ቤተሰቦች፣ የጉባኤው ክፍል በመሆን አምላክን አወድሱ
“እግዚአብሔርን በሕዝብ ጉባኤ መካከል ሆኜ አመሰግነዋለሁ።”—መዝሙር 26:12 “የ1980 ትርጉም”
1. በቤት ውስጥ ከማጥናትና ከመጸለይ በተጨማሪ የእውነተኛ አምልኮ አንዱ ዓቢይ ክፍል ምንድን ነው?
ይሖዋን ማምለክ በመጸለይና እቤት ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የአምላክ ጉባኤ ክፍል በመሆን እንቅስቃሴ ማድረግንም የሚጨምር ነው። የጥንቶቹ እስራኤላውያን የአምላክን ሕግ ተምረው በዚያው መንገድ መጓዝ ይችሉ ዘንድ “ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም” እንዲሰበስቡ ታዝዘው ነበር። (ዘዳግም 31:12፤ ኢያሱ 8:35) ሽማግሌዎች፣ “ጎልማሶችና ቆነጃጅቶች” የይሖዋን ስም በማወደስ ረገድ ተካፋይ እንዲሆኑ ተበረታተዋል። (መዝሙር 148:12, 13) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም ተመሳሳይ ዝግጅት አለ። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የመንግሥት አዳራሾች ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አድማጮችን በሚያሳትፉ ክፍሎች በነፃነት የሚካፈሉ ሲሆን ብዙዎቹም በዚህ መንገድ ተሳትፎ ማድረጋቸው ያስደስታቸዋል።—ዕብራውያን 10:23-25
2. (ሀ) ልጆች በስብሰባዎች እንዲደሰቱ በመርዳት ረገድ ዝግጅት ቁልፍ ሚና ይጫወታል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የእነማን ምሳሌነት አስፈላጊ ነው?
2 እርግጥ ነው ልጆች ጤናማ በሆኑት የጉባኤ እንቅስቃሴዎች የመሳተፍ ልማድ እንዲኖራቸው ማድረጉ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ከወላጆቻቸው ጋር በስብሰባ የሚገኙ አንዳንድ ልጆች ከስብሰባዎች ደስታ የማያገኙ ቢሆኑ ችግሩ ምን ሊሆን ይችላል? እርግጥ ነው ብዙ ልጆች አንድን ነገር በትኩረት የመከታተል ችሎታቸው አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ወዲያው ይሰለቻሉ። አስቀድሞ መዘጋጀት ይህን ችግር ለማስወገድ ሊረዳ ይችላል። ልጆች አስቀድመው ዝግጅት ካላደረጉ በስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ አይችሉም። (ምሳሌ 15:23) ዝግጅት ካላደረጉ መንፈሳዊ እድገት በማድረግ ደስታ ሊያገኙ አይችሉም። (1 ጢሞቴዎስ 4:12, 15) ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል? በመጀመሪያ ወላጆች እኔ ራሴ ለስብሰባዎች እዘጋጃለሁን? ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ የሚያሳዩት ምሳሌነት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። (ሉቃስ 6:40) ለቤተሰብ ጥናት ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ ማውጣትም በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
ልብን ማነጽ
3. በቤተሰብ ጥናት ወቅት ልብን ለማነጽ ልዩ ጥረት መደረግ የሚኖርበት ለምንድን ነው? ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል?
3 የቤተሰብ ጥናት እንዲያው አእምሮን በእውቀት ለመሙላት የሚደረግ ብቻ ሳይሆን ልብንም ለማነጽ መሆን ይኖርበታል። ይህም የቤተሰቡ አባላት የገጠሟቸውን ችግሮች ጠንቅቆ ማወቅንና ለእያዳንዱ ግለሰብ ፍቅራዊ አሳቢነት ማሳየትን ይጠይቃል። ይሖዋ ‘ልብን ይመረምራል።’—1 ዜና መዋዕል 29:17
4. (ሀ) ‘ልብ የጎደለው’ ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ‘ልብ ማግኘት’ ምን ማድረግን ይጠይቃል?
