የጥናት ርዕስ 43
እውነተኛ ጥበብ እየጮኸች ነው
“እውነተኛ ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮኻለች። በአደባባይ ላይ ያለማቋረጥ ድምፅዋን ታሰማለች።”—ምሳሌ 1:20
መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ
ማስተዋወቂያa
1. በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጥበብ ለምታሰማው ጥሪ ምን ምላሽ እየሰጡ ነው? (ምሳሌ 1:20, 21)
በብዙ አገሮች ውስጥ እግረኛ በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ፈገግ ብለው ለአላፊ አግዳሚው ጽሑፍ ሲያበረክቱ ማየት የተለመደ ነው። አንተስ በዚህ አስደሳች የአገልግሎት ዘርፍ ተካፍለህ ታውቃለህ? ከሆነ፣ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኘው ዘይቤያዊ አገላለጽ አስበህ መሆን አለበት፤ የምሳሌ መጽሐፍ፣ ጥበብ ሰዎች ምክሯን እንዲሰሙ በአደባባይ ላይ ቆማ እንደምትጣራ ይናገራል። (ምሳሌ 1:20, 21ን አንብብ።) በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎቻችን ውስጥ “እውነተኛ ጥበብ” ማለትም የይሖዋ ጥበብ ይገኛል። በውስጣቸው ያለው መረጃ፣ ሰዎች ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ይረዳቸዋል። ሰዎች ጽሑፎቻችንን ሲወስዱ ደስ ይለናል። ሆኖም ጽሑፎቻችንን የሚቀበሉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማወቅ አይፈልጉም። ሌሎች ደግሞ ይስቁብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን የሥነ ምግባር መመሪያዎች የሚተቹም አሉ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመሩ ሰዎች ጭፍንና ተመጻዳቂ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ሆኖም ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ሁሉም ሰዎች እውነተኛውን ጥበብ ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ አመቻችቷል። በየትኞቹ መንገዶች?
2. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ጥበብ የሚገኘው ከየት ነው? ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ምን ለማድረግ መርጠዋል?
2 ይሖዋ ሰዎች እውነተኛውን ጥበብ እንዲያገኙ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረቱ ጽሑፎቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? የይሖዋ በረከት ስላልተለየን ጽሑፎቻችን ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛሉ። መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን የሚያነብቡና የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች ጥቅም ያገኛሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች እውነተኛ ጥበብ ለምታሰማው ጥሪ ጆሮ ላለመስጠት መርጠዋል። ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ የራሳቸውን ፍላጎት ወይም ሌሎች ሰዎች የሚሰጧቸውን ምክር ለመከተል ይመርጣሉ። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች በመከተላችን ምክንያት እኛን ይንቁን ይሆናል። ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን፣ ይሖዋ የሚሰጠውን ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ይሖዋን ማወቅ ጥበብ ያስገኛል
3. እውነተኛ ጥበብ ምን ይጨምራል?
3 ጥበብ፣ እውቀትን ተጠቅሞ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታን ሊያመለክት ይችላል። ይሁንና እውነተኛ ጥበብ ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው፤ እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ማወቅም ማስተዋል ነው” ይላል። (ምሳሌ 9:10) እንግዲያው ከባድ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ውሳኔያችን በይሖዋ አስተሳሰብ ማለትም ‘እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ባለን እውቀት’ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በመመርመር እንዲህ ያለ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ እውነተኛ ጥበብ እንዳለን እናሳያለን።—ምሳሌ 2:5-7
4. እውነተኛ ጥበብ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
4 እውነተኛ ጥበብ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ሮም 16:27) የጥበብ ምንጭ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው? አንደኛ፣ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ስለ ፍጥረታቱ ገደብ የለሽ እውቀት አለው። (መዝ. 104:24) ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው። (ሮም 11:33) ሦስተኛ፣ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የይሖዋን ምክር የሚከተሉ ሰዎች ሁልጊዜ ጥቅም ያገኛሉ። (ምሳሌ 2:10-12) እውነተኛ ጥበብ ማግኘት ከፈለግን እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች መቀበል እንዲሁም ውሳኔ ከማድረጋችን ወይም አንድን እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት እነዚህን እውነታዎች ከግምት ማስገባት አለብን።
5. ሰዎች የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን አምነው አለመቀበላቸው ምን ውጤት አምጥቷል?
