በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽህናህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ
እሱ ጥቁር መልከ መልካም ነው። እሷ ጥሩ ተሰጥዎ ያላት ቆንጆ ሴት ናት። ሁለቱም አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ይሠራሉ። የተለየ አሳቢነት ታሳየዋለች። እሱም ለእሷ ያለውን አድናቆት ይገልጽላታል። ስጦታም ይለዋወጣሉ። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ፍቅረኛሞች ሆኑ። እሷን ብሎ ሚስቱን ተወ። በመጨረሻ እሷ ባሏን ላለመተውና በሁለቱ መካከል የተመሠረተው ፍቅር በዚሁ እንዲቋጭ ወሰነች። እሱም ልቡ እንደተከፈለ ከሚስቱ ጋር ለመታረቅ ሞከረ። ይሁን እንጂ ጸጸቱ ልባዊ ስላልነበረ አልተሳካለትም። ምንም እንኳ ሁሉም የየራሳቸውን ሕይወት መምራት ቢችሉም ስሜታቸው መጎዳቱ አልቀረም።
በዚህ ዓለም ውስጥ የጾታ ሥነ ምግባርን መጠበቅ አበጀ የሚያሰኝ ባሕርይ መሆኑ ቀርቷል። የዘመኑ ፈሊጥ ያለ አንዳች ቁጥብነት ደስታንና እርካታን ማሳደድ ሆኗል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “ዝሙት የትም ያለ ነገር እየሆነ የመጣ ይመስላል፤ እንዲያውም በአንዳንድ መልኩ የትዳርን ያክል የተለመደ ሆኗል” በማለት ይናገራል።
ሆኖም ይሖዋ አምላክ ትዳር “በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ” እንዲሆን ይፈልጋል። (ዕብራውያን 13:4) ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚከተለው በማለት ያሳስባሉ:- “አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ስለዚህ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን በሥነ ምግባር በረከሰው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር ያስፈልገናል።
በዙሪያችን ካለው በካይ ተጽዕኖ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ 5ኛ ምዕራፍ ላይ መልሱን ሰጥቷል። እስቲ የሚለንን እንመርምር።
የማሰብ ችሎታ ይጠብቅሃል
የእስራኤል ንጉሥ “ልጄ ሆይ፣ ለጥበቤ ልብህን ስጥ፤ ” በማለት ይጀምራል። አክሎም እንዲህ አለ:- “የማሰብ ችሎታን ትጠብቅ ዘንድ ወደ ማስተዋሌ ጆሮህን አዘንብል፤ ከንፈሮችህም እውቀትን ይጠብቁ።”—ምሳሌ 5:1, 2 NW
የሥነ ምግባር ብልግና ወደ መፈጸም የሚገፋፉ ፈተናዎችን ለመቋቋም ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውቀት በሥራ የመተርጎም ችሎታ የሆነው ጥበብ እንዲሁም መልካሙን ከክፉው ለይተን ትክክለኛውን አቅጣጫ እንድንመርጥ የሚረዳን ችሎታ ይኸውም ማስተዋል ያስፈልገናል። የማሰብ ችሎታችንን መጠበቅ እንችል ዘንድ ለጥበብና ማስተዋል ትኩረት እንድንሰጥ በጥብቅ ተመክረናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ማስተዋል እንዲሁም ፈቃዱንና ዓላማውን ለመረዳት ጆሯችንን ማዘንበል ያስፈልገናል። እንዲህ በማድረግ አስተሳሰባችን ፈር እንዳይለቅቅ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመምራት ያስችለናል። በዚህ መንገድ የሚገኝ የማሰብ ችሎታ ከአምላካዊ ጥበብና እውቀት ጋር ይስማማል። ይህን ችሎታ በሚገባ ከተጠቀምንበት ለብልግና በሚያነሳሱ ማባበያዎች አንታለልም።
በሽንገላ እንዳትታለል ተጠንቀቅ
በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽሕናን ጠብቆ ለመኖር የማሰብ ችሎታ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው የሚከተለው መንገድ አሳሳች ስለሆነ ነው። ሰሎሞን እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፣ አፍዋም ከቅቤ [“ከዘይት፣” የ1980 ትርጉም ] የለሰለሰ ነውና፤ ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፣ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም የተሳለ ነው።”—ምሳሌ 5:3, 4
በዚህ ምሳሌ ውስጥ ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት ‘በጋለሞታ’ ወይም በዝሙት አዳሪ ተመስላለች። ሰለባዋን ለማጥመድ የምትጠቀምባቸው ቃላት ከማር ወለላ ይጣፍጣሉ፣ ከወይራ ዘይት ይልቅም ይለሰልሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም የሚጋብዙ ሁኔታዎች የሚጀምሩት በዚህ መንገድ አይደለምን? ለምሳሌ ያህል በጸሐፊነት የምትሠራ ኤሚ የምትባል አንዲት የ27 ዓመት ቆንጆ ያጋጠማትን ሁኔታ ተመልከት። እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “የሥራ ባልደረባዬ የሆነው ይህ ሰው ለእኔ ልዩ ትኩረት እንዳለው ከማሳየቱም በላይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያሞግሰኛል። የሌሎችን ትኩረት ማግኘቱ ደስ ያሰኛል። ሆኖም እኔን የፈለገኝ ለጾታ ግንኙነት ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነበር። እኔ እንደሆንኩ ለእሱ የቃላት መደለያ እጄን አልሰጥም።” የተነገሩበትን ዋነኛ ዓላማ ለይተን ካላወቅን በስተቀር አንድ አታላይ ወንድ ወይም አንዲት አታላይ ሴት ለሽንገላ የሚጠቀሙባቸው ቃላት በአብዛኛው ማራኪ ናቸው። ይህን ለማድረግ የማሰብ ችሎታችንን ማዳበር ያስፈልገናል።
የሥነ ምግባር ብልግና የሚያስከትለው መዘዝ እንደ እሬት የመረረ እንዲሁም በሁለት ወገን ከተሳለ ሰይፍ ይልቅ ስል በመሆኑ ወደ ከፍተኛ ሥቃይ ብሎም ወደ ሞት የሚመራ ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት ብዙውን ጊዜ የህሊና ወቀሳ፣ ያልተፈለገ እርግዝና ወይም በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች እንደመለከፍ ያሉ መራራ መዘዞችን ያስከትላል። እንዲሁም ታማኝ ያልሆነው ወገን በትዳር ጓደኛው ላይ የሚያመጣውን ይህ ነው የማይባል የስሜት ቀውስ እስቲ አስበው። ለትዳር ጓደኛው ያለውን ታማኝነት የሚያጎድል ድርጊት መፈጸም ዕድሜ ልክ የማይሽር ቁስል ሊያስከትል ይችላል። አዎን፣ የሥነ ምግባር ብልግና ጉዳት አለው።
ጠቢቡ ንጉሥ ሥነ ምግባር ስለጎደላት ሴት አስተያየት ሲሰጥ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “እግሮችዋ ወደ ሞት ይወርዳሉ፣ አረማመድዋም ወደ ሲኦል ነው፤ የቀና የሕይወትን መንገድ አታገኝም፤ በአካሄድዋ የተቅበዘበዘች ናት፣ የሚታወቅም አይደለም። ” (ምሳሌ 5:5, 6) ሥነ ምግባር የጎደላት ሴት አካሄድ ወደ ሞት ማለትም የሰው ልጆች የጋራ መቃብር ወደ ሆነው ወደ ሲኦል ያደርሳታል። በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በተለይ ደግሞ ኤድስ እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ባለበት በዚህ ዘመን እነዚህ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! የእሷም ሆነ መጥፎ አካሄዷን የሚከተሉ ሰዎች መጨራሻቸው ተመሳሳይ ነው።
