ልባችሁን ወደ ማስተዋል አዘንብሉ
“እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ።”— ምሳሌ 2:6
1. ልባችንን ወደ ማስተዋል ማዘንበል የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ ታላቅ አስተማሪያችን ነው። (ኢሳይያስ 30:20, 21) ሆኖም በቃሉ ውስጥ ከሚገኘው “የአምላክ እውቀት” ለመጠቀም ምን ማድረግ አለብን? አንዱ ማድረግ ያለብን ነገር ‘ልባችንን ወደ ማስተዋል ማዘንበል’ ነው፤ ይህም ይህን ባሕርይ በውስጣችን ለመኮትኮትና በተግባር ለማሳየት ልባዊ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። ጠቢቡ ሰው “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ” በማለት ስለ ተናገረ ማስተዋልን ለማግኘት አምላክን መጠየቅ አለብን። (ምሳሌ 2:1-6) እውቀት፣ ጥበብና ማስተዋል ምንድን ናቸው?
2. (ሀ) እውቀት ምንድን ነው? (ለ) ጥበብ ምን ተብሎ ሊገለጽ ይችላል? (ሐ) ማስተዋል ምንድን ነው?
2 እውቀት በተሞክሮ፣ በምርምር ወይም በጥናት ከሚገኙ እውነታዎች ጋር መተዋወቅ ነው። ጥበብ ደግሞ እውቀትን በሥራ የመተግበር ችሎታ ነው። (ማቴዎስ 11:19) ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት ሴቶች በአንድ ልጅ ላይ የይገባኛል ክርክር ባስነሱበት ጊዜ ጥበብ ተጠቅሟል፤ ለክርክሩ እልባት ለማስገኘት እናት ለልጅዋ ስላላት ከፍተኛ ፍቅር ባለው እውቀት ተጠቅሟል። (1 ነገሥት 3:16-28) ማስተዋል “ፈጣን የማመዛዘን ችሎታ ነው።” “አእምሮ አንዱን ነገር ከሌላው የሚለይበት ኃይል ወይም ችሎታ” ነው። (ዌብስተርስ ዩኒቨርሳል ዲክሽነሪ) ልባችንን ወደ ማስተዋል ካዘነበልን ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ማስተዋልን ይሰጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:1, 7) ሆኖም ማስተዋል የተለያዩ የሕይወት ዘርፎችን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
ማስተዋልና አንደበታችን
3. ምሳሌ 11:12, 13ን እንዴት ታብራራዋለህ? ‘ልብ የጎደለው’ ሲባል ምን ማለት ነው?
3 ማስተዋል ‘ዝም ለማለትም ሆነ ለመናገር ጊዜ እንዳለው’ እንድንገነዘብ ይረዳናል። (መክብብ 3:7) በተጨማሪም ይህ ባሕርይ ስለ ምንናገረው ነገር እንድንጠነቀቅ ያደርገናል። ምሳሌ 11:12, 13 እንዲህ ይላል:- “ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ [“ልብ፣” NW] የጎደለው ነው፤ አስተዋይ ግን ዝም ይላል። ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፤ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል።” አዎን፣ አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት ሌላውን ሰው የሚንቁ ከሆነ ‘ልብ ጎድሏቸዋል።’ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ዊልሄልም ጋዛኑስ እንዳሉት እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ “ማስተዋል የጎደለው” ነው። እሷም ሆነች እሱ ጥሩ የማመዘዘን ችሎታ የሚጎድላቸው ሲሆን “ልብ” የሚለው አነጋገር እዚህ ላይ መግባቱ ውስጣዊ የሆኑ መልካም ባሕርያት የሚጎድሉ መሆናቸውን ያመለክታል። ክርስቲያን ነኝ የሚል አንድ ሰው ብዙ ማውራት የሚወድ ከሆነና ይህም ወደ ስም ማጥፋትና ስድብ ደረጃ ከደረሰ የተሾሙ ሽማግሌዎች ይህን አደገኛ ሁኔታ ለመግታት እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።— ዘሌዋውያን 19:16፤ መዝሙር 101:5፤ 1 ቆሮንቶስ 5:11
4. አስተዋይና ታማኝ የሆኑ ክርስቲያኖች ምሥጢራዊ የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ምን ያደርጋሉ?
