ምዕራፍ 4
ከአምላክ ለሚገኘው እውቀት ቁልፍ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ
1, 2. የዓለም ሃይማኖቶች የአምላክን እውቀት ለማግኘት የሚያስችለውን ቁልፍ ያድበሰበሱት እንዴት ነው?
እቤትህ በር ላይ ቆመህ ቁልፉን ለመክፈት እየታገልክ ነው እንበል። ውጭው በጣም ይበርዳል፣ ጊዜውም ጨልሟል። እቤትህ ለመግባት በጣም ቸኩለሃል። የበርህ ቁልፍ ግን አይሠራም። ቁልፉ አልተለወጠም፣ በርህ ግን ፍንክች አልል አለ። እንዴት ትዕግሥትን የሚፈታተን ሁኔታ ነው! ቁልፍህን ደጋግመህ ተመለከትከው። ቁልፉ ተሳስቷል ወይስ የበሩን ቁልፍ ያበላሸብህ ሰው አለ?
2 የዚህ ዓለም ሃይማኖታዊ ዝብርቅ ከአምላክ በሚገኘው እውቀት ላይ ያስከተለው ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። ብዙ ሰዎች ከአምላክ ለሚገኘው እውቀት ቁልፍ የሆነውን ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት አዛብተዋል። አንዳንድ ሃይማኖቶች ኢየሱስን ፈጽመው ከእምነታቸው በማስወገድ ቁልፉን አውጥተው ጥለዋል። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስን ሁሉን የሚችል አምላክ ነው ብለው በማምለክ የሌለውን ቦታ ሰጥተውታል። በዚያም ሆነ በዚህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤ ካላገኘን አምላክን የማወቁ አጋጣሚ ዝግ ይሆንብናል።
3. ኢየሱስ የአምላክን እውቀት ለማግኘት የሚያስችል ቁልፍ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
3 ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወትም፣ ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው” ብሎ እንደነበረ ታስታውስ ይሆናል። (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ ይህን ሲናገር ጉረኛ መሆኑ አልነበረም። ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ደጋግመው ያሳስባሉ። (ኤፌሶን 4:13፤ ቆላስይስ 2:2፤ 2 ጴጥሮስ 1:8፤ 2:20) ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነቢያት ሁሉ [ለኢየሱስ ክርስቶስ] ይመሰክሩለታል” ብሏል። (ሥራ 10:43) ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ [በኢየሱስ] ነው” ሲል ጽፏል። (ቆላስይስ 2:3) እንዲያውም ጳውሎስ ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ ፍጻሜ የሚያገኙት በኢየሱስ ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 1:20) ስለዚህ የአምላክን እውቀት ለማግኘት ቁልፉ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ስለ ኢየሱስ ያለን እውቀት ስለ ማንነቱና በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ስላለው ሚና ከሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች ሁሉ የጠራ መሆን ይኖርበታል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ተከታዮች ኢየሱስ በአምላክ ዓላማዎች አፈጻጸም ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ እንዳለው የሚያምኑት ለምንድን ነው?
እንደሚመጣ የተነገረለት መሲሕ
4, 5. በመሲሑ ላይ ያተኮሩት ተስፋዎች የትኞቹ ናቸው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትስ መሲሑን የተመለከቱት እንዴት ነው?
4 የአምላክ አገልጋዮች ከታማኙ ከአቤል ዘመን ጀምሮ እንደሚመጣ ይሖዋ አምላክ ራሱ አስቀድሞ የተናገረለት ዘር የሚገለጥበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት ሲጠባበቁ ኖረዋል። (ዘፍጥረት 3:15፤ 4:1–8፤ ዕብራውያን 11:4) ዘሩ መሲሕ በመሆን የአምላክን ዓላማ እንደሚፈጽም ተገልጾ ነበር። መሲሕ ማለት ደግሞ “ቅቡዕ” ማለት ነው። ይህ መሲሕ ሲመጣ ‘ኃጢአትን ይፈጽማል’ ተብሎ ነበር። የመንግሥቱም ክብር በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ተተንብዮአል። (ዳንኤል 9:24–26፤ መዝሙር 72:1–20) ታዲያ መሲሑ ማን ሆኖ ተገኘ?
