“እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ”
1-4. (ሀ) በሽፋን ሥዕሉ ላይ ከሚታዩት ነገሮች መካከል በየትኞቹ ብትካፈል ደስ ይልሃል? (ለ) ምን ዓይነት ክብራማ ተስፋ ከፊትህ ተዘርግቷል? (ሐ) እንዲህ ዓይነቱን ተስፋ የሚደግፉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?
በዚህ ብሮሹር ሽፋን ላይ ያሉትን ደስተኛ ሰዎች ተመልከት። ከእነዚህ ሰዎች መካከል መሆን ትፈልጋለህ? ‘እንዴታ’ ብለህ እንደምትመልስ የታወቀ ነው። ምክንያቱም የሰው ዘር በጠቅላላ የሚናፍቀው ሰላምና ስምምነት አላቸው። ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ ሳይል ከሁሉም ዘር የተውጣጡ ሰዎች እንደ አንድ ቤተሰብ ሆነው ይታያሉ። በጣም የሚያስደስት ሁኔታ ይታያል! በመካከላቸው ያለው አንድነት እጅግ የሚያስደንቅ ነው! እነዚህ ሰዎች ስለ ኑክሌር ቦምብ ወይም ስለ ሽብርተኝነት ጨርሶ እንደማይሰጉ ግልጽ ነው። ከዚህ ውብ መናፈሻ በላይ ያለውን ሰማይ ጸጥታ የሚያደፈርሱ የጦር ጄቶች አይኖሩም። ወታደር፣ ታንክ፣ ጠመንጃ የለም። ሌላው ቀርቶ ሥርዓት አስከባሪ ፖሊስ እንኳ የለም። በአጭሩ ጦርነትና ወንጀል የለም። እያንዳንዱ ሰው የግሉ የሆነ ቆንጆ ቤት ስላለው የመኖሪያ ቤት እጥረት የለም።
2 ልጆቹን ተመልከት! ሲጫወቱ ማየት በጣም ያስደስታል። ከእነዚህ እንስሳት ጋር መጫወት እንዴት የሚያስደስት ነው! እንስሳት በሙሉ ከሰዎች ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት ሰላማውያን ስለሆኑ እዚህ መናፈሻ ውስጥ የብረት ወይም የሽቦ አጥር የለም። አንበሳውና የበግ ግልገሏ እንኳ ጓደኛሞች ሆነዋል። ወዲያ ወዲህ የሚበሩትን በቀለማት ያሸበረቁ ወፎች ተመልከት፤ የወፎቹ ዝማሬ ከልጆቹ ሳቅ ጋር ተዳምሮ አካባቢውን ሲሞላው አዳምጥ። የወፎች መያዣ ቀፎ የለም እንዴ? የለም፤ በዚህ አካባቢ ሁሉም በነፃነትና በደስታ ወዲያ ወዲህ መንቀሳቀስ ይችላል። የአበቦቹን ጣፋጭ መዓዛ፣ ጅረቱ ሲፈስ የሚፈጥረውን ድምፅና ሰውነት ደስ የሚያሰኘውን የፀሐይ ሙቀት እስቲ አስበው። ቅርጫቱ ውስጥ ያለው ፍራፍሬ እንዴት ያስጎመጃል! በዚህ ውብ በሆነ የአትክልት ሥፍራ ያለው ነገር ሁሉ በጣም አስደሳች እንደሆነ ሁሉ ፍራፍሬውም በጣም ምርጥ ነው።
3 አንድ ሰው ‘ኧረ ለመሆኑ ያረጁ ሰዎች የታሉ? እነሱስ ከእነዚህ ደስተኛ ሰዎች ጋር መኖር የለባቸውም እንዴ?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። ወደ ወጣትነት ተመልሰው ነው እንጂ አርጅተው የነበሩም ሰዎች በመካከላቸው አሉ። እዚህ መናፈሻ ውስጥ በእርጅና ምክንያት የሚሞት ሰው የለም። ልጅ የሆነ ሰው ወደ ሙሉ ሰውነት ከደረሰ በኋላ አያረጅም። 20 ዓመት የሆነውም ይሁን 200 ዓመት በዚህ መናፈሻ ውስጥ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እያንዳንዳቸው የወጣትነት ውበታቸው ሳይጠፋ በሙሉ ጤንነት ተደስተው ይኖራሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን፣ ይህ መናፈሻ ምድር አቀፍ ስፋት ስለሚኖረው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚያ ይኖራሉ። ምድራችን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ሕይወት የሚኖርባት፣ ሰላም የሰፈነባትና ውበት የተላበሰች ትሆናለች። ምድር በአጠቃላይ ወደ ገነትነት ትለወጣለች። ገነት በመላዋ ምድር ተመልሳ ትቋቋማለች።
4 ይህ እንኳ ‘ለማመን ያስቸግራል’ ብለህ አሰብክ እንዴ? እስቲ በቅድሚያ ማስረጃዎቹን መርምር። በችግር በተሞላው በዚህ የነገሮች ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት በሕይወት የመትረፍና በሽፋኑ ላይ በሚታየው ሥዕል ወደተመሰለችው ገነት የመግባት አጋጣሚ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ ተዘርግቷል።a
ስለ ገነት የሚያብራራ መጽሐፍ
5. (ሀ) ስለ እነዚህ ነገሮች የሚገልጸው መጽሐፍ የትኛው ነው? (ለ) ይህን መጽሐፍ ልዩ የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
5 ስለ እነዚህ ታላላቅ ነገሮችም ሆነ እነዚህ ነገሮች እርግጠኛ ስለ መሆናቸው እስከ ዛሬ ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ይበልጥ ድንቅ በሆነው መጽሐፍ ውስጥ ተብራርቷል። ይህ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የተወሰኑ ክፍሎቹ የዛሬ 3,500 ዓመታት ገደማ የተጻፉ በጣም ጥንታዊ መጽሐፍ ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ ዘመናዊ አኗኗርን በተመለከተ ትክክለኛና ጠቃሚ ምክር በመስጠት ረገድ ወቅታዊ መጽሐፍ ነው። ትንቢቶቹ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ይፈነጥቃሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዛት የተሸጠ አንድም መጽሐፍ የለም፤ መላው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ዋና ዋና ክፍሎቹ ከ2,000 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ወደ 4,000,000,000 በሚገመቱ ቅጂዎች ታትሟል።
6. መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ቅዱስ ከሚታዩ ሌሎች መጻሕፍት የሚለየው ምንድን ነው?
6 የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በስፋት የተሰራጨ ሌላ ቅዱስ መጽሐፍ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን በዕድሜም የሚተካከለው የለም። የእስልምና ሃይማኖት መጽሐፍ የሆነው ቁርአን ከ1,400 ዓመት ያነሰ ዕድሜ ያለው ነው። ቡድሃና ኮንፍዩሼስ የኖሩት ከ2,500 ዓመታት ገደማ በፊት ሲሆን የጻፏቸው መጻሕፍት ዕድሜም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። የሺንቶ ቅዱሳን መጻሕፍት አሁን ባሉበት መልክ የተጠናቀሩት 1,200 ዓመታት ከማይበልጥ ጊዜ በፊት ነው። የሞርሞን መጽሐፍ ዕድሜ 160 ዓመት ብቻ ነው። ከእነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል የትኛውም ቢሆን እንደ መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ልጅ የ6,000 ዓመታት ታሪክ ከመጀመሪያ ጀምሮ በትክክል አይገልጽም። ስለዚህ የመጀመሪያውን ሃይማኖት ማወቅ የምንችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ለሰው ዘሮች ሁሉ የሚሆን ዓለም አቀፍ መልእክት የያዘ ብቸኛ መጽሐፍ ነው።
7. አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ብለዋል?
7 የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጥበብ የተሞላና ጠቃሚ መሆኑን በየትኛውም ብሔርና የኑሮ ደረጃ ውስጥ የሚገኙ አስተዋይ ሰዎች መስክረዋል። የስበትን ሕግ ያገኘው የታወቀው ሳይንቲስት ሰር አይዛክ ኒውተን “መጽሐፍ ቅዱስ ከየትኛውም ሳይንስ ይበልጥ ትክክለኝነቱ የተረጋገጠ መጽሐፍ ነው” ሲል ተናግሯል። “ነፃነት ስጡኝ አለዚያ ግደሉኝ” ሲል በተናገራቸው ቃላት የሚታወቀው አሜሪካዊው የለውጥ አራማጅ ፓትሪክ ሄንሪ “መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ከታተሙት መጻሕፍት ሁሉ ይበልጣል” ሲል ተናግሯል። ታላቁ የህንድ ሊቅ ሞሃንደስ ኬ ጋንዲ እንኳ ለአንድ የብሪታንያ እንደራሴ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር:- “የእኔም ሆነ የእርስዎ አገር ሕዝብ ክርስቶስ በዚህ የተራራ ስብከት በገለጸው ትምህርት ቢመራ የሁለታችንን አገሮች ችግሮች ብቻ ሳይሆን የመላውን ዓለም ችግሮች ለመፍታት እንችላለን።” ጋንዲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከማቴዎስ 5 እስከ 7 ስላሉት ምዕራፎች መናገራቸው ነበር። እነዚህን ምዕራፎች አንብብና ምን ያህል ኃይለኛ መልእክት እንደያዙ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ—የምሥራቃውያን መጽሐፍ
8, 9. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን የምዕራባውያን መጽሐፍ ብሎ መጥራት ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እንዴት ነው? ምን ያህል ጊዜስ ወስዷል? (ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መጻሕፍት ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ለምንድን ነው? (መ) መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ ምን ያህል ሰዎች አገልግለዋል? (ሠ) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ማን መሆኑን በተመለከተ ምን ምስክርነት ሰጥተዋል?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎች እንደሚያስቡት የምዕራባውያን ሥልጣኔ ውጤት ወይም ደግሞ የዚያን አካባቢ ሥልጣኔ የሚያወድስ መጽሐፍ አይደለም። መላው መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ይቻላል የተጻፈው በምሥራቅ አገሮች ውስጥ ነው። የጻፉት ሰዎች በጠቅላላ የምሥራቅ ሰዎች ናቸው። ቡድሃ ከኖረበት ዘመን አንድ ሺህ ዓመታት ቀደም ብሎ በ1513 ከዘአበ በመካከለኛው ምሥራቅ ይኖር የነበረው ሙሴ ዘፍጥረት የተባለውን የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲጽፍ አምላክ በመንፈሱ አነሳሳው። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ከመጀመሪያ መጽሐፍ ጀምሮ እስከ መጨረሻው እስከ ራእይ መጽሐፍ ድረስ እርስ በርሱ የሚስማማ አንድ ወጥ የሆነ ጭብጥ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ያለቀው ቡድሃ ከኖረበት ዘመን ከ600 ዓመታት ገደማ በኋላ በ98 እዘአ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ 66 የተለያዩ መጻሕፍትን የያዘ መሆኑን ታውቃለህ? አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ራሱን የቻለ ቤተ መጻሕፍት ነው!
