መልካም ስምህን ጠብቅ
የሚያማምሩ የሕንፃ ዲዛይኖችን የሚያወጣ አንድ ሰው የተዋጣለት የስነ ሕንፃ ምሁር የሚል ስም ያተርፋል። አንዲት ወጣት በትምህርቷ ጥሩ ውጤት ካመጣች ጎበዝ ተማሪ ትባላለች። ሌላው ቀርቶ ሥራ ጠልቶ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ ሰውም ሰነፍ የሚል ስም ያተርፋል። መጽሐፍ ቅዱስ መልካም ስም የማትረፍን ዋጋማነት ከፍ አድርጎ ሲናገር “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፣ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” ይላል።—ምሳሌ 22:1
በጊዜ ሂደት በርካታ ትንንሽ ድርጊቶች አንድ ላይ ተዳምረው መልካም ስም ያተርፉልናል። ሆኖም ይህ መልካም ስም በአንድ አጉል ድርጊት በቀላሉ ሊበላሽ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው አንዴ እንኳ የጾታ ብልግና ቢፈጽም ቀደም ሲል ያተረፈው መልካም ስም ሙሉ በሙሉ ሊጎድፍ ይችላል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ ውስጥ መልካም ስማችንን ሊያጎድፉና ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሹብን ስለሚችሉ ዝንባሌዎችና ድርጊቶች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ከእነዚህ መካከል ቸኩሎ ዋስ መሆን፣ ስንፍና፣ አታላይነትና የጾታ ብልግና የሚገኙበት ሲሆን እነዚህ ይሖዋ የሚጠላቸው ነገሮች ናቸው። ይህን ምክር መስማትና መከተል መልካም ስማችን እንዳይጠፋ ለመጠበቅ ይረዳናል።
በችኮላ ዋስ ከሆንክበት ሁኔታ ራስህን አውጣ
የምሳሌ መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ልጄ ሆይ፣ ለጎረቤትህ ዋስ ብትሆን፣ ስለ ሌላ [“ስለማታውቀው፣” NW ] ሰው እጅህን አጋና ብትመታ፣ በአፍህ ቃል ተጠመድህ፤ በአፍህ ቃል ተያዝህ። ልጄ ሆይ፣ ይህን አድርግ ራስህንም አድን፣ በጎረቤትህ እጅ ወድቀሃልና፤ ፈጥነህ ሂድ፣ ጎረቤትህንም ነዝንዘው።”—ምሳሌ 6:1-3
ይህ ምሳሌ ከሌሎች በተለይ ከማያውቁት ሰው ጋር በንግድ ጉዳይ መጠላለፍ አደገኛ መሆኑን በተመለከተ ምክር ይሰጣል። አዎን፣ እስራኤላውያን ‘ወንድማቸው ቢደኸይና እጅ ቢያጥረው መደገፍ’ ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 25:35-38) ሆኖም አንዳንድ እስራኤላውያን አጠያያቂ በሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ዓይናቸውን ጨፍነው ይገቡና የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ሌሎች ‘ዋስ’ እንዲሆኗቸው በማግባባት ዕዳ ውስጥ ይከቷቸው ነበር። በአሁኑ ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ ያህል የገንዘብ ተቋማት የማያስተማምን መስሎ ከታያቸው ብድር ከመፍቀዳቸው በፊት ተያዥ ሊጠይቁ ይችላሉ። ቸኩሎ ለሌሎች ተያዥ መሆን እንዴት ያለ ጥበብ የጎደለው ድርጊት ነው! ሳናስበው በዕዳ ልንጠየቅ እንችላለን፤ አልፎ ተርፎም በባንኮች ወይም በሌሎች የብድር ተቋማት ዘንድ መጥፎ ስም ሊያሰጠን ይችላል!
