ይሖዋ በሐሰተኛ አስተማሪዎች ላይ ያስተላለፈው ፍርድ
“በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ . . . ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ።”—ኤርምያስ 23:14
1. በመለኮታዊ የማስተማር ሥራ የሚሳተፍ ሰው በጣም ከባድ ኃላፊነት የሚሸከመው ለምንድን ነው?
በመለኮታዊ የማስተማር ሥራ የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው በጣም ከባድ ኃላፊነት ይሸከማል። ያዕቆብ 3:1 “ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፣ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና” በማለት አስጠንቅቋል። አዎን፣ ከሌሎች ክርስቲያኖች ይበልጥ የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ተቀባይነት ያለው ስሌት የማቅረብ ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። ታዲያ የሐሰት አስተማሪዎች ሆነው የተገኙ ሁሉ ምን ይደርስባቸዋል? እስቲ በኤርምያስ ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንመልከት። ይህ በኤርምያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ በዘመናችን ላለው ሁኔታ እንዴት ጥላ እንደሆነ እንመለከታለን።
2, 3. ይሖዋ በኢየሩሳሌም ሐሰተኛ አስተማሪዎች ላይ በኤርምያስ በኩል ያስተላለፈው ፍርድ ምን ነበር?
2 ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በ13ኛው ዓመት ማለትም በ647 ከዘአበ ኤርምያስ የይሖዋ ነቢይ የመሆን ኃላፊነት ተሰጠው። ይሖዋ ይሁዳን የሚወቅስበት ምክንያት ስለነበረው ይህን ቅሬታውን እንዲናገር ኤርምያስን ላከው። የኢየሩሳሌም ሐሰተኛ ነቢያት ወይም አስተማሪዎች በአምላክ ዓይን ‘በጣም አስከፊ የሆነ ድርጊት’ ይፈጽሙ ነበር። ክፋታቸው በጣም በዝቶ ስለነበረ አምላክ ኢየሩሳሌምን ከሰዶምና ገሞራ ጋር አመሳሰላት። ኤርምያስ ምዕራፍ 23 ይህንን ይነግረናል። ቁጥር 14 እንዲህ ይላል፦
3 “በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ።”
4. የኢየሩሳሌም አስተማሪዎች መጥፎ ሥነ ምግባር በአሁኑ ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
4 አዎን፣ እነዚህ ነቢያት ወይም አስተማሪዎች በመጥፎ ሥነ ምግባራቸው መጥፎ አርዓያ በመሆናቸው ሕዝቡም እነርሱ የሚያደርጉትን የመሰለ ድርጊት እንዲፈጽም አደፋፍረውታል። በአሁኑ ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለውን ሁኔታ ተመልከቱ! በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው ሁኔታ በኤርምያስ ዘመን ከነበረው ጋር አንድ ዓይነት አይደለምን? በአሁኑ ጊዜ ቀሳውስት አመንዝሮችና ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ከቅስናቸው ሳይወርዱ እንዲቆዩ፣ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያናዊ ሥርዓቶችን እንዲመሩ ፈቅደዋል። ታዲያ የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች የሆኑ በጣም ብዙ ሰዎች ምግባረ ብልሹ መሆናቸው ያስደንቃልን?
5. የሕዝበ ክርስትና የተበላሸ ሥነ ምግባር ከሰዶምና ከጎሞራ ይበልጥ የከፋ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከሰዶምና ገሞራ ነዋሪዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። የሕዝበ ክርስትና ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ ግን ከሰዶምና ከገሞራ ይበልጥ የከፋ ነው። አዎን፣ የሕዝበ ክርስትና ሥነ ምግባር በይሖዋ ፊት ከሰዶምና ገሞራ ይበልጥ አስከፊ ነው። አስተማሪዎቿም የክርስትናን የሥነ ምግባር ሕግጋት አቃልለዋል። ይህ ደግሞ ሁሉንም ዓይነት መጥፎ ነገሮች ለመፈጸም የሚያደፋፍር የሥነ ምግባር ንቅዘት አየር እንዲስፋፋ አድርጓል። ይህ ዓይነቱ የተበላሸ ሥነ ምግባር በጣም ከመስፋፋቱ የተነሣ በአሁኑ ጊዜ መጥፎ የሆኑ ድርጊቶች እንደ ጥሩ ተደርገው መታየት ጀምረዋል።
“በሐሰት ይሄዳሉ”
6. ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም ነቢያት መጥፎነት ምን ብሎ ነበር?
