ሐሰተኛ መልእክተኞች ሰላም የላቸውም!
“ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” — መዝሙር 37:9, 11
1. ‘በፍጻሜው ዘመን’ እውነተኛና ሐሰተኛ መልእክተኞች እንደሚኖሩ መጠበቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
ሐሰተኛ ወይስ እውነተኛ መልእክተኞች? ሁለቱም ዓይነት መልእክተኞች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ነበሩ። በእኛስ ዘመን? ዳንኤል 12:9, 10 ላይ ከሰማይ የመጣ አንድ መልእክተኛ ለአምላክ ነቢይ የሚከተለውን እንደተናገረ እናነባለን:- “ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤ ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፣ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ።” አሁን የምንኖረው በዚህ ‘የፍጻሜ ዘመን’ ነው። ታዲያ ‘በክፉዎች’ እና “ጥበበኞች” በሆኑ ሰዎች መካከል ጉልህ ልዩነት እንመለከታለንን? በእርግጥ እንመለከታለን!
2. ኢሳይያስ 57:20, 21 በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
2 በምዕራፍ 57 ቁጥር 20 እና 21 ላይ የአምላክ መልእክተኛ የነበረው ኢሳይያስ የተናገረውን ቃል እናነባለን:- “ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፣ ውኆቹም ጭቃና ጉድፍ ያወጣሉና። ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።” በእርግጥም ወደ 21ኛው መቶ ዘመን እየተቃረበ ያለው ይህ ዓለም የሚገኝበትን ሁኔታ በትክክል የሚገልጹ ቃላት ናቸው! እንዲያውም አንዳንዶች ‘እውነት 21ኛው መቶ ዘመን ላይ መድረስ እንችል ይሆን?’ ብለው ይጠይቃሉ። ታዲያ አስተዋይ የሆኑ መልእክተኞች ምን መልስ ይሰጡናል?
3. (ሀ) በ1 ዮሐንስ 5:19 ላይ ምን ነገር ተነጻጽሯል? (ለ) ‘አስተዋይ የሆኑት ሰዎች’ በራእይ ምዕራፍ ሰባት ላይ እንዴት ተገልጸዋል?
3 ሐዋርያው ዮሐንስ በመለኮታዊ መንፈስ አማካኝነት ልዩ የሆነ ማስተዋል አግኝቶ ነበር። 1 ዮሐንስ 5:19 “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደተያዘ እናውቃለን” ይላል። ከዚህ ዓለም በተቃራኒ ደግሞ ዕድሜያቸው እየገፋ የሄደ 144,000 መንፈሳዊ እስራኤላውያን አባላት ዛሬም ከእኛ ጋር አሉ። ዛሬ አስተዋዮች የሆኑ ከአምስት ሚልዮን በላይ የሆኑ “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ከእነርሱ ጋር እየተባበሩ ነው። “እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው።” ሽልማት ያገኙትስ ለምንድን ነው? በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን “ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም” ስላነጹ ነው። በተጨማሪም እነርሱም የብርሃን መልእክተኞች በመሆን ‘ቀንና ሌሊት [ለአምላክ] ቅዱስ አገልግሎት በማቅረብ ላይ ናቸው።’— ራእይ 7:4, 9, 14, 15
የሰላም መልእክተኛ ተብዬዎች
4. (ሀ) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉት የሰላም መልእክተኛ ተብዬዎች ሳይሳካላቸው የቀረው ለምንድን ነው? (ለ) ኤፌሶን 4:18, 19 በዛሬው ጊዜ የሚፈጸመው እንዴት ነው?
4 በሰይጣን ዓለማዊ ሥርዓት ውስጥ ያሉት “የሰላም መልእክተኞች” ነን ባዮችስ? ኢሳይያስ ምዕራፍ 33 ቁጥር 7 ላይ “እነሆ፣ ኃይለኞቻቸው በሜዳ ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ” የሚል እናነባለን። ይህ ቃል ሰላም ለማምጣት ከአንደኛው የዓለም ከተማ ወደ ሌላው ለሚማስኑት የዓለም መሪዎች ምንኛ እውነት ሆኗል! ከንቱ ልፋት ሆኖባቸዋል! ይህ የሆነው ለምንድን ነው? እነርሱ የሚደክሙት የዓለምን በሽታ ከምንጩ ለማጥፋት ሳይሆን የበሽታውን ምልክት ለማስታገሥ ብቻ ስለሆነ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎ የጠራው ሰይጣን መኖሩን መቀበል አይፈልጉም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ሰይጣን በሰው ልጆች ዓለም ውስጥ የክፋት ዘር ስለ ዘራ ብዙዎቹን የዓለም ገዥዎች ጨምሮ አብዛኞቹ ሰዎች በኤፌሶን 4:18, 19 ላይ የተገለጹትን ዓይነት ሰዎች ሆነዋል:- “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።”
5. (ሀ) ሰብዓዊ ድርጅቶች ሰላም ማምጣት የተሳናቸው ለምንድን ነው? (ለ) መዝሙር 37 ምን የሚያጽናና መልእክት ያስተላልፋል?
