ይሖዋን በመፍራት ደስተኛ ሁን!
“እግዚአብሔርን የሚፈራ . . . የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።”—መዝሙር 112:1
1, 2. አምላክን መፍራት ምን ያስገኛል?
ደስታ እንዲሁ በቀላሉ የሚገኝ ነገር አይደለም። እውነተኛ ደስታ ተገቢ ምርጫ በማድረግ፣ ትክክል የሆነውን በመፈጸምና ከመጥፎ ድርጊቶች በመራቅ ላይ የተመካ ነው። ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ ሕይወታችንን በተሻለ መንገድ እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ለማስተማር ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። በመሆኑም የይሖዋን መመሪያ በመሻትና በተግባር ላይ በማዋል አምላካዊ ፍርሃትን ማዳበር እንችላለን። ይህም እውነተኛ ደስታና እርካታ ያስገኝልናል።—መዝሙር 23:1፤ ምሳሌ 14:26
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ጤናማ የሆነ አምላካዊ ፍርሃት መጥፎ ድርጊቶችን እንድንፈጽም የሚደርስብንን ግፊት እንድንቋቋምና ትክክለኛውን ነገር ለመፈጸም የሚያስችል ድፍረት እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ቅዱስ ጽሑፋዊና ዘመናዊ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። አምላካዊ ፍርሃት፣ ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት የተሳሳተ አካሄድ ከመከተል እንድንመለስና ደስታ እንድናገኝ የሚረዳን መሆኑን እናያለን። ከዚህም በላይ አምላካዊ ፍርሃት ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያወርሷቸው የሚገባ ከሁሉ የላቀ ውድ ቅርስ እንደሆነ እንመለከታለን። የአምላክ ቃል “እግዚአብሔርን የሚፈራ . . . የተባረከ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—መዝሙር 112:1
ደስታን መልሶ ማግኘት
3. ዳዊት አካሄዱን እንዲያስተካክል የረዳው ምን ነበር?
3 በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ ዳዊት በሦስት የተለያዩ ጊዜያት ለአምላክ ተገቢ ፍርሃት ሳያሳይ በመቅረቱ ኃጢአት ሠርቷል። ይሁን እንጂ ይሖዋ በገሠጸው ጊዜ የሰጠው ምላሽ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው እንደነበር ያሳያል። ለይሖዋ ያለው ከፍተኛ አክብሮት ስህተቱን አምኖ እንዲቀበል፣ አካሄዱን እንዲያስተካክልና በድጋሚ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲመሠርት አስችሎታል። የሠራው ስህተት በእርሱም ሆነ በሌሎች ላይ መከራ ያመጣ ቢሆንም እውነተኛ ንስሐ በመግባቱ የይሖዋ ድጋፍና በረከት አልተለየውም። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ከባድ ኃጢአት ሊሠሩ ስለሚችሉ ከዳዊት ታሪክ ድፍረት የሚጨምር ትምህርት ያገኛሉ።
4. አንድ ሰው አምላክን መፍራቱ ደስታውን መልሶ እንዲያገኝ የሚረዳው እንዴት ነው?
4 የዞንያን ሁኔታ ተመልከት።a ዞንያ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆና ታገለግል የነበረ ቢሆንም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር በመግጠሟ ክርስቲያናዊ ያልሆነ አካሄድ መከተል ጀመረች። በዚህም ምክንያት ከጉባኤ ተወገደች። የኋላ ኋላ ዞንያ ወደ ልቧ በመመለስ ከይሖዋ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማደስ የሚያስፈልጓትን እርምጃዎች ሁሉ ወሰደች። ከጊዜ በኋላ የውገዳው ውሳኔ ተነሳላት። ይህ ሁሉ ሲሆን ይሖዋን የማገልገል ፍላጎቷ አልጠፋም። በመሆኑም በድጋሚ የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ቆየት ብላም ምሳሌ የሆነ የጉባኤ ሽማግሌ አግብታ በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቷ ጋር ሆና አምላክን በደስታ በማገልገል ላይ ትገኛለች። ዞንያ ከክርስትና ጎዳና ለጊዜውም ቢሆን መውጣቷ የሚጸጽታት ቢሆንም ለአምላክ ያላት ፍርሃት ወደ ይሖዋ እንድትመለስ ስለረዳት ደስተኛ ነች።
ኃጢአት ከመሥራት መከራ መቀበል ይሻላል
5, 6. ዳዊት ሳኦልን ሁለት ጊዜ ከሞት ያተረፈው እንዴት ነው? ለምንስ?
