“ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ”
ወጣቱ ብልህ፣ “መልከ መልካምና ውብ” ነበረ። የአሠሪው ባለቤት በወሲብ ስሜት ያበደች ኀፍረተ ቢስ ሴት ነበረች። በወጣቱ ውበት በእጅጉ ስለተማረከች በየዕለቱ ልታግባባው ትሞክር ነበር። “እንዲህም ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም። ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች።” ሆኖም የፓትርያርኩ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ለጶጢፋር ሚስት ልብሱን ትቶላት አመለጠ።—ዘፍጥረት 39:1-12
ፈታኝ ከሆኑ ሁኔታዎች የሚሸሹት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን አንድ ቀን ማታ መንገድ ላይ የተመለከተውን የአንድ ወጣት ሁኔታ ተመልከት። አንዲት ጋለሞታ ሴት ስታባብለው ‘በሬ ወደሚታረድበት ስፍራ እንደሚነዳ፤ ወዲያውኑ እርስዋን ተከትሎ ሄደ።’—ምሳሌ 7:21, 22 የ1980 ትርጉም
ክርስቲያኖች ‘ከዝሙት እንዲሸሹ’ ጥብቅ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣት ክርስቲያን ደቀ መዝሙር ለነበረው ለጢሞቴዎስ “ከክፉ የጒልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ” ሲል ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ዝሙት፣ ምንዝር ወይም ሌላ ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም የሚገፋፋ ሁኔታ ሲያጋጥመን ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት እንደሸሸ ሁሉ እኛም ያለ አንዳች ማመንታት መሸሽ ይገባናል። እንዲህ ያለ ቆራጥ አቋም እንድንወስድ ምን ሊረዳን ይችላል? ሰሎሞን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በምሳሌ መጽሐፍ 7ኛ ምዕራፍ ላይ ተወዳዳሪ የሌለው ምክር አስፍሮልናል። ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ሰዎች ማታለያዎች የሚጠብቁንን ትምህርቶች መናገር ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባር የጎደላት አንዲት ሴት አንድን ወጣት እንዴት እንዳታለለችው በሚገልጽ ሕያው ታሪክ አማካኝነት እነዚህ ሰዎች የሚጠቀሙበትን ዘዴም ያጋልጣል።
‘ትእዛዞቼን በጣቶችህ ላይ እሰራቸው’
ንጉሡ “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ጠብቅ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ። ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ፤ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ” የሚል አባታዊ ምክር በመስጠት ይጀምራል።—ምሳሌ 7:1, 2
ወላጆች በተለይ ደግሞ አባቶች ጥሩውንና መጥፎውን በተመለከተ አምላክ ያወጣውን የአቋም ደረጃ ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ሙሴ ለአባቶች “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሳም ተጫወተው” የሚል ጥብቅ ምክር ሰጥቶ ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) ሐዋርያው ጳውሎስም “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 6:4) ከዚህ የተነሳ አንድ ወላጅ ለልጆቹ ከሚያስተምራቸው ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ነገሮች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ማሳሰቢያዎች፣ ትእዛዛትና ሕጎች እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም።