4 “አስተዋይ” የሆኑ ሰዎች ‘ልብ እንደጎደላቸው’ ሰዎች አይደሉም፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ዝም ይላሉ። ምሥጢር አያወጡም። (ምሳሌ 20:19) አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ያልተገራ አንደበት ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ስለሚያውቁ ‘በመንፈስ ይታመናሉ።’ ለእምነት ጓደኞቻቸው ታማኞች ከመሆናቸውም በላይ የእምነት ጓደኞቻቸውን ሊጎዳ የሚችል ምሥጢር አያወጡም። አስተዋይ ክርስቲያኖች ከጉባኤ ጋር ግንኙነት ያለው ምንም ዓይነት ምሥጢራዊ ወሬ ቢደርሳቸው የይሖዋ ድርጅት ራሱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በጽሑፎች አማካኝነት ለሌሎች እስኪያሳውቅ ድረስ በምሥጢር ይይዙታል።
ማስተዋልና ምግባራችን
5. ‘ሰነፎች’ ብልግናን እንዴት ይመለከቱታል? ለምንስ?
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ማስተዋል እንዲኖረንና ከመጥፎ ምግባር እንድንርቅ ይረዱናል። ለምሳሌ ያህል ምሳሌ 10:23 እንዲህ ይላል:- “ክፉ ነገር ማድረግ ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው።” ብልግናን እንደ “ጨዋታ” አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አካሄዳቸው የተሳሳተ መሆኑ ፈጽሞ የማይታያቸው ከመሆኑም በላይ ሰዎች ሁሉ ለሚያደርጉት ነገር በአምላክ ፊት ተጠያቂ የመሆናቸውን ጉዳይ አቅልለው ይመለከቱታል። (ሮሜ 14:12) እንደዚህ ያሉት ‘ሰነፍ ሰዎች’ አስተሳሰባቸው የተዛባ በመሆኑ መጥፎ ድርጊታቸውን አምላክ የማያየው ይመስላቸዋል። ድርጊታቸው “አምላክ የለም” ብለው እንደሚያምኑ የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 14:1-3፤ ኢሳይያስ 29:15, 16) አምላካዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለማይመሩ ማስተዋል ይጎድላቸዋል፣ ነገሮችንም በትክክል ማመዛዘን አይችሉም።— ምሳሌ 28:5
6. የብልግና ድርጊት ቂልነት የሆነው ለምንድን ነው? ማስተዋል ካለን ብልግናን እንዴት እንመለከተዋለን?
6 “አስተዋይ ሰው” ብልግናን እንደ “ጨዋታ” አድርጎ አይመለከትም። እንዲህ ዓይነቱ ምግባር አምላክን እንደሚያሳዝንና ከእሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሸ እንደሚችል ያውቃል። ክብርን የሚነካ፣ ትዳርን የሚያፈርስ፣ አእምሮንም ሆነ አካልን የሚጎዳ ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሞኝነት ነው። እንግዲያው ልባችንን ወደ ማስተዋል በማዘንበል ከብልግና ወይም ከማንኛውም ዓይነት ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንራቅ።— ምሳሌ 5:1-23
ማስተዋልና መንፈሳችን
7. ንዴት በአካል ላይ የሚያስከትላቸው አንዳንድ ጉዳቶች ምንድን ናቸው?
