“የደግነት ሕግ” ይምራችሁ
“በጣም የማረከኝ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩኝ ደግነት ነው።” ሊሳa ይህን ያለችው ወደ እውነት እንድትመጣ ያነሳሳት ምን እንደሆነ ስትናገር ነው። የአን ተሞክሮም ተመሳሳይ ነው። አን “ከትምህርቱ ይበልጥ የማረከኝ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩኝ ደግነት ነው” ብላለች። አሁን ሁለቱም እህቶች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማሰላሰል ያስደስታቸዋል፤ ሆኖም በዋነኝነት የማረካቸው የተደረገላቸው ደግነት ነው።
እኛስ ደግነት በማሳየት የሌሎችን ልብ መንካት የምንችለው እንዴት ነው? ሁለት መንገዶችን እንመልከት፦ በአንደበታችን እና በድርጊታችን። ከዚያም ደግነት ማሳየት ያለብን ለእነማን እንደሆነ እናያለን።
“የደግነት ሕግ” አንደበታችሁን ይምራው
በምሳሌ ምዕራፍ 31 ላይ የተጠቀሰችው ባለሙያ ሚስት በአንደበቷ “የደግነት ሕግ” እንዳለ ተገልጿል። (ምሳሌ 31:26) የምትናገርበት ቃና እና የንግግሯ ይዘት በዚህ “ሕግ” እንዲመራ ታደርጋለች። አባቶችም በዚህ “ሕግ” አንደበታቸውን መምራት ይኖርባቸዋል። አብዛኞቹ ወላጆች ሸካራ ንግግር በልጆቻቸው ላይ መጥፎ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ያውቃሉ። ወላጆች በቁጣ እና ፍቅር በማይንጸባረቅበት መንገድ የሚናገሩ ከሆነ ልጃቸው የሚሉትን የመስማት አጋጣሚው ዝቅተኛ ይሆናል። ወላጆች በደግነት የሚናገሩ ከሆነ ግን ልጆቹ ወላጆቻቸው የሚሉትን ማዳመጥና መታዘዝ ቀላል ይሆንላቸዋል።
ወላጅ ሆንክም አልሆንክ፣ አንደበትህ በደግነት ሕግ እንዲመራ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የምሳሌ 31:26 የመጀመሪያ ክፍል ፍንጭ ይሰጠናል፤ “አፏን በጥበብ ትከፍታለች” ይላል። ይህም ከአፋችን የሚወጡትን ቃላትና የምንናገርበትን ቃና በጥበብ መምረጥን ይጨምራል። ከመናገራችን በፊት ‘የምናገረው ነገር ቁጣን ያነሳሳል ወይስ ቁጣን ያበርዳል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። (ምሳሌ 15:1) በእርግጥም ከመናገራችን በፊት አስቀድመን ማሰባችን ጥበብ ይሆናል።
አንድ ሌላ ምሳሌ ደግሞ “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” ይላል። (ምሳሌ 12:18) የምንናገረው ነገርና የምንናገርበት ቃና በሌሎች ላይ ምን ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል ካሰብን ንግግራችንን በተሻለ መንገድ መቆጣጠር እንችላለን። በእርግጥም ‘በደግነት ሕግ’ መመራታችን የሚጎዱ ቃላትን ከመናገርና ሸካራ አነጋገር ከመጠቀም ይጠብቀናል። (ኤፌ. 4:31, 32) አሉታዊ ሐሳብንና ንግግርን በአዎንታዊና ደግነት በሚንጸባረቅበት አነጋገር መተካት እንችላለን። ይሖዋ በፍርሃት የተዋጠውን አገልጋዩን ኤልያስን ባጽናናበት ወቅት በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ይሖዋን ወክሎ የመጣው መልአክ የተናገረው ‘ዝግ ባለና ለስለስ ባለ ድምፅ’ ነው። (1 ነገ. 19:12) እርግጥ ደግ መሆን ሲባል ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ መናገር ማለት ብቻ አይደለም፤ ደግነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት መፈጸምም ይኖርብናል። እንዴት?