5 ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ያዋቀሩት የትኛውም ድርጅት በዛሬው ጊዜ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘውን ስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነትና ጥላቻ ከሰዎች ልብ ውስጥ ነቅሎ ለማውጣት አይችልም። ይህን ማድረግ የሚችለው ፈጣሪያችን የሆነው የአጽናፈ ዓለሙ ጌታ ይሖዋ ብቻ ነው! በተጨማሪም ከሰው ልጆች መካከል የእሱን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑት በጣም ጥቂቶች የሆኑ ቅን ሰዎች ብቻ ናቸው። እነዚህ ቅን ሰዎችና ክፉ የሆኑት የዓለም ሰዎች የሚያጋጥማቸው ሁኔታ በመዝሙር 37:9-11 ላይ በሚከተለው መንገድ ተነጻጽሯል:- “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፣ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ገና ጥቂት ኃጢአተኛም አይኖርም። . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”
6, 7. የሐሰት ሃይማኖቶች የሰላም መልእክተኞች ሆነው ማገልገል እንደማይችሉ የሚያሳየው የትኛው ታሪካቸው ነው?
6 የሰላም መልእክተኞች በዚህ ታማሚ በሆነ ዓለም ሃይማኖቶች ውስጥ ሊገኙ ይችሉ ይሆን? ሃይማኖቶች እስካሁን ድረስ ያስመዘገቡት ታሪክ ምን ይመስላል? ሃይማኖት ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ በነበሩት ደም መፋሰሶች ተካፋይ፣ እንዲያውም ቀስቃሽ እንደነበረ ከታሪክ ምዕራፎች መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በነሐሴ 30, 1995 ሳምንት የወጣው ክርስቺያን ሰንቸሪ የተባለው መጽሔት በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ስላለው ብጥብጥ እንዲህ ብሏል:- “በሰርቦች በተያዘው የቦስኒያ ግዛት ቄሶች ራሱን በራሱ በሰየመው የመንግሥት ምክር ቤት መቀመጫዎች ፊተኛ ረድፍ ይቀመጣሉ። ወታደራዊ ጓዶችና የጦር መሣሪያዎች ለውጊያ ከመሰማራታቸው በፊት ቡራኬ በሚቀበሉባቸው ቦታዎችም በግንባር ተሰልፈዋል።”
7 ሕዝበ ክርስትና ለአንድ መቶ ዓመት ያህል በአፍሪካ ያካሄደችው ሚስዮናዊ ሥራም ቢሆን ከዚህ የተሻለ ውጤት አላስገኘም። ይህንንም ከጠቅላላው ሕዝብ 80 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊኮች በሆኑባት በሩዋንዳ ከደረሰው ሁኔታ መመልከት ይቻላል። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በሐምሌ 7, 1995 እትሙ ላይ የሚከተለውን ዘገባ አውጥቶ ነበር:- “በሊዮ [ፈረንሣይ] የሚታተመው ጎልያ የተባለው ነጻ አስተሳሰብ የሚያራምድ የካቶሊክ ምዕመናን መጽሔት ባለፈው ዓመት በሩዋንዳ የተፈጸመውን ግድያ ያበረታቱ ወይም በግድያው የተካፈሉ 27 ተጨማሪ ሩዋንዳውያን ቄሶችንና አራት ደናግልን ማንነት ለማጋለጥ አቅዷል።” በለንደን የሚገኝ አፍሪካን ራይትስ የተባለ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ደግሞ “አብያተ ክርስቲያናት በኃላፊነት የሚጠየቁት ግድያውን በዝምታ በማለፋቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ቄሶችና ሰባኪዎች እንዲሁም ደናግል ዘር በማጥፋቱ ወንጀል በቀጥታ በመካፈላቸው ጭምር ነው” የሚል ትችት ሰንዝሯል። ይህም የይሖዋ እውነተኛ መልእክተኛ የነበረው ኤርምያስ ስለ እስራኤል ገዦች፣ ካህናትና ነቢያት ‘ኀፍረት’ ከገለጸው ጋር በጣም ይመሳሰላል። “በእጆችሽም የንጹሐን ድሆች ደም ተገኝቶአል” ሲል አክሎ ተናግሯል።— ኤርምያስ 2:26, 34
8. ኤርምያስ የሰላም መልእክተኛ ነበር ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
8 ኤርምያስ ብዙ ጊዜ የጥፋት ነቢይ ተብሎ የሚጠራ ቢሆንም የአምላክ ሰላም መልእክተኛ ተብሎም ሊጠራ ይችላል። ከእርሱ በፊት ከኖረው ከኢሳይያስ እኩል ስለ ሰላም ተናግሯል። ይሖዋ ኤርምያስን በኢየሩሳሌም ላይ የፍርድ መልእክት እንዲናገር ተጠቅሞበታል። እንዲህ ብሏል:- “ከፊቴ አስወግዳት ዘንድ ይህች ከተማ ከሠሩአት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቁጣዬንና መዓቴን ለማነሣሣት ሆናለችና፣ ይህም እኔን ያስቆጡኝ ዘንድ እነርሱና ነገሥታቶቻቸው አለቆቻቸውም ካህናቶቻቸውም ነቢያቶቻቸውም የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ስላደረጉት ስለ እስራኤል ልጆችና ስለ ይሁዳ ልጆች ክፋት ሁሉ ነው።” (ኤርምያስ 32:31, 32) ይህ ደግሞ ይሖዋ በዘመናዊቷ ሕዝበ ክርስትና ውስጥ በሚገኙ ገዥዎችና ቀሳውስት ላይ ለሚያመጣው ፍርድ ጥላ ሆኗል። እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ እነዚህ ክፋትና ጠብ ጠንሳሾች መወገድ ይኖርባቸዋል! የሰላም መልእክተኞች እንዳልሆኑ የተረጋገጠ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም ያመጣልን?
9. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም መልእክተኛ ነኝ ሲል የቆየው እንዴት ነው?
9 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውነተኛ የሰላም መልእክተኛ ሊሆን አይችልምን? እንዲያውም ሂሮሽማን ያወደመው አቶሚክ ቦምብ ከመጣሉ ከ41 ቀናት በፊት በሰኔ ወር 1945 የተረቀቀው ድርጅቱ የተቋቋመበት ቻርተር መቅድም የድርጅቱ ዓላማ “መጪዎቹን ትውልዶች ከጦርነት መቅሰፍት ለማዳን” እንደሆነ ይገልጻል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕጩ አባላት የሆኑት 50 የሚያክሉ መንግሥታት “ኃይላቸውን አስተባብረው ዓለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ” እንደሚያሰፍኑ ቃል ገብተው ነበር። በዛሬው ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች 185 የደረሱ ሲሆን ሁሉም ይህንኑ ዓላማ ለማስፈጸም የቆረጡ መሆናቸውን ይናገራሉ።
10, 11. (ሀ) ሃይማኖታዊ መሪዎች የተባበሩት መንግሥታትን የደገፉት እንዴት ነው? (ለ) ርዕሳነ ሊቀ ጳጳሳቱ ‘የአምላክን መንግሥት ምሥራች’ አዛብተው ያቀረቡት እንዴት ነው?