5 እንድርያስ የተባለ አንድ ወጣት አይሁዳዊ የናዝሬቱ ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ሲሰማ ምን እንደተሰማው ልትገምት ትችላለህ። እንድርያስ ወደ ወንድሙ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ ሲሮጥ ሄደና “መሢሕን አግኝተናል” አለ። (ዮሐንስ 1:42) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው መሲሕ ስለመሆኑ እርግጠኞች ነበሩ። (ማቴዎስ 16:16) እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ ኢየሱስ ይመጣል ተብሎ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ወይም ክርስቶስ ስለመሆኑ ለነበራቸው እምነት ሕይወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት እንኳን ፈቃደኞች ነበሩ። ይህን የመሰለ ጠንካራ እምነት ሊኖራቸው የቻለው ምን ማስረጃ ቢኖራቸው ነው? በሦስት ዘርፍ የተከፈሉ ማስረጃዎችን እንመልከት።
ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች
6. (ሀ) ተስፋ የተደረገው መሲሕ የሚመጣው ከየትኛው የዘር ሐረግ ነበር? ኢየሱስስ የተገኘው ከዚህ የዘር ሐረግ እንደነበረ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ከ70 እዘአ ወዲህ የተነሳ ማንኛውም ሰው መሲሕ ነኝ ሊል የማይችለው ለምንድን ነው?
6 ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው መሲሕ መሆኑን ከሚያረጋግጡት ማስረጃዎች የመጀመሪያው የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ነው። ይሖዋ ተስፋ የተደረገው ዘር ከአብርሃም ዘር እንደሚመጣ ለአገልጋዩ ለአብርሃም ነግሮት ነበር። የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ፣ የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብና የያዕቆብ ልጅ ይሁዳ ይህንኑ ተስፋ በየተራ ተቀብለዋል። (ዘፍጥረት 22:18፤ 26:2–5፤ 28:12–15፤ 49:10) ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ መሲሑ ከንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚመጣ በተነገረ ጊዜ የመሲሑ የትውልድ መስመር ይበልጥ እየጠበበ መጣ። (መዝሙር 132:11፤ ኢሳይያስ 11:1, 10) የማቴዎስና የሉቃስ የወንጌል ትረካዎች ኢየሱስ ከዚህ የቤተሰብ መስመር የመጣ መሆኑን አረጋግጠዋል። (ማቴዎስ 1:1–16፤ ሉቃስ 3:23–38) ኢየሱስ ብዙ ጠላቶች የነበሩት ቢሆንም አንዳቸውም ቢሆኑ በጊዜው በሰፊው ታውቆ የነበረው የትውልድ መስመሩ ትክክል አይደለም ብለው ለመቃወም አልደፈሩም። (ማቴዎስ 21:9, 15) ስለዚህ የዘር ግንዱ ፈጽሞ የማያጠያይቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በ70 እዘአ ባጠፉ ጊዜ ግን የአይሁዳውያን ቤተሰቦች የትውልድ መዝገብ ጠፋ። ከዚያ በኋላ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ነኝ በማለት ማስረጃ ሊያቀርብ የሚችል ሰው አልነበረም።
7. (ሀ) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥልን ሁለተኛ የማስረጃ ዘርፍ ምንድን ነው? (ለ) ሚክያስ 5:2 በኢየሱስ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?
7 ሁለተኛው የማስረጃ ዘርፍ ፍጻሜ ያገኙ ትንቢቶች ናቸው። ስለ መሲሑ ምድራዊ ሕይወት የሚገልጹ በርካታ ትንቢቶች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይገኛሉ። በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ተነስቶ የነበረው ነቢዩ ሚክያስ ይህ ታላቅ ገዥ ከትላልቆቹ ከተሞች የማትቆጠር በነበረችው በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ተነበየ። በእስራኤል አገር ቤተ ልሔም ተብለው የሚጠሩ ሁለት ከተሞች ነበሩ። ይህ ትንቢት ግን መሲሑ የሚወለደው ንጉሥ ዳዊት በተወለደባት በቤተ ልሔም ኤፍራታ እንደሆነ ለይቶ አመልክቷል። (ሚክያስ 5:2) የኢየሱስ ወላጆች ዮሴፍና ማርያም ይኖሩ የነበረው ከቤተ ልሔም በስተ ሰሜን 150 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በናዝሬት ነበር። ይሁን እንጂ ማርያም ነፍሰ ጡር በነበረችበት ጊዜ ሮማዊው አውግስጦስ ቄሣር ሰዎች ሁሉ በየተወለዱባቸው ከተሞች እንዲመዘገቡ ትእዛዝ አወጣ።a በዚህም ምክንያት ዮሴፍ ነፍሰ ጡር የነበረችውን ሚስቱን ይዞ ወደ ቤተ ልሔም ሄደ። በዚያም ኢየሱስ ተወለደ።— ሉቃስ 2:1–7
8. (ሀ) ስድሳ ዘጠኙ “ሳምንታት” ወይም ሱባዔዎች የጀመሩት መቼና በምን ድርጊት ነበር? (ለ) ስድሳ ዘጠኙ “ሳምንታት” ምን ያህል ርዝመት ነበራቸው? በተፈጸሙ ጊዜስ ምን ሆነ?
