ጥበብን አግኝ ተግሣጽንም ተቀበል
ይሖዋ አምላክ የሕዝቡ ታላቅ አስተማሪ ነው። ስለ ራሱ ብቻ ሳይሆን ስለ ሕይወትም ያስተምራቸዋል። (ኢሳይያስ 30:20፤ 54:13፤ መዝሙር 27:11) ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር አስተማሪ ሆነው እንዲያገለግሉ ነቢያትን፣ ሌዋውያንን በተለይ ደግሞ ካህናትንና ጠቢባንን ሰጥቶ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 35:3፤ ኤርምያስ 18:18) ነቢያት ስለ አምላክ ዓላማዎችና ስለ ባሕርያቱ ሕዝቡን በማስተማር ሊከተሉት የሚገባቸውን ትክክለኛ ጎዳና ያመለክቷቸዋል። ካህናትና ሌዋውያን የይሖዋን ሕግ የማስተማር ኃላፊነት ነበረባቸው። ጠቢባን ሰዎች ወይም ሽማግሌዎች ደግሞ ከዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ምክር ይሰጡ ነበር።
የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ከእስራኤል ጠቢባን ሰዎች መካከል ጎልቶ የሚታይ ሰው ነበር። (1 ነገሥት 4:30, 31) ዕውቅ ከሆኑት ጎብኚዎቹ መካከል አንዷ የነበረችው የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ክብርና ብልጥግና ከተመለከተች በኋላ “እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል” በማለት ተናግራለች። (1 ነገሥት 10:7) ሰሎሞን ያን ሁሉ ጥበብ ከየት አገኘው? በ1037 ከዘአበ የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ ሰሎሞን “ጥበብንና እውቀትን” ለማግኘት ጸልዮ ነበር። ይሖዋ በጥያቄው በመደሰት እውቀትን፣ ጥበብንና አስተዋይ ልቦናን ሰጠው። (2 ዜና መዋዕል 1:10-12፤ 1 ነገሥት 3:12) ሰሎሞን “ሦስት ሺህ ምሳሌዎች” መናገር መቻሉ ምንም የሚያስደንቅ አይደለም! (1 ነገሥት 4:32) ከእነዚህ ምሳሌዎች መካከል ጥቂቶቹ “አጉር” እና ‘ንጉሥ ልሙኤል’ ከተናገሯቸው ምሳሌዎች ጋር ተዳምረው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረዋል። (ምሳሌ 30:1፤ 31:1) በእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ የሰፈሩት እውነቶች የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቁ ከመሆናቸውም በላይ ጊዜ የማይሽራቸው ናቸው። (1 ነገሥት 10:23, 24) እነዚህ ምሳሌዎች መጀመሪያ ሲነገሩ ጠቃሚ የነበሩትን ያህል ዛሬም ደስተኛና የተሳካ ሕይወት መምራት ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው እጅግ ጠቃሚ ናቸው።
ስኬትና የሥነ ምግባር ንጽሕና—እንዴት?
