እርዳታ ለማግኘት የሚጮኹትን የሚታደገው ማነው?
“[አምላክ] ሆይ፤ ፍርድህን ለንጉሥ፣ . . . ዐድል፤ ችግረኛው በጮኸ ጊዜ [ይታደገዋል]።”—መዝ. 72:1, 12
1. የዳዊት ሁኔታ ስለ አምላክ ምሕረት ምን ያስተምረናል?
የጥንቷ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እንደጻፈው የሚገመተው ይህ መዝሙር እንዴት የሚያጽናና ነው! ይህን ሐሳብ ከመጻፉ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸሙ ምክንያት ከፍተኛ ጸጸት ተሰምቶት ነበር። በዚያን ጊዜ ዳዊት፣ አምላክን እንደሚከተለው በማለት ተማጽኖት ነበር፦ “እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ . . . ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው። . . . ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ።” (መዝ. 51:1-5) ይሖዋ የወረስነውን ኃጢአት ግምት ውስጥ በማስገባት በምሕረት ዓይን ይመለከተናል።
2. መዝሙር 72 ምን ፍንጭ ይሰጠናል?
2 ይሖዋ ያለንበትን አሳዛኝ ሁኔታ ይረዳል። ይሁንና በትንቢት በተነገረው መሠረት በአምላክ የተቀባው ንጉሥ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል።” (መዝ. 72:12, 13) ታዲያ እፎይታ የሚገኘው እንዴት ነው? መልሱን በመዝሙር 72 ላይ እናገኛለን። የዳዊት ልጅ የነበረውን የሰለሞንን አገዛዝ አስመልክቶ የተቀናበረው ይህ መዝሙር፣ የአምላክ ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ የሰው ልጆችን እንዴት ከመከራ እንደሚገላግላቸው የሚጠቁም ፍንጭ ይሰጠናል።
የክርስቶስን አገዛዝ የሚያሳይ ናሙና
3. ሰለሞን የጠየቀው ምን ነበር? አምላክስ ምን ሰጠው?
3 አረጋዊ የነበረው ዳዊት፣ ሰለሞንን እንዲያነግሡት ከተናገረ በኋላ በታማኝነት ሊያከናውናቸው ስለሚገቡ ነገሮች ለሰለሞን ዝርዝር መመሪያ ሰጠው። (1 ነገ. 1:32-35፤ 2:1-3) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለሰለሞን በሕልም ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምን” አለው። ሰለሞንም “መልካሙንና ክፉውን በመለየት ሕዝብህን ማስተዳደር እንዲችል ለባሪያህ አስተዋይ ልብ ስጠው” በማለት አንድ ነገር ብቻ ጠይቋል። አምላክ፣ ሰለሞን ትሕትና የተንጸባረቀበት ጥያቄ ስላቀረበ የጠየቀውን ነገር ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ሰጥቶታል።—1 ነገ. 3:5, 9-13
4. በሰለሞን ዘመን የኖረች አንዲት ገዥ ስለ ሰለሞን አገዛዝ ምን ተናግራ ነበር?
4 ይሖዋ የሰለሞንን አገዛዝ ስለባረከለት የግዛት ዘመኑ በምድር ላይ የተነሳ ማንኛውም መንግሥት ካገኘው እጅግ የላቀ ሰላምና ብልጽግና የሰፈነበት ሊሆን ችሏል። (1 ነገ. 4:25) የሰለሞን አገዛዝ ምን እንደሚመስል ለማየት ከመጡት ሰዎች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው አጃቢ ይዛ የመጣችው የሳባ ንግሥት ትገኝበታለች። ንግሥቲቱ ሰለሞንን “ባገሬ ሳለሁ የሰማሁት ትክክል ነው፤ . . . በእርግጥ ግማሹን እንኳ አልነገሩኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት በላይ ነው” ብላው ነበር። (1 ነገ. 10:1, 6, 7) ይሁንና ኢየሱስ ከሰለሞን እጅግ የሚበልጥ ጥበብ እንዳለው አሳይቷል፤ በመሆኑም “ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ” ብሎ ስለ ራሱ መናገሩ የተገባ ነው።—ማቴ. 12:42
በታላቁ ሰለሞን አገዛዝ ሥር የሚገኘው እፎይታ
5. መዝሙር 72 ስለ ምን ነገር ይገልጻል? መዝሙሩ ስለየትኛው ጊዜ የሚጠቁም ናሙና ይዟል?
