መሸሸጊያቸው ሐሰት ነው!
“ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና በሐሰትም ተሰውረናልና”—ኢሳይያስ 28:15
1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የትኛው ድርጅት ነው በጥንቷ የይሁዳ መንግሥት ላይ የደረሰውን ነገር ማስተዋል ያለበት? (ለ) ይሁዳ በማይረባ ነገር ላይ እምነት የጣለችው እንዴት ነው?
እነዚያ ቃላት በጥንቷ ይሁዳ የሁለት ነገድ መንግሥት ላይ እንደሠሩ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ላለችው ሕዝበ ክርስትናም ይሠራሉን? በእርግጥ ይሠራሉ! ያ ተመሣሣይነት ደግሞ ለዘመናዊቷ ሕዝበ ክርስትና መጥፎ እንደሚመጣባት የሚያስጠነቅቅ ምልክት ነው። ይህ ማለት ከሐዲዋ ሃይማኖታዊት ድርጅት በቅርቡ ብትንትኗ ይወጣል ማለት ነው።
2 ከይሁዳ በስተሰሜን የአሥሩ ነገድ የእሥራኤል መንግሥት ትገኝ ነበር። እሥራኤል እምነተ ቢስ በሆነች ጊዜ ይሖዋ በ740 ከዘአበ በአሦር ድል ሆና እንድትያዝ አደረገ። እህቷ የይሁዳ መንግሥት ለዚህ ሁኔታ የዓይን ምሥክር ነበረች። ዳሩ ግን ይህ ዓይነቱ ነገር በሷ ላይ ፈጽሞ የማይደርስ መሰላት። ምክንያቱም መሪዎቿ እንደሚከተለው እያሉ በመኩራራት ይናገሩ ነበር፦ ‘የይሖዋ ቤተመቅደስ የሚገኘው በኢየሩሳሌም አይደለም እንዴ? እኛስ የአምላክ ምርጥ ሕዝብ አይደለንም እንዴ? ካህናቶቻችንና ነቢያቶቻችን በይሖዋ ስም ይናገሩ የለም እንዴ?’ (ከኤርምያስ 7:4, 8-11 ጋር አወዳድሩ) እነዚያ የሃይማኖት መሪዎች የሚያሰጋቸው ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኞች ነበሩ። ይሁን እንጂ ተሳስተው ነበር! እነሱም እንደ ሰሜኖቹ ወገኖቻቸው እምነተቢስ ነበሩ። ስለዚህ በሰማሪያ ላይ የደረሰው በኢየሩሳሌምም ላይ መድረስ ነበረበት።
3. ስለ መጪው ጊዜ ሕዝበ ክርስትና የምትተማመነው ለምንድንነው? ይሁን እንጂ ለትምክህቷ ጥሩ ምክንያት አላትን?
3 በተመሳሳይ መንገድ ሕዝበ ክርስትና ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና እንዳላት ትናገራለች። እሷም እንደሚከተለው እያለች ጉራዋን ትነዛለች፦ “በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትና በሙያቸው ቀሳውስት የሆኑ አገልጋዮች፤ እንደዚሁም በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችኮ አሉን። መጽሐፍ ቅዱስም አለን። በአምልኰአችንም የኢየሱስንም ስም እንጠቀምበታለን። በአምላክ የተወደድን እንደሆንን እርግጠኛ ነገር ነው!” ይሁን እንጂ በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው እንደ ከባድ ማስጠንቀቂያ ያገለግላል። ምንም እንኳን በቅርቡ ያልተጠበቁ ፖለቲካዊ ለውጦች ቢደረጉም ይሖዋ በሕዝበ ክርስትናና በሌሎች የሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ ወሳኝ እርምጃ እንደሚወስድ እናውቃለን።
“ከሞት ጋር ቃል ኪዳን”
4. ይሁዳ ምን ቃል ኪዳን አድርጌአለሁ ብላ ታስብ ነበር?