9 ስለዚህ ከሙሴ ዘመን ጀምሮ 1,600 ዓመታት ርዝመት ባለው ጊዜ ውስጥ 40 የሚያክሉ ሰዎች እርስ በርሱ የሚስማማውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጽፈዋል። እነዚህ ሰዎች ሟች ከሆኑት የሰው ልጆች የበለጠ ኃይል ያለው አካል በመንፈሱ እየመራቸው እንደጻፉ መስክረዋል። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ለትምህርት፣ ለተግሳጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት እንዲሁም በጽድቅ ላለው ምክር የሚጠቅም ነው።”b (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) ሐዋርያው ጴጥሮስም “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ሲል ገልጿል።—2 ጴጥሮስ 1:20, 21፤ 2 ሳሙኤል 23:2፤ ሉቃስ 1:70
10. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ሊቆይ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) በአሁኑ ጊዜም በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
10 መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቆ የቆየበት መንገድ ሌላው በጣም የሚያስደንቅ ነገር ነው። የማተሚያ መሣሪያ የተፈለሰፈው ከ500 ዓመታት ገደማ በፊት ሲሆን እስከዚህ ጊዜ ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ለብዙ ሺህ ዓመታት በእጅ ሲገለበጡ ቆይተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ከአንድ ቅጂ ወደ ሌላ ቅጂ በትጋት ሲገለበጥ የቆየ ጥንታዊ ጽሑፍ አይገኝም። በተደጋጋሚ ጊዜ ከአንድ ቅጂ ወደ ሌላ ቅጂ የተገለበጠ ቢሆንም ይገለበጥ የነበረው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። ከአንዱ ቅጂ ወደ ሌላ በሚገለበጥበት ጊዜ የተፈጸሙት ስሕተቶች በጣም ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ ቅጂዎቹን እርስ በርስ በማመሳከር አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው የመጀመሪያው ቅጂ የያዘውን መልእክት ማወቅ ተችሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን “ቅዱሳን ጽሑፎች ልክ በመጀመሪያው እንደተጻፉት ይዘታቸውን ሳይለውጡ ወደ እኛ መምጣታቸውን አጠራጣሪ ሊያደርግ ይችል የነበረው የመጨረሻው መሠረት ተወግዷል” ሲሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ ወደ 16,000 የሚጠጉ በእጅ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ወይም ከፊል ቅጂዎች የሚገኙ ሲሆን አንዳንዶቹ እንዲያውም ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ከተጻፈባቸው ከዕብራይስጥ፣ ከአረማይክና ከግሪክኛ ቋንቋዎች በሁሉም የምድር ቋንቋዎች ማለት ይቻላል በትክክል ተተርጉሟል።
11. ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር የሚስማሙ ዘመናዊ ግኝቶች የትኞቹ ናቸው?
11 አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ አይደለም በማለት ውድቅ ሊያደርጉት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ በቅርብ ዓመታት አርኪኦሎጂስቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱት ቦታዎች ይገኙ የነበሩ ጥንታዊ ከተሞችን ፍርስራሽ በመቆፈር በጣም ጥንታዊ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችና ቦታዎች በትክክል የነበሩ መሆናቸውን በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጡ የተቀረጹ ጽሑፎችንና ሌሎች ማስረጃዎችን አግኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ 4,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በኖኅ ዘመን እንደደረሰ የሚገልጸውን የጥፋት ውኃ የሚያመለክቱ በርካታ ማስረጃዎችን አርኪኦሎጂስቶች ቆፍረው አውጥተዋል። ፕሪንስ ሚካሳ የተባሉ አንድ የታወቁ አርኪኦሎጂስት ይህን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “በእርግጥ የጥፋት ውኃ ነበርን? . . . የጥፋት ውኃ ደርሶ እንደነበረ በሚገባ ተረጋግጧል።”c
የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ
12. (ሀ) አንዳንድ ፌዘኞች ስለ አምላክ ምን ይላሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን እንደ አባት አድርጎ የሚጠራው ለምንድን ነው? (ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም ማን ነው ይላል?
12 አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያፌዙ ሁሉ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ መኖሩን በተመለከተም የሚያሾፉ ሰዎች አሉ። (2 ጴጥሮስ 3:3-7) ‘አምላክን ላየው ስለማልችል እንዴት በእሱ ላምን እችላለሁ? ከሰዎች የሚበልጥ በዓይን የማይታይ ፈጣሪ በእርግጥ መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ አለ? አምላክ በማንኛውም ነገር ውስጥ የሚገኝ አይደለም እንዴ?’ ብለው ይጠይቃሉ። ሌሎች ደግሞ ‘አምላክም ሆነ ቡድሃ የሚባል ነገር የለም’ ይላሉ። ይሁን እንጂ ሁላችንም ምድራዊ በሆነ አባት አማካኝነት ሕይወት እንዳገኘን ሁሉ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንም ይሖዋ የተባለ ስም ካለው ሰማያዊ አባት ወይም ፈጣሪ ሕይወት እንዳገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—መዝሙር 83:18 NW፤ 100:3፤ ኢሳይያስ 12:2፤ 26:4
13. ይሖዋ ራሱን ለሰው ልጆች የገለጸባቸው ሁለት መንገዶች ምንድን ናቸው?
13 ይሖዋ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ራሱን ለሰዎች ገልጿል። ከእነዚህም መካከል ግንባር ቀደሙን ሚና የሚጫወተው ይሖዋ እውነትንና ዘላለማዊ ዓላማዎቹን የገለጸበት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ዮሐንስ 17:17፤ 1 ጴጥሮስ 1:24, 25) ሌላው መንገድ ደግሞ የፍጥረት ሥራው ነው። ብዙ ሰዎች በዙሪያቸው የሚገኙትን አስደናቂ ነገሮች በመመልከት ታላቅ ባሕርይው በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ የሚንጸባረቅ አንድ ፈጣሪ አምላክ መኖር አለበት ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።—ራእይ 15:3, 4
14. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን ይነግረናል?
14 ይሖዋ አምላክ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ነው። እሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም የሚኖር ታላቅ መንፈስ ነው። (ዮሐንስ 4:24፤ መዝሙር 90:1, 2) “ይሖዋ” የሚለው ስሙ ለፍጥረቶቹ ባለው ዓላማ ላይ የሚያተኩር ነው። ክፉዎችን በማጥፋትና እሱን የሚያፈቅሩ ሰዎች ከጥፋት ድነው ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ በማድረግ ይህን ታላቅ ስሙን ከነቀፋ ነፃ ማድረግ ዓላማው ነው። (ዘጸአት 6:2-8፤ ኢሳይያስ 35:1, 2) ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ ይህን የማድረግ ኃይል አለው። የጠቅላላው አጽናፈ ዓለም ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ተራ ከሆኑ ብሔራዊ አማልክትና ጣዖታት በጣም የላቀ ነው።—ኢሳይያስ 42:5, 8፤ መዝሙር 115:1, 4-8
15. ምሁራን በፍጥረት ላይ ያካሄዱት ጥናት ወደ ምን መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል?
15 በቅርብ መቶ ዓመታት ሳይንቲስቶች የፍጥረት ሥራዎችን ለማጥናት በርካታ ጊዜ አውለዋል። ይህስ ወደ ምን መደምደሚያ አደረሳቸው? በኤሌክትሪክ ምርምር ግንባር ቀደም ከሆኑት ሰዎች አንዱ የሆነው እንግሊዛዊው የፊዚክስ ሊቅ ሎርድ ኬልቪን “ሳይንስን ይበልጥ ጠልቀን በመረመርን መጠን አምላክ የለም ከሚለው አስተሳሰብ የዚያኑ ያህል እየራቅን እንደምንሄድ አምናለሁ” ሲል ተናግሯል። በትውልዱ አውሮፓዊ የሆነው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን አምላክ የለም የሚል አመለካከት እንደነበረው ቢነገርም እንዲህ ሲል አምኗል:- “ለእኔ . . . ገና ብዙም ስላልተረዳነው ስለ አስደናቂው የአጽናፈ ዓለም አወቃቀር ማሰቡና በተፈጥሮ ላይ ከተንጸባረቀው ጥበብ ውስጥ በጣም ኢምንቷን እንኳ ለመረዳት በትሕትና ጥረት ማድረጉ ብቻ በቂዬ ነው።” አሜሪካዊው ሳይንቲስትና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ አርተር ሆሊ ኮምተን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በሚገባ የተደራጀው አጽናፈ ዓለም ‘በመጀመሪያ እግዚአብሔር’ የሚለውን እስከ ዛሬ ከተነገሩት አነጋገሮች ሁሉ ይበልጥ የላቀ ሥፍራ የሚሰጠውን ታላቅ አነጋገር እውነተኝነት ይመሰክራል።” የመጽሐፍ ቅዱስን የመክፈቻ ቃላት መጥቀሳቸው ነው።
16. አጽናፈ ዓለም የአምላክን የፈጠራ ጥበብና ኃይል አጉልቶ የሚያሳየው እንዴት ነው?