5 እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ቀድሞውኑ አምላክን ፈርቶ ኃጢአት ከመሥራት ቢቆጠብ በጣም የተሻለ ነው። የዚህ እውነተኝነት በዳዊት ላይ ታይቷል። በአንድ ወቅት ሳኦል ሦስት ሺህ ወታደሮችን ይዞ ዳዊትን ሲያፈላልግ ከቆየ በኋላ ዳዊትና ሰዎቹ ተደብቀው ወደነበሩበት ዋሻ ገባ። በዚህ ጊዜ የዳዊት ሰዎች ቀንደኛ ጠላቱን በእጁ አሳልፎ የሰጠው ይሖዋ እንደሆነ በመግለጽ ሳኦልን እንዲገድለው አበረታቱት። ዳዊት ግን በቀስታ እየተሳበ ሄዶ የሳኦልን ልብስ ጫፍ ቆርጦ ወሰደ። ዳዊት አምላክን ይፈራ ስለነበር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ምንም ጉዳት የሌለውን ይህን ነገር በመፈጸሙ እንኳ ሕሊናው ወቅሶታል። ከዚያም ይገፋፉት የነበሩትን ሰዎች ‘እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ’ አላቸው።b—1 ሳሙኤል 24:1-7
6 ቆየት ብሎም፣ ሳኦልና ሠራዊቱ በሚያድሩበት ቦታ በሰፈሩ ጊዜ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለወደቀባቸው” ሁሉም ተኝተው ነበር። ዳዊትና ደፋር የሆነው የእህቱ ልጅ አቢሳ በሠራዊቱ ውስጥ ተሽሎክልከው በመግባት ሳኦል ከተኛበት ስፍራ ደረሱ። በዚህ ጊዜ አቢሳ ሳኦልን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስወግደው አሰበ። ሆኖም ዳዊት አቢሳን “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው?” ብሎ በመጠየቅ እንዲህ እንዳያደርግ ከለከለው።—1 ሳሙኤል 26:9, 12
7. ዳዊትን ኃጢአት ከመሥራት የጠበቀው ምን ነበር?
7 ዳዊት ሁለት ጊዜ ሳኦልን ለመግደል የሚያስችል አጋጣሚ ቢያገኝም እንዲህ ማድረግ ያልፈለገው ለምን ነበር? ምክንያቱም ከሳኦል ይበልጥ ይሖዋን ይፈራ ስለነበር ነው። ዳዊት ጤናማ አምላካዊ ፍርሃት ስለነበረው ኃጢአት ከመሥራት ይልቅ መከራ መቀበልን መርጧል። (ዕብራውያን 11:25) ይሖዋ ለእርሱና አብረውት ለነበሩት ሰዎች እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ሙሉ እምነት ነበረው። ዳዊት አምላክን መታዘዝና በእርሱ መታመን ደስታና የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝ፣ አምላክን ችላ ማለት ደግሞ ሞገሱን እንደሚያሳጣ ያውቅ ነበር። (መዝሙር 65:4) ከዚህም በተጨማሪ ዳዊት፣ አምላክ እንደሚያነግሠው የገባለትን ቃል እንደሚፈጽም እንዲሁም አምላክ ራሱ በፈለገው ጊዜና መንገድ ሳኦልን እንደሚያስወግደው ተገንዝቦ ነበር።—1 ሳሙኤል 26:10
አምላክን መፍራት ደስታ ያስገኛል
8. ዳዊት አስቸጋሪ ሁኔታ በገጠመው ጊዜ ያሳየው ባሕርይ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?
