ለሺህ ዓመትና ከዚያም በኋላ የሚዘልቅ ሰላም!
“ይህም አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር መሆን ይችል ዘንድ ነው።”—1 ቆሮ. 15:28
1. “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ወደፊት ምን አስደሳች ተስፋ ይጠብቀዋል?
ፍትሐዊና ሩኅሩኅ በሆነ ገዥ የሚመራ አንድ ኃያል መንግሥት በአንድ ሺህ ዓመት ውስጥ ለተገዥዎቹ እንዴት ያሉ በረከቶችን ሊያመጣ እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ? ይህ ክፉ ሥርዓት ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ወደ ፍጻሜው ሲመጣ በሕይወት የሚተርፈው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንዲህ ያለ አስደናቂ ተስፋ ይጠብቀዋል።—ራእይ 7:9, 14
2. ያለፈው 6,000 ዓመት የሰው ልጆች ታሪክ ምን ያሳያል?
2 ያለፈው 6,000 ዓመት የሰው ልጆች ታሪክ እንደሚያሳየው ሰዎች በራሳቸው መንገድ መሄዳቸውና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር መሞከራቸው ከፍተኛ ሥቃይና መከራ አስከትሎባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከረጅም ጊዜ በፊት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።” (መክ. 8:9) ታዲያ በዛሬው ጊዜ የሚታየው ምንድን ነው? ከጦርነቶችና ከሕዝባዊ ዓመፆች በተጨማሪ ድህነት፣ በሽታ፣ የአካባቢ መበከል፣ የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ችግሮች ከፍተኛ የሆነ ቀውስ እያስከተሉ እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ሰዎች ይህን የቸልተኝነት ዝንባሌያቸውን ካላስተካከሉ ውጤቱ የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
3. የሺህ ዓመቱ ግዛት ምን ያመጣል?
3 በመሲሐዊው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስና ከእሱ ጋር በሚገዙት 144,000ዎቹ የሚመራው የአምላክ መንግሥት፣ በሰው ልጆችና መኖሪያቸው በሆነችው በምድር ላይ የደረሰውን ጉዳት በሙሉ ደረጃ በደረጃ ያስተካክላል። የሺህ ዓመቱ ግዛት ይሖዋ ቃል የገባው የሚከተለው አስደሳች ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደርጋል፦ “እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም።” (ኢሳ. 65:17) ይሁንና ወደፊት የምንጠብቃቸው ገና ያልታዩ አስደናቂ ክንውኖች የትኞቹ ናቸው? እስቲ በአምላክ ትንቢታዊ ቃል በመታገዝ ገና ‘ያልታዩት’ ነገሮች ምን እንደሚመስሉ ለማወቅ እንሞክር።—2 ቆሮ. 4:18
‘ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ’
4. በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የሚኖሩት በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ነው?
4 ከቤተሰቡ ጋር ተረጋግቶ በሰላም የሚኖርበት የራሱ የሆነ ቤት እንዲኖረው የማይፈልግ ማን አለ? በዛሬው ጊዜ ግን ሰዎች በመኖሪያ ቤት እጦት ይሠቃያሉ። ብዙ ሰዎች በተጨናነቁ ከተሞች ውስጥ ታፍገው ይኖራሉ። ሌሎች ደግሞ በተጎሳቆሉ ከተሞችና ሰፈሮች ውስጥ በማይመች ሁኔታ መኖር ግድ ሆኖባቸዋል። በመሆኑም የራስ የሆነ ቤት ማግኘት ለብዙዎች የሕልም እንጀራ ነው።
5, 6. (ሀ) ኢሳይያስ 65:21 እና ሚክያስ 4:4 ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው? (ለ) ይህን በረከት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