16 የኃያላን መንግሥታት መሪዎች ባላቸው የአእምሮ ችሎታና በጠፈር ምርምር በደረሱባቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች ይኩራሩ ይሆናል። ነገር ግን የእነሱ ሳተላይቶች በምድር ዙሪያ ከምትሽከረከረው ከጨረቃና በፀሐይ ዙሪያ ከሚሽከረከሩት ፕላኔቶች ጋር ሲነጻጸሩ በጣም ኢምንት ናቸው! ይሖዋ ከፈጠራቸው በቢልዮን ከሚቆጠሩት ጋላክሲዎች ጋር ሲወዳደሩ እነዚህ ሟች የሆኑ ሰዎች የሠሯቸው ነገሮች በእርግጥም ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም። እነዚህ ጋላክሲዎች እያንዳንዳቸው ከእኛ ፀሐይ ጋር የሚመሳሰሉ በቢልዮን የሚቆጠሩ ፀሐዮችን የያዙ ሲሆን ይሖዋ በቡድን በቡድን አድርጎ በጠፈር ላይ ቁጥር ሥፍር ለሌለው ጊዜ አስቀምጧቸዋል! (መዝሙር 19:1, 2፤ ኢዮብ 26:7, 14) ይሖዋ ሰዎችን እንደ አንበጣ፣ ኃያላን መንግሥታትን ደግሞ ‘እንደ ምናምን’ መቁጠሩ የሚያስደንቅ አይደለም።—ኢሳይያስ 40:13-18, 22
17. በፈጣሪ ማመን ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 የምትኖርበት ቤት አለህ? ይህን ቤት ምናልባት አንተ ራስህ አልሠራኸው ወይም ማን እንደሠራው አታውቅ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ቤቱን ማን እንደሠራው አለማወቅህ ቤቱ አንድ ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው የሠራው የመሆኑን ሐቅ እንዳትቀበል አያግድህም። ቤቱ ራሱን በራሱ ነው የሠራው ብሎ ማሰብ ደግሞ ትልቅ ሞኝነት ይሆናል! ታላቁ አጽናፈ ዓለምና በውስጡ የሚገኙት ነገሮች አሠራር ይህ ነው የማይባል ታላቅ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ በመሆኑ ጥሩ የማሰብ ችሎታ ያለው ፈጣሪ መኖር አለበት ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይሆንምን? በእርግጥም፣ በልቡ “አምላክ የለም” የሚል አእምሮ የጎደለው ሰው ብቻ ነው።—መዝሙር 14:1፤ ዕብራውያን 3:4
18. አምላክ አንድ ራሱን የቻለ አካል እንደሆነና ውዳሴ እንደሚገባው የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 አበቦች፣ ወፎች፣ እንስሳት፣ አስገራሚ ፍጥረት የሆነው ሰው፣ የሕይወትና የመወለድ ተአምር በአጠቃላይ በዙሪያችን ያሉት አስደናቂ ነገሮች በሙሉ እነሱን ስለ ፈጠረው በዓይን የማይታይ ታላቅ ጠቢብ የሚመሠክሩ ናቸው። (ሮሜ 1:20) የማሰብ ችሎታ ካለ አእምሮ አለ። አእምሮ ካለ ደግሞ አንድ ሕያው አካል አለ። እንግዲያው የዚህ ታላቅ አእምሮ ባለቤት የሁሉም ነገሮች ፈጣሪና የሕይወት ሁሉ ምንጭ የሆነው ታላቁ ሕያው አካል ነው። (መዝሙር 36:9) ፈጣሪ በእርግጥም ሊወደስና ሊመለክ ይገባዋል።—መዝሙር 104:24፤ ራእይ 4:11
19. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የትኛውም መንግሥት ቢሆን አምላክ በጦርነት ድል ሰጠኝ ብሎ መናገር የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) መንግሥታት በሚያደርጉት ጦርነት ውስጥ አምላክ ምንም ተካፋይነት የሌለው ለምንድን ነው?
19 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አማካኝነት በደረሰባቸው በጣም አሳዛኝ ሁኔታ የተነሳ በአምላክ ላይ የነበራቸው እምነት የተናጋባቸው ሰዎች አሉ። በዚያን ወቅት የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንትም ሆነ የምሥራቃውያን ሃይማኖት ተከታይ የሆነ አገር ሁሉ የየራሱን “አምላክ” እርዳታ ይጠይቅ ነበር። አንዳንዶቹ አገሮች ድል እንዲመቱና አንዳንዶቹ ደግሞ ድል እንዲጎናጸፉ ያደረገው “አምላክ” ነው ሊባል ይችላልን? መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ አንዳቸውም ቢሆኑ ወደ እውነተኛው አምላክ ለእርዳታ እንዳልጮኹ ይገልጻል። የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ በመንግሥታት መካከል ለተፈጠረው ብጥብጥና ጦርነት ፈጽሞ ተጠያቂ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 14:33) የእሱ አሳብ ከዚህ ምድር ፖለቲካዊና ወታደራዊ መንግሥታት አሳብ ጨርሶ የራቀ ነው። (ኢሳይያስ 55:8, 9) በመሆኑም እውነተኛው ሃይማኖትና የይሖዋ አምልኮ መንግሥታት በሚያደርጉት ጦርነት ውስጥ ምንም ተካፋይነት የለውም። ይሖዋ ከብሔራዊ አማልክት ጨርሶ የተለየ አምላክ ነው። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰላም ወዳድ ወንዶችና ሴቶች የሚያመልኩት አምላክ በመሆኑ አምሳያ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ ነው።’ (ሥራ 10:34, 35) በየትኛውም ብሔር ውስጥ የሚገኙ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በመማርና የሰው ዘሮችን ሁሉ የፈጠረውን እውነተኛ ‘የሰላም አምላክ’ በማምለክ ላይ ናቸው።—ሮሜ 16:20፤ ሥራ 17:24-27
20. ሕዝበ ክርስትና ጨርሶ ከክርስትና የራቀችና ፀረ አምላክ እንደሆነች የሚያሳየው ምንድን ነው?
20 አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን በሚሉት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ ያለውን መከፋፈልና ግብዝነት ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም ‘የኑክሌር የጦር መሣሪያዎችን ለማከማቸት በመሯሯጥ ላይ ያሉት በመጽሐፍ ቅዱስ እንመራለን የሚሉ ብሔራት አይደሉም እንዴ? ታዲያ እኔ እንዴት በመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ላምን እችላለሁ?’ ብለው ይናገራሉ። ሐቁ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜም የማይለወጥ እውነት ሆኖ ቢቀጥልም የሕዝበ ክርስትና መንግሥታትና የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስትና የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ መሆኑ ነው። ክርስቲያን ነን ብለው መናገራቸው ግብዝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው ነገር ግን ትምህርቶቹን አይታዘዙም። የመጀመሪያው የአቶም ቦምብ በሂሮሺማ ላይ እንዲጣል ትእዛዝ የሰጡት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአንድ ወቅት ዓለምን ከገጠማት ቀውስ የሚያወጣ “እንደ ኢሳይያስ ወይም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ያለ ሰው ብናገኝ ምናለ!” ሲሉ ተናግረው ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው ኢሳይያስ ጋር የሚስማሙ ቢሆኑ ኖሮ ፈጽሞ የአቶም ቦምብ እንዲጣል አያደርጉም ነበር። ምክንያቱም ኢሳይያስ ‘ሰይፍ ወደ ማረሻነት፣ ጦር ወደ ማጭድነት እንዲለወጥ’ የሚፈልግ ሰው ነበር። ከዚህም በላይ “እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና” ሲል የጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ጳውሎስ ነው። (ኢሳይያስ 2:4፤ 2 ቆሮንቶስ 10:3, 4) የሕዝበ ክርስትና መንግሥታት ግን የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ የተሞላበት ምክር ከመከተል ይልቅ ራሳቸውን በራሳቸው ሊያጠፉ ወደሚችሉበት የጦር መሣሪያ እሽቅድድም ውስጥ ገብተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመሩ ክርስቲያኖች እንደሆኑ አድርገው የሚናገሩት ሁሉ ሐሰት ነው። ፈቃዱን ሳያደርጉ በመቅረታቸው የአምላክን ፍርድ መቀበል አለባቸው።—ማቴዎስ 7:18-23፤ ሶፎንያስ 1:17, 18
የይሖዋ ፍጥረታትና ተአምራት
21. አምላክ የፈጸማቸውን ተአምራት መጠራጠር ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው?
21 ይሖዋ ይፈጥራል፣ ተአምራትንም ያደርጋል። ውኃው ወደ ደም ስለመለወጡ፣ ቀይ ባሕር ስለመከፈሉ፣ ኢየሱስ ከድንግል ስለመወለዱና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተመዘገቡ ሌሎች ተአምራት አስበህ ታውቃለህ? ሰው የማሰብ ችሎታው ውስን በመሆኑ ፀሐይ በየቀኑ የምትወጣበትንና የምትጠልቅበትን ተአምር ሙሉ በሙሉ መረዳት እንዳልቻለ ሁሉ ከእነዚህ ተአምራት አንዳንዶቹ እንዴት እንደተፈጸሙ ጨርሶ ላይገባው ይችላል። የሰው አፈጣጠር ራሱ አንድ ተአምር ነው። ዛሬ ያሉት ሰዎች ይህን ተአምር አላዩም፤ ይሁን እንጂ ዛሬ የእነሱ በሕይወት መኖር ራሱ ለዚህ ነገር ማስረጃ በመሆኑ ይህ ተአምር እንደተፈጸመ ያውቃሉ። እርግጥ ሕይወት በጠቅላላውና መላው አጽናፈ ዓለም በአንድነት ምንጊዜም ሲታዩ የሚኖሩ ተአምራት ናቸው። ታዲያ ተመሳሳይ የሆኑ ተአምራት ዛሬ ባያስፈልጉም እንኳ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ጥንት ስለ ፈጸማቸው ተአምራት ሲነግረን እንጠራጠራለንን?
22. ስለ መጀመሪያው የአምላክ ፍጥረት ግለጽ።
22 የይሖዋ የፍጥረት ሥራ በጠቅላላ ተአምርና ድንቅ ነው! ይሁን እንጂ የመጀመሪያ የፍጥረት ሥራው ከሁሉም ይበልጥ አስደናቂ ነበር። ይህ የፍጥረት ሥራው ለአምላክ “በኩር” የሆነው መንፈሳዊ ልጅ ነው። (ቆላስይስ 1:15) ይህ በሰማይ የሚገኝ የአምላክ ልጅ “ቃል” ተብሎ ተጠርቷል። ከተፈጠረ ከብዙ ዘመናት በኋላ ወደ እዚህ ምድር መጥቶ ‘የሰው ልጅ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ’ ተብሎ ተጠራ። (1 ጢሞቴዎስ 2:5) ከዚያም ስለ እሱ እንዲህ ተብሏል:- “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን።”—ዮሐንስ 1:14
23. (ሀ) በአምላክና በልጁ መካከል ያለው ዝምድና እንዴት ሊገለጽ ይችላል? (ለ) ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ምን ፈጥሯል?