የምሳሌ መጽሐፍ ዋነኛ ዓላማ በመክፈቻ ቃላቱ ውስጥ ተብራርቷል። “የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤ ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ፣ የእውቀትንም ቃል ለማስተዋል፣ የጥበብን ትምህርት ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንም ለመቀበል፣ ብልሃትን ለአላዋቂዎች ይሰጥ ዘንድ ለጐበዛዝትም እውቀትንና ጥንቃቄን።”—ምሳሌ 1:1-4
“የሰሎሞን ምሳሌዎች” ምንኛ የላቀ ዓላማ ያላቸው ናቸው! “ጥበብንና ተግሣጽን ለማወቅ” ለሚፈልግ ሰው የተነገሩ ናቸው። ጥበብ የነገሮችን ምንነት ያገናዝብና ባገኘው መረጃ ላይ በመመርኮዝ ችግሮችን ይፈታል፣ ግቦች ላይ ይደርሳል፣ ራሱን ከአደጋ ይጠብቃል ወይም ይርቃል፤ ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ይረዳል። “በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ” ይላል አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “‘ጥበብ’ በዘዴ መኖርን የሚያመለክት ሲሆን ይህም ጥበብ የተሞላበት ምርጫ የማድረግና የተሳካ ሕይወት የመምራት ችሎታ ነው።” ጥበብን ማግኘት ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ምሳሌ 4:7
የሰሎሞን ምሳሌዎች ተግሣጽንም ይዘዋል። እንዲህ ያለው ማሠልጠኛ ያስፈልገናል? ተግሣጽ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የእርማትን፣ የወቀሳን ወይም የቅጣትን መንፈስ ያስተላልፋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዳሉት ተግሣጽ “የሞኝ ድርጊት ወደመፈጸም እያመራ ያለን ሰው እርማት በመስጠት ተፈጥሯዊ ሥነ ምግባሩን ማሠልጠንን ያመለክታል።” ራስን በራስ መገሠጽም ይሁን ሌሎች ሰዎች የሚሰጡት ተግሣጽ መቀበል መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም እንድንታቀብ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ለውጥ እንድናደርግ ያነሳሳናል። አዎን፣ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን ለመኖር ከፈለግን ተግሣጽ መቀበል ይኖርብናል።
ስለዚህ የምሳሌ መጽሐፍ ድርብ ዓላማ አለው፤ ጥበብን መስጠትና ተግሣጽን ማስተማር። ሥነ ምግባራዊ ሥልጠናና የማመዛዘን ችሎታ የተለያዩ ገጽታዎች አሏቸው። ለምሳሌ ያህል ጽድቅና ፍትሕ የሥነ ምግባር ባሕርያት ሲሆኑ ይሖዋ ካወጣቸው ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተጣብቀን እንድንኖር ይረዱናል።
ጥበብ እውቀትን፣ ማስተዋልን፣ ብልህነትንና የማሰብ ችሎታን ጨምሮ የብዙ ነገሮች ጥምረት ነው። ማስተዋል አንድን ነገር በጥልቀት የመመልከትና የነገሩን ምንነት ለማወቅ የተለያዩ ክፍሎቹ እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነትና አጠቃላዩን ይዘት በማወቅ መዋቅሩን የመረዳት ችሎታ ነው። ማስተዋል በምክንያት ላይ የተመሠረተ እውቀት ሲሆን አንድ አካሄድ ትክክል ወይም ስህተት የሆነበትን ምክንያት የመረዳት ችሎታ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ አስተዋይ የሆነ ሰው አንድ ሰው ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እያመራ እንዳለ ሊያውቅና በዚያ አቅጣጫ መጓዝ ስለሚያስከትለው አደጋ ቶሎ ብሎ ሊያስጠነቅቀው ይችላል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ በዚያ አቅጣጫ ለምን እያመራ እንዳለና ግለሰቡን ለመታደግ የሚያስችል ውጤታማ የሆነ መፍትሔ ማቅረብ እንዲችል የሚረዳው ማስተዋል ነው።
