እያንዳንዱን ቀን ለአምላክ ክብር ለማምጣት ተጠቀሙበት
መዝሙራዊው ዳዊት “በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮ ነበር። አክሎም “የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ” ብሏል። (መዝ. 143:8) ጠዋት ከእንቅልፍህ ተነስተህ ላገኘኸው ተጨማሪ ቀን ይሖዋን ስታመሰግነው ልክ እንደ ዳዊት፣ ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ይሖዋ እንዲመራህና ከሁሉ የተሻለውን እርምጃ እንድትወስድ እንዲረዳህ ትማጸነዋለህ? እንዲህ እንደምታደርግ ጥርጥር የለውም።
ራሳችንን የወሰንን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ‘ስንበላም ሆነ ስንጠጣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስናደርግ’ “ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር” ለማድረግ እንጥራለን። (1 ቆሮ. 10:31) ዕለታዊ ሕይወታችንን የምንመራበት መንገድ ይሖዋን ሊያስከብር አሊያም ሊያስነቅፍ እንደሚችል እንገነዘባለን። በተጨማሪም ሰይጣን የክርስቶስን ወንድሞች አልፎ ተርፎም በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ “ቀንና ሌሊት” እንደሚከሳቸው የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አንዘነጋም። (ራእይ 12:10) ስለዚህ ሰይጣን የሚሰነዝረው ክስ ሐሰት መሆኑን የሚያረጋግጥ መልስ ለመስጠት እንዲሁም ለሰማዩ አባታችን “ቀንና ሌሊት” ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ የእሱን ልብ ደስ ለማሰኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—ራእይ 7:15፤ ምሳሌ 27:11
በሕይወት የምናሳልፈውን እያንዳንዱን ቀን ለአምላክ ክብር ለማምጣት ልንጠቀምበት የምንችልባቸውን ሁለት ዋና ዋና መንገዶች በአጭሩ እንመርምር። የመጀመሪያው፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስቀደም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት ነው።
ለአምላክ የገባነውን ቃል ማክበር
ራሳችንን ለይሖዋ በመወሰን እሱን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት እንዳለን ገልጸን ነበር። በተጨማሪም “በየቀኑ” አልፎ ተርፎ ለዘላለም በመንገዶቹ ለመመላለስ ለይሖዋ ቃል ገብተናል። (መዝ. 61:5, 8 NW) ታዲያ ይህን ቃላችንን የምናከብረው እንዴት ነው? ይሖዋን በሙሉ ልባችን እንደምንወደው በእያንዳንዱ ቀን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ እንድንፈጽማቸው የሚጠብቅብንን ኃላፊነቶች በግልጽ ይናገራል። (ዘዳ. 10:12, 13) ከእነዚህ ኃላፊነቶች መካከል አንዳንዶቹ “አምላክ የሰጠን ኃላፊነቶች” በሚለው ገጽ 22 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል። እነዚህ ሁሉ ኃላፊነቶች ከአምላክ ያገኘናቸው በመሆናቸው አስፈላጊ ናቸው። ታዲያ የእኛን ትኩረት የሚሹ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ጉዳዮች በአንድ ጊዜ ሲገጥሙን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የትኛው እንደሆነ መወሰን የምንችለው እንዴት ነው?
ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለምናከናውነው ቅዱስ አገልግሎት ሲሆን ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን፣ ጸሎትን፣ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችንና አገልግሎታችንን የሚያካትት ነው። (ማቴ. 6:33፤ ዮሐ. 4:34፤ 1 ጴጥ. 2:9) መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን ሙሉ ቀን እንደማይወስዱብን የታወቀ ነው። ሥራ፣ ትምህርትና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች በፕሮግራማችን ውስጥ መካተት ይኖርባቸዋል። እንደዚያም ሆኖ ሥራችንንና ሌሎች ተግባሮቻችንን የምናከናውንበት መንገድ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደመገኘት ላሉ የቅዱስ አገልግሎት ዘርፎች እንቅፋት እንዳይሆንብን የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። ለምሳሌ ያህል፣ እረፍት ወጥተን ከአካባቢያችን እርቀን ለመዝናናት ስናስብ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉብኝት፣ ልዩ፣ ወረዳ ወይም የአውራጃ ስብሰባ እንዳያመልጠን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ኃላፊነቶቻችንን አቀናጅተን ማከናወን የምንችልበትን እቅድ ማውጣት እንችል ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ከቤተሰባችን ጋር ጊዜ ለማሳለፍ እንዲረዳን የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳቱ ሥራ ላይ በቤተሰብ ደረጃ መካፈል እንችላለን፤ ወይም የምሳ እረፍታችንን በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት ለሥራ ባልደረቦቻችን አሊያም አብረውን ለሚማሩ ምሥክርነት ለመስጠት ልንጠቀምበት እንችላለን። በእርግጥም ሥራ ከመፈለግ፣ ትምህርት ቤት ወይም ጓደኛ ከመምረጥ ጋር በተያያዘ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠውን ጉዳይ ማለትም የይሖዋን አምልኮ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።—መክ. 12:13
ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ
ይሖዋ ለሌሎች አሳቢነት እንድናሳይ ብሎም መልካም ነገር እንድናደርግላቸው ይፈልግብናል። ሰይጣን ግን ራስ ወዳድነትን ያስፋፋል። የሰይጣን ዓለምም ቢሆን ‘ራሳቸውን በሚወዱ፣’ ‘ደስታን በሚወዱ’ እንዲሁም ‘ለሥጋ ብለው በሚዘሩ’ ሰዎች የተሞላ ነው። (2 ጢሞ. 3:1-5፤ ገላ. 6:8) ብዙ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር በሌሎች ላይ የሚያስከትለው ውጤት እምብዛም አያሳስባቸውም። ‘የሥጋ ሥራ’ የማይታይበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል።—ገላ. 5:19-21
በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ተገፋፍተው ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ፍቅርን፣ ደግነትንና ጥሩነትን የሚያሳዩ ሰዎች አስተሳሰብ ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! (ገላ. 5:22) የአምላክ ቃል፣ ከራሳችን ጥቅም ይልቅ የሌሎችን እንድናስቀድም ይነግረናል። ስለዚህ በሰዎች የግል ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ላለመግባት ጥንቃቄ ማድረግ ቢኖርብንም ለሌሎች ሰዎች ጉዳይ ትኩረት እንሰጣለን። (1 ቆሮ. 10:24, 33፤ ፊልጵ. 2:3, 4፤ 1 ጴጥ. 4:15) በተለይ ደግሞ ለእምነት አጋሮቻችን አሳቢነት እናሳያለን። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። (ገላ. 6:10) ዛሬ ለምታገኘው ሰው ደግነት ማሳየት የምትችልበት አጋጣሚ ለማግኘት ጥረት ታደርጋለህ?—በገጽ 23 ላይ የሚገኘውን “አሳቢነት አሳዩአቸው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ለሰዎች አሳቢነት ለማሳየት የተለየ ቀን ወይም ሁኔታ መጠበቅ አያስፈልገንም። (ገላ. 6:2፤ ኤፌ. 5:2፤ 1 ተሰ. 4:9, 10) ከዚህ ይልቅ በየቀኑ ሌሎች ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ጥረት በማድረግ አመቺ በማይሆንበት ጊዜም እንኳ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ዝግጁ እንሆናለን። ያለንን ነገር ሁሉ ማለትም ጊዜያችንን፣ ቁሳዊ ንብረታችንን፣ ተሞክሯችንንና ያካበትነውን ጥበብ በልግስና መስጠት እንፈልጋለን። ይሖዋ፣ እኛ ለሌሎች ለጋስ ከሆንን እሱም ለእኛ ለጋስ እንደሚሆንልን ቃል ገብቶልናል።—ምሳሌ 11:25፤ ሉቃስ 6:38
