የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
“በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ፣ ውዴም በቈነጃጅት መካከል እንዲሁ ናት።” “በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ እንኰይ፣ ውዴም በጐልማሶች መካከል እንዲሁ ነው።” “እንደ ንጋት ብርሃን ብቅ የምትል፣ እንደ ጨረቃ የደመቀች፣ እንደ ፀሓይ ያበራች፣ . . . ይህች ማን ናት?” (ማሕልየ መሓልይ 2:2, 3፤ 6:10) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆነው ከማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ የተወሰዱት እነዚህ ጥቅሶች ምንኛ ማራኪ ናቸው! መጽሐፉ በአጠቃላይ ጥልቅ ትርጉም ያላቸውና ማራኪ የሆኑ ግጥሞችን የያዘ በመሆኑ “ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር” ተብሎ ተጠርቷል።—ማሕልየ መሓልይ 1:1
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን በ40ኛው የግዛት ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ማለትም በ1020 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ያቀናበረው ይህ መዝሙር፣ የአንድን እረኛና የሱላማጢሷን የገጠር ልጃገረድ የፍቅር ታሪክ የሚገልጽ ነው። በዚህ ግጥም ውስጥ የልጃገረዷ እናትና ወንድሞች፣ “የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት [የቤተ መንግሥቱ ወይዛዝርት]” እንዲሁም “የጽዮን ቈነጃጅት [የኢየሩሳሌም ሴቶች]” ተጠቅሰው እናገኛለን። (ማሕልየ መሓልይ 1:5፤ 3:11) ለአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ በማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ተናጋሪዎች መለየት አስቸጋሪ ቢሆንም የተናገሩትን ወይም ስለ እነርሱ የተነገረውን በመመልከት ማንነታቸውን ማወቅ ይቻላል።
የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ የአምላክ ቃል ክፍል እንደመሆኑ መጠን በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። (ዕብራውያን 4:12) በአንደኛ ደረጃ፣ በአንድ ወንድና ሴት መካከል ስለሚኖረው እውነተኛ ፍቅር ያስተምረናል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መዝሙሩ፣ በክርስቶስና በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ መካከል ላለው ፍቅር እንደ ምሳሌ ይሆናል።—2 ቆሮንቶስ 11:2፤ ኤፌሶን 5:25-31
‘ፍቅርን እንዳትቀሰቅሱት’
“በከንፈሩ መሳም ይሳመኝ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛልና።” (ማሕልየ መሓልይ 1:2) የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ የሚጀምረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ድንኳን የተወሰደች አንዲት የገጠር ልጃገረድ በተናገረቻቸው በእነዚህ ቃላት ነው። ይህቺ ልጃገረድ ወደ ሰሎሞን ድንኳን የመጣችው እንዴት ነው?
እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ተቈጡኝ፤ የወይን ተክል ቦታዎችም ጠባቂ አደረጉኝ።” ወንድሞቿ የተቆጧት፣ የምትወደው እረኛ በአንድ ደስ የሚል የጸደይ ቀን አብረው እንዲንሸራሸሩ ስለጠየቃት ነው። በመሆኑም ከእሱ ጋር እንዳትሄድ ብለው ‘የወይን ተክል ቦታቸውን የሚያጠፉትን ትንንሽ ቀበሮዎች’ እንድትጠብቅ አደረጓት። ይህን ሥራ ለማከናወን ሰሎሞን ወደሰፈረበት አካባቢ መሄድ ነበረባት። “ወደ ለውዙ ተክል ቦታ” በምትወርድበት ጊዜ ቁንጅናዋን ያዩ ሰዎች ወደ ንጉሡ ወሰዷት።—ማሕልየ መሓልይ 1:6፤ 2:10-15፤ 6:11
ልጃገረዷ የምትወደውን እረኛ ለማየት እንደምትናፍቅ ስትናገር የቤተ መንግሥቱ ወይዛዝርት ‘የበጎቹን ዱካ ተከትላ’ እንድትፈልገው ነገሯት። ይሁን እንጂ ሰሎሞን እንድትሄድ አልፈቀደላትም። ቁንጅናዋን በማድነቅ “ባለ ብር ፈርጥ፣ የወርቅ ጕትቻ” እንደሚሰጣት ቃል ገባላት። ሆኖም ልጃገረዷ በዚህ አልተማረከችም። እረኛው፣ ንጉሡ ወደሰፈረበት ቦታ ሄዶ ካገኛት በኋላ “ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነሽ እንዴትስ ያለሽ ቈንጆ ነሽ” ይላታል። ወጣቷ ልጃገረድ ደግሞ የቤተ መንግሥቱን ወይዛዝርት “ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት” በማለት ታስምላቸዋለች።—ማሕልየ መሓልይ 1:8-11, 15፤ 2:7፤ 3:5
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:2, 3 የ1954 ትርጉም—የእረኛው ፍቅር ትውስታ እንደ ወይን ጠጅ፣ ስሙም እንደሚፈስ ዘይት ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው? የወይን ጠጅ የሰውን ልብ ደስ እንደሚያሰኝና ዘይትም ራስ ላይ ሲፈስ እንደሚያረካ ሁሉ ልጃገረዷም የእረኛውን ስምና ፍቅሩን ስታስታውስ ትበረታታለች እንዲሁም ትጽናናለች። (መዝሙር 23:5፤ 104:15) በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች በተለይ ደግሞ ቅቡዓኑ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳያቸውን ፍቅር በማሰብ ማበረታቻና ማጽናኛ ያገኛሉ።
1:5—የገጠሯ ልጃገረድ ጥቁረቷን ‘ከቄዳር ድንኳኖች’ ጋር ያመሳሰለችው ለምንድን ነው? ከፍየል ጠጉር የተሠራ ጨርቅ ለተለያየ አገልግሎት ይውል ነበር። (ዘኍልቍ 31:20) ለምሳሌ ያህል፣ “የፍየል ጠጕር መጋረጃዎች” ‘የማደሪያ ድንኳኑን’ ለመሸፈን ያገለግሉ ነበር። (ዘፀአት 26:7) ዛሬ ያሉት ቤድዊን የተባሉ ዘላን የአረብ ጎሳዎች እንደሚጠቀሙባቸው ድንኳኖች ሁሉ የቄዳር ድንኳኖችም ከጥቁር የፍየል ጠጉር የተሠሩ ሳይሆኑ አይቀሩም።
1:15—እረኛው “ዐይኖችሽም እንደ ርግብ ዐይኖች ናቸው” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? እረኛው የሚወዳት ልጅ ዓይኖች ልክ እንደ ርግብ ዓይኖች የዋህነትና ደግነት የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ መግለጹ ነው።