6 አሁን ደግሞ ቁጥር 14 ስለ ኢየሩሳሌም ነቢያት የሚናገረውን ልብ በሉ። እነዚህ ነቢያት “በሐሰት ይሄዳሉ።” የቁጥር 15 የመጀመሪያ ክፍል ደግሞ “ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኩሰት [ክህደት አዓት] በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና” ይላል። ቁጥር 16ም ጨምሮ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፣ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ” ይላል።
7, 8. የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት እንደ ኢየሩሳሌም ሐሰተኛ ነቢያት የሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎችን የነካቸው እንዴት ነው?
7 እንደ ኢየሩሳሌም የሐሰት ነቢያት ሁሉ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም በአምላክ ቃል ውስጥ የማይገኙ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን እያስፋፉ በሐሰት ይመላለሳሉ። ከእነዚህ የሐሰት ትምህርቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? የነፍስ አለመሞት፣ ሥላሴ፣ መንጽሔ እንዲሁም ሰዎች ለዘላለም የሚሰቃዩበት የሲኦል እሳት መኖር ናቸው። በተጨማሪም ሰዎች ለመስማት የሚወዱትን ብቻ በመናገር የአድማጮቻቸውን ጆሮ ያክካሉ። ሕዝበ ክርስትና የአምላክ ሰላም ስላላት ምንም ዓይነት መዓት አያገኛትም በማለት ደጋግመው ይናገራሉ። ሆኖም ቀሳውስቱ የሚናገሩት “ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ” ነው። የሚናገሩት ሐሰት ነው። እንደነዚህ ያሉትን ውሸቶች የሚያምኑ ሁሉ መንፈሳዊነታቸው ይመረዛል። በተሳሳተ መንገድ በመመራት ወደ ጥፋት እየሄዱ ነው!
8 ይሖዋ በቁጥር 21 ላይ ስለነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት የተናገረውን ተመልከቱ፦ “እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ።” ስለዚህ በአሁኑ ጊዜም ቀሳውስቱ በአምላክ የተላኩ አይደሉም፤ የአምላክንም እውነት አያስተምሩም። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ቄሶቻቸው የሚመግቧቸው ዓለማዊ ፍልስፍናዎችን ብቻ ስለሆነ አሳዛኝ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሃይምነት አለባቸው።
9, 10. (ሀ) የኢየሩሳሌም ሐሰተኛ ነቢያት የሚያልሙት ሕልም ምን ዓይነት ነበር? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትም በተመሳሳይ ‘የሐሰት ሕልሞችን’ ያስተማሩት እንዴት ነው?
9 ከዚህም በተጨማሪ የዘመናችን ቀሳውስት የሐሰት ተስፋዎችን ያስፋፋሉ። ቁጥር 25 የሚለውን ልብ በሉ፦ “አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ።” የሚያልሙት ሕልም ምን ዓይነት ነው? ቁጥር 32 እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “እነሆ፣ ሐሰትን በሚያልሙ በሚናገሩም በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም። ለእነዚህም ሕዝብ ማናቸውም አይረቡአቸውም፣ ይላል እግዚአብሔር።”
10 ቀሳውስት ያስተማሩት የትኛውን የሐሰት ተስፋ ወይም ሕልም ነው? የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት የሚያገኝበት ብቸኛ ተስፋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው ብለው አስተምረዋል። በቅርብ ዓመታትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን “የመግባባትና የሰላም የመጨረሻው ተስፋ”፣ “ከፍተኛው የሰላምና የፍትሕ መድረክ” እንዲሁም “የጊዜያችን የዓለም ሰላም ተስፋ” ብለው ጠርተውታል። እንዴት ያለ ማታለያ ነው! የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት ነው። ቀሳውስት ግን የኢየሱስ ስብከት ዋነኛ መልእክት ስለነበረው ስለ ሰማያዊው መንግሥት የሚገልጸውን እውነት አይሰብኩም፣ አያስተምሩም።
11. (ሀ) የኢየሩሳሌም ሐሰተኛ አስተማሪዎች በአምላክ የግል ስም ላይ ምን መጥፎ ነገር አድርገው ነበር? (ለ) የዘመናችን የሐሰት ሃይማኖት አስተማሪዎች ከኤርምያስ ክፍል ተቃራኒ በሆነ መንገድ መለኮታዊውን ስም ምን አድርገውታል?
