ይሖዋ ሰላምንና እውነትን አትረፍርፎ ይሰጣል
“እፈውሳቸውማለሁ፤ የሰላምንና የእውነትን ብዛት እገልጥላቸዋለሁ።”—ኤርምያስ 33:6
1, 2. (ሀ) ሰላምን በተመለከተ ብሔራት ምን ታሪክ አስመዝግበዋል? (ለ) በ607 ከዘአበ ይሖዋ ሰላምን በተመለከተ ለእስራኤል ያስተማረው ምን ነበር?
ሰላም፣ ምንኛ ተፈላጊ ነገር ነው! ሆኖም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሰላም የተገኘባቸው ጊዜያት በጣም ጥቂት ናቸው። በተለይ 20ኛው መቶ ዘመን ጨርሶ ሰላም የጠፋበት ዘመን ሆኗል። እንዲያውም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ጥፋት ያስከተሉ ሁለት ጦርነቶች የተከሰቱበት ዘመን ነው። ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የዓለምን ሰላም ለማስከበር ተቋቁሞ ነበር። ሆኖም ይህ ድርጅት አልተሳካለትም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለተመሳሳይ ዓላማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመሠረተ። ይህ ድርጅት ምን ያህል ሳይሳካለት እንደቀረ ለማወቅ በየቀኑ የሚወጡትን ጋዜጦች ማንበብ ብቻ ይበቃል።
2 የሰው ልጅ ያቋቋማቸው ድርጅቶች ሰላም ለማምጣት አለመቻላቸው ሊያስደንቀን ይገባልን? ፈጽሞ አይገባም። ከ2,500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች የነበሩት እስራኤላውያን ይህን በተመለከተ አንድ ትምህርት አግኝተው ነበር። በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በወቅቱ ኃያል በነበረው የባቢሎን መንግሥት ምክንያት የእስራኤል ሰላም አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። እስራኤል ሰላም ለማግኘት በግብፅ ተማመነች። ግብፅ እስራኤልን ለመርዳት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀረ። (ኤርምያስ 37:5-8፤ ሕዝቅኤል 17:11-15) በ607 ከዘአበ የባቢሎናውያን ሠራዊት የኢየሩሳሌምን ግንቦች ካፈራረሱ በኋላ የይሖዋን ቤተ መቅደስ በእሳት አቃጠሉት። በዚህ መንገድ እስራኤላውያን በሰብዓዊ ድርጅቶች መታመን ከንቱ እንደሆነ በአስቸጋሪ ሁኔታ ተማሩ። የእስራኤል ሕዝብ ሰላም ከማግኘት ይልቅ ወደ ባቢሎን ተማርከው ተወሰዱ።—2 ዜና መዋዕል 36:17-21
3. ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የተናገራቸው ቃላት ሲፈጸሙ እስራኤል ስለ ሰላም ለሁለተኛ ጊዜ አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንድታገኝ ያደረጓት ታሪካዊ ክንውኖች የትኞቹ ናቸው?
3 ይሁን እንጂ ይሖዋ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት ለእስራኤል ሰላም የሚያመጣው እሱ እንጂ ግብፅ እንዳልሆነች ገልጾ ነበር። በኤርምያስ በኩል የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፦ “እፈውሳቸውማለሁ፤ የሰላምንና የእውነትን ብዛት እገልጥላቸዋለሁ። የይሁዳን ምርኮና የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፣ ቀድሞም እንደ ነበሩ አድርጌ እሠራቸዋለሁ።” (ኤርምያስ 33:6, 7) በ539 ከዘአበ ባቢሎን ድል ስትደረግና እስራኤላውያን ምርኮኞች ነፃ እንዲወጡ ጥሪ ሲቀርብ ይሖዋ የሰጠው ተስፋ መፈጸም ጀመረ። (2 ዜና መዋዕል 36:22, 23) በ537 ከዘአበ መገባደጃ ላይ አንድ የእስራኤላውያን ቡድን ከ70 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ምድር የዳስ በዓልን አከበረ! ከበዓሉ በኋላ የይሖዋን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመሩ። ይህ ሁኔታ ምን ስሜት አሳድሮባቸው ነበር? የታሪክ መዝገቡ “የእግዚአብሔርም ቤት ስለ ተመሠረተ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በታላቅ ድምፅ እልል አሉ” ይላል።—ዕዝራ 3:11
4. ይሖዋ የቤተ መቅደሱን ግንባታ ሥራ እንዲጀምሩ እስራኤላውያንን ያነሣሣቸው እንዴት ነው? ሰላምን በተመለከተ የሰጣቸው ተስፋስ ምን ነበር?
