“የአምላክ እስራኤል” እና “እጅግ ብዙ ሰዎች”
“አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ።”—ራእይ 7:9
1–3. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ክብራማ የሆነ ምን ሰማያዊ ተስፋ አላቸው? (ለ) ሰይጣን የመጀመሪያውን መቶ ዘመን ጉባኤ ለማጥፋት የሞከረው እንዴት ነበር? (ሐ) በ1919 ሰይጣን የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ ለመበከል ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት የሚጠቁም ምን ነገር ተከሰተ?
በ33 እዘአ ‘የአምላክ እስራኤል’ መመሥረቱ በአምላክ ዓላማዎች አፈጻጸም ረገድ ከፍተኛ ክንውን ነበር። (ገላትያ 6:16) ቅቡዓን አባላቱ የማይሞቱ መንፈሳዊ ፍጥረታት የመሆንና ከክርስቶስ ጋር በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ የመግዛት ተስፋ አላቸው። (1 ቆሮንቶስ 15:50, 53, 54) በዚህ ሥልጣናቸው የይሖዋን ስም ለማስቀደስና የታላቁን ባላጋራ የሰይጣን ዲያብሎስን ጭንቅላት በመቀጥቀጥ የመሪነት ቦታ ይይዛሉ። (ዘፍጥረት 3:15፤ ሮሜ 16:20) ሰይጣን በማሳደድም ሆነ ለመበከል በመጣር ይህን ጉባኤ ለማጥፋት የሚችለውን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም!—2 ጢሞቴዎስ 2:18፤ ይሁዳ 4፤ ራእይ 2:10
2 ሐዋርያት በሕይወት ሳሉ ሰይጣን በጉባኤው ውስጥ ክህደት ለማስገባት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። ሆኖም እነሱ ከሞቱ በኋላ ምንም የሚያግደው ሳይኖር ክህደት ተስፋፋ። ውሎ አድሮ በሰዎች አመለካከት ኢየሱስ የመሠረተው ንጹሕ የክርስቲያን ጉባኤ ሰይጣን በአሁኑ ወቅት ሕዝበ ክርስትና ተብሎ የሚታወቀውን ሃይማኖታዊ ክህደት ሲያመጣ የጠፋ መሰለ። (2 ተሰሎንቄ 2:3–8) ሆኖም እውነተኛ ክርስትና አልጠፋም።—ማቴዎስ 28:20
3 ኢየሱስ በስንዴውና በእንክርዳዱ ምሳሌው ላይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከ“እንክርዳዶቹ” ወይም ከሐሰተኛ ክርስቲያኖች ጋር ለተወሰነ ጊዜ እንደሚያድጉ ተንብዮአል፤ ይህም ተፈጽሟል። ይሁን እንጂ በመጨረሻዎቹ ቀናት “የመንግሥት ልጆች” ‘ከእንክርዳዶቹ’ እንደገና እንደሚለዩ ተናግሯል። (ማቴዎስ 13:36–43) ይህም ቢሆን ተፈጽሟል። እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 ከባቢሎናዊ ምርኮ ነፃ ወጡ። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በመሆን መለኮታዊ ተቀባይነት አገኙ፤ በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች በድፍረት መስበክ ጀመሩ። (ማቴዎስ 24:14, 45–47፤ ራእይ 18:4) አብዛኞቹ አሕዛብ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ የአብርሃም ዓይነት እምነት ስለ ነበራቸው በእርግጥም ‘የአብርሃም ዘር’ ነበሩ። ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ነበሩ።—ገላትያ 3:7, 26–29
“እጅግ ብዙ ሰዎች”
4. በተለይ በ1930ዎቹ ዓመታት ተለይቶ የታወቀው የትኛው የክርስቲያኖች ቡድን ነው?