4 በጥንት ዘመን እምነት አጉዳይዋ ኢየሩሳሌም በእውነተኞቹ የአምላክ ነቢያት አማካኝነት ብዙ ማስጠንቀቂያዎች ደርሰዋት ነበር፤ ግን አላመነችም። ከዚህ ይልቅ ሞት በሰሜናዊው የእሥራኤል መንግሥት ላይ እንዳደረገው እሷን ወደ ሲዖል ማለትም ወደ መቃብር እንደማይወስዳት ተኩራርታ ትናገር ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ ለይሁዳ የሚከተለውን እንዲነግራት በመንፈስ ተገፋፍቶ ነበር፦ “ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። እናንተም ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ብላችኋል።”—ኢሳይያስ 28:14, 15
5. (ሀ) ይሁዳ ከሞት ጋር አለኝ የምትለው ቃል ኪዳን ምን ነበር? (ለ) ይሁዳ የዘነጋችው ለንጉሥ አሣ የተሰጠውን የትኛውን ማስጠንቀቂያ ነበር?
5 አዎን፤ የኢየሩሳሌም መሪዎች ከተማቸው ሳትጠፋ ትኖር ዘንድ ከሞትና ከሲዖል ጋር የተስማሙ መስሏቸው ነበር። ግን ኢየሩሳሌም ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ማድረጓ ስለ ኃጢአትዋ ንስሐ ገብታለች፣ ለመዳንም አሁን በይሖዋ ተማምናለች ማለት ነበርን? (ኤርምያስ 8:6, 7) በፍጹም እንደዚያ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዕርዳታ ለማግኘት ወደ ሰብዓዊ ፖለቲካዊ መሪዎች ፊቷን አዞረች። ይሁን እንጂ በዓለማዊ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቿ ላይ መመካቷ ከንቱና ሐሰት ነበር። የተማመነችባቸው ዓለማውያን ሊያድኗት አይችሉም። ይሖዋን ስለተወችውም ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ትቷት ነበር። ነቢዩ አዛሪያስ ንጉሥ አሳን “እናንተ ከይሖዋ ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተውት ግን ይተዋችኋል” በማለት ያስጠነቀቀው በእርሷ ላይ ደረሰ።—2 ዜና 15:2
6, 7. ይሁዳ ለደህንነቷ ዋስትና ለማግኘት ምን እርምጃዎችን ወሰደች? ከምንስ የመጨረሻ ውጤት ጋር?
6 በፖለቲካዊ ወዳጆቻቸው ላይ በመመካት የኢየሩሳሌም መሪዎች “የሚትረፈረፍ መቅሰፍት” የሆኑ ምንም ዓይነት ወራሪ ሠራዊት ሰላማቸውንና ደኅንነታቸውን ለማወክ እንደማይቀርባቸው እርግጠኞች ነበሩ። ይሁዳ ከእሥራኤልና ከሦሪያ የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞች ወረራ ሲቃጣባት እርዳታ ለማግኘት ወደ አሦር ዘወር አለች። (2 ነገሥት 16:5-9) በኋላ የባቢሎናውያን የጦር ሠራዊት ኃይሎች ሲመጡባት ድጋፍ ለማግኘት ግብጽን ጠየቀች፤ ፈርዖንም ለዕርዳታ ሠራዊቱን በመላክ ምላሽ ሰጠ።—ኤርምያስ 37:5-8፤ ሕዝቅኤል 17:11-15
7 ይሁን እንጂ የባቢሎን ኃይሎች በጣም ስለበረቱባቸው የግብጽ ሠራዊት ማፈግፈግ ግድ ሆነበት። ኢየሩሳሌም በግብጽ ላይ እምነቷን መጣሏ ስሕተት ሆነ። ይሖዋም በ607 ከዘአበ አስቀድሞ የተነገረለት ጥፋቷ ሲመጣ አላስጣላትም። እንግዲያውስ የኢየሩሳሌም መሪዎችና ካህናት ተሳስተው ነበር! ሰላምንና ከወረራ ጥበቃን ለማግኘት በዓለማዊ የጦር ቃል ኪዳን ወዳጆች ላይ የጣሉት ትምክሕት በባቢሎን ሠራዊቶች ድንገት ደራሽ ጐርፍ ተጠርጎ የተወሰደ “ሐሰት” ነበር።
“የተፈተነውን የማዕዘን ድንጋይ” አለመቀበል
8. ሕዝበ ክርስትና ከጥንቷ ይሁዳ ጋር በጣም የሚመሳሰል አቋም የወሰደችው እንዴት ነው?
