“ቤተ መቅደሱ” እና “አለቃው” በዛሬው ጊዜ
“በሚገቡበት ጊዜ አለቃው በመካከላቸው ይግባ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ።”—ሕዝቅኤል 46:10
1, 2. ሕዝቅኤል የተመለከተውን የቤተ መቅደስ ራእይ ትርጉም ለመረዳት የሚያስችለን የትኛው ቁልፍ የሆነ እውነት ነው?
ጥንት የነበሩት አንዳንድ የአይሁድ ረቢዎች የሕዝቅኤል መጽሐፍ አይስባቸውም ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ከቅዱሳን ጽሑፎች ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት ቃጥተው እንደነበር ታልሙድ ይናገራል። በተለይ የቤተ መቅደሱ ራእይ ይከብዳቸው ስለነበረ ሰው ሊገባው የማይችል ራእይ ነው እስከማለት ደርሰዋል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንም ቢሆኑ በሕዝቅኤል የቤተ መቅደስ ራእይ ግራ መጋባታቸው አልቀረም። እኛስ?
2 ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ ከተቋቋመ ወዲህ ይሖዋ ሕዝቦቹ ብዙ መንፈሳዊ እውቀት እንዲያገኙ አድርጓል። ይህም መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን ዝግጅት እንደሚያመለክት ማስተዋልን ይጨምራል።a ይህ ቁልፍ የሆነ እውነት ሕዝቅኤል ከተመለከተው የቤተ መቅደስ ራእይ አብዛኛውን እንድንረዳ ያስችለናል። የዚህን ራእይ አራት ክፍሎች፣ ማለትም ቤተ መቅደሱን፣ ክህነቱን፣ አለቃውንና ምድሪቱን በይበልጥ ቀረብ ብለን እንመርምር። እነዚህ ነገሮች በዛሬው ጊዜ ምን ትርጉም አላቸው?
ቤተ መቅደሱና አንተ
3. ረጅም ከፍታ ካለው ጣሪያና በቤተ መቅደሱ መግቢያ ግድግዳዎች ላይ ከተቀረጹት ምስሎች ምን እንማራለን?
3 ራሳችንን ይህን ራእያዊ ቤተ መቅደስ በመጎብኘት ላይ እንዳለን አድርገን እናስብ። ሰባት ደረጃዎች ከወጣን በኋላ በጣም ግዙፍ ከሆኑት በሮች ወደ አንዱ እንሄዳለን። እዚህ በር ላይ እንደቆምን ከፊታችን በምንመለከተው ነገር ተደንቀን እንቆማለን። የጣሪያው ከፍታ ከ30 ሜትር ይበልጣል! ይህ ደግሞ ወደ ይሖዋ የአምልኮ ዝግጅት ለመግባት የሚያስፈልገው ብቃት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ያስታውሰናል። በመስኮቶቹ በኩል የሚገባው የብርሃን ጨረር በግድግዳው ላይ የተቀረጹትን የዘንባባ ዛፎች ምስል አድምቆ ያሳየናል። የዘንባባ ዛፎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ንጽሕናን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (መዝሙር 92:12፤ ሕዝቅኤል 40:14, 16, 22) ወደዚህ ቅዱስ ሥፍራ መግባት የሚችሉት ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን የሚጠብቁ ብቻ ናቸው። እኛም አምልኮታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር እንፈልጋለን።—መዝሙር 11:7
4. ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገቡ የተከለከሉት እነማን ናቸው? ይህስ እኛን ምን ያስተምረናል?