ብልህ የሆኑ ሰዎች አርቀው ስለሚመለከቱ በቀላሉ አይታለሉም። (ምሳሌ 14:15) አንድን መጥፎ ነገር ቀደም ብለው ሊገነዘቡና ዝግጁ ሆነው ሊጠብቁ ይችላሉ። እንዲሁም ጥበብ ሕይወታችንን በዓላማ መምራት እንችል ዘንድ ጤናማ የሆኑ አስተሳሰቦችንና ሐሳቦችን እንድናፈልቅ ያስችለናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ምሳሌዎች ጥበብንና ተግሣጽን ማወቅ እንችል ዘንድ የተመዘገቡልን በመሆናቸው በእርግጥም ጠቃሚያችን ናቸው። ሌላው ቀርቶ “ተሞክሮ የጎደለው” ሰው ትኩረት ሰጥቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ከተከታተለ ብልህ እንዲሆን፣ ወጣት ከሆነ ደግሞ እውቀትንና የማስተዋል ችሎታን እንዲያገኝ ይረዳዋል።
ለጠቢባን የሚሆኑ ምሳሌዎች
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምሳሌዎች የሚጠቅሙት ተሞክሮ የሌላቸውን ወይም ወጣቶችን ብቻ አይደለም። በማዳመጥ ረገድ ጥበበኛ ለሆነ ሰው ሁሉ ይጠቅማሉ። “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል፣ አስተዋይም መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል፣ ምሳሌንና ትርጓሜን የጠቢባንን ቃልና የተሸሸገውን ነገር [ያስተውላል]” በማለት ሰሎሞን ተናግሯል። (ምሳሌ 1:5, 6) ቀደም ብሎ ጥበብን የገበየ አንድ ግለሰብ ለምሳሌዎች ትኩረት በመስጠት የእውቀት አድማሱን ያሰፋል እንዲሁም አስተዋይ ሰው ኑሮውን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት ይችል ዘንድ ችሎታውን ከፍ ያደርግለታል።
አንድ ምሳሌ ጥቂት ቃላትን በመጠቀም ጥልቅ እውነትን ይገልጻል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ አመራማሪ በሆኑ አነጋገሮች የተቀናበረ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 1:17-19) አንዳንድ ምሳሌዎች ትርጉማቸው ካልተገለጠ ለመረዳት የሚያስቸግሩና ግራ የሚያጋቡ አረፍተ ነገሮችን የያዙ የዕንቆቅልሽ ዓይነት ይዘት ያላቸው ናቸው። አንድ ምሳሌ ንጽጽሮች፣ አባባሎችና ሰም ለበስ አነጋገሮች ሊኖሩት ይችላል። እነዚህን ለመረዳት ማሰላሰልና ጊዜ ይጠይቃል። ብዙ ምሳሌዎችን ያጠናቀረው ሰሎሞን የአንድን ምሳሌ ትርጉም የመረዳት ችሎታ ነበረው። ይህንንም ችሎታ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ለአንባቢዎቹ ያሰፈረላቸው በመሆኑ አንድ ጠቢብ ትኩረት ሰጥቶ ከተከታተለ ያንን ችሎታ ማግኘት ይችላል።
ወደ ግብ የሚያደርስ ጅምር
አንድ ሰው ጥበብንና ተግሣጽን ለመከታተል መጀመር የሚኖርበት ከየት ነው? ሰሎሞን “የጥበብ [“የእውቀት፣” NW] መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ሰነፎች ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ” በማለት መልሱን ይሰጣል። (ምሳሌ 1:7) እውቀት የሚጀምረው ይሖዋን በመፍራት ነው። ያለ እውቀት ጥበብንም ሆነ ተግሣጽን ማግኘት አይቻልም። ስለዚህ ይሖዋን መፍራት ማለት የጥበብና የተግሣጽ መጀመሪያ ነው።—ምሳሌ 9:10፤ 15:33
አምላክን መፍራት ሲባል በፍርሃት መራድ ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ጥልቅ የሆነ አድናቆትና አክብሮታዊ ፍርሃት ማሳየት ማለት ነው። እንዲህ ያለ ፍርሃት ከሌለ እውነተኛ እውቀት ሊኖር አይችልም። ሕይወት የተገኘው ከይሖዋ አምላክ ሲሆን እውቀት ለመቅሰም ደግሞ በሕይወት መኖር የግድ አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 36:9፤ ሥራ 17:25, 28) ከዚህም በላይ የሁሉም ነገር ፈጣሪ አምላክ ነው፤ ስለዚህ የሰው ልጅ እውቀት የአምላክን የእጅ ሥራዎች በማጥናት ላይ የተመሠረተ ነው። (መዝሙር 19:1, 2፤ ራእይ 4:11) በተጨማሪም አምላክ “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅመው በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ አለልን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ስለዚህ የእውነተኛ እውቀት ሁሉ ዋነኛ መሠረት ይሖዋ ሲሆን አንድ ሰው ይህን እውቀት ለማግኘት ከፈለገ ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ሊኖረው ይገባል።
