ምዕራፍ ሁለት
አንተንም የሚመለከቱ አጽናኝ ትንቢታዊ ቃላት
1. የኢሳይያስን ትንቢት ማጥናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ኢሳይያስ በስሙ የተጠራውን መጽሐፍ ከጻፈ ወደ 3, 000 የሚጠጉ ዓመታት ቢያልፉም መጽሐፉ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ሰዎችም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። እርሱ ከመዘገባቸው ታሪካዊ ክንውኖች እጅግ ጠቃሚ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንማራለን። እንዲሁም በይሖዋ ስም የጻፋቸውን ትንቢቶች በማጥናት እምነታችንን መገንባት እንችላለን። አዎን፣ ኢሳይያስ የሕያው አምላክ ነቢይ ነበር። ይሖዋ ወደፊት የሚፈጸመውን ታሪክ አስቀድሞ እንዲመዘግብ ወይም በሌላ አባባል ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት አስቀድሞ እንዲናገር በመንፈሱ አነሳስቶታል። በዚህ መንገድ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ መተንበይም ሆነ ወደፊት የሚከናወኑት ነገሮች እሱ ባሰበው መንገድ እንዲፈጸሙ ማድረግ እንደሚችል አሳይቷል። እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢሳይያስን መጽሐፍ በማጥናታቸው ይሖዋ የገባውን ቃል ሁሉ እንደሚፈጽም ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን ችለዋል።
2. ኢሳይያስ ትንቢታዊ መጽሐፉን በጻፈበት ጊዜ በኢየሩሳሌም የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? ምንስ ለውጥ ይመጣል?
2 ኢሳይያስ ትንቢቱን ጽፎ ባጠናቀቀበት ጊዜ ኢየሩሳሌም በአሦር ምክንያት በላይዋ ያንዣበበው የስጋት ደመና ተገፍፎ ነበር። ቤተ መቅደሱ አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ሲሆን ሕዝቡም ለብዙ መቶ ዓመታት ሲያደርግ እንደቆየው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውንና ተግባሩን እያከናወነ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ እንዳለ አይቀጥልም። የአይሁዳውያን ነገሥታት ሀብት ወደ ባቢሎን የሚጋዝበትና ወጣት አይሁዳውያንም በዚያች ከተማ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ሹማምንት የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል።a (ኢሳይያስ 39:6-7) ይህ የሚሆነው ከ100 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር።—2 ነገሥት 24:12-17፤ ዳንኤል 1:19
3. ኢሳይያስ ምዕራፍ 41 የያዘው መልእክት ምንድን ነው?
3 ይሁን እንጂ አምላክ በኢሳይያስ በኩል ያስነገረው የጥፋት መልእክት ብቻ ነበር ማለት አይደለም። የመጽሐፉ 40ኛ ምዕራፍ የሚጀምረው “አጽናኑ” በሚለው ቃል ነው።b አይሁዳውያኑ እነርሱ ወይም ደግሞ ልጆቻቸው ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ይሖዋ በሰጠው ዋስትና ይጽናናሉ። ኢሳ. ምዕራፍ 41 ይህንኑ የሚያጽናና መልእክት የሚናገር ሲሆን ይሖዋ መለኮታዊውን ፈቃድ ለማስፈጸም ሲል አንድ ኃያል ንጉሥ እንደሚያስነሣ ይተነብያል። አስተማማኝ ዋስትና የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ላይ መታመንን የሚያበረታታ ነው። በተጨማሪም ብሔራት የሚታመኑባቸው የሐሰት አማልክት ምንም ኃይል የሌላቸው መሆኑን ያጋልጣል። ይህ ሁሉ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩትንም ይሁን በዘመናችን ያሉትን ሰዎች እምነት የሚያጠናክር ነው።
ይሖዋ ለብሔራት ያቀረበው ፈተና
4. ይሖዋ ለብሔራት ያቀረበው ፈተና ምንድን ነው?
4 ይሖዋ በነቢዩ አማካኝነት እንዲህ ይላል:- “ደሴቶች ሆይ፣ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ በአንድነት እንቅረብ።” (ኢሳይያስ 41:1) ይሖዋ ከላይ እንደተገለጸው በማለት ሕዝቡን የሚቃወሙት ብሔራት ወገባቸውን ታጥቀው በፊቱ ቆመው እንዲከራከሩት ይጠይቃቸዋል! በኋላ እንደምናየው ይሖዋ በፍርድ ችሎት ላይ እንደተቀመጠ ዳኛ ሆኖ እነዚህ ብሔራት ጣዖቶቻቸው እውነተኛ አማልክት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ይጠይቃቸዋል። እነዚህ አማልክት አገልጋዮቻቸው ስለሚያገኙት መዳን ወይም በጠላቶቻቸው ላይ ስለሚወሰድ የፍርድ እርምጃ መተንበይ ይችላሉን? ከሆነስ እነዚህን ትንቢቶች ማስፈጸም ይችላሉ? እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።
5. የኢሳይያስ ትንቢት ከአንድ ጊዜ በላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው የሚችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
5 የኢሳይያስን ትንቢት በምንመረምርበት ጊዜ እንደ ሌሎቹ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሁሉ የእርሱም ቃላት ከአንድ ጊዜ በላይ ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው እናስታውስ። በ607 ከዘአበ ይሁዳ በምርኮ ወደ ባቢሎን ትጋዛለች። ይሁን እንጂ ይሖዋ በምርኮ የተያዙትን እስራኤላውያን ነፃ እንደሚያወጣቸው የኢሳይያስ ትንቢት ይገልጻል። ይህ የሚፈጸመው በ537 ከዘአበ ነው። የእነርሱ ነፃ መውጣት በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከተፈጸመ አንድ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት አለው። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በምድር የነበሩት የይሖዋ ቅቡዓን አገልጋዮች የመከራ ጊዜ አሳልፈዋል። በተደራጀ መልክ ይከናወን የነበረው የምሥራቹ ስብከት እንቅስቃሴ በ1918 የታላቂቱ ባቢሎን ዋና ተዋናይ የሆነችው ሕዝበ ክርስትና በቆሰቆሰችው የሰይጣን ዓለም ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ የተዳፈነ ያህል ሆኖ ነበር። (ራእይ 11:5-10) በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎች በሐሰት ክስ ወኅኒ ወረዱ። ዓለም ከአምላክ አገልጋዮች ጋር በሚያደርገው ትግል ድል የቀናው ይመስል ነበር። በኋላ ግን በ537 ከዘአበ እንደሆነው ሁሉ በዚህ ጊዜም ይሖዋ ሳይታሰብ ነፃ አወጣቸው። ታስረው የነበሩት በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሠሩ ወንድሞች በ1919 ተፈቱ። ተመስርቶባቸው የነበረውም ክስ ተነሣላቸው። መስከረም 1919 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ ተደርጎ የነበረው የአውራጃ ስብሰባ የይሖዋ አገልጋዮች የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩን ሥራ እንደገና እንዲቀጥሉ ከፍተኛ ኃይል ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 11:11, 12) ከዚያ ጊዜ አንስቶ የስብከቱ ሥራ በአስገራሚ ሁኔታ አድማሱን አስፍቷል። ከዚህም በላይ ብዙዎቹ የኢሳይያስ ቃላት ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ድንቅ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ከዚህ የተነሣ ኢሳይያስ ከረጅም ጊዜ በፊት የተናገራቸው ቃላት ዛሬ ያሉትን ሁሉንም ብሔራትና ሕዝቦች የሚመለከቱ ናቸው።
ነፃ አውጪ ተጠራ
6. ኢሳይያስ አስቀድሞ የተነገረለትን ድል አድራጊ የገለጸው እንዴት ነው?
6 ይሖዋ ሕዝቡን ከባቢሎን የሚታደግና በጠላቶቻቸው ላይ የሚፈርድ ድል አድራጊ እንደሚያስነሣ በኢሳይያስ አማካኝነት ተንብዮአል። ይሖዋ እንዲህ ሲል ይጠይቃል:- “ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ በጽድቅም ወደ እግሩ የጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፣ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው። አሳደዳቸው፣ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት መንገድ በደኅንነት አለፈ። ይህን የሠራና ያደረገ፣ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፣ ፊተኛው በኋለኞችም ዘንድ የምኖር፣ እኔ ነኝ።”—ኢሳይያስ 41:2-4
7. ትንቢት የተነገረለት ድል አድራጊ ማን ነው? ምንስ ያከናውናል?
7 ከምሥራቅ የሚነሣው ማን ነው? ሜዶ ፋርስና ኤላም የሚገኙት ከባቢሎን በስተ ምሥራቅ ነበር። ፋርሳዊው ቂሮስ ኃያል ሠራዊቱን ይዞ ከምሥራቅ ይዘምታል። (ኢሳይያስ 41:25፤ 44:28፤ 45:1-4, 13፤ 46:11) ቂሮስ ይሖዋን የሚያመልክ ሰው ባይሆንም ጻድቅ ከሆነው አምላክ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ሥራ ፈጽሟል። ቂሮስ ነገሥታትን ያንበረከከ ሲሆን በፊቱም እንደ ትቢያ ተበታትነዋል። በድል ላይ ድል ለመቀዳጀት እንቅፋቶችን ሁሉ እየተወጣ ወትሮ በማይታለፍባቸው መንገዶች “በደኅንነት” ወይም በሰላም አልፏል። በ539 ከዘአበ ኃያሏን የባቢሎን ከተማ ገልብጧታል። ከዚህ የተነሣ የአምላክ ሕዝቦች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ንጹሑን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም የሚያስችል ነፃነት አገኙ።—ዕዝራ 1:1-7c
8. ይሖዋ ብቻ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ምንድን ነው?
8 በዚህ መንገድ ይሖዋ ቂሮስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ኃያል ንጉሥ ሆኖ እንደሚነሣ በኢሳይያስ አማካኝነት ትንቢት አስነግሯል። እንዲህ ያለ ዝንፍ የማይል ትንቢት ሊናገር የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው። ከብሔራት የሐሰት አማልክት መካከል ይሖዋን የሚተካከል የለም። ይሖዋ “ክብሬን ለሌላ . . . አልሰጥም” ሲል የተናገረው ያለ ምክንያት አይደለም። “እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፣ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” ሊል የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 42:8፤ 44:6, 7
በፍርሃት የተዋጡ ሰዎች በጣዖታት ይታመናሉ
9-11. የቂሮስ ግስጋሴ በብሔራት ላይ ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርባቸዋል? ምንስ ያደርጋሉ?
9 ቀጥሎ ደግሞ ኢሳይያስ ይህ ድል አድራጊ ሲነሣ ብሔራት የሚሰማቸውን ስሜትና የሚወስዱትን እርምጃ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ደሴቶች አይተው ፈሩ፣ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም። ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፣ ወንድሙንም:- አይዞህ ይለው ነበር። አናጢውም አንጥረኛውን፣ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፣ ስለ ማጣበቅ ሥራውም:- መልካም ነው አለ፤ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው።”—ኢሳይያስ 41:5-7
10 ይሖዋ 200 ዓመታት ወደፊት አሻግሮ በመመልከት የዓለም መልክ ምን እንደሚመስል ይቃኛል። በቂሮስ የሚመራ ኃያል ሠራዊት ተቃዋሚዎችን ሁሉ ድል እያደረገ በፍጥነት ይገሰግሳል። በደሴቶች ማለትም ርቀው በሚገኙ ቦታዎች የሚኖሩ ሕዝቦች ሳይቀሩ በግስጋሴው ይርዳሉ። በፍርሃት ተውጠው ይሖዋ የቅጣት ፍርድ እንዲያስፈጽም ከምሥራቅ የጠራውን ለመቃወም ግንባር ይፈጥራሉ። አንዳቸው ሌላውን “አይዞህ” በማለት እርስ በርስ ለመበረታታት ይሞክራሉ።
11 የዕደ ጥበብ ሠራተኞች አንድ ላይ ተባብረው ሕዝቡን ነፃ የሚያወጡ የጣዖት አማልክትን ይሠራሉ። አናጢው የእንጨት ጥርቡን ያዘጋጅና አንጥረኛው በብረት ምናልባትም በወርቅ እንዲለብጠው ያደርጋል። ከዚያም የቅርፃ ቅርፅ ሠራተኛው ብረቱን አለስልሶ ቅርፅ ካስያዘው በኋላ አንድ ላይ እንዲያጣብቁት ይሰጣል። ጣዖቱን በችንካር ስለማጋጠም የሚገልጸው አነጋገር ጣዖቱ በይሖዋ ታቦት ፊት እንደተደፋው እንደ ዳጎን ምስል ሚዛኑን ስቶ እንዳይወድቅ ለማመልከት የገባ የምፀት አነጋገር ሳይሆን አይቀርም።—1 ሳሙኤል 5:4
አትፍሩ!
12. ይሖዋ ለእስራኤል ምን ዋስትና ሰጥቷል?
12 አሁን ደግሞ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ ራሱ ሕዝብ ያዞራል። በእውነተኛው አምላክ የሚታመኑ ሰዎች በድን በሆኑ ጣዖታት እንደሚታመኑት አሕዛብ የሚፈሩበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ይሖዋ የሰጠው ዋስትና እስራኤል የወዳጁ የአብርሃም ዝርያ መሆኑን በማሳሰብ ይጀምራል። ከፍተኛ የርኅራኄ ስሜት በተንጸባረቀበት በዚህ መግለጫ ኢሳይያስ የይሖዋን ቃላት እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል:- “ባሪያዬ እስራኤል፣ የመረጥሁህ ያዕቆብ፣ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፣ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና:- አንተ ባሪያዬ ነህ፣ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፣ እረዳህማለሁ፣ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።”—ኢሳይያስ 41:8-10
13. ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በምርኮ ለተያዙት አይሁዳውያን አጽናኝ የሆኑት ለምንድን ነው?
13 እነዚህ ቃላት በባዕድ አገር በግዞት ይኖሩ የነበሩትን የታመኑ አይሁዳውያን በእጅጉ አጽናንተዋቸው መሆን አለበት። የባቢሎን ንጉሥ ባሪያዎች ሆነው በግዞት እያሉ ይሖዋ “ባሪያዬ” ሲላቸው መስማት ምንኛ የሚያበረታታ ነው! (2 ዜና መዋዕል 36:20) ይሖዋ ታማኝ ሆነው ባለመገኘታቸው ምክንያት የሚቀጣቸው ቢሆንም ጨርሶ ይተዋቸዋል ማለት ግን አይደለም። እስራኤል የይሖዋ እንጂ የባቢሎን ንብረት አይደለችም። ይሖዋ ከጎናቸው ሆኖ ስለሚረዳቸው የአምላክ አገልጋዮች በድል አድራጊው ቂሮስ ግስጋሴ በፍርሃት የሚርዱበት ምክንያት አይኖርም።
14. ይሖዋ ለእስራኤል የተናገራቸው ቃላት ዛሬ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች የሚያጽናኑት እንዴት ነው?
14 በዘመናችን ያሉት የአምላክ አገልጋዮችም በእነዚህ ቃላት መጽናናትና መበረታታት ችለዋል። በ1918 ይሖዋ ለእነርሱ ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉተው ነበር። ከነበሩበት መንፈሳዊ ግዞት ነፃ የሚወጡበትን ጊዜ ይናፍቁ ነበር። ዛሬም ሰይጣን፣ ዓለምና አለፍጽምናችን ከሚያሳድሩብን ተጽዕኖ እፎይ የምንልበትን ጊዜ እንናፍቃለን። ይሁንና ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል መቼና እንዴት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት በትክክል እንደሚያውቅ እንገነዘባለን። ትንንሽ ልጆች የወላጆቻቸውን እጅ ሙጭጭ አድርገው እንደሚይዙ ሁሉ እኛም ይሖዋ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም እንድንችል እንደሚረዳን በመተማመን ኃያል እጁን አጥብቀን እንይዛለን። (መዝሙር 63:7, 8 አ.መ.ት ) ይሖዋ አገልጋዮቹን ይንከባከባቸዋል። ከ1918-19 በነበረው አስቸጋሪ ወቅትም ሆነ በጥንት እስራኤላውያን ዘመን የታመኑ ሕዝቦቹን እንደደገፋቸው ሁሉ እኛንም ይደግፈናል።
15, 16. (ሀ) የእስራኤል ጠላቶች ምን ይገጥማቸዋል? እስራኤል በትል የተመሰለችው በምን መንገድ ነው? (ለ) ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በአሁኑ ጊዜ ይበልጥ አበረታች የሚሆኑት ምን ዓይነት ጥቃት እየቀረበ ስላለ ነው?
15 ይሖዋ ቀጥሎ በኢሳይያስ አማካኝነት ምን እንደሚል ልብ በል:- “እነሆ፣ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፣ ይዋረዱማል፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፣ ይጠፉማል። የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፣ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ። እኔ አምላክህ እግዚአብሔር:- አትፍራ፣ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና። አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፣ አትፍሩ፤ እረዳሃለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር፣ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው።”—ኢሳይያስ 41:11-14
16 የእስራኤል ጠላቶች አያሸንፉም። በእስራኤል ላይ የሚቆጡ ሁሉ ያፍራሉ። የሚዋጓትም ሁሉ ይጠፋሉ። ምንም እንኳ በምርኮ ያሉት እስራኤላውያን በትቢያ ውስጥ እንደሚላወስ ትል ደካማና አቅመ ቢስ መስለው ቢታዩም ይሖዋ ይረዳቸዋል። በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች ውስጥ በዓለም ካሉ ሰዎች የከረረ ጥላቻና ተቃውሞ ለሚደርስባቸው እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ እንዴት ያለ ማበረታቻ ሆኖላቸዋል! (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በተጨማሪም በትንቢት ‘የማጎጉ ጎግ’ ተብሎ የተገለጸው ሰይጣን ጥቃት የሚሰነዝርበት ጊዜ እየተቃረበ ባለበት ባሁኑ ወቅት የይሖዋ የተስፋ ቃል ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ጎግ አስፈሪ ጥቃቱን በሚሰነዝርበት ጊዜ የአምላክ ሕዝብ ልክ እንደ አንድ ትል አቅመ ቢስ መስሎ ወይም “ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ ያለ መዝጊያም” እንደ ተቀመጠ ሕዝብ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ በፍርሃት የሚንቀጠቀጡበት ምክንያት የለም። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ራሱ እነርሱን ነፃ ለማውጣት ይዋጋላቸዋል።—ሕዝቅኤል 38:2, 11, 14-16, 21-23፤ 2 ቆሮንቶስ 1:3
ለእስራኤል የተነገረ ማጽናኛ
17, 18. ኢሳይያስ እስራኤል ኃይል የምታገኝበትን ሁኔታ በተመለከተ ምን ብሏል? እነዚህ ቃላት የላቀ ፍጻሜ የሚያገኙትስ እንዴት ነው?
17 ይሖዋ ሕዝቡን ማጽናናቱን ይቀጥላል:- “እነሆ፣ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፣ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ። ታበጥራቸዋለህ፣ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፣ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፣ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ።”—ኢሳይያስ 41:15, 16
18 እስራኤል የማጥቃት እርምጃ እንድትወስድና በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደ ተራራ የተመሰሉ ጠላቶቿን እንድታንበረክክ ኃይል ይሰጣታል። እስራኤላውያን ከምርኮ ተመልሰው ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሰው በሚገነቡበት ጊዜ የግንባታ ሥራውን ለማስቆም በሚሞክሩ ጠላቶቻቸው ላይ ድል ይቀዳጃሉ። (ዕዝራ 6:12፤ ነህምያ 6:16) ይሁን እንጂ የይሖዋ ቃላት ‘በአምላክ እስራኤል’ ላይ የላቀ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። (ገላትያ 6:16) ኢየሱስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች እንደሚከተለው ሲል ቃል ገብቷል:- “ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፣ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፣ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ።” (ራእይ 2:26, 27) በትንሣኤ አማካኝነት ሰማያዊ ክብር ያገኙ የክርስቶስ ወንድሞች የይሖዋ አምላክን ጠላቶች በማጥፋቱ ተግባር የሚካፈሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ተሰሎንቄ 1:7, 8፤ ራእይ 20:4, 6
19, 20. ኢሳይያስ እስራኤል ተመልሳ ውብ ሥፍራ እንደምትሆን ሲገልጽ ምን ብሏል? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
19 ይሖዋ ሕዝቡን ለመደገፍ የገባውን ቃል በምሳሌያዊ አገላለጽ ያጠናክረዋል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፣ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፣ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም። በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፣ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፣ የጥማትንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ። የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፣ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፣ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፣ በበረሀውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ።”—ኢሳይያስ 41:17-20
20 ግዞተኞቹ እስራኤላውያን ይኖሩ የነበረው በሀብት በበለጸገችው የዓለም ኃያል መንግሥት ዋና ከተማ ውስጥ ቢሆንም ለእነርሱ ውኃ እንደሌለባት በረሃ ነበረች። ዳዊት ከንጉሥ ሳኦል ተሸሽጎ በነበረበት ጊዜ የተሰማው ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። በ537 ከዘአበ ይሖዋ ወደ ይሁዳ ተመልሰው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደሱን መልሰው በመገንባት ንጹሕ አምልኮን እንዲያቋቁሙ በሩን ይከፍትላቸዋል። ይህን ሲያደርጉም ይሖዋ በአጸፋው ይባርካቸዋል። ቆየት ብሎ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “እግዚአብሔርም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርስዋም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፣ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔድን በረሃዋንም እንደ እግዚአብሔር ገነት ያደርጋል።” (ኢሳይያስ 51:3) አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ይህ ትንቢት በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል።
21. በዘመናችን ምን የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተከናውኗል? ወደፊትስ ምን ይከናወናል?
21 በዚህ ዘመንም ታላቁ ቂሮስ ክርስቶስ ኢየሱስ ንጹሑን አምልኮ መልሰው ያቋቁሙ ዘንድ ቅቡዓን ተከታዮቹን ከመንፈሳዊ ምርኮ ነፃ ባወጣቸው ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል። ታማኝ ሆነው የተገኙት እነዚህ ቅቡዓን ብዙ በረከት የተትረፈረፈበት መንፈሳዊ ገነት ማለትም ምሳሌያዊ የኤድን አትክልት ስፍራ በማግኘት ተባርከዋል። (ኢሳይያስ 11:6-9፤ 35:1-7) በቅርቡ አምላክ ጠላቶቹን በሚያጠፋበት ጊዜ ኢየሱስ ከአጠገቡ ተሰቅሎ ለነበረው ክፉ አድራጊ ቃል እንደገባለት መላዋ ምድር ቃል በቃል ወደ ገነትነት ትለወጣለች።—ሉቃስ 23:43
ለእስራኤል ጠላቶች የቀረበላቸው ፈተና
22. ይሖዋ ለብሔራት በድጋሚ ፈተና የሚያቀርብላቸው ምን በማለት ነው?
