ስንመረምር የምናየው ይሆናል። ይህም ከይሖዋ ጋር ያለንን የግል ዝምድና እንዴት እንደምናሻሽል እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ማድረግን በሕይወታችን ውስጥ አንደኛ ቦታ በመስጠት በኩል ይበልጥ መጠናከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድናስተውል ሊረዳን ይገባል።
ይሖዋ ጸሎቶቻችንን ይሰማል፤ይመልስልናልም
9. (ሀ) ዳዊት ኃጢአተኛ ቢሆንም እንኳን የተናገራቸው ቃላትና ድርጊቱ ምን ያሳያሉ? (ለ) ትክክለኛ የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?
9 ዳዊት ኃጢአተኛና ሟች ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ልመናዎቹን እንደሚሰማለት እምነት ነበረው። በትሕትና እንደሚከተለው ሲል ተማጽኗል፦ “አቤቱ፣ ጸሎቴን ስማ፤ በእውነት ልመናዬን አድምጥ፣ በጽድቅህም መልስልኝ ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባርያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ።” (መዝሙር 143:1, 2) ዳዊት አለፍጽምና እንዳለበት አልዘነጋም፤ ይሁንና አምላክን በሙሉ ልቡ ያገለግለው ነበር። በመሆኑም ለጸሎቱ በጽድቅ እንደሚመልስለት እርግጠኛ ነበር። ይህ እኛን አያበረታታንምን? የአምላክን የጽድቅ ደረጃዎች የማናሟላበት ጊዜ ቢኖርም በሙሉ ልባችን እስካገለገልነው ድረስ ጸሎታችንን እንደሚሰማልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (መክብብ 7:20፤ 1 ዮሐንስ 5:14) በጸሎት ከመጽናታችን ጎን ለጎን በእነዚህ ጭካኔ የሞላባቸው ቀናት ውስጥ ‘ክፉውን በመልካም የማሸነፍ’ ጽኑ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል።—ሮሜ 12:20, 21፤ ያዕቆብ 4:7
10. ዳዊት አስጨናቂ ጊዜያት ገጥመውት የነበረው ለምንድን ነው?
10 ዳዊትም እንደ እኛ ጠላቶች ነበሩት። ዳዊት ከሳኦል ለመሸሽ ማንም በማይደርስበት ገለልተኛ ቦታ ተሸሽጎ ለመኖር በተገደደበት ጊዜም ይሁን የጠላቶቹ ጥቃት መግቢያ መውጫ አሳጥቶት በነበረበት የንግሥናው ወቅት አስጨናቂ ጊዜያት አሳልፏል። ይህ እንዴት እንደነካው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጠላት ነፍሴን አሳድዶአታል፣ . . . በጨለማ አኑሮኛል። ነፍሴ [“መንፈሴ፣” አዓት] በውስጤ አለቀችብኝ፣ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።” (መዝሙር 143:3, 4) እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚያሳድር ነገር ገጥሞህ ያውቃልን?
11. በዚህ ዘመን የአምላክ አገልጋዮች ምን አስጨናቂ ወቅቶች ገጥመዋቸዋል?
11 የጠላት ተጽዕኖ፣ አስከፊ የኢኮኖሚ ችግር የሚያስከትለው ፈተና፣ ከባድ ሕመም ወይም ሌሎች የሚያስጨንቁ ችግሮች አንዳንድ የአምላክ ሕዝቦችን በውስጣቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያድርባቸው አድርገዋቸዋል። አንዳንዴም ልባቸው ሳይቀር እንደ ደነዘዘ ሆኖ ተሰምቷቸዋል። በየግላቸው “ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፣ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ . . . ተመልሰህም ደስ አሰኘኝ” በማለት ጩኸታቸውን ያሰሙ ያክል ነበር። (መዝሙር 71:20, 21) እርዳታ ያገኙት እንዴት ነው?
የጠላትን ጥቃት መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
12. ንጉሥ ዳዊት የገጠመውን አደጋ እንዲሁም የተለያዩ ፈተናዎች የተወጣው እንዴት ነው?
12 መዝሙር 143:5 ዳዊት አደጋና ከባድ ፈተናዎች ባዋከቡት ጊዜ ምን እንዳደረገ ይገልጻል፦ “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ።” ዳዊት አምላክ ከሕዝቦቹ ጋር ስላደረጋቸው ግንኙነቶችና እርሱንም እንዴት ከችግር እንዳወጣው አስታውሷል። ይሖዋ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል ባደረጋቸው ነገሮች ላይ አሰላስሏል። አዎን፣ ዳዊት ያለማቋረጥ ስለ አምላክ ሥራዎች ያስብ ነበር።
13. ፈተና በሚገጥመን ጊዜ የጥንቶቹንም ሆነ በዘመናችን ያሉትን የታመኑ አገልጋዮች ምሳሌ ማሰባችን ለመጽናት የሚረዳን እንዴት ነው?
