የይሖዋን ክንዶች መደገፊያህ ማድረግ
“መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፣ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው።”—ዘዳግም 33:27
1, 2. የይሖዋ ሕዝቦች ድጋፉን እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ለመሆን የሚችሉት ለምንድን ነው?
ይሖዋ ለሕዝቡ ያስባል። እስራኤላውያን ጭንቀት ባጋጠማቸው ጊዜ ሁሉ ‘እርሱም አብሯቸው ይጨነቅ ነበር።’ በፍቅርና በርኅራኄም “አንስቶ ተሸከማቸው።” (ኢሳይያስ 63:7-9) ስለዚህ እኛም ለአምላክ ታማኝ ከሆንን እንደሚደግፈን እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን።
2 ነቢዩ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “የጥንቱ አምላክ መሸሸጊያ ነው፣ ከበታችም ዘላለማዊ የሆኑት ክንዶች አሉ።” (ዘዳግም 33:27) አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ዘላለማዊው አምላክ መኖሪያህ ነው፣ የዘላለም ክንዶቹም ከበታችህ ናቸው” ይላል። (አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሺን) ይሁንና የአምላክ ክንዶች አገልጋዮቹን የሚደግፉት እንዴት ነው?
ይህ ሁሉ መከራ የኖረው ለምንድን ነው?
3. ታዛዥ የሆነው የሰው ዘር ‘የአምላክን ልጆች ክብራማ ነፃነት’ ሙሉ በሙሉ የሚያገኘው መቼ ነው?
3 ይሖዋን ማገልገላችን ፍጽምና በሌላቸው ሰዎች ላይ የሚደርሱት መከራዎች በእኛ ላይ እንዳይደርሱ አያደርግም። የአምላክ አገልጋይ የሆነው ኢዮብ እንዲህ አለ፦ “ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወት ዘመኑ ጥቂት ነው፣ መከራም ይሞላዋል።” (ኢዮብ 14:1) መዝሙራዊው ስለ ‘ሕይወት ዘመናችን’ “ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 90:10) ‘ፍጥረት ለከንቱነት ከተገዛበት ሁኔታ ነፃ እስኪሆንና የአምላክን ልጆች ክብርና ነፃነት እስኪያገኝ’ ድረስ ሕይወት በዚሁ መልኩ ይቀጥላል። (ሮሜ 8:19-22) ይህ ደግሞ የሚሆነው በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ነው። በዚያን ጊዜ የመንግሥቲቱ ሰብአዊ ተገዢዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት መሠረት ከኃጢአትና ከሞት ነፃነት ያገኛሉ። በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻም ላይ ክርስቶስና ነገሥታትና ካህናት የሚሆኑት ተባባሪዎቹ ታዛዥ የሆኑት የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና እንዲደርሱ ይረዳሉ፤ ሰይጣንና አጋንንቱ በሚያመጡት የመጨረሻ ፈተና ለአምላክ ታማኝ የሚሆኑት ስማቸው ለዘላለም “በሕይወት መጽሐፍ” ላይ ይጻፋል። (ራእይ 20:12-15) ከዚያ በኋላ የአምላክ ልጆች የሚያገኙትን ክብራማ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ያገኛሉ።
4. በሕይወታችን ውስጥ ስላጋጠመን ሁኔታ በማጉረምረም ፋንታ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
4 እስከዚያው ድረስ ግን በሕይወታችን ስላጋጠመን ሁኔታ ከማጉረምረም ይልቅ በይሖዋ እንታመን። (1 ሳሙኤል 12:22፤ ይሁዳ 16) በተጨማሪም “ምሕረትን እንድንቀበል፣ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ” ወደ አምላክ ልንቀርብ ለምንችልበት ለሊቀ ካህናታችን ለኢየሱስ አመስጋኞች እንሁን። (ዕብራውያን 4:14-16) በፍጹም እንደ አዳም መሆን አይገባንም። አዳም ይሖዋን መጥፎ ሚስት ሰጠኸኝ ብሎ በሐሰት ከሶታል፦ “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። (ዘፍጥረት 3:12) አምላክ የሚሰጠን ጥሩ ነገሮችን ብቻ ነው፣ መከራም አያመጣብንም። (ማቴዎስ 5:45፤ ያዕቆብ 1:17) ብዙውን ጊዜ ችግር የሚያጋጥመን እኛ ጥበብ በማጣታችን ወይም በሌላ ሰው ስህተት ምክንያት ነው። በተጨማሪም ኃጢአተኞች በመሆናችንና በሰይጣን ሥር ባለው ዓለም ውስጥ በመኖራችን ሊመጣ ይችላል። (ምሳሌ 19:3፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ሆኖም የይሖዋ ዘላለማዊ ክንዶች በእርሱ በመመካት የሚጸልዩለትንና የቃሉን ምክር በሕይወታቸው ተግባራዊ የሚያደርጉትን ምን ጊዜም ይደግፏቸዋል።—መዝሙር 37:5፤ 119:105
በሕመም ጊዜ ይደግፋል
5. ሕመምተኞች በመዝሙር 41:1-3 ላይ ምን መጽናኛ ያገኛሉ?