8 ነቢዩ ዳንኤል በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢየሩሳሌም እንድትታደስና እንደገና እንድትገነባ ትእዛዝ ከወጣ ከ69 “ሱባዔ” ወይም “ሳምንታት” በኋላ “አለቃው መሲሕ” እንደሚገለጥ ተንብዮአል። (ዳንኤል 9:24, 25) እያንዳንዱ “ሳምንት” የሰባት ዓመት ርዝመት አለው።b የመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የዓለም ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ኢየሩሳሌም ዳግመኛ እንድትሠራ ትእዛዝ የወጣው በ455 ከዘአበ ነው። (ነህምያ 2:1–8) ስለዚህ መሲሑ መገለጥ የነበረበት ከ455 ከዘአበ 483 ዓመታት (69 በ7 ሲባዛ) ቆይቶ ነው። ይህም ይሖዋ ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ ወደቀባበት ወደ 29 እዘአ ያደርሰናል። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ “ክርስቶስ” (“ቅቡዕ” ማለት ነው) ወይም መሲሕ ሆነ።— ሉቃስ 3:15, 16, 21, 22
9. (ሀ) መዝሙር 2:2 የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) በኢየሱስ ላይ የተፈጸሙ ሌሎች ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? (ሰንጠረዡን ተመልከት።)
9 እርግጥ ነው፣ የኢየሱስን መሲሕነት ሁሉም ሰው አልተቀበለውም። ይህ እንደሚሆን በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አስቀድሞ ተገልጿል። በመዝሙር 2:2 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ አነሳሽነት “የምድር ነገሥታት ተነሡ፣ አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ እንዲህ ሲሉ ተማከሩ” ሲል ተንብዮአል። ይህ ትንቢት ከአንድ በላይ ከሆኑ አገሮች የተውጣጡ መሪዎች የይሖዋን ቅቡዕ ወይም መሲሕ ለማጥቃት ተባብረው እንደሚነሱ አመልክቷል። ይህም በትክክል ተፈጽሟል። የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ንጉሥ ሄሮድስና ጴንጠናዊ ጲላጦስ የተባለው ሮማዊ ገዥ ኢየሱስን በማስገደሉ ተግባር ተካፍለዋል። ጠላትነት የነበራቸው ሄሮድስና ጲላጦስ ከዚያ ጊዜ ጀምረው የነፍስ ወዳጆች ሆነዋል። (ማቴዎስ 27:1, 2፤ ሉቃስ 23:10–12፤ ሥራ 4:25–28) ኢየሱስ መሲሕ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት “ጎላ ብለው የሚታዩ አንዳንድ መሲሐዊ ትንቢቶች” የሚለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።
10. ኢየሱስ ከእርሱ የተላከ ቅቡዕ መሆኑን ይሖዋ የመሠከረው እንዴት ነው?