4 ይሖዋ የልጆቻችንን ልብ ሲመረምር ምን ነገር ያገኛል? ብዙዎች አምላክን እንደሚወዱ ይናገራሉ፤ ይህም የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ልጅ ወይም በቅርቡ ስለ ይሖዋ መማር የጀመረ አንድ ግለሰብ በይሖዋ መንገዶች የሚኖረው ተሞክሮ በጣም የተወሰነ ነው። ያካበተው ተሞክሮ ውስን በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ‘ልብ የጎደለው’ ሊሆን ይችላል። የውስጥ ዝንባሌው ሁሉ መጥፎ ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም አንድ ሰው ልቡ አምላክን የሚያስደስት ልብ እንዲሆን ለማድረግ ጊዜ ያስፈልገዋል። ይህም ሰብዓዊ አለፍጽምና የሚፈቅደውን ያህል አስተሳሰቡን፣ ምኞቱን፣ ፍቅሩንና በሕይወቱ ውስጥ የሚያወጣቸውን ግቦች አምላክ ከሚፈልገው ነገር ጋር ማስማማትን ይጠይቃል። አንድ ሰው በዚህ መንገድ ውስጣዊ ማንነቱን በአምላካዊ መንገድ ለመቅረጽ የተቻለውን ሁሉ በሚያደርግበት ጊዜ “ልብ እያገኘ” ነው ማለት ነው።—ምሳሌ 9:4 NW፤ 19:8 NW
5, 6. ወላጆች ልጆቻቸው ‘ልብ እንዲያገኙ’ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?
5 ወላጆች ልጆቻቸው ‘ልብ እንዲያገኙ’ ሊረዷቸው ይችላሉ? እርግጥ ነው፣ በአንድ ሰው ውስጥ ጥሩ የልብ ዝንባሌ ማስቀመጥ የሚችል ማንም ሰው የለም። ሁላችንም የመምረጥ ነፃነት ያለን ሲሆን አብዛኛው ነገር የተመካው ለማሰብ በምንመርጠው ነገር ላይ ነው። ይሁን እንጂ ወላጆች አስተዋይ በመሆን ዘወትር ልጆቻቸው ሐሳባቸውን እንዲገልጹ በማድረግ በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ሊያውቁና በየትኛው አቅጣጫ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሊገነዘቡ ይችላሉ። ‘ስለዚህ ጉዳይ እንዴት ይሰማሃል?’ እና ‘በእርግጥ አንተ ማድረግ የምትፈልገው ምንድን ነው?’ የሚሉትን የመሰሉ ጥያቄዎችን ተጠቀሙ። ከዚያም በጥሞና አዳምጡ። ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ። (ምሳሌ 20:5) ልባቸውን ለመንካት ከፈለጋችሁ ደጎች፣ ችግራቸውን የምትረዱና አፍቃሪ መሆን ይኖርባችኋል።
6 ጤናማ የሆነ ዝንባሌ በውስጣቸው ለመትከል አዘውትራችሁ ስለ መንፈስ ፍሬዎችና ስለ እያንዳንዱ ዘርፍ ተወያዩ። ከዚያም ያንን ባሕርይ ለማዳበር በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ሥሩ። (ገላትያ 5:22, 23) ለይሖዋና ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርን ገንቡ። ይህንን የምታደርጉት እነርሱን መውደድ አለብን ብሎ በመናገር ብቻ ሳይሆን የምንወዳቸው ለምን እንደሆነ ምክንያቱንና ይህንንም ፍቅር እንዴት ልናሳይ እንደምንችል በማብራራት ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም በምክንያት እያብራራችሁ እንደዚያ የማድረግ ምኞታቸውን አጠናክሩላቸው። የተሳሳቱ አስተሳሰቦች፣ ንግግሮችና ጠባዮች ስለሚያስከትሉት መጥፎ ውጤት በመወያየት ከእነዚህ ባሕርያት የመራቅን ምኞት በውስጣቸው ገንቡ። (አሞጽ 5:15፤ 3 ዮሐንስ 11) የአንድ ሰው አስተሳሰብ፣ ንግግርና ጠባይ ጥሩም ይሁን መጥፎ ከይሖዋ ጋር በመሠረተው ዝምድና ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ግልጽ አድርጉላቸው።
7. ልጆች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ቅርርብ እንደጠበቁ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና ውሳኔ እንዲያደርጉ ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል?