8 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ፌዝ፣ ስደትና ሌሎች ችግሮችም እንደሚደርሱብን ልንጠብቅ እንችላለን። (ማቴዎስ 24:9፤ 2 ጴጥሮስ 3:3) እንዲያውም አንዳንዴ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ችግሮች ይገጥሙን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ሁሉን ነገር እንደሚመለከት፣ ጸሎታችንን እንደሚሰማና በተገቢው ጊዜ ችግሮቻችንን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መልኩ እንደሚፈታልን እናውቃለን። (ሮሜ 12:17-21፤ ዕብራውያን 4:16) በመሆኑም ተቃዋሚዎቻችንን ከመፍራት ይልቅ ይሖዋን በመፍራት እንዲያድነን እርሱን እንማጸናለን። እኛም ልክ እንደ ዳዊት፣ መበቀልም ሆነ መከራን ፈርተን የጽድቅ አቋማችንን ማላላት አንፈልግም። ይህን ማድረጋችን የኋላ ኋላ ደስታ ያስገኝልናል። ግን እንዴት?
9. ስደት ቢደርስብንም እንኳ አምላክን መፍራታችን ደስታ ሊያስገኝልን የሚችለው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
9 በአፍሪካ ውስጥ ለብዙ ዓመታት በሚስዮናዊነት ሲያገለግል የቆየ አንድ ወንድም እንደሚከተለው ብሏል:- “በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲ ካርድ ለመግዛት ፈቃደኛ ያልነበሩ አንዲት እናትና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ ሴት ልጇ ሁኔታ መቼም አይረሳኝ። በርካታ ሰዎች በጭካኔ ከደበደቧቸው በኋላ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ነገሯቸው። በመንገድ ላይ እያሉ እናትየዋ እንዲህ ያለ ሁኔታ የደረሰባቸው ለምን እንደሆነ ያልተረዳችውን ልጇን ለማባበል ትጥር ነበር። ይህ ሁኔታ በጊዜው ደስታ አላመጣላቸውም፤ ሆኖም ሕሊናቸው ንጹሕ ነበር። የኋላ ኋላ ግን አምላክን መታዘዛቸው ደስታ አስገኝቶላቸዋል። የፓርቲውን ካርድ ገዝተው ቢሆን ኖሮ የደበደቧቸው ሰዎች በጣም ደስ ብሏቸው ለስላሳ መጠጥ ጋብዘው አጅበዋቸው እየጨፈሩ ቤታቸው ባደረሷቸው ነበር። ልጅቷና እናቷ ደግሞ አቋማቸውን በማጉደፋቸው ምክንያት እጅግ መሪር ሐዘን በገጠማቸው ነበር።” አምላካዊ ፍርሃት ግን ከዚህ ሁሉ ጠብቋቸዋል።
10, 11. ሜሪ አምላክን መፍራቷ ምን ውጤት አስገኝቶላታል?
10 ለሕይወት ቅድስና አክብሮት ማሳየትን የሚመለከቱ ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም ቢሆን አምላካዊ ፍርሃት ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። ሜሪ ሦስተኛ ልጇን በጸነሰች ጊዜ ሐኪሙ እንደሚከተለው በማለት ጽንሱን እንድታስወርድ ነገራት:- “ያለሽበት ሁኔታ አደገኛ ነው። በማንኛውም ጊዜ ችግር ሊገጥምሽና በ24 ሰዓት ውስጥ ልትሞቺ ትችያለሽ። ከዚያም ልጁ ይሞታል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ስለ ልጁ ጤንነት ዋስትና ልንሰጥሽ አንችልም።” በጊዜው ሜሪ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና የነበረ ቢሆንም ገና አልተጠመቀችም። “ያም ሆኖ፣ ይሖዋን ለማገልገልና ምንም ሆነ ምን እርሱን ለመታዘዝ ቆርጬ ነበር” ብላለች።—ዘፀአት 21:22, 23
11 ሜሪ የእርግዝናዋን ወራት ያሳለፈችው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ለቤተሰቧ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ደፋ ቀና ስትል ነበር። በኋላም ልጁ ተወለደ። ሜሪ “በእርግጥ ሁኔታው በፊት ሁለቱን ልጆቼን ከወለድኩበት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ከበድ ያለ ነበር። ቢሆንም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር አልገጠመኝም” ስትል ተናግራለች። ሜሪ አምላክን መፍራቷ ንጹሕ ሕሊና እንዲኖራት ያስቻላት ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳትቆይ ልትጠመቅ ችላለች። የወለደችው ልጅ ካደገ በኋላ እርሱም እንደ እናቱ አምላክን መፍራት ተምሯል፤ በአሁኑ ወቅት በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛል።
‘በእግዚአብሔር በርቱ’
12. ዳዊት አምላክን መፍራቱ ያበረታው እንዴት ነው?