23 በይሖዋና በልጁ መካከል ያለውን ግንኙነት በአንድ የወርክ ሾፕ ባለቤትና በወርክ ሾፑ ውስጥ በሚሠራ ልጁ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር ማመሳሰል ይቻላል፤ አባትዬው የዕቃዎችን ንድፍ ያወጣል ልጁ ደግሞ በዚያ መሠረት ዕቃዎችን ይሠራል። ይሖዋ የሥራ ረዳቱ በሆነው የበኩር ልጁ አማካኝነት የአምላክ ልጆች የሆኑትን ሌሎች ብዙ መንፈሳዊ ፍጥረታት ፈጠረ። ከዚያም እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ዋና ሠራተኛ የሆነው የይሖዋ ልጅ ሰማይንና አሁን እኛ የምንኖርበትን ምድር ሲፈጥር በመመልከታቸው በጣም ተደስተዋል። እነዚህ ነገሮች በፍጥረት የተገኙ መሆናቸውን ትጠራጠራለህ? ይህ የፍጥረት ሥራ ከተከናወነ ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ለአንድ ታማኝ ሰው እንዲህ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር:- “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር። አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፣ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ።”—ኢዮብ 38:4, 7፤ ዮሐንስ 1:3
24. (ሀ) ከይሖዋ ምድራዊ ፍጥረታት ሁሉ የላቀው የትኛው ነው? በምንስ ረገድ? (ለ) ሰው ከእንስሳት ተሻሽሎ የመጣ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ የማይሆነው ለምንድን ነው?
24 ይሖዋ ዕፅዋትን፣ ዛፎችን፣ አበቦችን፣ ዓሦችን፣ ወፎችንና እንስሳትን ጨምሮ ቀስ በቀስ ቁሳዊ አካል ያላቸው ሕያዋን ነገሮች በዚህ ምድር ላይ ፈጠረ። (ዘፍጥረት 1:11-13, 20-25) ከዚያም አምላክ ዋና ሠራተኛው ለሆነው ረዳቱ እንዲህ አለው:- “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ . . . እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍጥረት 1:26, 27) የመጀመሪያ ሰው እንደ ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ኃይል ያሉት የአምላክ ዋና ዋና ባሕርያት እንዲኖሩት ተደርጎ በአምላክ መልክ የተፈጠረ ስለሆነ ከእንስሳት በእጅጉ የሚበልጥ ነበር። ሰው የማመዛዘን፣ ለወደፊት እቅድ የማውጣትና አምላክን የማምለክ ችሎታ ስላለው ከሌሎች እንስሳት የተለየ ነው። እንስሳት በተፈጥሮ እየተመሩ ይኖራሉ እንጂ የማመዛዘን ችሎታ የላቸውም። ፈጣሪ የለም፤ ብዙ ድንቅ ስጦታዎችን የተቸረውና የማሰብ ችሎታ ያለው ሰው የማሰብ ችሎታ ከሌላቸው ዝቅተኛ እንስሳት ተሻሽሎ የመጣ ነው ብሎ መናገር እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!—መዝሙር 92:6, 7፤ 139:14
25, 26. (ሀ) ሰው ምን ታላቅ ተስፋ ከፊቱ ተዘርግቶለት ነበር? (ለ) ምድር በሕዝብ ብዛት ትጨናነቃለች የሚል ስጋት የማይኖረው ለምንድን ነው?
25 አምላክ ሰውን “በምሥራቅ በዔደን ገነት” አኖረው። ምንም እንኳ በወቅቱ በዚያ የነበሩት ሁለት ሰዎች ማለትም አዳምና ሚስቱ ብቻ ቢሆኑም ልክ በዚህ ብሮሹር ሽፋን ላይ ከሚታየው ጋር ተመሳሳይ የሆነች አስደሳች የአትክልት ቦታ ነበረች። በኖኅ ዘመን በደረሰው የውኃ መጥለቅለቅ ስለጠፋች ያቺ የመጀመሪያዋ ገነት በአሁኑ ጊዜ የለችም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በስም የሚጠቅሳቸው በውስጧ ይፈሱ የነበሩት ወንዞች አሁንም ስላሉ ኤደን ገነት በመካከለኛው ምሥራቅ በየት አካባቢ ትገኝ እንደነበረ መገመት ይቻላል። (ዘፍጥረት 2:7-14) ሰው ይህችን የአትክልት ቦታ እንደ ማዕከል አድርጎ የመጠቀምና የአትክልት ቦታዋን በማስፋት ምድርን በጠቅላላ ገነት የማድረግ ትልቅ አጋጣሚ ነበረው።—ኢሳይያስ 45:12, 18
26 አምላክም ሆነ ልጁ ሠራተኛ እንደመሆናቸው መጠን አምላክ ለሰውም በዚህ ምድር ላይ ሥራ ሰጥቶት ነበር። (ዮሐንስ 5:17) ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ማለትም ለአዳምና ሔዋን እንዲህ አላቸው:- “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) ይህ ማለት ሰው ተባዝቶ ምድርን ከሞላም በኋላ ከመጠን በላይ እስክትጨናነቅ ድረስ መባዛቱን ይቀጥላል ማለት ነውን? አይደለም። አንድ ሰው በስኒ ሻይ እንድትቀዳለት ቢጠይቅህ ሻዪው ስኒውን ሞልቶ ጠረጴዛው ላይ እስኪፈስ ድረስ ዝም ብለህ መቅዳትህን አትቀጥልም። ስኒው ሲሞላ መቅዳትህን ታቆማለህ። በተመሳሳይም ይሖዋ “ምድርን ሙሉአት” ሲል ለሰው የሰጠው ትእዛዝ ሰዎች ምንም ሳይጨናነቁ ምድርን እንዲሞሏት ካደረገ በኋላ በምድር ላይ ያለው የሰዎች የመዋለድ ሂደት እንደሚቆም ያመለክታል። ፍጹም በሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ይህ ችግር አይፈጥርም። የሕዝብ ብዛት ችግር የሚፈጥረው ዛሬ ባለው ፍጽምና በሌላቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ውስጥ ብቻ ነው።
አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲኖሩ የፈቀደው ለምንድን ነው?
27. አሁን መልስ የሚያስፈልጋቸው የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው?
27 የአምላክ ዓላማ ገነት የሆነች ምድር ለማዘጋጀት ከሆነ ዛሬ ምድር በክፋት፣ በመከራና በሐዘን የተሞላችው ለምንድን ነው? አምላክ ሁሉን ቻይ ከሆነ እነዚህ ነገሮች ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥሉ የፈቀደው ለምንድን ነው? ከችግሮቻችን ሁሉ የምንገላገልበት ተስፋ አለ? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
28. ገነት ወደሆነችው የአትክልት ቦታ ዓመፅ የገባው እንዴት ነው?
28 የሰው ልጆች መከራ የጀመረው ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች መካከል አንዱ በይሖዋ ሉዓላዊነት ወይም የመግዛት ሥልጣን ላይ ባመፀበት ጊዜ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮሜ 1:20፤ መዝሙር 103:22 ባለ ማጣቀሻው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ይህ መልአክ ሰው ሲፈጠር በማየታቸው በጣም ከተደሰቱት መላእክት መካከል አንዱ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የስስት ምኞትና ኩራት በልቡ ውስጥ ሥር ሰደዱ፤ ከዚያም አዳምና ሔዋን ፈጣሪያቸውን ይሖዋን ከማምለክ ይልቅ እሱን እንዲያመልኩ የማድረግ ምኞት አደረበት። አንድ ሰው አሻንጉሊት እየተናገረ እንዳለ ማስመሰል እንደሚችል ሁሉ ይህ መልአክም በእባብ አማካኝነት በመናገር ሔዋን ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ላይ እንድታምፅ አደረጋት። ከዚያም ባሏ አዳምም በዓመፅዋ ተባበራት።—ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:1-6፤ ያዕቆብ 1:14, 15
29. (ሀ) እልባት የሚያሻቸው ምን አከራካሪ ጉዳዮች ተነሱ? (ለ) አምላክ ለዚህ አከራካሪ ጉዳይ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው? (ሐ) ለሰይጣን ስድብ ምላሽ በማስገኘት ረገድ አንተም ድርሻ ሊኖርህ የሚችለው እንዴት ነው?
29 ይህ ዓመፀኛ መልአክ “የቀደመው እባብ” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 12:9፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3) በተጨማሪም ሰይጣን ማለትም “ተቃዋሚ” እና ዲያብሎስ ማለትም “ስም አጥፊ” የሚል ስም ተሰጥቶታል። ይሖዋ ምድርን መግዛቱ ትክክለኛና ጽድቅ የመሆኑን ጉዳይ አጠያያቂ አደረገ፤ እንዲሁም ሰይጣን ሰዎችን ሁሉ ከእውነተኛው አምልኮ ዞር እንዲሉ ማድረግ እችላለሁ በማለት አምላክን ተገዳደረ። በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ማግኘት ይችል ዘንድ ሰይጣን ያስነሳውን ግድድር ለማረጋገጥ እንዲሞክር አምላክ 6,000 ዓመታት ያክል ፈቀደለት። ሰው ያለ አምላክ ራሱን በራሱ ለመምራት ያደረገው ሙከራ በሚያሳዝን ሁኔታ ሳይሳካ ቀረ። ሆኖም የእምነት ሰዎች ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን ተቋቁመው ለአምላክ የጸና አቋም በመያዝ የይሖዋ ትክክለኝነትና የዲያብሎስ ውሸታምነት እንዲረጋገጥ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል ኢየሱስ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። (ሉቃስ 4:1-13፤ ኢዮብ 1:7-12፤ 2:1-6፤ 27:5) አንተም ከአምላክ ጎን በመቆም የጸና አቋም ልትይዝ ትችላለህ። (ምሳሌ 27:11) ይሁን እንጂ እኛን የሚያጠቃን ጠላት ሰይጣን ብቻ አይደለም። ሌላ ምን ጠላት አለ?
