ምዕራፍ 28
“አንተ ብቻ ታማኝ ነህ”
1, 2. ክህደት ለንጉሥ ዳዊት እንግዳ ነገር አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?
ክህደት ለንጉሥ ዳዊት እንግዳ ነገር አልነበረም። በነውጥ የተሞላው የግዛት ዘመኑ በአንድ ወቅት የገዛ ብሔሩ አባላት በጠነሰሱት ሴራ ቀውስ ገጥሞት ነበር። በተጨማሪም ዳዊት የቅርቤ ናቸው የሚላቸው ሰዎች እንኳ ሳይቀር ከድተውታል። የዳዊት የመጀመሪያ ሚስት የሆነችውን ሜልኮልን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጀመሪያ ላይ “ዳዊትን ትወደው ነበር”፤ የንግሥና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትረዳውና ትደግፈው እንደነበረም ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ “በልቧ ናቀችው”፤ እንዲያውም ዳዊትን “እንደ አንድ ተራ ሰው” በመቁጠር ንቀቷን አሳይታለች።—1 ሳሙኤል 18:20፤ 2 ሳሙኤል 6:16, 20
2 የዳዊት የቅርብ አማካሪ የነበረው አኪጦፌልም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው። ምክሩ መሬት ጠብ የማይል ከመሆኑ የተነሳ በቀጥታ ከይሖዋ እንደመጣ ቃል ተደርጎ ይታይ ነበር። (2 ሳሙኤል 16:23) ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ እምነት የተጣለበት የዳዊት ሚስጥረኛ ከጊዜ በኋላ በዳዊት ላይ ካመፁ ሰዎች ጋር በማበር ከሃዲ ሆነ። ይህን ሴራ የጠነሰሰውስ ማን ነበር? የራሱ የዳዊት ልጅ አቢሴሎም ነው! ይህ ሴረኛ አሳቢ መስሎ በመቅረብና “የእስራኤልን ሰዎች ልብ [በመስረቅ]” የዳዊትን ሥልጣን መቀናቀን ጀመረ። አቢሴሎም ያቀነባበረው ዓመፅ እያየለና እየተጠናከረ በመምጣቱ ንጉሥ ዳዊት ነፍሱን ለማዳን መሸሽ ግድ ሆኖበታል።—2 ሳሙኤል 15:1-6, 12-17
3. ዳዊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?
3 ከዳዊት ጎን በታማኝነት የቆመ ማንም አልነበረም ማለት ነው? ዳዊት በመከራው ዘመን ሁሉ ከጎኑ የማይለይ ታማኝ ወዳጅ እንዳለው ያውቅ ነበር። ይህ ታማኝ ወዳጁ ማን ነው? ከይሖዋ አምላክ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። ዳዊት ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ” ብሏል። (2 ሳሙኤል 22:26) ታማኝነት ምንድን ነው? ይሖዋ ይህን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ አርዓያ የሆነውስ እንዴት ነው?
ታማኝነት ምንድን ነው?
4, 5. (ሀ) “ታማኝነት” ምንድን ነው? (ለ) ታማኝነት እንዲሁ እምነት የሚጣልበት ወይም አስተማማኝ ከመሆን የሚለየው እንዴት ነው?