5 ብዙ ሰዎች በተፈጥሮ ላይ አስደናቂ ንድፍ እንደሚንጸባረቅ አምነው ይቀበላሉ፤ ሆኖም ፈጣሪ መኖሩን በመካድ የዚህ ንድፍ ምንጭ ዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በአምላክ እንደሚያምኑ ቢናገሩም የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ጊዜ ያለፈባቸው እንደሆኑ ስለሚሰማቸው የራሳቸውን አካሄድ ለመከተል ይመርጣሉ። ይህስ ምን ውጤት አምጥቷል? ሰዎች ከአምላክ ጥበብ ይልቅ በራሳቸው ጥበብ መመራታቸው ዓለማችን የተሻለች ቦታ እንድትሆን አድርጓታል? እውነተኛ ደስታ ወይም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ማግኘት ችለዋል? በዙሪያችን የምንመለከተው ነገር የሚከተለውን እውነታ ያረጋግጣል፦ “ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ፣ ማስተዋልም ሆነ ምክር ከንቱ ነው።” (ምሳሌ 21:30) በእርግጥም እውነተኛ ጥበብ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለታችን ተገቢ ነው። የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ አያደርጉም። ለምን?
ሰዎች እውነተኛ ጥበብን የሚቃወሙት ለምንድን ነው?
6. በምሳሌ 1:22-25 መሠረት እውነተኛ ጥበብ ስትጮኽ ጥሪዋን ለመስማት አሻፈረኝ የሚሉት እነማን ናቸው?
6 እውነተኛ ጥበብ ‘መንገድ ላይ ስትጮኽ’ ብዙዎች ጥሪዋን ለመስማት አሻፈረኝ ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ጥበብን የሚቃወሙ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ፤ እነሱም “አላዋቂዎች፣” “ፌዘኞች” እና “ሞኞች” ናቸው። (ምሳሌ 1:22-25ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች አምላካዊ ጥበብን የሚቃወሙት ለምን እንደሆነ እንዲሁም እነሱን ከመምሰል መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር እንመልከት።
7. አንዳንዶች “አላዋቂዎች” ሆነው ለመኖር የሚመርጡት ለምንድን ነው?
7 “አላዋቂዎች” ወይም ተሞክሮ የሌላቸው ሰዎች ተላላ፣ የሰሙትን ሁሉ የሚያምኑ እንዲሁም በቀላሉ የሚታለሉ ናቸው። (ምሳሌ 14:15 ግርጌ) በአገልግሎት ስንካፈል ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ሰዎችን እናገኛለን። ለምሳሌ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሃይማኖታዊ ወይም በፖለቲካዊ መሪዎች እየተታለሉ ነው። አንዳንዶች በእነዚህ መሪዎች ሲታለሉ መኖራቸውን ሲያውቁ በጣም ይደነግጣሉ። በምሳሌ 1:22 ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ግን ወደውና ፈቅደው አላዋቂዎች ለመሆን ይመርጣሉ። (ኤር. 5:31) የራሳቸውን ፍላጎት መከተል ያስደስታቸዋል፤ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል መማር ወይም በመሥፈርቶቹ መመራት አይፈልጉም። ብዙዎች በኩዊቤክ፣ ካናዳ የምትኖር አንዲት አጥባቂ ሃይማኖተኛ የተናገረችውን ሐሳብ ይጋራሉ፤ ይህች ሴት አንድ የይሖዋ ምሥክር ሲያነጋግራት “ቄሱ አታሎን ከሆነ ይህ የእሱ ጥፋት ነው እንጂ የእኛ አይደለም” ብላዋለች። ሆን ብለው በአላዋቂነት የሚቀጥሉ ሰዎችን መምሰል እንደማንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም!—ምሳሌ 1:32፤ 27:12
8. ጥበብ ለማግኘት ምን ይረዳናል?