10 የኢየሱስን መሲሕነት ከሚያረጋግጡት የማስረጃ ዘርፎች ሦስተኛው የይሖዋ አምላክ ምሥክርነት ነው። ኢየሱስ ተስፋ የተደረገው መሲሕ መሆኑን ለሰዎች እንዲያሳውቁ ይሖዋ መላእክትን ልኳል። (ሉቀስ 2:10–14) እንዲያውም ይሖዋ ራሱ በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ወቅት የሚወደው ልጁ እንደሆነ ከሰማይ ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:16, 17፤ 17:1–5) ይሖዋ አምላክ ለኢየሱስ ተአምራት የማድረግ ኃይል ሰጥቶታል። እነዚህ ተአምራት እያንዳንዳቸው የኢየሱስን መሲሕነት የሚያረጋግጡ ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው፤ ምክንያቱም አምላክ አታላይ ለሆነ ሰው ተአምራት የማድረግ ኃይል እንደማይሰጥ የታወቀ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ የኢየሱስን መሲሕነት የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በብዛት የተተረጎመውና የተሰራጨው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲሆኑ በወንጌሎች ውስጥ የሚገኙትን ትረካዎች በመንፈሱ አስጽፏል።— ዮሐንስ 4:25, 26
11. ኢየሱስ መሲሕ ስለመሆኑ ምን ያህል ማስረጃዎች አሉ?
11 በአጠቃላይ እነዚህ የማስረጃ ዘርፎች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ በመቶ የሚቆጠሩ ማስረጃዎችን ያካትታሉ። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ‘ነቢያት ሁሉ የመሰከሩለትና’ ከአምላክ ለሚገኘው እውቀት ቁልፍ እንደሆነ አድርገው መመልከታቸው ተገቢ ነበር ማለት ነው። (ሥራ 10:43) ይሁን እንጂ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ የሚኖርብን መሲሕ መሆኑን ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ከየት መጣ? ምን ይመስል ነበር?
ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት የነበረው ሕልውና
12, 13. (ሀ) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበረ እንዴት እናውቃለን? (ለ) “ቃል” ማን ነው? ሰው ከመሆኑ በፊትስ ምን አድ ርጓል?
12 የኢየሱስ ሕይወት በሦስት ሊከፈል ይችላል። የመጀመሪያው ክፍል የጀመረው ምድር ላይ ከመወለዱ ከብዙ ዘመናት በፊት ነው። ሚክያስ 5:2 መሲሑ “አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ” ነው በማለት ይናገራል። ኢየሱስ ራሱም የመጣው “ከላይ” ማለትም ከሰማይ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:23፤ 16:28) ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ የኖረው ለምን ያህል ጊዜ ነው?
13 ኢየሱስ በቀጥታ በይሖዋ የተፈጠረ በመሆኑ የአምላክ “አንድያ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 3:16) ከዚያም በኋላ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” በመሆኑ አምላክ ሌሎቹን ፍጥረታት በሙሉ ለመፍጠር ተጠቅሞበታል። (ቆላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14) ዮሐንስ 1:1 “ቃል” (ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት በነበረው ሕልውና) “በመጀመሪያ” ከእግዚአብሔር ጋር እንደነበረ ይናገራል። ስለዚህ ‘ሰማያትና ምድር በተፈጠሩበት’ ጊዜ ቃል ከይሖዋ አምላክ ጋር ነበር ማለት ነው። እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ያለው ለቃል ነበር። (ዘፍጥረት 1:1, 26) በተመሳሳይም በምሳሌ 8:22–31 ላይ በጥበብ የተመሰለውና በፍጥረት ሥራ ከይሖዋ ጎን ሆኖ ይሠራ እንደነበረ የተነገረለት “ዋና ሠራተኛ” ቃል መሆን ይኖርበታል። ቃል ሕልውናውን ከይሖዋ አምላክ ካገኘ በኋላ ምድር ላይ ሰው ሆኖ መኖር ከመጀመሩ በፊት ለብዙ ዘመናት በሰማይ ኖሯል።
14. ኢየሱስ ‘የማይታየው አምላክ ምሳሌ’ የተባለው ለምንድን ነው?
14 ስለዚህ ቆላስይስ 1:15 ኢየሱስን ‘የማይታየው አምላክ ምሳሌ’ ሲል መጥራቱ ሊያስደንቀን አይገባም። ይህ ታዛዥ ልጅ ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው ዘመናት ከአባቱ ጋር ተቀራርቦ የኖረ በመሆኑ ልክ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ ሊሆን ችሏል። ኢየሱስ ሕይወት ሰጪ የሆነው ከአምላክ የሚገኘው እውቀት መክፈቻ ቁልፍ የሆነበት ሌላው ምክንያት ይህ ነው። ኢየሱስ ምድር ሳለ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ይሖዋ በእርሱ ቦታ ቢሆን ኖሮ የሚያደርጋቸውን ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን ማወቅ ስለ ይሖዋ ያለንን እውቀት ማሳደግ ማለት ነው። (ዮሐንስ 8:28፤ 14:8–10) እንግዲያው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን እውቀት መጨመር በጣም አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው።
የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት
15. ኢየሱስ ፍጹም ልጅ ሆኖ ሊወለድ የቻለው እንዴት ነው?
