-
በእርግጠኝነት ልታገኘው የምትችለው ውርስመጠበቂያ ግንብ—2004 | ጥቅምት 1
-
-
በእርግጠኝነት ልታገኘው የምትችለው ውርስ
“ከአንድ ሰው፣ ፈጽሞ ያልጠበቅከው ውርስ ልታገኝ እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ከደረሰህ ተጠንቀቅ። የአታላዮች ሲሳይ ልትሆን ትችላለህ።”
ይህ የዩናይትድ ስቴትስ ፖስታ ምርመራ አገልግሎት ድርጅት በድህረ ገጹ ላይ ያወጣው ማስጠንቀቂያ ነው። ማስጠንቀቂያው ለምን አስፈለገ? በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ‘አንድ ዘመድህ ሲሞት የተናዘዘልህ ውርስ አለ’ የሚል መልእክት እየደረሳቸው ስለነበረ ነው። በዚህ ምክንያት በርካታ ሰዎች ውርሱ የት እንደሚገኝና እንዴት መውሰድ እንደሚቻል ለማወቅ መልእክቱን ለላከላቸው ሰው 30 ወይም ከዚያ የሚበልጥ የአሜሪካ ዶላር የአገልግሎት ክፍያ ልከዋል። የሚያሳዝነው ግን ነገሩ እንዳሰቡት አልሆነም። ሁሉም ምንም ውርስ እንደሌላቸው የሚገልጽ ተመሳሳይ መልስ ደረሳቸው።
አጭበርባሪዎች የሰዎችን ውርስ የማግኘት ተፈጥሯዊ ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይህን የመሳሰሉ የረቀቁ ዘዴዎች ይጠቀማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “ደግ ሰው ለልጅ ልጆቹ ውርስ ትቶ ያልፋል” በማለት በእርግጠኝነት ውርስ ሊያወርሱ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ይናገራል። (ምሳሌ 13:22) እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” የሚለውን ተወዳጅና በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ተስፋ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 5:5
ኢየሱስ የሰጠው ይህ ተስፋ የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት በመንፈስ አነሳሽነት የተናገረውን ትንቢት ያስታውሰናል።—መዝሙር 37:11
‘ምድርን መውረስ’ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ሆኖም ይህ ተስፋ ሰዎችን አታልሎ አንድ ነገር ለመቀማት ታስቦ በተንኮል የተዶለተ ዘዴ አለመሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን? ይሖዋ ፈጣሪና የሁሉም ነገሮች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን እጹብ ድንቅ ከሆኑት ፍጥረታት መካከል አንዷ የሆነችውን ምድርን ለፈለገው የማውረስ ሕጋዊ መብት አለው። ይሖዋ በንጉሥ ዳዊት በኩል ለሚወደው ልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ትንቢታዊ ይዘት ያለው ቃል ገብቶለት ነበር:- “ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፤ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ።” (መዝሙር 2:8) በዚህ ምክንያት አምላክ ኢየሱስን ‘ሁሉን ወራሽ እንዳደረገው’ ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብራውያን 1:2) ስለዚህ ኢየሱስ የዋሆች “ምድርን ይወርሳሉ” ብሎ ሲናገር በእርግጥ የማውረስ ዓላማ እንደነበረውና ቃሉንም ለመፈጸም የሚያስችል የተሟላ ሥልጣን እንዳለው ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—ማቴዎስ 28:18
አሁን የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ ይህ ቃል ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? የሚለው ነው። በዛሬው ጊዜ በሁሉም ቦታዎች ኃይለኛና እብሪተኛ የሆኑ ሰዎች የተሳካላቸው መስለው የሚታዩ ከመሆኑም በላይ የሚፈልጉትን ሁሉ በእጃቸው ያስገባሉ። ታዲያ የዋሆች ምን የሚወርሱት ነገር ይተርፍላቸዋል? ከዚህም በላይ ምድር ክፉኛ እየተበከለች ሲሆን ስግብግቦችና ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ምድርን እየቦጠቦጧት ነው። ታዲያ ምድር በውርስነት ብትሰጥ ምን ትረባለች? ለእነዚህና ለሌሎች አንገብጋቢ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ርዕስ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
-
-
‘የዋሆች ምድርን ሊወርሱ’ የሚችሉት እንዴት ነው?መጠበቂያ ግንብ—2004 | ጥቅምት 1
-
-
‘የዋሆች ምድርን ሊወርሱ’ የሚችሉት እንዴት ነው?