8 ዛሬስ ተመሳሳይ ሁኔታ አለን? አዎን አለ። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ምንም መከራ እንደማይደርስባቸው ይሰማቸዋል። ኢሳይያስ እንደተነበየው “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናልና፤ ከሲዖልም ጋር ተማምለናልና ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፤ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሰፍት ቢመጣም አይደርስብንም” የሚሉ ያህል ነው። (ኢሳይያስ 28:15) እንደ ጥንቷ ኢየሩሳሌም ሁሉ ሕዝበ ክርስትናም ለደህንነቷ ዋስትና ለማግኘት የምትጠባበቀው ከዓለማዊ ወዳጆቿ ነው። ስለዚህ ቀሳውስቷ ወደ ይሖዋ ተጠግተው እርሱን መሸሸጊያቸው ለማድረግ እምቢ ብለዋል። ስሙንም እንኳ አይጠሩም። ያንን ስም የሚያከብሩትንም ሰዎች ያላግጡባቸዋል፤ ያሳድዷቸዋልም። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ልክ የአይሁድ የካህናት አለቆች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ኢየሱስን ባልተቀበሉ ጊዜ የወሰዱትን ዓይነት አቋም ወስደዋል። እነርሱም “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው ነበር።—ዮሐንስ 19:15
9. (ሀ) ኢሳይያስ ይሁዳን ያስጠነቅቅ እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ሕዝበ ክርስትናን እያስጠነቀቀ ያለው ማነው? (ለ) ሕዝበ ክርስትና ዘወር ማለት ያለባት ወደማን ነው?
9 ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች የፍርድ አስፈጻሚ ሠራዊት እንደ ጐርፍ ሕዝበ ክርስትናን በቅርቡ ሊጠራርጋት እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ። ከዚህም በላይ ከዚያ ጐርፍ መዳን የሚቻልበትን እውነተኛ መሸሸጊያ ምን እንደሆነም ያመለክታሉ። “ስለዚህ ጌታ [ይሖዋ (አዓት)] እንዲህ ይላል እነሆ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም” የሚለውን ኢሳይያስ 28:16ን ይጠቅሳሉ። ይህ ክቡር የማዕዘን ራስ ድንጋይ ማነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ እነዚህን ቃላት ጠቅሶ ለኢየሱስ ክርስቶስ አውሏቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:6) ሕዝበ ክርስትና ይሖዋ ከሾመው ንጉሥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሰላምን ለመመሥረት ፈልጋ ቢሆን ኖሮ ከመጭው የሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ልትድን ትችል ነበር።—ከሉቃስ 19:42-44 ጋር አወዳድሩ።
10. ሕዝበ ክርስትና በምን ውስጥ ገብታ ተጠላልፋለች?
10 ይሁን እንጂ እንዲህ አላደረገችም። ከዚህ ይልቅ ምንም እንኳን ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን ከአምላክ ጋር ጠላትነት ነው ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ቢያስጠነቅቅም ሕዝበ ክርስትና ሰላምና ለደኅንነቷ ዋስትና ለማግኘት በመንግሥታት ፖለቲካዊ መሪዎች ዘንድ ለመወደድ ትለማመጣለች። (ያዕቆብ 4:4) ከዚህም በላይ በ1919 የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የሰው ልጅ ከሁሉ የበለጠ የሰላም ተስፋ ነው ብላ አጥብቃ ደግፋለች። ከ1945 ጀምሮ ደግሞ ተስፋዋን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ አድርጋለች። (ከራእይ 17:3, 11 ጋር አወዳድር) ከዚህ ድርጅት ጋር ያላት መጠላለፍስ ምን ያህል ሰፊ ነው?
11. ሃይማኖት በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ምን ውክልና አለው?
11 በቅርቡ የወጣ መጽሐፍ የሚከተለውን በተናገረ ጊዜ ለመልሱ ፍንጭ ይሰጠናል፦ “ከሃያ አራት የማያንሱ የካቶሊክ ድርጅቶች በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ እንደራሴዎች አሏቸው። አያሌ የዓለም ሃይማኖት መሪዎች ዓለም አቀፉን ድርጅት ጐብኝተዋል። በጣም የማይረሱት ጉብኝቶች በ1965ቱ ጠቅላላ ስብሰባ ወቅት ብጹዕነታቸው ፓፓ ጳውሎስ ስድስተኛና በ1979 ደግሞ ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ናቸው። ብዙ ሃይማኖቶች ለተባበሩት መንግሥታት የሚያደርጓቸው ልመናዎች፣ ጸሎቶች፣ መዝሙሮችና ቅዳሴዎች አሏቸው። ልቀው የሚታዩት ምሳሌዎችም የካቶሊክ፣ የዩኒታሪያን ዩኒቨርሳሊስት፣ የባፕቲስትና የባሃይ እምነቶች ናቸው።”
ለሰላም ከንቱ ተስፋዎች
12, 13. ሰላም በአድማሱ ላይ እየታየ ነው የሚል የተዛመተ ተስፋ ቢኖርም የይሖዋ ምሥክሮች ማስጠንቀቂያዎቻቸው እውነት ለመሆናቸው እርግጠኞች የሆኑት ለምንድነው?