ወላጆች የሚያስተምሩት ትምህርት ሌሎች ሕጎችን ማለትም በቤተሰቡ ውስጥ የሚሠሩ ደንቦችንም የሚጨምር ሊሆን ይችላል። እነዚህ ለቤተሰቡ አባላት የሚጠቅሙ ደንቦች ናቸው። እርግጥ ነው፣ ደንቦቹ እንደየሁኔታው ከቤተሰብ ቤተሰብ ይለያዩ ይሆናል። ሆኖም ወላጆች በቤተሰባቸው ውስጥ ይበልጥ ሊሠራባቸው የሚችሉ ደንቦችን የማውጣት ኃላፊነት አለባቸው። አብዛኛውን ጊዜ የሚያወጧቸው ደንቦችም ለቤተሰባቸው ያላቸውን እውነተኛ ፍቅርና አሳቢነት የሚያሳዩ ናቸው። እዚህ ላይ ልጆች ወላጆቻቸው ለሚሰጧቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ብቻ ሳይሆን ለእነዚህ ደንቦችም ታዛዥ እንዲሆኑ ምክር ተሰጥቷቸዋል። አዎን፣ እነዚህን ትምህርቶች “እንደ ዓይንህ ብሌን” መጠበቅ ማለትም በከፍተኛ እንክብካቤ መያዝ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግ ይሖዋ ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች ችላ ማለት ከሚያስከትለው ከፍተኛ ጉዳት በመጠበቅ ‘በሕይወት ለመኖር’ ያስችላል።
ሰሎሞን ‘ ትእዛዞቼን በጣቶችህ ላይ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው’ በማለት ይቀጥላል። (ምሳሌ 7:3) ጣቶቻችን ምንጊዜም ከፊታችን እንደማይጠፉና የምንፈልገውን ለመሥራት ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጡን ሁሉ ከቅዱሳን ጽሑፎች የምናገኛቸው ትምህርቶች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትም የማይነጥፍ ማሳሰቢያና ማንኛውንም ሥራ ስናከናውን መመሪያ ይሆኑልናል። በልባችን ጽላት ላይ በመጻፍ የባሕርያችን ክፍል እንድናደርገው ተመክረናል።
ንጉሡ የጥበብንና የማስተዋልን አስፈላጊነት ሲገልጽ “ጥበብን:- አንቺ እኅቴ ነሽ በላት፣ ማስተዋልንም:- ወዳጄ ብለህ ጥራት” ሲል በጥብቅ ያሳስባል። (ምሳሌ 7:4) ጥበብ ከአምላክ የሚገኘውን እውቀት በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ የማዋል ችሎታ ነው። ጥበብን ተወዳጅ እንደሆነች እኅት ልናፈቅራት ይገባናል። ማስተዋል ምንድን ነው? አንድን ነገር በጥልቀት መመልከትና የጉዳዩ የተለያዩ ገጽታዎች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት የማወቅና አጠቃላዩን ገጽታ የመረዳት ችሎታ ነው። ማስተዋልን እንደልብ ወዳጃችን ማቅረብ ይገባናል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ማሰልጠኛዎችን የሙጥኝ ማለትና ከጥበብና ከማስተዋል ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ‘ከጋለሞታና ቃልዋን ከምታለዝብ ከሌላይቱ ሴት ራሳችንን ለመጠበቅ’ ነው። (ምሳሌ 7:5) አዎን፣ እንዲህ ማድረጋችን ጋለሞታ ወይም ሌላይቱ ሴት ማለትም ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ከሚጠቀምባቸው የለዘበ አነጋገርና አታላይ አቀራረብ ይጠብቀናል።
ወጣቱ ‘አጥማጅ ከሆነች ሴት’ ጋር ተገናኘ
የእስራኤል ንጉሥ በመቀጠል በዓይኑ በብረቱ የተመለከተውን ይናገራል:- “በቤቴ መስኮት [“በቤቴ መስኮት ሰቅሰቅ፣” የ1879 ትርጉም ] ሆኜ ወደ አደባባይ ተመለከትሁ፤ ከአላዋቂዎች መካከል አስተዋልሁ፤ ከጐበዛዝትም መካከል ብላቴናውን አእምሮ [“ልቦና፣” NW ] ጎድሎት አየሁ፣ በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም አቅራቢያ ሲያልፍ፤ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርስዋ አቀና፣ ማታ ሲመሽ፣ ውድቅትም ሲሆን፣ በሌሊትም በጽኑ ጨለማ።”—ምሳሌ 7:6-9
ሰሎሞን ወደ ውጪ የተመለከተበት የቤቱ መስኮት፣ ሰቅሰቅ ያለው ሲሆን ይህም ቄንጠኛ ሆኖ የተሠራ ጌጥ ያለው ሊሆን ይችላል። ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ጎዳናው ጨለምለም ይላል። ሰሎሞን ራሱን ለአደጋ ያጋለጠን አንድ ወጣት አየ። ይህ ወጣት የማስተዋል ወይም የማመዛዘን ችሎታውን መጠቀም ስለተሳነው ልቦና እንደጎደለው ያሳያል። ምን ዓይነት ሠፈር ውስጥ እንደገባና ምን ሊደርስበት እንደሚችል ሳይገነዘብ አልቀረም። ይህ ወጣት የቤትዋን መንገድ ይዞ ‘ቤትዋ አቅራቢያ’ ደረሰ። እሷ ማን ነች? የምትፈልገውስ ምንድን ነው?
