ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ የሚኖር ሕዝብ
“በአኗኗሩ የታመነው ጻድቁ ብሔር ይገባ ዘንድ በሮቹን ክፈቱ።”—ኢሳይያስ 26:2 አዓት
1. ኢሳይያስ ስለ “ጻድቁ ብሔር” የተናገረው ነገር አስገራሚ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ ሁሉም ዓይነት ብሔራት አሉ። አንዳንዶቹ ዲሞክራሲያዊ፣ ሌሎቹ ደግሞ አምባገነናዊ ናቸው። አንዳንዶቹ ሀብታሞች አንዳንዶቹ ደግሞ ድሀዎች ናቸው። የሁሉም የጋራ የሆነ ነገር ቢኖር ሁሉም ሰይጣን አምላክ የሆነለት ዓለም ክፍል መሆናቸው ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ከዚህ አንጻር ሲታይ ኢሳይያስ “እናንተ ሰዎች ሆይ፣ በአኗኗሩ የታመነው ጻድቁ ብሔር ይገባ ዘንድ በሮቹን ክፈቱ” በማለት የተናገራቸው ቃላት አንዳንድ ሰዎችን ሊያስገርሟቸው ይችላሉ። (ኢሳይያስ 26:2 አዓት) ጻድቅ ብሔር? አዎን፣ ትንቢቱ በእኛ ዘመን ጻድቅ ብሔር እንደሚኖር ስለሚያመለክት ጻድቅ ብሔር አለ። ይህ እንግዳ የሆነ ብሔር ተለይቶ ሊታወቅ የሚችለው እንዴት ነው?
2. “ጻድቁ ብሔር” ምንድን ነው? ይህንንስ እንዴት ልናውቅ እንችላለን?
2 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ኢሳይያስ 26:2ን በተረጎመው መሠረት ይህ ብሔር “በአኗኗሩ የታመነ” ተብሏል። የ1954 አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ደግሞ “እውነትን የሚጠብቅ ጻድቅ ሕዝብ” በማለት ይህን ጥቅስ ተርጉሞታል። ሁለቱም ተስማሚ መግለጫዎች ናቸው። እንዲያውም ጻድቁ ብሔር በምድር ላይ ካሉት ብሔራት ሁሉ ለንጉሡ ለክርስቶስ የሚገዛው እርሱ ብቻ ስለሆነ ይህን ብሔር መለየት አዳጋች አይደለም። በመሆኑም ይህ ብሔር የሰይጣን ዓለም ክፍል አይደለም። (ዮሐንስ 17:16) ስለዚህ የዚህ ብሔር አባላት ‘በአሕዛብ መካከል መልካም አኗኗር ይዘው በመመላለስ’ የታወቁ ናቸው ማለት ነው። አምላክን የሚያስከብር የአኗኗር ጎዳና ይከተላሉ። (1 ጴጥሮስ 2:12) ከዚህም በላይ በዓለም ላይ የሚኖሩበት ሥፍራ የትም ሆነ የት “የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን [“ጉባኤ” አዓት]” ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) እውነትን በመደገፍ ሕዝበ ክርስትና የምታስተምራቸውን አረማዊ ፍልስፍናዎች አይቀበሉም። “ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት” ይኸውም የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ይደግፋሉ። (1 ጴጥሮስ 2:2) በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” በቅንዓት ይሰብካሉ። (ቆላስይስ 1:23) ይህ ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀሪ አባላት በሆኑት በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የተገነባ መሆኑ ያጠራጥራልን? በፍጹም አያጠራጥርም!—ገላትያ 6:16
ብሔሩ ተወለደ
3. “ጻድቁ ብሔር” እንዴት እንደ ተወለደ ግለጽ።
3 “ጻድቁ ብሔር” የተወለደው መቼ ነው? ይህ ብሔር መቋቋም የጀመረበት ጊዜ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት ተነግሯል። በኢሳይያስ 66:7, 8 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “[ጽዮን] ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች። . . . ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለች።” ባልተለመደ ሁኔታ የአምላክ ሰማያዊ ድርጅት የሆነችው ጽዮን በምጥ ሳትሠቃይ “ወንድ ልጅ” ትወልዳለች ተብሎ ተተንብዮ ነበር። በ1914 መሲሐዊቷ መንግሥት በሰማያት ተወልዳለች። (ራእይ 12:5) ከዚያ በኋላ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የሚሳተፉት ብሔራት ቁጥራቸው እያደገ ሄደ፤ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ከባድ መከራና ስደት ደረሰባቸው። በመጨረሻ በ1919 መንፈሳዊው ብሔር ይኸውም ‘ወንዱ ልጅ’ በምድር ላይ ተወለደ። በዚህ መንገድ ጽዮን “ልጆችዋን” ማለትም የአዲሱ “ጻድቅ ብሔር” ቅቡዓን አባላትን ወልዳለች፤ እነዚህም ምን ጊዜም እየሰፋ ለሚሄደው የምሥክርነት ሥራ ተደራጁ።—ማቴዎስ 24:3, 7, 8, 14፤ 1 ጴጥሮስ 2:9
4. የአምላክ ጻድቅ ብሔር ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ለመኖር መታገል አስፈልጎት የነበረው ለምንድን ነው?
4 ይህ ብሔር ገና ከጅምሩ አንስቶ ንጹሕ አቋሙን የሚፈታተኑ ከባድ ፈተናዎች አጋጥመውታል። ለምን? ሰማያዊቷ መንግሥት ስትወለድ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ወደ ምድር ተጥለዋል። በዚያን ጊዜ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል አውጆአል፦ “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፣ ቀንና ሌሊትም በአምላክችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና። እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፣ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።” ሰይጣን ለዚህ የሁኔታዎች ለውጥ በታላቅ ቁጣ ምላሽ በመስጠት “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ [ከሴቲቱ ዘር] የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።” የሰይጣን ኃይለኛ ጥቃት የደረሰባቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጸንተው ቆመዋል። እስከ ጊዜያችን ድረስ የአምላክ ጻድቅ ብሔር ቀናተኛ አባላት “እስከ ሞት ድረስ” የሚያደርስ በሚሆንበትም ጊዜ እንኳ ንጹሕ አቋማቸውን ባለማጉደፍ በኢየሱስ ቤዛዊ ደም ላይ ያላቸውን እምነት አሳይተዋል፤ እንዲሁም ይሖዋ ለቀንደኛው ከሳሽ መልስ መስጠት እንዲችል ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።—ራእይ 12:1, 5, 9–12, 17፤ ምሳሌ 27:11
5. በዘመናችን ያሉት ምሥክሮች ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ ለመኖር እንዲችሉ የረዳቸው ምን ግሩም አመለካከት ነው?
5 በ1919 በዘመናችን ስለ አምላክ መንግሥት የሚሰጠው ምሥክርነት መካሄድ ሲጀምር በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥር ጥቂት ነበሩ፤ በእምነት ግን የበረቱ ነበሩ። ‘ጥበቃ የሚደረግላቸው ቅጥርና ምሽግ ላላት የጸናች ከተማ’ መሠረት የሆኑ አባላት ሆነዋል። ‘የዘላለም አምባ በሆነው በይሖዋ ታምነው ነበር።’ (ኢሳይያስ 26:1, 3, 4) በጥንት ዘመን እንደነበረው እንደ ሙሴ እንዲህ ሲሉ አውጀዋል፦ “የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁና፤ ለአምላካችን ታላቅነትን ስጡ። እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራው ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።”—ዘዳግም 32:3, 4
6. በእነዚህ መጨረሻ ቀናት ይሖዋ ሕዝቡን የባረከው በምን መንገድ ነው?