“ኢየሱስ ‘የዋሆች ምድርን ይወርሳሉ’ በማለት የሰጠውን አስደሳች ተስፋ ታውቅ ይሆናል። ሆኖም ሰዎች እርስ በርስ የሚደራረጉትንና በምድር ላይ እያደረሱ ያሉትን ጉዳት ስትመለከት የዋሆች ሊወርሱት የሚችሉት ነገር የሚያገኙ ይመስልሃል?”—ማቴዎስ 5:5፤ መዝሙር 37:11
ሚሪያም የተባለች የይሖዋ ምሥክር ይህን ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ለመክፈት ተጠቅማበት ነበር። ታነጋግረው የነበረው ሰው ‘ኢየሱስ ምድርን ትወርሳላችሁ ብሎ ቃል ከገባ ምድር ውርስ ለመባል የሚያስችል ብቃት ሊኖራት ይገባል፤ አትጠፋም ወይም ለመኖሪያነት የማታገለግል ፍርስራሽ አትሆንም ማለት ነው’ የሚል መልስ ሰጣት።
በእርግጥ ይህ ሰው የሰጠው ሐሳብ ጥሩ ነው። ነገር ግን እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርግ ምክንያት አለ? እንዴታ! መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ቃል እንደሚፈጸም እንድናምን የሚያደርጉ ጠንካራ ማስረጃዎችን ይዞልናል። የዚህ ተስፋ ፍጻሜ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ካለው ዓላማ ጋር የተያያዘ ነው። አምላክ ደግሞ ዓላማው ግቡን እንዲመታ እንደሚያደርግ አረጋግጦልናል። (ኢሳይያስ 55:11) ይሁንና አምላክ የሰው ልጆችን በተመለከተ የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምን ነበር? ይህስ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው?
አምላክ ለምድር ያለው ዘላለማዊ ዓላማ
ይሖዋ አምላክ ምድርን የፈጠረው ለአንድ ልዩ ዓላማ ነው። “ሰማያትን የፈጠረ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እኔ፣ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።’” (ኢሳይያስ 45:18) ስለዚህ ምድር የተፈጠረችው ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ነበር። ከዚህም በላይ አምላክ ይህ ዓላማው ለዘላለም እንዲቀጥል ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናሃት” ይላል።—መዝሙር 104:5፤ 119:90
በተጨማሪም አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በሰጣቸው ሥራ ላይ ተንጸባርቋል። ይሖዋ ለአዳምና ለሔዋን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) አምላክ ለአዳምና ለሔዋን በአደራ የሰጣቸው ምድር ለእነርሱም ሆነ ለዘሮቻቸው ዘላለማዊ መኖሪያ እንድትሆን አቅዶ ነበር። ይህ ከሆነ በርካታ መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ መዝሙራዊው “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” በማለት ተናግሯል።—መዝሙር 115:16
ይህ ድንቅ ተስፋ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አዳምና ሔዋንም ሆኑ ዘሮቻቸው ፈጣሪና ሕይወት ሰጪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሉዓላዊ ገዥያቸው መሆኑን መቀበልና ለእርሱ በፈቃደኝነት መታዘዝ አለባቸው። ይሖዋ ለአዳም “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” የሚል ትእዛዝ በመስጠት ይህን ማድረግ እንደሚኖርበት በግልጽ አስታውቆታል። (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳምና ሔዋን በዔድን ገነት ውስጥ ለዘለቄታው ለመኖር ይህን ቀላልና ግልጽ ትእዛዝ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ታዛዥ መሆናቸው ሰማያዊ አባታቸው ላደረገላቸው ነገሮች ሁሉ ያላቸውን አመስጋኝነት ያሳያል።
አዳምና ሔዋን ትእዛዙን ሆን ብለው መጣሳቸው፣ ያላቸውን ነገር ሁሉ ለሰጣቸው አምላክ ጀርባቸውን እንደሰጡ በግልጽ ያሳያል። (ዘፍጥረት 3:6) በዚህም ምክንያት እነርሱም ሆኑ ዘሮቻቸው መኖሪያቸው የነበረችውን ውብ ገነት አጡ። (ሮሜ 5:12) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት አለመታዘዝ አምላክ ምድርን የፈጠረበትን ዓላማ አጨናግፎት ይሆን?