“ቀንና ሌሊት” ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ
ለይሖዋ “ቀንና ሌሊት” ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ በእርግጥ ይቻላል? አዎን፣ በሁሉም የአምልኮታችን ዘርፎች አዘውታሪና ታታሪ በመሆን ይህን ማድረግ ይቻላል። (ሥራ 20:31) የአምላክን ቃል በየቀኑ በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል፣ ሳናቋርጥ በመጸለይ፣ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በመጣርና ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ ለመመሥከር በመጠቀም ሕይወታችን በቅዱስ አገልግሎት የተሞላ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን።—መዝ. 1:2፤ ሉቃስ 2:37፤ ሥራ 4:20፤ 1 ተሰ. 3:10፤ 5:17
ታዲያ በግለሰብ ደረጃ ለይሖዋ እንዲህ ዓይነት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረብን ነው? ቅዱስ አገልግሎት እያቀረብን ከሆነ በዕለቱ የምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ እሱን ለማስደሰትና ሰይጣን ያነሳው ክስ ሐሰት መሆኑን ለመመሥከር ፍላጎት እንዳለን የሚያንጸባርቅ ይሆናል። የምንገኝበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በምናደርገው ነገር ሁሉ ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን። ውሳኔ ስናደርግ እንዲሁም ከአነጋገራችንም ሆነ ከጠባያችን ጋር በተያያዘ ይሖዋ ባወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመራት እንጥራለን። ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ለሚያደርግልን እንክብካቤና ድጋፍ ያለንን አድናቆት ሙሉ በሙሉ በእሱ በመተማመን እንዲሁም ጉልበታችንን ሁሉ ለእሱ አገልግሎት በማዋል መግለጽ እንችላለን። በተጨማሪም ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ሳንፈጽም ቀርተን ምክርና ተግሣጽ ከተሰጠን በደስታ እንቀበላለን።—መዝ. 32:5፤ 119:97፤ ምሳሌ 3:25, 26፤ ቆላ. 3:17፤ ዕብ. 6:11, 12
ስለዚህ በእያንዳንዱ ቀን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ መኖራችንን እንቀጥል። እንዲህ ማድረጋችን ለነፍሳችን እረፍት የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ በሰማይ የሚኖረው አባታችንን ፍቅራዊ እንክብካቤ ለዘላለም ለማግኘት ያስችለናል።—ማቴ. 11:29፤ ራእይ 7:16, 17
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አምላክ የሰጠን ኃላፊነቶች
• ሳናቋርጥ መጸለይ።—ሮም 12:12
• መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ማጥናት፤ ያነበብነውን በሥራ ላይ ማዋል።—መዝ. 1:2፤ 1 ጢሞ. 4:15
• በጉባኤ ተገኝቶ ይሖዋን ማምለክ።—መዝ. 35:18፤ ዕብ. 10:24, 25
• የቤተሰባችንን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት ማሟላት።—1 ጢሞ. 5:8
• የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ፤ እንዲሁም ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ።—ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20
• አካላዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ጤንነታችንን መንከባከብ፤ ይህም በጤናማ መዝናኛዎች ላይ ለመካፈል ዝግጅት ማድረግን ይጨምራል።—ማር. 6:31፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ 1 ጢሞ. 4:8, 16
• የጉባኤ ኃላፊነቶቻችንን መወጣት።—ሥራ 20:28፤ 1 ጢሞ. 3:1
• የቤታችንንና የመንግሥት አዳራሻችንን ንጽሕና መጠበቅ።—1 ቆሮ. 10:32
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
አሳቢነት አሳዩአቸው
• ለአንድ አረጋዊ ወንድም ወይም እህት።—ዘሌ. 19:32
• በአካላዊ ወይም በስሜታዊ ሕመም ለሚሠቃይ ሰው።—ምሳሌ 14:21
• የእናንተ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልገው አንድ የጉባኤ አባል።—ሮም 12:13
• ለቅርብ የቤተሰብ አባል።—1 ጢሞ. 5:4, 8
• የትዳር ጓደኛ ለሞተባት ወይም ለሞተችበት የእምነት ባልንጀራ።—1 ጢሞ. 5:9
• ጉባኤያችሁን በትጋት ለሚያገለግል ሽማግሌ።—1 ተሰ. 5:12, 13፤ 1 ጢሞ. 5:17