4 ሆኖም ከዚህ አስደሳች ጅምር በኋላ ተቃዋሚዎቻቸው ተስፋ ስላስቆረጧቸው እስራኤላውያን የቤተ መቅደሱን ግንባታ አቋረጡ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እስራኤላውያን የግንባታውን ሥራ እንዲያጠናቅቁ ለማነቃቃት ይሖዋ ሐጌና ዘካርያስ የተባሉትን ነቢያት አስነሣ። ሐጌ ወደፊት የሚሠራውን ቤተ መቅደስ በተመለከተ “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ በዚህም ስፍራ ሰላምን እሰጣለሁ” በማለት ሲናገር መስማታቸው በጣም አስደስቷቸው መሆን ይኖርበታል።—ሐጌ 2:9
ይሖዋ የገባውን ቃል ይፈጽማል
5. ዘካርያስ ምዕራፍ ስምንትን በተመለከተ ምን ሊስተዋል ይገባል?
5 የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘካርያስ ትንቢት ውስጥ በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበሩትን የአምላክ ሕዝቦች ያበረታቱ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ ብዙ ራእዮችንና ትንቢቶችን እናነባለን። ዛሬም ቢሆን እነዚህ ትንቢቶች የይሖዋን እርዳታ እንደምናገኝ ያረጋግጡልናል። ይሖዋ በዘመናችንም ለሕዝቦቹ ሰላምን እንደሚሰጥ አሳማኝ ምክንያቶችን ያቀርቡልናል። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ዘካርያስ በእሱ ስም የተሰየመው መጽሐፍ ስምንተኛው ምዕራፍ ላይ አሥር ጊዜ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚሉትን ቃላት ተናግሯል። እነዚህ ቃላት በእያንዳንዱ ወቅት ከአምላክ ሕዝቦች ሰላም ጋር ግንኙነት ያለውን አንድ መለኮታዊ መግለጫ ያስተዋውቃሉ። ከእነዚህ ተስፋዎች መካከል አንዳንዶቹ በዘካርያስ ዘመን ተፈጽመዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሁሉም ተስፋዎች ወይ ተፈጽመዋል አሊያም በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።
‘ለጽዮን እቀናለሁ’
6, 7. ይሖዋ ‘ለጽዮን በታላቅ ቅንዓት የቀናው’ በምን በምን መንገዶች ነበር?
6 እነዚህ ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሱት በዘካርያስ 8:2 ላይ ነው። እዚህ ጥቅስ ላይ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፣ በታላቅም ቁጣ ስለ እርስዋ ቀንቻለሁ” የሚል እናነባለን። ይሖዋ ለሕዝቡ እቀናለሁ እንዲሁም ታላቅ ቅንዓት አለኝ በማለት ቃል መግባቱ ሰላማቸውን ለመመለስ ልዩ ትኩረት እንደሚያደርግ ያሳያል። እስራኤላውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውና ቤተ መቅደሱ እንደገና መሠራቱ ለዚህ ቅንዓቱ ማስረጃ ነበር።
7 ታዲያ የይሖዋን ሕዝቦች ይቃወሙ የነበሩት ሰዎች ምን ሆኑ? ለሕዝቦቹ የነበረው ቅንዓት በእነዚህ ጠላቶች ላይ ካሳየው ‘ታላቅ ቁጣ’ ጋር የሚመጣጠን ነበር። ታማኝ አይሁዳውያን እንደገና በተሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ የአምልኮ ሥርዓት ሲፈጽሙ በወቅቱ ወድቃ የነበረችው የባቢሎን ኃያል መንግሥት በደረሰባት ዕጣ ላይ ሊያሰላስሉ ይችሉ ነበር። በተጨማሪም ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዳይሠራ ለማድረግ ይጥሩ የነበሩት ጠላቶች ምን ያህል እንዳልተሳካላቸው ሊያስቡ ይችሉ ነበር። (ዕዝራ 4:1-6፤ 6:3) ከዚህም በላይ ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ በመፈጸሙ ሊያመሰግኑት ይችሉ ነበር። ቅንዓቱ ድል እንዲቀዳጁ አብቅቷቸዋል!