6 ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ አምላክ መንግሥት የሚያስገቡት በሮች ክፍት ሆነው ቆይተዋል። በመጀመሪያ የ144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪ አባላት የተሰባሰቡ ሲሆን አሁን ደግሞ የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች የይሖዋን መንግሥት ዓላማዎች በማሳወቁ ሥራ እየተባበሩ ነው። (ዮሐንስ 10:16) በመሆኑም በደስታ እንዲህ በማለት ማስታወቅ ይቻላል፦ “ሕዝብህን አበዛህ፣ አቤቱ፣ ሕዝብህን አበዛህ፤ አንተም ተከበርህ፣ የአገሪቱንም ዳርቻ አሰፋህ።” (ኢሳይያስ 26:15) በዛሬው ጊዜ ያለውን የዓለምን መስክ ስናጤን እነዚህ ቃላት ምንኛ እውነት ሆነው እናገኛቸዋለን! ስለመጪዋ የክርስቶስ መንግሥት የሚሰጠው ምሥክርነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ ተዳርሷል። (ሥራ 1:8) ይህ ስፋቱ ምን ያህል እንደሆነ ከገጽ 12 እስከ 15 ላይ ባለው የ1994 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፋዊ ሪፖርት መለካት ይቻላል።
የአስፋፊዎች አዲስ ከፍተኛ ቁጥር
7, 8. (ሀ) የአምላክ ሕዝብ ‘የድንኳኑን አውታር እንዳስረዘመ’ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? (ለ) የ1994ን የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት በመመልከት፣ በከፍተኛ ሁኔታ ‘ድንበራቸውን ያሰፉት’ በምን በምን ረገድ ነው ትላለህ?
7 በዚህ ሪፖርት ላይ ያሉትን አንዳንድ ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች እስቲ ተመልከት። በመስኩ ላይ የተሰማሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር 4,914,094 ደርሷል! ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡና ነጭ ልብስ ለብሰው በዙፋኑና በበጉ ፊት የቆሙ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ያለ መቋረጥ እየተሰበሰቡ መሆኑን ማየቱ ምንኛ የሚያስፈነድቅ ነው! አዎን፣ እነዚህም ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው የሚኖሩ መሆናቸውን አስመስክረዋል። በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላሳዩ ጻድቅ ሆነው በመቆጠር ‘ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም አንጽተዋል።’—ራእይ 7:9, 14
8 በተለይ ከ1919 ጀምሮ የሚከተለው ጥሪ ለይሖዋ ድርጅት ሲቀርብ ቆይቷል፦ “የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፣ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቆጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ።” (ኢሳይያስ 54:2) በምላሹ የስብከቱ ሥራ ሌላው ቀርቶ ከአላስካ ጋር በምትዋሰነው በበረዶ በተሸፈነችው በዩኮን እንኳ ሳይቀር እየተካሄደ ነው። በዚህ ስፍራ ተከታታይ ለሆኑ ሳምንታት የሚቆየውን ከዜሮ በታች ከ45 ዲግሪ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ የሚወርደውን ቅዝቃዜ የሚቋቋም ብርቱ የአቅኚዎች ቡድን ይገኛል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ በሚሄድ ፍጥነት ብዙ ሰዎች ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ በመኖር ላይ ወዳለው የይሖዋ ብሔር እየጎረፉ ነው። እነዚህን ሰዎች ከሕዝበ ክርስትና ውጪ ከሆኑ የእስያ አገሮች፣ ቀደም ሲል በኮሙኒስት ቀንበር ሥር ከነበሩ አገሮች፣ ከብዙ የአፍሪካ አገሮችና እንደ ኢጣሊያ፣ ስፔይን፣ ፖርቱጋልና ደቡብ አሜሪካ ከመሰሉ በካቶሊክ ተጽዕኖ ሥር ካሉ አገሮች ለመቀበል በሮቹ ይበልጥ ወለል ብለው ተከፍተዋል። ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሌላ መስክ ከፍተዋል። ለምሳሌ ያህል በእንግሊዝ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከተለያየ ዘር የተውጣጡ 13 የውጪ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድኖችን እየረዱ ነው።