4 በበሮቹ ግራና ቀኝ ሦስት የዘበኛ ቤቶች አሉ። ዘበኞቹ ወደነዚህ ቤቶች እንድንገባ ይፈቅዱልን ይሆን? ይሖዋ ‘በልቡ ያልተገረዘ እንግዳ ሁሉ’ ሊገባ እንደማይችል ለሕዝቅኤል ነግሮታል። (ሕዝቅኤል 40:10፤ 44:9) ይህ ምን ማለት ነው? አምላክ አምላኪዎቹ እንዲሆኑ የሚቀበለው ሕጉን የሚወዱትንና በዚያ መሠረት የሚመላለሱትን ብቻ ነው። (ኤርምያስ 4:4፤ ሮሜ 2:29) እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ተቀብሎ ወደ መንፈሳዊ ድንኳኑ ማለትም ወደ አምልኮ ቤቱ ያስገባል። (መዝሙር 15:1-5) ንጹሕ አምልኮ ዳግመኛ ከተቋቋመበት ከ1919 ወዲህ የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት የይሖዋን የሥነ ምግባር ሕግጋት በይበልጥ ለመረዳትና ለመጠበቅ ችሏል። ሆን ብለው ሕጉን የሚጥሱ ሰዎች ከሕዝቦቹ ጋር እንዲተባበሩ አይፈቀድላቸውም። ዛሬ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ንሥሐ ያልገቡ በደለኞችን የማስወገድ እርምጃ አምልኮታችን ንጹሕና እድፍ የሌለበት እንዲሆን አስችሏል።—1 ቆሮንቶስ 5:13
5. (ሀ) በሕዝቅኤል ራእይና በራእይ 7:9-15 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው የዮሐንስ ራእይ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ? (ለ) በሕዝቅኤል ራእይ ላይ በውጨኛው አደባባይ ሲያመልኩ የታዩት 12ቱ ነገዶች እነማንን ያመለክታሉ?
5 የመተላለፊያው በር ሕዝቡ ይሖዋን ወደሚያመልክበትና ወደሚያወድስበት ውጨኛ አደባባይ ያስገባል። ይህም ይሖዋን ‘ሌሊትና ቀን በመቅደሱ’ ስለሚያመልከው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚገልጸውን የሐዋርያው ዮሐንስ ራእይ ያስታውሰናል። በሁለቱም ራእዮች ውስጥ የዘንባባ ዝንጣፊዎች ታይተዋል። በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ የመግቢያውን ግድግዳዎች ለማስጌጫነት አገልግለዋል። በዮሐንስ ራእይ ውስጥ አምላኪዎቹ ይሖዋን ለማወደስና የኢየሱስን ንግሥና ለመቀበል በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ በእጆቻቸው የዘንባባ ዝንጣፊዎች ይዘዋል። (ራእይ 7:9-15) በሕዝቅኤል ራእይ አገባብ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች “ሌሎች በጎች”ን ያመለክታሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ከሉቃስ 22:28-30 ጋር አወዳድር።) መንግሥቱን በማወጅ ይሖዋን ለማወደስ በመቻላቸው ደስ ከሚሰኙት ሰዎች መካከል ናችሁ?
6. በውጨኛው አደባባይ የሚገኙት ዕቃ ቤቶች ዓላማ ምን ነበር? ይህስ ሌሎች በጎችን የትኛውን መብት ያስታውሳቸዋል?
6 የውጨኛውን አደባባይ በምንጎበኝበት ጊዜ ሕዝቡ በፈቃደኝነት ከሚያቀርቡት ቁርባን የሚካፈሉባቸውን 30 ዕቃ ቤቶች እንመለከታለን። (ሕዝቅኤል 40:17) በዛሬው ጊዜ የሌሎች በጎች አባላት የእንስሳ መሥዋዕት ባያቀርቡም ወደ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ባዶ እጃቸውን አይመጡም። (ከዘጸአት 23:15 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ [በክርስቶስ] እናቅርብለት። ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።” (ዕብራውያን 13:15, 16፤ ሆሴዕ 14:2) እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለይሖዋ ማቅረብ መቻል ትልቅ መብት ነው።—ምሳሌ 3:9, 27
7. የቤተ መቅደሱ መለካት ስለ ምን ነገር ማረጋገጫ ይሰጠናል?