“የእውነት ከተማ”
8. ቀደም ሲል ከነበሩት ጊዜያት አንፃር ሲታይ ኢየሩሳሌም በዘካርያስ ዘመን የእውነት ከተማ የነበረችው እንዴት ነው?
8 ዘካርያስ ለሁለተኛ ጊዜ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በማለት ጻፈ። በዚህ ወቅት ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ምንድን ናቸው? “ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፣ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፤ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፤ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል።” (ዘካርያስ 8:3) ከ607 ከዘአበ ቀደም ብሎ ኢየሩሳሌም የእውነት ከተማ እንዳልነበረች የተረጋገጠ ነው። በዚያ ወቅት ካህናቷና ነቢያቶቿ ብልሹዎች የነበሩ ሲሆን ሕዝቧ ደግሞ ከሃዲ ነበር። (ኤርምያስ 6:13፤ 7:29-34፤ 13:23-27) በዚህ ጊዜ ግን የአምላክ ሕዝቦች ለንጹሕ አምልኮ ታማኝ መሆናቸውን በማሳየት ቤተ መቅደሱን እንደገና በመሥራት ላይ ነበሩ። ይሖዋ እንደገና በኢየሩሳሌም ውስጥ በመንፈስ መኖር ጀምሮ ነበር። የንጹሕ አምልኮ እውነቶች በውስጧ እንደገና በመነገራቸው ምክንያት ኢየሩሳሌም “የእውነት ከተማ” ልትባል ትችል ነበር። በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ከፍተኛ ቦታዎች “የእግዚአብሔር ተራራ” ተብለው ሊጠሩ ይችሉ ነበር።
9. “የአምላክ እስራኤል” በ1919 ምን አስደናቂ ለውጥ ተመልክቷል?
9 እነዚህ ሁለት መግለጫዎች ለጥንቷ እስራኤል ትልቅ ትርጉም የነበራቸው ቢሆንም ይህ 20ኛው መቶ ዘመን ወደ ፍጻሜው በቀረበ መጠን ለእኛ የበለጠ ትርጉም ይኖራቸዋል። የጥንት እስራኤላውያን ወደ ባቢሎን ተማርከው እንደተወሰዱ ሁሉ ወደ 80 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት “የአምላክ እስራኤል”ን ይወክሉ የነበሩ በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ቅቡዓን በመንፈሳዊ ሁኔታ ተማርከው ነበር። (ገላትያ 6:16) በአንድ ትንቢታዊ መግለጫ ላይ በአደባባይ እንደ ተጣሉ ሬሳዎች ሆነው ተገልጸው ነበር። ሆኖም ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ ልባዊ ፍላጎት ነበራቸው። (ዮሐንስ 4:24) ስለዚህ ይሖዋ በ1919 በመንፈሳዊ ሞተው ከነበሩበት ሁኔታ በማስነሣት ከምርኮ ነፃ አወጣቸው። (ራእይ 11:7-13) በዚህ መንገድ ይሖዋ “በውኑ አገር [“ምድር” አዓት] በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን?” ለሚለው የኢሳይያስ ትንቢታዊ ጥያቄ አዎን በማለት የሚያስተጋባ ምላሽ ሰጠ። (ኢሳይያስ 66:8) በ1919 የይሖዋ ሕዝቦች በራሳቸው “ምድር” ወይም በምድር ላይ ባላቸው መንፈሳዊ ርስት ውስጥ እንደገና እንደ አንድ መንፈሳዊ ብሔር ሆነው ተገኝተዋል።
10. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከ1919 ጀምሮ በራሳቸው “ምድር” ውስጥ ያገኟቸው በረከቶች ምንድን ናቸው?
10 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በዚያ ምድር ያላንዳች ስጋት ተቀምጠው በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ በማገልገል ላይ ናቸው። የኢየሱስን ምድራዊ ንብረቶች እንዲንከባከቡ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመቀበላቸው “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሆኑ ተሹመዋል፤ 20ኛው መቶ ዘመን ወደ መደምደሚያው እየተቃረበ በሄደበት በዚህ ወቅትም እንኳን ይህን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:45-47) ይሖዋ ‘የሰላም አምላክ’ መሆኑን በሚገባ ተምረዋል።—1 ተሰሎንቄ 5:23
11. የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
11 ታዲያ የአምላክ እስራኤል ጠላቶች ምን ይሆናሉ? ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ቅንዓት በጠላቶቹ ላይ ከሚያወርደው ቁጣ ጋር ይመጣጠናል። የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ይህን እውነትን የሚናገር አነስተኛ የክርስቲያኖች ቡድን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአንድ ነገር ሕብረት ፈጥረው ነበር፤ በጦርነቱ በሁለቱም ወገኖች የተሰለፉትን መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮችን እንዲያጠፏቸው ይገፋፏቸው ነበር። የሃይማኖት መሪዎች ዛሬም ቢሆን በብዙ አገሮች ውስጥ መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮችን ክርስቲያናዊ የስብከት ሥራ እንዲገድቡ ወይም እንዲያግዱ በማነሣሣት ላይ ይገኛሉ።
12, 13. በሕዝበ ክርስትና ላይ የይሖዋ ቁጣ የተገለጠው እንዴት ነው?
