ትክክለኞቹን መልእክተኞች ለይቶ ማወቅ
“የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፣ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ።”— ኢሳይያስ 44:25, 26
1. ይሖዋ ትክክለኞቹ መልእክተኞች ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሐሰተኛ መልእክተኞችን የሚያጋልጠውስ እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ እውነተኛ መልእክተኞቹ እነማን እንደሆኑ ለይቶ በማሳወቅ ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። በእነርሱ አማካኝነት የሚናገረው መልእክት እንዲፈጸም በማድረግ እውነተኛ መልእክተኞቹ መሆናቸውን ለይቶ ያሳውቃል። በተጨማሪም ይሖዋ ሐሰተኛ መልእክተኞችን በማጋለጥ ረገድ አቻ የለውም። ግን የሚያጋልጣቸው እንዴት ነው? መልክታቸውንና ትንቢታቸውን ሁሉ ያከሽፋል። በዚህ መንገድ ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙና ከልባቸው አመንጭተው የሐሰት ትንቢት፤ አዎን፣ የቂልነት ሥጋዊ አስተሳሰብ ውጤት የሆነ ትንቢት የሚናገሩ ነቢያት መሆናቸው እንዲጋለጥ ያደርጋል!
2. በእስራኤል ዘመን በመልእክተኞች መካከል ምን ትልቅ ልዩነት ተፈጥሮ ነበር?
2 ኢሳይያስና ሕዝቅኤል የይሖዋ አምላክ መልእክተኞች እንደሆኑ ይናገሩ ነበር። ግን ከአምላክ የተላኩ ነቢያት ነበሩ? እስቲ እንመልከት። ኢሳይያስ ከ778 ከዘአበ እስከ 732 ከዘአበ ገደማ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ሕዝቅኤል ደግሞ በ617 ከዘአበ በባቢሎን በግዞት ነበር። በዚያ ለነበሩ አይሁዳውያን ወንድሞቹ ትንቢት ተናግሯል። ሁለቱም ነቢያት ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ በድፍረት ተንብየው ነበር። ሌሎች ነቢያት ግን አምላክ ይህ ሲሆን ዝም ብሎ አያይም ብለው ነበር። ታዲያ እውነተኛ መልእክተኛ ሆነው የተገኙት እነማን ናቸው?
ይሖዋ ሐሰተኛ ነቢያትን ያጋልጣል
3, 4. (ሀ) በባቢሎን ለነበሩት እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ምን ሁለት መልእክቶች ተነግሯቸው ነበር? ይሖዋ አንድን የሐሰት መልእክተኛ ያጋለጠው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ሐሰተኛ ነቢያት ምን እንደሚደርስባቸው ተናግሯል?
3 ሕዝቅኤል በባቢሎን በነበረበት ጊዜ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይፈጸም የነበረውን ሁኔታ በራእይ ተመልክቶ ነበር። በምሥራቃዊ በር መግቢያ 25 ሰዎች ነበሩ። ከእነርሱም መካከል ያእዛንያና ፈላጥያ የሚባሉ ሁለት የሕዝብ አለቆች ይገኙ ነበር። እነዚህን ሰዎች ይሖዋ እንዴት ተመለከታቸው? ሕዝቅኤል 11:2, 3 እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “የሰው ልጅ ሆይ፣ እነዚህ ክፋትን የሚያስቡ በዚህችም ከተማ ክፉን ምክር የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። እነርሱም:- በውኑ ቤቶችን የምንሠራበት ዘመን የቀረበ አይደለምን? . . . ብለዋል።” እነዚህ ትዕቢተኛ የሰላም መልእክተኞች ‘ኢየሩሳሌም ምንም ክፉ ነገር አይደርስባትም። በቅርቡ ተጨማሪ ቤቶችን እንሠራባታለን!’ ይሉ ነበር። በመሆኑም ሕዝቅኤል እነዚህ ውሸተኛ መልእክተኞች የሚናገሩትን የሚያስተባብል ትንቢት እንዲናገር አምላክ አዘዘው። ሕዝቅኤል በምዕራፍ 11 ቁጥር 13 ላይ ከሁለቱ በአንዱ ላይ ምን እንደደረሰ ይነግረናል:- “ትንቢትም በተናገርሁ ጊዜ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ።” ይህ ነገር በፈላጥያ ላይ የደረሰው እርሱ ከሁሉ ይበልጥ ስሙ የገነነና ተደማጭነት የነበረው የሕዝብ አለቃ እንዲሁም ቀንደኛ ጣዖት አምላኪ ስለነበረ ሳይሆን አይቀርም። በድንገት መሞቱ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር!