‘ይህን ዘወትር አድርጉ’
9. (ሀ) የ1994 የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ምን ይጠቁማል? (ለ) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተጠበቀው በላይ ከፍተኛ ተሰብሳቢዎች ከተገኙባቸው አገሮች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
9 ሌላው የዓመታዊው ሪፖርት ጎላ ያለ ነጥብ የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ሞቱ የሚዘከርበትን የመታሰቢያ በዓል አቋቁሞ ተከታዮቹን “ይህን ለመታሰቢያዬ [“ዘወትር” አዓት] አድርጉት” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:24) በ1994 በንቃት ከሚያገለግሉት አስፋፊዎች ቁጥር ከእጥፍ ጊዜ በላይ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው 12,288,917 ሰዎች የቂጣውና የወይኑ ተካፋዮችም ሆኑ የበዓሉ ተመልካቾች በአንድነት ይህን ትእዛዝ ለማክበር መሰባሰባቸውን ማወቁ በጣም ደስ የሚያሰኝ ነው። በአንዳንድ አገሮች የአስፋፊዎቹና የመታሰቢያ በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥር ሲነጻጸር ከዚህም የበለጠ ሆኖ ተገኝቷል። በኢስቶኒያ፣ በላትቪያና በሊቱዋኒያ የሚገኙት 4,049 አስፋፊዎች ከእነሱ ቁጥር ከሦስት ጊዜ እጥፍ በላይ የሚሆኑ 12,876 ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘታቸው ተደስተዋል። በቤኒንም በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት 16,786 ተሰብሳቢዎች የአስፋፊዎቹን ቁጥር አምስት ጊዜ ያህል የሚያጥፉ ነበሩ ማለት ይቻላል። አንድ ወደ 45 የሚጠጉ አስፋፊዎች ያሉት ጉባኤ 831 ተሰብሳቢዎች ነበሩት!
10. (ሀ) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሰብሳቢዎች መገኘታቸው ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል? (ለ) በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኘ ሰው ተጨማሪ እርዳታ ሲያገኝ ምን ሊሆን እንደሚችል ግለጽ።
10 የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች በዚያ ተስፋ ሰጪ በሆነ በዓል ላይ አብረዋቸው በመገኘታቸው ተደስተዋል። አሁን እነዚህ ሰዎች ስለ እውነት ያላቸውን ግንዛቤና ፍቅር ይበልጥ እንዲያሳድጉ ለመርዳት ይፈልጋሉ። አንዳንዶች በሩስያ የምትገኘው አላ ያሳየችውን ዓይነት ምላሽ ያሳዩ ይሆናል። አላ ከአንዲት ልዩ አቅኚ ጋር ታጠና ነበር፤ ሆኖም እምብዛም ዕድገት አላደረገችም ነበርና ጥናቱ ተቋረጠ። ያም ሆኖ ግን አላ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንድትገኝ የቀረበላትን ጥሪ ተቀበለች። ያ ስብሰባ ለእርሷ ትልቅ ትርጉም ያለው ሆኖ ነበር፤ ጥልቀት ባለው መንገድ ነካት። ወደ ቤቷ ስትመለስ ምስሎቿን ሁሉ ጣለችና ይሖዋ እንዲረዳት ጸለየች። ከሁለት ቀናት በኋላ አቅኚዋ እህት አላ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘቷ ምን ያህል እንዳስደሰታት ልትጠይቃት ወደ ቤቷ ሄደች። ፍሬያማ የሆነ ውይይት አደረጉ። የአላ ጥናት እንደገና ተጀመረ። ብዙም ሳትቆይ በምሥክርነቱ ሥራ መካፈል ጀመረች። ይህ ተሞክሮ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ሰዎችን ተከታትሎ የመርዳትን ጥቅም ያሳያል። ብዙዎች አላ ያሳየችው ዓይነት ምላሽ እንደሚያሳዩ የታወቀ ነው።
“መሰብሰባችንን አንተው”
11–13. (ሀ) ጻድቁ ብሔር ከሚያሳየው የታመነ አኗኗር አንዱ ምንድን ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