12 ይህን ጉዳይ ይሖዋ ሳይመለከተው አልቀረም። ሕዝበ ክርስትና ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ከቀሩት የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች ጋር ወድቃለች። (ራእይ 14:8) ሕዝበ ክርስትና በመንፈሳዊ የሞተች መሆኗን በሕዝብ ፊት የሚያጋልጡና ወደፊት እንደምትጠፋ የሚያስጠነቅቁ ምሳሌያዊ የሆኑ ተከታታይ መቅሠፍቶች ከፈሰሱባት ከ1922 ጀምሮ ውድቀቷ በግልጽ ታይቷል። (ራእይ 8:7 እስከ 9:21) በመላው ዓለም ሚያዝያ 23, 1995 “የሐሰት ሃይማኖት ጥፋት ቀርቧል” በሚል ርዕስ ንግግር ከተሰጠ በኋላ በመቶ ሚልዮን በሚቆጠሩ ቅጂዎች አንድ ልዩ የመንግሥት ዜና መሰራጨቱ አሁንም እነዚህ መቅሠፍቶች መፍሰሳቸውን እንደ ቀጠሉ ያረጋግጣል።
13 በአሁኑ ጊዜ ሕዝበ ክርስትና በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በሙሉ በቀሳውስቶቿና በአገልጋዮቿ ቡራኬ በተቀበሉ አረመኔያዊ ጦርነቶች አባላቶቿ እርስ በርሳቸው ተጨፋጭፈዋል። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ሕዝበ ክርስትና ጨርሶ ተደማጭነት እያጣች መጥታለች። ሕዝበ ክርስትና ከቀሩት የታላቂቱ ባቢሎን ክፍሎች ጋር እንድትጠፋ ተወስኗል።—ራእይ 18:21
ሰላም ለይሖዋ ሕዝብ
14. ሰላም ያለውን አንድ ሕዝብ በተመለከተ የተሰጠው ትንቢታዊ መግለጫ ምንድን ነው?
14 በሌላ በኩል ግን ይሖዋ በተናገረው ሦስተኛ መግለጫ ላይ እንደ ተገለጸው በዚህ በ1996 ዓመት የይሖዋ ሕዝቦች ተመልሶ በተቋቋመው ምድራቸው ውስጥ የተትረፈረፈ ሰላም ያገኛሉ፤ መግለጫው እንዲህ ይላል፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች [“አሮጊቶች” አዓት] በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፤ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል። የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ።”—ዘካርያስ 8:4, 5
15. በብሔራት መካከል ጦርነቶች ቢኖሩም የአምላክ አገልጋዮች ምን ዓይነት ሰላም አግኝተዋል?
15 ይህ አስደሳች መግለጫ በዚህ በጦርነት በሚታመስ ዓለም ውስጥ አንድ አስደናቂ የሆነ ነገር ማለትም ሰላም ያላቸውን ሕዝቦች ይገልጻል። ከ1919 ጀምሮ “በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፣ እፈውሰውማለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር። ክፉዎች ግን . . . ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ” የሚሉት የኢሳይያስ ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (ኢሳይያስ 57:19-21) እርግጥ የይሖዋ ሕዝቦች የዓለም ክፍል ባይሆኑም ብሔራት በሚያደርጉት ሽኩቻ መነካታቸው አይቀርም። (ዮሐንስ 17:15, 16) በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ከባድ ችግሮች ያጋጠማቸው ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ ተገድለዋል። ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሰላም አላቸው። በመጀመሪያ ደረጃ “በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም” አግኝተዋል። (ሮሜ 5:1) በሁለተኛ ደረጃ እርስ በርሳቸው ሰላም አላቸው። “በመጀመሪያ ንጽሕት፣ በኋላም ሰላማዊ” የሆነችውን “ላይኛይቱን ጥበብ” ኮትኩተዋል። (ያዕቆብ 3:17 አዓት፤ ገላትያ 5:22-24) ከዚህም በላይ ወደፊት ይበልጥ በተሟላ መልኩ ሰላም የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ፤ በዚያን ጊዜ “ገሮች ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
16, 17. (ሀ) “ሽማግሌዎችና አሮጊቶች”ም ሆኑ “ወንዶችና ሴቶች ልጆች” የይሖዋን ድርጅት ያጠናከሩት እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች ሰላም እንዳላቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?