15 የኢየሱስ ሕልውና ሁለተኛ ክፍል እዚህች ምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት ነው። አምላክ የኢየሱስን ሰማያዊ ሕይወት ታማኝ ወደነበረችው አይሁዳዊት ድንግል ወደ ማርያም ማኅፀን ሲያዛውር ኢየሱስም የይሖዋን ፈቃድ እሺ ብሎ ተቀብሏል። ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል በማርያም ላይ ‘በማጥላት’ እንድታረግዝና በኋላም ፍጹም የሆነ ልጅ እንድትወልድ አስችሏታል። (ሉቃስ 1:34, 35) የኢየሱስ ሕይወት የመጣው ፍጹም ከሆነ ምንጭ ስለነበረ ምንም ዓይነት የፍጽምና ጉድለት አልወረሰም። የአናጢው የዮሴፍ የማደጎ ልጅ ሆኖ በኑሮው ዝቅተኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ አደገ። የዚህ ቤተሰብ ልጆች በርካታ ሲሆኑ እርሱ የበኩር ልጅ ነበር።— ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:22, 23፤ ማርቆስ 6:3
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ተአምራት ለማድረግ ያስቻለውን ኃይል ያገኘው ከየት ነው? ካደረጋቸው ተአምራት አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? (ለ) ኢየሱስ ካሳያቸው ባሕርያት አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
16 ኢየሱስ ለይሖዋ አምላክ ያደረ ሰው መሆኑ ገና በ12 ዓመት ዕድሜው እንኳን ሊታይ ችሏል። (ሉቃስ 2:41–49) አድጎ 30 ዓመት ከሞላውና አገልግሎቱን ከጀመረ በኋላም ለሰው ልጆች የጠለቀ ፍቅር ያለው መሆኑን አሳይቷል። ከቅዱሱ የአምላክ መንፈስ ተአምራት የማድረግ ኃይል በተቀበለ ጊዜ በርህራሄ ስሜት ተነሳስቶ በሽተኞችን፣ ሽባዎችን፣ አካለ ስንኩላንን፣ ዓይነ ስውሮችን፣ ድዳዎችንና በሥጋ ደዌ የተያዙ ሰዎችን ፈውሷል። (ማቴዎስ 8:2–4፤ 15:30) ኢየሱስ በሺህ የሚቆጠሩ ረሀብተኞችን መግቧል። (ማቴዎስ 15:35–38) በወዳጆቹ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ተቃርቦ የነበረው ማዕበል ጸጥ እንዲል አድርጓል። (ማርቆስ 4:37–39) ሙታንን ሳይቀር አስነስቷል። (ዮሐንስ 11:43, 44) እነዚህ ተአምራት በሙሉ የተረጋገጡ የታሪክ ሐቆች ናቸው። የኢየሱስ ጠላቶች እንኳን ‘ብዙ ምልክቶች ያደረገ መሆኑን’ አልካዱም።— ዮሐንስ 11:47, 48
17 ኢየሱስ በትውልድ አገሩ በሙሉ ተዘዋውሮ ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯል። (ማቴዎስ 4:17) በተጨማሪም በጣም ታላቅ የሆነ የምክንያታዊነትና የታጋሽነት ምሳሌ ትቶልናል። ደቀ መዛሙርቱ እንደሚጠበቅባቸው ሆነው ባልተገኙ ጊዜ እንኳን በአዛኝነት “መንፈስስ ተዘጋጅታለች፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው” አላቸው። (ማርቆስ 14:37, 38) እውነትን የሚንቁትንና ችግረኛ ሰዎችን የሚጨቁኑትን ለመቃወም ግን ደፋርና ወደኋላ የማይል ነበር። (ማቴዎስ 23:27–33) ከሁሉ በላይ ደግሞ የአባቱን የፍቅር ምሳሌነት ፍጹም በሆነ መንገድ ኮርጆአል። ኢየሱስ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ወደፊት በሕይወት የመኖር ተስፋ እንዲያገኙ ሲል ለመሞት ፈቃደኛ ሆኗል። ስለዚህ ኢየሱስ የአምላክን እውቀት ለማግኘት የሚያስችል ቁልፍ ነው ብለን ብንጠራው የሚበዛበት አይሆንም! አዎን፣ እርሱ ሕያው ቁልፍ ነው! ግን ሕያው ቁልፍ የምንለው ለምንድን ነው? የዚህ መልስ ወደ ሦስተኛው የሕይወቱ ክፍል ያመጣናል።
ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ
18. በአሁኑ ጊዜስ በዓይነ ሕሊናችን ውስጥ ስለ ኢየሱስ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት እንዴት ያለ መሆን ይኖርበታል?
