አምላካዊ ፍርሃትን መኮትኮት
“እግዚአብሔርን ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ። ” — ምሳሌ 3:7
1. የምሳሌ መጽሐፍ የተጻፈው ለእነማን ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ብዙ መንፈሳዊ ምክሮችን ይዟል። ይሖዋ በመጀመሪያ ይህን የመመሪያ መጽሐፍ ያዘጋጀው በጥላነት የተጠቀመበትን የእስራኤል ሕዝብ ለማስተማር ነበር። የምሳሌ መጽሐፍ ዛሬም ‘የዘመናት መጨረሻ ለደረሰባቸው’ ቅዱስ ክርስቲያን ሕዝቦቹ ብዙ የጥበብ ምክሮች ይሰጣል። — 1 ቆሮንቶስ 10:11፤ ምሳሌ 1:1–5፤ 1 ጴጥሮስ 2:9
2. በምሳሌ 3:7 ላይ የሚገኘው ማስጠንቀቂያ ዛሬ ወቅታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ምሳሌ 3:7ን አውጥተን ስንመለከት እንዲህ እናነባለን:- “በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ከክፋትም ራቅ።” ሰብአዊው ጥበብ ብቻውን እባብ ‘መልካሙንና ክፉውን ታውቃላችሁ’ የሚል ተስፋ በመስጠት ሔዋንን ካሳተበት ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ዘመን ጀምሮ የሰውን ዘር ፍላጎቶች ማሟላት ሳይችል ቀርቷል። (ዘፍጥረት 3:4, 5፤ 1 ቆሮንቶስ 3:19, 20) ይህ ሁኔታ የሰው ልጅ አምላክ የለም ባይነትና የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰቦች ያስከተሏቸውን የዘረኝነት፣ የዓመፅና የተለያየ የሥነ ምግባር ብልግና ያስከተላቸውን ፍሬዎች ከሚያጭድበት ከዚህ ከ20ኛው መቶ ዘመን ይበልጥ ግልጽ ሆኖ የታየበት ዘመን የለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ይህ ‘የአዲስ ዓለም ሥርዓት’ ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የተለያዩ የዓለም ሃይማኖቶች ሊፈቱ የማይችሉት ‘የአዲስ ዓለም ምስቅልቅል’ ነው።
3. በዘመናችን ምን ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚፈጸሙ ተተንብዮአል?
3 አጋንንታዊ ኃይሎች ‘በታላቁ ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር . . . በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ . . . እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት’ እንደወጡ የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ይነግረናል። (ራእይ 16:14, 16) እነዚህ ነገሥታት ወይም ገዥዎች በቅርቡ ከይሖዋ በሚመጣ ፍርሃት ይዋጣሉ። ከነዓናውያን ኢያሱና እስራኤላውያን ሊያጠፏቸው በመጡ ጊዜ የወደቀባቸው ዓይነት ፍርሃት ይወድቅባቸዋል። (ኢያሱ 2:9–11) ዛሬ ግን ኢያሱ ጥላ የሆነለት፣ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ሁሉን የሚገዛውን የእግዚአብሔርን ‘ብርቱ ቁጣ’ በመግለጥ ‘አሕዛብን ይመታል፣ በብረት በትርም ይገዛቸዋል።’ — ራእይ 19:15, 16
4, 5. የሚድኑት እነማን ናቸው? ለምንስ?
