ይሖዋን ከልብ በመነጨ ደስታ አገልግሉት
“እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል . . . አምላክህን ይሖዋን በፍሥሐና ከልብ በመነጨ ደስታ አላገለገልክምና።” —ዘዳግም 28:45–47 አዓት
1. ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎች የሚያገለግሉበት ቦታ የትም ሆነ የት ደስተኞች እንደሆኑ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
የይሖዋ አገልጋዮች ፈቃዱን የሚያከናውኑት በሰማይም ይሁን በምድር ደስተኞች ናቸው። “አጥቢያ ኮከቦች” የሆኑት መላእክት ምድር ስትመሠረት በደስታ እልል ብለዋል፤ በሰማይ ያሉት እልፍ አዕላፍ መላእክት በደስታ ‘የአምላክን ቃል እየፈጸሙ’ እንዳሉ አያጠራጥርም። (ኢዮብ 38:4–7፤ መዝሙር 103:20) የይሖዋ አንድያ ልጅ በሰማይ ደስተኛ “ዋና ሠራተኛ” ነበር፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በመባል ሰው ሆኖ በምድር ላይ መለኮታዊውን ፈቃድ በመፈጸምም ደስታን አግኝቷል። ከዚህም በላይ “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል።”—ምሳሌ 8:30, 31፤ ዕብራውያን 10:5–10፤ 12:2
2. እስራኤላውያን በረከቶች አለዚያም መርገሞች እንዲደርሱባቸው ያደርግ የነበረው ነገር ምን ነበር?
2 እስራኤላውያን አምላክን ሲያስደስቱ እነርሱም ደስታ ያገኙ ነበር። ይሁን እንጂ ሕጉን ካፈረሱስ? እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር፦ “[መርገሞቹ] በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘላለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ። ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሐና በሐሴት አላመለክህምና [“ከልብ በመነጨ ደስታ አላገለገልክምና” አዓት] በራብና በጥማት በዕራቁትነትም ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል።” (ዘዳግም 28:45–48) በረከቶችና መርገሞች ማን የይሖዋ አገልጋይ እንደሆነ ማን ደግሞ እንዳልሆነ ቁልጭ አድርገው ያሳዩ ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹ መርገሞች የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ዓላማዎች አቅልሎ ማየትም ሆነ መናቅ እንደማይቻል የሚያሳዩም ነበሩ። እስራኤላውያን ጥፋት እንደሚደርስባቸውና ወደ ግዞት እንደሚወሰዱ ይሖዋ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ባለመቀበላቸው ኢየሩሳሌም “ለምድር አሕዛብ ሁሉ እርግማን” ሆነች። (ኤርምያስ 26:6) እንግዲያው አምላክን በመታዘዝ ሞገሱን እናግኝ። ደስታ ለአምላካዊ ነገሮች አክብሮት ያላቸው ሰዎች ከሚያገኟቸው ብዙ መለኮታዊ በረከቶች አንዱ ነው።
“ከልብ በመነጨ ደስታ” እንዴት ማገልገል እንደሚቻል
3. ምሳሌያዊው ልብ ምንድን ነው?