ሁኔታውን በትኩረት ይከታተል የነበረው ንጉሥ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እነሆ፣ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች፣ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች። ሁከተኛና አባያ ናት፣ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፤ አንድ ጊዜ በጎዳና፣ አንድ ጊዜ በአደባባይ፣ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች።”—ምሳሌ 7:10-12
የሴትዬዋ አለባበስ ስለ ማንነትዋ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 38:14, 15) አለባበስዋ እንደ ጋለሞታ ሴት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ “በተንኮለኛ” አእምሮዋና “በመሠሪ” ሐሳብዋ የሰውን ልብ ታጠምዳለች። ባለጌ፣ መንቻካ፣ ለፍላፊ፣ ሥርዓት አልበኛ፣ ጯሂ፣ ችኮ፣ ኀፍረተ ቢስና ዓይን አውጣ ነች። ሰለባዋን ለማጥመድ ስለሚያመቻት በቤት አርፋ ከመቀመጥ ይልቅ በየመንገድ ማዕዘኑ፣ በየአደባባዩ ማድባት ትመርጣለች። እንደዚህ ወጣት ያለ ሰው እስኪመጣላት ትጠብቃለች።
‘ብዙ የሽንገላ ቃላት’
ወጣቱ መሠሪ ሐሳብ ካላት ስድ ሴት ጋር በዚህ መንገድ ተገናኘ። ይህ ሁኔታ የሰሎሞንን ትኩረት በእጅጉ ስቦ መሆን አለበት! እንዲህ አለ:- “ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው:- መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ። ስለዚህ እንድገናኝህ፣ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፣ አግኝቼሃለሁም።”—ምሳሌ 7:13-15
ይህች ሴት ከንፈርዋ ልዝብ ነው። ያለ ምንም እፍረት በድፍረት ትናገራለች። የምትናገራቸው ቃላት ሁሉ ሆን ተብለው ወጣቱን ለማታለል የተቀነባበሩ ናቸው። የዚያን ዕለት የደኅንነት መሥዋዕት እንዳቀረበችና ስእለቷን እንዳገባች በመግለጽ በጥሩ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በመጠቆም ጻድቅ መስላ ለመታየት ትሞክራለች። ኢየሩሳሌም ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ሥጋ፣ ዱቄት፣ ዘይትና ወይን ለደኅንነት መሥዋዕት ይቀርብ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:5, 6፤ 22:21፤ ዘኁልቁ 15:8-10) የደህንነት መሥዋዕት ያቀረበው ሰው ከመሥዋዕቱ የተወሰነውን ለራሱና ለቤተሰቡ መውሰድ ይችል ስለነበር በቤትዋ የሚበላና የሚጠጣ እንደልብ እንደሚገኝ በተዘዋዋሪ መናገሯ ነው። ሐሳቧ ግልጽ ነው:- ወጣቱ አስደሳች ጊዜ ያሳልፋል ማለቷ ነው። ከቤቷ የወጣችው ሆን ብላ እሱን ፍለጋ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ማባበያ የሚቀበል ሰው ምንኛ ሞኝ ነው! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ሲናገሩ “እርግጥ ከቤት የወጣችው አንድ ሰው ለማግኘት ፈልጋ እንደነበረ እሙን ነው። ይሁን እንጂ የወጣችው እውነት ይህን ወጣት ለማግኘት ብላ ነው? እንደዚህ ወጣት ያለ ጅላጅል ካልሆነ በስተቀር ማንም አያምናትም” ብለዋል።
በአለባበስዋ፣ በሚሸነግሉ ቃላቶችዋ፣ በእጆችዋ በመደባበስና በመሳም ታማልለዋለች። እንዲህ ትለዋለች “በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፣ የግብጽንም ሽመልመሌ ለሀፍ። በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ።” (ምሳሌ 7:16, 17) አልጋዋን ከግብጽ በመጣ የሚያምር አልጋ ልብስ ያሳመረች ሲሆን ከከርቤ፣ ከዓልሙንና ከቀረፋ የተሠራ ሽቶ ረጭታበታለች።
ቀጥላም “ና፣ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፣ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን” ትለዋለች። ግብዣው ሁለቱ አብረው እራት ከመብላት ያለፈ ነገር እንዲያደርጉ ነው። የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ እያግባባችው ነው። ይህ ግብዣ ለዚህ ወጣት እንደ ጀብዱ የሚቆጠር አስደሳች ገጠመኝ ነው! አክላም “ባለቤቴ በቤቱ የለምና፣ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤ በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፤ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል” በማለት ታግባባዋለች። (ምሳሌ 7:18-20) ባለቤትዋ ለሥራ ጉዳይ ወደ ሩቅ አገር ስለሄደና በቅርቡም ስለማይመለስ ምንም የሚያሰጋቸው ነገር እንደሌለ ትነግረዋለች። አንድን ወጣት በማታለል ረገድ እንዴት የተካነች ነች! “በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች።” (ምሳሌ 7:21) እንደዚህ ባለው ማባበያ ላለመሸነፍ የዮሴፍን ዓይነት የሞራል ጥንካሬ ያስፈልጋል። (ዘፍጥረት 39:9, 12) ወጣቱ ማሸነፍ ይችል ይሆን?