10 ባለፉት ዓመታት ሁሉ የተባበሩት መንግሥታት በተለይ ከሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ሲያገኝ ቆይቷል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ 23ኛ ሚያዝያ 11, 1963 በፊርማቸው አጽድቀው ለመላው ዓለም ባስተላለፉት “ፓከም ኢን ቴሪስ” (ሰላም በምድር) የተባለ መልእክት እንዲህ ብለው ነበር:- “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአወቃቀርና በአቅም ጎልብቶ የተጣለበትን ታላቅና ክቡር ኃላፊነት እንዲወጣ ልባዊ ምኞታችን ነው።” ቆየት ብሎ ደግሞ በሰኔ ወር 1965 ከዓለም ሕዝቦች ግማሹን የሚወክሉ ናቸው የተባሉ የሃይማኖት መሪዎች በሳን ፍራንሲስኮ ተሰብስበው 20ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የልደት ቀን አክብረዋል። በተጨማሪም በ1965 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ የተባበሩት መንግሥታትን ከጎበኙ በኋላ ድርጅቱ “የመጨረሻው የስምምነትና የሰላም ተስፋ” እንደሆነ ተናግረዋል። በ1986 ደግሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ ዓለም አቀፉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ዓመት ደግፈዋል።
11 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጥቅምት 1995 ባደረጉት ጉብኝትም “ዛሬ የአምላክን መንግሥት ምሥራች እያከበርን ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ እርሳቸው በእርግጥ የአምላክ መንግሥት ምሥራች መልእክተኛ ናቸውን? ስለ ዓለም ችግሮች ሲናገሩ ደግሞ “እነዚህን ግዙፍ ችግሮች ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሚጫወተው ሚና እንዴት እውቅና ሳንሰጥ ማለፍ እንችላለን?” ብለዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የመረጡት የአምላክን መንግሥት ሳይሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ነው።
‘አምርረው የሚያለቅሱበት’ ምክንያት
12, 13. (ሀ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤርምያስ 6:14 ላይ በተገለጸው መሠረት የሄደው እንዴት ነው? (ለ) በኢሳይያስ 33:7 ላይ ያለው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን አመራር የሚያካትት የሆነው ለምንድን ነው?
12 ሃምሳኛው የተባበሩት መንግሥታት ክብረ በዓልም ቢሆን “ሰላም በምድር” የሚሰፍንበትን ተጨባጭ የሆነ ተስፋ ሊሰጥ አልቻለም። ዘ ቶሮንቶ ስታር የተባለው የካናዳ ጋዜጣ ጸሐፊ ይህ የሆነበትን አንዱን ምክንያት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “የተባበሩት መንግሥታት አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጸም የሚጮህ፣ ግን አባሎቹ መንጋጋው ውስጥ እስኪያስገቡለት ድረስ ሳይናከስ የሚጠብቅ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው።” ብዙውን ጊዜ የዚህ ድርጅት ንክሻ ጊዜው ካለፈ በኋላ ዘግይቶ የሚሰነዘርና የማያሳምም ነው። በአሁኑ የዓለም ሥርዓት ያሉ በተለይም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉት የሰላም መልእክተኞች “የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፣ ሰላም ሳይሆን ሰላም፣ ሰላም ይላሉ” የሚለውን የኤርምያስ 6:14ን ቃል ሲያስተጋቡ ኖረዋል።
13 በየተራ የተነሱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊዎች ድርጅቱ የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በሚቻላቸው ሁሉ ከልባቸው እንደጣሩ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ የተለያየ ዓላማ ባላቸው 185 አባል አገሮች መካከል ጦርነቶችን መግታትን፣ አንድ ወጥ የሆነ ፖሊሲ መንደፍንና ገንዘብ ነክ ችግሮችን መፍታትን በሚመለከት የማያባራ ሽኩቻ ስላለ የድርጅቱ ዓላማዎች ከንቱ ሆነው ቀርተዋል። የወቅቱ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ስለ 1995 ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት “ዓለም አቀፋዊ የኑክሌር እልቂት ይደርሳል የሚለው ስጋት እየቀነሰ መምጣቱ ብሔራት ለመላው የሰው ዘር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ለማምጣት ተባብረው የሚሠሩበትን መንገድ ይከፍታል” ብለዋል። ይሁን እንጂ በመቀጠል “ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታዩት የዓለም ሁኔታዎች ይህን የመሰለ ብሩሕ ተስፋ እንዳይኖረን የሚያደርጉ መሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው” ብለዋል። በእርግጥም የሰላም መልእክተኛ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ‘በምሬት እያለቀሱ ነው።’
14. (ሀ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በገንዘብም ሆነ በሥነ ምግባር ኪሳራ ደርሶበታል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ኤርምያስ 8:15 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