7 አንድ ልጅ ችግር በሚገጥመው ወይም አንድ ትልቅ ውሳኔ ማድረግ በሚያስፈልገው ጊዜ እንዲህ ብለን ልንጠይቀው እንችላለን:- ‘ይሖዋ ይህን እንዴት የሚመለከተው ይመስልሃል? እንዲህ እንድትል ያደረገህ ስለ ይሖዋ የምታውቀው ምን ነገር ነው? ይህን ጉዳይ ለእርሱ በጸሎት ነግረኸዋል?’ በተቻለ መጠን ገና ከሕፃንነታቸው አንስታችሁ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ መርምረው እንዲያውቁና በሥራ ለመተርጎም ልባዊ ጥረት እንዲያደርጉ አሰልጥኗቸው። ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ የግል ዝምድና እየመሠረቱ ሲሄዱ በእርሱ መንገዶች መጓዝ አስደሳች እየሆነላቸው ይመጣል። (መዝሙር 119:34, 35) ይህም ከእውነተኛው አምላክ ጉባኤ ጋር የመተባበር መብት ማግኘታቸውን እንዲያደንቁት ያደርጋቸዋል።
ለጉባኤ ስብሰባዎች መዘጋጀት
8. (ሀ) በቤተሰብ ጥናታችን ወቅት ትኩረታችንን የሚሹ ጉዳዮችን በሙሉ ለማካተት ምን ነገር ሊረዳን ይችላል? (ለ) እንዲህ ዓይነቱ ጥናት ምን ያክል ጠቃሚ ነው?
8 የቤተሰብ ጥናት በሚደረግበት ጊዜ ትኩረት ማግኘት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ሁሉንም እንዴት ማካተት ይቻላል? ሁሉን በአንድ ጊዜ ማከናወን አይቻልም። ሆኖም በዝርዝር መጻፉ ጠቃሚ ሆኖ ታገኙት ይሆናል። (ምሳሌ 21:5) ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህን ዝርዝር መለስ ብላችሁ እየተመለከታችሁ ልዩ ትኩረት የሚያሻው የትኛው እንደሆነ መርምሩ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚያደርገውን እድገት በንቃት ተከታተሉ። ለቤተሰብ ጥናት እንዲህ ያለ ዝግጅት ማድረጉ የክርስቲያናዊ ትምህርት አንዱ ዓቢይ ክፍል ከመሆኑም በላይ ለአሁኑ ሕይወት ያስታጥቀናል፤ ለወደፊቱ የዘላለም ሕይወትም ያዘጋጀናል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
9. ለስብሰባዎች መዘጋጀትን በሚመለከት በቤተሰብ ጥናታችን ወቅት ቀስ በቀስ ልንሠራባቸው የሚገቡ ምን ግቦች አሉ?
9 የቤተሰብ ጥናታችሁ ለጉባኤ ስብሰባዎች ዝግጅት ማድረግንም ይጨምራል? አንድ ላይ ሆናችሁ በምታጠኑበት ጊዜ ደረጃ በደረጃ ልታከናውኗቸው የምትችሏቸው በርካታ እቅዶች ይኖራሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን ለማከናወን ሳምንታት፣ ወራት ሌላው ቀርቶ ዓመታት ሊያስፈልግ ይችላል። አነዚህን ግቦች ተመልከቱ:- (1) እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ዝግጁ መሆን፤ (2) በራሱ አነጋገር ለመመለስ ጥረት ማድረግ፤ (3) በመልሱ ውስጥ ጥቅሶችን ማከል እንዲሁም (4) ትምህርቱን በግለሰብ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግን ግብ በማድረግ ማብላላት ናቸው። አንድ ግለሰብ እውነትን የራሱ እንዲያደርግ እነዚህ ነገሮች ሊረዱት ይችላሉ።—ምሳሌ 25:4, 5
10. (ሀ) ለእያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ እንዴት ትኩረት ልንሰጥ እንችላለን? (ለ) እንዲህ ማድረጉስ የሚክስ የሆነው ለምንድን ነው?
10 የቤተሰብ ጥናታችሁ በሳምንቱ ውስጥ በሚጠናው መጠበቂያ ግንብ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም በግልም ሆነ በቤተሰብ መልክ ለጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት፣ ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና ለአገልግሎት ስብሰባ የመዘጋጀትንም አስፈላጊነት አቅልላችሁ አትመልከቱ። እነዚህም ቢሆኑ በይሖዋ መንገድ እንድንጓዝ የሚያስተምሩን አስፈላጊ የሆኑ የስብሰባ ፕሮግራሞች ናቸው። አልፎ አልፎ በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆናችሁ ለስብሰባዎች መዘጋጀት ትችሉ ይሆናል። አንድ ላይ ሆናችሁ በመሥራታችሁ የማጥናት ችሎታችሁ ይሻሻላል። በውጤቱም ከስብሰባዎች በርካታ ጥቅም ማግኘት ይቻላል። ሌሎች ጉዳዮችንም ጨምሮ ለእነዚህ ስብሰባዎች አዘውትሮ መዘጋጀት የሚያስገኘውን ጥቅምና ለዚህም የሚሆን የተወሰነ ጊዜ መመደቡ ያለውን ጠቀሜታ ተወያዩበት።—ኤፌሶን 5:15-17
11, 12. በጉባኤ ለሚዘመሩ መዝሙሮች አስቀድመን መዘጋጀታችን ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው? መዘጋጀት የምንችለውስ እንዴት ነው?