2:7፤ 3:5—ልጃገረዲቱ የቤተ መንግሥቱን ወይዛዝርት “በሚዳቋና በሜዳ ዋልያ” ያስማለቻቸው ለምንድን ነው? ሚዳቋና ዋልያ ግርማ ሞገስ የተላበሱና በውበታቸው የሚታወቁ ናቸው። በመሆኑም ሱላማጢሷ ልጃገረድ፣ የቤተ መንግሥቱ ወይዛዝርት ፍቅርን እንዳይቀሰቅሱባት ውብና ማራኪ በሆነው ነገር ሁሉ ማስማሏ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:2፤ 2:6:- አንድ ወንድና ሴት በሚጠናኑበት ጊዜ በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ የሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ የፍቅር መግለጫዎች ከእውነተኛ ፍቅር የሚመነጩ እንጂ ወደ ጾታ ብልግና ሊመራ የሚችል ርካሽ የሆነ ስሜት መግለጫ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለባቸው።—ገላትያ 5:19
1:6፤ 2:10-15:- የሱላማጢሷ ልጃገረድ ወንድሞች፣ እህታቸውን ከምትወደው ሰው ጋር ብቻቸውን ሆነው በተራሮቹ ላይ ወደሚገኙት ከሰዎች እይታ ራቅ ያሉ ቦታዎች እንዳይሄዱ ከልክለዋታል፤ ይህን ያደረጉት ግን ሥነ ምግባር የጎደላት ስለሆነች ወይም መጥፎ ዓላማ ስለነበራት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ወደ ፈተና ሊያመራት የሚችል ነገር እንዳያጋጥማት ጥንቃቄ ማድረጋቸው ነው። በመሆኑም በመጠናናት ላይ ያሉ ወንድና ሴት ገለል ባሉ አካባቢዎች ብቻቸውን ከመሆን መቆጠብ ይኖርባቸዋል።
2:1-3, 8, 9:- ሱላማጢሷ ልጃገረድ ቆንጆ ብትሆንም “የሳሮን ጽጌረዳ” ማለትም ተራ ‘የሸለቆ አበባ’ እንደሆነች አድርጋ ራሷን በትሕትና ገልጻለች። በውበቷና ለይሖዋ ባላት ታማኝነት የተነሳ እረኛው “በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ” አድርጎ ተመልክቷታል። ስለ እርሱስ ምን ለማለት ይቻላል? መልከ መልካም በመሆኑ ለእርሷ እንደ “ሚዳቋ” ነበር። እርሱም ቢሆን አምላክን የሚፈራና ለይሖዋ ያደረ ሰው መሆን አለበት። ስለ እርሱ ስትናገር “በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ [ጥላና ፍሬ የሚሰጥ] እንኰይ፣ ውዴም በጐልማሶች መካከል እንዲሁ ነው” ብላለች። ይህ እኛም ለጋብቻ የምንመርጠው ሰው እምነት ያለውና ለአምላክ ያደረ መሆን እንዳለበት አያሳይም?
2:7፤ 3:5:- የገጠሯ ልጅ ለሰሎሞን ምንም ፍቅር አልነበራትም። ከዚህም በላይ የቤተ መንግሥቱን ወይዛዝርት ከእረኛው በቀር ማንንም እንድታፈቅር ለማድረግ እንዳይሞክሩ አስምላቸዋለች። ማንኛውንም ሰው ማፍቀር የማይቻል ከመሆኑም በላይ እንዲህ ማድረግ ተገቢም አይደለም። አንድ ያላገባ ክርስቲያን ለማግባት የሚያስበው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የሆነን ሰው ብቻ መሆን ይኖርበታል።—1 ቆሮንቶስ 7:39
“ሱላማጢስን የምትመለከቷት ለምንድን ነው?”
“እንደ ጢስ ዐምድ ከምድረ በዳ” የሚመጣ ነገር ይታያል። (ማሕልየ መሓልይ 3:6) የኢየሩሳሌም ሴቶች ሁኔታውን ለማየት ሲወጡ ምን ተመለከቱ? ሰሎሞንና አገልጋዮቹ ወደ ከተማ እየተመለሱ ነው! ንጉሡ ሱላማጢሷን ልጃገረድም ይዟት መጥቷል።
እረኛው ልጃገረዷን ሲከተላት ከቆየ በኋላ አገኛት። ከዚያም እንደሚወዳት ሲነግራት ከተማውን ለቅቃ መሄድ እንደምትፈልግ እንዲህ በማለት ገለጸችለት:- “ጎሕ ከመቅደዱ በፊት፣ ጥላውም ሳይሸሽ፣ ወደ ከርቤ ተራራ፣ ወደ ዕጣኑም ኰረብታ እወጣለሁ።” በኋላም እረኛውን ‘ወደ አትክልት ቦታው እንዲገባና ምርጥ ፍሬዎቹንም እንዲበላ’ ጋበዘችው። እርሱም “እኅቴ ሙሽራዬ፣ ወደ አትክልት ቦታዬ መጥቻለሁ” አላት። የኢየሩሳሌም ሴቶችም “ወዳጆች ሆይ፤ ብሉ፤ ጠጡ፤ እናንት ፍቅረኞች ሆይ፤ እስክትረኩ ጠጡ” አሏቸው።—ማሕልየ መሓልይ 4:6, 16፤ 5:1
