እውነትን የራስህ አድርገኸዋልን?
“የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ።”—ሮሜ 12:2
1, 2. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?
‘አስጨናቂ በሆነው በዚህ የመጨረሻ ቀን’ እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ቀላል አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በእርግጥም፣ አንድ ሰው የክርስቶስን ምሳሌ ለመከተል ከፈለገ ዓለምን ማሸነፍ አለበት። (1 ዮሐንስ 5:4) ኢየሱስ የክርስትናን መንገድ በማስመልከት የተናገረውን አስታውስ:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።” ጨምሮም “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:13, 14፤ ሉቃስ 9:23
2 አንድ ክርስቲያን ወደ ሕይወት የሚወስደውን ጠባብ መንገድ አንዴ ካገኘ በኋላ ቀጣዩ ተፈታታኝ ሁኔታ ከመንገዱ ሳይወጣ መሄዱ ላይ ይሆናል። ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? ራሳችንን መወሰናችንና መጠመቃችን ለሰይጣን መሠሪ ዘዴዎችና ስውር ማባበያዎች ዒላማ ስለሚያደርገን ነው። (ኤፌሶን 6:11፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በደካማ ጎናችን ገብቶ መንፈሳዊነታችንን ለማበላሸት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ደግሞስ ኢየሱስን በፈተና ለመጣል የሞከረ ለእኛ ይተኛል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?—ማቴዎስ 4:1-11
የሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች
3. ሰይጣን በሔዋን አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ የዘራው እንዴት ነው?
3 ሰይጣን የሚጠቀምበት አንደኛው ዘዴ በአእምሯችን ውስጥ ጥርጣሬ መዝራት ነው። ከመንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን መካከል የላላውን ይፈልጋል። ገና ከመጀመሪያው በሔዋን ላይ የተጠቀመው ይህንኑ ዘዴ ነው። “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን?” በማለት ጥያቄ አቀረበላት። (ዘፍጥረት 3:1) በሌላ አባባል ሰይጣን እንደሚከተለው ማለቱ ነበር:- ‘በእርግጥ አምላክ እንዲህ ያለ እገዳ በአንቺ ላይ ሊጥል ይችላል? ይህን የመሰለውን መልካም ነገር ይከለክልሻል? የለም፣ ከዛፉ በበላሽ ቀን ዓይኖችሽ እንደሚከፈቱና እንደ አምላክ መልካሙንና ክፉዉን የምታውቂ እንደምትሆኚ ስለሚያውቅ ነው!’ ሰይጣን የጥርጣሬ ዘር ከዘራ በኋላ እስኪበቅል ድረስ መጠበቅ ጀመረ።—ዘፍጥረት 3:5
4. በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች በየትኞቹ ጥርጣሬዎች ሊነኩ ይችላሉ?
4 ሰይጣን በዛሬው ጊዜ ይህን ዘዴ የሚጠቀምበት እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን፣ የግል ጥናታችንን፣ ጸሎታችንንና ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንንና ስብሰባዎቻችንን ችላ ካልን ሌሎች ሰዎች ለሚያነሱት ጥርጣሬ ራሳችንን ልናጋልጥ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል “ዛሬ የያዝነው ኢየሱስ ያስተማረውን እውነት መሆኑን እንዴት እናውቃለን?” “በእርግጥ ይህ የመጨረሻው ቀን ነው? እንዲያውም ወደ 21ኛው መቶ ዘመን ተሸጋግረናል።” “የምንገኘው በአርማጌዶን ደፍ ላይ ነው ወይስ ገና ረዥም ጊዜ እንጠብቃለን?” እንደነዚህ ያሉ የጥርጣሬ ስሜቶችን ለማስወገድ ምን ልናደርግ እንችላለን?
5, 6. ጥርጣሬ ቢፈጠርብን ምን ማድረግ አለብን?