11 የመታሰቢያው በዓል በይሖዋ ምሥክሮች አጀንዳ ላይ ትልቁን ቦታ የያዘ ስብሰባ ነው፤ ሆኖም ይህ ብቸኛው ስብሰባቸው አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች ለሚከተሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት በመታዘዝ በየሳምንቱ አንድ ላይ ይሰበሰባሉ፦ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በእርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በእርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) በታመነ አኗኗሩ ተለይቶ ከሚታወቀው የይሖዋ ጻድቅ ብሔር ጋር ተቀላቅለዋል። በአኗኗር የታመኑ መሆን በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ረገድም የታመኑ መሆንን ይጨምራል።
12 በፊሊፒንስ ውስጥ ይህን አባባል መረዳት አዳጋች አይሆንም፤ በጠቅላላው አገሪቱ እሁድ እሁድ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ተሰብሳቢዎች አማካይ ቁጥር የአስፋፊዎቹን ቁጥር 125 በመቶ ይሆናል። በአርጀንቲና ውስጥ የሚገኝ አንድ የምሥክሮችና ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ቡድንም ይህ አባባል በደንብ ይገባዋል። የሚኖሩበት ሥፍራ ከመንግሥት አዳራሹ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው። ያም ሆኖ ግን በበሽታ ሳቢያ ካልሆነ በስተቀር አንዳቸውም ቢሆኑ ስብሰባዎቹ እንደማያመልጧቸው የክልል የበላይ ተመልካቹ ሪፖርት አድርጓል። በጋሪ ወይም በፈረስ ላይ ተቆናጠው ለአራት ሰዓታት ይጓዛሉ። በበረዶ ወራትም በድቅድቅ ጨለማ ወደ ቤታቸው ይጓዛሉ።
13 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየቀረበ በመጣ መጠን ኑሮ በበለጠ አስቸጋሪ እየሆነ ይሄዳል፤ ችግሮች እየጨመሩ ይሄዳሉ፤ ዘወትር በስብሰባዎች ላይ መገኘትም ይበልጥ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች ባሉበት ሰዓት በእንዲህ ዓይነት ስብሰባዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በማንኛውም ቦታ ሊገኝ የማይችለው መንፈሳዊ ምግብና የሞቀ ወዳጅነት ከምን ጊዜውም በበለጠ ያስፈልገናል።
“በጥድፊያ ስሜት” ይሁን
14. የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን በተመለከተ የጥድፊያ ስሜት ያላቸው ለምንድን ነው? ይህንንስ የትኞቹ ውጤቶች ያሳያሉ?
14 ባለፈው ዓመት በኢጣሊያ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ “በኃይል የሰዎችን እምነት ለመለወጥ የሚደረግ ቅጥ የለሽ ዘመቻ” ብሎ ጠርቶታል። ይሁን እንጂ ምሥክሮቹ የሚያከናውኑት ሥራ ኃይል የተቀላቀለበትና ቅጥ ያጣ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎታቸው ለሰዎች ያላቸውን የጠለቀ ፍቅር የሚያሳይ መግለጫ ነው። በተጨማሪም ለሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት እንደሚታዘዙ የሚያሳይ ማስረጃ ነው፦ “ቃሉን ስበክ፤ በደህናውም ጊዜ ይሁን በአስቸጋሪው ጊዜ በጥድፊያ ስሜት ይህን አከናውን።” (2 ጢሞቴዎስ 4:2 አዓት) የጥድፊያ ስሜት የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎታቸው ቀናተኛ እንዲሆኑ ይገፋፋቸዋል። ይህም በ1994 ለሰዎች በመስበክ፣ ተመላልሰው በመጠየቅና በየሳምንቱ 4,701,357 የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ባሳለፉት በጠቅላላው 1,096,065,354 የሚሆን ሰዓት ታይቷል። ብዙዎች በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል ችለዋል። ይህም የአቅኚነቱ መንፈስ አሁንም ሕያው እንደሆነና እየሠራ እንዳለ የሚያሳይ ነው። በዓለም ዙሪያ በአማካይ 636,202 የሚሆኑ አቅኚዎች መኖራቸው ይህን ያረጋግጣል።
15, 16. (ሀ) ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉት የአቅኚነትን መንፈስ ያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) በ1994 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ላይ የተካተቱትን አገሮች አንድ በአንድ ስትመለከት በጣም ጎልቶ የሚታይ የአቅኚዎች ቁጥር የምታይባቸው የትኞቹ ናቸው?
