19 ሞኝ ከመሆንና ውሸት ከመናገር
ድሃ ሆኖ ንጹሕ አቋምን ጠብቆ መመላለስ ይሻላል።+
2 እውቀት የሌለው ሰው ጥሩ አይደለም፤+
ችኩል ሰውም ኃጢአት ይሠራል።
3 የሰውን መንገድ የሚያጣምምበት የገዛ ሞኝነቱ ነው፤
ልቡም በይሖዋ ላይ ይቆጣል።
4 ሀብት ብዙ ወዳጆችን ይስባል፤
ድሃን ግን ጓደኛው እንኳ ይተወዋል።+
5 ሐሰተኛ ምሥክር መቀጣቱ አይቀርም፤+
ባወራ ቁጥር የሚዋሽም ከቅጣት አያመልጥም።+
6 ብዙዎች በተከበረ ሰው ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ይጥራሉ፤
ስጦታ ከሚሰጥ ሰው ጋር ደግሞ ሁሉም ይወዳጃል።
7 ድሃን ወንድሞቹ ሁሉ ይጠሉታል፤+
ጓደኞቹማ ምን ያህል ይርቁት!+
እየተከታተለ ሊለማመጣቸው ይሞክራል፤ ምላሽ የሚሰጠው ግን የለም።
8 ማስተዋል የሚያገኝ ሰው ሁሉ ራሱን ይወዳል።+
ጥልቅ ግንዛቤን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ የሚመለከት ሁሉ ይሳካለታል።+
9 ሐሰተኛ ምሥክር መቀጣቱ አይቀርም፤
ባወራ ቁጥር የሚዋሽም ይጠፋል።+
10 ሞኝ ሰው ተንደላቆ መኖር አይገባውም፤
አገልጋይ መኳንንትን ቢገዛማ ምንኛ የከፋ ነው!+
11 ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል፤+
በደልንም መተዉ ውበት ያጎናጽፈዋል።+
12 የንጉሥ ቁጣ እንደ አንበሳ ግሳት ነው፤+
ሞገሱ ግን በሣር ላይ እንዳለ ጤዛ ነው።
13 ሞኝ ልጅ በአባቱ ላይ መከራ ያመጣል፤+
ጨቅጫቃ ሚስትም ያለማቋረጥ እንደሚያንጠባጥብ ጣሪያ ናት።+
14 ቤትና ሀብት ከአባቶች ይወረሳል፤
ልባም ሚስት ግን የምትገኘው ከይሖዋ ነው።+
15 ስንፍና ከባድ እንቅልፍ ላይ ይጥላል፤
ታካች ሰውም ይራባል።+
16 ትእዛዝን የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል፤+
መንገዱን ቸል የሚል ይሞታል።+
17 ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤+
ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል።+
18 ገና ተስፋ ሳለ ልጅህን ገሥጽ፤+
ለእሱም ሞት ተጠያቂ አትሁን።+
19 ግልፍተኛ ሰው ይቀጣል፤
ልታድነው ብትሞክር እንኳ በተደጋጋሚ እንዲህ ለማድረግ ትገደዳለህ።+
20 የኋላ ኋላ ጥበበኛ እንድትሆን
ምክርን ስማ፤ ተግሣጽንም ተቀበል።+
21 ሰው በልቡ ብዙ ነገር ያቅዳል፤
የሚፈጸመው ግን የይሖዋ ፈቃድ ነው።+
22 የሰው ተወዳጅ ባሕርይ ታማኝ ፍቅሩ ነው፤+
ውሸታም ከመሆን ድሃ መሆን ይሻላል።
23 ይሖዋን መፍራት ወደ ሕይወት ይመራል፤+
እንዲህ የሚያደርግ ሰው ጥሩ እረፍት ያገኛል፤ ጉዳትም አይደርስበትም።+
24 ሰነፍ እጁን ወደ ሳህን ያጠልቃል፤
ሆኖም ወደ አፉ እንኳ መመለስ ይሳነዋል።+
25 ተሞክሮ የሌለው ብልህ+ እንዲሆን ፌዘኛን ምታው፤+
ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኝም አስተዋይ የሆነን ሰው ውቀሰው።+
26 አባቱን የሚበድልና እናቱን የሚያባርር ልጅ
ኀፍረትና ውርደት ያመጣል።+
27 ልጄ ሆይ፣ ተግሣጽን መስማት ከተውክ
እውቀት ከሚገኝበት ቃል ትርቃለህ።
28 የማይረባ ምሥክር በፍትሕ ላይ ያፌዛል፤+
የክፉዎችም አፍ ክፋትን ይሰለቅጣል።+
29 ፌዘኞች ፍርድ ይጠብቃቸዋል፤+
ለሞኞች ጀርባ ደግሞ ዱላ ተዘጋጅቷል።+