7 ሕዝቅኤል አንድ መልአክ ይህን ራእያዊ ቤተ መቅደስ ሲለካ ይመለከታል። (ሕዝቅኤል 40:3) በተመሳሳይም ሐዋርያው ዮሐንስ “የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ” ተብሎ ነበር። (ራእይ 11:1) ይህ መለካት ምን ትርጉም አለው? በሁለቱም ጊዜያት የቤተ መቅደሱ መለካት ይሖዋ ንጹሕ አምልኮን አስመልክቶ ያለውን ዓላማ ከመፈጸም የሚገታው ምንም ነገር እንደሌለ ዋስትና መሆኑን ያሳያል። ዛሬም በተመሳሳይ ምንም ነገር፣ አስፈሪ የሆነ የመንግሥታት ተቃውሞ እንኳን ቢሆን፣ ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ እንዳይቋቋም ሊያግድ እንደማይችል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
8. ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚገቡት እነማን ናቸው? እነዚህ በሮችስ ምን ነገር ያስታውሱናል?
8 በውጨኛው አደባባይ በምናልፍበት ጊዜ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገቡ ሦስት በሮች እንዳሉ እንመለከታለን። የውስጠኞቹ በሮች ከውጨኞቹ በሮች ጋር ትይዩ ከመሆናቸውም በላይ በመጠናቸውም እኩል ናቸው። (ሕዝቅኤል 40:6, 20, 23, 24, 27) ወደ እነዚህ በሮች ሊገቡ የሚችሉት ካህናት ብቻ ናቸው። የውስጠኞቹ በሮች፣ ቅቡዓኑ መለኮታዊ መስፈርቶችንና ሕጎችን የግድ ማሟላት እንደሚኖርባቸው ያሳስቡናል። ሆኖም ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚመሩት በእነዚሁ መስፈርቶችና ሕጎች ነው። ይሁን እንጂ የካህናቱ ሥራ ምንድን ነው? ዛሬስ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
የታመነ ክህነት
9, 10. በሕዝቅኤል ራእይ በካህናት ክፍል የተወከሉት “የንጉሥ ካህናት” መንፈሳዊ መመሪያ ያቀረቡት እንዴት ነበር?
9 በቅድመ ክርስትና ዘመን ካህናት በቤተ መቅደሱ የሚያከናውኗቸው ብዙ ተግባሮች ነበሩ። ለመሥዋዕት የሚቀርቡትን ከብቶች ማረድ፣ መሠውያው ላይ ማኖርና ሕዝቡንና መሰል ካህናቱን ማገልገል ጉልበት የሚጠይቅ አድካሚ ሥራ ነበር። ይሁን እንጂ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ሥራም ነበራቸው። ይሖዋ ካህናቱን እንደሚከተለው ሲል አዟል:- “በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፣ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው።”—ሕዝቅኤል 44:23፤ ሚልክያስ 2:7
10 “የንጉሥ ካህናት” የሆኑት ቅቡዓን እንደ አንድ አካል በመሆን ለእውነተኛው አምልኮ ጠንክረው መሥራታቸውንና ያበረከቱትን የትህትና አገልግሎት ታደንቃላችሁ? (1 ጴጥሮስ 2:9) እንደ ጥንቱ ሌዋዊ ክህነት መንፈሳዊ መመሪያ በመስጠት ረገድ ግንባር ቀደሞች በመሆን ሰዎች በአምላክ ዓይን ንጹሕ የሆነውንና ያልሆነውን ነገር ለይተው እንዲያውቁ አስችለዋል። (ማቴዎስ 24:45) እነዚህ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲሁም ከጉባኤና ትላልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚገኙት መመሪያዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ አስችለዋል።—2 ቆሮንቶስ 5:20
11. (ሀ) የሕዝቅኤል ራእይ ካህናቱ ንጹህ መሆን እንደሚያስፈልጋቸው ያጎላው እንዴት ነበር? (ለ) በመጨረሻዎቹ ቀናት ቅቡዓኑ በመንፈሳዊ መንገድ እንዲነጹ የተደረጉት እንዴት ነው?