11 “የአምላክ የሕይወት መንገድ” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የስብሰባዎቻችን ሌላ ገጽታ ለሆነው ለመዝሙር ዝግጅት እንድናደርግ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ይህን ምክር ሠርታችሁበታል? እንዲህ ማድረጋችን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲቀረጽና በዚያውም ከጉባኤ ስብሰባዎች የምናገኘው ደስታ ከፍ እንዲል ሊያደርግልን ይችላል።
12 በስብሰባዎች ላይ እንዲዘመሩ ፕሮግራም የተያዘላቸውን መዝሙሮች ቃላት በማንበብና በቃላቱ ትርጉም ላይ ውይይት በማድረግ መዘጋጀት ከልባችን እንድንዘምር ሊረዳን ይችላል። በጥንቱ የእስራኤል አምልኮ ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያዎች ከፍተኛ ቦታ ነበራቸው። (1 ዜና መዋዕል 25:1፤ መዝሙር 28:7 የ1980 ትርጉም) ከቤተሰባችሁ መካከል የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት የሚችል ይኖር ይሆን? ታዲያ በሳምንቱ ውስጥ ከሚዘመሩት የመንግሥት መዝሙሮች መካከል አንዱን ለመለማመድና ከዚያም በቤተሰብ አንድ ላይ ለመዘመር የሙዚቃ መሣሪያውን ለምን አትጠቀሙበትም። በሌላም በኩል በቴፕ ክር የተዘጋጁትን መዝሙሮች መጠቀም ይቻላል። በአንዳንድ አገር የሚኖሩ ወንድሞቻችን ያለ ሙዚቃ እገዛ በቃላቸው ብቻ ውብ አድርገው ይዘምራሉ። ብዙውን ጊዜ በመንገድ ላይ እየሄዱ ወይም በማሳ ላይ ሥራቸውን እያከናወኑ በዚያው ሳምንት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩትን መዝሙሮች ይዘምራሉ።—ኤፌሶን 5:19
በቤተሰብ መልክ ለመስክ አገልግሎት መዘጋጀት
13, 14. ልባችንን ለመስክ አገልግሎት ለማዘጋጀት በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መወያየቱ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች መመሥከር የሕይወታችን ዓቢይ ክፍል ነው። (ኢሳይያስ 43:10-12፤ ማቴዎስ 24:14) ወጣቶችም ሆንን በእድሜ የገፋን አስቀድመን የምንዘጋጅ ከሆነ በዚህ እንቅስቃሴ የበለጠ ደስታና የተሻለ ውጤት ልናገኝ እንችላለን። ታዲያ በቤተሰብ ደረጃ ይህን እንዴት ልናደርግ እንችላለን?
14 የአምልኳችን ክፍል እንደሆኑት እንደ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ልባችንን ዝግጁ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ስለምናደርገው ነገር ብቻ ሳይሆን ለምን እንደምናደርገውም ጭምር መወያየት ይኖርብናል። በንጉሥ ኢዮሳፋጥ ዘመን ሕዝቡ በመለኮታዊው ሕግ በኩል መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ሕዝቡ “ገና ልባቸውን . . . አላዘጋጁም ነበር።” ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ ከእውነተኛው አምልኮ በሚያርቅ ወጥመድ ውስጥ ለመግባት ራሳቸውን አጋልጠው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 20:33፤ 21:11) ግባችን በመስክ አገልግሎት ያሳለፍነውን ሰዓት ሪፖርት ማድረግ ወይም ጽሑፎችን ማበርከት ብቻ አይደለም። አገልግሎታችን ለይሖዋና ሕይወት እንዲመርጡ አጋጣሚ ማግኘት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ያለንን ፍቅር የምናረጋግጥበት መሆን ይገባዋል። (ዕብራውያን 13:15) ይህ ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራው’ ሥራ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:9) እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! ይህንንም የምናደርገው ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመተባበር በአገልግሎት ስንካፈል ነው። (ራእይ 14:6, 7) ለዚህ ሥራ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ሳምንታዊውን ጥናት ወይም ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ ባለ ተስማሚ ጥቅስ ላይ ውይይት ከምናደርግበት የቤተሰብ ውይይታችን የተሻለ ሌላ ምን ጊዜ ሊኖር ይችላል?