ሱላማጢሷ ልጃገረድ ለቤተ መንግሥቱ ወይዛዝርት ሕልሟን ከነገረቻቸው በኋላ ‘በፍቅሩ እንደታመመች’ ገለጸችላቸው። እነርሱም “ውድሽ ከሌሎች እንዴት ቢበልጥ ነው?” አሏት። ልጃገረዷም “ውዴ ፍልቅልቅና ደመ ግቡ ነው፤ ከዐሥር ሺሆችም የሚልቅ ነው” አለቻቸው። (ማሕልየ መሓልይ 5:2-10) ሰሎሞን በፍቅር ቢያሞግሳትም እርሷ ግን “ሱላማጢስን የምትመለከቷት ለምንድን ነው?” በማለት በትሕትና መልሳለች። (ማሕልየ መሓልይ 6:4-13) ንጉሡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እንድትወደው ለማድረግ ሲል ይበልጥ ያሞጋግሳታል። ሆኖም ልጅቷ ለእረኛው ጽኑ ፍቅር ነበራት። በመጨረሻም ሰሎሞን ወደ ቤቷ እንድትሄድ ፈቀደላት።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
4:1፤ 6:5—የልጃገረዲቱ ጸጉር ‘ከፍየል መንጋ’ ጋር የተነጻጸረው ለምንድን ነው? ይህ ንጽጽር፣ ጸጉሯ እንደ ጥቁር የፍየል ጸጉር ሐር የመሰለና ብዛት ያለው መሆኑን የሚያመለክት ነው።
4:11—የሱላማጢሷ ‘ከንፈሮች የማር ወለላ ማንጠባጠባቸው’ እንዲሁም ‘ከአንደበቷ ወተትና ማር መፍለቁ’ ምን ያሳያል? የሱላማጢሷ ከንፈሮች የማር ወለላ ማንጠባጠባቸውም ሆነ ከልጃገረዷ አንደበት ወተትና ማር እንደሚፈልቅ መገለጹ ሱላማጢሷ የምትናገራቸው ቃላት ግሩምና ደስ የሚሉ መሆናቸውን የሚያጎላ ነው።
5:12—“ዐይኖቹ፣ በጅረት አጠገብ እንዳሉ ርግቦች፣ በወተት የታጠቡ . . . ናቸው” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? ልጃገረዷ እየተናገረች ያለችው ስለምትወደው ልጅ ውብ ዓይኖች ነው። ምናልባት የዓይኑ ብሌን ዙሪያውን በነጩ ክፍል ተከቦ ሲታይ በወተት የሚታጠቡ ግራጫ ቀለም ያላቸው ርግቦችን እንደሚመስል በቅኔ መልክ መናገሯ ሊሆን ይችላል።
5:14, 15—የእረኛው እጆችና እግሮች በዚህ መንገድ የተገለጹት ለምንድን ነው? ልጃገረዷ የእረኛውን ጣቶች እንደ ወርቅ ዘንግ፣ ጥፍሮቹን ደግሞ እንደ ዕንቁ ፈርጥ አድርጋ መግለጿ ሊሆን ይችላል። እግሮቹ ጠንካራና ውብ በመሆናቸው “የዕብነ በረድ ምሰሶዎችን” እንደሚመስሉ አድርጋ ገልጻቸዋለች።
6:4—ልጃገረዷ ከቴርሳ ጋር የተወዳደረችው ለምንድን ነው? ይህች የከነዓናውያን ከተማ በኢያሱ ድል የተደረገች ሲሆን ከሰሎሞን ዘመን በኋላ በስተ ሰሜን ያሉት አሥሩ የእስራኤል ነገዶች ዋና ከተማ ነበረች። (ኢያሱ 12:7, 24፤ 1 ነገሥት 16:5, 6, 8, 15) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ይህች ከተማ እጅግ ውብ ሳትሆን አትቀርም፤ እዚህ ላይ የተገለጸችውም ለዚህ መሆን አለበት።”
6:13—‘የመሃናይም ዘፈን’ ምንድን ነው? በዚህ ስም የምትጠራው ከተማ በዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ በያቦቅ መልካ አጠገብ ትገኝ ነበር። (ዘፍጥረት 32:2, 22፤ 2 ሳሙኤል 2:29) በመሆኑም ‘የመሃናይም ዘፈን’ የተባለው በበዓል ጊዜ በዚያች ከተማ የሚዘፈነውን ዘፈን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