7 ልባችንን ወደ ማስተዋል ማዘንበላችን መንፈሳችንን ለመቆጣጠር ጭምር ይረዳናል። ምሳሌ 14:29 “ለትዕግሥተኛ ሰው ብዙ ማስተዋል አለው፤ ቁጡ ግን ስንፍናውን ከፍ ከፍ ያደርጋል” በማለት ይገልጻል። አስተዋይ ሰው በቁጣ ከመገንፈል ለመራቅ የሚጥርበት አንዱ ምክንያት በራሱ በግለሰቡ አካል ላይ የሚያስከትለው አስከፊ ውጤት ስላለ ነው። የደም ግፊትን ሊጨምርና የመተንፈስ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ቁጣና ንዴት እንደ አስም፣ የቆዳ በሽታ፣ የምግብ አለመፈጨት ችግርና የጨጓራ አልሰር የመሳሰሉትን በሽታዎች እንደሚያባብሱ ወይም እንደሚያመጡ ሐኪሞች ይናገራሉ።
8. ትዕግሥት ማጣት ወደ ምን ሊመራ ይችላል? ሆኖም በዚህ ረገድ ማስተዋል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
8 አስተዋዮችና ‘ታጋሾች’ መሆን ያለብን ጤንነታችንን ላለመጉዳት ስንል ብቻ አይደለም። ትዕግሥት ማጣት የኋላ ኋላ የምንጸጸትበትን የቂልነት ድርጊት እንድንፈጽም ሊያደርገን ይችላል። ማስተዋል፣ አንደበትን አለመቆጣጠር ወይም ችኩል መሆን ምን ሊያስከትል እንደሚችል እንድናጤን ስለሚረዳን ጥበብ የጎደለው ነገር በመሥራት ‘ስንፍናን ከፍ ከፍ’ ከማድረግ ይጠብቀናል። የማስተዋል ችሎታ ካለን ንዴት የማሰብ ችሎታችንን በማዛባት በትክክል ማመዛዘን እንዲሳነን ሊያደርግ እንደሚችል እንድንገነዘብ ይረዳናል። መለኮታዊውን ፈቃድ የማድረግና በአምላክ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት የመመላለስ አቅማችንን ያዳክማል። አዎን፣ ግልፍተኛ መሆን መንፈሳዊ ጉዳት ያስከትላል። እንዲያውም “ቁጣ” የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳንወርስ ከሚያደርጉን የተጠሉ ‘የሥጋ ሥራዎች’ አንዱ ነው። (ገላትያ 5:19-21) እንግዲያው ‘ለመስማት የፈጠንን ለመናገርም የዘገየን’ አስተዋይ ክርስቲያኖች እንሁን።— ያዕቆብ 1:19
9. ማስተዋልና ወንድማዊ ፍቅር አለመግባባቶችን ለመፍታት ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
9 አስተዋይነት ምናልባት ብንናደድ እንኳ ከግጭት ለመራቅ ስንል ከመናገር መቆጠብ እንዳለብን ሊጠቁመን ይችላል። ምሳሌ 17:27 “ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፣ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው” ይላል። ወንድማዊ ፍቅር ማሳየትና አስተዋይ መሆን አንድ ጎጂ የሆነ ነገር አፋችን እንዳመጣልን ከመናገር መቆጠብ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። በቁጣ ገንፍለን ተናግረንም ከነበረ ፍቅርና ትሕትና ይቅርታ እንድንጠይቅና ችግሩን እንድናስተካክል ይገፋፋናል። ሆኖም አንድ ሰው አስቀይሞን ከሆነስ? ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ መፍጠርን ግብ በማድረግ በትሕትናና በለዘበ አንደበት ያስቀየመንን ሰው በግል እናነጋግረው።— ማቴዎስ 5:23, 24፤ 18:15-17
ማስተዋልና ቤተሰባችን
10. ጥበብና ማስተዋል በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ምን ሚና ይጫወታሉ?
10 ጥበብና ማስተዋል ቤተሰብን ይገነባሉ፤ ስለዚህ የቤተሰብ አባላት እነዚህን ባሕርያት ለማንጸባረቅ መጣር ያስፈልጋቸዋል። ምሳሌ 24:3, 4 “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል፤ በእውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ ጓዳዎች ይሞላሉ” ይላል። ጥበብና ማስተዋል የተሳካ ቤተሰብ ለመገንባት ስለሚያገለግሉ እንደ ጥሩ የግንባታ ቁሳቁስ ሊቆጠሩ ይችላሉ። የማስተዋል ችሎታ ክርስቲያን ወላጆች የልጆቻቸውን ውስጣዊ ስሜትና ጭንቀት እንዲረዱ ያስችላቸዋል። አስተዋይ የሆነ ሰው የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ፣ ማዳመጥና የትዳር ጓደኛውን ወይም ጓደኛዋን ጥልቅ ስሜትና ሐሳብ መረዳት አይከብደውም ወይም አይከብዳትም።— ምሳሌ 20:5
11. አስተዋይ የሆነች ሚስት ‘ቤቷን ልትገነባ’ የምትችለው እንዴት ነው?
