ወደ አምላክ ቅረብ
“ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም”
ትዝታ በረከት ሊሆን ይችላል። ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ያሳለፍናቸውን አስደሳች ጊዜያት መለስ ብለን ስናስታውስ ልባችን በደስታ ይሞላል። ይሁንና አንዳንድ ትዝታዎች እንደ እርግማን ሊሆኑብን ይችላሉ። በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህ አሳዛኝ ክስተቶች ያስከተሉት መጥፎ ትዝታ እያሠቃየህ ነው? ከሆነ ‘ይህ መጥፎ ትዝታ ከአእምሮዬ የሚወገድበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ነቢዩ ኢሳይያስ የጻፈው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ እጅግ የሚያጽናና መልስ ይሰጠናል።—ኢሳይያስ 65:17ን አንብብ።
ይሖዋ፣ መጥፎ ትዝታ ያስከተሉብንን ነገሮች ከሥረ መሠረታቸው የማስወገድ ዓላማ አለው። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በመከራ የተሞላውን ይህን ክፉ ዓለም አጥፍቶ በምትኩ ከሁሉ የተሻለ ሥርዓት በማምጣት ነው። ይሖዋ “እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ” በማለት በኢሳይያስ በኩል ቃል ገብቷል። ይሖዋ የገባው ይህ ቃል ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታችን ተስፋችን እንዲለመልም ያደርጋል።
አዲስ ሰማያት የተባሉት ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ለመረዳት የሚያስችሉን ሁለት ፍንጮች ይሰጠናል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አዲስ ሰማያት የጻፉት ሁለት ሌሎች ሰዎች እነዚህን ቃላት የተጠቀሙባቸው በምድር ላይ የሚደረጉ ሥር ነቀል ለውጦችን ለማመልከት ነው። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-4) ሁለተኛ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰማያት” የሚለው ቃል አገዛዝን ወይም መንግሥትን ሊያመለክት ይችላል። (ኢሳይያስ 14:4, 12፤ ዳንኤል 4:25, 26) ስለዚህ አዲስ ሰማያት የሚለው አገላለጽ በምድር ላይ ጽድቅ እንዲሰፍን የሚያደርግን አዲስ መንግሥት ያመለክታል። ይህን ሊያደርግ የሚችለው አገዛዝ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ብቻ ነው፤ ኢየሱስ እንድንጸልይ ያስተማረን ስለዚህ መንግሥት ነበር። ይህ መንግሥት፣ ጽድቅን የሚያሰፍነው የአምላክ ፈቃድ በምድር ዙሪያ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:9, 10
አዲስ ምድር የተባለውስ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚረዱንን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምድር” የሚለው ቃል አንዳንድ ጊዜ የሚሠራበት ግዑዙን መሬት ሳይሆን ሰዎችን ለማመልከት ነው። (መዝሙር 96:1) ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ አገዛዝ ሥር በመላው ምድር የሚገኙ ታማኝ ሰዎች ጽድቅን የሚማሩበት ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 26:9) በመሆኑም አዲስ ምድር የሚለው አገላለጽ ለአምላክ የሚገዙና የጽድቅ መሥፈርቶቹን የሚጠብቁ ሰዎችን ያቀፈውን ኅብረተሰብ ያመለክታል።
ታዲያ ይሖዋ መጥፎ ትዝታ ያስከተሉብንን ነገሮች ከሥረ መሠረታቸው የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ? ይሖዋ በቅርቡ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም በማምጣት ስለ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር የገባውን ቃል ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል።a በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ፣ መጥፎ ትዝታ እንዲኖረን የሚያደርጉ ይኸውም አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ሥቃይ የሚያስከትሉ ነገሮች ያለፈ ታሪክ ይሆናሉ። ታማኝ የሰው ልጆች ሕይወትን ሙሉ በሙሉ ያጣጥማሉ፤ እንዲሁም ስለ እያንዳንዱ ቀን አስደሳች ትዝታ ይኖራቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ እየደረሰብን ስላለው አእምሯዊና ስሜታዊ ሥቃይስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም” በማለት በኢሳይያስ በኩል ቃል ገብቷል። በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ስላጋጠመን ማንኛውም ሥቃይ ያለን ትዝታ ቀስ በቀስ እየጠፋ ይሄዳል። ይህ ተስፋ የሚያስደስት አይደለም? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይህን የመሰለ አስደሳች ጊዜ እንደሚያመጣ ቃል ወደገባው አምላክ ይበልጥ መቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ለማወቅ ለምን አትሞክርም?
በመጋቢት ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
◼ ከኢሳይያስ 63-66 እስከ ኤርምያስ 1-16
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ አምላክ መንግሥትና በቅርቡ ስለሚያከናውናቸው ነገሮች የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3, 8 እና 9 ተመልከት።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ፣ መጥፎ ትዝታ ያስከተሉብንን ነገሮች ከሥረ መሠረታቸው የማስወገድ ዓላማ አለው