ንጉሡ ከልብ ተጨንቆ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጠ:- “አሁንም ልጆቼ ሆይ፣ ስሙኝ፣ ከአፌም ቃል አትራቁ። መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፣ ወደ ቤትዋም ደጅ አትቅረብ። ”—ምሳሌ 5:7, 8
ሥነ ምግባር የጎደላቸው ሰዎች ከሚያደርሱት ተጽዕኖ በተቻለ መጠን መራቅ ያስፈልገናል። ወራዳ ሙዚቃዎችን በማዳመጥ፣ በካይ የመዝናኛ ዓይነቶችን በመከታተል ወይም ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን በማንበብ እንዲሁም በመመልከት በገዛ እጃችን ለምን በር እንከፍትላቸዋለን? (ምሳሌ 6:27፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33፤ ኤፌሶን 5:3-5) እንዲሁም አጉል በመሽኮርመም ወይም ልከኛ ባልሆነ አለባበስና አጋጌጥ ትኩረታቸውን መጋበዝ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!—1 ጢሞቴዎስ 4:8፤ 1 ጴጥሮስ 3:3, 4
ከባድ ኪሳራ
ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ከሚከተለው መንገድ መራቅ ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? ሰሎሞን እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል:- “ክብርህ ለሌላ እንዳትሰጥ፣ ዕድሜህም ለጨካኝ፤ ሌሎች ከሀብትህ እንዳይጠግቡ፣ ድካምህም በባዕድ ሰው ቤት እንዳይሆን። በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ። ”—ምሳሌ 5:9-11
ሰሎሞን የሥነ ምግባር ብልግና ከባድ ኪሳራ እንደሚያስከትል አጉልቶ ተናግሯል። ዝሙትና ለራስ አክብሮት ማጣት የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም። ራስን ሥነ ምግባር ለጎደለው ሰው ወይም የራስ ፍላጎት ማርኪያ አድርጎ ማቅረብ ውርደት አይደለምን? የትዳር ጓደኛችን ካልሆነ ሰው ጋር ጾታዊ ቅርርብ መፍጠር ለራስ አክብሮት ማጣት እንደሆነ አያሳይምን?
‘ዕድሜያችንን፣ ሃብታችንንና የድካማችንን ፍሬ ለሌሎች ወይም ለባዕዳን መስጠትስ’ ምንን ይጨምራል? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “የእነዚህ ጥቅሶች ሐሳብ ግልጽ ነው:- ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትል ይሆናል፤ ምክንያቱም በሴትዮዋ ራስ ወዳድነት የሞላበት ፍላጎት ወይም በማኅበረሰቡ ዘንድ በፈጸመው ቅሌት ሳቢያ አንድ ሰው ሲደክምለት የኖረውን ክብር፣ ሥልጣን ወይም ሃብት ሊያጣ ይችላል።” ሥነ ምግባር የጎደለው ግንኙነት ከፍተኛ ኪሳራ ያመጣል!
ሞኝ የሆነ ሰው ክብሩን ካጣና ጥሪቱን ካሟጠጠ በኋላ እንዲህ በማለት በራሱ ላይ ክፉኛ ያማርራል:- “እንዴት ትምህርትን ጠላሁ፣ ልቤም ዘለፋን ናቀ! የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፣ ጆሮቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም። በማኅበርና በጉባኤ መካከል ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ። ”—ምሳሌ 5:12-14
የኋላ ኋላ ይህ ኃጢአተኛው ሰው አንድ ሃይማኖታዊ ምሁር እንዳሉት “ምነው እንዲህ ባላደረግሁ ኖሮ” የሚሉ ቃላትን ሲደረድር ይሰማል። “ምነው አባቴ የሚለኝን በሰማሁ ኖሮ፤ ምነው ራሴን በገዛሁ ኖሮ፤ ምነው የሌሎችን ምክር በሰማሁ ኖሮ።” ሆኖም ይህ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንደሚባለው ነው። በሥነ ምግባር የረከሰው ግለሰብ ሕይወት አንዴ ተበላሽቷል፤ መልካም ስሙም ጎድፏል። የሥነ ምግባር ብልግና በሚያስከትለው ማጥ ውስጥ ከመዘፈቃችን በፊት ኪሳራውን ማስላት ምንኛ ጠቃሚ ነው!
