“ይሖዋ ወዴት አለ?” ብለህ ትጠይቃለህን?
‘ከእኔ ዘንድ ራቁ፣ . . . እግዚአብሔር ወዴት አለ? አላሉም።’—ኤርምያስ 2:5, 6
1. ሰዎች “እግዚአብሔር ወዴት አለ?” ብለው የሚጠይቁት ለምን ሊሆን ይችላል?
ብዙ ሰዎች “እግዚአብሔር ወዴት አለ?” ብለው ይጠይቃሉ። አንዳንዶች ይህን ጥያቄ የሚያነሱት ስለ ፈጣሪ መሠረታዊ ግንዛቤ ለማግኘት ይኸውም የሚኖርበትን ቦታ ለማወቅ ፈልገው ነው። ሌሎች መጠነ ሰፊ አደጋ ሲደርስ ወይም በግላቸው ችግሮች ሲፈራረቁባቸው አምላክ ጣልቃ ገብቶ ለምን እርምጃ እንዳልወሰደ ግራ ስለሚገባቸው እንደዚህ ብለው ይጠይቃሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች አምላክ የለም ብለው ስለሚያስቡ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ጨርሶ አያነሱም።—መዝሙር 10:4
2. አምላክን ለማግኘት ባደረጉት ጥረት የተሳካላቸው እነማን ናቸው?
2 እርግጥ ነው፣ አምላክ መኖሩን የሚያረጋግጡትን በርካታ ማስረጃዎች የሚቀበሉ ብዙ ሰዎች አሉ። (መዝሙር 19:1፤ 104:24) ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሃይማኖት ስላላቸው ብቻ ረክተው የሚኖሩ ናቸው። ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለእውነት ባላቸው ጥልቅ ፍቅር በመገፋፋት እውነተኛውን አምላክ ለመፈለግ ጥረት አድርገዋል። አምላክ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ ባለመሆኑ’ ይህ ጥረታቸው ከንቱ አልቀረም።—ሥራ 17:26-28
3. (ሀ) አምላክ የሚኖረው የት ነው? (ለ) “እግዚአብሔር ወዴት አለ?” የሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄ ምን ትርጉም አለው?
3 አንድ ሰው ከልብ ተነሳስቶ ይሖዋን ሲፈልግ ‘አምላክ መንፈስ መሆኑን’ ይኸውም በሰብዓዊ ዓይን ሊታይ የማይችል አካል መሆኑን ይገነዘባል። (ዮሐንስ 4:24) ኢየሱስ እውነተኛውን አምላክ ‘በሰማያት ያለው አባቴ’ ብሎ ጠርቶታል። እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? በመንፈሳዊ ዓይን ሲታይ የሰማዩ አባታችን የሚኖረው ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ ከፍ ባለ ሥፍራ መሆኑን መናገሩ ነበር። (ማቴዎስ 12:50፤ ኢሳይያስ 63:15) አምላክን በሥጋዊ ዓይናችን ልናየው ባንችልም እርሱን እንድናውቀውና ስለ ዓላማው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረን ሁኔታዎችን አመቻችቶልናል። (ዘጸአት 33:20፤ 34:6, 7) የሕይወትን ትርጉም ማወቅ የሚፈልጉ ቅን ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ሕይወታችንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ የእርሱን አቋም ይኸውም ለእነዚህ ጉዳዮች ምን አመለካከት እንዳለውና ፍላጎታችን ከዓላማው ጋር የሚስማማ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ ሰጥቶናል። ሕይወታችንን የሚነኩ ጉዳዮችን በተመለከተ የእርሱን አመለካከት ለማወቅ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅና መልሱን ለማግኘት ልባዊ ጥረት እንድናደርግ ይፈልጋል። የጥንቶቹ እስራኤላውያን እንደዚህ ሳያደርጉ በመቅረታቸው ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት ገስጿቸዋል። የአምላክን ስም ቢያውቁም “እግዚአብሔር ወዴት አለ?” ብለው አልጠየቁም። (ኤርምያስ 2:6) ለይሖዋ ዓላማ ቦታ አልሰጡም ነበር። የእርሱን አመራር ለማግኘት አልፈለጉም። አንተስ ከባድም ይሁን ቀላል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይ ሲያጋጥምህ “እግዚአብሔር ወዴት አለ?” ብለህ ትጠይቃለህ?