3 እስራኤላውያን ይሖዋን ‘በፍሥሐና ከልብ በመነጨ ደስታ’ ማገልገል ነበረባቸው። ዘመናዊ የአምላክ አገልጋዮችም እንደዚሁ ማድረግ አለባቸው። ፍሥሐ ማለት “መፈንደቅ፣ ደስታ በደስታ መሆን” ማለት ነው። ሥጋዊው ልብ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ቢጠቀስም ቃል በቃል ያስባል ወይም ያመዛዝናል ማለት አይደለም። (ዘጸአት 28:30) ልብ ዋነኛ ተግባሩ የሰውነትን ሴሎች የሚመግበውን ደም መርጨት ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ የመውደድ፣ የስሜታዊ ግፊትና የማስተዋል ችሎታ ማኅደር ከመሆንም አልፎ ሌላ ነገርንም የሚያመለክተውን ምሳሌያዊ ልብ ይጠቅሳል። ልብ “ማዕከላዊውን ክፍል በጥቅሉ፣ ውስጣዊውን ክፍል፣ እንዲሁም በተለያዩ ሥራዎቹ፣ በፍላጎቶቹ፣ በፍቅራዊ አሳቢነቱ፣ በስሜቶቹ፣ ለአንድ ነገር በሚያድርበት የመውደድ ስሜት፣ በዓላማዎቹ፣ በአስተሳሰቦቹ፣ በማስተዋል ችሎታው፣ በሚያልማቸው ነገሮች፣ በጥበቡ፣ በእውቀቱ፣ በሙያው፣ በእምነቶቹና በማስረዳት ችሎታው፣ በማስታወስ ችሎታውና በጥንቁቅነቱ ራሱን የሚገልጸውን ውስጣዊውን ሰው” እንደሚያመለክት ተገልጿል። (ጆርናል ኦቭ ዘ ሶሳይቲ ኦቭ ቢብሊካል ሊትሬቸር ኤንድ ኤክሰጀሲስ፣ 1882 ገጽ 67) ምሳሌያዊው ልባችን ደስታን ጨምሮ መንፈሳችንንና ስሜቶቻችንንም ያጠቃልላል።—ዮሐንስ 16:22
4. ይሖዋ አምላክን ከልብ በመነጨ ደስታ እንድናገለግለው ምን ሊረዳን ይችላል?
4 ይሖዋን ከልብ በመነጨ ደስታ እንድናገለግለው ምን ሊረዳን ይችላል? ላገኘናቸው በረከቶችና አምላክ ለሰጠን መብት ቀና እንዲሁም አድናቆት የተሞላበት አመለካከት መያዛችን ለዚህ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል ለእውነተኛው አምላክ ‘ቅዱስ አገልግሎት’ የማቅረብ መብታችንን በደስታ ስሜት ልናየው እንችላለን። (ሉቃስ 1:74) ከዚሁ ጋር በተያያዘም ምሥክሮቹ በመሆን የይሖዋን ስም የመሸከም መብት አለ። (ኢሳይያስ 43:10–12) በዚህም ላይ የአምላክን ቃል በመከተል እያስደሰትነው እንዳለን በማወቃችን የምናገኘውንም ደስታ መጨመር እንችላለን። በተጨማሪም መንፈሳዊ ብርሃን በማንጸባረቅና በዚህም መንገድ ብዙዎች ከጨለማ እንዲወጡ በመርዳት እንዴት ያለ ደስታ ይገኛል!—ማቴዎስ 5:14–16፤ ከ1 ጴጥሮስ 2:9 ጋር አወዳድር።
5. አምላካዊ ደስታ ምንጩ ምንድን ነው?
5 ሆኖም ይሖዋን ከልብ በመነጨ ደስታ ማገልገል እንዲሁ አዎንታዊ አስተሳሰብ በመያዝ የሚገኝ ነገር አይደለም። አዎንታዊ አመለካከት መያዙ ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ አምላካዊ ደስታ የጠባይ መሻሻል በማድረግ የምናፈራው ነገር አይደለም። የይሖዋ መንፈስ ፍሬ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) እንዲህ ዓይነት ደስታ ከሌለን የአምላክን መንፈስ ሊያሳዝን ከሚችል ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አስተሳሰብ ወይም ድርጊት በመራቅ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልገን ይሆናል። (ኤፌሶን 4:30) ይሁን እንጂ ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን ሆነን ስንኖር አንዳንድ ጊዜ ልባዊ ደስታ ብናጣ መለኮታዊ ተቀባይነት እንደተነፈገን የሚያሳይ ማስረጃ ነው የሚል ፍራቻ ሊያድርብን አይገባም። ፍጹማን አይደለንም፤ እንዲሁም ሥቃይ፣ ሐዘንና አልፎ ተርፎም አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ይደርስብናል። ይሖዋ ደግሞ ይህን ሁኔታችንን ይረዳልናል። (መዝሙር 103:10–14) እንግዲያው የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነው ደስታ አምላክ የሚሰጠው ነገር መሆኑን በማስታወስ ቅዱስ መንፈሱን ለማግኘት እንጸልይ። አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ለእንዲህ ዓይነቶቹ ጸሎቶች መልስ በመስጠት ከልብ በመነጨ ደስታ እንድናገለግለው ያስችለናል።—ሉቃስ 11:13
ደስታ ስናጣ
6. ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት የማንደሰት ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
6 በአገልግሎታችን የማንደሰት ከሆነ ከጊዜ በኋላ በይሖዋ አገልግሎት ልንቀዘቅዝ ወይም አልፎ ተርፎ ተግባራችንን በታማኝነት የማንፈጽም ሆነን ልንገኝ እንችላለን። በመሆኑም በትሕትናና በጸሎት የልባችንን ዓላማ መመርመርና አስፈላጊ ማስተካከያዎችን ማድረጋችን ጥበብ ነው። አምላክ የሚሰጠውን ደስታ ለማግኘት ይሖዋን በፍቅር ተነሳስተን እንዲሁም በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችንና አሳባችን ማገልገል አለብን። (ማቴዎስ 22:37) ጳውሎስ “በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ። እርስ በእርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ” በማለት ስለጻፈ በፉክክር መንፈስ ልናገለግል አይገባም። (ገላትያ 5:25, 26) የምናገለግለው ከሌሎች ልቀን ለመታየት ወይም ለመወደስ ብለን ከሆነ እውነተኛ ደስታ ሊኖረን አይችልም።
7. ከልብ የመነጨ ደስታችንን እንደገና ለማቀጣጠል የምንችለው እንዴት ነው?