አምላክ አልተለወጠም
አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ በኩል “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሎ ተናግሯል። (ሚልክያስ 3:6) ኤል ፊዮን የተባሉ ፈረንሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው መግለጫ ከመለኮታዊ ተስፋ ፍጻሜ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ይሖዋ ዓመጸኛ ሕዝቦቹን ድምጥማጣቸውን ማጥፋት ይችል ነበር፤ ነገር ግን ቃሉን የማያጥፍ በመሆኑ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ቀደም ሲል የሰጠውን ተስፋ ይጠብቃል።” አምላክ ለግለሰብ፣ ለአንድ ብሔር ወይም ለመላው የሰው ዘር የገባውን ቃል አይረሳም፤ ከዚህ ይልቅ ባቀደው ጊዜ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደርጋል። “ኪዳኑን ለዘላለም፣ ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺህ ትውልድ ያስታውሳል።”—መዝሙር 105:8
ታዲያ ይሖዋ ምድርን በተመለከተ ያወጣው የመጀመሪያ ዓላማ እንዳልተለወጠ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ታዛዥ የሰው ልጆች ምድርን እንደሚወርሱ የሚገልጸው መለኮታዊ ዓላማ፣ በመንፈሱ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት መጠቀሱ እቅዱ እንዳልተለወጠ ዋስትና ይሰጠናል። (መዝሙር 25:13፤ 37:9, 22, 29, 34) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም” በማለት ይሖዋ የባረካቸው ሰዎች ከስጋት ነፃ ሆነው እንደሚኖሩ በምሳሌያዊ ሁኔታ ይገልጻል። (ሚክያስ 4:4፤ ሕዝቅኤል 34:28) ይሖዋ የመረጣቸው “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።” እነዚህ ሰዎች ከዱር አራዊት ጋር እንኳ ሳይቀር በሰላም ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 11:6-9፤ 65:21, 25
ይህ ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያሳይ ናሙና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ እናገኛለን። የእስራኤል ብሔር በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን በሰላምና በብልጽግና ይኖር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ዘመን ስለነበረው ሁኔታ እንዲህ ይላል፦ “በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ።” (1 ነገሥት 4:25) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “ከሰሎሞን የሚበልጥ” መሆኑን የሚናገር ሲሆን መዝሙራዊው የእርሱን የግዛት ዘመን በሚመለከት “በዘመኑ ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም ሰላም ይበዛል” የሚል ትንቢት ተናግሯል። በዚያን ጊዜ ‘በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዛል።’—ሉቃስ 11:31፤ መዝሙር 72:7, 16
ቃሉን የማያጥፈው ይሖዋ አምላክ እሰጣችኋለሁ ያለንን ውርስ የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ይህ ውርስ ቀድሞ የነበረውን ውበት መልሶ እንዲያገኝ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 21:4 ላይ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው [ከሰዎች] ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና” በማለት አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ ምን እንደሚያደርግ ይገልጽልናል። በእርግጥም ይሖዋ ገነት የምትሆን ምድር ያወርሰናል።—ሉቃስ 23:43
ቃል የተገባልንን ውርስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
ምድርን ገነት የማድረጉ ሥራ ከሰማይ ሆኖ በሚገዛውና በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት አማካኝነት ይከናወናል። (ማቴዎስ 6:9, 10) በመጀመሪያ ይህ መንግሥት ‘ምድርን ያጠፏትን’ ያጠፋል። (ራእይ 11:18፤ ዳንኤል 2:44) ከዚያም “የሰላም ልዑል” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደርጋል። (ኢሳይያስ 9:6, 7) በዚያ መንግሥት አማካኝነት፣ ትንሣኤ የሚያገኙትን ሙታን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምድርን የመውረስ አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15
ይህን የመሰለ አስደሳች ውርስ የሚያገኘው ማን ይሆን? ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” እንዳለ ልብ በል። (ማቴዎስ 5:5) የዋህ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? አብዛኛውን ጊዜ መዝገበ ቃላት ይህን ቃል ገር፣ ቅን፣ ታዛዥ፣ ረጋ ያለ፣ አልፎ ተርፎም አይናፋር ሲሉ ይተረጉሙታል። ይሁን እንጂ የዋህ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም አለው። ዊሊያም ባርክሌይ በኒው ቴስታመንት ዎርድቡክ ላይ እንደገለጹት ቃሉ “ገርነት የሚል ሐሳብ” የሚያስተላልፍ ሲሆን “ከገርነት በስተጀርባ ደግሞ የብረትን ያህል ጥንካሬ አለ።” እንዲሁም አንድ ሰው ቅር ሳይለውና አጸፋ የመመለስ ሐሳብ ሳይኖረው ጉዳትን መቋቋም የሚችልበት ጽናት እንዲኖረው የሚያስችል መንፈሰ ጠንካራነትን ያመለክታል፤ እንዲህ ያለው ባሕርይ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና በመመሥረት የሚገኝ ሲሆን ዝምድናውም የብርታት ምንጭ ይሆንለታል።—ኢሳይያስ 12:2፤ ፊልጵስዩስ 4:13
የዋህ የሆነ ሰው ይሖዋ ያወጣውን የአቋም ደረጃ በትሕትና ተቀብሎ በሁሉም የሕይወቱ ዘርፍ ይሠራበታል እንጂ በራሱ አመለካከት ወይም በሌሎች ሰዎች አስተሳሰብ አይመራም። እንዲሁም ከይሖዋ ለመማር ፈቃደኛ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[ይሖዋ] ገሮችን በፍርድ ይመራል፣ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል።”—መዝሙር 25:9 የ1954 ትርጉም፤ ምሳሌ 3:5, 6
አንተስ ምድርን ከሚወርሱት “የዋሆች” መካከል ትገኝ ይሆን? ቃሉን በትጋት በማጥናት ይሖዋንና ፈቃዱን ካወቅህ እንዲሁም የተማርከውን በሥራ ካዋልክ ገነት የሆነች ምድር ለመውረስና በእርሷም ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ማድረግ ትችላለህ።—ዮሐንስ 17:3
-