12 ከዓለም ከፍተኛ የፖለቲካ መሪዎች አንዱ “ዛሬ በምድር ላይ ያለው ይህ ትውልድ በሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ የማይቀለበስ የሰላም ዘመን ሲገባ የዓይን ምሥክር ሊሆን ይችላል” ብለው በተናገሩ ጊዜ የብዙዎችን ተስፋ አስተጋብተዋል። ትክክል ነበሩን? በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት ሁኔታዎች ይሖዋ በአሕዛብ ላይ የጥፋት ፍርዱን እንደሚያስፈጽም የይሖዋ ምሥክሮች ያወጁት ቃል እንደማይፈጸም ያሳያሉን? የይሖዋ ምሥክሮች ተሳስተዋልን?
13 በፍጹም አልተሳሳቱም። እምነታቸውን ያደረጉት በይሖዋና የእውነት ቃሉ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሆነ እውነቱን እየተናገሩ እንዳሉ ያውቃሉ። ቲቶ 1:2 “እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም” ይላል። ስለዚህ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አንድ ነገር ይሆናል ካለ ሳይፈጸም እንደማይቀር ሙሉ ትምክህት አላቸው። ይሖዋ ራሱ “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል። የምሻውን ያደርጋል። የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” ብሏል።—ኢሳይያስ 55:11
14, 15. (ሀ) ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋቷ ጥቂት ቀደም ብሎ የይሁዳ መሪዎች ምን እያሉ ይለፍፉ ነበር? (ለ) በዚህ ዓለም ላይ ድንገተኛ ጥፋት ከመምጣቱ በፊት ጳውሎስ ይታወጃል ያለው ነገር ምንድንነው? (ሐ) በ1 ተሰሎንቄ 5:3 ላይ ትንቢት የተነገረለት አዋጅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ምን ልንጠብቅ እንችላለን?
14 ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታት መሪዎቿ “ሰላም ነው” “ሰላም ነው” እያሉ ይለፍፉ እንደነበረ ኤርምያስ ይነግረናል። (ኤርምያስ 8:11) ይሁን እንጂ ያ ሐሰት ነበር። በመንፈስ ተገፋፍተው የተናገሩት የይሖዋ እውነተኛ ነቢያት ማስጠንቀቂያ ይፈጸም ዘንድ ኢየሩሳሌም ጠፍታለች። በዘመናችንም ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጸም ሐዋርያው ጳውሎስ አስጠንቅቋል። ሰዎች ‘ሰላምና ደህንነት ሆነ!’ እያሉ እንደሚለፍፉ ሆኖም ያኔ “ጥፋት በድንገት” እንደሚመጣባቸው ተናግሯል።—1 ተሰሎንቄ 5:3
15 ወደ 1990ዎቹ ዓመታት ስንገባ በየስፍራው ያሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ቀዝቃዛው ጦርነት እንዳበቃና በመጨረሻው የዓለም ሰላም ብቅ ማለቱን እየተናገሩ ነው። ይሁን እንጂ ያኔ በመካከለኛው ምሥራቅ ኃይለኛ ጦርነት ፈነዳ። ይሁንና ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ የዓለም ሁኔታ በ1 ተሰሎንቄ 5:2,3 ትንቢት የተነገረለት “ሰላምና ደህንነት” ሆነ የሚል ልፈፋ ከፍተኛው ደረጃ ላይ እስኪደርስ እየጨመረ ይሄዳል። ተስፋችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ ሆኖ ስለተጣበቀ ያ ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ የአምላክ የጥፋት ፍርድ በፍጥነትና ያለ አንዳች መሳሳት እንደሚፈጸም እናውቃለን። ምንም ዓይነት