11 ጥበብና ማስተዋል ለደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት የግድ አስፈላጊ መሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ምሳሌ 14:1 “ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፤ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሰዋለች” ይላል። ጥበበኛና አስተዋይ የሆነች ባለትዳር ሴት በተገቢው መንገድ ለባሏ በመገዛትና ቤተሰቡን ለመጥቀም ጠንክራ በመሥራት ቤተሰቧ እንዲገነባ ጉልህ ሚና ትጫወታለች። ‘ቤቷ እንዲገነባ የምታደርግበት’ አንዱ መንገድ ምን ጊዜም ስለ ባሏ ጥሩ ጎኖች በመናገርና ሌሎች ለእሱ ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር በማድረግ ነው። ለይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላት ባለሙያና አስተዋይ ሚስት በሌሎች ትመሰገናለች።— ምሳሌ 12:4፤ 31:28, 30
ማስተዋልና አካሄዳችን
12. ‘ልብ የጎደላቸው’ ሰዎች የቂልነትን ድርጊት እንዴት ይመለከቱታል? ለምንስ?
12 ማስተዋል በማንኛውም የሕይወታችን ዘርፍ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘን እንድንሄድ ይረዳናል። ምሳሌ 15:21 “ልብ ለሌለው ሰው ስንፍና ደስታ ናት፤ አስተዋይ ግን አካሄዱን ያቃናል” በማለት ይህን ጉዳይ ይጠቁማል። ይህን ምሳሌ የምንረዳው እንዴት ነው? አእምሮ የጎደላቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች የቂልነት ወይም የጅልነት አካሄድ ያስደስታቸዋል። እነዚህ ሰዎች ‘ልብ ስለሚጎድላቸው’ ትክክለኛ ውስጣዊ ግፊት የላቸውም፤ እንዲሁም ጥበብ ስለሚጎድላቸው በቂልነት ድርጊቶች ይደሰታሉ።
13. ሰሎሞን ሳቅንና ቧልትን በተመለከተ ምን ነገር አስተውሏል?
13 አስተዋይ የነበረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ሳቅና ቧልት ከንቱ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። “እኔ በልቤ:- ና በደስታም እፈትንሃለሁ፣ መልካምንም ቅመስ አልሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነበረ። ሳቅን:- ዕብድ ነህ ደስታንም:- ምን ታደርጋለህ? አልሁት” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 2:1, 2) አስተዋይ ሰው የነበረው ሰሎሞን ሳቅና ቧልት የእውነተኛና ዘላቂ ደስታ ምንጭ ስላልሆኑ እነዚህ ነገሮች በራሳቸው እርካታ እንደማያስገኙ ለመገንዘብ ችሏል። ሳቅ ችግሮቻችንን ለጊዜው እንድንረሳ ሊያደርገን ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ሳቁ ካለፈ በኋላ ችግሮቹ ይባስ አፍጥጠው ሊመጡብን ይችላሉ። ሰሎሞን ሳቅን “ዕብድ ነህ” ብሎ መናገሩ ትክክል ነበር። ለምን? ምክንያቱም በሆነ ባልሆነው መሳቅ በትክክል የማመዛዘን ችሎታን ያጨልማል። አንድን ትልቅ ቁምነገር አቅልለን እንድንመለከት ሊያደርገን ይችላል። አንድ የንጉሥ አጫዋች የሚናገራቸው ቀልዶችና የሚያደርጋቸው ነገሮች የሚፈጥሩት ጊዜያዊ ደስታ የሚፈይደው ነገር አለ ሊባል አይችልም። ሰሎሞን ሳቅንና ጊዜያዊ ደስታን በተመለከተ በጥናት የደረሰበትን ዋና ፍሬ ነገር ማስተዋላችን ‘ከአምላክ ይልቅ ተድላን’ የምንወድ ከመሆን እንድንርቅ ይረዳናል።— 2 ጢሞቴዎስ 3:1, 4
14. አስተዋይ ሰው “አካሄዱን የሚያቃናው” እንዴት ነው?