22 አሁን ደግሞ ይሖዋ ከብሔራትና ከጣዖት አምላኮቻቸው ጋር የጀመረውን ክርክር ይቀጥላል:- “ክርክራችሁን አቅርቡ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ማስረጃችሁን አምጡ፣ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ። ያምጡ፣ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፣ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፣ የሚመጡትንም አሳዩን። አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ። እነሆ፣ እንዳልነበረ ናችሁ፣ ሥራችሁም ከንቱ ነው፤ የሚመርጣችሁም አስጸያፊ ነው።” (ኢሳይያስ 41:21-24) የአሕዛብ አማልክት ትክክለኛ ትንቢት በመናገር ከሰው የላቀ ኃይል እንዳላቸው ሊያስመሰክሩ ይችላሉን? እንደዚያ ማድረግ የሚችሉ ከሆነ ቃላቸውን የሚደግፍ በጎም ይሁን መጥፎ ውጤት መታየት ይኖርበታል። ሆኖም የጣዖት አማልክት ምንም ሊፈይዱ የማይችሉ በድኖች ናቸው።
23. ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት ጣዖታትን በተደጋጋሚ ያወገዘው ለምንድን ነው?
23 በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋ በኢሳይያስና በሌሎች ነቢያት አማካኝነት የጣዖት አምልኮን በማውገዝ ይህን ያህል ጊዜ ማጥፋት ለምን አስፈለገው ይሉ ይሆናል። ዛሬ ያሉ ብዙ ሰዎች የሰው እጅ ሥራ የሆኑት ጣዖታት ከንቱ መሆናቸው ምንም የማያጠያይቅ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ የሐሰት እምነት አንድ ጊዜ ሥር ከሰደደና በሰፊው ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ከሚያምኑት ሰዎች አእምሮ ውስጥ ነቅሎ ማውጣት ቀላል አይሆንም። ዛሬ ያሉ ብዙ እምነቶችም በድን የሆኑ ምስሎች አማልክት ናቸው ከሚለው እምነት ባልተለየ ሁኔታ ከንቱዎች ናቸው። ይሁንና ሰዎች አሳማኝ ማስረጃ ቢቀርብላቸውም እነዚህን እምነቶች ሙጥኝ ይላሉ። አንዳንዶች በይሖዋ መታመን ጥበብ እንደሆነ ማስተዋል የቻሉት እውነትን ደግመው ደጋግመው በመስማታቸው ነው።
24, 25. ይሖዋ ቂሮስን በድጋሚ በመጥቀስ ምን ብሏል? ይህስ የትኛውን ሌላ ትንቢት ያስታውሰናል?
24 ይሖዋ በድጋሚ ስለ ቂሮስ በመጥቀስ እንዲህ ይላል:- “አንዱን ከሰሜን አስነሣሁት፤ እርሱም ይመጣል፤ ከፀሐይ መውጫ የሚመጣው፣ ስሜን የሚጠራ ነው፤ ሸክላ ሠሪ ዐፈር እንደሚረግጥ፣ አለቆችን እንዲሁ እንደ ጭቃ ይረግጣል።” (ኢሳይያስ 41:25 አ.መ.ት)d ይሖዋ ነገሮችን ዳር ማድረስ ይችላል፤ የአሕዛብ አማልክት ግን ይህን ማድረግ አይችሉም። ቂሮስን “ከፀሐይ መውጫ” ማለትም ከምሥራቅ በማምጣት የመተንበይ ችሎታ እንዳለውና ወደፊት የሚከናወኑት ነገሮች ከትንቢቱ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲፈጸሙ ማድረግ የሚችል መሆኑን በተግባር ያሳያል።
25 እነዚህ ቃላት ሐዋርያው ዮሐንስ በእኛ ዘመን እርምጃ ለመውሰድ ስለሚነሡ ነገሥታት የሰጠውን ትንቢታዊ መግለጫ ያስታውሱናል። በራእይ 16:12 ላይ “ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት” መንገድ እንደሚዘጋጅላቸው ተገልጾልናል። እነዚህ ነገሥታት ከይሖዋ አምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆኑ አይችሉም። ቂሮስ ከረጅም ጊዜ በፊት የአምላክን ሕዝብ ነፃ እንዳወጣ ሁሉ ከእርሱ እጅግ የላቀ ኃይል ያላቸው እነዚህ ነገሥታት የይሖዋን ጠላቶች ጨርሰው በማጥፋት የአምላክን ሕዝብ እየመሩ ከታላቁ መከራ ወደ አዲሱ ዓለም ያሻግሩታል።—መዝሙር 2:8, 9፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 7:14-17
ይሖዋ የሁሉ የበላይ ነው!