16 አሁንም ቢሆን በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የይሖዋ ድርጅት ቀደም ሲል የተቀዳጀውን ድል የሚያስታውሱ “ሽማግሌዎችና አሮጊቶች” የሆኑ ቅቡዓን አሉ። ታማኝነታቸውና ጽናታቸው በጣም ይደነቃል። ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እያመሩ በነበሩት በ1930ዎቹ እሳታማ ጊዜያትና ከዚያ በኋላ ባሉት አስደሳች የእድገት ዓመታት ወጣት ቅቡዓን ግምባር ቀደም ሆነው አገልግለዋል። ከዚህም በላይ በተለይ ከ1935 ጀምሮ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑት የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” ማንነት በግልጽ ታውቋል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) የቅቡዓን ክርስቲያኖች ዕድሜ እየገፋና ቁጥራቸው እየቀነሰ በሄደ መጠን ሌሎች በጎች የስብከቱን ሥራ ተረክበው በመላው ዓለም በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። በቅርብ ዓመታት ሌሎች በጎች ወደ አምላክ ሕዝቦች ምድር በብዛት እየጎረፉ በመምጣት ላይ ናቸው። እንዲያውም ባለፈው ዓመት ብቻ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ 338,491 ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል! እነዚህ አዲስ ሰዎች በመንፈሳዊ አነጋገር ገና ልጆቸ እንደሆኑ የተረጋገጠ ነው። “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ” እያሉ የምስጋና ውዳሴዎችን የሚዘምሩ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምሩ ባደረጉ መጠን አዲስነታቸውና ቅንዓታቸው ከፍተኛ ግምት ይሰጠዋል።—ራእይ 7:10
17 በአሁኑ ጊዜ ‘አደባባዮቿ በወንዶችና በሴቶች ልጆች’ ማለትም የወጣትነት ብርታት በሚታይባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ተሞልተዋል። በ1995 የአገልግሎት ዓመት 232 አገሮችና ደሴቶች ሪፖርት አድርገዋል። ይሁን እንጂ በቅቡዓንና በሌሎች በጎች መካከል ዓለም አቀፍ ፉክክር፣ የጎሣ ጥላቻና ተገቢ ያልሆነ ቅናት አይታይም። ሁሉም በፍቅር ተሳስረው መንፈሳዊ እድገት አሳይተዋል። በእርግጥም ዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች የወንድማማች ማኅበር በዓለም ውስጥ በዓይነቱ ብቸኛና ልዩ ነው።—ቆላስይስ 3:14፤ 1 ጴጥሮስ 2:17
ለይሖዋ የሚሳነው ነገር አለን?
18, 19. ይሖዋ ከ1919 ጀምሮ ባሉት ዓመታት በሰው ዓይን ሲታይ በጣም አስቸጋሪ የሚመስል ነገር ያከናወነው እንዴት ነው?