15. በቤተሰብ መልክ አንድ ላይ ሆነን ለመስክ አገልግሎት መቼ ልንዘጋጅ እንችላለን?
15 የቤተሰብህን አባላት በሳምንቱ ውስጥ ለሚደረጉት የመስክ አገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ ከቤተሰብ ጥናታችሁ ላይ አልፎ አልፎ የተወሰነ ጊዜ ትመድባለህ? እንዲህ ማድረጉ በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) አገልግሎታቸው ትርጉም ያለውና ውጤታማ እንዲሆን ሊረዳቸው ይችላል። አልፎ አልፎ መላውን የጥናት ክፍለ ጊዜ የዚህ ዓይነቱ ዝግጅት ለማድረግ ልታውሉት ትችሉ ይሆናል። የቤተሰብ ጥናታችሁን አጥንታችሁ ስትጨርሱ ወይም በሳምንቱ መካከል ባለ በአንዱ ቀን ላይ የመስክ አገልግሎት የተለያዩ ዘርፎችን የሚመለከቱ ውይይቶችን ልታደርጉ ትችላላችሁ።
16. በአንቀጹ ውስጥ የሰፈሩት ደረጃዎች እያንዳንዳቸው ያላቸውን ዋጋማነት ግለጽ።
16 የቤተሰብ ጥናቱ ክፍለ ጊዜ የሚከተሉትን ነጥቦች ደረጃ በደረጃ በመፈጸም ላይ ትኩረት ሊያደርግ ይችላል። (1) አጋጣሚው የሚፈቅድ ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጥቅስ ማንበብን የሚጨምር ጥሩ ልምምድ የተደረገበት መግቢያ ማዘጋጀት። (2) በተቻለ መጠን እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የአገልግሎት ቦርሳ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማስታወሻ ደብተር፣ ብዕር ወይም እርሳስ፣ ትራክቶችና በጥሩ ሁኔታ የተያዙ ሌሎች ጽሑፎች መያዙን ማረጋገጥ። የአገልግሎት ቦርሳው በብዙ ወጪ የተገዛ መሆን ባያስፈልገውም በጥሩ ሁኔታ የተያዘ መሆን ይኖርበታል። (3) መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት የትና መቼ ሊደረግ እንደሚችል ተወያዩ። እንዲህ ያለ መመሪያ ከሚሰጥባቸው ጊዜያት በኋላ በመስክ አገልግሎት አንድ ላይ ሆናችሁ የምትሠሩበት ጊዜ መድቡ። የማሻሻያ ሐሳብ ስጡ፤ ሆኖም በአንድ ጊዜ በርካታ ነጥቦችን የሚዳስስ ምክር አትስጡ።
17, 18. (ሀ) የመስክ አገልግሎታችን ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆን የሚረዳው በቤተሰብ የሚደረገው የትኛው ዓይነት ዝግጅት ነው? (ለ) በየሳምንቱ ልናደርገው የምንችለው የትኛውን የዚህ ዝግጅት ዘርፍ ነው?
17 ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ እንዲሠሩት የሰጣቸው ዋነኛ ሥራ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ደቀ መዛሙርት ማድረግ ከመስበክ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጨምራል። ማስተማርን ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ውጤታማ እንድትሆኑ የቤተሰብ ጥናታችሁ እርዳታ ሊያበረክት የሚችለው እንዴት ነው?