14 አስተዋይ ሰው “አካሄዱን የሚያቃናው” እንዴት ነው? መንፈሳዊ ማስተዋልና አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል ትክክለኛ አካሄድ ለመከተል ያስችላል። የባይንግተን ትርጉም “አእምሮ የጎደለው ሰው በቂልነት ይደሰታል፤ ብልህ ግን ቀናውን መንገድ ይከተላል” በማለት በማያሻማ ሁኔታ አስቀምጦታል። ‘አስተዋይ ሰው’ ቀናውን መንገድ ይከተላል፤ እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ የአምላክን ቃል ተግባራዊ ስለሚያደርግ ትክክል የሆነውን ነገር ስሕተት ከሆነው መለየት አይቸግረውም።— ዕብራውያን 5:14፤ 12:12, 13
ማስተዋል ለማግኘት ምን ጊዜም ይሖዋን ጠይቁ
15. ከምሳሌ 2:6-9 ምን እንማራለን?
15 በሕይወታችን ውስጥ ቀና የሆነውን ጎዳና ለመከተል ሁላችንም ብንሆን ፍጹም አለመሆናችንን አምነን መቀበልና መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲሰጠን ይሖዋን መጠየቅ ያስፈልገናል። ምሳሌ 2:6-9 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤ እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።”— ከያዕቆብ 4:6 ጋር አወዳድር።
16. ይሖዋን በመቃወም ጥበብ፣ ማስተዋል ወይም ምክር የማይገኘው ለምንድን ነው?
16 ያለ ይሖዋ ምንም ማድረግ የማንችል መሆናችንን አምነን በመቀበል ቃሉን በጥልቀት ለመመርመርና ፈቃዱን ለማስተዋል በትሕትና እንጣር። ይሖዋ ፍጹም የተሟላ ጥበብ አለው፤ ምክሩ ምን ጊዜም መሬት ጠብ አይልም። (ኢሳይያስ 40:13፤ ሮሜ 11:34) እንዲያውም ይሖዋን የሚቃወም ማንኛውም ምክር ከንቱ ነው። ምሳሌ 21:30 “ጥበብ ወይም ማስተዋል ወይም ምክር በእግዚአብሔር ላይ የለም” በማለት ይገልጻል። (ከምሳሌ 19:21 ጋር አወዳድር።) ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና እንድንከተል የሚረዳን “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች አጋዥነት የአምላክን ቃል በማጥናት የምናገኘው መንፈሳዊ ማስተዋል ብቻ ነው። (ማቴዎስ 24:45-47) እንግዲያው ከይሖዋ ተቃራኒ የሆነው ምክር የቱንም ያህል እውነት ቢመስል ከይሖዋ ቃል ጋር ፈጽሞ ሊተካከል እንደማይችል አውቀን አኗኗራችንን ከእሱ ምክር ጋር እንዲስማማ እናድርግ።
17. የተሳሳተ ምክር መስጠት ምን ሊያስከትል ይችላል?
17 ሌሎችን የሚመክሩ አስተዋይ ክርስቲያኖች የሚሰጡት ምክር ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበትና አንድን ጥያቄ ከመመለሳቸው በፊት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርና በዚያ ላይ ማሰላሰል እንደሚያስፈልጋቸው ይገነዘባሉ። (ምሳሌ 15:28) ከባድ የሆኑ ጉዳዮችን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች በተሳሳተ መንገድ መልስ ቢሰጥ ውጤቱ በጣም አስከፊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመንፈሳዊ ለመርዳት በሚጥሩበት ጊዜ መንፈሳዊ ማስተዋል የሚያስፈልጋቸው ከመሆኑም በላይ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት መጸለይ ይኖርባቸዋል።
መንፈሳዊ ማስተዋል ይኑራችሁ
18. በጉባኤ ውስጥ አንድ ችግር ቢነሳ ማስተዋል መንፈሳዊ ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
18 ይሖዋን ለማስደሰት ‘በነገር ሁሉ አስተዋዮች’ መሆን ያስፈልገናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:7) መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናትና የአምላክ መንፈስና ድርጅት ከሚሰጡት መመሪያ ጋር ተስማምቶ መኖር በተሳሳተ አቅጣጫ ሊመሩን የሚችሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን እንድናስተውል ይረዳናል። ለምሳሌ ያክል በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ጉዳይ እኛ ባሰብነው መንገድ አልተያዘም እንበል። መንፈሳዊ ማስተዋል ካለን ይህ ጉዳይ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማቋረጥም ሆነ አምላክን ማገልገላችንን ለማቆም ምክንያት እንደማይሆን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ስላለን ይሖዋን የማገልገል መብት፣ ስላገኘነው መንፈሳዊ ነፃነትና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በመሆን ከምናከናውነው አገልግሎት ልናገኝ ስለምንችለው ደስታ አስቡ። መንፈሳዊ ማስተዋል ትክክለኛ የሆነ አመለካከት እንድንይዝና ራሳችንን ለአምለክ የወሰንን መሆናችንንና ሌሎች የፈለጉትን ቢያደርጉ እኛ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና እንደ ውድ ነገር አድርገን መያዝ እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል። አንድን ችግር ለመፍታት ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማድረግ የምንችለው ምንም ነገር ከሌለ ይሖዋ ለችግሩ መፍትሄ እስኪያመጣ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልገናል። ነገር ዓለሙን ሁሉ እርግፍ አድርገን ከመተው ወይም ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ‘ተስፋችንን በአምላክ ላይ እናድርግ።’— መዝሙር 42:5, 11 የ1980 ትርጉም
19. (ሀ) ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች በተመለከተ ያቀረበው ጸሎት ፍሬ ነገር ምን ነበር? (ለ) አንድን ነገር ሙሉ በሙሉ ካልተረዳነው ማስተዋል እንዴት ሊረዳን ይችላል?