4 በዚያ ጊዜ የሚድኑት እነማን ናቸው? በዚያ ጊዜ ከጥፋት የሚድኑት በፍርሃት የሚዋጡት ሳይሆኑ ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት የኮተኮቱት ናቸው። እነዚህ ሰዎች በራሳቸው አመለካከት ጠቢብ ከመሆን ይልቅ ‘ከክፉ ይርቃሉ።’ ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ አእምሮአቸውን ጥሩ ነገር ብቻ ስለሚመግቡ መጥፎ ነገሮች ወደ አእምሮአቸው ለመግባት ቦታ አያገኙም። ነውረኛ የነበረችውን ሰዶም ድምጥማጧን እንዳጠፋ ሁሉ በክፉ ድርጊታቸው የሚጸኑትን ሁሉ ለሚያጠፋውና “የምድር ሁሉ ፈራጅ” ለሆነው ሉዓላዊ ጌታ ለይሖዋ ያላቸውን ጤናማ አክብሮት እንደ ውድ ሀብት ይቆጥራሉ። (ዘፍጥረት 18:25) በእርግጥም ለአምላክ ሕዝቦች ‘ከሞት ወጥመድ ያመልጡ ዘንድ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] መፍራት የሕይወት ምንጭ’ ነው። — ምሳሌ 14:27
5 መለኮታዊ ፍርድ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ዘመን ለይሖዋ ያደሩና ይሖዋን እንዳያስቀይሙ የሚፈሩ ሁሉ በምሳሌ 3:8 ላይ “[የይሖዋ ፍርሃት] ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፣ ለአጥንትህም ጠገን” የሚለው በምሳሌያዊ ቃላት የተገለጸ ሐቅ እውነት መሆኑን ይገነዘባሉ።
ይሖዋን ማክበር
6. ምሳሌ 3:9ን እንድንከተል የሚገፋፋን ምን መሆን ይኖርበታል?
6 ለይሖዋ ያለን በአድናቆት ላይ የተመሠረተ ፍርሃትና ለእሱ ያለን ጥልቅ ፍቅር “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፣ ከፍሬህም ሁሉ በኩራት” የሚለውን ምሳሌ 3:9ን እንድንፈጽም ሊገፋፋን ይገባል። በምናቀርበው መሥዋዕት ይሖዋን እንድናከብር የምንጠየቀው በግዴታ አይደለም። በጥንት እስራኤል የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች በተመለከተ ከዘጸአት 35:29 እስከ ዘዳግም 23:23 ድረስ 12 ጊዜ ያህል እንደተገለጸው በፈቃደኝነት የሚደረግ መሆን ይኖርበታል። እነዚህ ለይሖዋ የምናቀርባቸው የፍሬያችን በኩራት በጣም ምርጥ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም ይሖዋ ለሚያሳየን ጥሩነትና ፍቅራዊ ደግነት ያለንን አድናቆት የምናሳይበት መንገድ ነው። (መዝሙር 23:6) እነዚህ ሥጦታዎቻችን ‘ከሁሉ አስቀድመን ጽድቁንና መንግሥቱን ዘወትር ለመፈለግ’ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያንጸባርቁ መሆን ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 6:33) ይሖዋን በሀብታችን በማክበራችን ምን ውጤት እናገኛለን? “ጎተራህም እህልን ይሞላል፣ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች።” — ምሳሌ 3:10
7. ለይሖዋ ማቅረብ የሚኖርብን የትኞቹን የፍሬያችንን በኩራት ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
7 ይሖዋ በመጀመሪያ ደረጃ የሚሰጠን በረከት መንፈሳዊ ነው። (ሚልክያስ 3:10) ስለሆነም በአንደኛ ደረጃ የምናቀርብለት የፍሬያችን በኩራት መንፈሳዊ መሆን ይኖርበታል። ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና በጣም አስፈላጊ የሆነውን ኃይላችንን የእሱን ፈቃድ ለማድረግ መጠቀም አለብን። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ለኢየሱስ የሚያበረታ “መብል” እንደሆነለት ሁሉ እኛንም ያበረታናል። (ዮሐንስ 4:34) መንፈሳዊ ጎተራዎቻችን ይሞላሉ። እንዲሁም በወይን የተመሰለው ደስታችን ሞልቶ ይፈስሳል። በተጨማሪም በይሖዋ በመታመን ለየቀኑ የሚበቃን ሰብአዊ ምግብ እንዲሰጠን ስለምንጸልይ ዓለም አቀፍ የሆነውን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ አቅማችን የቻለውን ያህል የልግስና እርዳታ ልንሰጥ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:11) ያለን ነገር ሁሉ፣ ቁሳዊ ንብረታችን ጭምር ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን የተገኘ ነው። እነዚህን ንብረቶች ይሖዋን ለማወደስ በተጠቀምን መጠን ተጨማሪ በረከቶች አትረፍርፎ ያፈስልናል። — ምሳሌ 11:4፤ 1 ቆሮንቶስ 4:7
የፍቅር ተግሣጾች
8, 9. ተግሣጽንና ወቀሳን እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