5 አብዛኞቻችን በሕመም ምክንያት የምንጨነቅበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ [ደስተኛ (አዓት)] ነው፤ [ይሖዋ (አዓት)] በክፉ ቀን ያድነዋል። [ይሖዋ (አዓት)] ይጠብቀዋል፣ ሕያውም ያደርገዋል፣ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፣ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም። [ይሖዋ (አዓት)] በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል።”—መዝሙር 41:1-3
6, 7. ዳዊት ታሞ ተኝቶ በነበረበት ጊዜ አምላክ የረዳው እንዴት ነው? ይህስ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የይሖዋ አገልጋዮች የሚያበረታታው እንዴት ነው?
6 አሳቢ የሆነ ሰው ችግረኞችን ይረዳል። እዚህ ላይ “ክፉ ቀን” የተባለው ክፉ ችግር የሚያጋጥምበት ማንኛውም አጋጣሚ ወይም አንድን ግለሰብ ሊያዳክም የሚችል ረጅም የመከራ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ በበሽታው ጊዜ እንዲጠብቀው በአምላክ ይታመናል፤ ሌሎችም ይሖዋ ለእርሱ ያደረገለትን የምሕረት ድርጊቶች በመናገር ‘በምድር ላይ በደስታ ያመሰግኑታል።’ አምላክ ዳዊትን “በደዌው አልጋ ሳለ” ረድቶታል። ይህም የሆነው የዳዊት ልጅ አቤሴሎም የእስራኤልን ዙፋን ለመቀማት በፈለገበት አስጨናቂ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።—2 ሳሙኤል 15:1-6
7 ዳዊት ለምስኪኖች አሳቢነትን ያሳየ በመሆኑ እርሱም በደዌ አልጋ ላይ ምንም አቅም እንደሌለው በሆነበት ጊዜ አምላክ እንደሚረዳው ተሰምቶት ነበር። (መዝሙር 18:24-26) በአደገኛ ሁኔታ ቢታመምም እንኳ በሽታውን በተዓምር በማስወገድ ሳይሆን በሚያጽናኑ አሳቦች እርሱን በማጠንከር አምላክ ‘አልጋውን እንደሚያነጥፍለት’ ትምክህት ነበረው። ይህም ይሖዋ የሕመም አልጋውን ወደ ማገገሚያ አልጋነት እንደሚለውጥለት ያህል ነበር። በተመሳሳይ እኛም የአምላክ አገልጋዮች ሆነን ብንታመም የይሖዋ ዘላለማዊ ክንዶች ይደግፉናል።
ለተጨነቁት የሚሆን መጽናኛ
8. አንድ ሕመምተኛ ክርስቲያን በአምላክ ላይ የሚመካ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
8 ሕመም የአእምሮ ጭንቀት ሊያመጣ ይችላል። አንዳንዴ ለማንበብ እንኳ ኃይል ያጣ የነበረ አንድ በጣም የታመመ ክርስቲያን “ይህ ሁኔታ በጣም እንድጨነቅ፣ ዋጋ እንደሌለኝ ሆኖ እንዲሰማኝ፣ እንዲያውም እንዳለቅስ ያደርገኝ ነበር” አለ። ሆኖም ሰይጣን ተስፋ በማስቆረጥ ሊያደቀው እንደሚፈልግ በማወቁና በይሖዋም እርዳታ ሊወድቅ እንደማይችል በመገንዘቡ ይህንን ስሜት ተዋጋው። (ያዕቆብ 4:7) ይህ ሰው በአምላክ እንደሚተማመን ለሚያውቁ ሁሉ መጽናኛ ሆኖላቸዋል። (መዝሙር 29:11) ሆስፒታል በገባበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር በሽተኞችን በመንፈሳዊ ለማነጽ ሲል ስልክ ይደውልላቸው ነበር። እንዲሁም የመንግሥቱን ሙዚቃና የዚህን መጽሔትና የዚህ መጽሔት ጓደኛ የሆነውን የንቁ! የካሴት ቅጂዎች በማዳመጥ እንዲሁም ከክርስቲያን ጓደኞቹ ጋር በመገናኘት እርሱ ራሱም ቢሆን ይታነጽ ነበር። ይህ ወንድም እንዲህ ይላል፦ “ብርታት፣ መመሪያና መጽናኛ እንዲሁም ለመጽናት የሚያስችለኝን እርዳታ እንዲሰጠኝ በመጠየቅ ዘወትር ይሖዋን በጸሎት አነጋግረዋለሁ።” ከባድ የሆነ የጤና ችግር ያጋጠመህ ክርስቲያን ከሆንክ ዘወትር በይሖዋ ተመካ፣ ዘላለማዊ ክንዶቹንም ድጋፍህ አድርጋቸው።
9. የአእምሮ ጭንቀት አንዳንድ ጊዜ የአምላክን ሕዝቦች ሊያስቸግር እንደሚችል የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ?
9 የመንፈስ ጭንቀት ረጅም ዕድሜ ያለው ችግር ነው። ኢዮብ በፈተና ላይ በነበረበት ጊዜ አምላክ እንደተወው ሆኖ እንደተሰማው ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 29:2-5) ነህምያ ኢየሩሳሌምና ቅጥሮችዋ በመፈራረሳቸው ምክንያት አዝኖና ፊቱ ጠቁሮ ነበር። ጴጥሮስም ክርስቶስን በመካዱ ምክንያት በጣም ተጨንቆ አልቅሶአል። (ነህምያ 2:1-8፤ ሉቃስ 22:62) አፍሮዲጡም በፊልጵስዩስ የነበሩ ክርስቲያኖች መታመሙን መስማታቸውን ሲሰማ ሐዘን ተሰምቶት ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:25, 26) በተሰሎንቄ የነበሩት ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ጳውሎስ “የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል አነጋግሯቸው” በማለት ስላሳሰበ የሚያስጨንቅ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ታዲያ አምላክ እንደነዚህ ያሉትን ግለሰቦች የሚረዳው እንዴት ነው?
10. የአእምሮ ጭንቀትን ለመቋቋም ምን ሊረዳ ይችላል?
10 ለከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሕክምና ስለመውሰድ የግል ውሳኔ መደረግ ይኖርበታል።a (ገላትያ 6:5) በቂ እረፍትና ሚዛናዊ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ ሊረዳ ይችላል። ጭንቀት የደረሰበት ግለሰብ ችግሮቹን በሙሉ አንድ ላይ አጠቃሎ ከመመልከት ይልቅ እያንዳንዱን ችግር በየተራ ሊፈታ ቢሞክር ቀላል ሊሆንለት ይችላል። በተለይ ይህ ስሜታዊ ችግር መንፈሳዊ አደጋን የሚፈጥር ከሆነ ከጉባኤ ሽማግሌዎች የሚገኝ አጽናኝ እርዳታ በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ያዕቆብ 5:13-15) ከሁሉም በላይ በይሖዋ መተማመንና ‘እርሱ ለእኛ የሚያስብ ስለሆነ ጭንቀታችንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል’ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው መጽናቱና ልባዊ የሆነ ጸሎት ማቅረቡ ‘በክርስቶስ ኢየሱስ ልብንና የማሰብ ኃይልን ሊጠብቅ የሚችለውን የአምላክን ሰላም’ ሊያመጣለት ይችላል።—1 ጴጥሮስ 5:6-11፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ይሖዋ ሐዘንን እንድንቋቋም ይረዳናል
11-13. የቅርብ ዘመዳችን በመሞቱ የመጣብንን ሐዘን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
11 ሌላው ጭንቀት የሚያስከትል ሁኔታ የቅርብ ወዳጅ ሞት ነው። አብርሃም ሚስቱን ሣራን በሞት በማጣቱ አልቅሶአል። (ዘፍጥረት 23:2) ዳዊት ልጁ አቤሴሎም ሲሞት በሐዘን ልቡ ተመቶ ነበር። (2 ሳሙኤል 18:33) ፍጹሙ ሰው ኢየሱስም ቢሆን ጓደኛው አልዓዛር በመሞቱ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) ስለዚህ የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ያሳዝናል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለውን ሐዘን ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?