11 ይሁን እንጂ ካህናቱ ግዴታቸው ሌሎች ንጹሕ እንዲሆኑ በማስተማር ብቻ አያቆምም። ራሳቸውም ንጹሕ መሆን ነበረባቸው። በመሆኑም ሕዝቅኤል የእስራኤል ክህነት ሲጸዳና ሲጣራ ተመልክቷል። (ሕዝቅኤል 44:10-16) በተመሳሳይ ይሖዋ በ1918 ወደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ‘እንደ አጣቢ’ ሆኖ በመምጣት ቅቡዓኑን የካህናት ክፍል መርምሯል። (ሚልክያስ 3:1-5) ቀድሞ ይፈጽሙ ከነበረው የጣዖት አምልኮ ድርጊት ንስሐ ገብተው በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆነው የተገኙት በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በነበራቸው የአገልግሎት መብት እንዲቀጥሉ ተፈቅዶላቸዋል። ቢሆንም ግለሰብ ቅቡዓን፣ እንደ ማንኛውም ግለሰብ በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባር ሊቆሽሹ ይችላሉ። (ሕዝቅኤል 44:22, 25-27) ‘የዓለም እድፍ እንዳይነካቸው’ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ያዕቆብ 1:27፤ ከማርቆስ 7:20-23 ጋር አወዳድር።
12. የቅቡዓኑን ሥራ ማድነቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
12 ሁላችንም ‘ቅቡዓን ባሳለፏቸው የበርካታ ዓመታት የታማኝነት አገልግሎት ያሳዩትን መልካም ምሳሌነት አደንቃለሁን? እምነታቸውን እመስላለሁ?’ ብለን ብንጠይቅ ጥሩ ይሆናል። የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ቅቡዓን ሁልጊዜ ከእነርሱ ጋር በዚህች ምድር እንደማይኖሩ ማስታወሳቸው ጥሩ ነው። ይሖዋ በሕዝቅኤል ራእይ ውስጥ ስለተገለጹት ካህናት “በእስራኤልም ዘንድ ግዛት [የግዛት መሬት] አትስጡአቸው፤ እኔ ግዛታቸው ነኝ” ሲል ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 44:28) በተመሳሳይም ቅቡዓኑ በምድር ላይ ምንም ዘላለማዊ ቦታ የላቸውም። ያላቸው ውርሻ ሰማያዊ ሲሆን በዚህች ምድር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች እነርሱን ማበረታታቱንና መደገፉን እንደ ውድ መብት ይቆጥሩታል።—ማቴዎስ 25:34-40፤ 1 ጴጥሮስ 1:3, 4
አለቃው ማን ነው?
13, 14. (ሀ) አለቃው ከሌሎች በጎች ክፍል መሆን ያለበት ለምንድን ነው? (ለ) አለቃው የሚያመለክተው እነማንን ነው?