‘ከጉድጓድህ ውኃ ጠጣ’
ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾታ ግንኙነት ይናገራል እንዴ? እንዴታ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት እርስ በርስ ፍቅርን በመለዋወጥ የሚያገኙት እርካታ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የተፈቀደው በትዳር ለተቆራኙ ሰዎች ብቻ ነው። ስለዚህ ሰሎሞን ትዳር ለመሠረተ ወንድ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ከጉድጓድህ ውኃ፣ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ። ምንጮችህ ወደ ሜዳ፣ ወንዞችህ ወደ አደባባይ ይፈስሳሉን? ለአንተ ብቻ ይሁኑ፣ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ። ”—ምሳሌ 5:15-17
“ጉድጓድህ” እና “ምንጭህ” የሚሉት ቃላት ተወዳጅ ለሆነች ሚስት የገቡ ቅኔያዊ አገላለጾች ናቸው። ከእሷ ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ ውኃ ጠጥቶ ከመርካት ጋር ይመሳሰላል። ሕዝብ ከሚቀዳበት ቦኖ ይልቅ ጉድጓድ ወይም ምንጭ እንደ ግል ንብረት ይታያል። አንድ ሰው ከተለያዩ ሴቶች ከመውለድ በቤቱ ካለች ሚስቱ ልጆች እንዲያፈራ ተመክሯል። ስለዚህ ለወንድ የተሰጠው ምክር ለሚስትህ ታማኝ ሁን የሚል ነው።
ጠቢቡ ሰው ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “ምንጭህ ብሩክ ይሁን፤ ከጉብዝናህም ሚስት ጋር ደስ ይበልህ። እንደ ተወደደች ዋላ እንደ ተዋበችም ሚዳቋ፣ ጡትዋ ሁልጊዜ ታርካህ፣ በፍቅርዋም ሁልጊዜ ጥገብ። ”—ምሳሌ 5:18, 19
‘ምንጭ’ የሚለው ቃል በጾታ ግንኙነት የሚገኘውን እርካታ ያመለክታል። ከትዳር ጓደኛ ጋር የጾታ ግንኙነት በማድረግ የሚገኘው ደስታ “ብሩክ” ወይም ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። በዚህ ምክንያት አንድ ሰው ከጉብዝና ሚስቱ ጋር እንዲደሰት ምክር ተሰጥቶታል። እሷ ለእሱ እንደ ሴት ዋልያ ተወዳጅና ውብ እንዲሁም እንደ ሚዳቋ የደስ ደስ ያላት ናት።
ሰሎሞን ቀጥሎ መልስ የማያሻቸው ሁለት ጥያቄዎችን ያነሳል:- “ልጄ ሆይ፣ ስለ ምን ጋለሞታ ሴት ትወድዳለህ? የሌላይቱንስ ብብት ለምን ታቅፋለህ?” (ምሳሌ 5:20) አዎን፣ አንድ ባለትዳር በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሌላ በማንኛውም ቦታ ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር በጾታ ፍቅር ለምን ይሳሳባል?