12 አምላክ የዘመድ ሞት የሚያስከትለውን ከባድ ሐዘን እንዲቋቋሙ ሕዝቡን ይረዳቸዋል። ቃሉ ትንሣኤ እንደሚኖር ይነግረናል። ስለዚህ ‘ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ማዘን’ አይገባንም። (1 ተሰሎንቄ 4:13፤ ሥራ 24:15) የይሖዋ መንፈስ ሰላምና እምነት እንዲኖረንና በቃሉ ውስጥ በተገለጹት ተስፋዎች ላይ እንድናሰላስል ይረዳናል። ይህም ስለሞተው ዘመዳችን አሳዛኝ አሳቦችን በማሰብ ሙሉ በሙሉ እንዳንዋጥ ይረዳናል። በተጨማሪም መጽናናት ጥቅሶችን ከማንበብና ወደ “መጽናናት ሁሉ አምላክ” ከመጸለይ ይገኛል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ መዝሙር 68:4-6
13 እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገረው እንደ ኢዮብ ከትንሣኤ ተስፋ መጽናናትን ልናገኝ እንችላለን፦ “[ይሖዋ] በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቁጣህ እስኪያልፍ ድረስ ምነው በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ! በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።” (ኢዮብ 14:13-15) አንድ የምንወደው ጓደኛችን ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ቢነሣ እንደገና እንደምናየው ተስፋ ስለምናደርግ ብዙውን ጊዜ በጣም አናዝንም። የአንድን ታማኝ ክርስቲያን ሞትም በተመሳሳይ መንገድ ብንመለከተው አንድ የምንወደው ሰው በመሞቱ ምክንያት የመጣብንን ጥልቅ ሐዘን ሊቀንስልን ይችል ይሆናል። ምድራዊ ተስፋ ያለው ከሆነ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ ከሞት እንቅልፍ ነቅቶ በዚህ ምድር ላይ ይኖራል። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:11-13) ለዘላለም በምድር ላይ ለመኖር ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ከሞት የሚነሡ ዘመዶቻችንን ለመቀበል እንችላለን።
14. የትዳር ጓደኞቻቸውን ያጡ ሁለት ክርስቲያን ሴቶች የባሎቻቸውን ሞት የተቋቋሙት እንዴት ነው?
14 አንዲት እህት ባልዋ ከሞተ በኋላ አምላክን እያገለገለች መኖር እንደሚገባ ተገነዘበች። ‘የጌታ ሥራ የበዛላት’ ከመሆኗም በተጨማሪ 800 ቁርጥራጭ ጨርቆችን እያቀጣጠለች የአልጋ ልብስ መስፋት ጀመረች። (1 ቆሮንቶስ 15:58) እርስዋም “ይህ ጥሩ ፕሮጀክት ነው” ትላለች፤ ቀጥላም “ይህን ሥራ በምሠራበት ጊዜ ሁሉ አእምሮዬን በሥራ የሚጠምዱ የመንግሥቱን የመዝሙር ሙዚቃዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ቴፖች ልሰማ እችል ነበር።” አንድ ተሞክሮ ያለው ሽማግሌና ሚስቱ ያደረጉላት ጉብኝት ትዝ ይላታል። ሽማግሌው አምላክ በእርግጥ ለመበለቶች እንደሚያስብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቀሰላት። (ያዕቆብ 1:27) አንድ ሌላ ክርስቲያን ሴትም ባልዋ በሞተበት ጊዜ ለራስ በማዘን ስሜት አልተሸነፈችም። ሌሎች ጓደኞችዋ የሚያደርጉላትን ድጋፍ አደነቀች፤ ለሌሎችም ከፍተኛ የሆነ የአሳቢነት ስሜት አደረባት። “ከበፊቱ የበለጠ ቶሎ ቶሎ እጸልይ ነበር፣ ከይሖዋ ጋር ያለኝን የተቀራረበ ዝምድናም አሳድጌአለሁ” ትላለች። የአምላክን ዘላለማዊ ክንዶች ድጋፍ ማግኘቱ በጣም ትልቅ በረከት ነው!
ስህተት ስንሠራ የምናገኘው እርዳታ
15. በመዝሙር 19:7-13 ላይ የሚገኙት የዳዊት ቃላት የያዙት ቁም ነገር ምንድን ነው?