5 ያዕቆብ የሚከተለውን በጻፈ ጊዜ ተግባራዊ ምክር ሰጥቷል:- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው።”—ያዕቆብ 1:5-8
6 እንግዲያው ምን ማድረግ አለብን? እምነትና ማስተዋል እንዲሰጠን እንዲሁም ለሚነሳብን ለማንኛውም ዓይነት ጥያቄ ወይም ጥርጣሬ መልስ ለማግኘት የግል ጥናት ስናደርግ እንዲረዳን ሳናቋርጥ ‘አምላክን መለመን’ ይኖርብናል። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ድጋፍ እንደሚሰጠን ፈጽሞ ሳንጠራጠር በእምነት ጠንካራ የሆኑ ሰዎችን እርዳታ ልንጠይቅ እንችላለን። በተጨማሪም ያዕቆብ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” በማለት ተናግሯል። አዎን፣ በጥናትና በጸሎት አማካኝነት ወደ አምላክ ይበልጥ እየቀረብን ስንሄድ ጥርጣሬያችን ሁሉ ይወገዳል።—ያዕቆብ 4:7, 8
7, 8. ኢየሱስ ያስተማረው አምልኮ የትኛው እንደሆነ ለመለየት የሚያስችሉት አንዳንዶቹ መሠረታዊ መመዘኛዎች ምንድን ናቸው? እነዚህን መመዘኛዎች የሚያሟሉትስ እነማን ናቸው?
7 ለምሳሌ ያህል ‘ኢየሱስ ያስተማረውን ዓይነት አምልኮ እየተከተልን እንዳለን እንዴት እናውቃለን?’ የሚለውን ጥያቄ እንውሰድ። የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የትኞቹን መመዘኛዎች መመርመር አለብን? መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመካከላቸው ፍቅር ሊኖር እንደሚገባ ይገልጻል። (ዮሐንስ 13:34, 35) ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም መቀደስ አለባቸው። (ኢሳይያስ 12:4, 5፤ ማቴዎስ 6:9) እንዲሁም ይህን ስም ለሌሎች ማሳወቅ አለባቸው።—ዘጸአት 3:15፤ ዮሐንስ 17:16
8 እውነተኛው አምልኮ ተለይቶ የሚታወቅበት ሌላኛው ገጽታ ለአምላክ ቃል ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ማሳየት ነው። ስለ አምላክ ባሕርይና ዓላማ የሚገልጥ ብቸኛ መጽሐፍ ነው። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በተጨማሪም እውነተኛ ክርስቲያኖች ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኘው ብቸኛው የሰው ልጆች ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያውጃሉ። (ማርቆስ 13:10፤ ራእይ 21:1-4) ብልሹ ከሆነው ከዚህ ዓለም ፖለቲካና ርኩስ ከሆነው የአኗኗር መንገዱ ራሳቸውን ይለያሉ። (ዮሐንስ 15:19፤ ያዕቆብ 1:27፤ 4:4) በዛሬው ጊዜ እነዚህን መመዘኛዎች በትክክል የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ማስረጃዎቹ በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው በማለት በማያሻማ መንገድ መልሱን ይሰጣሉ።
ጥርጣሬ ቢፈጠርብን ምን ማድረግ አለብን?
9, 10. ያደሩብንን ጥርጣሬዎች ለማሸነፍ ምን ማድረግ እንችላለን?
9 እኛስ በጥርጣሬ ማዕበል ብንዋጥ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንደሚከተለው በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”—ምሳሌ 2:1-5፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
10 ይህ የሚያስገርም ሐሳብ አይደለም? የአምላክን ጥበብ አጥብቀን የምንሻ ከሆነ ‘የአምላክን እውቀት እናገኛለን።’ አዎን፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ የሚናገረውን ለመቀበልና እንደ ውድ ነገር አድርገን ለመያዝ ፈቃደኞች ከሆንን የእርሱን እውቀት ማግኘት እንችላለን። ይህም በጸሎትና በግል ጥናት ወደ ይሖዋ ዞር ማለትን ይጠይቃል። ከተሸሸገ ሃብት ጋር የተመሳሰለው ቃሉ ማንኛውንም ጥርጣሬ ሊያስወግድና የእውነትን ብርሃን እንድናይ ሊረዳን ይችላል።
11. ጥርጣሬ በኤልሳዕ ሎሌ ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነው?
11 ጸሎት በፍርሃትና በጥርጣሬ ተውጦ የነበረን አንድ የአምላክ አገልጋይ እንዴት እንደረዳው የሚያሳይ አንድ ግልጽ ምሳሌ በ2 ነገሥት 6:11-18 ላይ ይገኛል። የኤልሳዕ ሎሌ መንፈሳዊ ማስተዋል ጎድሎት ነበር። በሶርያ ጦር ተከብቦ የነበረውን የአምላክ ነቢይ ለመርዳት የሰማይ ሠራዊት በአካባቢው እንደነበር መገንዘብ ሳይችል ቀረ። ሎሌው በፍርሃት ተውጦ “ጌታዬ ሆይ፣ ወዮ! ምን እናደርጋለን?” በማለት ጮሆ ተናገረ። ኤልሳዕ ምን ምላሽ ሰጠ? “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ አለው።” ይሁን እንጂ ሎሌውን ማሳመን የሚቻለው እንዴት ነው? የሰማይ ሠራዊት መኖራቸውን ማየት አይችልም።
12. (ሀ) የሎሌው ጥርጣሬ የተወገደው እንዴት ነው? (ለ) ማንኛውም ዓይነት ጥርጣሬ ቢኖርብን እንዴት ማስወገድ እንችላለን?