የሰው ልጅ ለአምላክ ፍርሃት ሳያሳድር እንዲሁ እውቀትና ዓለማዊ ጥበብ ማካበቱ ምን የሚፈይድለት ነገር ይኖራል? ሐዋርያው ጳውሎስ “ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 1:20) በዓለማዊ ጥበብ የተካነ አንድ ሰው አምላካዊ ፍርሃት ከሌለው ከሚታይ ማስረጃ በመነሳት የሚደርስበት መደምደሚያ የተሳሳተ ሊሆንና በመጨረሻም ‘እንደ ሞኝ’ ሊሆን ይችላል።
“ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና”
በመቀጠል ጠቢቡ ንጉሥ “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና” በማለት ወጣቶችን ይመክራል።—ምሳሌ 1:8, 9
በጥንቷ እስራኤል ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት ከአምላክ ተቀብለው ነበር። ሙሴ ለአባቶች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግም 6:6, 7) እናቶችም ቢሆኑ በዚህ ረገድ በቀላሉ የማይገመት አስተዋጽኦ ያበረክቱ ነበር። አንዲት ዕብራዊ ሚስት ከባሏ ሥልጣን ሳትወጣ ለቤተሰብ የተሰጡ ሕጎችን ማስፈጸም ትችል ነበር።
እንዲያውም ቤተሰብ ትምህርት የሚተላለፍበት መሠረታዊ ተቋም መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ይናገራል። (ኤፌሶን 6:1-3) ልጆች ለአማኝ ወላጆቻቸው ታዛዥ መሆናቸው በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚያምር የአበባ ጉንጉንና የክብር የአንገት ሐብል ይሆንላቸው ነበር።
“የባለቤቱን ነፍስ ይነጥቃል”
አንድ እስያዊ አባት የ16 ዓመት ወንድ ልጁን ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ከመላኩ በፊት ከመጥፎ ሰዎች ጋር እንዳይገጥም መከረው። ይህ ምክር ሰሎሞን “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል” የሚለውን ማስጠንቀቂያ የሚያስተጋባ ነው። (ምሳሌ 1:10) ሆኖም ሰሎሞን የሚያባብሉበትንም ስውር ዘዴ እንዲህ በማለት ጠቁሟል:- “ደምን ለማፍሰስ ከእኛ ጋር ና እናድባ፣ ለንጹሕም ያለ ምክንያት ወጥመድን እንሸምቅበት [ይላ]ሉ፤ በሕይወታቸው ሳሉ እንደ ሲኦል ሆነን እንዋጣቸው፣ በሙሉም ወደ ጉድጓድ እንደሚወድቁ ይሁኑ፤ መልካሙን ሀብት ሁሉ እናገኛለን፣ ከምርኮውም ቤታችንን እንሞላለን፤ ዕጣህን ከእኛ ጋር ጣል፤ ለሁላችንም አንድ ከረጢት ይሁን [ይላሉ።]”—ምሳሌ 1:11-14
የሚያባብሉበት ስውር ዘዴ ሀብት መሆኑ ግልጽ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ “ኃጢአተኞች” የዓመፃቸው ወይም የግፍ ሥራቸው ተካፋይ እንዲሆኑ ሌሎችን ያባብላሉ። እነዚህ ክፉ ሰዎች ለቁሳዊ ጥቅም ሲሉ ደምን ከማፍሰስ ወደኋላ አይሉም። መቃብር መላ አካልን እንደሚውጥ ሁሉ ‘የጥቃታቸው ሰለባ የሆነውን ሰው’ ያለውን ሁሉ በመዝረፍና ሙልጭ በማስቀረት ልክ ‘እንደ ሲኦል በሕይወት ሳለ ይውጡታል።’ ሰዎች የወንጀል ሥራን ሙያዬ ብለው እንዲይዙ በመጋበዝ ‘በምርኮ ቤታቸውን ለመሙላት’ ይፈልጋሉ። እንዲሁም ተሞክሮ የሌለው ሰው ‘ከእነርሱ ጋር ዕጣ ፈንታውን’ እንዲያደርግ ይፈልጋሉ። ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ወቅታዊ ማስጠንቀቂያ ነው! በአሁኑ ጊዜ ያሉት ወጣት ዱርዬዎችና አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ሌሎችን ለመመልመል የሚጠቀሙበት ዘዴ ይኸው አይደለም? ብዙ ሰዎች አጠያያቂ በሆነ የንግድ አንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሃብታም የመሆን ተስፋ አይደለምን?