‘ለእርድ እንደሚነዳ በሬ’
ሰሎሞን “እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፣ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፣ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፣ ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፣ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፣ ፍላጻ ጉበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 7:22, 23
ወጣቱ የቀረበለትን ግብዣ እምቢ ማለት አልቻለም። ማስተዋሉ ጠፍቶ ‘ለእርድ እንደሚነዳ በሬ’ ተከትሏት ሄደ። በእግረ ሙቅ የታሰረ ሰው ማምለጥ እንደማይችል ሁሉ ወጣቱም እንዲሁ በማይወጣበት ኃጢአት ውስጥ ሊዘፈቅ ነው። “ፍላጻ ጉበቱን እስኪሰነጥቀው” ማለትም ለሞት ሊዳርገው የሚችል ጉዳት እስኪያገኘው ድረስ አደጋው አይታየውም። በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፍ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ራሱን ስለሚያጋልጥ ሞቱ ቃል በቃል አካላዊ ሞት ሊሆን ይችላል።a ያጋጠመው ነገር “ለነፍሱ ጥፋት” ስለሚሆንበት ለመንፈሳዊ ሞትም ሊዳርገው ይችላል። መላ እሱነቱንና ሕይወቱን ክፉኛ የሚጎዳ ነገር ከማድረጉም በላይ በአምላክ ላይ ከባድ ኃጢአት ሠርቷል። ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል ወፍ እሱም በሞት መዳፍ ለመያዝ ይጣደፋል!
“በጎዳናዋ አትሳት”
ጠቢቡ ንጉሥ ከታዘበው ነገር ትምህርት በማግኘት እንዲህ ሲል አጥብቆ ይመክራል:- “ልጆቼ ሆይ፣ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ። ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል፤ በጎዳናዋ አትሳት። ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው። ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።”—ምሳሌ 7:24-27
ሰሎሞን ምክር እየሰጠ ያለው አንድ ሰው ለሞት የሚዳርገውን ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗር ትቶ ‘በሕይወት መኖሩን እንዲቀጥል’ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ምሳሌ 7:2) ይህ ምክር ለዘመናችን ምንኛ ወቅታዊ ነው! ሰዎችን ለማጥመድ የሚያደቡ ሰዎች ከማይጠፉበት ቦታ መራቅ እንዳለብን ምንም ጥያቄ የለውም። እንደዚህ ወዳሉ ቦታዎች በመሄድ ለእነሱ የማታለያ ዘዴዎች ራስህን ለምን ታጋልጣለህ? “ሌላይቱ ሴት” አድብታ በምትጠብቅበት መንገድ ላይ በመንቀዋለል ለምን ‘ልቦና እንደጎደለው’ ሰው ትሆናለህ?
ንጉሡ የተመለከታት “ጋለሞታ ሴት” ወጣቱን “በተወደደ መተቃቀፍ ደስ ይበለን” ስትል አባብላዋለች። ብዙ ወጣቶች በተለይ ደግሞ ሴቶች በተመሳሳይ መንገድ ጥቃት አልደረሰባቸውም? እስቲ አስበው:- አንድ ሰው የጾታ ብልግና እንድትፈጽም የሚያባብልህ በእውነት አፍቅሮ ነው ወይስ የራስ ወዳድነት ፍላጎቱን ለማርካት? አንዲትን ሴት ከልብ ያፈቀረ ሰው እንዴት ሕሊናዋን የሚያስጥስ ድርጊት እንድትፈጽም ይገፋፋታል? ሰሎሞን “ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል” ሲል አጥብቆ መክሯል።
አታላይ ሰው ብዙውን ጊዜ የሚሸነግሉና በሚገባ የታሰበባቸው ቃላትን ይጠቀማል። ጥበብንና ማስተዋልን ማዳበራችን የተነገሩበትን ዓላማ ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። የይሖዋ ትእዛዛት ከክፉ እንደሚጠብቁን ፈጽሞ አትዘንጋ። እንግዲያው ‘የአምላክን ትእዛዛት ጠብቀን በሕይወት እንድንቆይ’ እንዲያውም ለዘላለም እንድንኖር ዘወትር ጥረት እናድርግ።—1 ዮሐንስ 2:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ አንዳንድ በሽታዎች ጉበትን ያጠቃሉ። ለምሳሌ ያህል ቂጥኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ የባክቴሪያው ዘአካላት ጉበት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ። እንዲሁም ጨብጥ አማጭ ዘአካላት ጉበት እንዲያብጥ ያደርጋሉ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆችህ ያወጡትን ደንብ የምትመለከተው እንዴት ነው?
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ማለት ሕይወት ማለት ነው