5 በታላቁ ሰለሞን በኢየሱስ ክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለሚገኘው በረከት የማወቅ ግብ ይዘን እስቲ መዝሙር 72ን እንመርምር። (መዝሙር 72:1-4ን አንብብ።) ይህ መዝሙር ይሖዋ “የሰላም ልዑል” ስለሆነው ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አለቅነት’ ወይም የልዑል አገዛዝ ምን እንደሚሰማው ይገልጻል። (ኢሳ. 9:6, 7) ታላቁ ሰለሞን በአምላክ አመራር ሥር ሆኖ “ለተቸገረው ሕዝብ ይሟገታል፤ የድኾችን ልጆች ያድናል።” አገዛዙ ሰላምና ጽድቅ የሰፈነበት ይሆናል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ በመጪው የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ምን ነገር እንደሚከናወን የሚጠቁም ናሙና አሳይቷል።—ራእይ 20:4
6. በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚመጣውን በረከት ለማሳየት ሲል ኢየሱስ እንደ ናሙና የሚሆኑ ምን ነገሮችን አከናውኗል?
6 ኢየሱስ ክርስቶስ በመዝሙር 72 ፍጻሜ መሠረት ወደፊት ለሰው ልጆች ምን እንደሚያከናውን ለማሳየት ሲል የፈጸማቸውን እንደ ናሙና የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች እንመልከት። እነዚህን ታሪኮች ስንመረምር በሥቃይ ላይ ላሉ ሰዎች ባሳየው ታላቅ ርኅራኄ መደነቃችን አይቀርም። (ማቴ. 9:35, 36፤ 15:29-31) ለምሳሌ ያህል፣ በሥጋ ደዌ በሽታ ሲሠቃይ የነበረ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለምኖት ነበር። ኢየሱስም “እፈልጋለሁ፣ ንጻ” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ ተፈወሰ! (ማር. 1:40-42) በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ አንድ ልጇን በሞት ያጣችን መበለት አገኘ። ኢየሱስም ለዚች ሴት ‘በጣም ስላዘነላት’ ልጇን “ተነስ እልሃለሁ” አለው፤ ልጁም ተነሳ። እንደገና በሕይወት መኖር ጀመረ!—ሉቃስ 7:11-15
7, 8. የኢየሱስን የመፈወስ ኃይል የሚያሳዩት አንዳንድ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
7 ይሖዋ ኢየሱስ ተአምራት መፈጸም እንዲችል ኃይል ሰጥቶታል። ‘ለአሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት ከኖረች አንዲት ሴት’ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ሁኔታ ይህን ያሳያል። ‘ይህች ሴት ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ ብዙ ተሠቃይታና ያላትን ጥሪት ሁሉ ጨርሳ የነበረ ቢሆንም ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም።’ ሴትየዋም በሕዝቡ መካከል ገብታ ኢየሱስን ነካችው፤ አንድ ሰው ‘ፈሳሽ ደም እያለው’ እንዲህ ቢያደርግ ሕጉን ይተላለፋል። (ዘሌ. 15:19, 25) ኢየሱስ ከእሱ ኃይል እንደወጣ ሲያውቅ ማን እንደነካው ጠየቀ። ሴትየዋም “በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው።” ይሖዋ እንደፈወሳት ስለተገነዘበ ኢየሱስ በደግነት “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም እረፊ” አላት።—ማር. 5:25-27, 30, 33, 34
8 ኢየሱስ ከአምላክ ያገኘው የመፈወስ ኃይል የታመሙ ሰዎችን መፈወስ ብቻ ሳይሆን ተአምራቱን በተመለከቱ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ስሜት አሳድሮ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ዝነኛውን የተራራ ስብከት ከመስጠቱ በፊት ሰዎችን ሲፈውስ ብዙዎች ተገርመው ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 6:17-19) መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት መልእክተኞችን በላከ ጊዜ ሰዎቹ ኢየሱስን ‘ብዙዎችን ከሕመም፣ ከከባድ በሽታና ከክፉ መናፍስት ሲፈውስና የብዙ ዓይነ ስውራንንም ዓይን ሲያበራ’ አገኙት። ኢየሱስ ለሁለቱ ሰዎችም እንዲህ በማለት ነገራቸው፦ “ሄዳችሁ የሰማችሁትንና ያያችሁትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ዓይናቸው እየበራ ነው፣ አንካሶች እየተራመዱ ነው፣ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፣ ደንቆሮዎች እየሰሙ ነው፣ ሙታን እየተነሱ ነው፣ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።” (ሉቃስ 7:19-22) ይህ መልእክት ዮሐንስን ምን ያህል አጽናንቶት ይሆን!
9. ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ምን የሚያሳዩ ናቸው?
9 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሲሠቃዩ ለነበሩ ሰዎች ያስገኘው እፎይታ ጊዜያዊ እንደነበር የታወቀ ነው። ከሕመማቸው የፈወሳቸውም ሆነ ከሞት ያስነሳቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ሞተዋል። ያም ሆኖ ኢየሱስ ምድር ላይ እያለ የፈጸማቸው ተአምራት በመሲሐዊ አገዛዙ ሥር የሰው ልጆች የሚያገኙትን ዘላቂ እፎይታ የሚያሳዩ ናቸው።
ከፊታችን የሚጠብቀን ምድር አቀፍ ገነት!
10, 11. (ሀ) መንግሥቱ የሚያመጣቸው በረከቶች የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው? የኢየሱስ አገዛዝ ከምን ጋር ተመሳስሏል? (ለ) ከክርስቶስ ጋር በገነት የሚሆነው ማን ነው? ለዘላለም መኖር የሚችለውስ እንዴት ነው?
10 ምድር ገነት ስትሆን ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። (መዝሙር 72:5-9ን አንብብ።) እውነተኛውን አንድ አምላክ ብቻ የሚያመልኩ ሰዎች ፀሐይና ጨረቃ እስካሉ ድረስ ማለትም ከዘላለም እስከ ዘላለም በገነት ውስጥ እየተደሰቱ ይኖራሉ! ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በታጨደ መስክ ላይ ከሚወርድ ዝናብና ምድርን ከሚያረሰርስ ካፊያ’ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ እርካታና እፎይታ ያመጣል።
11 የዚህን መዝሙር ፍጻሜ በዓይነ ሕሊናህ ስትመለከት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ልብህ አልተነሳሳም? ኢየሱስ ከጎኑ ተሰቅሎ ለነበረው ክፉ አድራጊ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ባለው ጊዜ ሰውየው በጣም ተደስቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 23:43) በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ይህ ሰው እንደገና ሕያው ይሆናል። ለክርስቶስ አገዛዝ ከተገዛ ፍጹም ጤንነትና ደስታ አግኝቶ በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራል።
12. በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከሞት ለሚነሱ ዓመፀኞች ምን አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል?
12 በታላቁ ሰለሞን በኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት ሥር “ጻድቅ ይለመልማል” ማለትም ያብባል ወይም ይበለጽጋል። (መዝ. 72:7 NW) ኢየሱስ በምድር ላይ እያለ እንደነበረው ሁሉ በግዛቱ ዘመን ለብዙዎች ፍቅሩንና አሳቢነቱን ያሳያል። ከሞት የሚነሱት “ዓመፀኞች” እንኳ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የይሖዋን መሥፈርቶች ተምረው በዚያ መሠረት እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ፍቅራዊ ዝግጅት ይደረግላቸዋል። (ሥራ 24:15) እርግጥ ነው፣ ከመለኮታዊው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች በሕይወት መኖራቸውን ቀጥለው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት እንዲያደፈርሱ አይፈቀድላቸውም።
13. የአምላክ መንግሥት ግዛት ምን ያህል ሰፊ ነው? የሚያመጣው ሰላምስ የማይደፈርሰው ለምንድን ነው?
13 ቀጥሎ የተገለጸው ሐሳብ የታላቁ ሰለሞን አገዛዝ ምድር አቀፍ መሆኑን ይጠቁማል፦ “ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ ከታላቁም [ኤፍራጥስ] ወንዝ እስከ ምድር ዳርቻ ይገዛል። የበረሓ ዘላኖች በፊቱ ይሰግዳሉ፤ ጠላቶቹም ዐፈር ይልሳሉ።” (መዝ. 72:8, 9) አዎን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ መላውን ምድር ይገዛል። (ዘካ. 9:9, 10) አገዛዙን የሚቀበሉና የሚያመጣውን በረከት ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች ‘ይሰግዱለታል’ ይኸውም በፈቃደኝነት ይገዙለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑ ኃጢአተኞች ይጠፋሉ፤ ‘መቶ ዓመት’ ቢሞላቸው እንኳ በአጭሩ እንደተቀጩ ይቆጠራል። (ኢሳ. 65:20) እነዚህ ሰዎች “ዐፈር ይልሳሉ።”
በርኅራኄ ተነሳስቶ ያስብልናል
14, 15. ኢየሱስ የሰዎችን ስሜት እንደሚረዳና ‘ችግረኛው በጮኸ ጊዜ እንደሚታደገው’ እንዴት ማወቅ እንችላለን?