11 ቁጥር 27 ተጨማሪ ነገር ይነግረናል። “አባቶቻቸው ስለ በኣል ስሜን እንደ ረሱ፣ እያንዳንዱ ለባልንጀራው በሚናገራት ሕልማቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ።” የኢየሩሳሌም የሐሰት ነቢያት ሕዝቡ የአምላክን ስም እንዲረሳ አድርገው ነበር። የዘመናችንስ ሐሰተኛ የሃይማኖት አስተማሪዎች ይህንኑ የሚመስል ነገር አላደረጉምን? ከዚህም የባሰ ነገር አድርገዋል። ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ደብቀዋል። በአምላክ ስም መጠቀም አስፈላጊ አይደለም ብለው ከማስተማራቸውም በላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው አውጥተውታል። የአምላክ ስም ይሖዋ ነው ብለው የሚያስተምሩትንም ሰዎች ይቃወማሉ። የኤርምያስ ክፍል ማለትም በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያን ቀሪዎች ግን ከባልንጀሮቻቸው ጋር ሆነው ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው አድርገዋል። በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ስም አስተምረዋል።—ዮሐንስ 17:6
መጥፎነታቸውን ማጋለጥ
12. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖት አስተማሪዎች ከፍተኛ የደም ዕዳ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ውስጥ ቀሳውስት ምን ሚና ተጫውተዋል?
12 የኤርምያስ ክፍል፣ ቀሳውስት መንጎቻቸውን ወደ ጥፋት በሚመራው ሰፊ መንገድ ላይ የሚነዱ ሐሰተኛ አስተማሪዎች መሆናቸውን በተደጋጋሚ አጋልጧል። አዎን፣ ቀሪዎቹ እነዚህ አላሚዎች የይሖዋን የቁጣ ፍርድ መቀበል የሚገባቸው ለምን እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ አገልጋዮች “በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም” በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ እንደተገኘ የሚናገረውን ራእይ 18:24ን ብዙ ጊዜ ይጠቅሳሉ። እስቲ በሃይማኖታዊ ልዩነቶች ምክንያት የተደረጉትን ጦርነቶች በሙሉ አስቡ። ሐሰተኛ የሃይማኖት አስተማሪዎች ያለባቸው የደም ዕዳ እንዴት ብዙ ነው! ትምህርቶቻቸው መለያየት ከመፍጠራቸውም በላይ የተለያየ እምነትና ብሔር ባላቸው ሰዎች መካከል ያለውን ጥላቻ አፋፍመዋል። ፕሪቸርስ ፕሬዘንት አርምስ የተባለው መጽሐፍ ስለ መጀመሪያው ዓለም ጦርነት ሲናገር “ጦርነቱ መንፈሳዊ ትርጉምና ግፊት እንዲያገኝ ያደረጉት ቀሳውስት ናቸው። . . . በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የጦርነቱ ተባባሪና አጫፋሪ ሆናለች” ብሎ ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ከዚህ የተለየ አልነበረም። ቀሳውስት ተዋጊዎቹን ብሔራት ሙሉ በሙሉ ከመደገፋቸውም በላይ ሠራዊቶቻቸውን ባርከዋል። ሁለት የዓለም ጦርነቶች የተጀመሩት የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች እርስ በርሳቸው በተጨፋጨፉባቸው ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ ነው። ክርስቲያን ነን በሚሉ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ዓለማዊና ሃይማኖታዊ ወገኖች እስከ ዛሬ ድረስ እርስ በርሳቸው ደም ይፋሰሳሉ። የሐሰት ትምህርታቸው እንዴት ያለ አስከፊ ውጤት አምጥቷል!
13. ኤርምያስ 23:22 የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ከይሖዋ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
13 ኤርምያስ ምዕራፍ 23 ቁጥር 22 የሚለውን ልብ በሉ፦ “በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ [ከቅርብ ወዳጆቼ ጋር ቢቆሙ ኖሮ፣ አዓት] ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፣ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር።” የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ነቢያት የይሖዋ ወዳጆች ቢሆኑ ኖሮ፣ እንደ ታማኝና ልባም ባሪያ ከአምላክ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ቢኖራቸው ኖሮ፣ የአምላክን ሕግጋት አክብረው ይኖሩ ነበር። የሕዝበ ክርስትና አባላት የአምላክን ቃል እንዲሰሙ ያደርጉ ነበር። የዘመናችን ሐሰተኛ አስተማሪዎች ግን ተከታዮቻቸውን የአምላክ ጠላት የሆነው የሰይጣን ዲያብሎስ የታወሩ አገልጋዮች አድርገዋቸዋል።
14. በ1958 የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት የሚያጋልጥ ምን ኃይለኛ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር?