13 አሁን አንድ ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ይነሳል። ታዲያ አለቃው የሚያመለክተው ማንን ነው? እንደ ግለሰብም፣ እንደ ቡድንም ሆኖ ስለተጠቀሰ የሰዎችን ቡድን ያመለክታል ብለን ለመገመት እንችላለን። (ሕዝቅኤል 44:3፤ 45:8, 9) ግን የትኛውን የሰዎች ቡድን? ቅቡዓንን እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በራእዩ ውስጥ ከካህናቱ ጋር የሚሠራ ቢሆንም ከካህናቱ አንዱ አይደለም። ከካህናቱ በተለየ ሁኔታ በምድሩ ላይ ርስት ስለተሰጠው የወደፊት መኖሪያው ሰማይ ሳይሆን ምድር ነው። (ሕዝቅኤል 48:21) በተጨማሪም ሕዝቅኤል 46:10 እንዲህ ይላል:- “[ካህናት ያልሆኑት ነገዶች ወደ ውጨኛው የቤተ መቅደስ አደባባይ] በሚገቡበት ጊዜ አለቃው በመካከላቸው ይግባ፣ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ።” ከሕዝቡ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ እየገባና እየወጣ በውጨኛው አደባባይ ያመልካል እንጂ ወደ ውስጠኛው አደባባይ አይገባም። እነዚህ ሁኔታዎች አለቃው የሌሎች በጎች ክፍል ከሆኑት ከእጅግ ብዙ ሰዎች መካከል መሆን እንደሚገባው በማያሻማ ሁኔታ ያረጋግጣሉ።
14 አለቃው በአምላክ ሕዝቦች መካከል የተወሰኑ ኃላፊነቶች እንዳሉት ግልጽ ነው። በውጨኛው አደባባይ በምሥራቅ በር በሚገኘው ደጀ ሰላም ይቀመጣል። (ሕዝቅኤል 44:2, 3) ይህ መሆኑ በከተማ በሮች ተቀምጠው ዳኝነት ይሰጡ የነበሩት የእስራኤል ሽማግሌዎች ከነበራቸው ኃላፊነት ጋር ተመሳሳይ የሆነ የበላይ ተመልካችነት ማዕረግ እንዳለው ያመለክታል። (ሩት 4:1-12፤ ምሳሌ 22:22) ዛሬ በሌሎች በጎች መካከል የበላይ ተመልካችነት ቦታ ያላቸው እነማን ናቸው? ምድራዊ ተስፋ ያላቸው በመንፈስ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ናቸው። (ሥራ 20:28) ስለዚህ የአለቃው ክፍል በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለሚያከናውነው የአስተዳደር ሥራ ሥልጠናና ልምምድ በማግኘት ላይ ነው።
15. (ሀ) የሕዝቅኤል ራእይ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት በሆኑት ሽማግሌዎችና በቅቡዓኑ ክህነታዊ ክፍል መካከል ባለው ዝምድና ላይ ብርሃን የሚፈነጥቀው እንዴት ነው? (ለ) ቅቡዓን ሽማግሌዎች በአምላክ ምድራዊ ድርጅት ውስጥ ምን ዓይነት አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል?
15 ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በቅቡዓኑ የካህናት ክፍልና በእነዚህ በአሁኑ ጊዜ በበላይ ተመልካችነት በሚያገለግሉት የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? የሕዝቅኤል ራእይ እንደሚያመለክተው ቅቡዓኑ መንፈሳዊ አመራር ሲሰጡ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑት ሽማግሌዎች ከእነርሱ በታች ሆነው የድጋፍ ሰጪነት ተግባር ይፈጽማሉ። እንዴት? በራእዩ ውስጥ የታዩት ካህናት ሕዝቡን ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች የማስተማር ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አስታውሱ። በተጨማሪም ዳኞች በመሆን ሕግ ነክ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ ተነግሯቸዋል። በተጨማሪም ሌዋውያኑ በቤተ መቅደሱ በሮች ‘በረኞች’ የመሆን ሥራ ተሰጥቷቸዋል። (ሕዝቅኤል 44:11, 23, 24) አለቃው ካህናቱ ለሚሰጡት አመራርና አገልግሎት በትሕትና መታዘዝ እንደሚገባው ግልጽ ነው። ስለዚህ በዘመናችንም ቅቡዓን በንጹሕ አምልኮ ጉዳዮች አመራር ሰጪ መሆናቸው ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት የተመረጡት ከቅቡዓን መካከል ነው። እነዚህ ታማኝ ቅቡዓን ሽማግሌዎች ከዕለት ወደ ዕለት እያደገ የመጣውን የአለቃው ክፍል ላለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል። የዚህን ክፍል አባላት በመጪው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚጠብቃቸው ሙሉ ኃላፊነት አዘጋጅተዋቸዋል።
16. በኢሳይያስ 32:1, 2 መሠረት ሁሉም ሽማግሌዎች መመላለስ ያለባቸው እንዴት ነው?