26. ይሖዋ ያነሣው ጥያቄ ምን የሚል ነው? ጥያቄውስ መልስ አግኝቷል?
26 ይሖዋ እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ መሆኑን በድጋሚ ይገልጻል። እንዲህ በማለት ጥያቄ ያቀርባል:- “እናውቅ ዘንድ ከጥንት የተናገረው:- እውነት ነው እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? የሚናገር የለም፣ የሚገልጥም የለም፣ ቃላችሁንም የሚሰማ የለም።” (ኢሳይያስ 41:26) በእርሱ የሚታመኑትን ነፃ የሚያወጣ ድል አድራጊ እንደሚነሣ የተነበየ አንድም ጣዖት የለም። እንዲህ ዓይነቶቹ አማልክት በሙሉ መናገር የማይችሉ በድኖች ናቸው። ጨርሶ አማልክትም አይደሉም።
27, 28. በኢሳይያስ ምዕራፍ 41 የመደምደሚያ ቁጥሮች ላይ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ሐቅ ምንድን ነው? ይህንንስ የሚያውጁት እነማን ብቻ ናቸው?
27 ኢሳይያስ ይሖዋ የተናገራቸውን እነዚህን ቀስቃሽ ትንቢታዊ ቃላት ከዘገበ በኋላ የሚከተለውን ሐቅ ጎላ አድርጎ ገልጿል:- “በመጀመሪያ [“መጀመሪያ የሆነው፣” NW ] ለጽዮን:- እነኋቸው እላለሁ፤ ለኢየሩሳሌምም የምስራች ነጋሪን እሰጣለሁ። ብመለከት ማንም አልነበረም፤ ብጠይቃቸውም የሚመልስልኝ አማካሪ በመካከላቸው የለም። እነሆ፣ እነርሱ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፣ ሥራቸውም ምንምን ናት፤ ቀልጠው የተሠሩት ምስሎቻቸውም ነፋስና ኢምንት ናቸው።”—ኢሳይያስ 41:27-29
28 ይሖዋ መጀመሪያ ነው፤ የሁሉም የበላይ ነው! የሕዝቡን ነፃ መውጣት በማወጅ ምሥራችን የሚነግር እውነተኛ አምላክ ነው። ታላቅነቱን ለአሕዛብ የሚነግሩት የእርሱ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። ይሖዋ ጣዖቶቻቸው እንደ “ነፋስና ኢምንት” መሆናቸውን በመግለጽ በጣዖት አምልኮ የሚታመኑትን ሰዎች ይሳለቅባቸዋል። ይህ እውነተኛውን አምላክ የሙጥኝ እንድንል የሚገፋፋ እንዴት ያለ ጠንካራ ምክንያት ነው! ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት የሚገባው አምላክ ይሖዋ ብቻ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
c በ1919 ‘የእግዚአብሔር እስራኤልን’ ከመንፈሳዊ ግዞት ነፃ ያወጣው ታላቁ ቂሮስ ከ1914 ጀምሮ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ከተሾመው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።—ገላትያ 6:16
d የቂሮስ የትውልድ አገር ከባቢሎን በስተ ምሥራቅ ቢሆንም በከተማዋ ላይ የመጨረሻውን ጥቃት ሊሰነዝር የመጣው ግን ከሰሜን ማለትም ከትንሿ እስያ ነበር።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቂሮስ አረማዊ ሰው ቢሆንም አምላክ ዓላማውን ለማስፈጸም መርጦታል
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብሔራት የሚታመኑት በድን በሆኑ ጣዖታት ነው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እስራኤል እንደ “ባለ ጥርስ ማሄጃ” ‘ተራራዎችን ታደቅቃለች’