4 ይሖዋ በፈላጥያ ላይ የወሰደው እርምጃ ሌሎቹ የሐሰት ነቢያት በአምላክ ስም ውሸት እንዳይናገሩ አልገታቸውም። እነዚህ አታላዮች ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረኑ ትንቢቶችን በመናገር በዕብደት አካሄዳቸው ገፉበት። በመሆኑም ይሖዋ አምላክ ለሕዝቅኤል “ምንም ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው!” ሲል ነግሮታል። ‘ሰላም ሳይኖር ለኢየሩሳሌም የሰላም ራእይ’ የሚያዩላት ዓመፀኛ ነቢያት ልክ እንደ ፈላጥያ በሕይወት ‘አይኖሩም።’— ሕዝቅኤል 13:3, 15, 16
5, 6. ብዙ የሐሰት መልእክተኞች ቢኖሩም ኢሳይያስ እውነተኛ ነቢይ መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?
5 ኢሳይያስ ስለ ኢየሩሳሌም የተናገራቸው መለኮታዊ መልእክቶች በሙሉ ተፈጽመዋል። ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ በበጋ ወራት ከተማዋን በመደምሰስ አይሁዳውያን ቀሪዎችን ምርኮኛ አድርገው ወደ ባቢሎን ወሰዱ። (2 ዜና መዋዕል 36:15-21፤ ሕዝቅኤል 22:28፤ ዳንኤል 9:2) ይህ መቅሰፍት ሐሰተኛ ነቢያቱ በአምላክ ሕዝብ ላይ የከንቱ ልፈፋ ውርጅብኝ ከማዝነብ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋልን? በፍጹም፤ እነዚያ ሐሰተኛ ነቢያት በድርጊታቸው ገፍተውበታል!
6 እስራኤላውያን ምርኮኞች ይህ እንዳይበቃቸው ደግሞ በባቢሎን ትዕቢተኛ ምዋርተኞች፣ ጠንቋዮችና ኮከብ ቆጣሪዎች የሚናገሩትን ትንቢት ለመስማት ተገድደው ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህ ሐሰተኛ መልእክተኞች በሙሉ ተገላቢጦሽ የሆነውን ነገር የሚናገሩ ሞኞች መሆናቸውን አረጋግጧል። በጊዜውም እንደ ኢሳይያስ ሁሉ ሕዝቅኤልም እውነተኛ መልእክተኛው መሆኑን አሳይቷል። ይሖዋ በእነርሱ በኩል የተናገረው ነገር በሙሉ ልክ ቃል በገባው መሠረት እንዲፈጸም አድርጓል:- “የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፣ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፣ ጥበበኞቹንም ወደኋላ እመልሳለሁ። እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤ የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፣ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ።”— ኢሳይያስ 44:25, 26
ስለ ባቢሎንና ስለ ኢየሩሳሌም የተነገረ አስገራሚ መልእክት
7, 8. ኢሳይያስ በመንፈስ ተነድቶ ስለ ባቢሎን ምን ተናግሯል? ይህስ ምን ማለት ነው?
7 ይሁዳና ኢየሩሳሌም ለ70 ዓመታት ፍጹም ባድማና ኗሪ አልባ ሆነው መቆየት ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ በኢሳይያስና በሕዝቅኤል አማካኝነት ከተማዋ እንደገና እንደምትሠራና ምድሪቱም አስቀድሞ በተነገረለት ትክክለኛ ጊዜ የሰዎች መኖሪያ እንደምትሆን ተናግሯል! ይህ በጣም አስገራሚ ትንቢት ነበር። ለምን? ባቢሎን እስረኞቿን ከእጅዋ እንደማታስወጣ ይነገርላት ስለነበር ነው። (ኢሳይያስ 14:4, 15-17) ታዲያ እነዚህን ግዞተኞች ነፃ ሊያወጣቸው የሚችለው ማን ነው? ታላላቅ ቅጥሮች ያሏትንና በወንዝ የታጠረችውን ኃያልዋን ከተማ ባቢሎንን ማን ሊጥላት ይችላል? ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ ይችላል! ይህንኑ እንደሚያደርግ ተናግሯል:- “ቀላዩንም [ለከተማይቱ እንደ መከላከያ ሆኖ የሚያገለግለውን ውኃ ማለት ነው] ደረቅ ሁን፣ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፤ ቂሮስንም:- እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን:- ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።”— ኢሳይያስ 44:25, 27, 28
8 እስቲ ገምቱት! ኤፍራጥስ የሰው ኃይል በቀላሉ የሚደፍረው ወንዝ አልነበረም። በይሖዋ ፊት ግን በፍም ላይ ጠብ እንዳለ የውኃ ጠብታ ትሽ! ብሎ ወዲያው እንደሚጠፋ ያህል ነው። ባቢሎን ትወድቃለች። ፋርሳዊው ቂሮስ ከመወለዱ ከ150 ዓመት በፊት ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት ይህ ንጉሥ ባቢሎንን ድል አድርጎ በመያዝ አይሁዳውያን ግዞተኞችን ነፃ እንደሚያወጣና ወደ አገራቸው ተመልሰው ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን እንዲገነቡ ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ተንብዮ ነበር።
9. ይሖዋ ባቢሎንን ለመቅጣት የወከለው ማንን ነው?