የተጠጋገነ የሰላምና ደህንነት አዋጅ አምላክ በትንቢት ያስነገረው ጥፋት አይመጣም ብለን እንድናስብ ሊያደርገን አይገባም። የይሖዋ ፍርዶች በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደማይለወጡ ሆነው ተመዝግበዋል። ሕዝበ ክርስትና ከሌሎች የሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ጋር ትጠፋለች። ከዚያም የይሖዋ የጥፋት ፍርድ በተቀረው የሰይጣን ዓለም ላይ ይፈጸማል። (2 ተሰሎንቄ 1:6-8፤ 2:8፤ ራእይ 18:21፤ 19:19-21) የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋ ቃሉን እንደሚፈጽም እርግጠኞች ስለሆኑ በታማኝና ልባም ባሪያው ክፍል እየተመሩ ነቅተው መጠባበቃቸውንና የዓለም ሁኔታዎች ምን ቅርጽ በመያዝ ላይ መሆናቸውን በጥንቃቄ መከታተላቸውን ይቀጥላሉ። (ማቴዎስ 24:45-47) ሰዎች ምንም ዓይነት ሰላምን የማምጣት ጥረት ቢያደርጉ ይሖዋ የኃጢአት ጫና በተሸከመችው ሕዝቡ ክርስትና ላይ የጥፋት ወጀብ ለማምጣት ያለውን ዓላማ ትቶታል ብለን እንድናስብ ሊያደርገን አይገባም።
“አምላክ መሸሸጊያችን ነው”
16, 17. የይሖዋ ምሥክሮች እውነቱን አፍረጥርጦ የሚገልጽ መልእክት ስላቀረቡ አንዳንዶች ቅር ቢላቸው ምሥክሮቹ ምን መልስ ይሰጣሉ?
16 የይሖዋ ምሥክሮች እውነቱን ፍርጥርጥ አድርገው በመናገራቸው አንዳንዶች ቅር ይላቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች መጠጊያ ያደረጉት ሐሰተኛ ነገር መሆኑን ሲናገሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መናገራቸው ብቻ ነው። ሕዝበ ክርስትና የዓለም ክፍል በመሆኗ ቅጣት ይገባታል ሲሉም አምላክ ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገረውን መግለጻቸው ብቻ ነው። (ፊልጵስዩስ 3:18, 19) ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና እምነቷን የምትጥለው በዓለም ድርጅቶች ላይ በመሆኑ እንደ እውነቱ ከሆነ እየደገፈች ያለችው የሐሰት አባት መሆኑን ኢየሱስ የተናገረለትን የዚህን ዓለም አምላክ ሰይጣን ዲያብሎስን ነው።—ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4
17 ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች አቋማቸውን እንደሚከተለው በማለት ያስታውቃሉ፦ እኛ በበኩላችን የዓለም ፖለቲካዊ መድረክ በመለወጡ ምክንያት በሐሰተኛ የዓለም ሰላም ተስፋ ማድረግን አናበረታታም። በዚህ ፋንታ የሚከተሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት መልሰን እናስተጋባለን፦ “እግዚአብሔር . . . መጠጊያችን ስለሆነ ችግራችሁን ሁሉ ለእርሱ ንገሩት ሰዎች ሁሉ ተንኖ እንደሚጠፋ ትንፋሽ ናቸው፤ ታናናሾችም ሆኑ ታላላቆች ሁሉም ከንቱ ናቸው። በሚዛን ቢመዘኑ ምንም ክብደት የላቸውም። ከትንፋሽ እንኳ የቀለሉ ናቸው።” (መዝሙር 62:8, 9) ሕዝበ ክርስትናንና የቀረውን የዚህን የነገሮች ሥርዓት ለማጠናከርና ለመጠበቅ የሚደረገው የሰው ሙከራ ሁሉ ውሸት፣ ሐሰትም ነው! ከአፍ የሚወጣ የሞቀ አየር የይሖዋን ዓላማዎች ለማክሸፍ እንደማይችል ሁሉ እነርሱም እንደዚያ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ኃይል የላቸውም!
18. ለአሁኑ ጊዜ ተገቢ የሆነው የትኛው የመዝሙራዊው ማስጠንቀቂያ ነው?