16 ይሁን እንጂ ወደፊት የአለቃው ክፍል በመሆን ሰፊ ኃላፊነት የሚሰጣቸው እነዚህ አባላት ምን ዓይነት የበላይ ተመልካቾች ናቸው? በኢሳይያስ 32:1, 2 ላይ የሚገኘው ትንቢት እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ ንጉሥ በጽድቅ ይነግሣል፣ መሳፍንትም በፍርድ ይገዛሉ። ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከአውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።” ቅቡዓንም ሆኑ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንጋውን እንደ ስደትና ተስፋ መቁረጥ ካሉት ‘አውሎ ነፋሳት’ በመጠበቅ የወደፊቶቹ መሳፍንት ለመሆን የሚበቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ስለሚኖርባቸው ይህ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ነው።
17. ክርስቲያን እረኞች ራሳቸውን መመልከት ያለባቸው እንዴት ነው? መንጋውስ እንዴት ሊመለከታቸው ይገባል?
17 በዕብራይስጥ አንድ ዓይነት ትርጉም ያላቸው ‘መስፍን’ እና “አለቃ” የሚሉት ቃላት ሰዎችን ከፍ ለማድረግ የተሰጡ የማዕረግ ስሞች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ሰዎች ለአምላክ በጎች በሚሰጡት እንክብካቤ መሸከም የሚኖርባቸውን ኃላፊነት የሚያመለክቱ ናቸው። ይሖዋ “የእስራኤል አለቆች ሆይ፣ ይብቃችሁ፤ ግፍንና ብዝበዛን አስወግዱ፣ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ” ሲል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ሕዝቅኤል 45:9) የዛሬዎቹ ሽማግሌዎች በሙሉ ይህንን ምክር ልብ ቢሉ ጥሩ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) መንጋው በበኩሉ እነዚህን እረኞች ‘የወንዶች ስጦታ’ አድርጎ የሰጠው ኢየሱስ እንደሆነ ይገነዘባል። (ኤፌሶን 4:8) የሚፈለጉባቸው ብቃቶች በመንፈስ በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ ተዘርዝረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9) ስለዚህ ክርስቲያኖች ሽማግሌዎች የሚሰጡትን አመራር ይከተላሉ።—ዕብራውያን 13:7
18. ወደፊት የአለቃው ክፍል አባላት የሚሆኑት በአሁኑ ጊዜ ያሏቸው አንዳንድ ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው? ወደፊትስ ምን ኃላፊነቶች ይኖሯቸዋል?
18 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት አንዳንድ አለቆች ከሌሎች የበለጠ ሥልጣን ነበራቸው። ዛሬም የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት የሆኑ ሽማግሌዎች የተለያየ ኃላፊነት አላቸው። አንዳንዶች በአንድ ጉባኤ ውስጥ ብቻ የሚያገለግሉ ሲሆን ሌሎች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በመሆን በርካታ ጉባኤዎችን ያገለግላሉ፤ ሌሎች ደግሞ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት በመሆን አንድ ሙሉ አገር ያገለግላሉ። የአስተዳደር ክፍልን የተለያዩ ኮሚቴዎች በቀጥታ የሚረዱም አሉ። ኢየሱስ በአዲሱ ዓለም ውስጥ በምድር ላይ የሚኖሩትን የይሖዋ አምላኪዎች የሚመሩ “መሳፍንትን” በመላው ምድር ላይ ይሾማል። (መዝሙር 45:16 NW) ኢየሱስ ብዙዎቹን የሚመርጠው ከዛሬዎቹ ታማኝ ሽማግሌዎች መካከል እንደሚሆን አያጠራጥርም። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ እንኳን ብቃታቸውን በማስመስከር ላይ በመሆናቸው የአለቃውን ክፍል ሚና በሚገልጥበት በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለብዙዎቹ አሁን ካላቸው የበለጡ መብቶች ሊሰጣቸው ይፈቅዳል።
በዛሬው ጊዜ ያለው የአምላክ ሕዝቦች ምድር
19. በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የታየው ምድር ምን ያመለክታል?