9 ይህን ትንቢት በኢሳይያስ 45:1-3 ላይ እናገኘዋለን:- “እግዚአብሔር ለቀባሁት፣ አሕዛብንም በፊቱ አስገዛ ዘንድ . . . በሮቹም እንዳይዘጉ መዝጊያዎቹን በፊቱ እከፍት ዘንድ፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት ለቂሮስ እንዲህ ይላል:- በፊትህ እሄዳለሁ ተራሮችንም ትክክል አደርጋለሁ፣ የናሱንም ደጆች እሰብራለሁ የብረቱንም መወርወሪያዎች እቆርጣለሁ፤ በስምህም የምጠራህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ታውቅ ዘንድ በጨለማ የነበረችውን መዝገብ በስውርም የተደበቀችውን ሀብት እሰጥሃለሁ።”
10. ቂሮስ ‘የተቀባው’ በምን መንገድ ነው? ከመወለዱ ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት ይሖዋ ሊያነጋግረው የቻለው እንዴት ነበር?
10 ይሖዋ ቂሮስን በሕይወት እንዳለ አድርጎ እንደሚያነጋግረው ልብ በሉ። ይህም ‘አምላክ የሌለውን እንዳለ አድርጎ ይጠራል’ ከሚለው የጳውሎስ ቃል ጋር ይስማማል። (ሮሜ 4:17) በተጨማሪም አምላክ፣ ቂሮስ ‘በእርሱ የተቀባ’ እንደሆነ ተናግሯል። እንዲህ ያለው ለምን ነበር? በቂሮስ ራስ ላይ ቅዱስ ቅባት ያፈሰሰበት የይሖዋ ሊቀ ካህናት የለም። ይህ በትንቢታዊ ሁኔታ መቀባቱን የሚያሳይ እንደሆነ እሙን ነው። አንድ ልዩ ሹመት ማግኘቱን ያመለክታል። በመሆኑም አምላክ ወደፊት ለቂሮስ የሚሰጠውን ሹመት እንደ መቀባት አድርጎ ሊገልጸው ችሏል።— ከ1 ነገሥት 19:15-17፤ 2 ነገሥት 8:13 ጋር አወዳድር።
አምላክ የመልእክተኞቹን ቃል ይፈጽማል
11. የባቢሎን ነዋሪዎች ተማምነውና ተረጋግተው የተቀመጡት ለምን ነበር?
11 ቂሮስ በባቢሎን ላይ በዘመተ ጊዜ የባቢሎን ነዋሪዎች ተማምነውና አለምንም ሥጋት ተቀምጠው ነበር። ከተማቸው ዙሪያዋን በኤፍራጥስ ወንዝ አማካኝነት በተሠራ ስፋትና ጥልቀት ባለው በውኃ የተሞላ ጉድጓድ የተከበበች ነበረች። ከተማይቱን መሐል ለመሐል አቋርጦ ከሚያልፈው ወንዝ በስተ ምሥራቅ የተገነባ መተላለፊያ ነበረ። ናቡከደነፆር ይህን መተላለፊያ ከከተማይቱ ለመለየት ሲል ራሱ እንደተናገረው “ልክ እንደ ተራራ ሊነቃነቅ [የማይችል] . . . ተራራ የሚያህል ከፍታ ያለው ቅጥር” ሠርቶ ነበር።a ይህ ቅጥር ግዙፍ የሆኑ የነሐስ በሮች ነበሩት። በበሮቹ ለመግባት የፈለገ ሰው ከወንዙ ዳርቻ ላይ ያለውን መወጣጫ መውጣት ይኖርበታል። በባቢሎን ግዞተኛ ሆነው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ነጻ ልንወጣ እንችላለን የሚል ተስፋ ሊኖራቸው አለመቻሉ ምንም አያስደንቅም!