የአምላክን አመራር የጠየቁ ሰዎች
4. ዳዊት የይሖዋን አመራር በመጠየቅ ረገድ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
4 የእሴይ ልጅ የነበረው ዳዊት ገና ከወጣትነቱ ጀምሮ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ነበረው። ይሖዋ ‘ሕያው አምላክ’ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ዳዊት በግሉ የይሖዋን ጥበቃ አግኝቷል። ‘ለይሖዋ ስም’ በነበረው ፍቅርና በይሖዋ ላይ ባለው እምነት ተገፋፍቶ ሙሉ ትጥቅ የነበረውን ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ መግደል ችሏል። (1 ሳሙኤል 17:26, 34-51) ሆኖም ዳዊት በዚህ ረገድ ያገኘው ስኬት በራሱ እንዲመካ አላደረገውም። ከአሁን በኋላ ምንም ባደርግ ይሖዋ ይባርከኛል ብሎ አላሰበም። ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ሁሉ ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገው በተደጋጋሚ ጊዜያት ይሖዋን ጠይቋል። (1 ሳሙኤል 23:2፤ 30:8፤ 2 ሳሙኤል 2:1፤ 5:19) “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 25:4, 5) ልንከተለው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!
5, 6. ኢዮሣፍጥ በሕይወቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ይሖዋን የፈለገው እንዴት ነበር?
5 በዳዊት በኩል በመጣው ንጉሣዊ መስመር አምስተኛ ንጉሥ በነበረው በኢዮሣፍጥ የግዛት ዘመን ሦስት ብሔራት ግንባር ፈጥረው በይሁዳ ላይ ጦርነት ከፈቱ። እንዲህ ያለ ብሔራዊ አደጋ ባንዣበበበት ወቅት ኢዮሣፍጥ ‘እግዚአብሔርን ለመፈለግ ፊቱን አቀና።’ (2 ዜና መዋዕል 20:1-3) ኢዮሣፍጥ የይሖዋን አመራር ሲፈልግ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አልነበረም። ንጉሡ ከዳተኛ የነበረው ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ከተከተለው የበዓል አምልኮ በመራቅ በይሖዋ መንገድ ለመጓዝ መርጧል። (2 ዜና መዋዕል 17:3, 4) ታዲያ ኢዮሣፍጥ እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው ‘ይሖዋን የፈለገው’ እንዴት ነበር?
6 ኢዮሣፍጥ በዚያ የጭንቅ ሰዓት ኢየሩሳሌም ውስጥ በሕዝብ ፊት ያቀረበው ጸሎት ይሖዋ ወደር የማይገኝለት ኃይል እንዳለው መገንዘቡን ያሳያል። ኢዮሣፍጥ፣ ይሖዋ ሌሎች ብሔራትን አስለቅቆ ምድሪቱን ለእስራኤላውያን ባወረሰ ጊዜ ዓላማው ምን እንደነበር በጥልቅ ሳያስብበት አልቀረም። ንጉሡ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተናግሯል። (2 ዜና መዋዕል 20:6-12) በዚህ አስጨናቂ ወቅት ይሖዋ ለኢዮሣፍጥ ተገኝቶለት ይሆን? እንዴታ! በሌዋዊው በየሕዚኤል በኩል ግልጽ መመሪያ የሰጣቸው ሲሆን በማግሥቱም ለሕዝቡ ድል አጎናጽፏቸዋል። (2 ዜና መዋዕል 20:14-28) አንተም ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጥህ በፈለግኸው ጊዜ እንደሚገኝልህ እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
7. አምላክ የሚሰማው የእነማንን ጸሎት ነው?