8 ምሳሌ ምዕራፍ 3 ቁጥር 11 እና 12 አምላካዊ በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ እንዲሁም በይሖዋና ምድር ላይ ባሉት በተወደዱ መንፈሳዊ ልጆቹ መካከል ስለሚኖረው የአባትና ልጅ ዝምድና ይናገራል። እንዲህ እናነባለን:- “ልጄ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፣ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፣ አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።” የዓለም ሰዎች ተግሣጽ ይጠላሉ። የይሖዋ ሕዝቦች ግን ተግሣጽን በደስታ መቀበል ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን የምሳሌ መጽሐፍ ቃላት በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ልጄ ሆይ፣ የጌታን ቅጣት አታቅልል፣ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና። . . . ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፣ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።” — ዕብራውያን 12:5, 6, 11
9 አዎን፣ ከወላጆቻችን ወይም ከክርስቲያን ጉባኤ ወይም በግል ጥናታችን ወቅት ያገኘናቸውን ጥቅሶች በምናሰላስልበት ጊዜ በምናገኘው ተግሣጽና ወቀሳ ለእያንዳንዳችን ከሚሰጠው ማሠልጠኛ አስፈላጊ የሆነውን ዋነኛ ክፍል ይይዛል። ምሳሌ 4:1, 13 “እናንት ልጆች፣ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፣ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ። ተግሣጽን ያዝ፣ አትተውም፤ ጠብቀው፣ እርሱ ሕይወትህ ነውና” በማለት እንደሚገልጸው ተግሣጽ መቀበል የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው።
ከሁሉ የሚበልጠው ደስታ
10, 11. በምሳሌ 3:13–18 ላይ ያሉት አስደሳች ቃላት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?
10 ቀጥሎ ያሉት ቃላት በጣም ውብ ናቸው! በእርግጥም ‘ያማሩና እውነተኛ ቃላት’ ናቸው። (መክብብ 12:10) እነዚህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ የሰለሞን ቃላት እውነተኛውን ደስታ ይገልጻሉ። እንዲህ እናነባለን:-
11 “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና፤ ከቀይ ዕንቁም ትከብራለች፣ የተከበረም ነገር ሁሉ አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፣ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፣ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚይዙአት የሕይወት ዛፍ ናትና፣ የተመረኮዘባትም ሁሉ ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው።” — ምሳሌ 3:13–18
12. ጥበብና ማስተዋል ሊጠቅሙን የሚገባው እንዴት ነው?
12 ጥበብ የሚለው ቃል በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ 46 ጊዜ ተደጋግሞ ተጠቅሷል! “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” ይህ አምላካዊ ጥበብ፣ በአምላክ ቃል እውቀት ላይ የተመሠረተና ተግባራዊ የሆነ ጥበብ ሲሆን የአምላክን ሕዝቦች በሰይጣን ዓለም ውስጥ ባለው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ይመራቸዋል። (ምሳሌ 9:10) በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ 19 ጊዜ የተጠቀሰው ማስተዋል ደግሞ የሰይጣንን ዘዴዎች ለመቋቋም የሚረዳንና ከጥበብ ጋር በጣም የሚቀራረብ ነው። ታላቁ ባለጋራ ዲያብሎስ የተንኮል ድርጊቶቹን ሲፈጽም ባካበተው የብዙ ሺህ ዓመት ልምድ ይጠቀማል። እኛ ግን ከልምድ የተሻለ ሊያስተምረን የሚችል ነገር አለን። ይህም ትክክለኛ የሆነውን ከተሳሳተው የመለየትና የምንሄድበትን ትክክለኛ መንገድ የመምረጥ ችሎታ እንዲኖረን የሚያደርገው አምላካዊ ማስተዋል ነው። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚያስተምረን ይህን ማስተዋል ነው። — ምሳሌ 2:10–13፤ ኤፌሶን 6:11
13. አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ባለባቸው ጊዜያት ምን ሊጠብቀን ይችላል? እንዴትስ?