12, 13. ባቢሎን በቂሮስ እጅ በወደቀች ጊዜ ይሖዋ በመልእክተኛው በኢሳይያስ በኩል የተናገረው ቃል የተፈጸመው እንዴት ነው?
12 ይሁን እንጂ በይሖዋ ላይ እምነት የነበራቸው አይሁዳውያን ግዞተኞች ተስፋ አልቆረጡም! ብሩሕ ተስፋ ነበራቸው። አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት ነፃ እንደሚያወጣቸው ቃል ገብቶ ነበር። ታዲያ አምላክ የገባውን ቃል የፈጸመው እንዴት ነው? ቂሮስ ወታደሮቹ ከባቢሎን በስተ ሰሜን ብዙ ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብለው የኤፍራጥስ ወንዝ አቅጣጫውን ለውጦ እንዲፈስ እንዲያደርጉ አዘዘ። ዋነኛው የከተማይቱ መከላከያ በአንፃራዊ ሁኔታ ውኃው ተሟጥጦ ያለቀበት ጐድጓዳ ሥፍራ ሆነ። በዚያ ወሳኝ የሆነ ምሽት በመጠጥ ሲራጩ የነበሩት ባቢሎናውያን በግዴለሽነት በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ የነበሩትን ባለ ሁለት ተካፋች በሮች ሳይዘጉ ቀሩ። ይሖዋ ቃል በቃል የነሐስ በሮቹ እንዲሰባበሩ ወይም የበሮቹ መወርወሪያ እንዲቆራረጥ አላደረገም፤ ይሁን እንጂ በሚያስገርም ሁኔታ በሮቹ ክፍት ሆነው እንዲያድሩ ማድረጉ ተመሳሳይ የሆነ ውጤት ነበረው። የባቢሎን ቅጥሮች ምንም የፈየዱት ነገር አልነበረም! የቂሮስ ጭፍሮች ለቅጥሩ መወጣጫ መሥራት ሳያስፈልጋቸው ዘልቀው ገቡ። ይሖዋ ከቂሮስ ፊት እየሄደ ‘ተራራውን’ ማለትም እንቅፋቱን ሁሉ አስወገደለት። ኢሳይያስ የአምላክ እውነተኛ መልእክተኛ መሆኑ ተረጋገጠ።
13 ቂሮስ ከተማይቱን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ካደረገ በኋላ የከተማዋን ውድ ንብረቶች በሙሉ በጨለማ ቦታ የተደበቁትን እንኳ ሳይቀር በእጁ አስገብቷል። ይሖዋ አምላክ ለቂሮስ እንዲህ ያደረገለት ለምንድን ነው? ‘በስሙ የጠራው’ አምላክ ይሖዋ የእውነተኛ ትንቢት ምንጭና የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ መሆኑን ያውቅ ዘንድ ነው። ሕዝቡን እስራኤልን ነፃ እንዲያወጣ ሥልጣን ላይ ያወጣው አምላክ እንደሆነ እንዲያውቅ ነበር።
14, 15. ቂሮስ በባቢሎን ላይ ድል የተቀዳጀው በይሖዋ እርዳታ እንደሆነ እንዴት እናውቃለን?
14 ይሖዋ ለቂሮስ የተናገረውን ቃል አዳምጡ:- “ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ መረጥሁትም ስለ እስራኤል ብዬ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ በቁልምጫ ስምህ ጠራሁህ፣ አንተ ግን አላወቅኸኝም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፣ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም ሌላ ማንም የለም። ብርሃንን ሠራሁ፣ ጨለማውንም ፈጠርሁ። ደኅንነትን እሠራለሁ [በግዞት ለነበሩት ሕዝቡ ማለት ነው]፣ ክፋትንም [በባቢሎን ላይ] እፈጥራለሁ፣ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።”— ኢሳይያስ 45:4-7
15 በዚያች ክፉ ከተማ ላይ ሊያደርግ የወደደውን እንዲፈጽምና ሕዝቦቹን ነፃ እንዲያወጣ ያበረታው ይሖዋ በመሆኑ ቂሮስ በባቢሎን ላይ ላገኘው ድል ሊመሰገን የሚገባው እርሱ ነው። አምላክ በዚህ መንገድ የራሱ ሰማያት የጽድቅ ኃይሎችን እንዲያዘንቡ አድርጓል። የራሱ ምድርም እንድትከፈትና ለግዞተኛ ሕዝቦቹ ጽድቅና ደህንነትን እንድታበቅል አዟል። የይሖዋ ምሳሌያዊ ሰማያትና ምድርም ይህንን ትእዛዝ ፈጽመዋል። (ኢሳይያስ 45:8) ኢሳይያስ ከሞተ ከአንድ መቶ ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ እውነተኛ የይሖዋ መልእክተኛ መሆኑ ተረጋግጧል!