4 መጀመሪያ ላይ የእነዚህን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስብከት የተቀበሉ ሁሉ መንፈሳዊ እስራኤላውያን ማለትም ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው የ144,000ዎቹ ቀሪዎች ሆነው ነበር። (ራእይ 12:17) ይሁን እንጂ በተለይ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ሌላ ቡድን ተለይቶ ታወቀ። እነዚህ ሰዎች በበረቶቹ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት “ሌሎች በጎች” እንደሆኑ ተስተዋለ። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ሌሎች በጎች በምድራዊት ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያላቸው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናቸው። በምሳሌያዊ አነጋገር የቅቡዓን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ዘሮች ናቸው። (ኢሳይያስ 59:21፤ 66:22፤ ከ1 ቆሮንቶስ 4:15, 16 ጋር አወዳድር።) የቅቡዓን ክርስቲያን ጉባኤ ታማኝና ልባም ባሪያ እንደሆነ ያምናሉ፤ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ቅቡዓን ወንድሞቻቸው ሁሉ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር አላቸው፣ በኢየሱስ መሥዋዕት ያምናሉ፣ አምላክን በቅንዓት ያወድሳሉ እንዲሁም ለጽድቅ ሲሉ ለመሰደድ ፈቃደኛ ናቸው።
5. የሌሎች በጎች ቦታ ደረጃ በደረጃ በተሻለ መንገድ የተስተዋለው እንዴት ነው?
5 በመጀመሪያ የእነዚህ ሌሎች በጎች ቦታ በደንብ አልታወቀም ነበር፤ ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ቦታቸው ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ። በ1932 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎች በጎች በስብከቱ ሥራ እንዲሳተፉ ማበረታታት ጀመሩ፤ ብዙ የሌሎች በጎች አባላት ቀደም ሲል ይህን ሥራ መሥራት ጀምረው ነበር። በ1934 ሌሎች በጎች በውኃ እንዲጠመቁ ማበረታቻ ተሰጣቸው። በ1935 ሌሎች በጎች በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሱት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ክፍል እንደሆኑ ተለይቶ ታወቀ። በ1938 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንደ ተመልካቾች ሆነው እንዲገኙ ተጋበዙ። በ1950 ከመካከላቸው ብስለት ያላቸው ወንዶች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ሆነው ከሚያገለግሉት “መሳፍንት” መካከል እንደሚሆኑ ተስተዋለ። (መዝሙር 45:16 አዓት ፤ ኢሳይያስ 32:1, 2) በ1953 የአምላክ ምድራዊ ድርጅት በአዲሱ ዓለም የሚኖረው ምድራዊ ኅብረተሰብ ቆርቋሪ እንደሚሆን መገንዘብ ተቻለ፤ በዚያ ወቅት የዚህን ድርጅት አብዛኛውን ክፍል ይዘው የነበሩት ሌሎች በጎች ነበሩ። በ1985 ሌሎች በጎች በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከአርማጌዶን በሕይወት የመትረፍ ተስፋ ያላቸው የአምላክ ወዳጆች ሆነው እንደ ጻድቃን እንደሚቆጠሩ ተስተዋለ።
6. በአሁኑ ወቅት ቅቡዓንና ሌሎች በጎች ያላቸው ቦታ እንዴት ይነጻጸራል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?
6 አሁን በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ የኋለኞቹ ዓመታት አብዛኞቹ የ144,000 አባላት ሞተው ሰማያዊ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ራእይ 6:9–11፤ 14:13) በአሁኑ ወቅት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች አብዛኛውን ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ እያከናወኑ ነው፤ በዚህ ረገድ የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞችን መርዳትን እንደ መብት ይቆጥሩታል። (ማቴዎስ 25:40) ይሁን እንጂ እነዚህ ቅቡዓን በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ ሲያቀርቡ የቆዩ ታማኝና ልባም ባሪያ ናቸው። ቅቡዓን በሙሉ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ሲቀበሉ የሌሎች በጎች ሁኔታ ምን ይሆናል? በዚያን ጊዜ ለሌሎች በጎች ምን ዝግጅቶች ይደረጉላቸዋል? በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የነበረውን ሁኔታ በአጭሩ መመልከታችን እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ይረ ዳናል።
በጥላበት የሚያገለግል “የካህናት መንግሥት”
7, 8. የጥንቷ እስራኤል በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ የነበረችው እስከ ምን ድረስ ነው?
7 ይሖዋ እስራኤላውያንን እንደ ልዩ ሕዝቡ አድርጎ ሲመርጥ “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ” በማለት ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን አድርጎ ነበር። (ዘጸአት 19:5, 6) እስራኤላውያን የይሖዋ ልዩ ሕዝብ የሆኑት በሕጉ ቃል ኪዳን መሠረት ነበር። ሆኖም የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ሕዝብ እንደሚሆኑ የተሰጣቸው ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት ነው?