መጀመሪያ ምንም ችግር የሌለበት መስሎን የገባንበት ጉዳይ በኋላ ላይ ጠለቅ ብለን ስንመረምረው ጣጣ ውስጥ እንደዘፈቀን ብንገነዘብስ? ለዚህ የተሰጠው ምክር ኩራትህን ዋጥ አድርገህ “ጎረቤትህን ነዝንዘው” የሚል ነው። ችግሩን ለመፍታት የቻልነውን ሁሉ ማድረግ ይገባናል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ዕዳው በአንተ ወይም በቤተሰብህ ላይ ከመውደቁ በፊት ተሟጋችህን አሳምነህ ሐሳቡን ለማስለወጥ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ” የሚል ምክር ይሰጣል። እንዲህ ለማድረግ መዘግየት የለብህም፤ ምክንያቱም ንጉሡ “ለዓይንህ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶችህም እንጉልቻን አትስጥ፣ እንደ ሚዳቋ ከአዳኝ እጅ፣ እንደ ወፍም ከአጥማጅ እጅ ትድን ዘንድ” በማለት አክሎ ተናግሯል። (ምሳሌ 6:4, 5) በተቻለ መጠን ወጥመድ ውስጥ ከመግባትህ በፊት ጥበብ የጎደለው እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ የተሻለ ነው።
እንደ ጉንዳን ታታሪ ሁን
ሰሎሞን “አንተ ታካች፣ ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፣ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን” በማለት አጥብቆ ይመክራል። ትንሽ የሆነችው ጉንዳን ከምታደርገው ነገር ምን ጥበብ ማግኘት እንችላለን? ንጉሡ “አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች፣ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች ” በማለት መልስ ይሰጣል።—ምሳሌ 6:6-8
ጉንዳኖች በሚያስገርም መንገድ የተደራጁና የሚያስደንቅ ኅብረት ያላቸው ፍጥረታት ናቸው። ለወደፊት የሚሆናቸውን ምግብ በደመ ነፍስ ይሰበስባሉ። ‘አለቃ፣ አዛዥ ወይም ገዢ’ የላቸውም። እርግጥ ነው ንግሥት አለቻቸው፤ ሆኖም ንግሥቷ እንቁላል ከመጣሏና የመንጋው እናት ከመሆኗ በስተቀር ምንም የምታደርገው ነገር የለም። ምንም ዓይነት ትእዛዝ አትሰጥም። የሚወተውታቸው አለቃ ወይም ምን እየሠሩ እንዳለ የሚከታተል ተቆጣጣሪ ሳይኖራቸው ያለመታከት ይሠራሉ።
እኛስ እንደ ጉንዳን ታታሪ መሆን አይገባንም? በቅርብ ሆኖ የሚቆጣጠረን ኖረም አልኖረ ተግተን መሥራታችንና የሥራችንን ጥራት በየጊዜው ለማሻሻል መጣራችን ጥቅሙ ለእኛው ነው። አዎን፣ በትምህርት ቤት፣ ተቀጥረን በምንሠራበት ቦታና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በምንካፈልበት ጊዜ አቅማችን የፈቀደውን መሥራት አለብን። ጉንዳን ከታታሪነቷ ጥቅም እንደምታገኘው ሁሉ አምላክ ‘በድካማችን ሁሉ ደስ እንዲለን’ ይፈልጋል። (መክብብ 3:13, 22፤ 5:18) ንፁሕ ሕሊናና የመንፈስ እርካታ ተግቶ በመሥራት የሚገኙ በረከቶች ናቸው።—መክብብ 5:12
ሰሎሞን ለማስተላለፍ የፈለገውን ነጥብ ጠንከር አድርጎ በመግለጽ ሰነፍን ከስንፍናው ለመቀስቀስ “አንተ ታካች፣ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?” የሚሉትን ሁለት ጥያቄዎች ተጠቅሟል። ንጉሡ በማሾፍ አነጋገር አክሎ እንዲህ ይላል:- “ጥቂት ትተኛለህ፣ ጥቂት ታንቀላፋለህ፣ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፣ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።” (ምሳሌ 6:9-11) ሰነፍ ሰው ተንጋሎ እንደተኛ ድህነት እንደ ሽፍታ ፈጥኖ ይደርስበታል፤ ማጣትም ሰይፍ እንደታጠቀ ሰው ጥቃት ይሰነዝርበታል። የሰነፍ ሰው እርሻ ወዲያው አረምና ሳማ ይወርሰዋል። (ምሳሌ 24:30, 31) ንግዱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይከስራል። አንድ አሠሪ ዳተኛ ሠራተኛን እስከ መቼ ይታገሠዋል? ማጥናት የማይወድ ተማሪ በትምህርቴ ጥሩ ውጤት አገኛለሁ ብሎ ሊጠብቅ ይችላል?