15 የይሖዋን ሕግ የምናፈቅር ብንሆንም እንኳ አልፎ አልፎ እንሳሳታለን። ይህ ጭንቀት እንደሚፈጥርብን አያጠራጥርም። የአምላክን ሕጎች፣ ማሳሰቢያዎች፣ ትዕዛዞችና የፍርድ ውሳኔዎች ከወርቅ የበለጠ ይወድ የነበረው ዳዊትም ቢሆን ይህ ነገር ደርሶበታል። እርሱ እንዲህ አለ፦ “ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል። ስህተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፣ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ።” (መዝሙር 19:7-13) እስቲ እነዚህን ቃላት እንመርምር።
16. የድፍረት አድራጎቶችን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
16 በድፍረት የሚሠራ ኃጢአት በስህተት ከሚሠራ ኃጢአት በጣም ይከብዳል። ሳኦል ንጉሥ እንዳይሆን የተናቀው በድፍረት መስዋዕት በማቅረቡና አምላክ አማሌቃውያን መደምሰስ እንዳለባቸው ማዘዙን እያወቀ የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግንና የተማረኩትን ጥሩ ጥሩ ዕቃዎች በማትረፉ ነው። (1 ሳሙኤል 13:8-14፤ 15:8-19) ንጉሥ ዖዝያንም ቢሆን በድፍረት የካህናቱን ሥራ በመንጠቁ በቁምጥና ተመቷል። (2 ዜና መዋዕል 26:16-21) የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም በሚወሰድበትና ጋሪውን የሚጎትቱት እንስሳት ታቦቱን ሊገለብጡት በተቃረቡበት ጊዜ ዖዛ አክብሮት በጎደለው መንገድ በእጁ ስለደገፈው አምላክ ቀስፎታል። (2 ሳሙኤል 6:6, 7) ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚኖርብን ወይም አንድን ሥራ ለመሥራት ሥልጣን ያለን መሆኑንና አለመሆኑን ካላወቅን አቅምንና ቦታን የማወቅን ባሕርይ ማሳየትና የማስተዋል ችሎታ ያላቸውን ማማከር ይኖርብናል። (ምሳሌ 11:2፤ 13:10) በእርግጥ እስከ ዛሬ ድረስ የትዕቢትን ጠባይ አሳይተን ከሆነ ይቅርታ ለማግኘት መጸለይና ለወደፊቱ ከትዕቢት ጠባይ እንድንጠበቅ እንዲረዳን አምላክን መጠየቅ ይኖርብናል።
17. የተደበቁ ኃጢአቶች አንድን ሰው የሚጎዱት እንዴት ነው? ሆኖም ይቅርታና እፎይታ ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
17 የተደበቁ ኃጢአቶች ጭንቀትን ሊፈጥሩ ይችላሉ። በመዝሙር 32:1-5 ላይ እንደተገለጸው ዳዊት ኃጢአቱን ለመደበቅ ሞክሮ ነበር፣ ሆኖም እንዲህ አለ፦ “ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፣ እርጥበቴም ለበጋ ትኩሳት ተለወጠ።” ይወቅሰው የነበረውን ኅሊና ዝም ለማሰኘት መሞከሩ ዳዊትን አድቅቆት ነበር፤ ዳዊት በጭንቀቱ ምክንያት በድርቅ ወይም በበጋ ሐሩር እርጥበቱን አጥቶ እንደደረቀ ዛፍ ኃይል አጥቶና ጠውልጎ ነበር። በአእምሮውም ሆነ በአካሉ ጉዳት አስከትሎበት እንደነበር ግልጽ ነው፤ ኃጢአቱን ሳይናዘዝ በመቅረቱም ደስታውን አጥቶ ነበር። ይቅርታንና እፎይታን ሊያገኝ የሚችለው ለአምላክ ኃጢአቱን ቢናዘዝ ብቻ ነው። ዳዊት እንዲህ አለ፦ “መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። . . . ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ [ለይሖዋ (አዓት)] መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።” ከክርስቲያን ሽማግሌዎች የሚገኝ ፍቅራዊ እርዳታ መንፈሳዊ ፈውስ ለማግኘት ሊረዳ ይችላል።—ምሳሌ 28:13፤ ያዕቆብ 5:13-20
18. ኃጢአት ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ጎጂ ውጤቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ የሚያሳየው ማስረጃ ምንድን ነው? ሆኖም እነዚህ ነገሮች ሲደርሱ ማጽናኛ ከየት ማግኘት ይቻላል?
18 ኃጢአት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጎጂ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጽሞ ባልዋ እንዲገደል ካደረገ በኋላ ያረገዘችውን መበለት ባገባ ጊዜ እንዲህ ያለው ውጤት ደርሶበታል። (2 ሳሙኤል 11:1-27) በመንግሥቱ ቃል ኪዳን፣ ዳዊት ንስሐ በመግባቱና ሌሎችን የሚምር በመሆኑ ምክንያት አምላክ ምሕረት ቢያደርግለትም ‘ከገዛ ቤቱ መከራ’ ደርሶበታል። (2 ሳሙኤል 12:1-12) ከምንዝር የተወለደው ልጅ ሞተ። የዳዊት ልጅ አምኖን የአባቱ ልጅ የሆነችውን ትዕማርን በጾታ ስላስነወራት በወንድምዋ በአቤሴሎም ትዕዛዝ ተገደለ። (2 ሳሙኤል 12:15-23፤ 13:1-33) አቤሴሎም ከዳዊት ቁባቶች ጋር የጾታ ግንኙነት በማድረግ ዳዊትን አዋርዶታል። ዙፋኑንም ለመቀማት ሞክሮ ተገደለ። (2 ሳሙኤል 15:1 እስከ 18:33) ዛሬም ቢሆን ኃጢአት የሚያስከትላቸው ችግሮች አሉት። ለምሳሌም ያህል አንድ የተወገደ ኃጢአተኛ ሰው ንስሐ ገብቶ ወደ ጉባኤ ሊመለስ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በኃጢአት ምክንያት የተበላሸውን ስሙን ለማደስና ካስከተለበት የስሜት ቁስል ለመሻር ዓመታት ሊወስድ ይችላል። እስከዚያው ድረስ የይሖዋን ይቅርታና የዘላለም ክንዶቹን ድጋፍ ማግኘቱ ምንኛ የሚያጽናና ይሆንለታል!
ከሚደርሱብን ጭንቀቶች መዳን
19. ከባድ ፈተና ሲደርስብን የአምላክ መንፈስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
19 ከባድ ፈተና ሲደርስብን ውሳኔ ለማድረግና ፈተናውን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ጥበብና ኃይል ልናጣ እንችላለን። ይህን የመሰለ ሁኔታ ሲያጋጥም የአምላክ መንፈስ “ድካማችንን ያግዛል፣ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል።” (ሮሜ 8:26) ይሖዋ ሁኔታዎችን የሚለውጥልን ከሆነ አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል። ሆኖም ክንዱ በሌላም መንገድ ሊያድነን ይችላል። ጥበብ እንዲሰጠን ብንጸልይ ይሖዋ በመንፈሱ ማድረግ የሚገባንን ነገር ያመለክተናል፣ ለዚህም የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5-8) በእርሱ እርዳታም በተለያዩ ፈተናዎች ምክንያት በሚደርስብን ሐዘን ልንጸና እንችላለን። ፈተናዎቹንም በተፈተነና በተጠናከረ እምነት ልንወጣ እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 1:6-8
20. ዘላለማዊ የሆኑትን የይሖዋ ክንዶች ድጋፋችን ካደረግን ምን እናገኛለን?
20 በጸሎት ወደ አምላክ ለመቅረብ በፍጹም አንሰልች። ዳዊት እንዲህ አለ፦ “እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ናቸው። እኔ ብቻዬን ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም። የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ። ድካሜንና መከራዬን እይ፣ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።” (መዝሙር 25:15-18) እኛም እንደ ዳዊት የይሖዋን ዘላለማዊ ክንዶች ድጋፋችን ካደረግን መለኮታዊ ማዳንን፣ ሞገስንና ይቅርታን ልናገኝ እንችላለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በንቁ! መጽሔት ጥቅምት 22, 1987 ዕትም ገጽ 2-16 ላይ ስለ መንፈስ ጭንቀት የወጡትን ርዕሰ ትምህርቶች ተመልከት
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አምላክ ሕመምተኛ የሆኑ አገልጋዮቹን የሚረዳቸው እንዴት ነው?
◻ የአእምሮ ጭንቀትን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
◻ የቅርብ ዘመዳችን በመሞቱ ምክንያት የደረሰብንን ሐዘን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
◻ ኃጢአታቸውን የደበቁ ሰዎች እፎይታ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች ከባድ ፈተና ሲደርስባቸው ምን እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ?
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላካዊ ሰው እንደነበረው እንደ ኢዮብ ከትንሣኤ ተስፋ ማጽናኛ ልናገኝ እንችላለን