14 ዚ ኦሬንጅ ካውንቲ ሬጅስተር በተባለ የካሊፎርኒያ ጋዜጣ የወጣ አምድ “የተባበሩት መንግሥታት በገንዘብና በሥነ ምግባር የከሰረ ድርጅት ነው” ብሏል። ጽሑፉ እንዳለው ከ1945 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት ከ80 የሚበልጡ ጦርነቶች ተደርገው 30 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ከዚያም በሪደርስ ዳይጀስት መጽሔት በጥቅምት 1995 እትም ላይ አንድ ጸሐፊ ያሉትን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “የተባበሩት መንግሥታት ወታደራዊ ዘመቻዎች መለያ ባሕርይ ‘ብቃት የጎደላቸው አዛዦች፣ ዲስፕሊን የሌላቸው ወታደሮች፣ ከጦረኛ ወገኖች ጋር ማበር፣ እልቂት እንዳይደርስ ለመከላከል አለመቻልና እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለሰቆቃው አስተዋጽኦ ማድረግ ሆኗል።’ ከዚህም በላይ ‘ብክነት፣ ማጭበርበርና ከአግባብ ውጭ የሆኑ ድርጊቶች አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።’” ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ50 ዓመት ዕድሜው” በሚል ክፍል ሥር “የአስተዳደር ጉድለትና ብኩንነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ታላላቅ ዓላማዎች እየናዱ ነው” የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር። በለንደን እየታተመ የሚወጣው ዘ ታይምስ የተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ “በ50 ዓመት ዕድሜው የተሽመደመደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥንካሬውን መልሶ ለማግኘት የብቃት ማጠናከሪያ መርኃ ግብር ያስፈልገዋል” የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ይዞ ወጥቶ ነበር። ሁኔታው ኤርምያስ ምዕራፍ 8 ቁጥር 15 ላይ እንደተገለጸው ሆኗል:- “ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፣ መልካምም አልተገኘም። መጠገንን በተስፋ ተጠባበቅን፣ እነሆም፣ ድንጋጤ ሆነ።” የኑክሌር እልቂት አሁንም በሰው ልጅ ላይ እንዳንዣበበ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የሰው ልጅ የሚያስፈልገው ሰላም መልእክተኛ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
15. የጥንቷ ባቢሎንና ሃይማኖታዊ ልጆቿ አጥፊና አደንዛኝ ሆነው የተገኙት እንዴት ነው?
15 ታዲያ የዚህ ሁሉ ነገር መጨረሻ ምን ይሆን? የይሖዋ ትንቢታዊ ቃል በማያሻማ ሁኔታ ይነግረናል። በመጀመሪያ ደረጃ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ለዚህን ያክል ረጅም ጊዜ የጠበቀ ወዳጅነት የነበራቸው የዓለም ሐሰተኛ ሃይማኖቶች ምን ይጠብቃቸዋል? እነዚህ ሃይማኖቶች ጣዖት አምላኪ ከሆነችው ከጥንትዋ ባቢሎን ጋር ከአንድ ምንጭ የተቀዱ ናቸው። በመሆኑም ራእይ 17:5 ላይ “ታላቂቱ ባቢሎን የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት” በሚል አጠቃላይ ስም መጠራታቸው ተገቢ ነው። ኤርምያስ ይህች ግብዝ ድርጅት የሚደርስባትን ጥፋት ገልጿል። እንደ አመንዝራ ሴት የምድር ፖለቲከኞችን ሲያባብሉ ኖረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሲያወድሱ ከመቆየታቸውም በተጨማሪ የድርጅቱ አባሎች ከሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ሕገ ወጥ ሽርክና መስርተዋል። በታሪክ ዘመናት በተደረጉት ጦርነቶች ዋነኛ ተካፋይ ነበሩ። አንድ የዜና ተንታኝ በሕንድ አገር ተደርጎ ስለ ነበረው የሃይማኖት ጦርነት እንዲህ ብለዋል:- “ካርል ማርክስ ሃይማኖት የብዙሐኑ ሕዝብ ማደንዘዣ ኦፒየም ነው ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ኦፒየም ሰዎችን የሚያፈዝና የሚያደነዝዝ ዕፅ በመሆኑ ይህ አባባል ትክክል ሊሆን አይችልም። ሃይማኖት ከፍተኛ ኃይል ባለው ኮኬይን ቢመሰል ተገቢ ይሆናል። በጣም አጥፊ ኃይል በመሆኑ ሰዎችን ለከፍተኛ ዓመፅና ጠብ ያነሳሳል።” ይሁን እንጂ እኚህም ጸሐፊ ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደሉም። የሐሰት ሃይማኖት የአጥፊነት እንዲሁም የማፍዘዝ እና የማደንዘዝ ባሕርይ አለው።
16. በአሁኑ ጊዜ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን መሸሽ ያለባቸው ለምንድን ነው? (በተጨማሪም ራእይ 18:4, 5ን ተመልከት።)
16 ታዲያ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? የአምላክ መልእክተኛ የሆነው ኤርምያስ መልሱን ይሰጠናል:- “ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ፣ እያንዳንዳችሁም ነፍሳችሁን አድኑ፤ . . . የእግዚአብሔር በቀል ጊዜ ነውና።” በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን መዳፍ በመውጣታቸው ደስ ይለናል። አንተ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ነህን? ከሆንክ ታላቂቱ ባቢሎን በምድር ብሔራት ላይ ያስከተለችውን ሁኔታ ለመረዳት ትችላለህ። “አሕዛብም ከጠጅዋ ጠጥተዋል፤ ስለዚህ አሕዛብ አብደዋል።”— ኤርምያስ 51:6, 7
17. በቅርቡ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ምን የፍርድ እርምጃ ይወሰድባታል? ከዚያስ በኋላ ምን ይቀጥላል?