4 “ታማኝነት” የሚለውን ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ካለው አገባብ አንጻር ስንመለከተው አንድን አካል በፍቅር የሙጥኝ በማለትና ከዚህ አካል ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ ዳር እስኪደርስ ድረስ ከእሱ ጎን በመቆም የሚገለጽ ደግነት ነው። ታማኝ ሰው ይህን የሚያደርገው እንዲሁ ግዴታን ለመወጣት ያህል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ነው።a በመሆኑም ታማኝ መሆን እምነት የሚጣልበት ወይም አስተማማኝ ሆኖ ከመገኘት የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው ጨረቃ ሁልጊዜ በምሽት የምትወጣ በመሆኗ “በሰማያት ታማኝ ምሥክር” ሆና እንደምትኖር ተናግሯል። (መዝሙር 89:37) እዚህ ላይ ጨረቃ ታማኝ ተብላ የተጠራችው አስተማማኝ በመሆኗ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ማሰብ የሚችሉ አካላት ከሚያሳዩት ታማኝነት የተለየ ነው። ለምን? ምክንያቱም ታማኝነት የፍቅር መገለጫ ነው፤ ግዑዝ ፍጥረታት ደግሞ ፍቅር ማሳየት አይችሉም።
ጨረቃ ታማኝ ምሥክር ተብላ ተጠርታለች፤ የይሖዋን ዓይነት ታማኝነት ሊያንጸባርቁ የሚችሉት ግን የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት ብቻ ናቸው
5 ታማኝነት የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ባለው አገባብ መሠረት ወዳጃዊ መንፈስ የሚንጸባረቅበት ባሕርይ ነው። አንድ ሰው ለሌላው ታማኝ የሚሆነው በሁለቱ መካከል የጠበቀ ወዳጅነት ሲኖር ነው። እንዲህ ያለው ታማኝነት ጊዜያዊ አይደለም። በነፋስ እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ተለዋዋጭ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ታማኝነት ወይም ታማኝ ፍቅር በጣም አስቸጋሪ የሆኑ መሰናክሎችን ሁሉ ማለፍ የሚያስችል ጥንካሬና ጽናት ያለው ባሕርይ ነው።
6. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ታማኝነት እየጠፋ ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስስ ይህን የሚገልጸው እንዴት ነው? (ለ) ታማኝነት ምን እንደሚጠይቅ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? ለምንስ?
6 እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለው ታማኝነት እየጠፋ ነው ሊባል ይችላል። “እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች” በዝተዋል። የትዳር ጓደኛቸውን ጥለው የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። (ምሳሌ 18:24፤ ሚልክያስ 2:14-16) ታማኝነት ማጉደል በጣም እየተለመደ በመምጣቱ እኛም እንደ ነቢዩ ሚክያስ “ታማኝ ሰው ከምድሪቱ ጠፍቷል” ብለን ለመናገር እንገፋፋለን። (ሚክያስ 7:2) ምንም እንኳ የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ ታማኝነታቸውን የሚያጎድሉ ቢሆንም ይሖዋ ይህን ተወዳጅ ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ የላቀ ምሳሌ ነው። እንዲያውም ታማኝነት ምን እንደሚጠይቅ ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ይሖዋ የፍቅሩ ታላቅ መግለጫ የሆነውን ይህን ባሕርይ እንዴት እንዳንጸባረቀ መመርመር ነው።
አቻ የማይገኝለት የይሖዋ ታማኝነት
7, 8. ‘ይሖዋ ብቻ ታማኝ ነው’ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “አንተ ብቻ ታማኝ ነህ” ይላል። (ራእይ 15:4) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አስደናቂ የሆነ የታማኝነት አቋም ያሳዩ ሰዎችና መላእክት አሉ አይደለም እንዴ? (ኢዮብ 1:1፤ ራእይ 4:8) ኢየሱስ ክርስቶስስ ቢሆን ግንባር ቀደሙ የይሖዋ “ታማኝ አገልጋይ” አይደለም? (መዝሙር 16:10) ታዲያ ‘ይሖዋ ብቻ ታማኝ ነው’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
8 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ታማኝነት የፍቅር አንዱ ገጽታ እንደሆነ አስታውስ። “አምላክ ፍቅር ነው”፤ በሌላ አነጋገር የዚህ ባሕርይ ዋነኛ መገለጫ እሱ ነው። ታዲያ ከይሖዋ በተሻለ ሁኔታ ታማኝ ሊሆን የሚችል ማን ይኖራል? (1 ዮሐንስ 4:8) መላእክትም ሆኑ ሰዎች የአምላክን ባሕርያት ሊያንጸባርቁ ቢችሉም ከሁሉ በላቀ ደረጃ ታማኝ የሆነው ይሖዋ ብቻ ነው። “ከዘመናት በፊት የነበረ” እንደመሆኑ መጠን ከየትኛውም ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ፍጡር ይበልጥ ለረጅም ዘመን ታማኝነት ሲያሳይ ኖሯል። (ዳንኤል 7:9) በመሆኑም ይሖዋ የታማኝነት ዋነኛ ተምሳሌት ነው። ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቀው ከማንኛውም ፍጡር በላቀ ደረጃ ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።
9. ይሖዋ ‘በሥራው ሁሉ ታማኝ’ የሆነው እንዴት ነው?