የደግነት ድርጊት የሌሎችን ልብ ይነካል
አነጋገራችንም ሆነ ድርጊታችን ደግነት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን በማድረግ ይሖዋን መምሰል እንችላለን። (ኤፌ. 4:32፤ 5:1, 2) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊሳ የይሖዋ ምሥክሮች ስላሳዩአት ደግነት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ቤተሰቦቼ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤታችንን ለቅቀን እንድንወጣ ተገድደን ነበር። በዚያ ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁለት ባልና ሚስቶች ከሥራ እረፍት ወስደው ዕቃችንን ለመሸከፍ አገዙን። በዚያ ወቅት ገና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንኳ አልጀመርኩም ነበር።” ወንድሞች ያሳዩአት ደግነት ሊሳ እውነትን በጥልቀት እንድትመረምር አነሳስቷታል።
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው አንም የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩአት ደግነት ልቧ ተነክቷል። እንዲህ ብላለች፦ “በዓለማችን ላይ የሚታየው ነገር ተጠራጣሪ እንድሆን አድርጎኝ ነበር። ሰዎችን ማመን ይከብደኝ ነበር።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተገናኘሁበት ወቅት ዓላማቸውን ተጠራጥሬ ነበር። ‘አሳቢነት የሚያሳዩኝ ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናኝ እህት ያሳየችኝ ልባዊ ደግነት እንዳምናት አነሳሳኝ።” ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? አን “በኋላም ጥናቴን በቁም ነገር መመልከት ጀመርኩ” ብላለች።
ሊሳ እና አን በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች ያደረጉላቸው ደግነት ልባቸውን በጥልቅ እንደነካውና እውነትን እንዲማሩ እንዳነሳሳቸው ልብ በል። ወንድሞች ያሳዩአቸው ደግነት ልባቸውን እንዲከፍቱ ረድቷቸዋል።
ለሌሎች አምላካዊ ደግነት አሳዩ
አንዳንዶች በባሕላቸው የተነሳ ደግነት የሚንጸባረቅበት ንግግር መናገር ወይም ፈገግ ማለት ይቀናቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች በባሕላቸው ወይም በተፈጥሯዊ ባሕርያቸው የተነሳ ደግነት ማሳየታቸው የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም ደግነት የምናሳየው በእነዚህ ነገሮች ተነሳስተን ብቻ ከሆነ አምላካዊ ደግነት አሳይተናል ማለት ላይሆን ይችላል።—ከሐዋርያት ሥራ 28:2 ጋር አወዳድር።
አምላካዊ ደግነት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22, 23) ስለዚህ እውነተኛ ደግነት ለማዳበር የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። እንዲህ በማድረግ ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። በተጨማሪም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለሌሎች ከልባችን እናስባለን። ስለዚህ ደግነት እንድናሳይ የሚያነሳሳን ለይሖዋ አምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር ነው። እንዲህ ያለው ደግነት ከልብ የመነጨ ግሩም ባሕርይ ነው፤ እንዲሁም አምላክን ያስደስተዋል።
ደግነት ማሳየት ያለብን ለእነማን ነው?
ደግነት ለሚያሳዩን ወይም ለምናውቃቸው ሰዎች ደግነት ማሳየት ቀላል ሊሆን ይችላል። (2 ሳሙ. 2:6) ለእነዚህ ሰዎች ደግነት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ በማመስገን ነው። (ቆላ. 3:15) ይሁንና አንድ ሰው ደግነት የማይገባው እንደሆነ ቢሰማንስ?
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ይሖዋ ጸጋ ወይም የማይገባ ደግነት በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል፤ በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉም ስለዚህ ባሕርይ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጠናል። ‘ተቀባዩ ይገባኛል ሊለው የማይችል ደግነት’ የሚል ትርጉም ያለው “ጸጋ” የሚለው ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። ታዲያ አምላክ ደግነት የሚያሳየን እንዴት ነው?
ይሖዋ ለሕይወት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን በማቅረብ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ለኖሩ ሰዎች በሙሉ ደግነት አሳይቷል። (ማቴ. 5:45) ይሖዋ እሱን ከማወቃችን በፊት እንኳ ደግነት አሳይቶናል። (ኤፌ. 2:4, 5, 8) ለምሳሌ ለሁሉም ሰዎች ሲል እጅግ የሚወደውን አንድያ ልጁን ሰጥቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ “በተትረፈረፈ ጸጋው መሠረት” ቤዛውን እንዳዘጋጀልን ጽፏል። (ኤፌ. 1:7) በተጨማሪም ኃጢአት የምንሠራና ይሖዋን የምናሳዝነው ቢሆንም እኛን መምራቱንና ማስተማሩን ቀጥሏል። ትምህርቱና ቃሉ ‘እንደሚያረሰርስ ዝናብ’ ነው። (ዘዳ. 32:2) ይሖዋ ላሳየን ደግነት ውለታውን መመለስ የምንችልበት ምንም መንገድ የለም። የወደፊት ሕይወታችንም ቢሆን በይሖዋ ደግነት ላይ የተመካ ነው።—ከ1 ጴጥሮስ 1:13 ጋር አወዳድር።
በእርግጥም የይሖዋ ደግነት ልብ የሚነካና የሚያበረታታ ግሩም ባሕርይ ነው። በመሆኑም ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ደግነት ከማሳየት ይልቅ በየዕለቱ ለሁሉም ሰው ደግነት በማሳየት ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (1 ተሰ. 5:15) ሁልጊዜ ደግነት የምናሳይ ከሆነ በብርድ ቀን እንደሚያሞቅ እሳት እንሆናለን። ለቤተሰቦቻችን፣ ለእምነት አጋሮቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ለሚማሩ ልጆች እና ለጎረቤቶቻችን የብርታት ምንጭ እንሆናለን።
በቤተሰብህ ወይም በጉባኤህ ውስጥ ደግነት የሚንጸባረቅበት ንግግር በመናገር ወይም የደግነት ድርጊት በመፈጸም ልታበረታታው የምትችለው ሰው ይኖር እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ቤት በማጽዳት፣ አትክልት በመንከባከብ ወይም ዕቃ በመሸመት ልትረዳው የምትችለው ሰው በጉባኤህ ውስጥ ሊኖር ይችላል። በተጨማሪም በስብከቱ ሥራ ስትካፈል እገዛ የሚያስፈልገው ሰው ካጋጠመህ ተግባራዊ የሆነ እርዳታ መስጠት ትችል ይሆን?
ይሖዋን በመምሰል ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን ምንጊዜም ‘በደግነት ሕግ’ እንዲመራ እናድርግ።
a ስሞቹ ተቀይረዋል።