ጠላት የሆነው ሞት
30. ሰው ባለመታዘዙ ምክንያት ስለተወሰነበት ቅጣት ቅዱሳን ጽሑፎች ምን ይላሉ?
30 አምላክ አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት ሞት መሆኑን ገልጿል። ይሖዋ በመጀመሪያዋ ሴት ላይ የፍርድ ብያኔውን ሲያስተላልፍ እንዲህ አለ:- “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።” ለአዳም ደግሞ እንዲህ አለው:- “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።” (ዘፍጥረት 3:16-19) ዓመፀኛ የሆኑት ባልና ሚስት ገነት ከሆነው አስደሳች አካባቢ ወዳልለማው መሬት ተባረሩ። ከጊዜ በኋላ ሞቱ።—ዘፍጥረት 5:5
31. ኃጢአት ምንድን ነው? በሰው ዘሮችስ ላይ ምን ውጤት አስከትሏል?
31 አዳምና ሔዋን ልጆችን መውለድ የጀመሩት የፍጽምናን ደረጃ ካጡ በኋላ ነው። ዛሬ ያሉት ሰዎች ሁሉ አለፍጽምናን የወረሱ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ስለሆኑ ሁሉም ይሞታሉ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሁኔታውን በዚህ መንገድ ይገልጸዋል:- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” “ኃጢአት” ምንድን ነው? የፍጹምነትን ወይም የምሉዕነትን ደረጃ አለማሟላት ማለት ነው። ይሖዋ አምላክ ፍጽምና የጎደለው ምንም ነገር እንዲኖር አይፈልግም። ሁሉም ሰዎች ከመጀመሪያው ሰው ማለትም ከአዳም ኃጢአትንና አለፍጽምናን ስለወረሱ በላያቸው ላይ ‘ሞት ነግሦአል።’ (ሮሜ 5:12, 14) ፍጽምና ያጣው የሰው ልጅ ሌሎች እንስሳት እንደሚሞቱት ሁሉ እሱም ይሞታል።—መክብብ 3:19-21
32. መጽሐፍ ቅዱስ እኛ የወረስነውን ሞት እንዴት አድርጎ ይገልጸዋል?
32 “ሞት” ምንድን ነው? ሞት የሕይወት ተቃራኒ ነው። ሰው ታዛዥ ቢሆን ኖሮ አምላክ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከፊቱ ዘርግቶለት ነበር። ሆኖም ሳይታዘዝ በመቅረቱ ሞት ተፈረደበት፤ ሲሞት የማይሰማ የማይለማ በድን ይሆናል ማለት ነው። አምላክ የሰውን ሕይወት ወደ መንፈሳዊ ዓለም እንደሚያሻግር ወይም ሳይታዘዝ ከቀረና ከሞተ ደግሞ ወደ እሳታማ “ሲኦል” ውስጥ እንደሚከት ምንም የተናገረው ነገር የለም። ሰውን “ሞትን ትሞታለህ” ሲል አስጠንቅቆት ነበር። “ሞትን አትሞቱም” ሲል የዋሸው ነፍሰ ገዳይ የሆነው ዲያብሎስ ነው። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:4፤ ዮሐንስ 8:44) ሰዎች ሁሉ ከአዳም የወረሱት ሞት ወደ አፈርነት እንዲለወጡ የሚያደርግ ነው።—መክብብ 9:5, 10፤ መዝሙር 115:17፤ 146:4 NW
33. (ሀ) የሰው ዘርና ይህች ምድር ምን ክብራማ ጊዜ ይጠብቃቸዋል? (ለ) ይሖዋ በልጁ አማካኝነት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ምን ሦስት ነገሮች ያከናውናል?
33 እንግዲያው ሰው ሲሞት ወደፊት ምንም ተስፋ የለውም ማለት ነውን? አስደሳች ተስፋ አለው! አምላክ አሁን ሞተው ያሉትን ጨምሮ ለሰው ልጆች በጠቅላላ ገነት የሆነች ምድር ለመስጠት ያለው ዓላማ በፍጹም እንደማይከሽፍ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ሰማይ ዙፋኔ ነው፣ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት።” “የእግሬንም ስፍራ አከብራለሁ።” (ኢሳይያስ 66:1፤ 60:13) ይሖዋ ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ የሰው ዘር ዓለም በልጁ አማካኝነት ሕይወት ያገኝ ዘንድ ቃል የሆነውን ልጁን ወደዚህ ምድር ልኮታል። (ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 4:9) ቀጥሎ የምናያቸው ይሖዋ በልጁ አማካኝነት የሚያከናውናቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እነሱም (1) ከሞት መዳፍ እንድንላቀቅ ማድረግ (2) የሞቱትን ወደ ሕይወት መመለስ እና (3) መላውን የሰው ዘር የሚያስተዳድር ፍጹም የሆነ መንግሥት ማቋቋም ናቸው።
ከሞት መላቀቅ
34, 35. (ሀ) ሰው ከሞት ሊዋጅ የሚችለው እንዴት ብቻ ነው? (ለ) ቤዛ ምንድን ነው?
34 ጥንት የነበሩ የአምላክ ነቢያት ሰው ያለመሞት ባሕርይ አለው የሚል እምነት አልነበራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ከሞት ‘እንደሚቤዣቸው’ በሰጠው ተስፋ ላይ ሙሉ ትምክህት እንዳላቸው ገልጸዋል። (ሆሴዕ 13:14) ሆኖም ሰው ከሞት ባርነት መላቀቅ የሚችለው እንዴት ነው? ፍጹም የሆነው የይሖዋ ፍትሕ “ነፍስ በነፍስ፣ ዓይን በዓይን፣ ጥርስ በጥርስ” እንዲከፈል የሚጠይቅ ነበር። (ዘዳግም 19:21) ስለዚህ አዳም ሆን ብሎ በአምላክ ላይ በማመፅ ለሰው ዘር በሙሉ ሞትን ስላወረሰና ሰብዓዊ ፍጽምናን ስላጣ አዳም ያጣውን መልሶ ለመግዛት ፍጹም ሕይወቱን መክፈል የሚችል ሌላ ፍጹም ሰው በአዳም ምትክ የግድ ያስፈልግ ነበር።
35 ‘አንድ ነገር ቢጠፋ ወይም ቢሰበር ተመሳሳዩን መክፈል’ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ትክክለኛ መሠረታዊ ደንብ ነው። “ቤዛ መክፈል” የሚለው አነጋገር በጣም የተለመደ ነው። ለመሆኑ ቤዛ ምንድን ነው? “አንድን ሰው ወይም ነገር ከምርኮ ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ነው። ስለሆነም የጦር ምርኮኞች ወይም በባርነት ስር የሚገኙ ሰዎች በለውጡ አንድ ተመጣጣኝ ነገር ተደርጎ ነፃ እንዲወጡ በሚደረግበት ጊዜ ተቤዡ ይባላል። . . . ለሌላኛው ወገን በምትክነት ወይም በለውጥ የሚሰጠው ማንኛውም ነገር ነፃ ለወጣው ግለሰብ ቤዛ ነው።”d አዳም ኃጢአት ከሠራበት ጊዜ ጀምሮ መላው የሰው ዘር በአለፍጽምናና በሞት ታስሮ ስለሚገኝ ልክ እንደ ጦር ምርኮኞች ወይም ለባርነት እንደተሸጡ ሰዎች ሆኖ ነበር። የሰው ዘሮችን ለማስለቀቅ ቤዛ መከፈል ነበረበት። የቤዛውን ዋጋ ተመጣጣኝነት በተመለከተ አሁንም ሆነ ወደፊት ውዝግብ እንዳይነሳ ለማድረግ ከአዳም ጋር እኩል የሆነ አንድ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መሥዋዕት እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነበር።
36. ይሖዋ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ቤዛ አድርጎ ያዘጋጀው እንዴት ነው?
36 ሆኖም እንዲህ ዓይነት ፍጹም ሰው ከየት ሊገኝ ይችላል? ሁሉም ሰዎች ፍጽምናውን ያጣው የአዳም ዝርያዎች እንደመሆናቸው መጠን ፍጽምና የሌላቸው ሆነው ተወልደዋል። “ወንድም ወንድሙን አያድንም፣ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውንም ለእግዚአብሔር አይሰጥም።” (መዝሙር 49:7) ይሖዋ ለሰው ዘር ባለው ጥልቅ ፍቅር ተገፋፍቶ የሚያስፈልገውን ቤዛ አቀረበ፤ እንዲያውም ይህን ተፈላጊ መሥዋዕት ለማቅረብ ቤዛ አድርጎ የተጠቀመው ውድ የሆነውን “የበኩር” ልጁን ነው። ቃል ተብሎ የሚጠራውን የዚህን መንፈሳዊ ልጅ ፍጹም ሕይወት ማርያም ተብላ ወደምትጠራ አንዲት ድንግል አይሁዳዊት ማኅፀን አዛወረው። ይህች ወጣት አይሁዳዊት ሴት አረገዘችና ጊዜው ሲደርስ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ይህም ልጅ “ኢየሱስ” የሚል ስም ተሰጠው። (ማቴዎስ 1:18-25) የሕይወት ፈጣሪ የሆነው አምላክ እንዲህ ዓይነት አስገራሚ ተአምር ለመፈጸም መቻሉ የሚበዛበት አይሆንም።
37. ኢየሱስ ሕይወት ለሚፈልጉ ሰዎች በጠቅላላ ፍቅሩን ያሳየው እንዴት ነው?
37 ኢየሱስ አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ራሱን ለይሖዋ በማቅረብ ተጠመቀ። ከዚያም አምላክ ፈቃዱን እንዲያደርግ ተልዕኮ ሰጠው። (ማቴዎስ 3:13, 16, 17) የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ከሰማይ የመጣና ፍጹም ስለሆነ ይህን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የሰውን ዘር ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት መሥዋዕት አድርጎ ሊያቀርበው ይችላል። (ሮሜ 6:23፤ 5:18, 19) እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።” “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 10:10፤ 15:13) ኢየሱስ በዚህ ቤዛዊ ዝግጅት የሚያምኑ ሰዎች ሕይወት እንደሚያገኙ ስለሚያውቅ ሰይጣን በመከራ እንጨት ላይ እንዲገደል ሲያደርገው ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ የሞት ጽዋ ለመጠጣት ፈቃደኛ ሆኗል።—ማቴዎስ 20:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6
ወደ ሕይወት መመለስ
38. የአምላክ ልጅ እንደገና ሕያው የሆነው እንዴት ነው? ለዚህስ ምን ማረጋገጫ አለ?