13 እኛስ አምላክ ከሕዝቦቹ ጋር ስላደረጋቸው ግንኙነቶች ብዙ ጊዜ እናስብ የለምን? አዎን እናስባለን! ይህም በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩት ‘እንደ ደመና ያሉ ብዙ ምሥክሮች’ ስላስመዘገቡት ታሪክ ማሰብን ይጨምራል። (ዕብራውያን 11:32-38፤ 12:1) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ‘የቀድሞውን ዘመንና’ በጽናት ያሳለፉትን ጊዜ እንዲያስቡ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 10:32-34) የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ላይ ስለወጡት በዘመናችን የሚገኙ ምሥክሮች ተሞክሮዎችስ ምን ማለት ይቻላል?a በዚህ መጽሐፍና በሌሎች ቦታዎችም የሚገኙት ዘገባዎች ይሖዋ ሕዝቦቹ እገዳዎችን፣ እስርን፣ የሕዝብ ድብደባ እንዲሁም በማጎሪያና የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች ውስጥ የገጠማቸውን ችግር በጽናት እንዲቋቋሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ ለማስታወስ ይረዱናል። እንደ ቡሩንዲ፣ ላይቤርያ፣ ሩዋንዳ እና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ በመሳሰሉት በጦርነት የሚታመሱ አገሮች ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመዋቸዋል። የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ጠንካራ ዝምድና ጠብቀው በመገኘታቸው ተቃውሞ በሚነሣበት ጊዜ መጽናት ችለዋል። የአምላክን ፈቃድ ማድረግን በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሰጡትን ሁሉ በክንዱ ደግፏቸዋል።
14. (ሀ) ይሖዋ እኛ ካለንበት ሁኔታ ጋር ሊመሳሰለል በሚችል ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን እንደሚደግፍ የሚያሳየው አንዱ ምሳሌ የትኛው ነው? (ለ) ከዚህ ምሳሌ ምን ትማራለህ?
14 ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ የጭካኔ ድርጊት ተፈጽሞብኝ አያውቅም ወደፊትም ፈጽሞ ይገጥመኛል ብዬ አላስብም ትል ይሆናል። ይሁንና አምላክ ሕዝቦቹን የሚደግፈው አንዳንድ ሰዎች በጣም ከባድ እንደሆኑ አድርገው በሚያስቧቸው ወቅቶች ላይ ብቻ አይደለም። ብዙ “ተራ” ሰዎች የገጠሟቸውን “የተለመዱ” ሁኔታዎች እንዲያሸንፉ ረድቷቸዋል። ከብዙዎቹ ምሳሌዎች መካከል አንዱ የሚከተለው ነው፦ የታኅሣሥ 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ፐነሎፒ ማክሪስ የተናገረችውን ተሞክሮ ይዞ ወጥቷል። ይህ ታሪክ ክርስቲያናዊ ንጹሕ አቋም ጠባቂትን የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ጎረቤቶቿ ያደረሱባትን ምን ዓይነት ችግሮች እንደተቋቋመች፣ ከባድ የጤና ችግሮችን እንዴት ትታገል እንደነበርና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ለመቆየት ምን ያህል ጥረት እንዳደረገች ታስታውሳለህ? በሚትሊን ስላገኘችውስ አስደሳች ተሞክሮ ምን ትላለህ? ቁም ነገሩ እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች በመወሰንና የአምላክን ፈቃድ ማድረግን በሕይወታችን ውስጥ በአንደኛ ቦታ በማስቀመጥ ረገድ ሊረዱን እንደሚችሉ መገንዘብህ ላይ ነው።
15. ልናሰላስልባቸው የሚገቡን አንዳንዶቹ የይሖዋ ሥራዎች ምንድን ናቸው?