ለጽዮን የተነገረው የመልእክተኛው ምስራች!
16. ባቢሎን ተሸንፋ ከወደቀች በኋላ በፈራረሰችው የኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ምን ምስራች ሊታወጅ ችሎ ነበር?
16 ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አላበቃም። ኢሳይያስ 52:7 ለኢየሩሳሌም ስለተነገረ ምስራች ይገልጻል። እንዲህ ይላል:- “የምስራች የሚናገር፣ ሰላምንም የሚያወራ፣ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፣ መድኃኒትንም የሚያወራ፣ ጽዮንንም:- አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው።” ከተራራ ወደ ኢየሩሳሌም የሚመጣ መልእክተኛ መመልከት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ እስቲ አስቡት! አንድ ዜና ይዞ መሆን አለበት። ምን ዜና ይሆን? ለጽዮን የተነገረ አስደሳች ዜና ነው። የሰላም ዜና፣ አዎን የአምላክን በጎ ፈቃድ የሚያበስር ዜና ነው። ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ ዳግመኛ ሊሠሩ እንደሆነ የሚገልጽ ዜና ነው! መልእክተኛውም በድል አድራጊነት ስሜት “አምላክሽ ነግሦአል” ይላል።
17, 18. ቂሮስ በባቢሎን ላይ የተቀዳጀው ድል የይሖዋን ስም የነካው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ በጥላነት ያገለግል የነበረውንና በዳዊት የንግሥና መሥመር ያሉ ነገሥታት ይቀመጡበት የነበረው ዙፋኑን ባቢሎናውያን በ607 ከዘአበ እንዲገለብጡ ሲፈቅድላቸው ከዚያ በኋላ እርሱ ንጉሥ እንዳልሆነ ተደርጎ ታይቶ ሊሆን ይችላል። በእርሱ ፋንታ የባቢሎን ዋነኛ አምላክ የሆነው ማርዱክ የነገሠ መስሎ ነበር። ሆኖም የጽዮን አምላክ ባቢሎን እንድትገለበጥ ባደረገ ጊዜ አጽናፈ ዓለማዊ ልዕልናውንና ከሁሉ የበላይ የሆነው ንጉሥ እርሱ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ይህን እውነታ በተጨባጭ ለማረጋገጥ “የታላቁ ንጉሥ ከተማ” የሆነችው ኢየሩሳሌም ከነቤተ መቅደስዋ ዳግመኛ መገንባት ነበረባት። (ማቴዎስ 5:35) ይህን የምስራች ይዞ የመጣው መልእክተኛ እግሮች አቧራ የለበሱ፣ የቆሸሹና በእንቅፋት የቆሳሰሉ ቢሆኑም ጽዮንን በሚወዱ ሰዎችና በጽዮን አምላክ ዓይኖች በጣም ያማሩ ሆነው ይታያሉ!
18 የባቢሎን መውደቅ ከትንቢት አፈጻጸም አንጻር ሲታይ የአምላክ መንግሥት እንደተቋቋመ የሚቆጠር ሲሆን ምስራቹን ይዞ የመጣውም ሰው ይህንኑ እውነት የሚያውጅ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ከዚህም በላይ ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረለት ይህ የጥንት መልእክት አድራሽ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ምስራች ለሚያበስረው መልእክተኛ ጥላ ሆኗል። ምስራቹ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው መልእክቱ ልብ የሚነካ በመሆኑና የመልእክቱ ጭብጥ ለሁሉም የእምነት ሰዎች አስገራሚ ለውጥ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት በመሆኑ ነው።
19. ይሖዋ በሕዝቅኤል አማካኝነት ስለ እስራኤል ምድር ምን መልእክት አስተላልፏል?
19 ሕዝቅኤልም በጣም አስደሳች የሆኑ የተሐድሶ ትንቢቶች ተናግሯል። እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- . . . በከተሞች ሰዎችን አኖራለሁ፣ ባድማዎቹ ስፍራዎች ይሠራሉ። ሰዎችም:- ባድማ የነበረች ይህች ምድር እንደ ዔድን ገነት ሆናለች ይላሉ።”— ሕዝቅኤል 36:33, 35
20. በኢሳይያስ በኩል ስለ ኢየሩሳሌም የተነገረው አስደሳች ትንቢታዊ ማበረታቻ ምንድን ነው?