7 ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነውን ቃል በመጠበቅ ደስታ እናገኛለን። በመጀመሪያ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን በክርስቲያናዊ ኑሮ በቅንዓት መመላለስ ጀምረን ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎችን እናጠና ነበር፤ እንዲሁም ዘወትር በስብሰባዎች ላይ እንገኝ ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) በአገልግሎቱ መካፈል ደስታ ሰጥቶን ነበር። ይሁንና አሁን ደስታችን ቀንሶ ከሆነስ? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ በአገልግሎት መሳተፍ፣ በአጠቃላይ በማንኛውም ክርስቲያናዊ ዘርፍ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ለሕይወታችን መንፈሳዊ መረጋጋት ሊሰጠውና መጀመሪያ ላይ የነበረንን ፍቅርም ሆነ ቀደም ሲል የነበረንን ከልብ የመነጨ ደስታ እንደገና ሊያቀጣጥልልን ይገባል። (ራእይ 2:4) እንዲህ ካደረግን ደስታ እንደሌላቸውና ብዙውን ጊዜ መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሰዎች አንሆንም። ሽማግሌዎች ለመርዳት ዝግጁ ናቸው፤ ሆኖም በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል መፈጸም አለብን። ሌላ ማንም ሰው ይህን ሊያደርግልን አይችልም። እንግዲያው ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን የገባነውን ቃል ለመፈጸምና እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የዘወትሩን ክርስቲያናዊ ልማድ መከተልን ግባችን እናድርግ።
8. ደስተኞች እንድንሆን ከተፈለገ ንጹሕ ሕሊና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
8 የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነው ደስታ እንዲኖረን ከተፈለገ ንጹሕ ህሊና ሊኖረን ያስፈልጋል። የእስራኤሉ ንጉሥ ዳዊት ኃጢአቱን ለመደበቅ እስከሞከረ ድረስ በሐዘን ይዋጥ ነበር። እንዲያውም የሕይወቱ ርጥበት እንደ ተነነ ያህል ተሰምቶት ነበር። አካላዊ ሕመም ደርሶበትም ሊሆን ይችላል። ንስሐ ሲገባና ኃጢአቱን ሲናዘዝ እንዴት ያለ እፎይታ አግኝቶ ይሆን! (መዝሙር 32:1–5) አንዳንድ ከባድ ኃጢአቶችን ደብቀን ከሆነ ደስተኞች መሆን አንችልም። እንደዚያ ካደረግን የመከራ ሕይወት እየገፋን እንኖራለን። በዚህ መንገድ ደስታ ሊገኝ እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ መናዘዝና ንስሐ መግባት እፎይታን ከማምጣቱም ሌላ የተነጠቅነውን የደስተኛነት መንፈስ ይመልስልናል።—ምሳሌ 28:13
በደስታ መጠበቅ
9, 10. (ሀ) አብርሃም ምን ተስፋ ተቀብሎ ነበር? ይሁን እንጂ እምነቱና ደስታው ተፈትኖ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ አብነት መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
9 መጀመሪያ ስለ መለኮታዊው ዓላማ ስንማር ደስታ ማግኘት አንድ ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ደስተኛ እንደሆኑ መዝለቁ የተለየ ነገር ነው። ይህን የታማኙን አብርሃም ሁኔታ እንደ ምሳሌ በመጠቀም ማስረዳት ይቻላል። በአምላክ ትእዛዝ ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ካለ በኋላ አንድ መልአክ የሚከተለውን መልእክት ነገረው፦ “እግዚአብሔር፦ በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፣ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፣ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ [“ራሳቸውን ይባርካሉ” አዓት]፣ ቃሌን ሰምተሃልና።” (ዘፍጥረት 22:15–18) አብርሃም በዚህ ተስፋ እጅግ እንደተደሰተ ምንም አያጠራጥርም።