5 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ ቤት የማግኘት ፍላጎቱ ይሟላለታል፤ ምክንያቱም “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ” የሚል ትንቢት በኢሳይያስ አማካኝነት ተነግሯል። (ኢሳ. 65:21) ይሁን እንጂ ወደፊት የምንጠብቀው ተስፋ የራሳችን የሆነ ቤት ማግኘት ብቻ አይደለም። ምክንያቱም ዛሬም ቢሆን የራሳቸው የሆነ ቤት ያላቸው ሰዎች አሉ፤ እንዲያውም አንዳንዶች በጣም ትላልቅ በሆኑ ቤቶችና ሰፊ ጋሻ መሬት ላይ በተሠሩ ቪላዎች ውስጥ ይኖራሉ። ያም ቢሆን እነዚህ ሰዎች ምንጊዜም የሚኖሩት በስጋት ነው፤ አንዳንዶች በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ቤታችንን ልናጣው እንችላለን ብለው ይጨነቃሉ። ሌሎች ደግሞ በዘራፊዎች ጥቃት ይሰነዘርብናል በሚል ስጋት እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ። በአምላክ መንግሥት ሥር ግን ሁኔታዎች ምንኛ የተለዩ ይሆናሉ! ነቢዩ ሚክያስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም።”—ሚክ. 4:4
6 ይህን ግሩም ተስፋ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? ሁላችንም መኖሪያ ቤት እንደሚያስፈልገን እሙን ነው። ያም ሆኖ የምናልመውን ቤት አሁኑኑ ለማግኘት ከመፍጨርጨር፣ ምናልባትም ዕዳ ውስጥ ከመዘፈቅ ይልቅ ይሖዋ በሰጠን ተስፋ ላይ ትኩረት ማድረግ የጥበብ አካሄድ አይሆንም? ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ስለ ራሱ የተናገረውን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፦ “ቀበሮዎች ጉድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም መስፈሪያ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ራሱን እንኳ የሚያሳርፍበት ቦታ የለውም።” (ሉቃስ 9:58) ኢየሱስ ከማንኛውም ሰው የተሻለ ቤት የማግኘት አቅሙም ሆነ ችሎታው ነበረው። ታዲያ እንዲህ ያላደረገው ለምንድን ነው? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ የመንግሥቱን ጉዳዮች እንዳያስቀድም በሚያደርጉት ነገሮች ትኩረቱ እንዲሳብ ወይም እንዲጠላለፍ አልፈለገም። እኛስ የእሱን ምሳሌ በመከተል አጥርቶ የሚያይ ዓይን እንዲኖረን ማድረግ ማለትም በቁሳዊ ነገሮች ከመጠላለፍና በዚህ ምክንያት ጭንቀት ውስጥ ከመግባት መቆጠብ እንችላለን?—ማቴ. 6:33, 34
“ተኵላና የበግ ጠቦት በአንድነት ይበላሉ”
7. ሰዎች ከእንስሳት ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ይሖዋ ምን ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር?
7 ይሖዋ በፍጥረት ሥራው መጨረሻ ላይ የፈጠረው ሰዎችን ሲሆን ይህም ምድር ላይ ካከናወናቸው ሥራዎች ሁሉ ትልቁን ቦታ የሚይዝ ነው። ይሖዋ፣ ሰውን በፈጠረበት ወቅት ስላለው ዓላማ ዋና ሠራተኛው ለሆነው ለበኩር ልጁ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው።” (ዘፍ. 1:26) በመሆኑም አዳምንና ሔዋንን ጨምሮ ሁሉም የሰው ልጆች እንስሳትን እንዲገዙ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር።
8. በዛሬው ጊዜ እንስሳት ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየታቸው የተለመደ ነው?
8 እንስሳትን በሙሉ መግዛትና ከእነሱ ጋር በሰላም መኖር በእርግጥ የሚቻል ነገር ነው? ብዙ ሰዎች እንደ ድመትና ውሻ ካሉ የቤት እንስሳት ጋር ይቀራረባሉ። ስለ ዱር እንስሳትስ ምን ማለት ይቻላል? አንድ ሪፖርት “ከአራዊት ጋር አብረው በመኖር በእነሱ ላይ ጥናት ያደረጉ የሳይንስ ሊቃውንት ሁሉም አጥቢ እንስሳት ስሜት እንዳላቸው ተገንዝበዋል” በማለት ገልጿል። እንስሳት አደጋ እንደሚደርስባቸው ሲያስቡ ድንጉጦችና ቁጡዎች እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፤ ይሁንና የፍቅር ስሜት ማሳየትስ ይችላሉ? ሪፖርቱ አክሎ “አጥቢዎች እጅግ ግሩም የሆነ ባሕርይ እንዳላቸው ይኸውም ሌሎችን የመውደድ አስገራሚ ችሎታ እንዳላቸው የሚታወቀው ልጆቻቸውን በሚያሳድጉበት ጊዜ ነው” ብሏል።
9. ከእንስሳት ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት ለውጦችን መጠበቅ እንችላለን?