8 እስራኤላውያን ታማኝ በነበሩበት ወቅት የይሖዋን ሉዓላዊነት ከመገንዘባቸውም በተጨማሪ እንደ ንጉሣቸው አድርገው ተቀብለውት ነበር። (ኢሳይያስ 33:22) ስለዚህ አንድ መንግሥት ነበሩ። ይሁን እንጂ ቆየት ብሎ እንደተገለጸው ስለ “መንግሥት” የተሰጠው ተስፋ ከዚህ የበለጠም ትርጉም አለው። በተጨማሪም የይሖዋን ሕግ ሲታዘዙ ንጹሕ የሆኑና በዙሪያቸው ካሉት ሕዝቦች የተለዩ ነበሩ። ቅዱስ ሕዝብ ነበሩ። (ዘዳግም 7:5, 6) የካህናት መንግሥት ነበሩን? በእስራኤል ውስጥ የሌዊ ነገድ ለቤተ መቅደስ አገልግሎት ተመድቦ ነበር፤ በዚህ ነገድ ውስጥ ሌዋውያን የክህነት መብት ነበራቸው። የሙሴ ሕግ በሥራ ላይ መዋል ሲጀምር ሌዋውያን ወንዶች ሌዋዊ ባልሆነ የእያንዳንዱ ቤተሰብ በኩር ፈንታ ተወሰዱ።a (ዘጸአት 22:29፤ ዘኁልቁ 3:11–16, 40–51) በዚህ መንገድ በእስራኤል ያለ እያንዳንዱ ቤተሰብ በምሳሌያዊ ሁኔታ በቤተ መቅደስ ውስጥ በሚሰጠው አገልግሎት ተወክሎ ነበር። ይህ ውክልና ሕዝቡ ክህነት ያገኘበት መንገድ ነበር። ያም ሆነ ይህ ይሖዋን በብሔራት ፊት ወክለውታል። እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ የሚፈልግ ማንኛውም የውጭ አገር ሰው ይህን ማድረግ የሚችለው ከእስራኤላውያን ጋር በመተባበር ነበር።—2 ዜና መዋዕል 6:32, 33፤ ኢሳይያስ 60:10
9. ይሖዋ ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ‘እንደ ካህናት ሆኖ እንዲያገለግለው’ ያልፈለገው ለምንድን ነው?
9 ሰሎሞን ከሞተ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች በንጉሥ ኢዮርብዓም በሚመራው በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥትና በንጉሥ ሮብዓም በሚመራው በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ተከፋፈሉ። የንጹሕ አምልኮ ማዕከል የሆነው ቤተ መቅደሱ በይሁዳ የግዛት ክልል ውስጥ ይገኝ ስለነበር ኢዮርብዓም በብሔራዊ ክልሉ ወስጥ የጥጃ ምስል በማቆም ሕገ ወጥ አምልኮ እንዲጀመር አደረገ። ከዚህም በላይ “በኮረብቶቹም ላይ መስገጃዎች ሠራ፣ ከሌዊ ልጆች ካይደሉ ከሕዝብ ሁሉ ካህናትን አደረገ።” (1 ነገሥት 12:31) ንጉሥ አክዓብ ከሌላ አገር ያገባት ሚስቱ ኤልዛቤል በአገሩ ውስጥ የበኣል አምልኮን እንድታስፋፋ በፈቀደላት ወቅት ሰሜናዊው መንግሥት በሐሰት አምልኮ ውስጥ ተዘፈቀ። በመጨረሻም ይሖዋ በዓመፀኛው መንግሥት ላይ የፍርድ መልእክት አስነገረ። በሆሴዕ አማካኝነት እንዲህ አለ፦ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ።” (ሆሴዕ 4:6) ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሦራውያን ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት አጠፉት።
10. ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ታማኝ በነበረበት ወቅት በአሕዛብ መካከል ይሖዋን የወከለው እንዴት ነው?