19 በተጨማሪም የሕዝቅኤል ራእይ ዳግመኛ የተቋቋመችውን የእስራኤል ምድር ሁኔታ ይገልጻል። ይህ የራእዩ ክፍል ምን ያመለክታል? ሌሎች የተሐድሶ ትንቢቶች የእስራኤል ምድር እንደ ኤደን ገነት እንደምትሆን ተንብየዋል። (ሕዝቅኤል 36:34, 35) ዛሬም ቢሆን የምንኖረው ተመልሶ በተቋቋመ “ምድር” ሲሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ኤደናዊ ምድር ነው ለማለት ይቻላል። ስለ መንፈሳዊ ገነታችን ስንናገር ይህን መጥቀሳችን ነው። መጠበቂያ ግንብ ይህ ‘ምድራችን’ የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ‘የእንቅስቃሴ ቀጣና’ ነው ብሏል።b አንድ የይሖዋ አገልጋይ የትም ይኑር የት የክርስቶስ ኢየሱስን ፈለግ ተከትሎ በመመላለስ እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ጥረት እስካደረገ ድረስ በዚህ ዳግመኛ በተቋቋመ ምድር ውስጥ ነው።—1 ጴጥሮስ 2:21
20. በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ከተጠቀሰው ‘የተቀደሰ መባ’ ምን መሠረታዊ ሥርዓት ልንማር እንችላለን? ይህንን መሠረታዊ ሥርዓትስ ተግባራዊ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
20 ‘የተቀደሰ መባ’ የተባለው የምድሩ ክፍልስ? ይህ ክፍል ሕዝቡ ክህነቱንና ከተማይቱን ለመደገፍ የሚያዋጡት ነበር። “የአገሩም ሕዝብ ሁሉ” በተመሳሳይ ለአለቃው የሚሆነውን መሬት አዋጥተው ይሰጣሉ። ዛሬ ይህ ሁሉ ምን ትርጉም አለው? የአምላክ ሕዝቦች ደመወዝ የሚከፈላቸውን የቀሳውስት ክፍል ተሸክመው መኖር አለባቸው ማለት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። (2 ተሰሎንቄ 3:8) ከዚህ ይልቅ ለሽማግሌዎቹ የሚሰጠው ድጋፍ በአብዛኛው መንፈሳዊ ነው። በወቅቱ በመከናወን ላይ በሚገኘው ሥራ መርዳትን፣ የትብብርና የታዛዥነት መንፈስ ማሳየትን ይጨምራል። ዛሬም ይህ መዋጮ የሚሰጠው በሕዝቅኤል ዘመን እንደነበረው ሁሉ ለሰው ሳይሆን “ለይሖዋ” [NW] ነው።—ሕዝቅኤል 45:1, 7, 16
21. በሕዝቅኤል ራእይ ላይ ከታየው የመሬት ክፍፍል ምን መማር እንችላለን?
21 በዚህ ተመልሶ የተቋቋመ ምድር ውስጥ ምድብ ቦታ የሚኖራቸው አለቃውና ካህናቱ ብቻ አይደሉም። የመሬቱ መከፋፈል እንደሚያመለክተው 12ቱ ነገዶች በሙሉ የተረጋገጠ ርስት ይኖራቸዋል። (ሕዝቅኤል 47:13, 22, 23) ስለዚህ የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት በዛሬው ጊዜ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ ካገኙት ቦታ በተጨማሪ በአምላክ መንግሥት ምድራዊ ግዛት ውስጥ የራሳቸው የሆነ ርስት ይሰጣቸዋል።
22. (ሀ) በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የታየው ከተማ ምን ያመለክታል? (ለ) ከተማው በሁሉም ጎኖች በሮች ያሉት መሆኑ ምን ያስተምረናል?