19 መንፈሳዊ ማስተዋል ለአምላክና ለሕዝቦቹ ታማኞች ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል:- “ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፣ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።” (ፊልጵስዩስ 1:9, 10) በትክክል ለማመዛዘን ‘ትክክለኛ እውቀትና የተሟላ ማስተዋል’ ያስፈልገናል። እዚህ ላይ “ማስተዋል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “የሥነ ምግባር ሁኔታን ቶሎ የመገንዘብ ችሎታ” ያመለክታል። አንድ ነገር በምንማርበት ጊዜ ይህ ነገር ከአምላክና ከክርስቶስ ጋር ስላለው ግንኙነት መገንዘብ እንፈልጋለን፤ እንዲሁም የይሖዋን ባሕርያትና ዝግጅቶች ምን ያህል አጉልቶ እንደሚያሳይ እናሰላስላለን። ይህም ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረጉልን ነገር ያለን ማስተዋልና አድናቆት ከፍ እንዲል ያደርጋል። ማስተዋል አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ባይገባን እንኳ ስለ አምላክ፣ ስለ ክርስቶስና ስለ መለኮታዊው ዓላማ በተማርናቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ላይ ያለንን እምነት እርግፍ አድርገን መተው እንደሌለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል።
20. መንፈሳዊ ማስተዋል ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
20 አስተሳሰባችንንም ሆነ ድርጊቶቻችንን ምን ጊዜም ከአምላክ ቃል ጋር የምናስማማ ከሆነ መንፈሳዊ ማስተዋል ይኖረናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) እንዲህ ማድረጋችን ሐሳበ ግትሮችና ተቺዎች ከመሆን ይልቅ ትሑቶች እንድንሆን ይረዳናል። ማስተዋል ከሚሰጡን እርማቶች እንድንጠቀምና በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንድንለይ ይረዳናል። (ምሳሌ 3:7) እንግዲያው ይሖዋን ለማስደሰት ባለን ፍላጎት ተገፋፍተን በቃሉ ትክክለኛ እውቀት ለመሞላት እንጣር። ይህም ትክክል የሆነውን ስሕተት ከሆነው ለመለየት፣ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለይቶ ለማወቅና ከይሖዋ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና በታማኝነት የሙጢኝ ብለን እንድንይዝ ያስችለናል። ይህን ሁሉ ማድረግ የምንችለው ልባችንን ወደ ማስተዋል ካዘነበልን ነው። ሆኖም ሌላም የሚያስፈልግ ነገር አለ። አስተዋይነት እንዲጠብቀን ማድረግ አለብን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ልባችንን ወደ ማስተዋል ማዘንበል ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ማስተዋል የአንደበታችንን አጠቃቀምና አኗኗራችንን ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
◻ ማስተዋል በመንፈሳችን ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?
◻ ማስተዋልን ለማግኘት ምንጊዜም ይሖዋን መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማስተዋል መንፈሳችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስተዋይ የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን ሳቅና ቧልት እውነተኛ እርካታ እንደማያስገኝ ተገንዝቧል