9 ወደፊት በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም እንደሚሰፍን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስናነብ ልንደነቅ አይገባም። (ኢሳይያስ 11:6-9ን እና 65:25ን አንብብ።) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኖኅና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው በኋላ ከመርከብ ሲወጡ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት የነገራቸውን ነገር አስታውሱ፦ “አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ፦ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን።” ይህ መሆኑ እንስሳቱ ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳቸዋል። (ዘፍ. 9:2, 3) ታዲያ ይሖዋ ሰዎች በእንስሳት ላይ ያላቸውን አስፈሪነትና አስደንጋጭነት በተወሰነ መጠን በማስወገድ መጀመሪያ ላይ የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም? (ሆሴዕ 2:18) በሕይወት ተርፈው በዚያን ወቅት በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይጠብቃቸዋል!
“እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል”
10. በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ማልቀስ የተለመደ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?
10 ሰለሞን “ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ግፍ ሁሉ” ሲመለከት “የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም” በማለት ሐዘኑን ገልጿል። (መክ. 4:1) አሁን ያለንበት ሁኔታ ይብስ እንደሆን እንጂ የተለወጠ ነገር የለም። ከእኛ መካከል በሆነ ምክንያት እንባውን ያላፈሰሰ ማን አለ? እርግጥ የደስታ እንባ የምናነባበት ጊዜ አለ። አብዛኛውን ጊዜ ግን እንድናለቅስ የሚያደርገን የልባችን ሐዘን ነው።
11. ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ በተለይ ልብህን የሚነካህ የትኛው ነው?
11 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸውን አሳዛኝና ልብ የሚነኩ ታሪኮችን ወደ አእምሯችን ለማምጣት እንሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ ሣራ በ127 ዓመቷ ስትሞት “አብርሃምም ለሣራ ሊያለቅስና ሊያዝን መጣ” በማለት ይናገራል። (ዘፍ. 23:1, 2) ኑኃሚን መበለት የሆኑትን ሁለቱን ምራቶቿን ለመለያየት ስትሰነባበት “ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ።” ዘገባው ሲቀጥል “እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ” ይላል። (ሩት 1:9, 14) ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በጠና በመታመሙ ምክንያት ሊሞት ተቃርቦ በነበረበት ወቅት “ምርር ብሎ አለቀሰ”፤ ይሖዋም ቢሆን የሕዝቅያስ ሁኔታ እንዳሳዘነው ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ነገ. 20:1-5) ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን ከካደው በኋላ ስለተሰማው ስሜት የሚገልጸውን ዘገባ ሲያነብ ልቡ የማይነካ ማን አለ? ጴጥሮስ የዶሮ ጩኸት ሲሰማ “ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።”—ማቴ. 26:75
12. የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች እውነተኛ እፎይታ የሚያመጣው እንዴት ነው?
12 ቀላልም ይሁን ከባድ፣ ሁሉም ሰዎች አሳዛኝ ሁኔታ ስለሚያጋጥማቸው ማጽናኛ ማግኘት በጣም ያስፈልጋቸዋል። የሺው ዓመት አገዛዝ ለተገዥዎቹ የሚያመጣው እንዲህ ያለ እፎይታ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:4) ሐዘን፣ ለቅሶና ሥቃይ አለመኖሩ ከፍተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ የታወቀ ነው፤ አምላክ የሰው ልጆች ቀንደኛ ጠላት የሆነውን ሞትን ጭምር እንደሚያስወግድ ቃል መግባቱ ደግሞ የበለጠ ያስደስታል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው?
‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ይወጣሉ’
13. አዳም ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ ጀምሮ ሞት በሰው ልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?