13 በዛሬው ዓለም ውስጥ የሚታየው የኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ለሚከተለው በሕዝቅኤል 7:19 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መንገድ ጠራጊ ነው:- “ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጉድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም።” በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ቁሳዊ ሀብት ጥበብና ማስተዋል ካላቸው የማዳን ኃይል ጋር አይወዳደርም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በሌላም ሥፍራ “ጥበብም እንደ ገንዘብ ለጥበቃ ያገለግላል። የዕውቀት ብልጫ ግን ጥበብ ባለቤትዋ ያደረጋትን ሕይወት መጠበቅዋ ነው” ሲል ገልጿል። (መክብብ 7:12 አዓት) ዛሬም አስደሳች በሆኑት የይሖዋ መንገዶች የሚሄዱና “ረጅም ዘመን” ማለትም አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሚያምን ለማንኛውም ሰው የሰጠውን የዘላለም ሕይወት የመረጡ ሁሉ በእርግጥም ደስተኞች ናቸው! — ምሳሌ 3:16፤ ዮሐንስ 3:16፤ 17:3
እውነተኛውን ጥበብ መኮትኮት
14. ይሖዋ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ጥበብ ያሳየው በምን መንገዶች ነው?
14 እኛ በአምላክ አምሳል የተፈጠርን፣ ሰዎች ይሖዋ አስደናቂ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ ያሳያቸውን የጥበብና የማስተዋል ባሕርያት ለመኮትኮት መጣራችን ተገቢ ነው። “እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፣ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።” (ምሳሌ 3:19, 20) ከዚያም ቀጥሎ ሕያዋን ፍጥረታትን ሊታወቅ በማይችልና ምሥጢራዊ በሆነ የዝግመተ ለውጥ ሂደት ሳይሆን ጥበብ ለተሞላበት ዓላማ በቀጥታ “እንደየ ወገኑ” ፈጠረ። (ዘፍጥረት 1:25) በመጨረሻም ሰው ከእንሰሳት በጣም የላቀ አእምሮና ችሎታዎች እንዲኖረው ተደርጎ በተፈጠረ ጊዜ የአምላክ መላእክታዊ ልጆች ጭብጨባ በሰማይ ከዳር እስከ ዳር አስተጋብቶ መሆን አለበት። (ከኢዮብ 38:1, 4, 7 ጋር አወዳድር።) የይሖዋ አርቆ አስተዋይነት፣ ጥበቡና ፍቅሩ በምድር ላይ ባሉት ሥራዎቹ ሁሉ በግልጽ ታይቷል። — መዝሙር 104:24
15. (ሀ) ጥበብን መኮትኮት ብቻ በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ምሳሌ 3:25, 26 ምን ትምክህት እንዲኖረን ያደርጋል?
15 የይሖዋን የጥበብና የማስተዋል ባሕርያት ከመኮትኮት በተጨማሪ እነዚህን ባሕርያት አጥብቀን ለመያዝ የአምላክን ቃል በትጋት ማጥናት ያስፈልገናል። ይሖዋ እንዲህ ሲል ያስጠነቅቀናል:- “ልጄ ሆይ፣ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፣ ለአንገትህም ሞገስ።” (ምሳሌ 3:21, 22) እንዲህ ካደረግን በሰይጣን ዓለም ላይ በሚፈነዳውና እንደ ሌባ ሆኖ በሚመጣው ‘ድንገተኛ የጥፋት’ ቀን እንኳን በጸጥታና በእርጋታ ልንመላለስ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3) በራሱ በታላቁ መከራ ወቅትም “ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፣ ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናል፣ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና።” — ምሳሌ 3:23–26
መልካም ለማድረግ ያለህ ፍቅር
16. ክርስቲያኖች በአገልግሎቱ ቀናተኛ ከመሆን በተጨማሪ ምን ተግባር ይፈለግባቸዋል?