38 የአምላክ ልጅ ምንም እንኳ ጠላቶቹ ቢገድሉትም ለአምላክ የነበረውን ጽኑ አቋም ስለጠበቀ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የማግኘት መብቱን በፍጹም አላጣም። ሆኖም ኢየሱስ ሞቶ መቃብር ውስጥ ከገባ ዋጋማ የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወት የማግኘት መብቱን እንዴት አድርጎ ለሰው ልጆች ጥቅም ሊያውለው ይችላል? ይሖዋ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ሌላ ተአምር የፈጸመው በዚህ ጊዜ ነበር። ኢየሱስ ሞቶ በተቀበረ በሦስተኛው ቀን ይሖዋ የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር በማድረግ ከሞት አስነሳው። (ሮሜ 6:9፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) ኢየሱስ በትንሣኤ ላይ ያላቸውን እምነት ለማጠንከር ሲል ሰብዓዊ አካል በመልበስ በተለያዩ ጊዜያት ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጧል፤ እንዲያውም አንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡት ታይቷል። እነዚህ ደቀ መዛሙርትም ሆኑ ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ በተገለጠለት ጊዜ ዓይኑ ታውሮ የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስን ተአምራዊ ትንሣኤ የሚጠራጠሩበት አንዳችም ምክንያት አልነበራቸውም።—1 ቆሮንቶስ 15:3-8፤ ሥራ 9:1-9
39. (ሀ) ኢየሱስ የመሥዋዕቱን ዋጋ የሚጠቀምበት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ለእነማን? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ስለየትኛው ሌላ አስደናቂ ተአምር ነው?
39 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከ40 ቀን በኋላ የሰው ልጆችን ነፃ የሚያወጣውን የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት ዋጋ ለማስረከብ አምላክ ወደሚገኝበት ወደ ሰማይ አረገ። “እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፣ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል።” (ዕብራውያን 10:12, 13) በዚህ ቤዛ አማካኝነት በመጀመሪያ ነፃ የሚወጡት የታማኝ ክርስቲያኖች “ታናሽ መንጋ” አባላት ማለትም ‘የክርስቶስ የሆኑት’ ናቸው። (ሉቃስ 12:32፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22, 23) እነዚህ ‘ከሰዎች መካከል የተዋጁ’ ናቸው፤ ትንሣኤ በሚያገኙበት ጊዜ መንፈሳዊ አካል በመልበስ በሰማይ የክርስቶስ ተባባሪዎች ይሆናሉ። (ራእይ 14:1-5) ሆኖም አሁን በመቃብር ውስጥ ያሉ እጅግ ብዙ የሰው ዘሮችስ? ኢየሱስ አባቱ የመፍረድና ሕይወት የመስጠት ሥልጣን እንዳጎናጸፈው እዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ተናግሮ ነበር። አክሎም “በመታሰቢያ መቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን ሰምተው ለትንሣኤ የሚወጡበት ሰዓት ይመጣልና በዚህ አትደነቁ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:26-29 NW) ገነት በሆነች ምድር ውስጥ እነዚህን መልሶ ወደ ሕይወት ያመጣቸዋል።
40, 41. (ሀ) “ትንሣኤ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አብራራ። (ለ) አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?
40 “በዚህ አታድንቁ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ልብ በሉ። ሆኖም አንድ ሰው ሙታን ከሞት ተላቅቀው ወደ ሕይወት ይመለሳሉ ብሎ እንዴት ሊጠባበቅ ይችላል? አካላቸው ወደ አፈርነት ተመልሶ የለምን? እንዲያውም አካላቸው የተሠራባቸው አንዳንድ ንጥረ ነገሮች እንደ እፅዋትና እንስሳት ከመሳሰሉት ሌሎች ሕያዋን ነገሮች ጋር ተዋሕደው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ትንሣኤ ማለት እነዚያኑ የመጀመሪያዎቹን ንጥረ ነገሮች መልሶ አንድ ላይ ማሰባሰብ ማለት አይደለም። ትንሣኤ ማለት አምላክ ያንኑ ሰው ቀድሞ የነበረውን ባሕርይ እንደያዘ እንደገና ይፈጥረዋል ማለት ነው። አምላክ ምድራዊ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም አዲስ አካል ከፈጠረ በኋላ ሰውዬው ከመሞቱ በፊት የነበረውን ፀባይ፣ ለይቶ የሚያሳውቀውን ባሕርይ፣ ትዝታና፣ የአኗኗር ዘይቤ በዚህ አካል ውስጥ መልሶ ይጨምራል።
41 በጣም የምትወደው ቤትህ በእሳት ጋይቶ ወድሞብህ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ የምትወደው ቤት ምን ይመስል እንደነበረ ሁሉንም ነገር አንድ በአንድ ስለምታስታውስ በቀላሉ ያንኑ ቤት መልሰህ መሥራት ትችላለህ። እንግዲያው የማስታወስ ችሎታን የፈጠረው አምላክ ከአእምሮው የማይጠፉትን የሚወዳቸውን ሰዎች እንደገና እንደዚያው አድርጎ ሊፈጥራቸው ይችላል። (ኢሳይያስ 64:8) መጽሐፍ ቅዱስ “መታሰቢያ መቃብር” የሚለውን አገላለጽ የሚጠቀመው ለዚህ ነው። አምላክ የሞቱትን ሰዎች እንደገና ወደ ሕልውና መልሶ የሚያመጣበት ጊዜ ሲደርስ የመጀመሪያውን ሰው በመፍጠር ተአምር እንደፈጸመ ሁሉ አሁንም ተአምር ይፈጽማል። አሁን ልዩነቱ ያንን ተአምር በጣም ብዙ ጊዜ የሚፈጽም መሆኑ ብቻ ነው።—ዘፍጥረት 2:7፤ ሥራ 24:15
42. በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚቻልና እርግጠኛ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?
42 በድጋሜ ሳይሞቱ በምድር ላይ የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸው በማድረግ አምላክ የሰው ዘሮችን መልሶ ወደ ሕይወት ያመጣል። ሆኖም እንዴት በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይቻላል? ይህ መለኮታዊ ፈቃድና ዓላማ ስለሆነ የሚቻልና እርግጠኛ የሆነ ነገር ነው። (ዮሐንስ 6:37-40፤ ማቴዎስ 6:10) ዛሬ በምድር ላይ ሰው የሚሞተው ከአዳም ሞትን ስለወረሰ ብቻ ነው። ሆኖም ሰው እንዲደሰትባቸው ተብለው የተፈጠሩትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ግሩምና ድንቅ ነገሮች ስናስብ መቶ ዓመት የማይሞላው የሰው ዕድሜ ከመጠን በላይ አጭር ሆኖ እናገኘዋለን! አምላክ ይህችን ምድር ለሰው ልጆች ሲሰጥ ዓላማው ሰዎች ለመቶ ወይም ለሺህ ዓመት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም እሱ በፈጠራቸው አስደናቂ ነገሮች እየተደሰቱ እንዲኖሩ ነበር!—መዝሙር 115:16፤ 133:3
ፍጹም የሆነው የሰላም መንግሥት
43. (ሀ) ፍጹም የሆነ መንግሥት ማግኘት ምን ያህል አስፈላጊ ሆኗል? (ለ) ይሖዋ በዚህ ረገድ ምን ዓላማ አለው?
43 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የአምላክን ሕግ ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ሰብዓዊ አገዛዝ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ወደቀ። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም አምላክ” ሲል መጥራቱ ትክክል ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) በዚህ ዓለም ላይ የሚታየው ጦርነት፣ ጭካኔ፣ ሙስናና የመንግሥታት አለመረጋጋት እውነትም የዚህ ዓለም አምላክ እሱ መሆኑን ያረጋግጣል። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ዝብርቁን ማስወገድና ሰላም ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። የሰው ዘር የሰላም መንግሥት ለማግኘት በመጮኽ ላይ ነው። ይህችን ምድር ወደ ገነትነት ለመለወጥ ዓላማ ያለው ፈጣሪ ለዚያች ገነት ፍጹም የሆነ መንግሥት ያዘጋጃል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንምን? ይሖዋም ዓላማው ይኸው ነው። በዚህ መንግሥት እሱን የሚወክለው የእሱ ‘የሰላም ገዥ’ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ሲሆን “በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7
44. (ሀ) ይህ መንግሥት የሚገኘው በየት ነው? (ለ) ይህ መንግሥት የተዋቀረው እንዴት ነው?
44 መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ፍጹም የሆነ መንግሥት በሰማይ እንደሚገኝ ይገልጻል። ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ አመቺ ቦታ በመሆን መላዋን ምድር በተሳካ ሁኔታ በጽድቅ ይገዛል። ከዚህም በላይ በዚህ በማይታየው ሰማያዊ መንግሥት ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ተባባሪ ገዢዎች ታማኝ ከሆኑ ሰዎች መካከል የተመረጡና በፈተናም ጊዜ ከእርሱ ጋር የሙጥኝ ብለው የጸኑ የኢየሱስ ተከታዮች ናቸው፤ ኢየሱስ “አባቴ ከእኔ ጋር የመንግሥት ቃል ኪዳን እንዳደረገ እኔም ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:28, 29 NW) ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ለመግዛት ወደ ሰማይ የሚወሰዱት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህም የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ተመርጠው የፓርላማ አባላት በመሆን እንዲያስተዳድሩ ከሚደረግበት ዛሬ ካሉ መንግሥታት አሠራር የተለየ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ቁጥራቸው 144,000 ብቻ የሆነ ተባባሪ ገዢዎች እንደሚኖሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ስለዚህ የአምላክ መንግሥት ወይም ሰማያዊው መንግሥት ክርስቶስ ኢየሱስንና ከምድር ወደ ሰማይ የተወሰዱ 144,000 ሰዎችን ያቀፈ ነው። (ራእይ 14:1-4፤ 5:9, 10) ምድርስ? መዝሙር 45:16 ንጉሡ ‘በምድር ላይ መሳፍንትን’ እንደሚሾም ይናገራል። ለጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች የጠለቀ ፍቅር ያላቸው ሰብዓዊ “መሳፍንት” ወይም አስተዳደራዊ የበላይ ተመልካቾች ከሰማይ ይሾማሉ።—ከኢሳይያስ 32:1 ጋር አወዳድር።
45, 46. (ሀ) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ዋና የስብከቱ ጭብጥ ምን ነበር? (ለ) ፍጹም የሆነው መንግሥት ወዲያው ያልተቋቋመው ለምን ነበር? (ሐ) በትንቢትና በዓለም ሁኔታዎች ረገድ 1914 እዘአ ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት የሆነው እንዴት ነው?