10 ደቡባዊ የእስራኤል መንግሥት የነበረው ይሁዳስ ምን ሆነ? ይሖዋ በሕዝቅያስ ዘመን በኢሳይያስ በኩል እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ። . . . ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ . . . [ናችሁ።]” (ኢሳይያስ 43:10, 20፤ 44:21) ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ታማኝ በነበረበት ወቅት የይሖዋን ክብር ለሕዝብ ለማወጅና በቤተ መቅደሱ እንዲያመልኩት ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለመሳብ አገልግሏል፤ በተጨማሪም ሕጋዊ መብት ባላቸው የሌዊ ነገድ ካህናት ይገለገል ነበር።
እስራኤል ውስጥ የነበሩ መጻተኞች
11, 12. ከእስራኤል ጋር ሆነው ይሖዋን ያመልኩ የነበሩ የአንዳንድ መጻተኞችን ስም ጥቀስ።
11 በብሔር ደረጃ የተሰጠውን ይህን ምሥክርነት የተቀበሉ መጻተኞች ሚስቱ ሲፓራ ምድያማዊት በነበረችው በሙሴ በኩል በተሰጠው ሕግ አማካኝነት ዝግጅት ተደርጎላቸዋል። እስራኤላውያን ያልሆኑ “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” ከእስራኤል ጋር ከግብፅ ወጥተዋል፤ ሕጉ በሚሰጥበትም ወቅት በቦታው ተገኝተዋል። (ዘጸአት 2:16–22፤ 12:38፤ ዘኁልቁ 11:4) ረዓብና ቤተሰቧ ከኢያሪኮ ጥፋት ከዳኑ በኋላ በአይሁዳውያን ጉባኤ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል። (ኢያሱ 6:23–25) ከጥቂት ጊዜ በኋላ ገባዖናውያን ከእስራኤል ጋር እርቅ ፈጠሩና ከመገናኛው ድንኳን ጋር የተያያዙ ሥራዎች ተሰጧቸው።—ኢያሱ 9:3–27፤ በተጨማሪም በ1 ነገሥት 8:41–43፤ አስቴር 8:17
12 ከጊዜ በኋላ መጻተኞች ከፍተኛ ሥልጣን መያዝ ጀመሩ። እንደ አሞናዊው ጼሌቅ ሁሉ ኬጢያዊው የቤርሳቤህ ባል ኦርዮም ከዳዊት “ኃያላን” መካከል ተቆጥሮ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 11:26, 39, 41፤ 2 ሳሙኤል 11:3, 4) ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ በቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር፤ በንጉሡ ፊትም መቅረብ ይችል ነበር። (ኤርምያስ 38:7–9) እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ከተመለሱ በኋላ እስራኤላውያን ያልሆኑ ናታኒሞች ካህናቱን የመርዳት ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጣቸው። (ዕዝራ 7:24) እነዚህ በርካታ ታማኝ የሆኑ የሌላ አገር ሰዎች ወይም መጻተኞች በዘመናችን ላሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ጥላ ስለሆኑ የእነሱን ሁኔታ ማወቅ እንፈልጋለን።
13, 14. (ሀ) እስራኤል ውስጥ የነበሩ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች ምን መብቶችና ኃላፊነቶች ነበሯቸው? (ለ) ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ታማኝ ሰዎችን እስራኤላውያን እንዴት ይመለከቷቸው ነበር?
13 እነዚህ ሰዎች ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ፣ ከእስራኤላውያን ጋር ከአሕዛብ የተለዩ በሙሴ ሕግ ሥር የነበሩ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ነበሩ። (ዘሌዋውያን 24:22) እንደ እስራኤላውያን ሁሉ መሥዋዕቶችን ያቀርቡ፣ ከሐሰት አምልኮና ከደም ይርቁ ነበር። (ዘሌዋውያን 17:10–14፤ 20:2) የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ሲገነባ ረድተዋል፤ ንጉሥ አሳና ንጉሥ ሕዝቅያስ እውነተኛውን አምልኮ እንደገና ሲያቋቁሙ ተባባሪ ሆነዋል። (1 ዜና መዋዕል 22:2፤ 2 ዜና መዋዕል 15:8–14፤ 30:25) ጴጥሮስ በ33 እዘአ የመንግሥቱን የመጀመሪያ ቁልፍ ሲጠቀም ‘አይሁድም ሆኑ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች’ ቃሉን ሰምተዋል። በዚያን ወቅት ከተጠመቁት መካከል አንዳንዶቹ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀርም። (ሥራ 2:10, 41) ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ለቆርኔሌዎስና ለቤተሰቡ የመንግሥቱን የመጨረሻ ቁልፍ ከመጠቀሙ በፊት ፊልጶስ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጠውን ኢትዮጵያዊ አጠመቀው። (ማቴዎስ 16:19፤ ሥራ 8:26–40፤ 10:30–48) ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች እንደ አሕዛብ ይታዩ እንዳልነበር ግልጽ ነው።
14 ሆኖም ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች እስራኤል ውስጥ የነበራቸው ቦታ የአገሩ ተወላጅ እንደነበሩት እስራኤላውያን ዓይነት አልነበረም። ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች ካህናት ሆነው አያገለግሉም ነበር፤ የበኩር ልጆቻቸውም በሌዊ ክህነት ውስጥ አልተወከሉም።b በተጨማሪም ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች እስራኤል ውስጥ የሚወርሱት መሬት አልነበራቸውም። ሆኖም እስራኤላውያን ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡ ታማኝ ሰዎች አሳቢነት እንዲያሳዩና እነሱን እንደ ወንድሞቻቸው አድርገው እንዲመለከቷቸው ታዘው ነበር።—ዘሌዋውያን 19:33, 34
መንፈሳዊ ሕዝብ
15. ሥጋዊ እስራኤላውያን መሲሑን አለመቀበላቸው ምን ውጤት አስከተለባቸው?
