‘ሰላም የሚሆንበት ጊዜ’ ቀርቧል!
“ለሁሉ ዘመን አለው፣ . . . ለጦርነት ጊዜ አለው፣ ለሰላምም ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1, 8
1. በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ጦርነትንና ሰላምን በተመለከተ እርስ በርሱ የማይጣጣም ምን ሁኔታ አለ?
አብዛኛው የሰው ዘር ሰላምን አጥብቆ የሚሻበት በቂ ምክንያት አለው። ሃያኛው መቶ ዘመን ከየትኛውም የታሪክ ዘመን ይበልጥ ሰላም የጠፋበት ወቅት ነው። የሚገርመው ደግሞ ሰላምን ለማስጠበቅ የዚህን ያህል ጥረት የተደረገበት ጊዜ የለም። በ1920 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተቋቋመ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ሰላም ለማስፈን ከተደረጉ ተከታታይ ጥረቶች ሁሉ እጅግ የላቀ” ብሎ የጠራውን የ1928ቱን የኬሎግ ብሪያንድ ውል “አብዛኞቹ የዓለም ብሔራት ከእንግዲህ ጦርነትን ብሔራዊ ፖሊሲ አድርገን አንንቀሳቀስም ሲሉ” ፈርመዋል። ከዚያም በ1945 ተግባሩን ማከናወን የተሳነው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተተካ።
2. የተባበሩት መንግሥታት የታለመለት ግብ ምን ነበር? ምን ያህልስ ተሳክቶለታል?
2 እንደ መንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት ግብም የዓለምን ሰላም ማረጋገጥ ነበር። ሆኖም ያገኘው ስኬት በጣም ውስን ነው። እርግጥ ነው፣ በዓለም ላይ ከሁለቱ ታላላቅ ጦርነቶች ጋር የሚመጣጠን ጦርነት በየትኛውም ቦታ እየተደረገ አይደለም። ያም ሆኖ ግን በደርዘን የሚቆጠሩ አነስተኛ ግጭቶች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የአእምሮ ሰላም፣ ንብረትና አብዛኛውን ጊዜም ሕይወታቸውን ጭምር በመንጠቅ ላይ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት 21ኛውን መቶ ዘመን ‘የሰላም ጊዜ’ ሊያደርገው ይችላል ብለን ተስፋ ልናደርግ ይዳዳናልን?
የእውነተኛ ሰላም መሠረት
3. እውነተኛ ሰላምና ጥላቻ ጎን ለጎን ሊሄዱ የማይችሉት ለምንድን ነው?
3 በሰዎችና በብሔራት መካከል ሰላም ማስፈን ከመቻቻል የበለጠ ነገር ይጠይቃል። አንድ ሰው ከሚጠላው ሰው ጋር በእርግጥ ሰላም ሊኖረው ይችላል? “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው” በሚለው በ1 ዮሐንስ 3:15 መሠረት ሰላም ሊኖረው አይችልም። የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ሥር የሰደዱ ጥላቻዎች በቀላሉ ወደ ዓመፅ ድርጊቶች ያመራሉ።
4. ሰላም ሊኖራቸው የሚችሉት እነማን ብቻ ናቸው? ለምንስ?
4 ይሖዋ “ሰላምን የሚሰጥ” አምላክ በመሆኑ ሰዎች ሰላም ሊኖራቸው የሚችለው ለአምላክና ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ የጠለቀ አክብሮት ሲኖራቸው ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ ሰላምን የሚሰጠው ለሁሉም ሰው አይደለም። “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።” ይህ የሆነበት ምክንያት ክፉዎች በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመመራት እምቢተኛ በመሆናቸው ሲሆን ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች መካከል ደግሞ አንዱ ሰላም ነው።—ሮሜ 15:33 የ1980 ትርጉም፤ ኢሳይያስ 57:21፤ ገላትያ 5:22
5. ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የማይታሰብ ነገር የሆነው ምንድን ነው?