12 “ኤልሳዕም:- አቤቱ፣ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፣ እባክህ፣ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፣ አየም፤ እነሆም፣ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።” ኤልሳዕን ይጠብቁ የነበሩትን የሰማይ ሠራዊት መመልከት እንዲችል ይሖዋ በዚህ መንገድ የሎሌውን ዓይን ከፈተለት። ይሁን እንጂ ዛሬ እንዲህ ያለ መለኮታዊ እርዳታ እናገኛለን ብለን መጠበቅ አይኖርብንም። የነቢዩ ሎሌ እምነቱን ለማጠንከር እንዲችል የሚያነበው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳልነበረው አትዘንጋ። እኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አለን። ጥሩ አድርገን ከተጠቀምንበት የእኛም እምነት በተመሳሳይ ሊጠነክር ይችላል። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ በሰማያዊ ችሎት እንደተቀመጠ በሚናገሩ በተለያዩ ዘገባዎች ላይ ልናሰላስል እንችላለን። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን የትምህርት መርሐ ግብር የሚደግፍ ሰማያዊ ድርጅት እንዳለው እንድንጠራጠር የሚያደርግ ምንም ምክንያት የለም።—ኢሳይያስ 6:1-4፤ ሕዝቅኤል 1:4-28፤ ዳንኤል 7:9, 10፤ ራእይ 4:1-11፤ 14:6, 7
ከሰይጣን ሽንገላ ተጠንቀቁ!
13. ሰይጣን አጥብቀን የያዝነውን እውነት ለማስለቀቅ የሚሞክረው ምን ዘዴዎችን በመጠቀም ነው?
13 ሰይጣን መንፈሳዊነታችንን ለማዳከምና አጥብቀን የያዝነውን እውነት ለማስለቀቅ የሚጠቀምባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው? ከሚጠቀምባቸው በርካታ ዘዴዎች መካከል አንዱ በተለያየ መንገድ የሚንጸባረቀው የጾታ ብልግና ነው። በጾታ ያበደው ይህ ዓለም የተከፈለው ተከፍሎ ደስታ ማግኘት አለብኝ በሚለው መርሆው በድብቅ የጾታ ብልግና መፈጸም ወይም ለአንድ ሌሊት አብሮ ማደር የተለመደ ነገር ሆኗል። ሲኒማዎች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና የቪዲዮ ፊልሞች እንዲህ ያለውን አኗኗር ያስፋፋሉ። ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች የመገናኛ ብዙሐንን በተለይ ደግሞ ኢንተርኔትን አጥለቅልቀዋል። የማወቅ ጉጉት አድሮባቸው እነዚህን ነገሮች ለማየት ወይም ለማንበብ የሚነሳሱ ሰዎች ራሳቸውን ለፈተና ያጋልጣሉ።—1 ተሰሎንቄ 4:3-5፤ ያዕቆብ 1:13-15
14. አንዳንድ ክርስቲያኖች በሰይጣን ሽንገላዎች የተታለሉት ለምንድን ነው?