“ልጄ ሆይ፣ ከእነርሱ ጋር በመንገድ አትሂድ፣ ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ፤ እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉና፣ ደም ለማፍሰስም ይፈጥናሉና። መርበብ በወፎች ዓይን ፊት በከንቱ ትተከላለችና። እነርሱም በደማቸው ላይ ያደባሉ፣ በነፍሳቸውም ላይ ይሸምቃሉ። እንዲሁ ይህ መንገድ ትርፍን ለማግኘት የሚሳሳ ሁሉ ነው። የባለቤቱን ነፍስ ይነጥቃል።”—ምሳሌ 1:15-19
‘የማይገባ ትርፍ ለማግኘት የሚቋምጥ ሁሉ’ በራሱ አካሄድ ይጠፋል። ክፉዎች ሌሎችን ለማጥመድ የሚያስቀምጡት ወጥመድ መልሶ ራሳቸውን ይይዛቸዋል። ሆነ ብለው ክፉ የሚሠሩ ከአካሄዳቸው ይመለሱ ይሆን? በጭራሽ። አንድ መረብ ግልጽ በሆነ ቦታ ላይ ቢቀመጥም ወፎች በቀጥታ ወደ መረቡ መሄዳቸውን አይተዉም። በተመሳሳይም በስግብግብነት ዓይናቸው የታወሩ ክፉዎች ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ በወጥመድ ውስጥ መግባታቸው ባይቀርም የወንጀል ድርጊት ከመፈጸም ፈጽሞ ወደኋላ አይሉም።
የጥበብን ድምፅ የሚሰማ ማን ነው?
ኃጢአተኞች በእርግጥ ወደ ጥፋት እየሄዱ እንዳሉ ያውቃሉ? አካሄዳቸው ስለሚያስከትልባቸው ጉዳት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ይሆን? ግልጽ የሆነ መልእክት በአደባባይ እየተነገረ ስለሆነ አላወቁም ነበር የሚለው ምክንያት ፈጽሞ ተቀባይነት አይኖረውም።
ሰሎሞን እንዲህ አለ:- “ጥበብ በጎዳና ትጮኻለች፤ በአደባባይ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤ በአደባባይ ትጣራለች፤ በከተማይቱ መግቢያ በር ቃልን ትናገራለች።” (ምሳሌ 1:20, 21) ጥበብ ሁሉም መንገደኛ መስማት በሚችልበት መጠን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ትጮሃለች። በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ሽማግሌዎች በከተማዋ መግቢያ ላይ ሆነው ጥበብ የሞላበት ምክር ይለግሱ እንዲሁም ፍርድ ይሰጡ ነበር። ለእኛ ደግሞ ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛ ጥበብ አስመዝግቦ በስፋት እንዲሰራጭ አድርጓል። እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ያሉ አገልጋዮቹ ይህንን መልእክት በሁሉም ቦታ ለሚገኙ ሰዎች በአደባባይ እያወጁ ናቸው። በእርግጥም አምላክ ለሁሉም ሰው ጥበብ እንዲነገር በማድረግ ላይ ነው።
ታዲያ እውነተኛ ጥበብ ምን እያለች ነው? እንዲህ እያለች ነው:- “እናንት አላዋቂዎች፣ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? ፌዘኞችም ፌዝን ይፈቅዳሉ? . . . በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፣ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም [አላስተዋለም።]” ሰነፎች ጥበብ የምታሰማውን ድምፅ ለመስማት ፈቃደኞች አይደሉም። በዚህም የተነሳ “የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ።” ‘ከጥበብ መራቃቸውና ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል።’ —ምሳሌ 1:22-32
ይሁን እንጂ ጊዜ ወስዶ ጥበብ የምታሰማውን ድምፅ ያዳመጠ ምን ነገር ያገኛል? “በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።” (ምሳሌ 1:33) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ምሳሌዎች በጥንቃቄ በመከታተል ጥበብን ከሚያገኙና ተግሣጽን ከሚቀበሉ ሰዎች መካከል ያድርጋችሁ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ጥበብ በስፋት ይገኛል