7 ይሖዋ አያዳላም። ሰዎች ሁሉ በጸሎት ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ጋብዟቸዋል። (መዝሙር 65:2፤ ሥራ 10:34, 35) ልመናቸውን ወደ እርሱ የሚያቀርቡትን ሰዎች የልብ ዝንባሌ ያውቃል። የጻድቃንን ጸሎት እንደሚሰማ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 15:29) ስለ እርሱ የማወቅ ፍላጎት ያልነበራቸው ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የእርሱን አመራር ሲፈልጉ ምላሽ ይሰጣቸዋል። (ኢሳይያስ 65:1) ሌላው ቀርቶ ሕግጋቱን ጥሰው የነበሩ ሰዎች በትሕትና ንስሐ ገብተው የሚያቀርቡትን ጸሎት እንኳ ይሰማል። (መዝሙር 32:5, 6፤ ሥራ 3:19) ሆኖም አንድ ሰው አምላክን ከልቡ የማይታዘዝ ከሆነ ጸሎቱ ምላሽ አያገኝም። (ማርቆስ 7:6, 7) እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ይሖዋን ቢጠይቁም ምላሽ አላገኙም
8. ንጉሥ ሳኦል ያቀረበው ጸሎት ምላሽ ያላገኘው ለምን ነበር?
8 ንጉሥ ሳኦል ታዛዥ ባለመሆኑ ምክንያት አምላክ እንደተወው ነቢዩ ሳሙኤል ሲነግረው ሳኦል በይሖዋ ፊት ሰግዷል። (1 ሳሙኤል 15:30, 31) ይሁን እንጂ ይህን ያደረገው ለይስሙላ ነበር። የሳኦል ፍላጎት አምላክን መታዘዝ ሳይሆን የሕዝቡን አክብሮት ማትረፍ ነበር። ቆየት ብሎም ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ሲወጉ ሳኦል እንዲያው ለደንቡ ያህል ይሖዋን ጠየቀ። ሆኖም ምላሽ ሲያጣ ድርጊቱ በይሖዋ የተወገዘ መሆኑን እያወቀ ወደ መናፍስት ጠሪ ሄደ። (ዘዳግም 18:10-12፤ 1 ሳሙኤል 28:6, 7) አንደኛ ዜና መዋዕል 10:14 ሳኦል ‘እግዚአብሔርን አልጠየቀም’ በማለት ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል። እንዲህ የተባለው ለምንድን ነው? ሳኦል የጸለየው በእምነት አልነበረም። ሁኔታው ያልጸለየ ያህል ነበር።
9. ሴዴቅያስ የይሖዋን አመራር ለማግኘት ያቀረበው ጸሎት ምላሽ ያላገኘው ለምን ነበር?
9 በተመሳሳይም የይሁዳ መንግሥት ሊወድቅ በተቃረበበት ወቅት ብዙ ሰዎች ወደ ይሖዋ ይጸልዩና ነቢያቱን ይጠይቁ ነበር። ሕዝቡ ለይሖዋ አክብሮት እንዳላቸው ይናገሩ እንጂ ጣዖት ማምለካቸውን አልተዉም። (ሶፎንያስ 1:4-6) ለይስሙላ ያህል አምላክን ለመጠየቅ ቢሞክሩም ራሳቸውን ለፈቃዱ ለማስገዛት ልባቸውን አላዘጋጁም። ንጉሥ ሴዴቅያስ ይሖዋን እንዲጠይቅለት ኤርምያስን ለምኖት ነበር። ንጉሡ ምን ማድረግ እንዳለበት ይሖዋ ቀደም ብሎ ነግሮታል። ሆኖም እምነት ስላልነበረውና ሕዝቡን ስለፈራ ይሖዋን አልታዘዘም፤ ይሖዋም ንጉሡ የፈለገውን መልስ አልሰጠውም።—ኤርምያስ 21:1-12፤ 38:14-19
10. ዮሐናን የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ባደረገው ሙከራ ስህተቱ ምን ነበር? እኛስ ከእርሱ ስህተት ምን እንማራለን?
10 ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰችና ባቢሎናውያን አይሁዳውያንን በግዞት ከወሰዷቸው በኋላ ዮሐናን በይሁዳ የቀሩትን ሰዎች ይዞ ወደ ግብጽ ለመሄድ አሰበ። አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቅቀው ሲያበቁ ወደ ግብጽ ለመሄድ ከመነሳታቸው በፊት ስለ እነርሱ ወደ ይሖዋ እንዲጸልይና መመሪያ እንዲጠይቅላቸው ኤርምያስን ለመኑት። ይሁን እንጂ ያገኙት መልስ እነርሱ እንደጠበቁት ሳይሆን ሲቀር የይሖዋን ምክር ችላ በማለት ያሰቡትን አደረጉ። (ኤርምያስ 41:16 እስከ 43:7) ከእነዚህ ታሪኮች ይሖዋ በምትፈልገው ጊዜ እንዲገኝልህ ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚያሳይ ትምህርት አግኝተሃል?