18 በ1918 ቅቡዓን ቀሪዎች በመንፈሳዊ ምርኮ ውስጥ የሚገኙ በጥቂት ሺዎች ብቻ የሚቆጠሩ ተስፋ የቆረጡ ነፍሳትን ያቀፉ ነበሩ፤ በተጨማሪም አንዳቸውም ቢሆኑ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አያውቁም ነበር። ሆኖም በአራተኛው ትንቢታዊ መግለጫ ላይ “ይህ፣ አሁን በምርኮ ከመወሰድ ለተረፉት ሰዎች የማይቻል ነገር መስሎ ይታያቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ለእኔ የማይቻል ነገር አይደለም” በማለት ስላረጋገጠ ይሖዋ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ያውቅ ነበር።—ዘካርያስ 8:6 የ1980 ትርጉም
19 ይሖዋ ሕዝቦቹ ከፊት ለፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ በ1919 በመንፈሱ አማካኝነት አነቃቃቸው። ሆኖም የይሖዋ አምላኪዎችን ካቀፈው ትንሽ ድርጅት ጋር ጸንቶ መቆም እምነት የሚጠይቅ ነገር ነበር። እነዚህ ቅቡዓን በጣም ጥቂቶች የነበሩ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ብዙ ያልተረዷቸው ነገሮች ነበሩ። ሆኖም ይሖዋ በድርጅት ደረጃ ቀስ በቀስ አጠናከራቸውና ምሥራቹን በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ክርስቲያናዊ ሥራ አስታጠቃቸው። (ኢሳይያስ 60:17, 19፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ቀስ በቀስ እንደ ገለልተኛነትና ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ያሉትን ወሳኝ ጉዳዮች እንዲያስተውሉ ረዳቸው። ይሖዋ በዚያ አነስተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን በመጠቀም ፈቃዱን መፈጸም ተስኖት ነበርን? መልሱ በፍጹም አልተሳነውም ነው! በ1995 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች የሥራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል የሚያሳየው ከገጽ 12 እስከ 15 የሚገኘው ሰንጠረዥ ይህን ያረጋግጣል።
“አምላክ እሆናቸዋለሁ”
20. በትንቢት የተነገረው የአምላክ ሕዝቦች መሰብሰብ ምን ያህል ስፋት ነበረው?
20 አምስተኛው መግለጫ በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ያሉበትን ሌላ አስደሳች ሁኔታ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፤ አመጣቸዋለሁምም፣ በኢየሩሳሌም ውስጥ ይኖራሉ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፣ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ።”—ዘካርያስ 8:7, 8
21. የይሖዋ ሕዝቦች ያገኙት የተትረፈረፈ ሰላም ተጠብቆ የኖረውና እያደር እየጨመረ የሄደው እንዴት ነው?
21 ያለ ጥርጥር በ1996 ምሥራቹ “ከምሥራቅ” እስከ “ምዕራብ” ድረስ በዓለም ዙሪያ በመሰበክ ላይ ነው ልንል እንችላለን። ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ደቀ መዛሙርት ሆነዋል፤ በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” በማለት ይሖዋ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ተመልክተዋል። (ኢሳይያስ 54:13) ከይሖዋ ስለ ተማርን ሰላም አግኝተናል። ይህን ትምህርት ለመስጠት ሲባል ከ300 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ጽሑፎች ታትመዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ 21 ሌሎች ቋንቋዎች ታክለዋል። በአሁኑ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በአንድ ጊዜ በ111 ቋንቋዎች፣ ንቁ! መጽሔት ደግሞ በ54 ቋንቋዎች በመታተም ላይ ናቸው። ብሔራዊና ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች የአምላክ ሕዝቦች ሰላም ለሕዝብ በግልጽ እንዲታይ ያደርጋሉ። ሳምንታዊ ስብሰባዎች አንድ የሚያደርጉን ከመሆናቸውም በተጨማሪ ጸንተን ለመቆም የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እናገኝባቸዋለን። (ዕብራውያን 10:23-25) አዎን፣ ይሖዋ ሕዝቡን “በእውነትና በጽድቅ” በማስተማር ላይ ነው። ለሕዝቡ ሰላም እየሰጠ ነው። ይህን የተትረፈረፈ ሰላም በማግኘታችን ምንኛ ተባርከናል!
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ በዘመናችን ይሖዋ ለሕዝቡ ‘በታላቅ ቅንዓት የቀናው’ እንዴት ነው?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች በጦርነት በሚታመሱ አገሮች ውስጥም እንኳ ሰላም ያገኙት እንዴት ነው?
◻ ‘አደባባዮች በወንዶችና በሴቶች ልጆች የተሞሉት’ በምን መንገድ ነው?
◻ የይሖዋ ሕዝቦች ከእሱ ለመማር እንዲችሉ ምን ዝግጅቶች ተደርጎላቸዋል?“እውነትንና ሰላምን ውደዱ”!
[በገጽ 12-15 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የይሖዋ ምሥክሮች የ1995 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት
(መጽሔቱን ተመልከት)
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ቤተ መቅደሱን እንደገና የሠሩት ታማኝ አይሁዳውያን አስተማማኝ የሰላም ምንጭ ይሖዋ ብቻ መሆኑን ተገንዝበዋል