10 አብርሃም ቃል የተገባለት በረከት የሚመጣበት “ዘር” ይስሐቅ ነው ብሎ ጠብቆ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በይስሐቅ በኩል የመጣ ምንም ዓይነት አስደሳች ነገር ሳይኖር ዓመታት እያለፉ ሲሄድ የአብርሃምና የቤተሰቡ እምነትና ደስታ ተፈትኖ ሊሆን ይችላል። አምላክ ተስፋውን አስመልክቶ ለይስሐቅ በኋላም ለልጁ ለያዕቆብ የሰጠው ማረጋገጫ ዘሩ የሚመጣው ገና ወደፊት እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል። ይህ ደግሞ እምነታቸውንና ደስታቸውን ይዘው ለመቆየት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ይሁን እንጂ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ አምላክ ለእነርሱ የገባውን ተስፋ ፍጻሜ ሳያዩ አልፈዋል፤ ሆኖም ደስታ የራቃቸው የአምላክ አገልጋዮች አልነበሩም። (ዕብራውያን 11:13) እኛም ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ መፈጸም እየጠበቅን እርሱን በእምነትና በደስታ ማገልገላችንን መቀጠል እንችላለን።
ስደት ቢኖርም መደሰት
11. ስደት ቢኖርም ደስተኞች መሆን የምንችለው ለምን ድን ነው?
11 ምንም እንኳ ስደት ቢደርስብንም የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን ከልብ በመነጨ ደስታ ልናገለግለው እንችላለን። ኢየሱስ ለእሱ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ሰዎች ደስተኞች ናቸው ብሏል። ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ ብሏል፦ “ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሴት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፣ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን [“ደስተኞች” አዓት] ናችሁ።” (1 ጴጥሮስ 4:13, 14፤ ማቴዎስ 5:11, 12) ለጽድቅ ስትሉ ስደትንና መከራን ጸንታችሁ የምትቋቋሙ ከሆነ የይሖዋን መንፈስና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን ታገኛላችሁ፤ ይህም ደስታን ይጨምራል።
12. (ሀ) የእምነት ፈተናዎችን በደስታ ልናስተናግዳቸው የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በግዞት ከነበረ አንድ ሌዋዊ ሁኔታ ምን መሠረታዊ ትምህርት መቅሰም ይቻላል?
12 አምላክ መሸሸጊያችን ስለሆነ የእምነት ፈተናዎችን በደስታ ልናስተናግዳቸው እንችላለን። ይህ በመዝሙር 42 እና 43 ላይ ቁልጭ ብሎ ተገልጿል። በሆነ ምክንያት አንድ ሌዋዊ በግዞት ይገኝ ነበር። በአምላክ መቅደስ የሚከናወነው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በጣም ስለናፈቀው ደረቅና ጠፍ በሆነ ምድር ውኃ ለማግኘት እንደቋመጠች ዋላ ተሰምቶት ነበር። ይሖዋንና በመቅደሱ አምላክን የማገልገልን መብት ‘ተጠምቶ’ ወይም ናፍቆ ነበር። (መዝሙር 42:1, 2) የዚህ ግዞተኛ ተሞክሮ ከይሖዋ ሕዝብ ጋር ዘወትር ለመገናኘት ስለመቻላችን የአመስጋኝነት መንፈስ እንድናሳይ ሊገፋፋን ይገባል። በስደት ሳቢያ መታሰርን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ለጊዜው ከእነርሱ እንድንለይ ካደረጉን አብረን በቅዱስ አገልግሎት ያሳለፍናቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች ወደ ኋላ መለስ እያልን እናሰላስል፤ እንዲሁም ከአምላኪዎቹ ጋር የዘወትሩን እንቅስቃሴ ማድረግ ወደምንችልበት ሁኔታ እንዲመልሰን ‘አምላክን በተስፋ እየተጠባበቅን’ መጽናት እንድንችል እንጸልይ።—መዝሙር 42:4, 5, 11፤ 43:3–5 የ1980 ትርጉም
‘ይሖዋን በደስታ አገልግሉ’
13. መዝሙር 100:1, 2 ደስታ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት አንዱ ገጽታ መሆን እንዳለበት የሚያሳየው እንዴት ነው?