8 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አላዋቂዎች ሆነን ከመኖር ይልቅ ‘በማስተዋል ችሎታችን የጎለመስን እንድንሆን’ ያበረታታናል። (1 ቆሮ. 14:20) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ጥበብ ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከችግር ለመራቅና ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ እንደሚረዱን በሕይወታችን እናያለን። በዚህ ረገድ የምናደርገውን እድገት መገምገማችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመርክ ረዘም ያለ ጊዜ ቢያልፍም ሕይወትህን ለይሖዋ ወስነህ ካልተጠመቅክ ‘እስካሁን እዚህ ግብ ላይ ያልደረስኩት ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ ደግሞ ምሥራቹን በመስበክና በማስተማር ረገድ ማሻሻያ እያደረግክ ነው? የምታደርጋቸው ውሳኔዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደምትመራ ያሳያሉ? ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ታንጸባርቃለህ? በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ከተገነዘብክ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ላይ አሰላስል፤ ምክንያቱም የይሖዋ ማሳሰቢያ “ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል።”—መዝ. 19:7
9. “ፌዘኞች” ጥበብን እንደሚቃወሙ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
9 በሁለተኛ ደረጃ፣ አምላካዊ ጥበብን የሚቃወሙት “ፌዘኞች” ናቸው። በአገልግሎት ስንካፈል አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያሉ ሰዎች ያጋጥሙናል። እነዚህ ሰዎች በሌሎች ላይ ማሾፍ ያስደስታቸዋል። (መዝ. 123:4) መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ፌዘኞች እንደሚበዙ ይናገራል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) እንደ ጻድቁ ሎጥ አማቾች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም መለኮታዊ ማስጠንቀቂያዎችን ችላ ይላሉ። (ዘፍ. 19:14) ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚመሩ ሰዎች ይሳለቃሉ። እነዚህ ፌዘኞች ‘መጥፎ ምኞታቸውን ይከተላሉ።’ (ይሁዳ 7, 17, 18) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፌዘኞች የሚሰጠው መግለጫ ከሃዲዎችንና ይሖዋን የሚቃወሙ ሌሎች ሰዎችን በሚገባ ይገልጻቸዋል።
10. መዝሙር 1:1 እንደሚለው የፌዘኞችን ጎዳና ከመከተል መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
10 የፌዘኞችን ጎዳና ከመከተል መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ የተቺነት ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ አለማሳለፍ ነው። (መዝሙር 1:1ን አንብብ።) ይህም ሲባል ከሃዲዎችን ከመስማት ወይም እነሱ ያዘጋጁትን ማንኛውንም ነገር ከማንበብ እንቆጠባለን ማለት ነው። ካልተጠነቀቅን የተቺነት ዝንባሌ በቀላሉ ልናዳብር እንዲሁም ይሖዋንና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ መጠራጠር ልንጀምር እንደምንችል እንገነዘባለን። እንዲህ ካለው አካሄድ ለመራቅ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘አዲስ መመሪያ ወይም ማብራሪያ ሲሰጠን አሉታዊ ነገር መናገር ይቀናኛል? አመራር ከሚሰጡት ወንድሞች ላይ ስህተት የመለቃቀም ዝንባሌ አለኝ?’ እንዲህ ያሉ ዝንባሌዎችን ቶሎ ብለን የምናርም ከሆነ ይሖዋ ይደሰትብናል።—ምሳሌ 3:34, 35
11. “ሞኞች” ይሖዋ ላወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው?
11 በሦስተኛ ደረጃ፣ ጥበብን የሚቃወሙት “ሞኞች” ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ ሞኝ የተባሉት በአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ለመመራት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው። በራሳቸው ዓይን ትክክል መስሎ የታያቸውን ነገር ያደርጋሉ። (ምሳሌ 12:15) እንዲህ ያሉት ሰዎች የጥበብ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ይቃወማሉ። (መዝ. 53:1) አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው እንዲህ ያሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በማክበራችን ብዙውን ጊዜ የሰላ ትችት ይሰነዝሩብናል። ሆኖም የተሻለ ምክር ሊሰጡ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሞኝ ሰው እውነተኛ ጥበብ ሊገኝ የማይችል ነገር ነው፤ በከተማው በር ላይ አንዳች የሚናገረው ነገር የለውም” ይላል። (ምሳሌ 24:7) ሞኞች አንዳች የጥበብ ቃል አይወጣቸውም። በእርግጥም ይሖዋ ‘ከሞኝ ሰው እንድንርቅ’ ያስጠነቀቀን መሆኑ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 14:7
12. የሞኞችን አካሄድ ከመከተል እንድንቆጠብ የሚረዳን ምንድን ነው?
