የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ምሳሌ 3:5, 6—“በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ”
“በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6 አዲስ ዓለም ትርጉም
“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።”—ምሳሌ 3:5, 6 የ1954 ትርጉም
የምሳሌ 3:5, 6 ትርጉም
አስፈላጊ ውሳኔዎችን ስናደርግ በራሳችን ከመታመን ይልቅ የይሖዋንa አመራር ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
“በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን።” ማንኛውንም ነገር አምላክ በሚፈልገው መንገድ የምናከናውን ከሆነ በእሱ እንደምንታመን እናሳያለን። ሙሉ በሙሉ በአምላክ መታመን ይኖርብናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልብ የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ነው፤ ይህም ስሜቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ዝንባሌውንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋውን ስሜት ያጠቃልላል። ስለዚህ በሙሉ ልባችን በአምላክ መታመን እንዲሁ የስሜት ጉዳይ ብቻ አይደለም። በሙሉ ልባችን በአምላክ የምንታመነው ፈጣሪያችን ለእኛ የተሻለውን ነገር እንደሚያውቅ እርግጠኞች ስለሆንን ነው።—ሮም 12:1
“በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ።” ኃጢአተኞች ስለሆንን በራሳችን የማመዛዘን ችሎታ መመካት አንችልም፤ ስለዚህ በአምላክ መታመን ይኖርብናል። ሙሉ በሙሉ በራሳችን ችሎታ ተማምነን ወይም በስሜት ተገፋፍተን አንድ ውሳኔ እናደርግ ይሆናል፤ እንዲህ ያለው ውሳኔ መጀመሪያ ላይ ጥሩ መስሎ ቢታየንም የኋላ ኋላ መጥፎ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። (ምሳሌ 14:12፤ ኤርምያስ 17:9) የአምላክ ጥበብ ከእኛ ጥበብ እጅግ የላቀ ነው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ሕይወታችንን የምንመራው ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር በሚስማማ መንገድ ከሆነ ስኬታማ እንሆናለን።—መዝሙር 1:1-3፤ ምሳሌ 2:6-9፤ 16:20
“በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ።” በእያንዳንዱ የሕይወታችን እንቅስቃሴ እንዲሁም በምናደርገው በእያንዳንዱ ትላልቅ ውሳኔ የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርገው መመሪያ ለማግኘት ወደ እሱ በመጸለይና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ በሥራ ላይ በማዋል ነው።—መዝሙር 25:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
“እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” አምላክ ሕይወታችንን ከእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንመራ በመርዳት ጎዳናችንን ቀና ያደርግልናል። (ምሳሌ 11:5) ይህም ሳያስፈልግ ችግር ውስጥ ከመግባት እንድንርቅና ይበልጥ ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ ይረዳናል።—መዝሙር 19:7, 8፤ ኢሳይያስ 48:17, 18
የምሳሌ 3:5, 6 አውድ
የምሳሌ መጽሐፍ በአምላክ ዓይን ደስተኛና ስኬታማ ሕይወት እንድመራ የሚያስችሉ መሠረታዊ መመሪያዎችን ይዟል። የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ምዕራፎች የተጻፉት አንድ አባት ለሚወደው ልጁ ምክር እንደሚሰጥ ሆነው ነው። ምዕራፍ 3 የፈጣሪያችንን ጥበብ ከፍ አድርገው የሚመለከቱና ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ምሳሌ 3:13-26
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18