ሐቀኛ ሁን
ሰሎሞን አንድ ሰው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያተረፈውን መልካም ስምና ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት ስለሚያበላሽበት ሌላ ባሕርይ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ምናምንቴ ሰው የበደለኛም ልጅ በጠማማ አፍ ይሄዳል፤ በዓይኑ ይጠቅሳል፣ በእግሩ ይናገራል፣ በጣቱ ያስተምራል፤ ጠማማነት በልቡ አለ፣ ሁልጊዜም ክፋትን ያስባል፤ ጠብንም ይዘራል።”—ምሳሌ 6:12-14
ይህ ስለ አታላይ የተነገረ መግለጫ ነው። ውሸታም ሰው ብዙውን ጊዜ ውሸቱን ለመደበቅ ይጥራል። እንዴት? ይህን የሚያደርገው ‘በጠማማ አነጋገር’ ብቻ ሳይሆን በሰውነት እንቅስቃሴውም ጭምር ነው። አንድ ሃይማኖታዊ ምሁር “የሰውነት እንቅስቃሴ፣ የድምፅ ቃና እንዲሁም በፊት ላይ የሚነበበው ነገር ለማታለል ተብሎ የሚቀነባበር ዘዴ ነው፤ ከላይ ከሚታየው ቅንነት በስተጀርባ ጠማማ አስተሳሰብና ቀና ያልሆነ መንፈስ አለ” በማለት ተናግረዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ተንኮል ስለሚሸርብ ሁልጊዜ ጠብን ይዘራል። ይህ ሰው መጨረሻው ምን ይሆናል?
የእስራኤል ንጉሥ “ስለዚህ ጥፋቱ ድንገት ይደርስበታል፤ ድንገት ይደቅቃል፣ ፈውስም ከቶ የለውም” በማለት መልስ ይሰጣል። (ምሳሌ 6:15) ውሸታም በተጋለጠ ጊዜ ስሙ ወዲያው ይጠፋል። ከዚያ በኋላ ማን ያምነዋል? ዘላለማዊ ሞት ይጠብቃቸዋል ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል ‘ሐሰተኞች ሁሉ’ ስለሚገኙበት መጨረሻው ጥፋት ነው። (ራእይ 21:8) በተቻለን መጠን ‘በነገር ሁሉ በሐቀኝነት ለመመላለስ’ እንጣጣር።—ዕብራውያን 13:18 NW
ይሖዋ የሚጠላውን ጥሉ
ለክፉ ነገር ጥላቻ ካለን መልካም ስማችንን የሚያጎድፍ ድርጊት ከመፈጸም እንድንቆጠብ ያደርገናል! ታዲያ ክፉ የሆነውን የመጸየፍ ዝንባሌ ማዳበር አይገባንም? ሆኖም መጥላት የሚገባን የትኞቹን ነገሮች ነው? ሰሎሞን እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፣ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፣ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፣ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፣ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።”—ምሳሌ 6:16-19
በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱት ሰባት ነገሮች መሠረታዊ በመሆናቸው ሁሉንም ዓይነት መጥፎ ነገሮች ያጠቃልላሉ ማለት ይቻላል። “ትዕቢተኛ ዓይን” እና “ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ” በሐሳብ ደረጃ የሚፈጸሙ ኃጢአቶች ናቸው። “ሐሰተኛ ምላስ” እና “በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር” በክፋት የሚነገሩ ቃላት ናቸው። “ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ” እና “ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር” የተባሉት የክፋት ድርጊቶች ናቸው። በተለይ ይሖዋ በሰላም አብረው በሚኖሩ ሰዎች መካከል ጠብ በመዝራት የሚደሰትን ሰው ይጠላል። የሰው ልጆች የሚሠሩት ክፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሚሄድ ቁጥሩ ከስድስት ወደ ሰባት ከፍ ማለቱ ዝርዝሩ በዚሁ የሚያበቃ እንዳልሆነ የሚያመለክት ነው።
እርግጥ ነው፣ አምላክ ለሚጠላው ነገር ፍጹም ጥላቻ ማዳበር ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል “ትዕቢተኛ ዓይን” ወይም ሌላ ዓይነት ኩራት እንዳይኖርብን መጠንቀቅ ይገባናል። እንዲሁም ጎጂ ሐሜት ‘በወንድማማች መካከል’ በቀላሉ ጠብ ሊዘራ ስለሚችል ሊወገድ ይገባዋል። መጥፎ አሉባልታ፣ ያልተረጋገጠ ወሬ ወይም ውሸት በማዛመት ‘ንጹሕ ደም አናፈስስ’ ይሆናል፤ ነገር ግን የአንድን ሰው መልካም ስም ልናጎድፍ እንችላለን።