14 የኤርምያስ ክፍል ቀሳውስቱን ጠንከር ባለ ቃላት አጋልጧቸዋል። ለምሳሌ ያህል በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው መለኮታዊ ፈቃድ የተባለ የይሖዋ ምስክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ምክትል ፕሬዘዳንት ካሰማው ቃል ከፊሉ እንደሚከተለው ይል ነበር፦ “የዚህ ሁሉ ወንጀል፣ የወጣቶች ዓመፅ፣ ጠብ፣ ጥላቻ፣ ግጭት . . . እና ኃይለኛ ብጥብጥ ዋና ምክንያት የማይታየው የሰው ልጅ ጠላት በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ የሚመራው የተሳሳተ ሃይማኖት፣ የሐሰት ሃይማኖት መሆኑን አለአንዳች ማጋነንና ማመንታት እንናገራለን። ዓለም ለምትገኝበት ሁኔታ ከማንም ይበልጥ በኃላፊነት የሚጠየቁት ሃይማኖታዊ መምህራንና መሪዎች ናቸው። የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ቀሳውስት ደግሞ ከሌሎቹ ሃይማኖታዊ መሪዎችና አስተማሪዎች የባሱ መጥፎዎች ናቸው። . . . ከመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ወዲህ ባሉት ዓመታት በሙሉ ሕዝበ ክርስትና ከአምላክ ጋር ያላት ዝምድና በኤርምያስ ዘመን የነበረችው እስራኤል የነበራትን ዓይነት ሆኗል። አዎን፣ ሕዝበ ክርስትና ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ላይ ሲደርስ ከተመለከተው ይበልጥ አውዳሚና አሰቃቂ የሆነ ጥፋት ተደቅኖባታል።”
በሐሰተኛ አስተማሪዎች ላይ የተፈረደ ፍርድ
15. ቀሳውስት ስለ ሰላም ምን ተንብየው ነበር? ትንቢቶቻቸው ይፈጸሙላቸዋልን?
15 ቀሳውስቱ ይህን የመሰለ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ከዚያ ወዲህ ምን አድርገዋል? ቁጥር 17 እንደሚለው “ለሚንቁኝ ሁልጊዜ፦ እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ።” ታዲያ ይህ እውነት ነውን? በፍጹም! ይሖዋ የእነዚህ ቀሳውስት ትንቢት ሐሰት እንደሆነ ያጋልጣል። በስሙ የሚናገሩትን ትንቢት አይፈጽምላቸውም። ይሁን እንጂ ይህ ቀሳውስት ከአምላክ ይመጣል የሚሉት የውሸት የሰላም ዋስትና በጣም አታላይ ነው!
16. (ሀ) የዚህ ዓለም የሥነ ምግባር አየር ምን ዓይነት ነው? ለዚህ ዓይነቱ ሁኔታስ እነማን ጭምር ተጠያቂዎች ይሆናሉ? (ለ) የኤርምያስ ክፍል ይህ ዓለም ባሉት ወራዳ የሥነ ምግባር አመለካከቶች ላይ ምን እያካሄደ ነው?