‘ጌታን ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ’
11. ኤፌሶን 5:9, 10ን ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
11 እውነተኛው አምልኮ ራሳችንን መወሰናችንን ለማሳየት በውኃ ከመጠመቅ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘትና በአገልግሎት ከመካፈል የበለጠ ነገርን ይጨምራል። መላው ሕይወታችን በአምልኮታችን ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆን ይኖርበታል። በየዕለቱ ለአምላክ ያደርን በመሆን ከምንከተለው ጎዳና እንድንወጣ ተጽዕኖ የሚያደርጉ የረቀቁ አሊያም ግልጽ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። እነዚህን ተጽዕኖዎች መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘ጌታን ደስ የሚያሰኘውን እንዲመረምሩ’ አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 5:9, 10) ይህን ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም የሚያሳዩ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉ።
12. ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ ባደረገው ሙከራ ይሖዋ ያልተደሰተው ለምን ነበር?
12 የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ እስራኤል ተመልሶ ለበርካታ ዓመታት በቂርያትይዓሪም ከተቀመጠ በኋላ ንጉሥ ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት ፈለገ። ከሕዝቡ አለቆች ጋር ከተማከረ በኋላ ‘ነገሩ መልካም መስሎ ከታያቸውና የይሖዋም ፈቃድ ከሆነ’ ታቦቱን እንደሚያመጣው ተናገረ። ሆኖም በዚህ ጉዳይ ላይ የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በቂ ምርምር አላደረገም። እንደዚያ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ታቦቱ በሰረገላ ላይ ባልተጫነ ነበር። ከዚህ ይልቅ አምላክ በግልጽ በሰጠው መመሪያ መሠረት ከቀዓት ወገን የሆኑ ሌዋውያን ይሸከሙት ነበር። ዳዊት በተደጋጋሚ ይሖዋን ይጠይቅ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን በተገቢው መንገድ አልፈለገውም። ውጤቱም አሳዛኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት “እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ” በማለት ተናግሯል።—1 ዜና መዋዕል 13:1-3፤ 15:11-13፤ ዘኍልቍ 4:4-6, 15፤ 7:1-9
13. ታቦቱ በተሳካ ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም ከተጓጓዘ በኋላ በተዘመረው መዝሙር ውስጥ ምን ማሳሰቢያ ይገኛል?
13 ሌዋውያን ታቦቱን ተሸክመው ከአቢዳራ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ባመጡት ጊዜ ዳዊት ያቀናበረው መዝሙር ተዘመረ። በመዝሙሩ ውስጥ “እግዚአብሔርን ፈልጉት፣ . . . ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ። . . . የሠራትን ድንቅ አስቡ፣ ተአምራቱንም የአፉንም ፍርድ” የሚለው ከልብ የመነጨ ማሳሰቢያ ይገኝበታል።—1 ዜና መዋዕል 16:11-13
14. ሰሎሞን ከተወው ጥሩ ምሳሌና በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ ከፈጸመው ስህተት ምን እንማራለን?
14 ዳዊት ከመሞቱ በፊት ልጁን ሰሎሞንን “[ይሖዋን] ብትፈልገው ታገኘዋለህ” በማለት መክሮት ነበር። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ሰሎሞን ዙፋኑን ከወረሰ በኋላ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ የመገናኛው ድንኳን ወደሚገኝበት ወደ ገባዖን ሄደ። እዚያም ይሖዋ ‘እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ለምነኝ’ በማለት ጠየቀው። ሰሎሞን በጠየቀው መሠረት ይሖዋ እስራኤልን ለማስተዳደር የሚያስችል ጥበብና እውቀት ብቻ ሳይሆን ሃብትና ክብርም አብዝቶ ሰጠው። (2 ዜና መዋዕል 1:3-12) ሰሎሞን ይሖዋ ለዳዊት የሰጠውን ንድፍ በመከተል እጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ገነባ። ይሁን እንጂ ሰሎሞን ትዳሩን በሚመለከት የይሖዋን አመራር አልተከተለም። ይሖዋን የማያመልኩ ሴቶችን በማግባቱ በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ ሚስቶቹ ከይሖዋ አምልኮ ልቡን አዘነበሉት። (1 ነገሥት 11:1-10) የቱንም ያህል የተከበርን፣ ጠቢብ ወይም አዋቂ የሆንን ቢመስለን ‘ጌታን ደስ የሚያሰኘውን መመርመራችን’ አስፈላጊ ነው!