18 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሞት ቢናገርም አሁን ሕያው ነው! እንዲያውም ከሙታን ስለመነሳቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የዓይን ምሥክሮች ሆነዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:3–8) አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው ከዚያ በኋላ በሰማይ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ንጉሣዊ ሥልጣኑን የሚቀበልበትን ጊዜ ሲጠባበቅ ቆይቷል። (መዝሙር 110:1፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስን በዓይነ ሕሊናችን የምንመለከተው እንዴት ነው? በግርግም ውስጥ ተጠቅልሎ እንደተኛ ምስኪን ሕፃን ነው? ወይስ ሊሞት ተቃርቦ እንደሚያጣጥር ሰው? የለም፣ አሁን ኃያል ንጉሥ ነው! በቅርቡ ደግሞ በመከራ በተሞላችው ምድር ላይ ግዛቱን ያሰ ፍናል።
19. ኢየሱስ በቅርቡ ምን እርምጃ ይወስዳል?
19 ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ 19:11–15 ላይ ክፉዎችን ለማጥፋት በታላቅ ሥልጣን እንደሚመጣ ሥዕላዊ በሆነ መንገድ ተገልጿል። ይህ አፍቃሪ ሰማያዊ ገዥ በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እያስጨነቀ ያለውን መከራ ለማስቀረት ምን ያህል ጉጉት ይኖረው ይሆን! በተጨማሪም ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የተወልንን ፍጹም አርዓያ ለመከተል የሚጥሩትን ሰዎች ለመርዳት ከዚህ ያላነሰ ጉጉት አለው። (1 ጴጥሮስ 2:21) እነዚህን ሰዎች ብዙ ጊዜ አርማጌዶን ተብሎ ከሚጠራው ‘ሁሉን የሚችል አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ በሕይወት ጠብቆ ለማሳለፍና የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ምድራዊ ተገዥዎች በመሆን ለዘላለም እንዲኖሩ ለማስቻል ይፈልጋል።— ራእይ 7:9, 14፤ 16:14, 16
20. በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ኢየሱስ ለሰው ልጆች ምን ያደርጋል?