17 በቅርቡ ይሖዋ ‘ያበዱትን’ የተባበሩት መንግሥታት አባሎች በራእይ 17:16 ላይ በተገለጸው መንገድ በሐሰት ሃይማኖት ላይ እንዲነሱ ያደርጋል:- “ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።” ይህም በማቴዎስ 24:21 ላይ የተገለጸውና ሁሉን የሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን በሆነው በአርማጌዶን የሚቋጨው ታላቅ መከራ መጀመሪያ ይሆናል። ታላቂቱ ባቢሎን እንደ ጥንትዋ ባቢሎን በኤርምያስ 51:13, 25 ላይ የተወሰነባትን ፍርድ ትቀበላለች:- “አንቺ በብዙ ውኃ አጠገብ የተቀመጥሽ በመዝገብም የበለጠግሽ ሆይ፣ እንደ ስስትሽ መጠን ፍጻሜሽ ደርሶአል። አንተ ምድርን ሁሉ የምታጠፋ አጥፊ ተራራ ሆይ፣ እነሆ፣ እኔ በአንተ ላይ ነኝ ይላል እግዚአብሔር፣ እጄንም እዘረጋብሃለሁ ከድንጋዮችም ላይ አንከባልልሃለሁ፣ የተቃጠለም ተራራ አደርግሃለሁ።” ከዚያ በኋላ ጦርነት ቆስቋሽ የሆኑት ምግባረ ብልሹ ብሔራት የይሖዋ የበቀል ቀን ሲያገኛቸው እንደ ሐሰት ሃይማኖት ለጥፋት ይዳረጋሉ።
18. ኢሳይያስ 48:22 ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ እና እንዴት ይሆናል?
18 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:3 ስለ ክፉዎች እንዲህ ይላል:- “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።” ኢሳይያስም “እነሆ . . . የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ” ሲል የተናገረው ስለ እነዚህ ክፉዎች ነው። (ኢሳይያስ 33:7) በእርግጥም ኢሳይያስ 48:22 ላይ እንደምናነበው “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል እግዚአብሔር።” ይሁን እንጂ የአምላካዊ ሰላም እውነተኛ መልእክተኞችስ ከፊታቸው ምን ነገር ይጠብቃቸዋል? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራልናል።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የአምላክ ነቢያት ሐሰተኛ ነቢያትን ያጋለጡት እንዴት ባሉ ጠንካራ ቃላት ነው?
◻ ሰብዓዊ ድርጅቶች ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያደርጓቸው ጥረቶች የማይሰምሩት ለምንድን ነው?
◻ በእውነተኛ የሰላም መልእክተኞችና ለተባበሩት መንግሥታት ሽንጣቸውን ገትረው በሚከራከሩት ወገኖች መካከል ምን ልዩነት አለ?
◻ ቅን የሆኑ ሰዎች ይሖዋ ቃል በገባው ሰላም ለመደሰት ከፈለጉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢሳይያስ፣ ኤርምያስም ሆነ ዳንኤል ሰዎች ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉት ጥረት እንደማይሰምር ተንብየዋል
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል።’— ሐዋርያው ዮሐንስ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ልቦናቸው ጨልሟል።’— ሐዋርያው ጳውሎስ