14 አንዳንድ ክርስቲያኖች የማወቅ ጉጉታቸው እንዲያሸንፋቸው በመፍቀዳቸው እርቃንን አልፎ ተርፎም የጾታ ግንኙነት ሲፈጸም በግልጽ የሚያሳዩ ሥዕሎችን በማየት አእምሯቸውንና ልባቸውን በክለዋል። በሰይጣን ማባበያዎች በመታለል ራሳቸውን ወጥመድ ውስጥ ከተዋል። እንዲህ ያለው አካሄድ ብዙውን ጊዜ ለመንፈሳዊ ውድቀት ይዳርጋል። እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ‘ለክፋት ነገር ምንጊዜም ሕፃናት’ መሆን እንደሚገባ ዘንግተዋል። ‘በማስተዋል ችሎታቸው አልጎለመሱም።’ (1 ቆሮንቶስ 14:20 NW ) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶችና የአቋም ደረጃዎች ሳይጠብቁ በመቅረታቸው በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፍተኛ ውድቀት ይዳረጋሉ። “የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ” መልበስና ለአንድ አፍታም እንኳ ቢሆን አለማውለቅ አስፈላጊ መሆኑን ዘንግተዋል።—ኤፌሶን 6:10-13፤ ቆላስይስ 3:5-10፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19
ያለንን ነገር በአድናቆት መመልከት
15. አንዳንዶች ያገኙትን መንፈሳዊ ውርሻ ማድነቅ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
15 ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:32) አብዛኞቹ ምሥክሮች ከቀድሞ አኗኗራቸው መላቀቅና የነበራቸውን ሃይማኖታዊ ግንኙነት ማቋረጥ አስፈልጓቸዋል። ስለዚህ እውነት የሚያስገኘውን ነፃነት በቀላሉ ሊያደንቁ ይችላሉ። በሌላው በኩል ደግሞ እውነት ቤት ባሉ ወላጆች ያደጉ አንዳንድ ወጣቶች ያገኙትን መንፈሳዊ ሀብት ማድነቅ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ከዚህ ቀደም የሃሰት ሃይማኖት አባል ወይም በተድላ ወዳድነቱ፣ አደገኛ ዕፆችን በመውሰድና በፆታ ብልግና ተለይቶ የሚታወቀው የዚህ ዓለም ክፍል ሆነው አያውቁም። በዚህም የተነሳ እኛ ባለንበት መንፈሳዊ ገነትና በሰይጣን ብልሹ ዓለም መካከል ያለውን ጉልህ ልዩነት ሳይገነዘቡ ቀርተው ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች እንደቀረባቸው ሆኖ የተሰማቸውን የዓለምን መርዝ እንዲቀምሱ ለሚገፋፋ ፈተና እጃቸውን ሰጥተዋል!—1 ዮሐንስ 2:15-17፤ ራእይ 18:1-5
16. (ሀ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን? (ለ) ምን ነገር እንማራለን? ምንስ እንድናደርግ እንበረታታለን?
16 ሥቃይንና ሕመምን ለማወቅ እጃችንን እሳት ውስጥ መጨመር ይኖርብናል? ሌሎች ሰዎች ከደረሰባቸው መጥፎ ነገር መማር አንችልም? የቀረብን አንድ ነገር እንዳለ ለማወቅ ወደዚህ ዓለም “ጭቃ” መመለስ ይኖርብናል? (2 ጴጥሮስ 2:20-22) ጴጥሮስ ቀድሞ የሰይጣን ዓለም ክፍል የነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” በማለት ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። በእርግጥም ደግሞ ሰዎች ምን ያህል ልቅ ኑሮ እንደሚኖሩ ለማየት በዓለም ውስጥ ያለውን ‘ያዘቀጠ ምግባር’ መከተል አያስፈልገንም። (1 ጴጥሮስ 4:3, 4 NW ) ከዚያ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መስጫ ማዕከል በሆኑት በመንግሥት አዳራሾቻችን ውስጥ ይሖዋ ያወጣቸውን ከፍተኛ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃዎች እንማራለን። እንዲሁም እውነትን እንደያዝን ለማረጋገጥና እውነትን የራሳችን ለማድረግ የማመዛዘን ችሎታችንን እንድንጠቀም በየጊዜው ማበረታቻ ይሰጠናል።—ኢያሱ 1:8፤ ሮሜ 12:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14-17
ስማችን እንዲያው መጠሪያ ብቻ አይደለም
17. ውጤታማ የይሖዋ ምሥክሮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
17 እውነትን የራሳችን ካደረግን ባገኘነው አመቺ አጋጣሚ ሁሉ እውነትን ለሌሎች ለማካፈል እንፈልጋለን። እንዲህ ሲባል ግን ፍላጎት የሌላቸውን ሰዎች በማስገደድ እውነትን እንዲቀበሉ እናደርጋለን ማለት አይደለም። (ማቴዎስ 7:6) ከዚያ ይልቅ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለሌሎች ለማሳወቅ ፈጽሞ አናፍርም። አንድ ሰው ቀና የሆኑ ጥያቄዎች በመጠየቅ ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመውሰድ ትንሽ ፍላጎት እንዳለው ቢያሳይ እንኳ ተስፋችንን ለማካፈል ፈጣኖችና ዝግጁዎች እንሆናለን። ይህም የትም ቦታ ብንሆን ማለትም በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በሱቅ ወይም በመዝናኛ ቦታ ብንሆን ጽሑፎችን ሁልጊዜ መያዝ እንዳለብን ያሳስበናል።—1 ጴጥሮስ 3:15
18. ክርስቲያን መሆናችንን በግልጽ ማሳወቃችን በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው?