15 ሕጉ የተሰጠው እስራኤላውያን በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ የተለዩ ንጹሕ ሕዝብ እንዲሆኑ ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ሕጉ ለሌላ ዓላማም አገልግሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 3:24) አብዛኞቹ እስራኤላውያን በሕጉ አማካኝነት ወደ ክርስቶስ ለመመራት አለመቻላቸው ያሳዝናል። (ማቴዎስ 23:15፤ ዮሐንስ 1:11) ስለዚህ ይሖዋ አምላክ ያንን ሕዝብ ተወና ‘የአምላክ እስራኤል’ እንዲወለድ አደረገ። ከዚህም በላይ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች በዚህ አዲስ እስራኤል ውስጥ ሙሉ ዜግነት ያላቸው እንዲሆኑ ተጋበዙ። (ገላትያ 3:28፤ 6:16) ይሖዋ በዘጸአት 19:5, 6 ላይ ንጉሣዊ ክህነትን በተመለከተ ቃል የገባው ተስፋ የመጨረሻ አስደናቂ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው በዚህ አዲስ ሕዝብ ላይ ነው። እንዴት?
16, 17. በምድር ላይ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ነገሥታት” እንዲሁም “ካህናት” የሆኑት በምን መንገድ ነው
16 ጴጥሮስ በዘመኑ ለነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲጽፍ ዘጸአት 19:6ን ጠቅሶ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይህ ምን ማለት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ሳሉ ነገሥታት ናቸውን? አይደሉም፣ የንግሥና ሥልጣን የሚያገኙት ገና ወደፊት ነው። (1 ቆሮንቶስ 4:8) ሆኖም ወደፊት ለሚያገኟቸው መንግሥታዊ መብቶች ስለ ተመረጡ ‘ለንግሥና’ ብቁ ናቸው። አሁንም እንኳ ቢሆን በታላቁ ሉዓላዊ ጌታ በይሖዋ አምላክ በተሾመው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ሥር ያለ ብሔር ናቸው። ጳውሎስ “[ይሖዋ] ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” ብሏል።—ቆላስይስ 1:13
17 በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ካህናት ናቸውን? በአንዳንድ መንገዶች ሲታይ ናቸው። በጉባኤ ደረጃ የሚያስፈልገውን ነገር በማቅረብ የማያጠያይቅ ክህነታዊ አገልግሎት ያከናውናሉ። ጴጥሮስ “እናንተ . . . ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” ብሎ ሲናገር ይህን ጉዳይ ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 2:5፤ 1 ቆሮንቶስ 3:16) በዛሬው ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በቡድን ደረጃ መንፈሳዊ ምግብ የሚከፋፈልበት መገናኛ መሥመር ማለትም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሆነው ያገለግላሉ። (ማቴዎስ 24:45–47) እንደ ጥንቷ እስራኤል ሁሉ ይሖዋን ለማምለክ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ይህን ማድረግ የሚችለው ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር በመተባበር ነው።
18. በምድር ላይ ያሉት የቅቡዓን ክርስቲያን ጉባኤ አባላት ካህናት እንደ መሆናቸው መጠን ምን ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው?