‘ውበትዋን አትመኘው’
ሰሎሞን የምክሩን ቀጣይ ክፍል እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፣ በአንገትህም እሰረው።” ለምን? “ስትሄድም ይመራሃል፤ ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣ ያነጋግርሃል።”—ምሳሌ 6:20-22
ቅዱሳን ጽሑፎች በሚሰጡት ምክር መሠረት ማደግ በእርግጥ ከጾታ ብልግና ወጥመድ ሊጠብቀን ይችላልን? አዎን፣ ሊጠብቀን ይችላል። እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል:- “ትእዛዝ መብራት፣ ሕግም ብርሃን ነውና፣ የተግሣጽም ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነውና፣ ከክፉ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ ከሌላይቱም ሴት ምላስ ጥፍጥነት።” (ምሳሌ 6:23, 24) የአምላክን ቃል ‘ለእግራችን መብራት እንዲሁም ለመንገዳችን ብርሃን’ አድርገን መጠቀማችንና የሚሰጠውን ምክር ማስታወሳችን መጥፎ ሴት ወይም መጥፎ ወንድ በሚያቀርቡልን ማባበያ እንዳንሸነፍ ይረዳናል።—መዝሙር 119:105
ጠቢቡ ንጉሥ “ውበትዋን በልብህ አትመኘው፤ የአይኖችዋም ውበት አያማልልህ።” በማለት አጥብቆ ያሳስባል። ለምን? “ሰው ለጋለሞታ ሴት ሲል ለቁራሽ ዳቦ ይዳረጋል፤ የሌላውም ሰው ሚስት ውድ የሆነውን ነፍስ እንኳ ታጠምዳለች።”—ምሳሌ 6:25, 26 NW
ሰሎሞን አንዲትን አመንዝራ ሚስት እንደ ጋለሞታ አድርጎ መጥቀሱ ነውን? ምናልባት። ወይም ከአንዲት ዝሙት አዳሪ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸምና ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ማመንዘር በሚያስከትለው መዘዝ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስቀመጥ ሊሆን ይችላል። የጋለሞታ ወዳጅ የሚሆን ሰው “ለቁራሽ ዳቦ” ማለትም ለከፋ ድህነት ይዳረጋል። አልፎ ተርፎም ገዳይ የሆነውን ኤድስን ጨምሮ በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፉ የሚያሰቃዩና የሚያማቅቁ በሽታዎች ሊጋለጥ ይችላል። በሌላ በኩል ከሌላ ሰው የትዳር ጓደኛ ጋር አጉል ወዳጅነት መመሥረት የሚፈልግ በሕጉ ሥርም ቢሆን ያላንዳች ጥርጥር ከባድ ቅጣት ይጠብቀው ነበር። አመንዝራዋ ሚስት አብሯት የሚማግጠውን ሰው ‘ውድ ነፍስ’ አደጋ ላይ ትጥላለች። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ልቅ አኗኗሩ ሕይወቱን አሳጠረውም አላሳጠረው . . . ይህን ኃጢአት የሠራው ሰው የሞት ቅጣት አይቀርለትም” በማለት ይገልጻል። (ዘሌዋውያን 20:10፤ ዘዳግም 22:22) ያም ሆነ ይህ ምንም ያህል ውብ ብትሆን እንዲህ ዓይነቷን ሴት መመኘት አያስፈልግም።
‘በጉያህ እሳት አትታቀፍ’
በተጨማሪም ሰሎሞን ዝሙት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ለመናገር “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? በፍም ላይ የሚሄድ፣ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?” ሲል ጠይቋል። የምሳሌውን ትርጉም ሲያብራራ “ወደ ሰው ሚስትም የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ ሳይቀጣ አይቀርም” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 6:27-29) እንደዚህ ዓይነቱ ኃጢአተኛ ከቅጣት አያመልጥም።
“ሌባ በተራበ ጊዜ ነፍሱን ሊያጠግብ ቢሰርቅ ሰዎች አይንቁትም” በማለት ያስታውሰናል። ይሁን እንጂ “ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፣ በቤቱም ያለውን ሁሉ ይሰጣል።” (ምሳሌ 6:30, 31) በጥንቷ እስራኤል አንድ ሌባ ያለውን ሁሉ የሚያሳጣው ቢሆንም እንኳ እንዲከፍል ይጠየቅ ነበር።a ስለ ፈጸመው ብልግና ምክንያት ማቅረብ የማይችለው ዝሙት አድራጊማ ቅጣቱ ከዚህ የባሰ መሆን አለበት!