12 አምላክ የሚሰጠውን ምክር ከሚጠሉ ሰዎች በተለየ መልኩ ለአምላክ አስተሳሰብ እንዲሁም ለሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ፍቅር እናዳብራለን። መታዘዝ የሚያስገኘውን ውጤት አለመታዘዝ ከሚያስከትለው መዘዝ ጋር ማወዳደራችን ይህን ፍቅር ለማጠናከር ይረዳናል። ሰዎች ይሖዋ የሚሰጠውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር በሞኝነት ችላ በማለታቸው በራሳቸው ላይ ስንት መከራ እንደሚያመጡ ለማሰብ ሞክር። ከዚያም አምላክን በመታዘዝህ ሕይወትህ ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ አስብ።—መዝ. 32:8, 10
13. ይሖዋ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን ምክሩን እንድንታዘዝ ያስገድደናል?
13 ይሖዋ ሁሉም ሰው ጥበብን የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ አድርጓል፤ ሆኖም ማንም ጥበብን እንዲሰማ አያስገድድም። ያም ቢሆን ጥበብን አለመስማት የሚያስከትለውን ውጤት ገልጿል። (ምሳሌ 1:29-32) ይሖዋን ላለመታዘዝ የሚመርጡ ሰዎች “መንገዳቸው የሚያስከትለውን መዘዝ ይቀበላሉ።” የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና ውሎ አድሮ ጭንቀት፣ መከራ፣ በመጨረሻም ጥፋት ያመጣባቸዋል። በሌላ በኩል ግን፣ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የይሖዋን ምክር የሚሰሙና በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች እንዲህ የሚል ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፦ “እኔን የሚሰማ ሰው ግን ተረጋግቶ ይኖራል፤ መከራ ይደርስብኛል የሚል ስጋትም አያድርበትም።”—ምሳሌ 1:33
እውነተኛ ጥበብ ጥቅም ያስገኝልናል
14-15. ከምሳሌ 4:23 ምን እንማራለን?
14 የአምላክን ጥበብ በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ ሁልጊዜም እንጠቀማለን። እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ምክሮች በቀላሉ ማግኘት እንድንችል አድርጓል። ለአብነት ያህል፣ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ጊዜ የማይሽራቸውን ምክሮች ሰጥቶናል፤ እነዚህን ምክሮች በሥራ ላይ ካዋልን ሕይወታችን ይሻሻላል። እንዲህ ካሉት ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ምክሮች መካከል አራቱን ብቻ እንመልከት።
15 ምሳሌያዊ ልብህን ጠብቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ ነውና” ይላል። (ምሳሌ 4:23) ሥጋዊ ልባችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ለማሰብ ሞክር። ጤናማ ምግብ መመገብ፣ አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም ከመጥፎ ልማዶች መራቅ ይኖርብናል። ምሳሌያዊ ልባችንን ለመጠበቅም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብን። በየዕለቱ የአምላክን ቃል እንመገባለን። ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዘጋጃለን፤ በስብሰባዎች ላይ እንገኛለን፤ እንዲሁም ተሳትፎ እናደርጋለን። አዘውትረን በአገልግሎት በመካፈል በምሳሌያዊ ሁኔታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እናደርጋለን። በተጨማሪም ሥነ ምግባር ከጎደላቸው መዝናኛዎች፣ ከመጥፎ ጓደኞች እንዲሁም አስተሳሰባችንን ሊበክሉ ከሚችሉ ሌሎች ነገሮች በመራቅ መጥፎ ልማዶችን ከማዳበር እንቆጠባለን።
16. ምሳሌ 23:4, 5 በዛሬው ጊዜ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
16 ባለህ ነገር ረክተህ ኑር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል፦ “ሀብት ለማግኘት አትልፋ። . . . ዓይንህን ስትጥልበት በዚያ አታገኘውም፤ የንስር ዓይነት ክንፎች አውጥቶ ወደ ሰማይ ይበርራልና።” (ምሳሌ 23:4, 5) ቁሳዊ ሀብት በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል። ያም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ ያሉ ሀብታሞችም ሆኑ ድሆች፣ ሀብት የማካበት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። እንዲህ ያለው ፍላጎት መልካም ስማቸውን፣ ከሌሎች ጋር ያላቸውን ዝምድና አልፎ ተርፎም ጤንነታቸውን የሚጎዳ ነገር እንዲያደርጉ ምክንያት ይሆናል። (ምሳሌ 28:20፤ 1 ጢሞ. 6:9, 10) በሌላ በኩል ግን ጥበብ ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። እንዲህ ያለው አመለካከት ከስግብግብነት እንድንጠበቅ፣ ባለን ነገር እንድንረካ እንዲሁም ደስተኞች እንድንሆን ያስችለናል።—መክ. 7:12