5 በተለይ በ20ኛው መቶ ዘመን ያሉ ክርስቲያን ነን ባዮች አብዛኛውን ጊዜ እንዳደረጉት በመሰል ሰብዓዊ ፍጥረታት ላይ ጦርነት መክፈት በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ የማይታሰብ ነገር ነው። (ያዕቆብ 4:1-4) እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ የተሳሳተ ሐሳብ የሚያስተላልፉ ትምህርቶችን የሚዋጉ ቢሆንም ይህ ውጊያ ግለሰቦችን ለመጉዳት ሳይሆን ለመርዳት የታቀደ ነው። በሃይማኖት ልዩነቶች ምክንያት ሌሎችን ማሳደድ ወይም በብሔራዊ ስሜት ተነሳስቶ አካላዊ ጥቃት መፈጸም እውነተኛውን ክርስትና በእጅጉ የሚቃረን ነው። ጳውሎስ በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖችን “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል።—ሮሜ 12:17-19፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25
6. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ሰላም ሊገኝ የሚችለው የት ብቻ ነው?
6 በዛሬው ጊዜ አምላክ የሚሰጠው ሰላም የሚገኘው በይሖዋ አምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ዘንድ ብቻ ነው። (መዝሙር 119:165፤ ኢሳይያስ 48:18) በየትኛውም ቦታ ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኞች በመሆናቸው ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ልዩነት አንድነታቸውን አያናጋውም። (ዮሐንስ 15:19፤ 17:14) “በአንድ ልብና በአንድ አሳብም [የተባበሩ]” በመሆናቸው ሰላማቸውን የሚያሰጋ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ልዩነት የላቸውም። (1 ቆሮንቶስ 1:10) የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ሰላም በዘመናችን የታየ ተአምር ሲሆን አምላክ “አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ” በማለት ከሰጠው ተስፋ ጋር የሚስማማ ነው።—ኢሳይያስ 60:17፤ ዕብራውያን 8:10
‘ለጦርነት ጊዜ ያለው’ ለምንድን ነው?
7, 8. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማዊ አቋም ቢኖራቸውም ያለንበትን ጊዜ የሚመለከቱት እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያኖች በሚያካሂዱት ውጊያ የሚጠቀሙበት ዋነኛው መሣሪያ ምንድን ነው?
7 የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማዊ አቋም ያላቸው ቢሆንም በተለይ አሁን ያለንበትን ዘመን በዋነኛነት ‘የጦርነት ጊዜ’ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። በእርግጥ ይህ ቀጥተኛ ውጊያ ማካሄድ ማለት አይደለም፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በጦር ኃይል እያስገደዱ ሰዎች እንዲሰሙት ማድረግ አምላክ “የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” በማለት ካቀረበው ግብዣ ጋር የሚቃረን ይሆናል። (ራእይ 22:17 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ሰዎችን አስገድዶ እምነት ማስለወጥ የሚባል ነገር የለም! የይሖዋ ምሥክሮች የሚያካሂዱት ውጊያ መንፈሳዊ ብቻ ነው። ጳውሎስ “የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፣ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው” ሲል ጽፏል።—2 ቆሮንቶስ 10:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:18
8 ‘ከጦር ዕቃችን’ መካከል አንዱና ዋነኛው ‘የመንፈስ ሰይፍ የሆነው የአምላክ ቃል’ ነው። (ኤፌሶን 6:17) ይህ ሰይፍ ኃይለኛ ነው። “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) ክርስቲያኖች በዚህ ሰይፍ በመጠቀም “በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ” ለማፍረስ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 10:5) የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን፣ ጎጂ ልማዶችንና መለኮታዊ ሳይሆን ሰብዓዊ ጥበብን የሚያንጸባርቁ ፍልስፍናዎችን ለማጋለጥ ያስችላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 2:6-8፤ ኤፌሶን 6:11-13
9. በኃጢአተኛው ሥጋችን ላይ ከምናካሂደው ጦርነት ወደ ኋላ ልንል የማንችለው ለምንድን ነው?