18 ክርስቲያን መሆናችንን በግልጥ ማሳወቃችን የሰይጣንን መሠሪ ጥቃቶች መመከት የሚያስችል ጥንካሬ ያስገኝልናል። ልደትን ወይም የገና ግብዣን ወይም ሎተሪን በተመለከተ አንድ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ የሥራ ባልደረቦቻችን “አታስቸግሯት። እርሷ የይሖዋ ምሥክር ናት” በማለት ብዙውን ጊዜ ስለ እኛ ይናገራሉ። በተመሳሳይም እኛ ባለንበት የብልግና ቀልድ ከማውራት እንዲቆጠቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ስለዚህ ክርስቲያናዊ አቋማችንን ማሳወቃችን በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሐዋርያው ጴጥሮስም “በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ” በማለት ተናግሯል።—1 ጴጥሮስ 3:13, 14
19. ወደ መጨረሻው ቀን በጣም ዘልቀን የገባን መሆናችንን እንዴት እናውቃለን?
19 እውነትን የራሳችን ማድረጋችን የሚያስገኝልን ሌላው ጥቅም በዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ላይ እንደምንኖር በእርግጠኝነት እንድናምን ያደርገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ትንቢቶች በዚህ በእኛ ዘመን የመጨረሻ ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳሉ እናውቃለን።a ጳውሎስ ‘የመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ይሆናል’ ብሎ የተናገረው ማስጠንቀቂያ እውነት መሆኑን ባለፈው መቶ ዘመን የተከሰቱት አሰቃቂ ክስተቶች በማያሻማ መንገድ አረጋግጠዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማርቆስ 13:3-37) በቅርቡ የወጣ አንድ ጋዜጣ “የአረመኔዎች ዘመን በሚል ስም ሲታወስ የሚኖር” በሚል ርዕስ 20ኛውን መቶ ዘመን በሚመለከት አትቶ ነበር። ይኸው የጋዜጣ ርዕስ “1999 በነፍስ ግድያ ተለይቶ በሚታወቀው በሃያኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ከሁሉ የከፋ የነፍስ ግድያ የተፈጸመበት ዓመት ነው” በማለት ተናግሯል።
20. አሁን ምን የምናደርግበት ጊዜ ነው?
20 አሁን የምንወላውልበት ጊዜ አይደለም። ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ከዚህ ቀደም ሆኖ በማያውቅ መጠን በዓለም ዙሪያ እየተካሄደ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ይሖዋ እየባረከው እንዳለ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አለ። (ማቴዎስ 24:14) እውነትን የራስህ አድርግ፤ ለሌሎችም አካፍል። ወደፊት የዘላለም ሕይወት ማግኘትህ የተመካው አሁን በምታደርገው ነገር ላይ ነው። ወደኋላ ማለት የይሖዋን በረከት አያስገኝም። (ሉቃስ 9:62) ከዚያ ይልቅ ‘ድካማችን በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቀን የምንደላደል፣ የማንነቃነቅ፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የበዛልን’ የምንሆንበት ጊዜ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:58
ታስታውሳለህን?
• ጥርጣሬን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው?
• ከኤልሳዕ ሎሌ ምን ልንማር እንችላለን?
• ራሳችንን አለማቋረጥ መጠበቅ ያለብን ከየትኛው የሥነ ምግባር ፈተና ነው?
• የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን በግልጽ ማሳወቅ ያለብን ለምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የጥር 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12-14ን ተመልከት። አንቀጽ 13-18 ከ1914 ጀምሮ በመጨረሻዎቹ ዘመን እንደምንኖር የሚያረጋግጡ ስድስት አሳማኝ ማስረጃዎችን ያቀርባል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማጥናትና መጸለይ ጥርጣሬን ለማስወገድ ይረዳል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኤልሳዕ ሎሌ በተመለከተው ራእይ ጥርጣሬው ተወግዶለታል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤኒን በሚገኘው በዚህ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ እንደሚታየው በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የይሖዋን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎች እንማራለን