18 በቤተሰብ አንድ ላይ ሆናችሁ ለማን ተመላልሶ መጠየቅ ቢደረግ የተሻለ እንደሚሆን ተወያዩ። አንዳንዶቹ ጽሑፍ ወስደው ይሆናል፤ ሌሎች ደግሞ ጥሩ አድርገው አዳምጠው ይሆናል። ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት የተገኙ ወይም በገበያ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተመሠከረላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። የአምላክ ቃል ይምራችሁ። (መዝሙር 25:9፤ ሕዝቅኤል 9:4) በዚያ ሳምንት ማንኛችሁ ለማን ተመላልሶ መጠየቅ እንደምታደርጉ ወስኑ። ስለምን ጉዳይ ትነጋገራላችሁ? በቤተሰብ ደረጃ ውይይት ማድረጉ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል እንዲዘጋጅ ሊረዳው ይችላል። ፍላጎት ላሳየው ግለሰብ የምታካፍሉትን ጥቅስና አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? ከተባለው ብሮሹር ወይም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ የምትጠቅሷቸውን ተስማሚ ነጥቦች አስቀድማችሁ ምረጡ። ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርጉበት ወቅት በርካታ ነጥቦችን ለመሸፈን አትሞክሩ። በሚቀጥለው ጉብኝት ለቤቱ ባለቤት የምትመልሱት አንድ ጥያቄ አቅርባችሁ ተመለሱ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለማን ተመላልሶ መጠየቅ እንደሚያደርግ፣ ተመላልሶ መጠየቁን ስለሚያደርግበት ቀንና ምን ነገር ለመፈጸም አልሞ መነሳት እንዳለበት መወያየቱን ለምን የሳምንታዊው የቤተሰብ ጥናታችሁ ክፍል አታደርጉትም። እንዲህ ማድረጉ መላው ቤተሰብ በሚያደርገው የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴ ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆን ይረዳል።
የይሖዋን መንገድ ማስተማራችሁን ቀጥሉ
19. የቤተሰብ አባላት በይሖዋ መንገድ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ምን ማግኘት ይኖርባቸዋል? ለዚህስ ምን ነገሮች አስተዋጽዖ ያበረክታሉ?
19 በዚህ ክፉ ዓለም የቤተሰብ ራስ መሆን በጣም ተፈታታኝ ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ የይሖዋ አገልጋዮችን መንፈሳዊነት ለመደምሰስ ቆርጠው ተነስተዋል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ከዚህም በላይ በዛሬው ጊዜ በእናንተ በወላጆች ላይ በተለይ ደግሞ ነጠላ ወላጅ በሆናችሁት ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ይህ ነው አይባልም። ማድረግ የምትፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ ለማከናወን የሚያስችል ጊዜ ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው። በአንድ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት አንድ ሐሳብ እንኳ ቢሆን ጥረታችሁ የሚያስቆጭ አይሆንም። እንዲሁም ቀስ በቀስ የቤተሰብ ጥናታችሁ ፕሮግራም እየጎለበተ ይሄዳል። የቅርብ ዘመዶቻችሁ በይሖዋ መንገድ በታማኝነት ሲጓዙ መመልከቱ ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነው። በይሖዋ መንገድ ላይ በተሳካ ሁኔታ ለመጓዝ የቤተሰብ አባላት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና በመስክ አገልግሎት በመካፈል ደስታ የሚያገኙ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ ሁኔታ እውን ሊሆንላችሁ የሚችለው ስትዘጋጁ ማለትም ልብን የሚገነባና እያንዳንዳችሁ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት ስታደርጉ ብቻ ነው።
20. በርካታ ወላጆች በ3 ዮሐንስ 4 ላይ የተገለጸውን የመሰለ ነገር እንዲያገኙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
20 ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈሳዊ የረዳቸውን ሰዎች በማስመልከት ሲጽፍ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” ብሏል። (3 ዮሐንስ 4) ግልጽ ዓላማ በአእምሮ በመያዝ የሚመራ የቤተሰብ ጥናትና እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚያስፈልገውን ለማሟላት በደግነት ጠቃሚ እርዳታ የሚሰጥ የቤት ራስ መኖሩ ቤተሰቡ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ደስታ እንዲያገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ወላጆች ለይሖዋ የሕይወት መንገድ አድናቆት በማዳበር ቤተሰቦቻቸው ከሁሉም በተሻለው የሕይወት መንገድ ደስ እያላቸው እንዲጓዙ ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ።—መዝሙር 19:7-11
ልታብራራ ትችላለህ?
◻ ለስብሰባዎች መዘጋጀት ለልጆቻችን በጣም ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ወላጆች ልጆቻቸው ‘ልብ እንዲያገኙ’ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?
◻ ለሁሉም ስብሰባዎች ዝግጅት በማድረግ በኩል የቤተሰብ ጥናት እገዛ ሊያበረክት የሚችለው እንዴት ነው?
◻ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ለመስክ አገልግሎት መዘጋጀት ይበልጥ ውጤታማ እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቤተሰብ ጥናታችሁ ለጉባኤ ስብሰባዎች ዝግጅት ማድረግንም ሊያካትት ይችላል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩትን መዝሙሮች መለማመድ ጠቃሚ ነው