13 አዳም ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ ጀምሮ ሞት በሰው ልጆች ላይ ነግሷል። ሞት ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ሸሽተው ሊያመልጡት ያልቻሉት እንዲሁም ሰዎችን ለከባድ ሐዘንና ሰቆቃ የዳረገ የማይበገር ጠላት ነው። (ሮም 5:12, 14) እንዲያውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ሞትን በመፍራት በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ ለባርነት [ተዳርገዋል]።”—ዕብ. 2:15
14. ሞት ሲደመሰስ ምን ውጤት ይገኛል?
14 መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት” የሚደመሰስበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። (1 ቆሮ. 15:26) ይህ መሆኑ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ሁለት ቡድኖች አሉ። በአንድ በኩል በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ይህን ሥርዓት በሕይወት አልፈው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ማግኘት የሚችሉበት በር ይከፍትላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በሞት ያንቀላፉ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትንሣኤ እንዲያገኙ ያስችላል። እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ ከሞት የሚነሱትን በሚቀበሉበት ወቅት ምን ያህል ደስታ ሊኖር እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ? ትንሣኤ ስላገኙ ሰዎች የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በጥልቀት መመርመራችን በዚያን ጊዜ የሚኖረውን ሁኔታ በጥቂቱም ቢሆን እንድንረዳ ያስችለናል።—ማርቆስ 5:38-42ን እና ሉቃስ 7:11-17ን አንብብ።
15. የምትወዳቸው ሰዎች ከሞት ሲነሱ ምን የሚሰማህ ይመስልሃል?
15 “የሚሆኑት እስኪጠፋቸው ድረስ በጣም ተደሰቱ” እና “አምላክን ያወድሱ ጀመር” ስለሚሉት አገላለጾች ለአንድ አፍታ ለማሰብ ሞክሩ። እናንተም በቦታው ተገኝታችሁ ቢሆን ኖሮ ተመሳሳይ ስሜት እንደሚሰማችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። የምንወዳቸውን ሰዎች በትንሣኤ ስናገኛቸው የምንሆነው እስኪጠፋን ድረስ በደስታ እንደምንፈነጥዝ የታወቀ ነው። ኢየሱስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 5:28, 29) ማናችንም ብንሆን በዚህች ምድር ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከናወን አይተን ባናውቅም ይህ ከማይታዩት እጅግ ታላላቅ ነገሮች መካከል አንዱ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
አምላክ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል
16. (ሀ) ከሌሎች ጋር ስንገናኝ፣ ገና ስላልታዩት ነገሮች በጋለ ስሜት መናገራችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ለማበረታታት ምን ብሏል?
16 በዚህ አስጨናቂ ዘመን ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ሰዎች እጅግ አስደናቂ ተስፋ ይጠብቃቸዋል! እነዚህ ታላላቅ በረከቶች ገና ያልታዩ ቢሆኑም በአእምሯችን ውስጥ ሕያው ሆነው እንዲታዩን ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ እንዲሁም በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚገኙ ቅጽበታዊ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች ትኩረታችንን እንዳይሰርቁት ይረዳናል። (ሉቃስ 21:34፤ 1 ጢሞ. 6:17-19) በቤተሰብ አምልኳችን ወቅት፣ ከእምነት ባልጀሮቻችን ጋር ስንጨዋወት እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንና ፍላጎት ካሳዩ ሰዎች ጋር ስንወያይ አስደናቂ ስለሆነው ተስፋችንና ወደፊት ስለምናገኛቸው በረከቶች በጋለ ስሜት እንናገር። እንዲህ ማድረጋችን ተስፋችን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ ሕያው እንዲሆን ያስችላል። ሐዋርያው ጳውሎስም የእምነት ባልንጀሮቹን ያበረታታቸው እንዲህ እንዲያደርጉ ነበር። በሌላ አባባል የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሐሳባቸው እስከ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ድረስ እንዲጓዙ አድርጓቸው ነበር። እስቲ ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:24, 25, 28 (ጥቅሱን አንብብ።) ላይ የተናገረው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ሲያገኝ የሚኖረውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናችሁ ለማየት ሞክሩ።
17, 18. (ሀ) በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ ይሖዋ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” የሆነው እንዴት ነበር? (ለ) ኢየሱስ በአጽናፈ ዓለሙ ቤተሰብ ውስጥ የነበረውን አንድነትና ኅብረት እንደገና ለመመለስ ምን ያደርጋል?