9 ይሖዋ ‘በሥራው ሁሉ ታማኝ ነው።’ (መዝሙር 145:17) እንዴት? መዝሙር 136 ለዚህ መልስ ይሰጠናል። መዝሙሩ እስራኤላውያን በተአምራዊ መንገድ ቀይ ባሕርን የተሻገሩበትን ሁኔታ ጨምሮ ይሖዋ የወሰዳቸውን የተለያዩ የማዳን እርምጃዎች ይጠቅሳል። በዚህ መዝሙር ላይ የሚገኘው እያንዳንዱ ቁጥር “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” በሚል ዓረፍተ ነገር እንደሚቋጭ ልብ በል። ይህ መዝሙር በገጽ 289 ላይ በሚገኘው “ለማሰላሰል የሚረዱ ጥያቄዎች” በሚለው ሣጥን ውስጥ ተካትቷል። በዚህ መዝሙር ላይ የተገለጹትን ይሖዋ ለሕዝቡ ታማኝ ፍቅር ያሳየባቸውን የተለያዩ መንገዶች ስትመለከት መደነቅህ አይቀርም። አዎን፣ ይሖዋ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮቹ የእሱን እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ልመና በመስማትና ራሱ በወሰነው ጊዜ እርምጃ በመውሰድ ታማኝነቱን ያሳያቸዋል። (መዝሙር 34:6) አገልጋዮቹ ለእሱ ታማኝ ሆነው እስከተገኙ ድረስ ይሖዋ ለእነሱ ያለው ታማኝ ፍቅር ፈጽሞ አይቀንስም።
10. ይሖዋ ከመሥፈርቶቹ ጋር በተያያዘ ታማኝ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ምንጊዜም በመጠበቅ ለአገልጋዮቹ ታማኝነት ያሳያል። ይሖዋ በስሜትና በግብታዊነት እንደሚመሩ ወላዋይ ሰዎች፣ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ያለውን አመለካከት በየጊዜው አይለዋውጥም። ባለፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች፣ ስለ ጣዖት አምልኮና ስለ ነፍስ ግድያ ያለው አመለካከት ፈጽሞ አልተለወጠም። “እስከ እርጅናችሁ ዘመን ድረስ እኔ ያው ነኝ” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:4) በመሆኑም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ግልጽ የሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ጥቅም እንደምናገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ኢሳይያስ 48:17-19
11. ይሖዋ የገባውን ቃል በመፈጸም ረገድ ታማኝ እንደሆነ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
11 ይሖዋ የገባውን ቃል በመጠበቅም ታማኝ መሆኑን ያሳያል። አስቀድሞ የሚናገረው ነገር ሁሉ ፍጻሜውን ማግኘቱ አይቀርም። ስለሆነም ይሖዋ “ከአፌ [የሚወጣው] ቃሌ . . . ደስ የሚያሰኘኝን ነገር ያደርጋል፣ የተላከበትንም ዓላማ በእርግጥ ይፈጽማል እንጂ ያላንዳች ውጤት ወደ እኔ አይመለስም” ሲል ገልጿል። (ኢሳይያስ 55:11) ይሖዋ ቃሉን በመጠበቅ ለሕዝቡ ያለውን ታማኝነት ያሳያል። የማይፈጽምላቸውን ነገር በጉጉት እንዲጠብቁ አያደርግም። ይሖዋ ቃሉን በመጠበቅ ረገድ ያተረፈው ስም ምንም እንከን የማይወጣለት በመሆኑ አገልጋዩ ኢያሱ “ይሖዋ ለእስራኤል ቤት ከገባው መልካም ቃል ሁሉ ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም፤ ሁሉም ተፈጽሟል” ብሎ መናገር ችሏል። (ኢያሱ 21:45) እንግዲያው ይሖዋ የገባውን ቃል ሳይፈጽም ቀርቶ ለሐዘን ይዳርገናል ብለን የምንሰጋበት ምንም ምክንያት የለም።—ኢሳይያስ 49:23፤ ሮም 5:5
12, 13. የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
12 ቀደም ሲል እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ታማኝ ፍቅር “ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል። (መዝሙር 136:1) ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ኃጢአትን ይቅር የሚለው ለዘለቄታው ነው። በምዕራፍ 26 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ አንድን ሰው አንዴ ይቅር ካለው በኋላ ጥፋቱን መልሶ አያነሳበትም። ‘ሁላችንም ኃጢአት ሠርተናል እንዲሁ የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ ተስኖናል’፤ በመሆኑም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል።—ሮም 3:23