15 ከእነዚህ አቅኚዎች መካከል ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች በአሜሪካ ውስጥ የሚማሩበትን ክፍል ዋነኛ የአገልግሎት ክልላቸው በማድረግ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ ባሉበት ወቅት የዘወትር አቅኚዎች ሆነው እያገለገሉ ነው። እነዚህ ወጣቶች በዚያ አገር ውስጥ ባሉ ብዙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተዛምተው ከሚገኙት ከዕፆች፣ ከሥነ ምግባር ብልግናና ከዓመፅ ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ አቅኚነት ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ብዙ ወጣቶችም ትምህርታቸውን ሲጨርሱ አቅኚ የመሆን ግብ አላቸው። በዩክሬን ውስጥ የምትገኘው ኢርና ትምህርቷን ስትጨርስ አቅኚ ሆና ማገልገል እንድትችል በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በምትማርበት ጊዜ ሁሉ ረዳት አቅኚ ሆና በማገልገል ራሷን አዘጋጀች። ትምህርቷን ስትጨርስ ቤተሰቧን ወክላ በዘወትር አቅኚነት እንድታገለግል ቤተሰቦቿ የሚያስፈልጓትን ገንዘብ ነክ ነገሮች በማሟላት ለመተባበር ፈቃደኛ ሆኑ። በዩክሬን ውስጥ ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከባድ ነው። ይሁን እንጂ ኢርና “ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለምሰብክላቸውም ሰዎች ሕይወትን የሚያስገኝ ሥራ እየሠራሁ እንዳለሁ አውቃለሁ” ብላለች። በዛሬው ጊዜ በጣም ብዙ ወጣቶች የኢርና ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው ማየቱ በእውነት የሚያስደስት ነገር ነው። ‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን በወጣትነታቸው ለማስታወስ’ ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖራቸዋልን?—መክብብ 12:1
16 ብዙ አቅኚዎች ዕድሜያቸው ገፍቷል። ከእነዚህ መካከል አንዷ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አባቷና ወንድሟ በጦርነቱ ሲዋጉ እንደተገደሉ ገልጻለች። እናቷና እህቷ ደግሞ በአንድ የድሆች መንደር ውስጥ ተገደሉ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ወንድ ልጅዋን በሞት ተነጠቀች። ዕድሜዋ በመግፋቱ የተነሣ እየደከመችና በጤና መጓደል እየተሠቃየች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቀደም ሲል ካጣቻቸው ቤተሰቦች በእጅጉ የሚበልጡ ቤተሰቦች ሰጥቷታል። እንዲሁም የዘወትር አቅኚ ሆና ሌሎችን በመርዳት እየተደሰተች ነው።
17, 18. እያንዳንዳችን አቅኚዎች ሆንም አልሆን የአቅኚነትን መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
17 እርግጥ ነው፣ ሁሉም ሰው አቅኚ ሊሆን አይችልም። እያንዳንዳችን ካለንበት ሁኔታ አንጻር የምናቀርበው አሥራት ምንም ይሁን ምን ይሖዋ አሥራታችንን በሙሉ ማለትም ልናቀርበው የምንችለውን ምርጥ ነገር ለመቀበል ፈቃደኛ ነው። (ሚልክያስ 3:10 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) በእርግጥም ሁላችንም የእነዚህን ቀናተኛ ምሥክሮች መንፈስ መኮትኮትና የምሥራቹን ስብከት ሥራ ይበልጥ ለማራመድ ሁኔታዎቻችን የሚፈቅዱልንን ሁሉ ለማድረግ እንችላለን።