15. ኢትዮጵያዊው ዝሪ ይሁዳን በወረረበት ወቅት አሳ ይሖዋ እንደሚያድናቸው በመተማመን መጸለይ የቻለው ለምን ነበር?
15 የሰሎሞን የልጅ ልጅ፣ ልጅ ስለ ሆነው ስለ ንጉሥ አሳ የሚናገረው ታሪክ እንደዚህ የማድረጉን አስፈላጊነት ያጠናክርልናል። አሳ ከነገሠ ከአሥራ አንድ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያዊው ዝሪ አንድ ሚልዮን ሠራዊት አሰልፎ ይሁዳን ለመውጋት መጣ። ይሖዋ ይሁዳን ይታደጋት ይሆን? ከ500 ዓመታት በፊት ይሖዋ እርሱን ከሰሙና ትእዛዙን ከጠበቁ ምን እንደሚያደርግላቸውና እንደዚህ ካላደረጉ ደግሞ ምን እንደሚጠብቃቸው ለሕዝቡ በግልጽ ነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 28:1, 7, 15, 25) አሳ በግዛቱ መጀመሪያ ላይ ለሐሰት አምልኮ የሚያገለግሉ መሠዊያዎችንና ሐውልቶችን ከይሁዳ ካስወገደ በኋላ ሕዝቡ ‘ይሖዋን እንዲፈልጉ’ አሳስቧቸዋል። አሳ ይሖዋን መፈለግ የጀመረው ችግር ሲያጋጥመው አልነበረም። በመሆኑም እንደሚረዳቸው በመተማመን ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። ይሖዋም አስደናቂ ድል አጎናጽፏቸዋል።—2 ዜና መዋዕል 14:2-12
16, 17. (ሀ) አሳ በውጊያው ድል ቢቀዳጅም ይሖዋ ምን ማሳሰቢያ ሰጥቶታል? (ለ) አሳ ማስተዋል የጎደለው እርምጃ በወሰደ ጊዜ ምን እርዳታ ተሰጥቶት ነበር? የእርሱስ ምላሽ ምን ነበር? (ሐ) የአሳን ታሪክ በመመርመር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
16 የሆነ ሆኖ አሳ ድል አድርጎ ሲመለስ ይሖዋ ዓዛርያስን ልኮ እንዲህ አለው:- “አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፣ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።” (2 ዜና መዋዕል 15:2) አሳ ቅንዓቱን እንደገና በማቀጣጠል እውነተኛውን አምልኮ አስፋፋ። ይሁን እንጂ ከ24 ዓመታት በኋላ እንደገና ጦርነት ሲያጋጥመው ይሖዋን ሳይፈልግ ቀረ። ምክር ለማግኘት አምላክን አልጠየቀም እንዲሁም የኢትዮጵያ ሠራዊት ይሁዳን በወረረ ጊዜ ይሖዋ ያደረገላቸውን አላስታወሰም። ከሶርያ ጋር ስምምነት በማድረግ የሞኝነት እርምጃ ወሰደ።—2 ዜና መዋዕል 16:1-6
17 በዚህም ምክንያት ይሖዋ አሳን ለመገሠጽ ባለ ራእዩን አናኒን ላከበት። በዚህ ጊዜም እንኳ አሳ የይሖዋ አመለካከት ሲነገረው መስተካከል በቻለ ነበር። እርሱ ግን በአናኒ ተቆጥቶ በግዞት ቤት አኖረው። (2 ዜና መዋዕል 16:7-10) እንዴት የሚያሳዝን ነው! እኛስ እንዴት ነን? አምላክን እየፈለግን ምክር ሲሰጠን ግን ለመቀበል እምቢተኛ እንሆናለን? በዓለማዊ ጉዳዮች እንደተጠላለፍን ያስተዋለ አንድ ሽማግሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ በአሳቢነት ምክር ቢሰጠን ‘ጌታን ደስ የሚያሰኘውን’ እንድናውቅ ሲል የሰጠንን ፍቅራዊ እርዳታ እናደንቃለን?