13 ይሁን እንጂ የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ የሚኖርበት ሌላም አቅጣጫ አለ። የአምላክ ቃል፣ ጻድቅ ሰው “በጅረቶች ዳር እንደተተከለ፣ ፍሬውን በወቅቱ እንደሚሰጥ፣ ቅጠሉም እንደማይጠወልግ ዛፍ ይሆናል። የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 1:3) ቅጠሉ የማይደርቅ የለመለመ ዛፍ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር! እኛም የአምላክን ቃል በማንበብ ከልብ የምንደሰት ከሆነ ረጅም፣ ሰላማዊና ፍሬያማ ሕይወት ይኖረናል። ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያፈስስላቸው በረከቶች ዘላለማዊ ናቸው። በእርግጥም ይሖዋ በሚያመጣው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ለዘላለም የማጣጣም አጋጣሚ ያገኛሉ።—ራእይ 21:3, 4
ይሖዋ ‘ታማኝ አገልጋዮቹን አይተዋቸውም’
14. ይሖዋ አገልጋዮቹ ስለሚያሳዩት ታማኝነት ምን ይሰማዋል?
14 ይሖዋ በተደጋጋሚ ጊዜያት ታማኝነቱን አሳይቷል። ፈጽሞ የማይለዋወጥ አምላክ በመሆኑ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚያሳየው ታማኝነት መቼም ቢሆን አይቀንስም። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤ ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም። ይሖዋ ፍትሕን ይወዳልና፤ ታማኝ አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም።” (መዝሙር 37:25, 28) ይሖዋ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ልናመልከው እንደሚገባ የታወቀ ነው። (ራእይ 4:11) ይሁንና ይሖዋ ታማኝ ስለሆነ በታማኝነት የምናከናውነውን መልካም ተግባር ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ሚልክያስ 3:16, 17
15. ይሖዋ ለእስራኤላውያን ያደረገው ነገር ታማኝነቱን እንዴት ጎላ አድርጎ እንደሚያሳይ ግለጽ።
15 ይሖዋ ሕዝቡ ችግር ላይ ሲወድቁ በተደጋጋሚ ጊዜያት በታማኝ ፍቅሩ ተገፋፍቶ አስፈላጊውን እርዳታ አድርጎላቸዋል። መዝሙራዊው “እሱ የታማኝ አገልጋዮቹን ሕይወት ይጠብቃል፤ ከክፉዎች እጅ ይታደጋቸዋል” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 97:10) ለእስራኤል ሕዝብ ያደረገውን ነገር ተመልከት። እስራኤላውያን፣ በቀይ ባሕር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ባዳናቸው ጊዜ “የታደግካቸውን ሕዝቦች በታማኝ ፍቅርህ መራሃቸው” በማለት ይሖዋን በመዝሙር አወድሰዋል። (ዘፀአት 15:13) በእርግጥም ይሖዋ በቀይ ባሕር ያከናወነው ታላቅ የማዳን ሥራ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። በመሆኑም ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ይሖዋ እናንተን የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ ይልቅ ቁጥራችሁ ስለበዛ አይደለም፤ ቁጥራችሁማ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ አነስተኛ ነበር። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እናንተን ከባርነት ቤት ይኸውም ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ ይታደጋችሁ ዘንድ ይሖዋ በብርቱ እጅ ያወጣችሁ ስለወደዳችሁና ለአባቶቻችሁ የማለላቸውን መሐላ ስለጠበቀ ነው።”—ዘዳግም 7:7, 8
16, 17. (ሀ) እስራኤላውያን አድናቆት ጎድሏቸው እንደነበረ ያሳዩት እንዴት ነው? ሆኖም ይሖዋ ርኅራኄ ያሳያቸው እንዴት ነው? (ለ) አብዛኞቹ እስራኤላውያን ‘ፈውስ የማይገኝላቸው’ ደረጃ ላይ የደረሱት እንዴት ነው? ይህስ ለእኛ ማስጠንቀቂያ የሚሆነን እንዴት ነው?