16 ይህ የምንኖርበት ዘመን የመንግሥቱን ምሥራች ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን በቅንዓት የምንሰብክበት ጊዜ ነው። ይሁን እንጂ በምሳሌ 3:27, 28 ላይ ቀጥሎ እንደተገለጸው ይህ የምስክርነት ሥራ በሌሎች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችም መደገፍ አለበት። “ለተቸገረ ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል፣ ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን። ወዳጅህን:- ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ አትበለው፣ በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ።” (ከያዕቆብ 2:14–17 ጋር አወዳድር።) አብዛኛው ዓለም በድህነትና በረሐብ ተጠፍሮ ስለተያዘ ሰዎችን ሁሉ በተለይም መንፈሳዊ ወንድሞቻችንን በአስቸኳይ እንድንረዳ የሚያስገድድ ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ረገድ የይሖዋ ምስክሮች ምን አድርገዋል?
17-19. (ሀ) በ1993 ምን አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ ቀርቦ ነበር? ምን ምላሽስ ተሰጠ? (ለ) ችግር የደረሰባቸው ወንድሞቻችንን ችግሮቻቸውን በድል አድራጊነት በመወጣት ላይ እንደሚገኙ የሚያሳየን ምንድን ነው?
17 አንድ ምሳሌ እንውሰድ:- ባለፈው ዓመት ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አንድ አስቸኳይ የእርዳታ ጥሪ ቀርቦ ነበር። በጎረቤት አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች በአስደናቂ ሁኔታ ደርሰውላቸዋል። ባለፈው ቀዝቃዛ የክረምት ወራት በርካታ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ የጭነት መኪናዎች የጦርነት ቀጠናዎችን ሰንጥቀው ወቅታዊ ጽሑፎች፣ ብርድ ልብሶች፣ ምግብና መድኃኒቶችን በችግር ላይ ለነበሩት ምስክሮች ለማድረስ ችለዋል። አንድ ጊዜ ወንድሞች 150 ኩንታል የእርዳታ ቁሳቁሶች ለማስገባት ድንበር ላይ የይለፍ ፈቃድ እንዲሰጣቸው አመለከቱ። ይሁን እንጂ የይለፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ለ300 ኩንታል ነበር። በኦስትሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ተጨማሪ ሦስት የጭነት መኪናዎች በአስቸኳይ ላኩ። በአጠቃላይ 250 ኩንታል የሚያህል የእርዳታ ቁሳቁስ ወደተፈለገው ቦታ ደረሰ። ወንድሞቻችን ይህን የተትረፈረፈ መንፈሳዊና ቁሳዊ እርዳታ ሲቀበሉ እንዴት ተደስተው ይሆን!
18 እርዳታውን የተቀበሉት ወንድሞች እንዴት ተሰማቸቸው? በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በሳሪየቮ የሚኖሩ ወንድሞችና እኅቶች ደህና ናቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ በዚህ የእብደት ጦርነት ለመጽናት የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ አለን። በምግብ ረገድ ከፍተኛ ችግር አለ። ላደረጋችሁልን ጥረት ሁሉ ይሖዋ ይባርካችሁ፤ ብድራችሁንም ይክፈላችሁ። የይሖዋ ምስክሮች ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አኗኗር ስላላቸውና ባለ ሥልጣኖችን ስለሚያከብሩ ባለ ሥልጣኖች በልዩ ሁኔታ ያከብሩአቸዋል። በተጨማሪም ለላካችሁልን መንፈሳዊ ምግብ በጣም እናመሰግናችኋለን።” — ከመዝሙር 145:18 ጋር አወዳድር።
19 እነዚህ አደጋ ላይ ወድቀው የነበሩ ወንድሞች አድናቆታቸውን ቅንዓት በተሞላበት የመስክ አገልግሎት አሳይተዋል። ከጎረቤቶቻቸው ብዙዎቹ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያደርጉላቸው ይጠይቋቸዋል። 50 ኩንታል የእርዳታ ምግብ በደረሰባት በቱዝላ ከተማ በጉባኤው ውስጥ ያሉት 40 አስፋፊዎች በወሩ ውስጥ እያንዳንዳቸው በአማካኝ 25 ሰዓት እንዳገለገሉ ሪፖርት አድርገዋል። በዚያው ጉባኤ ውስጥ ለሚገኙት 9 አቅኚዎች ጥሩ ድጋፍ ሰጥተዋል። በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ 243 ሰዎች ተገኝተው ነበር። እነዚህ የተወደዱ ወንድሞች በእርግጥም ‘በወደደን በእርሱ ሙሉ በሙሉ አሸናፊዎች እየሆኑ ነው።’ — ሮሜ 8:37
20. በቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ምን ‘እኩልነት’ ተከናወነ?