20 የአምላክ ሕዝቦች በባቢሎን በግዞት ሆነው ስለ ጽዮን ያለቅሱ ነበር። (መዝሙር 137:1) አሁን ግን ሊደሰቱ ይችላሉ። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል አበረታቷቸዋል:- “እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፣ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፣ በአንድነትም ዘምሩ። እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፣ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ።”— ኢሳይያስ 52:9, 10
21. ከባቢሎን ሽንፈት በኋላ ኢሳይያስ 52:9, 10 ላይ የሚገኙት ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?
21 አዎን፣ የይሖዋ ምርጥ ሕዝቦች የሚደሰቱበት ትልቅ ምክንያት ነበራቸው። ባድማ ሆነው ወደ ቆዩት ቦታዎቻቸው ተመልሰው እንደ ዔድን ገነት ሊያደርጓቸው ነው። ይሖዋ ‘የተቀደሰውን ክንዱን ገልጦላቸዋል።’ ሕዝቦቹን ወደ ውድ ምድራቸው ለመመለስ እጅጌውን የጠቀለለ ያክል ነበር። ይህ በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሌለው ተራ ነገር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በዚያን ጊዜ ይኖሩ የነበሩት ሕዝቦች በሙሉ ‘የተገለጠው ክንዱ’ አንድን ብሔር አስገራሚ በሆነ መንገድ ለማዳን በሰው ልጅ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ሲገባ አይተዋል። ኢሳይያስና ሕዝቅኤል የይሖዋ እውነተኛ መልእክተኞች እንደሆኑ የማያጠያይቅ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል። በመላው ምድር ላይ ከጽዮን አምላክ በስተቀር እውነተኛና ሕያው አምላክ አለመኖሩን ሊጠራጠር የሚችል አልነበረም። ኢሳይያስ 35:2 ላይ “የእግዚአብሔርንም ክብር የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ” የሚል ቃል እናነባለን። የይሖዋን አምላክነት የሚያረጋግጠውን ይህን ማስረጃ የተቀበሉ ሁሉ እርሱን ለማምለክ መርጠዋል።
22. (ሀ) ዛሬ ስለ ምን ነገር አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን? (ለ) ይሖዋ በተለይ ሐሰተኛ መልእክተኞችን በማጋለጡ አመስጋኞች መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
22 ይሖዋ እውነተኛ መልእክተኞቹ ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርግ በመሆኑ ምንኛ ደስ ሊለን ይገባል! በእርግጥም እርሱ ‘የባሪያውን ቃል የሚያጸና እና የመልእክተኞቹንም ምክር የሚፈጽም’ አምላክ ነው። (ኢሳይያስ 44:26) ለኢሳይያስና ሕዝቅኤል የሰጣቸው የተኃድሶ ትንቢቶች ለአገልጋዮቹ ያሳየውን ታላቅ ፍቅር፣ ይገባናል የማንለው ደግነት እና ምሕረት ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። በእርግጥም ይሖዋን ለዚህ ነገር ልናወድሰው ይገባል! ዛሬም እኛ በተለይ ሐሰተኛ መልእክተኞችን የሚያጋልጥ በመሆኑ ደስ ሊለን ይገባል። ምክንያቱም ዛሬ በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኛ መልእክተኞች አሉ። የሚናገሯቸው መልእክቶች ከተገለጠው የይሖዋ ዓላማ ጋር አይጣጣምም። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ሐሰተኛ መልእክተኞች ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኢራ ሞሪስ ፕራይስ የተዘጋጀው ዘ ሞንይሜንትስ ኤንድ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ 1925
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ይሖዋ እውነተኛ መልእክተኞቹ ተለይተው እንዲታወቁ የሚያደርገው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል እንደተናገረው ባቢሎንን ድል እንዲያደርግ የወከለው ማንን ነበር?
◻ ባቢሎንን ስለሚገጥማት ሽንፈት የሚገልጹት የኢሳይያስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?
◻ የባቢሎን መሸነፍ በይሖዋ ስም ላይ ምን በጎ ውጤት ነበረው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባቢሎን በሕዝቅኤል ዘመን በነበሩት ብሔራት ዘንድ የማትደፈር መስላ ትታይ ነበር