16 እርግጥ ነው፣ እስራኤላውያን በብሔር ደረጃ ይሖዋ ላሳያቸው ታማኝ ፍቅር አድናቆት ሳያሳዩ ቀርተዋል። ነፃ ካወጣቸው በኋላ “በልዑሉ አምላክ ላይ በማመፅ በእሱ ላይ ኃጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ።” (መዝሙር 78:17) በቀጣዮቹ መቶ ዘመናትም ይሖዋን በመተው፣ የሐሰት አማልክትን በማምለክና የሚያረክሱ አረማዊ ድርጊቶችን በመፈጸም በተደጋጋሚ ጊዜያት ዓምፀውበታል። ያም ሆኖ ይሖዋ ቃል ኪዳኑን አላፈረሰም። ከዚህ ይልቅ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል “ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፣ ተመለሽ . . . እኔ ታማኝ ስለሆንኩ እናንተን በቁጣ አልመለከትም” ሲል ሕዝቡን ተማጽኗል። (ኤርምያስ 3:12) ይሁን እንጂ ምዕራፍ 25 ላይ እንደተገለጸው አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለመስተካከል ያደረጉት ጥረት የለም። እንዲያውም “በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣ ቃሉን ይንቁና በነቢያቱ ላይ ያፌዙ ነበር።” ይህ ምን ውጤት አስከተለ? በመጨረሻ ‘ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ።’—2 ዜና መዋዕል 36:15, 16
17 ከዚህ ምን እንማራለን? ይሖዋ ታማኝ ነው ሲባል ሰዎች የሚፈጽሙትን መጥፎ ድርጊት እንዲሁ ችላ ይላል ወይም በቀላሉ ይታለላል ማለት አይደለም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ ነው። ደግሞም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል በቂ ምክንያት ሲኖር ምሕረት ማድረግ ያስደስተዋል። ይሁን እንጂ አንድ ኃጢአተኛ ለመታረም ፈቃደኛ በማይሆንበት ጊዜስ ምን ያደርጋል? በዚህ ጊዜ ይሖዋ የራሱን የጽድቅ መሥፈርቶች በመጠበቅ በግለሰቡ ላይ የቅጣት እርምጃ ይወስድበታል። ለሙሴ እንደገለጸለት “ጥፋተኛውን . . . በምንም ዓይነት ሳይቀጣ የማያልፍ” አምላክ ነው።—ዘፀአት 34:6, 7
18, 19. (ሀ) ይሖዋ በክፉዎች ላይ የሚወስደው እርምጃ ራሱ ታማኝነቱን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በደረሰባቸው ከባድ ስደት ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡ አገልጋዮቹ ታማኝነቱን የሚያሳየው በምን መንገድ ነው?