12 ዳዊት ይሖዋን መፍራቱ የረዳው ከክፉ ድርጊት እንዲርቅ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ችግሮች ሲያጋጥሙት ቆራጥ አቋም እንዲወስድና ችግሩን በጥበብ እንዲወጣ ብርታት ሰጥቶታል። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከሳኦል ሸሽተው ጺቅላግ በተባለች የፍልስጥኤማውያን ከተማ ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ተቀምጠው ነበር። (1 ሳሙኤል 27:5-7) አንድ ቀን ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በነበረበት ወቅት አማሌቃውያን ከተማይቱን በመውረር ካቃጠሏት በኋላ ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውንና ከብቶቻቸውን ማርከው ወሰዱ። ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ከተማዋ መጥተው የሆነውን ሁሉ ሲመለከቱ እጅግ አለቀሱ። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎች መሪር ሐዘን ወደ ቁጣ ተለወጠና ዳዊትን ሊወግሩት ተማከሩ። ዳዊት በሁኔታው እጅግ ቢጨነቅም ተስፋ አልቆረጠም። (ምሳሌ 24:10) አምላካዊ ፍርሃት ያለው መሆኑ ወደ አምላክ እንዲመለከትና ‘በእግዚአብሔር እንዲበረታ’ አስችሎታል። በኋላም ዳዊትና ሰዎቹ በአምላክ እርዳታ አማሌቃውያን ላይ ተከታትለው በመድረስ የተወሰደባቸውን ሁሉ ማስመለስ ችለዋል።—1 ሳሙኤል 30:1-20
13, 14. አንዲት ክርስቲያን አምላክን መፍራቷ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የረዳት እንዴት ነው?
13 በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም በይሖዋ ላይ መታመንና ቆራጥ አቋም መውሰድ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ክርስቲናን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ክርስቲና ልጅ ሳለች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና ነበር። ይሁንና በትላልቅ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ፒያኖ የመጫወት ሕልም ነበራት። ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ የሚያስችላት ከፍተኛ መሻሻልም አድርጋ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለሰዎች መመሥከር ያሳፍራት ስለነበር ጥምቀት የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረችም። ሆኖም የአምላክን ቃል ማጥናቷን ስትቀጥል ቃሉ ምን ያህል ኃይል እንዳለው መገንዘብ ጀመረች። ይሖዋን መፍራት የተማረች ሲሆን ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በፍጹም ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ ሐሳባቸውና ኃይላቸው እንዲወድዱት እንደሚፈልግም ተገነዘበች። (ማርቆስ 12:30) ይህም ራሷን ለይሖዋ እንድትወስንና እንድትጠመቅ ገፋፋት።
14 ክርስቲና መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ትችል ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳት ጠየቀች። “በትልልቅ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ ፒያኖ መጫወት ከቦታ ቦታ መዘዋወርና በዓመት ከ400 የሚበልጡ የሙዚቃ ዝግጅቶችን ለማቅረብ መዋዋልን ይጠይቃል። በመሆኑም ይህን ትቼ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ለማገልገል ፈለግሁ፤ ራሴን እየረዳሁ በዚህ አገልግሎት ለመካፈል ስል መምህር ለመሆን ወሰንኩ።” በዚህ ጊዜ ክርስቲና በአገሪቱ ባለው ዝነኛ የሙዚቃ አዳራሽ ውስጥ የመጀመሪያ ዝግጅቷን ለሕዝብ ለማቅረብ እየተጠባበቀች ነበር። ይህንን አስመልክታ ስትናገር “ይህ የሙዚቃ ዝግጅት የመጀመሪያዬም የመጨረሻዬም ሆነ” ብላለች። ክርስቲና የጉባኤ ሽማግሌ የሆነ ወንድም ያገባች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለቱም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ይሖዋ ትክክለኛ ውሳኔ እንድታደርግ የሚያስችል ብርታት ስለሰጣት እንዲሁም ጊዜና ጉልበቷን ለእርሱ አገልግሎት በማዋሏ ደስተኛ ነች።
እጅግ ውድ የሆነ ቅርስ
15. ዳዊት ለልጆቹ ማውረስ የፈለገው ምንድን ነው? ይህንንስ ያደረገው እንዴት ነው?