13 ደስታ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት አንዱ ገጽታ መሆን አለበት። ይህ መዝሙራዊው “ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፣ በደስታም ለእግዚአብሔር ተገዙ፣ በሐሴትም ወደ ፊቱ ግቡ” በማለት በዘመረው የምስጋና ዝማሬ ላይ ተገልጿል። (መዝሙር 100:1, 2) ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው፤ አገልጋዮቹም ራሳቸውን ለእርሱ ሲወስኑ የገቡትን ቃል በመፈጸም ደስታ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦች በይሖዋ ሐሴት ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ የምስጋና ቃላችን ደግሞ ልክ ድል እንዳደረገ ሠራዊት ‘ሆታ’ በድምቀት ማስተጋባት ይኖርበታል። አምላክን ማገልገል መንፈስን የሚያድስ ስለሆነ ደስታ የግድ አብሮት ይገኛል። በመሆኑም መዝሙራዊው ሰዎች አምላክ ወዳለበት ቦታ በእልልታና “በሐሴት” እንዲመጡ አጥብቆ አሳስቧል።
14, 15. መዝሙር 100:3–5 በዛሬው ጊዜ ላሉት ደስተኛ የይሖዋ ሕዝቦች የሚሠራው እንዴት ነው?
14 መዝሙራዊው እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ እወቁ [እውቅና ስጡት፣ አምናችሁ ተቀበሉ]፤ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የማሰማርያውም በጎች ነን።” (መዝሙር 100:3) የበጎች እረኛ ባለቤታቸው እንደሆነ ሁሉ እኛም የይሖዋ ንብረት ነን፤ ምክንያቱም እርሱ ፈጣሪያችን ነው። አምላክ ለኛ ልዩ እንክብካቤና አያያዝ ስለሚያደርግልን በአመስጋኝነት ስሜት ከፍ ከፍ እናደርገዋለን። (መዝሙር 23) ይሖዋን በተመለከተ መዝሙራዊው እንዲህ በማለትም ዘምሯል፦ “ወደ ደጆቹ በመገዛት፣ ወደ አደባባዮቹም በምስጋና ግቡ፤ አመስግኑት፣ ስሙንም ባርኩ፤ እግዚአብሔር ቸር፣ ምሕረቱም ለዘላለም፣ እውነቱም ለልጅ ልጅ ነውና።”—መዝሙር 100:4, 5
15 በዛሬው ጊዜ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ደስተኛ ሰዎች ምስጋናና ውዳሴ ለማቅረብ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ አደባባዮች እየገቡ ነው። ምን ጊዜም ስለ ይሖዋ መልካም ነገር በመናገር በደስታ የአምላክን ስም እንባርካለን፤ ታላላቅ ባሕርያቱም እንድናወድሰው ይገፋፉናል። ምንም እንከን የማይወጣለት አምላክ ነው፤ ለአገልጋዮቹ ያለው ፍቅራዊ ደግነት ወይም ርኅራኄ ለዘላለም የሚቀጥል በመሆኑ ምን ጊዜም ትምክህት ሊጣልበት የሚችል ነው። ይሖዋ ፈቃዱን ለሚያደርጉ ፍቅር በማሳየት ረገድ ‘ለዘላለም’ ታማኝ ነው። (ሮሜ 8:38, 39) እንግዲያው ‘ይሖዋን በደስታ የምናገለግልበት’ ጥሩ ምክንያት እንዳለን አያጠራጥርም።
በተስፋችሁ ደስ ይበላችሁ
16. ክርስቲያኖች በየትኞቹ ተስፋዎችና ወደፊት የሚመጡ ሁኔታዎች መደሰት ይችላሉ?