17 በሺህ ዓመቱ ፍጻሜ ላይ “አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር [ይሆናል]”፤ በዚያ ጊዜ የሚኖረውን ሕይወት ለመግለጽ ከዚህ የተሻለ አባባል የለም። ይሁንና ይህ አባባል ምን ትርጉም አለው? እስቲ አዳምና ሔዋን ፍጹም እያሉ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላችሁ አስቡ፤ በዚያን ወቅት አዳምና ሔዋን የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባላት ነበሩ። የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የሆነው ይሖዋ ሰዎችንና መላእክትን ጨምሮ ፍጥረታቱን ሁሉ በቀጥታ ይገዛ ነበር። ፍጥረታቱም ቢሆን ከይሖዋ ጋር በቀጥታ መነጋገር ይችሉ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እሱን ያመልኩ እንዲሁም በረከቱን ያገኙ ነበር። ያን ጊዜ ይሖዋ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆን ነበር።
18 የሰው ልጆች በሰይጣን ተጽዕኖ በመሸነፍ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ሲያምፁ ግን ይህ ቤተሰባዊ አንድነት ተናጋ። ይሁንና ከ1914 ጀምሮ መሲሐዊው መንግሥት ይህንን አንድነትና ኅብረት እንደገና ለመመለስ ደረጃ በደረጃ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። (ኤፌ. 1:9, 10) በአሁኑ ጊዜ ‘የማይታዩት’ አስደናቂ ነገሮች በሺህ ዓመቱ የግዛት ዘመን እውን ይሆናሉ። ከዚያም የክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት “ፍጻሜ” ይሆናል። ከዚያስ በኋላ ምን ይሆናል? ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው ቢሆንም ለሥልጣን የሚጓጓ አይደለም። የይሖዋን ቦታ የመንጠቅ ፍላጎት የለውም። ከዚህ ይልቅ በትሕትና “መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ” ያስረክባል። ኢየሱስ ያለውን ልዩ ቦታና ሥልጣን ‘አምላክን ለማክበር’ ይጠቀምበታል።—ማቴ. 28:18፤ ፊልጵ. 2:9-11
19, 20. (ሀ) ሁሉም የመንግሥቱ ተገዥዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደተቀበሉ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ምን ግሩም ተስፋ ይጠብቀናል?
19 በሺው ዓመት ፍጻሜ ላይ የመንግሥቱ ምድራዊ ተገዥዎች ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የይሖዋን ሉዓላዊነት በፈቃደኝነትና በትሕትና ይቀበላሉ። እነዚህ ሰዎች የመጨረሻውን ፈተና በተሳካ ሁኔታ በማለፍ እንዲህ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያሉ። (ራእይ 20:7-10) ከዚያ በኋላ የሚያምፅ ማንኛውም ፍጡር፣ የሰው ልጅም ይሁን መንፈሳዊ አካል ለዘላለም ይወገዳል። ይህ ወቅት እንዴት የሚያስደስት ይሆን? የአጽናፈ ዓለሙ ቤተሰብ በሙሉ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” የሚሆነውን ይሖዋን በደስታ ያወድሳል።—መዝሙር 99:1-3ን አንብብ።
20 በቅርቡ የምንጠብቃቸው የመንግሥቱ አስደናቂ እውነቶች፣ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንድታተኩር አላነሳሱህም? የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸው የሐሰት ተስፋዎች ወይም ማጽናኛዎች ልብህን እንዳያሸፍቱት ጥረት ማድረግ ትችላለህ? የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከርስ አልተገፋፋህም? እንግዲያው ይህን ለዘላለም የማድረግ ፍላጎት እንዳለህ በተግባር አሳይ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ለሺህ ዓመትና ከዚያም በኋላ የሚዘልቅ ሰላምና ብልጽግና በማግኘት ትባረካለህ!