ሐዋርያው ጳውሎስ ላገቡ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ምክር ይሰጣል:- “ዳሩ ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እናገራለሁ፣ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 7:29) ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል? መቼም የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ‘አስቀድመው መንግሥቱን መፈለግ’ አለባቸው። (ማቴዎስ 6:33) ስለዚህ ባልና ሚስቶች ስለ ትዳራቸው ብቻ በማሰብ ለመንግሥቱ ጉዳዮች ሁለተኛ ቦታ መስጠት የለባቸውም።
ራስን መግዛት ያስፈልጋል
የጾታን ስሜት መቆጣጠር ይቻላል። ይሖዋ እንዲቀበላቸው የሚፈልጉ ሰዎች የግድ ይህን ማድረግ አለባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ያሳስባል:- “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፣ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፣ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ [የራሱን ሰውነት] በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ [ይወቅ]።”—1 ተሰሎንቄ 4:3, 4
እንግዲያው ወጣቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የጾታ ስሜት ስለተሰማቸው ብቻ ቸኩለው ማግባት አይገባቸውም። ጋብቻ ቃል ኪዳን ውስጥ ያስገባል፤ የገቡትን ቃል ጠብቆ መኖር ደግሞ ብስለትን ይጠይቃል። (ዘፍጥረት 2:24) አንድ ሰው “ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ” እስኪደርስ ማለትም የጾታ ስሜቱ አይሎ የማመዛዘን ችሎታውን ሊያዛባ የሚችልበት ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ ቢጠብቅ የተሻለ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:36) ለአካለ መጠን ደርሶ ማግባት የሚፈልግ አንድ ሰው የትዳር ጓደኛ ስላላገኘ ብቻ የሥነ ምግባር ብልግና ቢፈጽም እንዴት ያለ ሞኝነትና ኃጢአት ነው!
‘ኃጢአተኛን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች’
የጾታ ብልግና ስሕተት የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ለሰዎች ሕይወትንም ሆነ በጾታ ስሜት የመርካት ችሎታን የሰጠው ይሖዋ የሚያወግዘው ነገር ስለሆነ ነው። ስለዚህ ንጉሥ ሰሎሞን ለሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ትልቅ ቦታ ሲሰጥ “የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና፣ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና” ብሏል። (ምሳሌ 5:21) አዎን፣ “እኛን በሚቆጣጠር” በአምላክ ፊት የሚሰወር ነገር የለም። (ዕብራውያን 4:13) ማንኛውም የጾታ ርኩሰት ምንም ያህል በምስጢር ቢፈጸም ወይም ምንም ዓይነት አካላዊና ማኅበራዊ መዘዝ ሊያስከትል ቢችል ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማበላሸቱ አይቀርም። ለጥቂት ደቂቃዎች ደስታ ሲባል ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ማደፍረስ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!
በእፍረተ ቢስነት የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ አንዳንድ ሰዎች ለጊዜው ከቅጣት የሚያመልጡ ይመስላቸዋል። ሰሎሞን እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “ኀጥኣንን ኃጢአቱ ታጠምደዋለች፣ በኃጢአቱም ገመድ ይታሰራል። አልተቀጣምና እርሱ ይሞታል፤ በስንፍናውም ብዛት ይስታል። ”—ምሳሌ 5:22, 23
ታዲያ ሁላችንም ብንሆን የምንስትበት ምን ምክንያት አለ? የምሳሌ መጽሐፍ ዓለም ከሚከተለው አሳሳች ጎዳና እንድንጠበቅ በቅድሚያ ያስጠነቅቀናል። እንዲሁም የጾታ ብልግና በጤናችን፣ ባለን ቁሳዊ ነገር፣ በጥንካሬያችንና በክብራችን ላይ ከባድ ኪሳራ እንደሚያስከትል ከወዲሁ ያስገነዝበናል። እንደዚህ ያለ አርቆ አስተዋይነት ካለን “ምነው እንዲህ ባላደረግሁ ኖሮ” ከሚለው ከንቱ ጸጸት አዎን፣ ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት ባስጻፈው ቃሉ አማካኝነት የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ በሥነ ምግባር በረከሰ ዓለም ውስጥ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሥነ ምግባር ብልግና የሚያስከትለው መዘዝ እንደ እሬት የመረረ ነው
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከጉብዝናህ ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ ”