የአምላክን መንጋ በፍቅር መጠበቅ
“በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ።”—1 ጴጥሮስ 5:2
1, 2. የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ምንድን ነው? ይህ ባሕርይ የሚገለጸውስ እንዴት ነው?
በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ፍቅር የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ ተገልጿል። 1 ዮሐንስ 4:8 “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል። ፍቅሩ በተግባር የተገለጸ በመሆኑ 1 ጴጥሮስ 5:7 አምላክ “ስለ እናንተ ያስባል” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው አሳቢነት በጎቹን በእንክብካቤ ከሚጠብቅ አንድ አፍቃሪ እረኛ ሁኔታ ጋር ተመሳስሏል፦ “እነሆ፣ ጌታ እግዚአብሔር . . . መንጋውን . . . ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” (ኢሳይያስ 40:10, 11) ዳዊት “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፣ የሚያሳጣኝም የለም” ብሎ መናገር እስኪችል ድረስ ምንኛ ተጽናንቶ ነበር!—መዝሙር 23:1
2 በጎች ሰላማውያን፣ ተገዢዎችና ለሚጠብቃቸው እረኛ ታዛዥ ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሞገስ የሚያገኙ ሰዎችን ከበጎች ጋር ማመሳሰሉ ተገቢ ነው። ይሖዋ አፍቃሪ እረኛ እንደመሆኑ መጠን በግ መሰል ለሆኑት ሕዝቡ በጣም ያስባል። ለሕዝቡ ቁሳዊ ነገርንም ሆነ መንፈሳዊ ነገርን በመስጠትና በዚህ ክፉ ዓለም አስቸጋሪ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ ሕዝቡን ወደ መጪው የጽድቅ አዲስ ዓለም በመምራት ይህን አሳቢነቱን አሳይቷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13፤ ማቴዎስ 6:31–34፤ 10:28–31፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
3. መዝሙራዊው ይሖዋ በጎቹን የሚይዝበትን መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ለበጎቹ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ተመልከት፦ “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። . . . ጻድቃን ጮኹ፣ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል። የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።” (መዝሙር 34:15–19) የጽንፈ ዓለሙ እረኛ በግ መሰል ለሆኑት ሕዝቡ እንዴት ያለ ታላቅ መጽናኛ ይሰጣቸዋል!
የመልካሙ እረኛ ምሳሌ
4. የአምላክን መንጋ በመንከባከብ ረገድ ኢየሱስ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?
4 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “መልካም እረኛ” ብሎ ስለሚጠራው የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከአባቱ በደንብ ተምሯል። (ዮሐንስ 10:11–16) ኢየሱስ ለአምላክ መንጋ የሚሰጠው እጅግ አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ ተገልጿል። በቁጥር 9 ላይ በዘመናችን ያሉት የአምላክ አገልጋዮች ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ተብለዋል። ከዚያም ቁጥር 17 እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “በጉ [ኢየሱስ] እረኛቸው ይሆናልና፣ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።” ኢየሱስ የአምላክን በጎች ወደ ዘላለም ሕይወት ወደሚወስደው የሕይወት ውኃ ይመራቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስ “በጉ” ተብሎ መጠራቱን ልብ በል። ይህም የራሱን በግ መሰል ባሕርያት ያመለክታል። ለአምላክ በመገዛት ረገድ ዋነኛ ምሳሌ ነው።
5. ኢየሱስ ስለ ሰዎች ምን ተሰምቶት ነበር?
5 ኢየሱስ በምድር ላይ ከሰዎች ጋር በመኖር የነበሩበትን አሳዛኝ ሁኔታ ተመልክቷል። ችግራቸውን ሲመለከት ምን ተሰማው? “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” (ማቴዎስ 9:36) እረኛ የሌላት በግ ከአውሬ በሚደርስባት ጥቃት ክፉኛ ልትሠቃይ ትችላለች፤ ምንም የማያስቡላቸው እረኞች ያሏቸው በጎችም እንደዚሁ ናቸው። ኢየሱስ ግን በጣም አስቦላቸዋል፤ ምክንያቱም እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28–30
6. ኢየሱስ ለተጨቆኑት ሰዎች ምን አሳቢነት አሳያቸው?
6 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ኢየሱስ ሰዎችን በፍቅር እንደሚይዛቸው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፦ “እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ . . . የሚያለቅሱትንም ሁሉ አጽናና ዘንድ።” (ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:17–21) ኢየሱስ ድሆቹንና ምስኪኖቹን አልናቃቸውም። ከዚህ ይልቅ “የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፣ የሚጤስንም ክር አያጠፋም” የሚለውን ኢሳይያስ 42:3ን ፈጽሟል። (ከማቴዎስ 12:17–21 ጋር አወዳድር።) እንግልት የደረሰባቸው ሰዎች እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆና ነዳጁ በማለቁ ሊጠፋ እንደተቃረበ የኩራዝ ክር ነበሩ። ኢየሱስ ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ በመገንዘብ አዘኔታ አሳይቷቸዋል፤ እንዲሁም በመንፈሳዊና በሥጋዊም በመፈወስ ብርታትና ተስፋ ሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 4:23
7. ኢየሱስ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጡት የነበሩትን ሰዎች በማን ላይ እንዲያተኩሩ ያደርግ ነበር?
7 ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በግ መሰል ሰዎች ኢየሱስ ላደረገላቸው ነገሮች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ትምህርቶቹ በጣም የሚማርኩ ስለነበሩ እርሱን እንዲይዙ ተልከው የነበሩት መኮንኖች “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” በማለት ተናግረዋል። (ዮሐንስ 7:46) እንዲያውም ግብዞቹ ሃይማኖታዊ መሪዎች “ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል” በማለት በምሬት ተናግረዋል! (ዮሐንስ 12:19) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለራሱ ክብር ወይም ታላቅነት ለማግኘት አልፈለገም። ሰዎች በአባቱ ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል። ይሖዋን ባሉት አስደናቂ ባህርያት የተነሣ በፍቅር ተገፋፍተው እንዲያገለግሉት አስተምሯቸዋል፦ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።”—ሉቃስ 10:27, 28
8. የአምላክ ሕዝብ ለእርሱ የሚያሳዩት ታዛዥነት ሌሎች ሰዎች ለዓለማዊ መሪዎች ከሚያሳዩት ታዛዥነት የሚለየው እንዴት ነው?
8 በግ መሰል የሆኑት ሕዝቡ ለእርሱ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ሲደግፉ ይሖዋ ይከበራል። ደስ ስለሚሉት ባህሪዎቹ ካላቸው እውቀት የተነሣ እርሱን በፈቃደኝነት ለማገልገል ይመርጣሉ። በፍርሃት ወይም ያለ ውዴታ አለዚያም አንድ ዓይነት ጥቅም የማግኘት ድብቅ ፍላጎት ስላላቸው ብቻ የሚታዘዙ ተገዢዎች ካሏቸው ከዚህ ዓለም መሪዎች ምንኛ የተለየ ነው! “[ጳጳሱ] በብዙዎች አድናቆት የተቸራቸው፣ በሁሉም ዘንድ የሚፈሩና በማንም ሰው የማይፈቀሩ ናቸው” ተብሎ ስለ አንድ የሮማ ካቶሊክ ጳጳስ የተነገረው ነገር ለይሖዋም ሆነ ለኢየሱስ ፈጽሞ ሊባል የማይችል ነገር ነው።—በፒተር ደ ሮሳ የተጻፈ ቪካርስ ኦቭ ክራይስት—ዘ ዳርክ ሳይድ ኦቭ ዘ ፓፓሲ የተባለ መጽሐፍ
በእስራኤል የነበሩ ጨካኝ እረኞች
9, 10. በጥንቷ እስራኤልና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የሕዝብ መሪዎች ሁኔታ ግለጽ።
9 ከኢየሱስ በተለየ መልኩ በእርሱ ዘመን የነበሩት የእስራኤል ሃይማኖታዊ መሪዎች ለበጎቹ ምንም ዓይነት ፍቅር አልነበራቸውም። ይሖዋ እንዲህ በማለት እንደተናገራቸው ከእነርሱ በፊት በእስራኤል ውስጥ እንደነበሩት የሕዝብ መሪዎች ነበሩ፦ “ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? . . . የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቆናም ገዛችኋቸው።”—ሕዝቅኤል 34:2–4
10 ልክ እንደ እነዚህ የፖለቲካ እረኞች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎችም ልባቸውን አደንድነው ነበር። (ሉቃስ 11:47–52) ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ኢየሱስ ሌቦች ዘርፈውና ደብድበው በሕይወትና በሞት መካከል በመንገድ ዳር ጥለውት ስለሄዱ አንድ አይሁዳዊ ተናግሮ ነበር። አንድ እስራኤላዊ ካህን በዚያ በኩል መጣ፤ አይሁዳዊውን ሲመለከት ግን አቅጣጫውን ቀይሮ በሌላ መንገድ ሄደ። አንድ ሌዋዊም እንዲሁ አደረገ። ከዚያም እስራኤላዊ ያልሆነ አንድ የተናቀ ሳምራዊ በዚያ በኩል መጣ። የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆነውን ሰውም አዘነለት። ቁስሉን አሰረለትና በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ አንድ አነስተኛ ሆቴል በመውሰድ እንክብካቤ አደረገለት። ለሆቴሉ ባለቤት ገንዘብ ከፈለና ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል ተመልሶ እንደሚመጣ ነገረው።—ሉቃስ 10:30–37
11, 12. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ሃይማኖታዊ መሪዎች ይፈጽሙት የነበረው ኃጢአት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው እንዴት ነው? (ለ) በመጨረሻ ሮማውያን ሃይማኖታዊ መሪዎቹን ምን አደረጓቸው?
11 በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ምግባራቸው እጅግ ያዘቀጠ ስለነበረ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሣበት ወቅት የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የፍርድ ሸንጎውን ጠሩና እንዲህ አሉ፦ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው [ኢየሱስ] ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ።” (ዮሐንስ 11:47, 48) ኢየሱስ ለሞተው ሰው የፈጸመው መልካም ነገር ግድ አልሰጣቸውም። እነርሱ ያሳሰባቸው ከፍተኛ ቦታቸውን የማጣታቸው ጉዳይ ነበር። ስለዚህ “ከዚያ ቀን ጀምረው [ኢየሱስን] ሊገድሉት ተማከሩ።”—ዮሐንስ 11:53
12 በክፋታቸው ላይ ክፋት ለመጨመር የካህናት አለቆቹ “አልዓዛርን ደግሞ ሊገድሉት ተማከሩ፣ ከአይሁድ ብዙዎች ከእርሱ የተነሣ ሄደው በኢየሱስ ያምኑ ነበርና።” (ዮሐንስ 12:10, 11) ኢየሱስ “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ብሏቸው ስለነበር የነበራቸውን ከፍተኛ ቦታ ለመጠበቅ ያደረጓቸው የራስ ወዳድነት ጥረቶች ከንቱ ልፋት ነበሩ። (ማቴዎስ 23:38) ያለውም አልቀረ፤ በዚያ ትውልድ ሮማውያን መጥተው ‘አገራቸውንና ወገናቸውን’ ወሰዱ፤ ሕይወታቸውንም ለሕልፈት ዳረጉት።
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አፍቃሪ እረኞች
13. ይሖዋ መንጋዬን እንዲጠብቅ እልከዋለሁ ብሎ ቃል የገባው ማንን ነው?
13 በጨካኞቹና በራስ ወዳዶቹ እረኞች ፈንታ ይሖዋ መንጋውን እንዲጠብቅ መልካሙን እረኛ ኢየሱስን አስነሣ። በተጨማሪም በጎቹን እንዲጠብቁ አፍቃሪ የበታች እረኞችን እንደሚያስነሣ ቃል ገብቶ ነበር፦ “የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፣ ዳግመኛም አይፈሩም።” (ኤርምያስ 23:4) ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ‘በየከተማው ሽማግሌዎች ይሾማሉ።’ (ቲቶ 1:5) በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጹትን ብቃቶች ያሟሉ እነዚህ በመንፈሳዊ የሸመገሉ ወንድሞች ‘የአምላክን መንጋ ይጠብቃሉ።’—1 ጴጥሮስ 5:2፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1–7፤ ቲቶ 1:7–9
14, 15. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ የትኛውን አመለካከት ማዳበር አቅቷቸው ነበር? (ለ) ሽማግሌዎች ትሑት አገልጋዮች መሆን እንዳለባቸው ለማሳየት ኢየሱስ ምን አደረገ?
14 ሽማግሌዎች በጎቹን በመጠበቅ ረገድ “ከሁሉ በፊት” ለበጎቹ ‘የጠለቀ ፍቅር’ ሊኖራቸው ይገባል። (1 ጴጥሮስ 4:8) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግን ክብርና ማዕረግ ለማግኘት ከመጠን በላይ ያስቡ ስለነበረ ይህን መማር ነበረባቸው። ስለዚህ የሁለቱ ደቀ መዛሙርት እናት ኢየሱስን “እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ” ባለችው ጊዜ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ተቆጡ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን።”—ማቴዎስ 20:20–28
15 በሌላ ወቅት ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ “ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን?” ብለው ከተከራከሩ በኋላ ኢየሱስ “ሰው ፊተኛ ሊሆን ቢወድ ከሁሉ በኋላ የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። (ማርቆስ 9:34, 35) ራስን ዝቅ ማድረግና ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን የባሕርያቸው ክፍል መሆን ነበረበት። ሆኖም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከመሞቱ አንድ ቀን አስቀድሞ በነበረው ሌሊት በመጨረሻው እራት ላይ ማን ታላቅ እንደሚሆን በመካከላቸው የጦፈ “ክርክር” ተነሥቶ ስለነበር በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ያላቸው ችግር አልለቀቃቸውም ነበር! ኢየሱስ አንድ ሽማግሌ እንዴት መንጋውን ማገልገል እንዳለበት ያሳያቸው ቢሆንም እንኳ ይህ ነገር ተከስቷል። ኢየሱስ ራሱን ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቦ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ እግራችሁን ትጠጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።”—ሉቃስ 22:24፤ ዮሐንስ 13:14, 15
16. መጠበቂያ ግንብ በ1899 እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የሽማግሌዎች ብቃት አስመልክቶ ምን ሐሳብ ሰጠ?
16 ሽማግሌዎች እንደዚህ መሆን እንዳለባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሁልጊዜ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ወደ አንድ መቶ ዘመን ከሚጠጋ ጊዜ በፊት የሚያዝያ 1, 1899 መጠበቂያ ግንብ በ1 ቆሮንቶስ 13:1–8 ላይ ያሉትን የጳውሎስን ቃላት ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሐዋርያው እጅግ አስፈላጊ የሆኑት መመዘኛዎች እውቀትና የተዋጣለት ተናጋሪ መሆን እንዳልሆነ ለይቶ አመልክቷል። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና የሚመዘንበት ትክክለኛ መመዘኛ ወደ ልብ ዘልቆ የሚገባው፣ በሕይወት ዘመን ሁሉ እየጎለበተ የሚሄደውና ሟች አካላችንን የሚያንቀሳቅሰው ፍቅር ነው። . . . በቅዱስ ነገሮች ለማገልገል የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ተደርጎ ተቀባይነት ያገኘ ማንኛውም ሰው ከምንም ነገር በላይ ሊፈልገው የሚገባ አንደኛ ደረጃ የሚሰጠው ባሕርይ የፍቅር መንፈስ ነው።” ከፍቅር ተነሣስተው በትሕትና የማያገለግሉ ሰዎች “ጥሩ አስተማሪዎች አይደሉም፤ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል” ሲል ገልጿል።—1 ቆሮንቶስ 8:1
17. ሽማግሌዎች ሊኖሯቸው የሚገቡትን ባሕርያት መጽሐፍ ቅዱስ ጎላ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?
17 ስለዚህ ሽማግሌዎች በጎቹን ‘በኃይል መግዛት’ የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:3) ከዚህ ይልቅ “ቸሮችና ርኅሩኆች” በመሆን ረገድ ቀዳሚ ሆነው መገኘት አለባቸው። (ኤፌሶን 4:32) ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጎላ አድርጎ ገልጾታል፦ “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ . . . በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቆላስይስ 3:12–14
18. (ሀ) ጳውሎስ ከበጎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል? (ለ) ሽማግሌዎች በጎቹ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በማሟላት ረገድ ችላ ማለት የሌለባቸው ለምንድን ነው?
18 ጳውሎስ እንዲህ ማድረግን ተምሮ ነበር። እንዲህ አለ፦ “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።” (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲህ ብሏል፦ “የተጨነቁትን አጽናኑአቸው፤ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።” (1 ተሰሎንቄ 5:14 አዓት) ሽማግሌዎች በጎቹ ምንም ዓይነት ችግር ቢያቀርቡላቸው ምሳሌ 21:13ን ማስታወስ ይኖርባቸዋል፦ “የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፣ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።”
19. አፍቃሪ ሽማግሌዎች በረከት የሚሆኑት ለምንድን ነው? በጎቹስ ይህን ለመሰለው ፍቅር ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
19 መንጋውን በፍቅር የሚጠብቁ ሽማግሌዎች ለበጎቹ በረከት ናቸው። ኢሳይያስ 32:2 እንዲህ ሲል አስቀድሞ ተናግሯል፦ “ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።” በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ ሽማግሌዎቻችን ከዚህ ማራኪና አጽናኝ መግለጫ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚሠሩ መሆናቸውን ማወቃችን ያስደስተናል። “በወንድማማች መዋደድ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በእርሳችሁ ተከባበሩ [አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ አዓት]” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ማዋልን ተምረዋል። (ሮሜ 12:10) ሽማግሌዎች እንዲህ ዓይነቱን ፍቅርና ትሕትና ሲያሳዩ በጎቹ ‘ስለ ሥራቸው በፍቅር ከመጠን ይልቅ በማክበር’ አጸፋውን ይመልሱላቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 5:12, 13
የሰውን ነፃ ፈቃድ አክብሩ
20. ሽማግሌዎች የሰውን ነፃ ፈቃድ ማክበር ያለባቸው ለምንድን ነው?
20 ይሖዋ የሰው ልጆች የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ እንዲችሉ ነፃ ፈቃድ ሰጥቶ ፈጥሮአቸዋል። ምንም እንኳ ሽማግሌዎች መምከርና አልፎ ተርፎም መገሰጽ ቢችሉም የሌላውን ሰው ሕይወት ወይም እምነት ሊቆጣጠሩ አይችሉም። ጳውሎስ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፣ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም። በእምነታችሁ ቆማችኋልና” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 1:24) አዎን፣ “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም” ይሸከማል። (ገላትያ 6:5) ይሖዋ በሕግጋቱና በመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ክልል ውስጥ ሰፊ ነጻነት ሰጥቶናል። ስለዚህ ሽማግሌዎች ቅዱስ ጹሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስካልተጣሱ ድረስ ደንቦችን ከማውጣት መታቀብ ይኖርባቸዋል። የራሳቸውን የግል አመለካከቶች እንደ ሃይማኖታዊ ሕግ አድርገው የማቅረብ ዝንባሌ እንዳይጠናወታቸው መከላከል አለባቸው። ወይም ደግሞ እንዲህ ዓይነቶቹን አመለካከቶች ሌላ ሰው ሳይስማማባቸው ሲቀር ኩራት ተሰምቷቸው ችግር እንዲፈጠር ቀዳዳ መክፈት የለባቸውም።—2 ቆሮንቶስ 3:17፤ 1 ጴጥሮስ 2:16
21. ጳውሎስ ለፊልሞና ከነበረው አመለካከት ምን መማር ይቻላል?
21 ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት በትንሿ እስያ ውስጥ በምትገኘው በቆላስይስ ውስጥ ይኖር የነበረውንና የባሪያ አሳዳሪ የነበረውን ክርስቲያኑን ፊልሞና እንዴት እንደመከረው ተመልከት። አናሲሞስ የተባለ የፊልሞና ባሪያ ጠፍቶ ወደ ሮም ከሄደ በኋላ ክርስቲያን ሆነና ጳውሎስን መርዳት ጀምሮ ነበር። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ለፊልሞና ጻፈለት፦ “እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፣ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፣ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም።” (ፊልሞና 13, 14) ጳውሎስ ፊልሞና እንደ አንድ ክርስቲያን ወንድም አድርጎ እንዲይዘው በመለመን አናሲሞስን መልሶ ወደ እርሱ ላከው። ጳውሎስ መንጋው የእርሱ ሳይሆን የአምላክ መሆኑን ያውቅ ነበር። የመንጋው ጌታ ሳይሆን አገልጋይ ነበር። ጳውሎስ ፊልሞናን እንዲህ እንድታደርግ አላለውም፤ ነፃ ፈቃዱን አክብሮለታል።
22. (ሀ) ሽማግሌዎች ቦታቸው ምን እንደሆነ መረዳት ይኖርባቸዋል? (ለ) ይሖዋ ምን ዓይነት ድርጅት እያጎለበተ ነው?
22 የአምላክ ድርጅት ባደገ ቁጥር ብዙ ሽማግሌዎች ተሹመዋል። እነርሱም ሆኑ ከእነርሱ የበለጠ ልምድ ያላቸው ሽማግሌዎች የያዙት ቦታ ራስን ዝቅ በማድረግ ከሚከናወኑት አገልግሎቶች አንዱ መሆኑን መረዳት አለባቸው። በዚህ መንገድ አምላክ ድርጅቱን ወደ አዲሱ ዓለም በገፋው መጠን ድርጅቱ እሱ በሚፈልገው መንገድ ማለትም ሥራን በተቀላጠፈ መንገድ ለማከናወን ሲል ፍቅርንና ርኅራኄን መሥዋዕት ሳያደርግ በደንብ የተደራጀ ሆኖ ማደጉን ይቀጥላል። በዚህ መንገድ “አምላክ እርሱን ለሚወዱት ጥቅም ሲል ሥራዎቹን ሁሉ እንደሚያቀናጅ” የሚያሳይ ማስረጃ በድርጅቱ ውስጥ የሚመለከቱት በግ መሰል ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ድርጅቱ ይበልጥ ይማርካቸዋል። ይህም በፍቅር ላይ ከተመሠረተ አንድ ድርጅት የሚጠበቅ ነገር ነው። ምክንያቱም “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም።”—ሮሜ 8:28 አዓት፤ 1 ቆሮንቶስ 13:8
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን አሳቢነት የሚገልጸው እንዴት ነው?
◻ የአምላክን መንጋ በመንከባከብ ረገድ ኢየሱስ ምን ሚና ይጫወታል?
◻ ሽማግሌዎች ምን ዋነኛ ባህርይ ሊኖራቸው ይገባል?
◻ ሽማግሌዎች በጎቹ ያላቸውን ነፃ ፈቃድ ማስታወስ ያለባቸው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“መልካሙ እረኛ” ኢየሱስ አዘኔታ አሳይቷል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብልሹዎቹ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን ለመግደል አሲረዋል