16 ‘እኔ? እንዴት በቀሳውስት ትምህርት እሞኛለሁ? በፍጹም ሊሆን የማይችል ነው’ ብለህ ታስባለህን? ይህን ያህል እርግጠኛ አትሁን። የቀሳውስቱ የሐሰት ትምህርት ስውርና አስነዋሪ የሆነ የሥነ ምግባር አየር እንዳስፋፋ አስታውስ። ልቅ የሆነው ትምህርታቸው ማንኛውንም ድርጊት ምንም ያህል ሥነ ምግባር የጎደለው ቢሆን ትክክል ነው ብሎ ይቀበላል። ይህ የተበላሸ የሥነ ምግባር አየር ደግሞ በማንኛውም የመዝናኛ መስክ፣ በፊልሞች፣ በቴሌቪዥን፣ በመጽሔቶችና በሙዚቃ ውስጥ ይገኛል። ስለዚህ በጣም ጠንቃቆች ካልሆንን በዚህ ቀስ በቀስ ሳይታወቅበት በሚማርከው ወራዳ የሥነ ምግባር አየር እንሸነፋለን። ወጣቶች ወራዳ በሆኑ ቪድዮዎችና ሙዚቃ ሊጠመዱ ይችላሉ። ምንም ነውር የሆነ ነገር የለም የሚለው ይህ የዘመናችን ሰዎች አመለካከት የቀሳውስት የሐሰት ትምህርትና የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ያለማክበራቸው ቀጥተኛ ውጤት እንደሆነ አስታውስ። የኤርምያስ ክፍል ይህንን ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አመለካከት በመዋጋትና የይሖዋ አገልጋዮች ሕዝበ ክርስትናን ከዋጠው ብልሹ ምግባር እንዲርቁ በመርዳት ላይ ነው።
17. (ሀ) ኤርምያስ በክፉዋ ኢየሩሳሌም ላይ ምን ይመጣባታል ብሎ ተናግሮ ነበር? (ለ) በቅርቡ ሕዝበ ክርስትና ምን ይደርስባታል?
17 የሕዝበ ክርስትና የሐሰት አስተማሪዎች ከታላቁ ፈራጅ ከይሖዋ ምን ዓይነት ፍርድ ይቀበላሉ? ቁጥር 19, 20, 39 እና 40 መልሱን ይሰጠናል፦ “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፣ እርሱም ቁጣው፣ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፋስ ወጥቶአል፤ የዓመፀኞችን ራስ ይገለባብጣል። የእግዚአብሔር ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ . . . እነሆ፣ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ። የዘላለምንም ስድብ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘላለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።” ይህ ሁሉ በክፉዋ ኢየሩሳሌምና በቤተ መቅደሷ ላይ በትክክል ተፈጽሟል። አሁን ደግሞ ክፉዋ ሕዝበ ክርስትና መዓት ይመጣባታል!
‘የይሖዋን ሸክም’ ማወጅ
18, 19. ኤርምያስ በይሁዳ ላይ የተናገረው ‘የይሖዋ ሸክም’ ምንድን ነው? ምን እንደሚመጣስ ተናገረ?
18 ታዲያ የኤርምያስ ክፍልና የባልንጀሮቻቸው ኃላፊነት ምንድን ነው? ቁጥር 33 እንዲህ ሲል ይነግረናል፦ “ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፣ አንተ፦ ሸክሙ እናንተ ናችሁ፣ እጥላችሁማለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር ትላቸዋለህ።”
19 “ሸክም” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ሁለት ትርጉም አለው። ከባዱን መለኮታዊ ቃል ወይም አንድን ሰው ሊከብድና ሊያደክም የሚችለውን ጭነት ያመለክታል። እዚህ ላይ “የእግዚአብሔር ሸክም” የተባለው ኢየሩሳሌም ለጥፋት የተወሰነች መሆኗን የሚገልጸው ከባድ የትንቢት ቃል ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች ኤርምያስ ከይሖዋ ተቀብሎ በተደጋጋሚ የነገራቸውን ይህን ከባድ ትንቢታዊ መልእክት ለመስማት ፈልገው ነበርን? አልፈለጉም። ‘አሁን ደግሞ ምን ትንቢት (ሸክም) አለህ? ትንቢትህ ሌላ አድካሚ ጭነት እንደሚሆን እርግጠኞች ነን’ ብለው በኤርምያስ ላይ ይዘብቱበት ነበር። ይሖዋ ግን ምን አላቸው? “ሸክሙ እናንተ ናችሁ፣ እጥላችሁማለሁ” አላቸው። አዎን፣ እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ ሸክም ሆነውበት ነበር፤ አሁን ግን ዳግመኛ ሸክም እንዳይሆኑበት አራግፎ ሊጥላቸው ነው።
20. ዛሬስ ‘የይሖዋ ሸክም’ ምንድን ነው?