14 ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ በእጅጉ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መገላገል እንደምንችል ተስፋ አለን። (መዝሙር 72:12-14ን አንብብ።) ታላቁ ሰለሞን ኢየሱስ ፍጽምና በጎደለው ሁኔታ ውስጥ እንደምንኖር ስለሚገነዘብ ይራራልናል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ለጽድቅ ሲል ሥቃይ የደረሰበት ሲሆን አምላክም ኢየሱስ የደረሰበትን መከራ በራሱ እንዲወጣ ፈቅዷል። እንዲያውም ኢየሱስ ‘ላቡ ወደ ምድር እንደሚንጠባጠብ የደም ነጠብጣብ’ እስኪሆን ድረስ ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ደርሶበት ነበር። (ሉቃስ 22:44) በመከራ እንጨት ላይ በተሰቀለበት ጊዜም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” በማለት በታላቅ ድምፅ ጮዃል። (ማቴ. 27:45, 46) ኢየሱስ ይህ ሁሉ ሥቃይ ቢደርስበትም እንዲሁም ሰይጣን ይሖዋን እንዲተው ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ ጥረት ቢያደርግም እንኳ ኢየሱስ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ መሆኑን አስመሥክሯል።
15 ኢየሱስ ያለብንን ሥቃይ ተመልክቶ ‘ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን እንደሚታደገው’ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም ለሰዎች ባለው ፍቅራዊ አሳቢነት ተነሳስቶ “ችግረኞችን ይሰማል” እንዲሁም “ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል።” (መዝ. 69:33፤ 147:3) “እንደ እኛው በሁሉም ረገድ የተፈተነ” በመሆኑ ‘በድካማችን ይራራልናል።’ (ዕብ. 4:15) ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ላይ እየገዛ እንደሆነና የሰው ልጆችን ከሥቃይ የሚገላግልበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ማወቅ እንዴት የሚያስደስት ነው!
16. ሰለሞን ለተገዥዎቹ እንዲያዝን ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?
16 ሰለሞን ጥበብና ማስተዋል ስለነበረው “ለችግረኞች ይራራ” እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ የእሱ ሕይወት በሐዘንና በአሰቃቂ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር። ወንድሙ አምኖን እህቱን ትዕማርን የደፈራት ሲሆን አቤሴሎም ደግሞ ወንድሙ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት አምኖንን ገድሎታል። (2 ሳሙ. 13:1, 14, 28, 29) አቤሴሎም የዳዊትን ዙፋን ለመገልበጥ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ሙከራው ከሽፎ በኢዮአብ ተገድሏል። (2 ሳሙ. 15:10, 14፤ 18:9, 14) ከጊዜ በኋላ የሰለሞን ወንድም አዶንያስ ዙፋኑን ለመውረስ ሞክሮ ነበር። አዶንያስ ቢሳካለት ኖሮ ሰለሞንን እንደሚያስገድለው ምንም ጥርጥር አልነበረውም። (1 ነገ. 1:50) ሰለሞን የይሖዋ ቤተ መቅደስ በተመረቀ ጊዜ ባቀረበው ጸሎት ላይ የተናገረው ሐሳብ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ እንደሚረዳ በግልጽ ያሳያል። ንጉሡ ተገዥዎቹን አስመልክቶ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ ‘ማንም ሰው ጭንቀቱና ሕመሙ ተሰምቶት ጸሎትና ልመና ቢያቀርብ ይቅር በል፤ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ክፈለው።’—2 ዜና 6:29, 30
17, 18. አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ምን ዓይነት ‘ጭንቀትና ሕመም’ መቋቋም ግድ ሆኖባቸዋል? እንዲቋቋሙ የረዳቸውስ ምንድን ነው?
