የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ ከእሴይና ከዳዊት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ዘር ሆኖ ሳለ የቅድመ አያቶቹ የእሴይና የዳዊት “ሥር” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?
አንድ ተክል ወይም ዛፍ ግንድና ቅርንጫፎች ከማውጣቱ በፊት ሥር እንደሚያወጣ የታወቀ ነው። ስለሆነም ከጊዜ በኋላ ኢየሱስን ያስገኘው ሥር እሴይ (ወይም ልጁ ዳዊት) ነው ተብሎ መነገር የነበረበት ሊመስል ይችላል። ሆኖም በኢሳይያስ 11:10 ላይ መሲሕ ሆኖ የሚመጣው ሰው “የእሴይ ሥር” እንደሚሆን ተተንብዮ ነበር። ይህ ትንቢትም ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያመለክት መሆኑ በሮሜ 15:12 ላይ ተገልጿል። ከጊዜ በኋላም ኢየሱስ በራእይ 5:5 ላይ “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር” ተብሏል። ኢየሱስን የእሴይና የዳዊት ሥር ተብሎ እንዲጠራ ያበቁት ምክንያቶች አሉ።
ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ዛፍን አንድን ነገር በምሳሌ ለማስረዳት ይጠቀምበታል። ምክንያቱም አንድ ዘር በቅሎ በሚያድግበት ጊዜ ሥሩ ከዋናው ቅርንጫፍ፣ ከሌሎቹ ንዑስ ቅርንጫፎች ወይም ከፍሬው ቀድሞ በመውጣቱ እንዲሁም ሁሉም ክፍሎች የሚያድጉት በሥሩ አማካኝነት በሚያገኙት ድጋፍ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ ኢሳይያስ 37:31 እንዲህ ይነበባል፦ “ያመለጠው የይሁዳ ቤት ቅሬታ ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፣ ወደ ላይም ያፈራል።”—ኢዮብ 14:8, 9፤ ኢሳይያስ 14:29
ሥሩ ጉዳት ቢያገኘው የቀሩት የዛፉ ክፍሎችም ይጎዳሉ። (ከማቴዎስ 3:10፤ 13:6 ጋር አወዳድር።) ስለሆነም ሚልክያስ “የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፣ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ሲል ጽፏል። (ሚልክያስ 4:1) ትርጉሙ ሙሉ በሙሉ መቆረጥ ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ወላጆች (ሥሮች) ይቆረጣሉ፤ ልጆቻቸውም (ቅርንጫፎቻቸውም) አብረው ይቆረጣሉ ማለት ነበር።a ይህም ወላጆች ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ያጎላል። ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች የወደፊት ዕድል የሚወሰነው ወላጆቻቸው በአምላክ ፊት ባላቸው አቋም መሠረት ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:14
በኢሳይያስ 37:31 እና በሚልክያስ 4:1 ላይ ያሉት አገላለጾች የዋናዎቹ ቅርንጫፎች (ወይም በንዑስ ቅርንጫፎች ላይ ያሉት ፍሬዎች) ሕይወት የተመካው በሥሩ ላይ መሆኑን ያሳያሉ። ኢየሱስ “የእሴይ ሥር” ወይም “የዳዊት ሥር” የሆነበትን ምክንያት ለመረዳት የሚያስችለን ቁልፍ ነገር ይህ ነው።
በሥጋዊ መንገድ ሲታይ እሴይና ዳዊት የኢየሱስ ቅድመ አያቶች ነበሩ፤ ማለትም እነርሱ ሥሮች እርሱ ደግሞ ቡቃያ ወይም ግንድ። ኢሳይያስ 11:1 መሢሕ ሆኖ ስለሚመጣው ሲናገር “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከሥሩም ቁጥቋጥ ያፈራል” ብሏል። በተመሳሳይም ኢየሱስ በራእይ 22:16 ላይ ራሱን ‘የዳዊት ዘር ነኝ’ ብሏል። ሆኖም ኢየሱስ እዚያው ላይ “የዳዊት ሥር” ብሎ ራሱን ጠርቷል። ኢየሱስ ይህን ያለው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ የእሴይ እና የዳዊት “ሥር” የሆነበት አንዱ ምክንያት የትውልድ ሐረጋቸው ተጠብቆ ሊኖር የቻለው በኢየሱስ አማካኝነት ስለሆነ ነው። ዛሬ ማንም ሰው ከሌዊ፣ ከዳን ወይም ከይሁዳ ነገድ አንኳ የመጣ መሆኑን ሊያስረዳ አይችልም። ነገር ግን ስለ እሴይ ወይም ስለ ዳዊት የትውልድ መስመሮች በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ስለሚኖር ነው።—ማቴዎስ 1:1–16፤ ሮሜ 6:9
በተጨማሪም ኢየሱስ ሰማያዊ ንጉሥ የመሆን ሥልጣን አግኝቷል። (ሉቃስ1:32, 33፤ 19:12, 15፤ 1 ቆሮንቶስ 15:25) ይህም ከቅድመ አያቶቹ ጋር ያለውን ዝምድና ሳይቀር ይነካል። ዳዊት በትንቢት ኢየሱስን ጌታዬ ብሎታል።—መዝሙር 110:1፤ ሥራ 2:34–36
በመጨረሻም ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ የመሆን ሥልጣን አግኝቷል። በመጪው የሺህ ዓመት ግዛት ውስጥ የኢየሱስ መሥዋዕት ለእሴይና ለዳዊትም ጭምር ጥቅም ያስገኝላቸዋል። በዚያን ጊዜ እሴይና ዳዊት በምድር ላይ የሚኖራቸው ሕይወት የተመካው ለእነርሱም ጭምር “የዘላለም አባት” በሆነው በኢየሱስ ላይ ይሆናል።
እንግዲያው ምንም እንኳ ኢየሱስ ከእሴይና ከዳዊት መሥመር የመጣ ቢሆንም አሁን ያለበት ሁኔታም ሆነ ወደፊት የሚያደርገው ነገር “የእሴይ ሥር” ወይም “የዳዊት ሥር” ተብሎ ለመጠራት ያስችለዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በጥንታዊ የፊንቃውያን አንድ መቃብር ሐውልት ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ ተመሳሳይ አባባል ተጠቅሟል። መቃብሩን ስለሚከፍቱት ሰዎች “ከታች ሥር ከላይም ፍሬ አይኑራቸው!” የሚሉ የእርግማን ቃላት ተጽፈውበት ነበር።—ዊተስ ቴስታሜንተም፣ ሚያዝያ 1961
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.