18 የይሖዋ ምሥክሮች በተጨማሪ እንደሚከተለው የሚናገረውን መዝሙር 33:17-19ን ይጠቅሳሉ፦ “ፈረስም [ጦርነትን የሚያመለክተው የግብጽ ፈረስ] ከንቱ ነው፤ አያድንም፤ ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም፤ እነሆ የይሖዋ ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፤ በምህረቱም ወደሚታመኑ ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ።” በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በይሖዋና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ብቸኛ ዝግጅቱ በሆነው ሰማያዊው መንግሥቱ ላይ ትምክሕታቸውን ይጥላሉ።
ሕዝበክርስትና “መረገጫ ሥፍራ”
19. ፖለቲካዊ ድርጅቶችም የዓለም ሰላም ያመጣሉ ብሎ መተማመን ሞኝነትና ሐሰት የሆነው ለምንድን ነው?
19 በአምላክ መንግሥት ፋንታ በምንም ዓይነት ሰው ሰራሽ ምትክ ላይ እምነት መጣል ያንን ምትክ የሚመለክበት ምስል ያደርገዋል። (ራእይ 13:14, 15) ስለዚህ ሰላምንና የደኅንነት ዋስትና ያመጣል ብሎ እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመሰሉ ፖለቲካዊ ተቋሞች ላይ እምነትን እንዲጥሉ ማበረታታት ሊጨበጥ የማይችል ነገር፣ ሐሰትም ነው። ሐሰተኛ ተስፋ የሚጣልባቸው እንዲህ ዓይነት ነገሮችን በሚመለከት ኤርምያስ “ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና እስትንፋስም የላቸውምና እነሱ ምናምንቴና የቀልድ ሥራ ናቸው። በተጎበኙ ጊዜ ይጠፋሉ” ብሏል። (ኤርምያስ 10:14, 15) ስለዚህ የግብጽ አምሳያ የሆኑት የጦርነት ፈረሶች ማለትም የዘመናችን መንግሥታት ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኃይል በውድቀቷ ቀን ሕዝበ ክርስትናን አያድኗትም። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ከዚህ ዓለም ጋር የፈጠሩት ኅብረት ምንም ሳያስጥላቸው ይቀራል።
20, 21. (ሀ) የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ምን ደረሰበት? (ለ) ሕዝበ ክርስትና ከዓለም ጋር ያላት ሽርክና እንደማያድናት ኢሳይያስ ያሳየው እንዴት ነው?
20 ሕዝበ ክርስትና ተስፋዋን በመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ላይ ጥላ ነበር። ይሁን እንጂ እሱ አርማጌዶን እንኳ ሳይመጣ ተገለበጠ። አሁን ደግሞ ታማኝነቷን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዛውራለች። ይሁን እንጂ እሱም በቅርቡ “ታላቁና ሁሉን የሚችለው የእግዚአብሔር ጦርነት ቀን” ይመጣበታል። ከዚያም አያመልጥም። (ራእይ 16:14) እንደገና ሕይወት የተሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቢሆን ሰላምንና ዋስትና ያለው ኑሮ ሊያመጣ አይችልም። የአምላክ ትንቢታዊ ቃል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአባል መንግሥታቱ ጋር ሆኖ ‘ከበጉ [በመንግሥታዊ ሥልጣን ላይ ካለው ከክርስቶስ ጋር] እንደሚዋጉና እሱ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ እንደሚያሸንፋቸው’ ያሳያል።—ራእይ 17:14
21 ከሰይጣን ዓለም ጋር ኅብረት ፈጥራ ያለችው ሕዝበ ክርስትና መዳን እንደማትችል የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጠኛነት ይናገራሉ። ይህን በሚናገሩበት ጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚናገረውን ማመልከታቸው ብቻ ነው። ኢሳይያስ 28:17, 18 ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ እንደሚናገር ይጠቅሳል፦ “ፍትሕን የመሠረቱ መለኪያ ጽድቅንም ቱምቢ አደርጋለሁ። በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል። ውሆችም መሠወሪያውን እንደ ጐርፍ ይጠራርጉታል። ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል። ከሲዖል ጋር የተማማላችሁት መሃላ አይጸናም። የሚትረፈረፍ ጐርፍ ባለፈ ጊዜ ትረግጡበታላችሁ።” አዓት
22. በሕዝበ ክርስትና ላይ ፍጹም ፍትሕ ሲፈጸም ውጤቱ ምን ይሆናል?