45 ፍጹም የሆነው መንግሥት የተቋቋመው መቼና እንዴት ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የስብከቱ ዋና ጭብጥ ይህ መንግሥት ነበር። (ማቴዎስ 4:17፤ ሉቃስ 8:1) ሆኖም ኢየሱስ በዚያን ጊዜም ሆነ በትንሣኤው ጊዜ ይህን መንግሥት አላቋቋመም ነበር። (ሥራ 1:6-8) ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ እንኳ ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ነበረበት። (መዝሙር 110:1, 2፤ ዕብራውያን 1:13) ይሖዋ የወሰነው ጊዜ 1914 እዘአ እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ያሳያል። ሆኖም አንድ ሰው ‘1914 ይህ ነው የማይባል ዓለም አቀፍ ወዮታ የጀመረበት ጊዜ እንጂ ፍጹም መንግሥት የተቋቋመበት ጊዜ ነው እንዴ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ይህ በጣም ትክክል ነው! ቀጥሎ እንደምናየው በአምላክ መንግሥት መምጣትና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚታዩት አውዳሚ ክስተቶች መካከል የቅርብ ግንኙነት አለ።
46 መጠበቂያ ግንብ (በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ከማንኛውም ሃይማኖታዊ መጽሔት በበለጠ በስፋት በመሰራጨት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው መጽሔት) ከ1914 ቀደም ብሎ ለ35 ዓመታት ያህል 1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጉልህ ትርጉም ያለው ዓመት መሆኑን ሲያመለክት ቆይቷል። በ1914 እነዚህ ትንቢቶች አስደናቂ ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀምረዋል። ከእነዚህ ትንቢቶች አንዱ በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ የሚከሰተውንና ኢየሱስ በዓይን በማይታይ ሁኔታ ንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚያረጋግጠውን “ምልክት” አስመልክቶ ራሱ ከ1,900 ዓመታት በፊት የተናገረው ትንቢት ነው። ኢየሱስ ይህን “ምልክት” አስመልክቶ ደቀ መዛሙርቱ ላቀረቡለት ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ አለ:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።” (ማቴዎስ 24:3, 7, 8) በ1914 የጀመረው አንደኛው የዓለም ጦርነት ከዚያ በፊት በነበሩት 2,500 ዓመታት ውስጥ የተደረጉት 900 ጦርነቶች በሙሉ ካስከተሉት ጥፋት ሰባት እጥፍ የሚበልጥ ጥፋት በማስከተል አስደናቂ ፍጻሜውን አግኝቷል! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምጥ ጣሩ አላቋረጠም። ከ1914 ወዲህ በምድር ላይ የደረሱት አውዳሚ ጦርነቶች፣ የምግብ እጥረቶች ወይም ታላላቅ የምድር መንቀጥቀጦች አንተን በሕይወትህ አጋጥመውህ ያውቃሉን? ከሆነ የዚህን የነገሮች ሥርዓት “የፍጻሜ ዘመን” አስመልክቶ የተሰጠው “ምልክት” ሲፈጸም አይተሃል ማለት ነው።—ዳንኤል 12:4
47. “የምልክቱ” ፍጻሜ የሆኑት ሁኔታዎች በቅርብ ዓመታት በጣም የተባባሱት እንዴት ነው?
47 ባስከተለው ውድመት ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በአራት እጥፍ የሚበልጠውና ለኑክሌር ዘመን በር ከፋች የሆነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ‘የምጥ ጣሩን’ ይበልጥ ያባባሰው ሲሆን የሚከተለው ሌላው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ አድርጓል:- “የሚያስፈራም ነገር ከሰማይም ታላቅ ምልክት ይሆናል።” (ሉቃስ 21:11) በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜያት ያሉት አሳሳቢ ሁኔታዎች ማለትም ወንጀልና ክፋት፣ የልጆች ዓመፀኝነት እንዲሁም አምላክ የለሽነትና የሥነ ምግባር ብልሽት እየጨመሩ መሄዳቸው የዚህ ክፉ ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” ገጽታ እንደሚሆን አስቀድሞ ተነግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:12
48. በምድር ላይ ላለው ወዮታ ተጠያቂው ማን ነው? ወዮታው ከ1914 ወዲህ እየጨመረ የሄደውስ ለምንድን ነው?
48 ሆኖም ሰማያዊው መንግሥት በ1914 ከተቋቋመ በምድር ላይ ይህ ሁሉ ሥቃይ የኖረው ለምንድን ነው? ለዚህ ተጠያቂው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣን እንደተቀበለ የመጀመሪያ እርምጃው በማይታየው ሰማይ ውስጥ በሰይጣን ላይ ጦርነት መክፈት ነበረ። በዚህም የተነሳ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው” ሰይጣን ከነመላእክቱ ወደ ምድር አካባቢ ተጣለ። የሚጠፋበት ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ስለሚያውቅ በምድር ላይ ከፍተኛ ብጥብጥ እንዲቀሰቀስ ያደርጋል። “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”—ራእይ 12:7-9, 12
49. (ሀ) “ምድርን የሚያጠፉ” ምን ይደርስባቸዋል? (ለ) ይሖዋ በብሔራት ላይ “ፍርዱን” የሚያስፈጽመው እንዴት ነው?
49 እነዚህ ወዮታዎች ማክተሚያ ይኖራቸው ይሆን? እንዴታ! ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ መንግሥት ማለትም በሰማይ የሚገኘው መስተዳድር ‘ምድርን የሚያጠፉትን በማጥፋት’ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ እነዚህ ወዮታዎች ያከትማሉ። (ራእይ 11:18፤ ዳንኤል 2:44) አምላክ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ወይም ማንኛውም ሰው ቢሆን የእጁ ሥራ የሆነችውን ምድር በኑክሌር መሣሪያቸው እንዲያጠፏት በፍጹም አይፈቅድም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላል:- “መዓቴንና የቁጣዬን ትኩሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነው።” (ሶፎንያስ 3:8) ይሖዋ በምድር ላይ ሰይጣንን በሚከተሉ ሁሉ ላይ ታላቅ ጥፋት ለማምጣት በክርስቶስ አማካኝነት በአጽናፈ ዓለም ውስጥ በቁጥጥሩ ሥር ባሉ ታላላቅ ኃይላት ይጠቀማል። ይህም በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ ጋር የሚመሳሰል ምድር አቀፍ የሆነ መጠነ ሰፊ ጥፋት ይሆናል።—ኤርምያስ 25:31-34፤ 2 ጴጥሮስ 3:5-7, 10
50. (ሀ) “አርማጌዶን” ምንድን ነው? (ለ) ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት እነማን ብቻ ናቸው?
50 በክፉዎች ብሔራት ላይ የሚመጣው ይህ ጥፋት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ የአርማጌዶን ጦርነት ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 16:14-16) ከአርማጌዶን በሕይወት ተርፈው ወደ አምላክ ሰላማዊ አዲስ ሥርዓት የሚገቡት ይሖዋንና ጽድቅን አጥብቀው የሚፈልጉ ገር የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ሶፎንያስ 2:3፤ ኢሳይያስ 26:20, 21) መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” (መዝሙር 37:11) ከዚያም ምድርን ወደ ገነትነት የመለወጡ ታላቅ ሥራ ይቀጥላል!
ወደ ገነት ለመግባት የሚያበቃ ትምህርት
51. አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?
51 በገነት ውስጥ ለመኖር ትፈልጋለህ? መልስህ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ ኢየሱስ ዛሬ ስላለው አስጨናቂ ሥርዓትና በዚህ ሥርዓት የሚመጣው ጥፋት መቅረቡን ስለሚያሳየው “ምልክት” በተናገረ ጊዜ “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ሲል አክሎ እንደተናገረ ስታውቅ ትደሰታለህ። (ማቴዎስ 24:34) የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ ላይ በመጓዝ ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 7:13, 14) ለውጥ ለማድረግ የሚችሉበት ጊዜ እያለቀባቸው ነው። ይሖዋ ማስጠንቀቂያው በወቅቱ እንዲደርስህ በማድረጉ ምንኛ አመስጋኝ መሆን ይገባሃል! ይሖዋ ሕይወት እንድታገኝ ስለሚፈልግ ትክክለኛውን እርምጃ እንድትወስድ ይረዳሃል።—2 ጴጥሮስ 3:9፤ ሕዝቅኤል 18:23
52. ሃይማኖትን በተመለከተ ጥበብ የተሞላበት ምርጫ ለማድረግ ምን ያስፈልግሃል?
52 አሁን በአስቸኳይ የሚያስፈልግህ ነገር ትክክለኛ እውቀት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4፤ ዮሐንስ 17:3) ይህን እውቀት ከየት ማግኘት ትችላለህ? በማንኛውም ሃይማኖት ሊገኝ ይችላልን? አንዳንድ ሰዎች በአንድ ተራራ ላይ የሚገኙ መንገዶች በሙሉ ወደ ተራራው አናት እንደሚያደርሱ ሁሉ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ ቦታ ነው የሚያደርሱት ይላሉ። እነዚህ ሰዎች በጣም ተሳስተዋል! ተራራ የሚወጡ ሰዎች ትክክለኛውን መንገድ ለማግኘት ካርታ ከመጠቀማቸውም በላይ መንገድ የሚመራቸው ሰው ይቀጥራሉ። በተመሳሳይም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው አንድ እውነተኛ ሃይማኖት ብቻ ነው፤ ይህን እውነተኛ ሃይማኖት ለማግኘት ደግሞ የሚመራ ያስፈልጋል።—ሥራ 8:26-31
53. (ሀ) የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግህን መቀጠል ይኖርብሃል? (ለ) ሰይጣን የሚያመጣቸውን የትኞቹን ፈተናዎች መቋቋም ሊያስፈልግህ ይችላል?