17. በምሳሌ 12:18 ላይ የተጠቀሰው ዓይነት “የጥበበኞች ምላስ” እንዲኖረን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
17 ከመናገርህ በፊት አስብ። ካልተጠነቀቅን በንግግራችን ከፍተኛ ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 12:18) ሌሎች ስላለባቸው ድክመት ሐሜት ከማውራት የምንቆጠብ ከሆነ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ምሳሌ 20:19) ንግግራችን ጉዳት የሚያደርስ ሳይሆን ፈውስ የሚያመጣ እንዲሆን ከፈለግን ልባችንን ከአምላክ ቃል በሚገኘው እውነት መሙላት አለብን። (ሉቃስ 6:45) መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ ካሰላሰልን ንግግራችን የሌሎችን መንፈስ የሚያድስ “የጥበብ ምንጭ” ይሆናል።—ምሳሌ 18:4
18. ምሳሌ 24:6ን ተግባራዊ ማድረጋችን በአገልግሎታችን ስኬታማ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
18 መመሪያ ተከተል። መጽሐፍ ቅዱስ ስኬት ለማግኘት የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል፤ እንዲህ ይላል፦ “ጥበብ ያለበት አመራር ተቀብለህ ለውጊያ ትወጣለህ፤ በብዙ አማካሪዎችም ስኬት ይገኛል።” (ምሳሌ 24:6 ግርጌ) ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጋችን በስብከቱና በማስተማሩ ሥራችን ስኬት ለማግኘት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። አገልግሎታችንን በራሳችን መንገድ ከማከናወን ይልቅ የሚሰጡንን መመሪያዎች ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ እናገኛለን። ተሞክሮ ያላቸው “አማካሪዎች” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ንግግሮችና በሠርቶ ማሳያዎች አማካኝነት ያሠለጥኑናል። በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ የሚያግዙ ጠቃሚ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን አዘጋጅቷል። አንተስ እነዚህን መሣሪያዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እየተማርክ ነው?
19. ይሖዋ ስለሚሰጠው ጥበብ ምን ይሰማሃል? (ምሳሌ 3:13-18)
19 ምሳሌ 3:13-18ን አንብብ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው ጠቃሚ ምክር ምንኛ አመስጋኞች ነን! እንዲህ ያለውን ግሩም ምክር ባናገኝ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውን ምክሮች በዚህ ርዕስ ውስጥ ተመልክተናል። እርግጥ ነው፣ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ከይሖዋ በሚገኙ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ምክሮች የተሞላ ነው። እንግዲያው ይሖዋ የሚሰጠውን ጥበብ ምንጊዜም ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ዓለም እንዲህ ላለው ጥበብ አድናቆት ባይኖረውም እኛ ግን ‘ጥበብን አጥብቀው የሚይዟት ደስተኞች እንደሚባሉ’ እርግጠኞች ነን።
መዝሙር 36 ልባችንን እንጠብቅ
a ይሖዋ የሚሰጠው ጥበብ፣ ዓለም ሊሰጠን ከሚችለው ከማንኛውም ነገር የላቀ ዋጋ አለው። በዚህ ርዕስ ላይ፣ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኝ ትኩረት የሚስብ አንድ ዘይቤያዊ አገላለጽ እንመለከታለን፤ የምሳሌ መጽሐፍ፣ ጥበብ በአደባባይ ላይ እንደምትጮኽ ይናገራል። እውነተኛ ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ፣ አንዳንዶች ለጥበብ ጆሯቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑት ለምን እንደሆነ እንዲሁም ጥበብ ለምታሰማው ጥሪ ምላሽ መስጠታችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን እንመለከታለን።