15 ይህ ዳዊት እንዳደረገው በይሖዋ ሥራዎች ላይ እንድናሰላስል ያበረታታናል። ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም ልጁ እንዲሞት፣ ትንሣኤ እንዲያገኝና ከፍ ያለ ክብር እንዲጎናጸፍ በማድረግ መዳን የሚገኝበትን ዝግጅት አድርጓል። (1 ጢሞቴዎስ 3:16) ሰማያዊ መንግሥቱን አቋቁሟል፣ ሰማይን ከሰይጣንና ከአጋንንቱ አጽድቷል፤ እንዲሁም በዚህች ምድር ላይ እውነተኛ አምልኮ ተመልሶ እንዲቋቋም አድርጓል። (ራእይ 12:7-12) መንፈሳዊ ገነት አቋቁሞ ሕዝቦቹ ጭማሪ እንዲያገኙ በማድረግ ባርኳቸዋል። (ኢሳይያስ 35:1-10፤ 60:22) በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻ ምሥክርነት በመስጠት ላይ ናቸው። (ራእይ 14:6, 7) በእርግጥም የምናሰላስልባቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
16. በምን ላይ እንድናተኩር ተበረታተናል? ይህስ ምን እምነት ያሳድርብናል?
16 በሰብዓዊ ጥረቶች አእምሮን ከማስጠመድ ይልቅ በአምላክ የእጅ ሥራዎች ላይ ማተኮራችን የይሖዋን ኃይል ሊገድበው የሚችል አንዳችም ነገር እንደሌለ እምነት ያሳድርብናል። ይሁንና እነዚህ ሥራዎቹ በሰማይና በዚህች ምድር በተከናወኑት ግሩም የሆኑ ግዑዛን ፍጥረታት ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። (ኢዮብ 37:14፤ መዝሙር 19:1፤ 104:24) ጥንት የነበሩት የተመረጡ ሕዝቦቹ ካሳለፉት ተሞክሮ እንደታየው ድንቅ ሥራዎቹ ሕዝቦቹን ከጠላቶቻቸው የጭቆና መዳፍ ነፃ ለማውጣት የሠራቸውን ነገሮችም ይጨምራሉ።—ዘጸአት 14:31፤ 15:6
የምንሄድበትን መንገድ ማወቅ
17. ይሖዋ ለዳዊት ምን ያህል እውን ነበር? ይህስ ለእኛ ምን ነገር ያረጋግጥልናል?
17 ዳዊት በውስጡ የሕይወት ውኃ እንዳይደርቅበት በመስጋት እርዳታ ለማግኘት ጸልዮአል፦ “እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች። አቤቱ፣ ፈጥነህ ስማኝ፤ ነፍሴ [“መንፈሴ፣” አዓት] አልቃለች፤ ፊትህን ከኔ አትመልስ፣ ወደ ጉድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን።” (መዝሙር 143:6, 7) ዳዊት ኃጢአተኛ ቢሆንም የነበረበትን ሁኔታ አምላክ እንደሚረዳለት ያውቅ ነበር። (መዝሙር 31:7) እኛም አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊነታችን እንደተሟጠጠ ሆኖ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ አብቅቶልናል ማለት አይደለም። ጸሎቶቻችንን የሚሰማው ይሖዋ አፍቃሪ በሆኑ ሽማግሌዎች፣ መጠበቂያ ግንብ ላይ በሚወጡ ርዕሶች ወይም ሆን ተብሎ ለእኛ የተዘጋጁ በሚመስሉ የጉባኤ ክፍሎች አማካኝነት መንፈሳችንን በማደስ እንደገና የምንነቃቃበትን መንገድ ሊያፋጥንልን ይችላል።—ኢሳይያስ 32:1, 2
18, 19. (ሀ) ይሖዋን ከልባችን መማጸን የሚኖርብን ስለ ምንድን ነው? (ለ) ስለ ምን ነገርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
18 በይሖዋ የምንታመን መሆናችን እንደሚከተለው ብለን እንድንማጸነው ያነሳሳናል፦ “አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ ነፍሴን ወደ አንተ አንስቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።” (መዝሙር 143:8) በአንድ የግሪክ ደሴት ላይ ብቻዋን የነበረችውን እህት ማክሪስን ይሖዋ መታመኛ ሳይሆንላት ቀርቷልን? የእርሱን ፈቃድ ማድረግን በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሰጠኸው አንተንስ ቢሆን ያሳፍርሃልን? ዲያብሎስና የእርሱ ወኪሎች ስለ አምላክ መንግሥት የማወጁን ሥራችንን ለማስተጓጎል ወይም ጭራሹኑ ለማቆም ይፈልጋሉ። የምንኖረው እውነተኛው አምልኮ በተፈቀደበትም አገር ይሁን ተጽእኖ በሚደረግበት አገር በአንድነት የምናሰማው ጸሎት ዳዊት እንደሚከተለው ሲል ካቀረበው ልመና ጋር ይስማማል፦ “አቤቱ፣ ወደ አንተ ተማጽኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ።” (መዝሙር 143:9) ከመንፈሳዊ አደጋዎች ጥበቃ የምናገኘው በልዑሉ ጥላ ሥር ስናድር ነው።—መዝሙር 91:1
19 ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምን ስለመሆኑ ያለን የጸና እምነት በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመ ነው። (ሮሜ 12:1, 2) እንግዲያውስ ዓለም በሰብዓዊ ዓይን በጣም አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምንበትን ነገር በውስጣችሁ ለመቅረጽ የሚያደርገውን ጥረት ተቋቋሙ። ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር የአምላክን ፈቃድ ማድረግ መሆኑን እንደምትገነዘቡ በእያንዳንዱ የኑሯችሁ ዘርፍ ማሳየታችሁን ቀጥሉ።—ማቴዎስ 6:10፤ 7:21
20. (ሀ) ከመዝሙር 143:1-9 ስለ ዳዊት ምን ተምረናል? (ለ) ዛሬ ክርስቲያኖች የዳዊትን መንፈስ ሊያንጸባርቁ የሚችሉት እንዴት ነው?