18 ለምሳሌ ያህል በአውስትራሊያ ሚያዝያ 16 ከመንገድ ወደ መንገድ ምሥክርነት የሚሰጥበት ልዩ ቀን እንዲሆን ተወስኖ ነበር። በዚያ ወር በተመዘገበው 58,780 የአስፋፊዎች አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ላይ እንደታየው ይህ ዘመቻ በአስፋፊዎቹና በአቅኚዎቹ ጥሩ ድጋፍ አግኝቶ ነበር። በተጨማሪም የተሰራጩት መጽሔቶች ባለፈው ዓመት በዚያው ወር ከተበረከቱት መጽሔቶች በ90,000 ብልጫ አላቸው። በዚያ ልዩ ቀን አንዲት እህት መጽሔቶችን ለአንድ ሰው አበረከተችና ፍላጎቱን ለመኮትኮት በማሰብ ስሙንና አድራሻውን በምትጽፍበት ጊዜ ዘመዳሞች መሆናቸውን አወቀች! ለ30 ዓመታት ያልተገናኙ የእህትማማች ልጆች ነበሩ። ይህም አስደሳች ተመላልሶ መጠየቆችን ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እንደፈጠረ አያጠራጥርም!
እስከ ፍጻሜው ንጹሕ አቋሟችሁን ጠብቃችሁ ኑሩ
19. የይሖዋ ጻድቅ ብሔር እስከ ፍጻሜው ድረስ ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ መኖሩ አጣዳፊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 የሰይጣን ዓለም ወደ ሞት አፋፍ እየቀረበ በሄደ መጠን የአምላክ ጻድቅ ብሔር በሙሉ ንጹሕ አቋሙን ሳያጎድፍ መኖሩ አጣዳፊ ጉዳይ ነው። በቅርቡ የይሖዋ ቅዱስ ሕዝብ የሚከተለውን ጥሪ ይሰማል፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ ና ወደ ቤትህም ግባ፣ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” ይህ በደም አፍሳሽነት ተጠያቂ የሆነ ዓለም የመለኮታዊ ፍርድ ቀማሽ መሆኑ አይቀሬ ነው። “በምድር በሚኖሩት ላይ በበደላቸው ምክንያት ቁጣውን ያመጣባቸው ዘንድ፣ እነሆ፣ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፣ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።” (ኢሳይያስ 26:20, 21) እያንዳንዳችን ከይሖዋ ጻድቅ ብሔር ጋር በመቀላቀል ንጹሕ አቋማችንን የማናጎድፍ ክርስቲያኖች ሆነን ጸንተን እንኑር። ከዚያ በኋላ በክርስቶስ መንግሥት ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ግዛት ውስጥ የዘላለም ሕይወት በማግኘት እንደሰታለን።
ታስታውሳለህን?
◻ “ጻድቁ ብሔር” የተወለደው መቼ ነው?
◻ በእነዚህ መጨረሻ ቀኖች የአምላክ ሕዝብ ጽናት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
◻ በ1994 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት ላይ የሚታየው ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥርና በአገልግሎት ላይ የዋለው ሰዓት ምን ያሳያል?
◻ ይህ ዓለም ወደ ፍጻሜው በጣም እየቀረበ ሲሄድ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ከአምላክ ጻድቅ ብሔር ጋር የተቀላቀሉ ሁሉ ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ መኖር ያለባቸው ለምንድን ነው?
[ከገጽ 12-15 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
የይሖዋ ምሥክሮች የ1994 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፍ ሪፖርት
(መጽሔቱን ተመልከት)
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ ጻድቅ ብሔር ውስጥ ያሉ ንጹሕ አቋሟቸውን ሳያጎድፉ የሚኖሩ ሰዎች ፍጽምና ያለው የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