22 የይሖዋ የፍርድ ውሳኔዎች በፍጹም ፍትህ መሠረት ይፈጸማሉ። የሕዝበ ክርስትና መተማመኛ መሠረትም “ከሞት ጋር ያደረገችው ቃል ኪዳን” በድንገት ደራሽ ጐርፍ እንደሚጠረግ ያህል ይሆናል። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ማለዳ ማለዳ ቀንና ሌሊት ያልፋል። ወሬውንም (የተሰማውን ነገር) ማስተዋል ድንጋጤ (ብቻ) ይሆናል።” (ኢሳይያስ 28:19) ለተመልካቾች ሁሉ የይሖዋን ፍርድ ሙሉ ኃይል ማየት ምን ያህል የሚያሸብር ይሆናል! የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና ተከታዮቻቸው የተማመኑበት ነገር ሐሰት እንደነበረ ሰዓቱ ካለፈባቸው በኋላ መገንዘቡ እንዴት የሚያሰቅቅ ይሆን!
የይሖዋ ስም “የጸና ግንብ”
23, 24. የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ዓለም ላይ ተጠግተው ለደኅንነታቸው ዋስትና ለማግኘት ከመፈለግ ይልቅ ምን ያደርጋሉ?
23 የይሖዋ ምሥክሮችስ? ዓለም አቀፍ ጥላቻና ስደት እያጋጠማቸውም እንኳን ከዓለም የተለዩ ሆነው በመኖር ይቀጥላሉ። ኢየሱስ ስለ ተከታዮቹ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነሱም ከዓለም አይደሉም” ብሎ የተናገረውን ፈጽሞ አይረሱም። (ዮሐንስ 17:16) በእነዚህ የፍጻሜ ዘመናት ሁሉ እምነታቸውን በሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ ሳይሆን በይሖዋ መንግሥት ላይ ጥለዋል። ስለዚህ በሕዝበ ክርስትና ላይ የሚወርደው የመከራ ዶፍ የይሖዋ ምሥክሮችን አያሸብራቸውም። ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሚያምን [አይሸበርም። (አዓት)]”—ኢሳይያስ 28:16
24 ምሳሌ 18:10 “[የይሖዋ (አዓት)] ስም የጸና ግንብ ነው ጻድቅ ወደርሱ ሮጦ መጠጊያ ያገኛል” ይላል። ስለዚህ በግ መሰል ሰዎች ሁሉ እምነታቸውን በይሖዋና በክርስቶስ በኩል በሚመራው መንግሥቱ ላይ እንዲያደርጉ እንጋብዛለን። ይሖዋ ከአደጋ መሸሸጊያ በመሆን በኩል ሐሰት አይደለም! በክርስቶስ የሚመራው መንግሥቱም ውሸት አይደለም! የሕዝበ ክርስትና መሸሸጊያ ሐሰት ነው፤ የእውነተኛ ለክርስቲያኖች መሸሸጊያ ግን እውነት ነው።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ የጥንቷ ይሁዳ ሐሰትን መሸሸጊያ ያደረገችው እንዴት ነው?
◻ ሕዝበ ክርስትና ራሷን በሐሰት ውስጥ ሰውራ ለማዳን የሞከረችው እንዴት ነው?
◻ ኢሳይያስ ይሁዳን ያስጠነቀቀው እንዴት ነው? ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ የሚናገሩት እንዴት ነው?
◻ ሕዝበ ክርስትና እምነቷን ባልባሌ ቦታ ላይ እንደጣለች የምትገነዘበው እንዴት ነው?
◻ ከሕዝበ ክርስትና በሚቃረን መንገድ የይሖዋ ምሥክሮች የያዙት ምን አቋም ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው እየተነገረለት ነው
“ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ኅብረተሰብ አንድ ሆኖአል። የተባበሩት መንግሥታት ጥሩ መሪ ይሆናል ተብሎ የተደረገው ተስፋ ዛሬ መሥራቾቹ ከሩቅ ያዩት ነገር እውን ሆኖአል። . . . ስለዚህ ዛሬ ለረጅም ዘመን ተስፋ የተደረገለትን አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማስገኘት አጋጣሚውን ዓለም ሊጠቀምበት ይገባል።”—የዩናይትድ ስቴትስ መሪ ፕሬዚዳንት ቡሽ ለሕዝባቸው ጥር 29, 1991 ያደረጉት ንግግር