18 አምላክ በክፉዎች ላይ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ ራሱ ታማኝነቱን የሚያሳይ ነው። እንዴት? በራእይ መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ የሚገኘው፣ ይሖዋ ለሰባቱ መላእክት የሰጠው ትእዛዝ ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው። ይሖዋ ሰባቱን መላእክት “ሂዱና የአምላክን ቁጣ የያዙትን ሰባቱን ሳህኖች በምድር ላይ አፍስሱ” ሲል አዟቸዋል። ሦስተኛው መልአክ “በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ወንዞችና ወደ ውኃ ምንጮች” ባፈሰሰ ጊዜ ውኃው ወደ ደም ተለወጠ። ከዚያም መልአኩ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “ያለህና የነበርክ ታማኝ አምላካችን፣ እነዚህን የፍርድ ውሳኔዎች ስላስተላለፍክ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ምክንያቱም የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም አፍስሰዋል፤ አንተም ደም እንዲጠጡ ሰጥተሃቸዋል፤ ደግሞም ይገባቸዋል።”—ራእይ 16:1-6
19 መልአኩ የፍርድ መልእክቱን በሚያስተላልፍበት ጊዜ ይሖዋን “ታማኝ አምላካችን” ብሎ እንደጠራው ልብ በል። ይህን ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ክፉዎችን ማጥፋቱ ለአገልጋዮቹ ታማኝ መሆኑን ስለሚያሳይ ነው፤ ከእነዚህ አገልጋዮቹ መካከል ብዙዎች በደረሰባቸው ከባድ ስደት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይሖዋ እንዲህ ያሉትን አገልጋዮቹን መቼም አይረሳቸውም። በሞት የተለዩትን እነዚህን ታማኝ አገልጋዮቹን ዳግመኛ ሊያያቸው ይናፍቃል፤ በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ከሞት በማስነሳት ወሮታ የመክፈል ዓላማ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። (ኢዮብ 14:14, 15) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ስለሞቱ ብቻ አይረሳቸውም። እንዲያውም “በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው።” (ሉቃስ 20:37, 38) ይሖዋ በአእምሮው ማኅደር ያኖራቸውን ሰዎች ዳግም ሕያው ለማድረግ ዓላማ ያለው መሆኑ ታማኝነቱን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ይሖዋ ሕይወታቸውን ጭምር አሳልፈው በመስጠት ታማኝ መሆናቸውን ያስመሠከሩትን አገልጋዮቹን በማስታወስና ከሞት በማስነሳት ታማኝ መሆኑን ያሳያል
የይሖዋ ታማኝ ፍቅር መዳን ያስገኛል
20. “የምሕረት ዕቃዎች” የተባሉት እነማን ናቸው? ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ታማኝነት ያሳየውስ እንዴት ነው?
20 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ለታማኝ ሰዎች በጣም የሚያስደንቅ ታማኝነት አሳይቷል። እንዲያውም ይሖዋ “ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች” በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት “በብዙ ትዕግሥት [ችሏቸዋል]።” ለምን? “ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች ላይ ለመግለጥ” ነው። (ሮም 9:22, 23) እነዚህ “የምሕረት ዕቃዎች” ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ገዢዎች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ናቸው። (ማቴዎስ 19:28) ይሖዋ እነዚህ የምሕረት ዕቃዎች መዳን የሚችሉበትን አጋጣሚ በመክፈት ለአብርሃም ያለውን ታማኝነት አሳይቷል፤ ምክንያቱም ይሖዋ “ቃሌን ስለሰማህ የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ” ሲል ለአብርሃም ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበር።—ዘፍጥረት 22:18
21. (ሀ) ይሖዋ “ታላቁን መከራ” የማለፍ ተስፋ ላላቸው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ታማኝነቱን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ታማኝነት ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል?
21 ይሖዋ “ታላቁን መከራ” አልፈው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ‘እጅግ ብዙ ሕዝብም’ ተመሳሳይ የሆነ ታማኝነት አሳይቷል። (ራእይ 7:9, 10, 14) አገልጋዮቹ ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ በታማኝ ፍቅሩ ተነሳስቶ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ይህን ያደረገው እንዴት ነው? የይሖዋ ታማኝነት ከሁሉ በላቀ ደረጃ የተንጸባረቀበትን የቤዛውን ዝግጅት በመጠቀም ነው። (ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 5:8) የይሖዋ ታማኝነት ጽድቅን የተራቡ ሰዎች ወደ እሱ እንዲሳቡ እያደረገ ነው። (ኤርምያስ 31:3) ይሖዋ እስካሁን ያሳየውም ሆነ ወደፊት የሚያሳየው ታማኝነት ይበልጥ ወደ እሱ እንድትቀርብ አይገፋፋህም? የዘወትር ምኞታችን ይበልጥ ወደ አምላክ መቅረብ እንደመሆኑ መጠን፣ እሱን በታማኝነት ለማገልገል ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ በመጽናት ላሳየን ፍቅር አዎንታዊ ምላሽ እንስጥ።
a በ2 ሳሙኤል 22:26 ላይ “ታማኝ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በሌሎች ቦታዎች ላይ “ታማኝ ፍቅር” ተብሎ ተተርጉሟል።