20 እንደሚመጣ በቅድሚያ በተነገረለት የኢየሱስ የሺህ ዓመት የሰላም ግዛት ውስጥ ለመላው የሰው ልጅ ጥቅም የሚያስገኙ ተአምራት ያደርጋል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:1–10፤ ራእይ 20:6) ኢየሱስ ማንኛውንም ዓይነት በሽታ ይፈውሳል፣ ሞትንም ያጠፋል። በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኙ ከሙታን ያስነሳቸዋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ቆየት ብለህ በሌላ ምዕራፍ ላይ ስለ ኢየሱስ መሲሐዊ መንግሥት ተጨማሪ እውቀት ስታገኝ በጣም እንደምትደሰት እናምናለን። በኢየሱስ መንግሥት ግዛት ውስጥ የምናገኘው ሕይወት ምን ያህል አስደናቂ እንደሚሆን መገመት እንኳን እንደማንችል እርግጠኛ ሁን። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይበልጥ መተዋወቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! አዎን፣ ወደ ዘላለም ሕይወት ለሚመራውና ከአምላክ ለሚገኘው እውቀት መክፈቻ የሆነውን ሕያው ቁልፍ ኢየሱስን አለመርሳታችን በጣም አስፈላጊ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህ ምዝገባ ለሮማ መንግሥት ግብር እንዲሰበሰብ የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል። ስለዚህም አውግስጦስ ሳያውቀው “አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው ይነሣል” የሚለውን ትንቢት ፈጽሟል። ይኸው ትንቢት “የቃል ኪዳኑ አለቃ” ወይም መሲሑ በዚህ ንጉሥ ምትክ በሚነሣው ገዥ ዘመን ‘እንደሚሰበር’ ተንብዮአል። ኢየሱስ የተገደለው በአውግስጦስ ወራሽ በጢባርዮስ ዘመነ መንግሥት ነበር።— ዳንኤል 11:20–22
b የጥንቶቹ አይሁዶች ዓመታትን በሳምንት ወይም በሱባዔ ከፍለው ይቆጥሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል ሰባተኛው ቀን ሰንበት እንደሆነ ሁሉ ሰባተኛውም ዓመት የሰንበት ዓመት ነበር።— ዘጸአት 20:8–11፤ 23:10, 11
እውቀትህን ፈትሽ
የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
በኢየሱስ ላይ ከተፈጸሙ መሲሐዊ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
ኢየሱስ ከእርሱ የተላከ ቅቡዕ መሆኑን አምላክ በቀጥታ ያሳየው እንዴት ነው?
ኢየሱስ የአምላክን እውቀት ለማግኘት የሚያስችል ሕያው ቁልፍ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 37 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
ጎላ ብለው የሚታዩ አንዳንድ መሲሐዊ ትንቢቶች
ትንቢት ድርጊት ፍጻሜ
የልጅነት ሕይወቱ
ኢሳይያስ 7:14 ከድንግል ተወለደ ማቴዎስ 1:18–23
ኤርምያስ 31:15 ከተወለደ በኋላ ሕፃናት ተገደሉ ማቴዎስ 2:16–18
አገልግሎቱ
ኢሳይያስ 61:1, 2 ከአምላክ የተሰጠው ተልዕኮ ሉቃስ 4:18–21
ኢሳይያስ 9:1, 2 አገልግሎቱ ሰዎች ማቴዎስ 4:13–16
ታላቅ ብርሃን እንዲያዩ አስቻለ
መዝሙር 69:9 ለይሖዋ ቤት ቅንዓት አሳይቷል ዮሐንስ 2:13–17
ኢሳይያስ 53:1 ሰዎች አላመኑበትም ዮሐንስ 12:37, 38
ዘካርያስ 9:9፤ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ማቴዎስ 21:1–9
መዝሙር 118:26 ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፤ የንጉሥ አቀባበል
ተደረገለት፤ በይሖዋ ስም የሚመጣም
እርሱ እንደሆነ ተነገረ
አማሟቱና አልፎ የተሰጠበት ሁኔታ
መዝሙር 41:9፤ 109:8 አንድ ሐዋርያ ከሃዲ ሆነ ሥራ 1:15–20
ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጠ
በኋላ በሌላ ሰው ተተካ
ዘካርያስ 11:12 በ30 ብር ተሸጠ ማቴዎስ 26:14, 15
መዝሙር 27:12 የሐሰት ምሥክሮች ማቴዎስ 26:59–61
እንዲመሰክሩበት ተደረገ
መዝሙር 22:18 በልብሱ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ ዮሐንስ 19:23, 24
ኢሳይያስ 53:12 ከኃጢአተኞች ጋር ተቆጠረ ማቴዎስ 27:38
መዝሙር 22:7, 8 በሚሞትበት ጊዜ ማርቆስ 15:29–32
ሰዎች ተሳለቁበት
መዝሙር 69:21 ኮምጣጤ ተሰጠው ማርቆስ 15:23, 36
ኢሳይያስ 53:5፤ ተወጋ ዮሐንስ 19:34, 37
ኢሳይያስ 53:9 ከሀብታሞች ጋር ተቀበረ ማቴዎስ 27:57–60
መዝሙር 16:8–11 ሥጋው ከመበስበሱ በፊት ተነሣ ሥራ 2:25–32፤
አዓት የግርጌ ማስታወሻ 13:34–37
[በገጽ 35 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የታመሙትን እንዲፈውስ አምላክ ኃይል ሰጥቶታል