ሰሎሞን “ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮው የጐደለው ነው” በማለት ተናግሯል። ‘እንዲህ የሚያደርግ ነፍሱን ስለሚያጠፋ ’ አእምሮ የጎደለው ማለትም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የሌለው መሆኑን ያሳያል። (ምሳሌ 6:32) ከላይ ሲታይ መልካም ሥነ ምግባር ያለው ሰው ሊመስል ይችላል፤ ውስጣዊ ስብዕናው ግን አእምሮ የጎደለው ነው።
ዝሙት የሚፈጽም ሰው ሌላም ፍሬ ያጭዳል። “ቁስልንና ውርደትን ያገኛል፣ ስድቡም አይደመሰስም። ቅንዓት ለሰው የቁጣ ትኩሳት ነውና፣ በበቀልም ቀን አይራራለትምና። እርሱም ምንም ካሣ አይቀበልም፣ ስጦታም ብታበዛለት አይታረቅም።”—ምሳሌ 6:33-35
አንድ ሌባ የሰረቀውን መልሶ ሊተካ ይችላል፤ ዝሙት የሠራ ሰው ግን መመለስ የሚችለው ነገር የለም። በንዴት ለበገነው ባል ምን ካሳ ሊሰጥ ይችላል? የቱንም ያህል ቢማጸን አይታዘንለትም። ዝሙት የፈጸመው ሰው በምንም መንገድ ኃጢአቱን የሚሸፍን ካሳ መክፈል አይችልም። ስሙ እንደጎደፈና እንደተበላሸ ይኖራል። ከዚህም በላይ ፈጽሞ ከቅጣት ሊያመልጥ ወይም ራሱን ነፃ ሊያደርግ አይችልም።
ስማችንን ከሚያጎድፈውና በአምላክ ላይ ነቀፋ ሊያስከትል ከሚችለው ከዝሙት እንዲሁም ሌላ ዓይነት ጠባይና ዝንባሌ መራቅ ምንኛ ጥበብ ነው! እንግዲያው ቸኩለን ዋስ በመሆን የሞኝነት ድርጊት እንዳንፈጽም እንጠንቀቅ። ስማችን በታታሪነትና በሐቀኝነት የሚታወቅ ይሁን። እንዲሁም ይሖዋ የሚጠላውን ለመጥላት ስንጣጣር በእርሱም ሆነ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ጥሩ ስም የምናተርፍ እንሁን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ ሌባ ሁለት፣ አራት ወይም አምስት እጥፍ እንዲከፍል ይጠየቅ ነበር። (ዘጸአት 22:1-4) “ሰባት እጥፍ” የሚለው አነጋገር ከፍተኛውን የቅጣት መጠን ሳያመለክት አይቀርም፤ ይህ ደግሞ የሰረቀውን ብዙ እጥፍ ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ገንዘብ ለሚበደር ሰው ዋስ በመሆን ረገድ ጠንቃቃ ሁን
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንደ ጉንዳን ታታሪ ሁን
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጎጂ ሐሜት ተቆጠብ