15 ዳዊት “ልጆቼ ሆይ፣ ኑ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 34:11) ዳዊት አባት እንደመሆኑ መጠን ለልጆቹ ውድ የሆነ ቅርስ ማስተላለፍ ማለትም እውነተኛ፣ ሚዛናዊና ጤናማ በሆነ መንገድ ይሖዋን እንዲፈሩት ልጆቹን ማስተማር እንዳለበት ተሰምቶታል። ዳዊት በንግግሩም ሆነ በምግባሩ፣ ይሖዋ ጨቋኝ፣ አስፈሪ፣ ከሕጉ ጥቂት ፈቀቅ ያሉትን ለመቅጣት የሚጠባበቅ አምላክ ሳይሆን አፍቃሪ፣ ተንከባካቢና በምድር ላይ የሚኖሩ ልጆቹን ይቅር የሚል አባት መሆኑን አሳይቷል። ዳዊት “ስሕተትን ማን ያስተውላታል?” ብሎ ከጠየቀ በኋላ ይሖዋ በእኛ ላይ ስህተት የሚፈላልግ አምላክ አለመሆኑን እንደሚያምን ሲገልጽ “ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ” ብሏል። ከዚህ በተቃራኒ ዳዊት ከልቡ ጥረት ካደረገ ቃሉም ሆነ አሳቡ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነበር።—መዝሙር 19:12, 14 የ1954 ትርጉም
16, 17. ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲፈሩ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
16 ዳዊት በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ ወላጆች ምሳሌ ይሆናል። ከወንድሙ ጋር ሆኖ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኘው ራልፍ እንዲህ ይላል:- “ወላጆቻችን ያሳደጉን የእውነት ቤት አስደሳች እንዲሆንልን አድርገው ነው። ልጆች እያለን የጉባኤ እንቅስቃሴዎችን አስመልክተው ሲጨዋወቱ እኛም ሐሳብ እንድንሰጥ ያደርጉ ነበር፤ ይህም ልክ እንደ እነርሱ ለእውነት ከፍተኛ ጉጉት አሳድሮብናል። ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደምንችል ሆኖ እንዲሰማን አድርገው አሳድገውናል። ቤተሰባችን ለብዙ ዓመታት ይኖር የነበረው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ የነበረ በመሆኑ አዳዲስ ጉባኤዎችን በማቋቋሙ ሂደት እርዳታ አበርክቷል።
17 “በትክክለኛው መንገድ መመላለሳችንን እንድንቀጥል የረዳን በርካታ የማያፈናፍኑ ሕጎች ስለተሰጡን አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለወላጆቻችን እውን እንዲሁም እጅግ በጣም ደግና ጥሩ አምላክ ስለሆነላቸው ነው። ወላጆቻችን፣ ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅና እርሱን ለማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። እኛም ለአምላክ እውነተኛ ፍርሃት ማዳበር እንዳለብንና ልንወደው እንደሚገባ ከእነርሱ ተምረናል። አንድ ዓይነት ጥፋት በምንሠራበት ጊዜ እንኳ ወላጆቻችን ይሖዋ እንደማይወደን ሆኖ እንዲሰማን አያደርጉም ወይም ደግሞ በንዴት ተነሳስተው አላስፈላጊ ገደቦችን አይጥሉብንም ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ቁጭ አድርገው በረጋ መንፈስ ያነጋግሩናል፤ እንዲያውም አንዳንዴ እማማ ልባችን እስኪነካ ድረስ እያለቀሰች ትመክረናለች። ይህም መልካም ውጤት አስገኝቷል። ወላጆቻችን በቃላቸውም ይሁን በተግባራቸው ይሖዋን መፍራት ከሁሉ ነገር የላቀ እንደሆነና የእርሱ ምሥክር መሆን የሚያስደስት እንጂ ከባድ ሸክም እንዳልሆነ አስተምረውናል።”—1 ዮሐንስ 5:3
18. እውነተኛውን አምላክ መፍራታችን ምን ያስገኝልናል?
18 ‘ዳዊት ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት’ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- “ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔርም የሚያስተዳድር፣ እርሱ፣ ደመና በሌለበት፣ በማለዳ ፀሓይ በምትወጣበት ጊዜ፣ እንዳለው ብርሃን ነው።” (2 ሳሙኤል 23:1, 3, 4) የዳዊት ልጅና አልጋ ወራሽ የሆነው ሰሎሞን ይህን ነጥብ በሚገባ ተረድቶ ስለነበር ይሖዋን “አስተዋይ [“ታዛዥ፣” NW] ልብ” እንዲሁም ‘መልካሙንና ክፉውን የመለየት’ ችሎታ እንዲሰጠው ጠይቋል። (1 ነገሥት 3:9) ሰሎሞን ይሖዋን መፍራት የጥበብ መንገድ መሆኑንና ደስታንም እንደሚያስገኝ ተገንዝቧል። ቆየት ብሎም በመክብብ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ የሚከተሉትን ቃላት አስፍሯል:- “እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፤ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና። መልካምም ይሁን ክፉ፣ ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ ማንኛውንም ሥራ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።” (መክብብ 12:13, 14) ይህን ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት” ጥበብንና ደስታን ብቻ ሳይሆን “ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን” እንደሚያስገኙልን እንገነዘባለን።—ምሳሌ 22:4
19. “እግዚአብሔርን መፍራት” ምን ማለት መሆኑን ለማወቅ ምን ይረዳናል?
19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩ ምሳሌዎችንና በዘመናችን ያሉ ተሞክሮዎችን መመልከታችን ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ማሳየት በእውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለመገንዘብ አስችሎናል። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት በሰማይ የሚኖረው አባታችንን የሚያሳዝን ድርጊት ከመፈጸም እንድንቆጠብ ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችንን ለመጋፈጥ የሚረዳ ድፍረት እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮችንና ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንድናገኝ ያደርገናል። ስለሆነም ወጣቶችም ሆን አረጋውያን ሁላችንም የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናት፣ ባነበብናቸው ነገሮች ላይ በማሰላሰልና ዘወትር ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቅረብ። እንዲህ ስናደርግ ‘የአምላክን እውቀት’ ማግኘት ብቻ ሳይሆን “እግዚአብሔርን መፍራት” ምን ማለት መሆኑን እንረዳለን።—ምሳሌ 2:1-5 የ1954 ትርጉም
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስሟ ተቀይሯል።
ልታብራራ ትችላለህ?
አምላክን መፍራት
• ከኃጢአት ጎዳና እንድንመለስ የሚረዳን
• በችግርና በፈተና ውስጥ ብንሆንም ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርገን
• የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስችል ብርታት የሚሰጠን
• ለልጆቻችን ውድ ቅርስ የሚሆነው
እንዴት ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳዊት አምላክን መፍራቱ ንጉሥ ሳኦል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንዲቆጠብ አድርጎታል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላካዊ ፍርሃት ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያወርሱት የሚገባ እጅግ ውድ ቅርስ ነው