20 ዛሬስ “የእግዚአብሔር ሸክም” ምንድን ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ከባድ ትንቢታዊ መልእክት ነው። ይህ መልእክት በጣም የቀረበውን የሕዝበ ክርስትና ውድመት የሚያስታውቅ የጥፋት መልእክት ነው። እኛ በበኩላችን ይህን ‘የእግዚአብሔርን ሸክም’ የማሳወቅ ከባድ ኃላፊነት አለብን። መጨረሻው እየቀረበ በሄደ መጠን ከቀና ጎዳና የወጡት የሕዝበ ክርስትና አባላት የሆኑ ሕዝቦች በሙሉ ለይሖዋ አምላክ “ሸክም”፣ አዎን፣ ‘ታላቅ ሸክም’ እንደሆኑና በቅርቡ ሕዝበ ክርስትናን ለጥፋት አሳልፎ በመጣል ከዚህ “ሸክም” እንደሚገላገል መናገር ይገባናል።
21. (ሀ) ኢየሩሳሌም በ607 ከዘአበ የጠፋችው ለምን ነበር? (ለ) ከኢየሩሳሌም ጥፋት በኋላ በሐሰተኞቹ ነቢያት ላይ ምን ደረሰ? በእውነተኞቹ የይሖዋ ነቢያትስ ላይ? ይህስ በዛሬው ጊዜ ለኛ ምን ማስተማመኛ ይሰጠናል?
21 የይሖዋ ፍርድ በኤርምያስ ዘመን የተፈጸመው ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በ607 ከዘአበ ባጠፉ ጊዜ ነበር። በትንቢት እንደተነገረው በዚያ ጊዜ የደረሰው ጥፋት አንገተ ደንዳናና ከሃዲ የነበሩትን እስራኤላውያን ‘የሚያዋርድና’ ‘የሚያሳፍር’ ነበር። (ኤርምያስ 23:39, 40 የ1980 ትርጉም) በተደጋጋሚ ያቃለሉት ይሖዋ የክፋታቸውን ውጤት እንዲያጭዱ ፈጽሞ የጣላቸው መሆኑን አረጋግጧል። በመጨረሻው የእብሪተኞቹ ሐሰተኛ ነቢያት አፍ ተዘጋ። የኤርምያስ አፍ ግን ትንቢትን መናገሩን አላቋረጠም። ይሖዋ አልጣለውም። በዚህ ትንቢታዊ ጥላ መሠረት ይሖዋ ከባድ የሆነው የፍርዱ ውሳኔ የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስትና የቀሳውስቱን ውሸት ያመኑትን ሰዎች አድቅቆ ሕይወት አልባ ሲያደርግ የኤርምያስን ክፍል ግን አይጥልም።
22. ይሖዋ በሕዝበ ክርስትና ላይ ሲፈርድባት ምን ያህል የተዋረደች ትሆናለች?
22 አዎን፣ ሃይማኖታዊቷ ሕዝበ ክርስትና ሀብቷ ከተገፈፈባትና እርቃኗን ከቀረች በኋላ ከ607 ከዘአበ በኋላ ባድማና ወና የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች። ይሖዋ የሐሰት አስተማሪዎች መቀበል ይገባቸዋል ብሎ የፈረደባቸው የፍርድ ውሳኔ ይህ ነው። ይህ ፍርድ ሳይፈጸም አይቀርም። ኤርምያስ በመንፈስ ተነሣስቶ የተናገራቸው የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በሙሉ በጥንት ዘመን በትክክል እንደተፈጸሙ ሁሉ በዘመናችንም በትክክል ይፈጸማሉ። ሰዎች ሁሉ የይሖዋ የጽድቅ ፍርድ በሐሰት ሃይማኖት አስተማሪዎች ሁሉ ላይ በሙሉ ኃይሉ የሚወርደው ለምን እንደሆነ ያውቁ ዘንድ ልክ እንደ ኤርምያስ የይሖዋን ትንቢታዊ ሸክም ለሰው ሁሉ በድፍረት እንናገር!
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ የጥንቷ ኢየሩሳሌም በይሖዋ ዓይን ምን ያህል መጥፎ ነበረች?
◻ ሕዝበ ክርስትና ‘በሐሰት የተመላለሰችው’ በምን በምን መንገዶች ነው?
◻ ዘመናዊዎቹ ቀሳውስት የባሱ በደለኞች መሆናቸው የተጋለጠው እንዴት ነው?
◻ አሁን እየታወጀ ያለው ‘የይሖዋ ሸክም’ ምንድን ነው?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሩሳሌም ነቢያት ‘አስከፊ ድርጊቶችን’ ፈጽመዋል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ”
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሩሳሌም ከጠፋች በኋላ የነበራት ሁኔታ ለሕዝበ ክርስትና የመጨረሻ ዕጣ ምሳሌ ነው