16 ጳውሎስ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” ሲል ጽፏል። (ሮሜ 12:12) የኢየሱስ ክርስቶስ የተቀቡ ተከታዮች አምላክ በልጁ በኩል የከፈተላቸውን የማይከስም ሰማያዊ ሕይወት ታላቅ ተስፋ ሲያስቡ ይደሰታሉ። (ሮሜ 8:16, 17፤ ፊልጵስዩስ 3:20, 21) ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም የሚደሰቱበት ምክንያት አላቸው። (ሉቃስ 23:43) ሁሉም የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች በመንግሥቱ ተስፋ የሚደሰቱበት ምክንያት አላቸው፤ ምክንያቱም ወይ የሰማያዊው መንግሥት አባላት ይሆናሉ፤ አለዚያም በምድራዊ ግዛቱ ውስጥ ይኖራሉ። እንዴት ያለ አስደሳች በረከት ነው!—ማቴዎስ 6:9, 10፤ ሮሜ 8:18–21
17, 18. (ሀ) በኢሳይያስ 25:6–8 ላይ አስቀድሞ የተነገረው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ይህ የኢሳይያስ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? ወደፊትስ የሚፈጸመው እንዴት ነው?
17 በተጨማሪም ታዛዥ የሰው ዘሮች አስደሳች የወደፊት ጊዜ እንደሚጠብቃቸው ኢሳይያስ አስቀድሞ ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።”—ኢሳይያስ 25:6–8
18 የይሖዋ አምላኪዎች እንደመሆናችን መጠን በዛሬው ጊዜ የምንካፈልበት መንፈሳዊ ድግስ በእርግጥም አስደሳች ግብዣ ነው። እንዲያውም በአዲሱ ዓለም እንደሚኖሩ ቃል የገባቸውን ቃል በቃል ጥሩ የሆኑ ነገሮች ግብዣ በጉጉት እየተጠባበቅን አምላክን በቅንዓት ስናገለግለው ደስታችን እጥፍ ድርብ ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛ አማካኝነት በአዳም ኃጢአት ምክንያት በሰው ዘር ላይ የተጣለውን “መጋረጃ” ያስወግዳል። ኃጢአትና ሞት ተወግደው ማየቱ እንዴት ያለ ደስታ ነው! የምናፈቅራቸውን በትንሣኤ የሚነሱ ሰዎች እንደገና መቀበሉ፣ እንባ መቅረቱን መመልከቱና የይሖዋ ሕዝቦች በማይነቀፉበት ከዚህ ይልቅ አምላክ ለቀንደኛው ከሳሽ ለሰይጣን መልስ መስጠት እንዲችል በሚያደርጉበት ገነት ምድር ላይ መኖር ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ምሳሌ 27:11
19. ምሥክሮቹ እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ ከፊታችን ለዘረጋልን ተስፋ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
19 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን እንደሚያደርግላቸው ማወቁ በደስታና በአመስጋኝነት ስሜት እንድትሞላ አላደረገህምን? በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ታላላቅ ተስፋዎች ለደስታችን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ! ከዚህም በላይ ቅዱሱ ተስፋችን ደስተኛ፣ አፍቃሪና ለጋስ የሆነውን አምላካችንን በእንዲህ ዓይነት ስሜት እንድንመለከተው ያደርገናል፦ “እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፣ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሴትም እናደርጋለን።” (ኢሳይያስ 25:9) እጹብ ድንቅ የሆነውን ተስፋችንን በአእምሯችን ላይ በማይፋቅ ሁኔታ ቀርጸን ይሖዋን ከልብ በመነጨ ደስታ ለማገልገል በጋለ ስሜት ማንኛውንም ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አንበል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋን “ከልብ በመነጨ ደስታ” ልናገለግለው የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት የማንደሰት ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?
◻ ስደት ቢኖርም የይሖዋ ሕዝቦች ደስታ ሊኖራቸው የሚችለው ለምንድን ነው?
◻ በተስፋችን ለመደሰት የሚያበቁን ምን ምክንያቶች አሉን?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሁሉም የክርስቲያናዊ ኑሮ ገጽታዎች መካፈሉ ደስታችንን ይጨምርልናል