17 ምናልባትም እኛ ‘ጭንቀትና ሕመም’ የሚሰማን ከዚህ በፊት በሕይወታችን ውስጥ ባጋጠመን አሳዛኝ ሁኔታ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው ሜሪa የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “ደስተኛ መሆን የምችልበት በቂ ምክንያት አለኝ፤ ሆኖም በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠመኝ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የኀፍረት ስሜት እንዲሰማኝና ራሴን እንድጠላ ያደርገኛል። በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የሐዘን ስሜት ስለሚሰማኝ ልክ ሁሉ ነገር ትናንትና የተፈጸመብኝ ይመስል ለማልቀስ ይዳዳኛል። ፈጽሞ ከአእምሮዬ ሊጠፋ ያልቻለው መጥፎ ትዝታ አሁንም የከንቱነትና የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኛል።”
18 በርካታ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል፤ ሆኖም እንዲህ ያለውን ስሜት ተቋቁመው ለመጽናት የሚያስችላቸውን ብርታት እንዲያገኙ ምን ሊረዳቸው ይችላል? ሜሪ እንዲህ ብላለች፦ “እውነተኛ ወዳጆቼና መንፈሳዊ ቤተሰቦቼ ደስተኛ እንድሆን ረድተውኛል። እኔም ብሆን ይሖዋ ስለወደፊቱ ጊዜ በሰጠው ተስፋ ላይ ትኩረት ለማድረግ እሞክራለሁ፤ እንዲሁም በዚያን ጊዜ እርዳታ ለማግኘት የማሰማው ጩኸት ወደ ደስታ ጩኸት እንደሚለወጥ እርግጠኛ ነኝ።” (መዝ. 126:5) ተስፋችንን አምላክ በሾመው ገዥ በልጁ በኢየሱስ ላይ ማድረግ ይኖርብናል። እሱን በሚመለከት እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሯል፦ “ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል፤ ደማቸውም በእርሱ ፊት ክቡር ነው።” (መዝ. 72:13, 14) ይህ እንዴት የሚያጽናና ነው!
ሁሉም ነገር የተትረፈረፈበት አዲስ ዓለም ከፊታችን ይጠብቀናል
19, 20. (ሀ) በመዝሙር 72 ላይ እንደተገለጸው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የትኛው ችግር ይወገዳል? (ለ) የክርስቶስ አገዛዝ ለሚያስገኘው በረከት በዋነኝነት መመስገን የሚገባው ማነው? መንግሥቱ ስለሚያከናውነው ነገር ምን ይሰማሃል?
19 የታላቁ ሰለሞን አገዛዝ በሚያመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ጻድቅ ሰዎች የሚያገኙትን የወደፊት ሕይወት እንደገና በአእምሮህ ለመሳል ሞክር። ‘በምድሪቱ ላይ እህል እንደሚትረፈረፍና በተራሮችም ዐናት ላይ እንደሚወዛወዝ’ ተስፋ ተሰጥቶናል። (መዝ. 72:16) እህል በተራራ ዐናት ላይ መብቀሉ የተለመደ ነገር ስላልሆነ ይህ አባባል ምድር ምን ያህል የተትረፈረፈ ምርት እንደምትሰጥ ያጎላል። ምድር በምትሰጠው ምርት የተነሳ በሰለሞን የግዛት ዘመን የተትረፈረፈ ምርት ይገኝባት እንደነበረው “እንደ ሊባኖስ” ትሆናለች። እስቲ አስበው! በዚያ ጊዜ የምግብ እጥረት አይኖርም፣ ማንም ሰው በተመጣጠነ ምግብ እጦት አይሠቃይም እንዲሁም ማንም ሰው አይራብም! ለሁሉም ሰው “ታላቅ የምግብ ግብዣ” ይደረጋል።—ኢሳ. 25:6-8፤ 35:1, 2
20 ለዚህ ሁሉ በረከት መመስገን ያለበት ማነው? በዋነኝነት ሊመሰገን የሚገባው ዘላለማዊ ንጉሥና የአጽናፈ ዓለም ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ሁላችንም በምሳሌያዊ ሁኔታ ድምፃችንን አስተባብረን በዚህ ማራኪና አስደሳች መዝሙር መደምደሚያ ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ እንዘምራለን፦ “[ንጉሥ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ስም] ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ፤ ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ይባረኩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው። ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ይባረክ። ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ፤ ምድርም ሁሉ በክብሩ ይሞላ። አሜን፤ አሜን።”—መዝ. 72:17-19
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሟ ተለውጧል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በመዝሙር 72 ላይ የሚገኘው ትንቢታዊ ሁኔታ ለየትኛው ጊዜ እንደ ናሙና ይሆናል?
• ታላቁ ሰለሞን ማነው? ግዛቱስ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል?
• በመዝሙር 72 ላይ በትንቢት ከተነገሩት በረከቶች መካከል በግለሰብ ደረጃ አስደሳች ሆኖ ያገኘኸው የትኛውን ነው?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሰለሞን አገዛዝ ወቅት የነበረው ብልጽግና ለምን ነገር ጥላ ነበር?
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በታላቁ ሰለሞን አገዛዝ ሥር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሕይወት ለማግኘት ምንም ያህል ጥረት ቢጠይቅ የሚያስቆጭ አይደለም