20 የመዝሙር 143 የመጀመሪያ ዘጠኝ ቁጥሮች ዳዊት ከይሖዋ ጋር የነበረውን የተቀራረበ ዝምድና የሚያጎሉ ናቸው። ጠላቶቹ ዙሪያውን ባጠሩበት ጊዜ በፍርሃት ሳይሸማቀቅ አምላክ መመሪያ እንዲሰጠው ተማጽኗል። ትክክለኛውን ጎዳና ለመከተል የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት ልቡን አፍስሷል። ዛሬም ቢሆን በምድር ላይ ያሉት በመንፈስ የተቀቡ ቀሪዎችና ጓደኞቻቸው ያሉበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ እንዲመራቸው በመማጸን ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ያሳያሉ። ዲያብሎስና ዓለም ተጽዕኖ ቢያሳድሩባቸውም የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸውን ከማንኛውም ነገር በፊት ያስቀድማሉ።
21. ሌሎች ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ ስለሚገባው ነገር እንዲማሩ ለመርዳት ከፈለግን እኛ ጥሩ ምሳሌ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
21 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ያሉት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነገር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ለቃሉ ታዛዥ ከመሆን ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጎላ አድርጎ የሚገልጸውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ 13ኛ ምዕራፍ ስናስጠናቸው ይህንን ነጥብ እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው እንችላለን።b እርግጥ የምናስተምራቸውን ነገር ስንሠራበት ሊያዩ ይገባል። እነርሱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊከተሉት የሚገባው ጎዳና ምን እንደሆነ ይገነዘባሉ። እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ በግላቸው ሲገነዘቡ ብዙዎቹ ራሳቸውን ለመወሰንና ለመጠመቅ ይገፋፋሉ። ከዚያ ወዲያ ጉባኤዎችም በሕይወት ጎዳና መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ ይረዷቸዋል።
22. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የሚብራሩት ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው?
22 ብዙዎች የአምላክ ፈቃድ በሕይወታቸው ውስጥ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ እንደሚገባው ለመናገር ምንም አያመነቱም። ይሁንና ይሖዋ አገልጋዮቹ ፈቃዱን እንዲያደርጉ ደረጃ በደረጃ የሚያስተምራቸው እንዴት ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል? በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እነዚህ ጥያቄዎችና ቁልፍ የሆነው የመዝሙር 143:10 ጥቅስ ይብራራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ እና ትራክት ማኅበር በ1993 የታተመ
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ እና ትራክት ማኅበር በ1995 የታተመ።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ በፊልጵስዩስ 1:9, 10 መሠረት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች መወሰን የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚሰጠው ነገር ምን እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው?
◻ ዳዊት በፈተና ወቅት ካደረገው ነገር ምን መማር እንችላለን?
◻ መዝሙር 143:1-9 ዛሬ የሚረዳን በምን መንገድ ነው?
◻ በእኛ ሕይወት ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት የወሰደው እርምጃ በይሖዋ ላይ እንደሚታመን የሚያሳይ ነበር
[ምንጭ]
ምንጭ፦ Illustrirte Pracht - Bibel/Heilige Schrift des Alten und Neuen Testaments, nach der deutschen Uebersetzung D. Martin Luther’s