9 ሌላኛው መንፈሳዊ ውጊያ ደግሞ በኃጢአተኛው ሥጋችን ላይ የምናካሂደው ነው። ክርስቲያኖች “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” በማለት የተናገረውን የጳውሎስን ምሳሌ ይከተላሉ። (1 ቆሮንቶስ 9:27) በቆላስይስ የሚገኙ ክርስቲያኖች ‘በምድር ያሉቱን ብልቶቻቸውን በመግደል ዝሙትን፣ ርኵሰትን፣ ፍትወትን፣ ክፉ ምኞትንና ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀትን’ እንዲያስወግዱ በጥብቅ ተመክረው ነበር። (ቆላስይስ 3:5) እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ይሁዳ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት [እንዲጋደሉ]” አሳስቧቸዋል። (ይሁዳ 3) እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? ጳውሎስ ሲመልስ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ” ብሏል። (ሮሜ 8:13) ከዚህ ግልጽ ሐሳብ በመነሳት ከመጥፎ ዝንባሌዎች ጋር ከምናካሂደው ውጊያ ሊገታን የሚችል ምንም ነገር አይኖርም።
10. በ1914 ምን ተከናውኗል? ይህስ በቅርቡ ወደ ምን ይመራል?
10 ይሁንና የአሁኑ ዘመን የጦርነት ጊዜ ተደርጎ ሊታይ የሚችልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ‘አምላክ የሚበቀልበት ቀን’ ቅርብ መሆኑ ነው። (ኢሳይያስ 61:1, 2) በ1914 ይሖዋ መሲሐዊውን መንግሥት ለማቋቋምና በሰይጣን ሥርዓት ላይ ጦርነት እንዲከፍት ሥልጣን ለመስጠት የወሰነው ጊዜ ደርሶ ነበር። ሰዎች ያለ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የሰው አገዛዝ ምን እንደሚመስል እንዲያዩት የተሰጣቸው ጊዜ በዚያ ወቅት አከተመ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ ዛሬም አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክ መሲሐዊ ገዥ ለመገዛት በእምቢተኝነታቸው ገፍተውበታል። (ሥራ 28:27) በመሆኑም በመንግሥቱ ላይ በሚደርሰው ተቃውሞ ምክንያት ክርስቶስ ‘በጠላቶቹ መካከል ለመግዛት’ ተገድዷል። (መዝሙር 110:2) ደስ የሚለው ነገር ራእይ 6:2 ‘ድል እንደሚነሣ’ ይናገራል። ይህን የሚያደርገው ‘በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባለው በታላቁ ሁሉን በሚገዛው በእግዚአብሔር የጦርነት ቀን’ ላይ ይሆናል።—ራእይ 16:14, 16
‘የመናገር ጊዜ’ አሁን ነው
11. ይሖዋ ይህን ያህል የታገሠው ለምንድን ነው? ሆኖም በመጨረሻ ምን ይመጣል?
11 የሰው ዘር ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ ከተሸጋገረበት ከ1914 ወዲህ 85 ዓመታት አልፈዋል። ይሖዋ የሰውን ዘር በእጅጉ ታግሷል። ምሥክሮቹ የሁኔታውን አጣዳፊነት ሙሉ በሙሉ እንዲገነዘቡ አድርጓል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት በቋፍ ላይ ይገኛል። ይሖዋ “ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ” ስለሚፈልግ እነዚህ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ሊሰሙ ይገባል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ያም ሆኖ ግን “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ . . . [የሚገለጥበት]” ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። ከዚያም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት ለመስማት እምቢተኛ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ኢየሱስ፣ ‘አምላክን በማያውቁትና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በማይታዘዙት ላይ’ ከሚያመጣው ‘የበቀል’ እርምጃ ይቀምሳሉ።—2 ተሰሎንቄ 1:6-9
12. (ሀ) ታላቁ መከራ የሚጀምርበትን ጊዜ ለመገመት መሞከር እርባና የሌለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ረገድ ኢየሱስ ስለ ምን ነገር አስጠንቅቋል?