20 በቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት የሚኖሩ ወንድሞች ብዙ ጭነት የእርዳታ ምግብና ብርድ ልብስ በመላክ ከተደረገላቸው ልግስና ጋር የሚመጣጠን ቅንዓት አሳይተዋል። ለምሳሌ በሞስኮ በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር 7,549 ነበር። ባለፈው ዓመት ከነበረው ከ3,500 ጋር ሲወዳደር በጣም ከፍተኛ ቁጥር ነው። በዚሁ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ጉባኤዎች ቁጥር ከ12 ወደ 16 ከፍ ብሏል። በመላው የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት (የቦልቲክ አገሮችን ሳይጨምር) በጉባኤዎች 14 በመቶ፣ በመንግሥቱ አስፋፊዎች 25 በመቶ እና በአቅኚዎች 74 በመቶ ጭማሪ ተገኝቷል። እንዴት ያለ የቅንዓትና ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ነው! በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን ‘እኩልነት’ ያስታውሰናል። መንፈሳዊና ቁሳዊ ንብረቶች የነበሯቸው ክርስቲያኖች ችግር ባለባቸው ቦታዎች ላሉት በልግስና ሰጥተዋል። እነዚህ ተቸግረው የነበሩት ክርስቲያኖች ያሳዩት ቅንዓት ደግሞ እርዳታ ላደረጉት ወንድሞችና እኅቶች ደስታና ማበረታቻ አምጥቶላቻዋል። — 2 ቆሮንቶስ 8:14
ክፉውን ጥላ!
21. በምሳሌ ምዕራፍ 3 የመዝጊያ ቃላት ላይ ጥበበኞችና ሰነፎች የተነጻጸሩት እንዴት ነው?
21 የምሳሌ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ የሚከተለውን ምክር በመስጠት ይደመድማል:- “በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ፣ እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ። ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ፣ እርሱ ክፉ ካልሠራብህ። በግፈኛ ሰው አትቅና፣ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። የእግዚአብሔር መርገም በኀጥእ ቤት ነው፣ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። በፌዘኛ እርሱ ያፌዛል፣ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ የሰነፎች ከፍታቸው ግን መዋረድ ነው።” — ምሳሌ 3:29–35
22. (ሀ) ከሰነፎች ጋር ከመቆጠር ለመራቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ጥበበኞች የሚጠሉት ምንን ነው? ምንን ይኮተኩታሉ? ምንስ ሽልማት ያገኛሉ?
22 ከሰነፎች ጋር ከመቆጠር ለመራቅ የምንችለው እንዴት ነው? ክፉ የሆነውን መጥላትን መማር አለብን። አዎን፣ ይሖዋ የሚጸየፋቸውን ተጸየፍ፤ የዚህን ደም አፍሳሽ የሆነ ዓለም ተንኮል ተጸየፍ። (በተጨማሪም ምሳሌ 6:16–19ን ተመልከት።) በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ የሆነውን ማለትም ቅንነትን፣ ጽድቅንና የዋህነትን መኮትኮት አለብን። እንዲህ ካደረግን በትሕትናና ይሖዋን በመፍራት “ባለጠግነት ክብር ሕይወትም” ልናገኝ እንችላለን። (ምሳሌ 22:4) ይህም “በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን” የሚለውን ማሳሰቢያ በታማኝነት ሥራ ላይ ለምናውል ሁሉ የሚሰጥ የታማኝነት ሽልማት ይሆናል።
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ የዚህ ጥናት መልእክት የተመሠረተበት ጥቅስ በዛሬው ጊዜ የሚሠራው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋን ልናከብር የምንችለው እንዴት ነው?
◻ ተግሣጽን ማቃለል የማይኖርብን ለምንድን ነው?
◻ ትልቅ ደስታ የሚገኘው ከየት ነው?
◻ ጥሩውን ልንወድና ክፉውን ልንጠላ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምርጣቸውን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡ የተትረፈረፈ በረከት ያገኛሉ