18 ከዚህም በላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እስራኤል የነበራትን በአሕዛብ መካከል ስለ ይሖዋ ታላቅነት የመመስከር መብት ተረክበዋል። በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ጴጥሮስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን የንጉሥ ካህናት ብሎ ሲጠራቸው የስብከቱን ሥራ በአእምሮው ይዞ እንደነበር ይጠቁማል። እርግጥ “እናንተ . . . ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ . . . የንጉሥ ካህናት . . . ናችሁ” ብሎ ሲናገር ይሖዋ በዘጸአት 19:6 ላይ የሰጠውን ተስፋ በኢሳይያስ 43:20 ላይ ለእስራኤል ከተናገረው ቃል ጋር በአንድ ጥቅስ ማጣመሩ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:9) ከዚህ ጋር በመስማማት ጳውሎስ የይሖዋን ክብር መናገር ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደሚቀርብ መሥዋዕት ያህል መሆኑን ተናግሯል። “ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ [በኢየሱስ] እናቅርብለት” ሲል ጽፏል።—ዕብራውያን 13:15
ሰማያዊ ፍጻሜ
19. እስራኤል የንጉሥ ካህናት ትሆናለች ተብሎ የተሰጠው ተስፋ የመጨረሻ ታላቅ ፍጻሜ ምንድን ነው?
19 ይሁን እንጂ በመጨረሻ ዘጸአት 19:5, 6 ከዚህ የላቀ ክብራማ ፍጻሜ ይኖረዋል። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያዊ ፍጥረታት ከሞት የተነሣውን ኢየሱስን ሲያወድሱት ይህንን ጥቅስ በሚከተለው መንገድ ተጠቅመውበታል፦ “ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው።” (ራእይ 5:9, 10) ይህ ንጉሣዊ ክህነት በመጨረሻ አፈጻጸሙ ላይ ኢየሱስ እንድንጸልይ ያስተማረን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የመግዛት ሥልጣን ነው። (ሉቃስ 11:2) እስከ መጨረሻው የሚጸኑ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በዚህ መንግሥታዊ ዝግጅት ውስጥ ቦታ ይኖራቸዋል። (ራእይ 20:4, 6) ከረጅም ጊዜ በፊት በሙሴ አማካኝነት የተሰጠው ተስፋ ወደፊት እንዴት ያለ አስደናቂ ተፈጻሚነት ያገኛል!
20. መልስ የሚያስፈልገው ምን ጥያቄ ይቀረናል?
20 ይህ ሁሉ ቅቡዓን በሙሉ አስደናቂ ውርሻቸውን በሚቀበሉበት ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች ወደፊት ከሚኖራቸው ሁኔታ ጋርና አሁን ካሉበት ሁኔታ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ይህ ሐሳብ በዚህ ተከታታይ ትምህርት የመጨረሻ ርዕስ ላይ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የእስራኤል ክህነት በሥራ ላይ ሲውል ሌዋውያን ያልሆኑ የእስራኤል ነገዶች የበኩር ልጆችና የሌዊ ነገድ ወንዶች ተቆጠሩ። የእስራኤላውያን የበኩር ልጆች ቁጥር ከሌዊ ወንዶች ቁጥር በ273 በለጠ። ስለዚህ ለተረፉት ለ273ቱ ለእያንዳንዳቸው አምስት ሰቅል እንደ ቤዛ ሆኖ እንዲከፈል ይሖዋ አዘዘ።
b ሕጉ በ1513 ከዘአበ በሥራ ላይ መዋል ሲጀምር ብዙ ድብልቅ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች ተገኝተው ነበር፤ ይሁን እንጂ ሌዋውያን በእስራኤላውያን የበኩር ልጆች ፈንታ ሲወሰዱ የበኩር ልጆቻቸው አልተቆጠሩም። (አንቀጽ 8ን ተመልከት።) ስለዚህ ሌዋውያን እስራኤላውያን ባልሆኑ የበኩር ልጆች ፈንታ አልተወሰዱም።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የሌሎች በጎች ቦታ ደረጃ በደረጃ በተሻለ መንገድ የተስተዋለው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት እንደ ካህናት ሆኖ እንዲያገለግለው ያልፈለገው ለምንድን ነው?
◻ የይሁዳ መንግሥት ታማኝ በነበረበት ወቅት በብሔራት መካከል ምን ቦታ ነበረው?
◻ ወደ አይሁድ እምነት የተለወጡ ሰዎች በእስራኤል ውስጥ ምን ቦታ ነበራቸው?
◻ የቅቡዓን ጉባኤ የንጉሥ ካህናት ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅቡዓን ክርስቲያኖች የንጉሥ ካህናት እንደመሆናቸው መጠን በምድር ላይ የይሖዋን ክብር ያውጃሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዘጸአት 19:6 የመጨረሻ ፍጻሜ መንግሥቲቱ ናት