12 ይሖዋ በመጨረሻ ትዕግሥቱ የሚሟጠጠው መቼ ይሆናል? “ታላቁ መከራ” የሚጀምርበትን ጊዜ ለመገመት መሞከር እርባና የለውም። ኢየሱስ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን . . . የሚያውቅ የለም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ በማለት አሳስቧል:- “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። . . . እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።” (ማቴዎስ 24:21, 36, 42, 44) በቀላል አነጋገር የዓለም ሁኔታዎችን በንቃት መከታተልና የታላቁን መከራ መጀመር ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን ማለት ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:1-5) ብዙም መጨነቅ አያስፈልግም በሚል ፈሊጥ መመላለስና ሁኔታዎች ወዴት እንደሚያመሩ ቀስ ብሎ ማየት ይሻላል በሚል ስሜት ነገሮችን አቅልሎ መመልከቱ አደገኛ ነው! ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።” (ሉቃስ 21:34, 35) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ “አራት መላእክት” የያዟቸው ‘አራቱ አውዳሚ ነፋሳት’ ለዘላለም እንደተያዙ እንደማይቀጥሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ራእይ 7:1-3
13. ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ምን ነገር ተገንዝበዋል?
13 በፍጥነት በመቅረብ ላይ ካለው ከዚህ የፍርድ ቀን አንፃር ሰሎሞን “ለመናገርም ጊዜ አለው” በማለት የተናገራቸው ቃላት ልዩ ትርጉም አላቸው። (መክብብ 3:7) ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉት የይሖዋ ምሥክሮች ለመናገር ጊዜው አሁን መሆኑን በመገንዘብ ቅንዓት በተሞላበት መንገድ ስለ አምላክ ክብራማ ንግሥና በመናገርና ስለ በቀል ቀኑ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው። በዚህ በክርስቶስ የኃይል ቀን ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ።—መዝሙር 110:3 NW፤ 145:10-12
‘ሰላም ሳይኖር ስለ ሰላም’ የሚናገሩ
14. በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተነሱት ሐሰተኛ ነቢያት የትኞቹ ነበሩ?
14 የአምላክ ነቢያት የሆኑት ኤርምያስና ሕዝቅኤል በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ኢየሩሳሌም አምላክን ለመታዘዝ እምቢተኛ በመሆን በተከተለችው ዓመፀኛ አካሄድ ምክንያት ስለሚወሰድባት የፍርድ እርምጃ የሚገልጹ መለኮታዊ መልእክቶችን ተናግረው ነበር። ታዋቂ የሆኑና ተሰሚነት የነበራቸው የሃይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ የተቃወሟቸው ቢሆንም እንኳ የአምላክ መልእክተኞች የተነበዩት ጥፋት በ607 ከዘአበ ተፈጽሟል። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ‘ሰላም ሳይኖር ሰላም ሰላም እያሉ የአምላክን ሕዝብ በማታለላቸው’ ‘ሰነፍ ነቢያት’ መሆናቸውን አስመስክረዋል።—ሕዝቅኤል 13:1-16፤ ኤርምያስ 6:14, 15፤ 8:8-12
15. በዛሬው ጊዜ ተመሳሳይ ሐሰተኛ ነቢያት አሉን? አብራራ።