7:4—ሰሎሞን፣ የሱላማጢሷን ልጃገረድ አንገት “በዝሆን ጥርስ እንዳጌጠ መጠበቂያ ማማ” አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው? ቀደም ሲል ልጃገረዷ “ዐንገትሽ . . . የዳዊትን የመጠበቂያ ማማ ይመስላል” ተብላ ነበር። (ማሕልየ መሓልይ 4:4) ብዙውን ጊዜ ማማ ረዥምና ቀጠን ያለ ሲሆን የዝሆን ጥርስ ደግሞ ለስላሳ ነው። ሰሎሞን የልጅቷ አንገት ረዥምና የተስተካከለ በመሆኑ ተደንቆ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
4:7:- ሱላማጢሷ ልጃገረድ ፍጹም ባትሆንም እንኳ የሰሎሞንን ማባበያዎች በመቋቋም የሥነ ምግባር ንጽሕናዋን ጠብቃለች። በሥነ ምግባር ረገድ ጠንካራ መሆኗ ውበት ጨምሮላታል። ክርስቲያን ሴቶችም እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ሊኖራቸው ይገባል።
4:12:- በአትክልት ወይም በግንብ እንደታጠረና በተቆለፈው በር በኩል ካልሆነ በቀር መግባት እንደማይቻልበት ውብ የአትክልት ሥፍራ፣ ሱላማጢሷ ልጃገረድም ፍቅሯን የምታሳየው ለወደፊት ባሏ ብቻ ነው። ይህ ላላገቡ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
“እንደ ያህ ነበልባል”
የሱላማጢሷ ልጃገረድ ወንድሞች ወደ ቤቷ ስትመለስ ሲመለከቱ “ውዷን ተደግፋ፣ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት?” ብለው ጠየቁ። ከጥቂት ጊዜያት በፊት ከወንድሞቿ መካከል አንዱ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እርሷ ቅጥር ብትሆን፣ በላይዋ የብር መጠበቂያ ማማ እንሠራባታለን፤ በር ብትሆን፣ በዝግባ ዕንጨት እንከልላታለን።” በዚህ ጊዜ ሱላማጢሷ ታማኝ አፍቃሪ መሆኗ ተፈትኖ ስለተረጋገጠ እንዲህ ትላለች:- “እነሆ እኔ ቅጥር ነኝ፤ ጡቶቼም እንደ ማማ ግንቦች ናቸው፤ እኔም በዐይኖቹ ፊት፣ ሰላምን እንደሚያመጣ ሰው ሆንሁ።”—ማሕልየ መሓልይ 8:5, 9, 10
እውነተኛ ፍቅር “እንደ ያህ ነበልባል” ነው። ለምን? ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ፍቅር የሚመነጨው ከይሖዋ ከመሆኑም ሌላ የማፍቀርን ችሎታ የሰጠን እርሱ ነው። ፍቅር ነበልባሉ እንደማይጠፋ እሳት ነው። የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ በወንድና በሴት መካከል ያለው ፍቅር ‘እንደ ሞት የበረታ [የማይለወጥ]’ መሆን እንደሚችል ግሩም በሆነ ሁኔታ ያሳያል።—ማሕልየ መሓልይ 8:6 NW
ወደር የሌለው የሰሎሞን መዝሙር፣ በኢየሱስ ክርስቶስና በሰማይ ባሉት ‘የሙሽራዋ’ ክፍል አባላት መካከል ያለውን ትስስር እንድንገነዘብም ይረዳናል። (ራእይ 21:2, 9) ኢየሱስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ያለው ፍቅር በወንድና በሴት መካከል ካለው ከማንኛውም ፍቅር ይበልጣል። የሙሽራዋ ክፍል አባላት ለአምላክ ያላቸው ታማኝነት ፈጽሞ የማይናወጥ ነው። ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስቶ ‘ለሌሎች በጎችም’ ጭምር ሕይወቱን ሰጥቷል። (ዮሐንስ 10:16) ስለዚህ ሁሉም እውነተኛ አምላኪዎች የሱላማጢሷን ጽኑ ፍቅርና ታማኝነት ሊኮርጁ ይችላሉ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የማሕልየ መሓልይ መጽሐፍ ልናገባው ከምናስበው ሰው ምን ዓይነት ባሕርያትን መጠበቅ እንዳለብን ያስተምረናል?