22 በመጨረሻ በራእዩ ውስጥ የታየው ከተማ ምን ያመለክታል? ‘ቅዱስ ባልሆነ ሥፍራ’ መካከል የሚገኝ በመሆኑ ሰማያዊ ከተማ አይደለም። (ሕዝቅኤል 48:15-17 NW) ስለዚህ ምድራዊ መሆን አለበት። ከተማ ምንድን ነው? ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው የተደራጀና የተዋቀረ ነገር የመመስረታቸውን ሐሳብ አያስተላልፍም? አዎን ያስተላልፋል። ስለዚህ ከተማው ጻድቅ የሆነው ምድራዊ ማኅበረሰብ የሚጠቀምበትን ምድራዊ አስተዳደር የሚያመለክት ይመስላል። ተግባሩን በተሟላ ሁኔታ የሚፈጽመው በመጪው “አዲስ ምድር” ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13) በከተማው በሁሉም ጎኖች ለእያንዳንዱ ነገድ የተመደቡ በሮች መኖራቸው ግልጽነትን ያመለክታል። ዛሬ የአምላክ ሕዝብ በአንድ ዓይነት ድብቅና ምስጢራዊ በሆነ አመራር ሥር አይደሉም። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚቀረቡ ናቸው፤ የሚመሩባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች በሁሉም ዘንድ የታወቁ ናቸው። የከተማይቱ መተዳደሪያ የሆነውን መሬት የሚያለሙት ከሁሉም ነገዶች የተውጣጡ ሰዎች መሆናቸው ሌሎች በጎች በዚህ አስተዳደር የሚመራውን ዓለም አቀፋዊ ዝግጅት በቁሳዊ ነገሮች ሳይቀር እንደሚደግፉ ያስታውሰናል።—ሕዝቅኤል 48:19, 30-34
23. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
23 ከቤተ መቅደሱ የሚፈስሰው ወንዝስ? ይህ ወንዝ አሁንና ወደፊት ምን እንደሚያመለክት በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ሦስተኛና የመጨረሻ ርዕስ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 64 አንቀጽ 22 ተመልከት።
b መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1, 1995 ገጽ 20ን ተመልከት።
[ለክለሳ የሚሆኑ ነጥቦች]
◻ በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የታየው ቤተ መቅደስ ምን ያመለክታል?
◻ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉት ካህናት እነማንን ያመለክታሉ?
◻ የአለቃው ክፍል ምንድን ነው? አንዳንድ ኃላፊነቶቹስ ምንድን ናቸው?
◻ በሕዝቅኤል ራእይ ላይ የታየው ምድር ምንድን ነው? ለ12ቱ ነገዶች የተከፋፈለውስ በምን መንገድ ነው?
◻ ከተማው ምን ያመለክታል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )
በሕዝቅኤል ራእይ ላይ በሥዕላዊ መንገድ የተገለጸው የመሬት ክፍፍል
አሥራ ሁለቱ ነገዶች
ታላቁ ባሕር
የገሊላ ባሕር
የዮርዳኖስ ወንዝ
የጨው ባሕር
ዳን
አሴር
ንፍታሌም
ምናሴ
ኤፍሬም
ሮቤል
ይሁዳ
አለቃው
ብንያም
ስምዖን
ይሳኮር
ዛብሎን
ጋድ
[መግለጫ]
የተቀደሰ መባ መስፋፋት
ሀ. “ይሖዋ ራሱ በዚያ ይገኛል” (ይሖዋ ሻማህ)፤ ለ. የከተማው ለም መሬት
የሌዋውያን ድርሻ
የይሖዋ መቅደስ
የካህናቱ ድርሻ
ለ ሀ ለ