15 በዚያን ወቅት እንደነበሩት እንደ ‘ሰነፎቹ ነቢያት’ በዛሬው ጊዜ የሚገኙት አብዛኞቹ የሃይማኖት መሪዎችም ስለ መጪው የአምላክ የፍርድ ቀን ሰዎችን ሳያስጠነቅቁ ቀርተዋል። ከዚያ ይልቅ ፖለቲካዊ ቡድኖች ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንደሚሳካላቸው አድርገው ይናገራሉ። ይበልጥ የሚያሳስባቸው አምላክን ሳይሆን ሰዎችን ማስደሰት ስለሆነ የአምላክ መንግሥት መቋቋሙንና መሲሐዊው ንጉሥ በቅርቡ ድል የሚቀዳጅ መሆኑን ከማሳወቅ ይልቅ ለአባላቶቻቸው ጆሮ የሚጥም ነገር ብቻ ይናገራሉ። (ዳንኤል 2:44፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4፤ ራእይ 6:2) ሐሰተኛ ነቢያት እንደመሆናቸው መጠን እነሱም ‘ሰላም ሳይኖር ሰላም ሰላም’ ይላሉ። ሆኖም ማንነቱን አዛብተው በማቅረብ በስሙ ላይ ይህ ነው የማይባል ነቀፌታ የከመሩበትን አካል ቁጣ ለመጋፈጥ ሲገደዱ የነበራቸው ጽኑ እምነት በድንገት ወደ ታላቅ ድንጋጤ ይለወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ በጋለሞታ ሴት የሚመስላት የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት መሪዎች አሳሳች የሰላም ጩኸታቸውን በማሰማት ላይ እያሉ ድንገት ጥፋት ይመጣባቸዋል።—ራእይ 18:7, 8
16. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች መሆናቸውን አስመስክረዋል? (ለ) ‘ሰላም ሳይኖር ሰላም ሰላም’ ከሚሉ ሰዎች የሚለዩት እንዴት ነው?
16 ታዋቂ የሆኑና ተሰሚነት ያላቸው አብዛኞቹ መሪዎች ግብዝነት ያለበት የሰላም ተስፋ መስጠታቸውን መቀጠላቸው አምላክ በሰጠው እውነተኛ የሰላም ተስፋ ላይ ትምክህት የጣሉ ሰዎችን እምነት አያናውጥም። ከአንድ ምዕተ ዓመት ለሚበልጡ ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ቃል በታማኝነት ጥብቅና የቆሙ፣ የሐሰት ሃይማኖትን በድፍረት የሚቃወሙና የአምላክን መንግሥት በልበ ሙሉነት የሚደግፉ መሆናቸውን አስመስክረዋል። ስለ ሰላም በሚነገር ሽንገላ ሰዎችን በመደለል እንዲያንቀላፉ ከማድረግ ይልቅ ጊዜው የጦርነት መሆኑን ተገንዝበው እንዲነቁ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።—ኢሳይያስ 56:10-12፤ ሮሜ 13:11, 12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:6
ይሖዋ ዝም የሚልበት ጊዜ ያበቃል
17. ይሖዋ ዝም የሚልበት ጊዜ በቅርቡ ያበቃል ሲባል ምን ማለት ነው?
17 በተጨማሪም ሰሎሞን “ለነገር ሁሉ . . . ጊዜ አለውና በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል” ብሏል። (መክብብ 3:17) አዎን፣ ይሖዋ በሐሰት ሃይማኖትና “በእግዚአብሔርና በመሢሑ” ላይ ‘በሚነሱት የምድር ነገሥታት’ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የቀጠረው ጊዜ አለ። (መዝሙር 2:1-6፤ ራእይ 16:13-16) ይህ ጊዜ ሲደርስ ይሖዋ “ዝም” የሚልበት ጊዜ ያበቃል። (መዝሙር 83:1፤ ኢሳይያስ 62:1፤ ኤርምያስ 47:6, 7) ዙፋን ላይ በተቀመጠው መሲሐዊ ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ተቃዋሚዎቹ ሊረዱት በሚችሉት ብቸኛ ቋንቋ “ይናገራል”:- “እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል። ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፣ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ፣ ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፣ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፣ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ። ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፣ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፣ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፣ አልተዋቸውምም።”—ኢሳይያስ 42:13-16 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
18. የአምላክ ሕዝቦች በቅርቡ ‘ዝም የሚሉት’ በምን መልኩ ነው?