53 የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ብሮሹር ያዘጋጁት አንተን ለመርዳት ነው። አሁን እንኳን አንዳንድ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንድታውቅ ረድቶሃል፤ አይደለም እንዴ? እያንዳንዱ ነጥብ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃል ውስጥ የሚገኝ መሆኑንና አለመሆኑን እንዳረጋገጥክ ጥርጥር የለውም። እንግዲህ ወደምትፈልገው ግብ ለመድረስ መማርህን መቀጠል አለብህ። አንድ ሰው በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ከተፈለገ ተገቢውን ሰብዓዊ ትምህርት ማግኘት እንዳለበት ሁሉ ከመጪው ጥፋት በሕይወት ተርፎ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ከሚኖረው ኅብረተሰብ መካከል ለመሆን ተገቢውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መቅሰም ያስፈልገዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ሰይጣን የቅርብ ወዳጆችህ እንዲቃወሙህ በማድረግ ወይም ቁሳዊ ነገሮችን በራስ ወዳድነት በማሳደድ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ አካሄድ እንድትፈተን በማድረግ ይህን የጀመርከውን ጥናት ለማስተው ሊሞክር ይችላል። ለሰይጣን እጅ አትስጥ። የአንተም ሆነ የቤተሰቦችህ ደህንነትና የወደፊት ሁኔታ የተመካው መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ በማጥናትህ ላይ ነው።—ማቴዎስ 10:36፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
54. ይሖዋ በአቅራቢያህ ምን ተጨማሪ የማስተማሪያ ዝግጅት አድርጓል?
54 አሁን የጀመርከውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመቀጠልህ በተጨማሪ ትምህርት የምታገኝበት ሌላም ዝግጅት አለ። ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፍላጎት ያላቸው በአካባቢህ ያሉ ሰዎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ አዘውትረው ስብሰባዎችን ይካፈላሉ። በዚያ የሚገኙ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለመቅሰምና የተሻሉ ሰዎች ሆነው ለመገኘት ከልብ የሚጥሩ ናቸው። አዳዲስ ሰዎች ሲመጡ እንደሚከተለው በማለት በደስታ ይቀበሏቸዋል:- “ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ [የአምልኮ ሥፍራ] . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን።” (ኢሳይያስ 2:3) ዕብራውያን 10:24, 25 በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኝበትን ጥሩ ምክንያት ይገልጽልናል። እንዲህ ይነበባል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።”
55. (ሀ) የይሖዋ ድርጅት ከሌሎች የሚለየው በምን መንገዶች ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሰዎች የተለየ አንድነት ያላቸው እንዴት ነው?
55 ከይሖዋ ድርጅት ጋር ስትቀራረብ በዚያ ያለው ሁኔታ በቤተ መቅደሶችና በቤተ ክርስቲያኖች አካባቢ ካለው ሁኔታ በጣም የተለየ ሆኖ ታገኘዋለህ። ሙዳየ ምጽዋት አይዞርም፣ ሐሜት ወይም ጥል የለም፣ በተጨማሪም በዘር ሐረግ ወይም በሀብት መድልዎ አይደረግም። የይሖዋ ምሥክሮች ተለይተው የሚታወቁበት ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ነው። በአንደኛ ደረጃ ይሖዋን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን ይወዳሉ። ይህ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት ነው። (ማቴዎስ 22:37-39፤ ዮሐንስ 13:35) አንተ ራስህ በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘትና እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። ባላቸው አንድነት እንደምትደነቅ ጥርጥር የለውም። በዓለም ዙሪያ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ከአምስት ሚልዮን በላይ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ሆኖም በምድር ዙሪያ በስብሰባዎቻቸው የሚከተሉት ፕሮግራም አንድ ዓይነት ነው። ጽሑፎች በአንድ ጊዜ በብዙ ቋንቋዎች ስለሚታተሙ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸው በጥቂት ሰዓታት ልዩነት አንድ ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን ያጠናሉ። በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የይሖዋ ድርጅት ያለው አንድነት በዘመናችን የተፈጸመ አንድ ትልቅ ተአምር ነው።
56. (ሀ) ከይሖዋ ድርጅት ጋር በመተባበርህ ምን በረከቶችን ታገኛለህ? (ለ) ችግሮች ሲነሱ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? (ሐ) ሕይወትህን ለይሖዋ መወሰን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
56 ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር ዘወትር ስትተባበር ‘አዲሱን ሰው መልበስ’ እና የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆኑትን “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” መኮትኮት ያስፈልግሃል። (ቆላስይስ 3:10, 12-14፤ ገላትያ 5:22, 23) ይህም ከፍተኛ እርካታ ያመጣልሃል። ከምትኖርበት ብልሹ ዓለምና ካለብህ አለፍጽምና የተነሳ ለማሸነፍ ትግል የሚጠይቁ ችግሮች አልፎ አልፎ ያጋጥሙህ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ይረዳሃል። እሱን ለማስደሰት ከልብ ለሚጥሩ ሰዎች የይሖዋ ቃል እንዲህ በማለት ዋስትና ይሰጣል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በይሖዋ ፍቅር ስለምትማረክ እሱን ለማገልገል ትገፋፋለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወትህን ለዚህ አፍቃሪ አምላክ ለመወሰንና ልዩ መብት ካገኙት ምሥክሮቹ መካከል ለመቆጠር የምትችልበትን መንገድ ለማሳየት ፈቃደኞች ናቸው። (መዝሙር 104:33፤ ሉቃስ 9:23) በእርግጥም ይህ ትልቅ መብት ነው። እስቲ አስበው! ይሖዋን በማምለክ በምድር ላይ በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ልትጣጣር ትችላለህ።—ሶፎንያስ 2:3፤ ኢሳይያስ 25:6, 8
57. (ሀ) በአዲሱ ሥርዓት በአምላክና በሰው ዘር መካከል ምን ዓይነት የቀረበ ዝምድና ይኖራል? (ለ) በዚያ ጊዜ የምታገኛቸው አንዳንድ በረከቶች ምንድን ናቸው?
57 እንግዲያው ማጥናትህን እንዲሁም ለይሖዋ አምላክ፣ ለልጁና ለሰማያዊው የጽድቅ መንግሥት ባለህ ፍቅርና አድናቆት ማደግህን ቀጥል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የአምላክን መንግሥትና ይህ መንግሥት የሚያዘንባቸውን በረከቶች ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል።” በዛሬው ጊዜ ካለው ራስ ወዳድና አጥፊ ከሆነው የሰው አገዛዝ በጣም ከፍ ከፍ ብሎ የሚገኘው “እግዚአብሔር እርሱ ራሱ” በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚያፈቅሩትና ለሚያመልኩት ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ደግ አባት አጠገባቸው ይሆናል። በዚያን ጊዜ ከእውነተኛው የይሖዋ አምልኮ በስተቀር አንድም ሌላ ሃይማኖት አይኖርም፤ አምላኪዎቹ ከእሱ ጋር የልጅና የአባት ዓይነት የቀረበ ዝምድና ይኖራቸዋል። በጣም አፍቃሪ አባት መሆኑን ያስመሰክራል! “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4
58. ይሖዋ ‘ሁሉን አዲስ እንደሚያደርግ’ እንዴት እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ?
58 ፍጹም በሆነ ሰማያዊ መንግሥት ሥር ገነት የሆነች ምድር የማቋቋሙ አስደናቂ ተአምር በዚህ መንገድ ይከናወናል። ነገ ፀሐይ መውጣቷና መጥለቋ እንደማያጠራጥር ሁሉ ይህ እንደሚፈጸምም የዚያኑ ያህል አያጠራጥርም። የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ የገባው ቃል “የታመነና እውነተኛ” ነው። “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” ሲል በሰማይ ከሚገኘው ዙፋኑ ሆኖ የተናገረው እሱ ነው።—ራእይ 21:5
ይህን ብሮሹር ለመከለስ ያህል የሚከተሉትን ጥያቄዎች ምን ብለህ ትመልሳለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መጽሐፍ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
ስለ አምላክ ምን ተምረሃል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?
ሰይጣን ዲያብሎስ ማን ነው?
አምላክ ክፋትን ለምን ፈቀደ?
ሰው የሚሞተው ለምንድን ነው?
ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
ቤዛ ምንድን ነው?
ትንሣኤ የሚከናወነው የትና እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ምንስ ያከናውናል?
“የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” “ምልክቱ” ምንድን ነው?
በገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ራስህን ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ከላይ ያሉትን አንቀጾች የሚደግፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች:- (1) ሥራ 17:26፤ መዝሙር 46:9፤ ሚክያስ 4:3, 4፤ ኢሳይያስ 65:21-23፤ (2) ኢሳይያስ 65:25፤ 11:6-9፤ 55:12, 13፤ መዝሙር 67:6, 7፤ (3) ኢዮብ 33:25፤ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ 33:24፤ መዝሙር 104:24፤ (4) ኢሳይያስ 55:11
b ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች ከ1954 የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የተወሰዱ ናቸው። ከጥቅሱ ቀጥሎ “NW” ሲባል ጥቅሱ የተወሰደው በዘመናዊ እንግሊዝኛ ከተዘጋጀው ባለማጣቀሻ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም መሆኑን ያመለክታል።
c ሞናርክስ ኤንድ ቱምስ ኤንድ ፒፕልስ—ዘ ዶውን ኦቭ ዚ ኦሪየንት ገጽ 25
d ሳይክሎፔዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክለዚያስቲካል ሊትሬቸር በጄ ማክሊንቶክ እና ጄ ስትሮንግ የተዘጋጀ ጥራዝ 8 ገጽ 908
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሰው ከእንስሳት ሁሉ የላቀ ፍጡር ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ፍጹም ሰው ከነበረው ከአዳም ጋር እኩል ነበር