18 ይሖዋ ለአምላክነቱ ጥብቅና በመቆም ‘ስለሚናገር’ ከዚያ በኋላ ሕዝቦቹ ስለ ራሳቸው ጥብቅና መቆም አያስፈልጋቸውም። እነሱ ደግሞ በተራቸው ‘ዝም ይላሉ።’ “በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም፤ . . . ተሰለፉ፣ ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ” የሚሉት ቃላት ለጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች እንደሠሩ ሁሉ አሁንም ይሠራሉ።—2 ዜና መዋዕል 20:17
19. የክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች በቅርቡ ምን መብት ያገኛሉ?
19 ለሰይጣንና ለድርጅቱ እንዴት ያለ ከባድ ሽንፈት ይሆንባቸዋል! ክብር የተጎናጸፉት የክርስቶስ ወንድሞች “የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል” በሚለው ተስፋ መሠረት ለጽድቅ በሚደረገው ውጊያ አንጸባራቂ ድል ይቀዳጃሉ። (ሮሜ 16:20) ከዚያ በኋላ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲጠበቅ የቆየው ሰላም ይጨበጣል።
20. በቅርቡ ምን የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል?
20 ከዚህ ከይሖዋ ታላቅ ኃይል መገለጥ በሕይወት የሚተርፉ የምድር ነዋሪዎች በሙሉ እንዴት የተባረኩ ናቸው! ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ለትንሣኤ የተቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ከሞት ከሚነሱት ጥንት የነበሩ የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ጋር ይቀላቀላሉ። በእርግጥም የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ‘የመትከል፣ የመፈወስ፣ የመሥራት፣ የመሳቅ፣ የመጨፈር፣ የመተቃቀፍና የመፈቃቀር ጊዜ ይሆናል።’ አዎን፣ ለዘላለም ‘የሰላም ጊዜ’ ይሆናል!—መክብብ 3:1-8፤ መዝሙር 29:11፤ 37:11፤ 72:7
መልስህ ምንድን ነው?
◻ ዘላቂ ለሆነ ሰላም መሠረቱ ምንድን ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች የዛሬውን ጊዜ ‘የጦርነት ጊዜ’ አድርገው የሚመለከቱት ለምንድን ነው?
◻ የአምላክ ሕዝቦች ‘የሚናገሩትና’ ‘ዝም የሚሉት’ መቼ ነው?
◻ ይሖዋ ዝም የሚልበት ጊዜ የሚያበቃው እንዴትና መቼ ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ይሖዋ እነዚህን የሚያደርግበት ጊዜ ቀጥሯል
◻ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ጎግን የሚያመጣበትን።—ሕዝቅኤል 38:3, 4, 10-12፤
◻ ሰብዓዊ መንግሥታት ታላቂቱ ባቢሎንን የማጥፋት ሐሳብ በልባቸው የሚያኖርበትን።—ራእይ 17:15-17፤ 19:2፤
◻ የበጉ ሰርግ የሚከናወንበትን።—ራእይ 19:6, 7፤
◻ የአርማጌዶን ጦርነት የሚጀመርበትን።—ራእይ 19:11-16, 19-21፤
◻ ሰይጣንን በማሰር የኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት እንዲጀምር የሚያደርግበትን።—ራእይ 20:1-3
እነዚህ ክንውኖች የተዘረዘሩት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በሚገኙበት ቅደም ተከተል ነው። አምስቱም ክንውኖች ይሖዋ በወሰነው ቅደም ተከተልና በቀጠረው ትክክለኛ ጊዜ ላይ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በእርግጥም የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት . . .
የመሳቅ፣
የመተቃቀፍ፣
የመፈቃቀር፣
የመትከል፣
የመጨፈር፣
የመሥራት ጊዜ ይሆናል