“ይሖዋ ወዴት አለ?” ብለህ መጠየቅ እንዳለብህ አትዘንጋ
18. ኤሊሁ ለኢዮብ ከሰጠው ማሳሰቢያ ምን ትምህርት እናገኛለን?
18 በይሖዋ አገልግሎት ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረው ሰው እንኳ ተደራራቢ ችግር ሲያጋጥመው ይሖዋን የማያስደስት ነገር ሊያደርግ ይችላል። ኢዮብ በአስከፊ በሽታ ሲመታ፣ ልጆቹን ጨምሮ አለኝ የሚለውን ሁሉ ሲያጣ እንዲሁም ወዳጆቹ በሐሰት ሲወነጅሉት ስለራሱ ብቻ ማሰብ ጀምሮ ነበር። ኤሊሁ “ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም” ሲል ተናግሮታል። (ኢዮብ 35:11) ኢዮብ ትኩረቱን ወደ ይሖዋ በማድረግ እርሱ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ መጣጣር አስፈልጎት ነበር። ኢዮብ የተሰጠውን ማሳሰቢያ በትሕትና የተቀበለ ሲሆን እኛም ምሳሌውን በመኮረጅ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን።
19. እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ምን ሳያደርጉ ቀርተዋል?
19 እስራኤላውያን አምላክ ለሕዝቡ ያደረጋቸውን ነገሮች ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ሆኖም ብዙውን ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ አንዳንድ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው አምላክ ያደረገላቸውን ነገሮች ይዘነጉ ነበር። (ኤርምያስ 2:5, 6, 8) በሕይወታቸው ውስጥ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ጉዳይ ሲያጋጥማቸው ‘ይሖዋ ወዴት አለ?’ ብለው ከመጠየቅ ይልቅ የራሳቸውን ምኞት ለማሳካት ይሯሯጡ ነበር።—ኢሳይያስ 5:11, 12
“ይሖዋ ወዴት አለ?” ብለህ መጠየቅህን አታቋርጥ
20, 21. (ሀ) ዛሬ የይሖዋን አመራር በመጠየቅ ረገድ የኤልሳዕን ምሳሌ የተከተሉት እነማን ናቸው? (ለ) እነርሱ የተዉትን የእምነት ምሳሌ መኮረጅና ከእርሱም ትምህርት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
20 ኤልያስ አገልግሎቱን ሲያጠናቅቅ የእርሱ አገልጋይ የነበረው ኤልሳዕ ከኤልያስ የወደቀውን መጎናጸፊያ ወስዶ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሄድ ውሃውን ከመታ በኋላ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” በማለት ጠየቀ። (2 ነገሥት 2:14) ይሖዋም መንፈሱ በኤልሳዕ ላይ እንደሆነ በማሳየት ለጥያቄው መልስ ሰጥቶታል። ከዚህ ምን እንማራለን?
21 በዘመናችንም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ተፈጽሟል። በስብከቱ ሥራ አመራር የሚሰጡ አንዳንድ ቅቡዓን የይሖዋ አገልጋዮች ምድራዊ ሕይወታቸውን ሲያጠናቅቁ የእነርሱን ኃላፊነት የተረከቡት ወንድሞች ቅዱሳን ጽሑፎችን በመመርመርና በመጸለይ የይሖዋን አመራር ጠይቀዋል። ምንጊዜም ‘ይሖዋ ወዴት አለ?’ ብለው ይጠይቁ ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ሕዝቡን መምራቱንና ሥራቸውን መባረኩን አላቋረጠም። እኛስ እንደ እነርሱ ያለ እምነት አለን? (ዕብራውያን 13:7) ከሆነ ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ድርጅት ተጠግተን እንኖራለን፣ ድርጅቱ የሚሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ከማድረጋችንም ባሻገር በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር የሚያከናውነውን ሥራ በሙሉ ነፍስ እንደግፋለን።—ዘካርያስ 8:23
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ‘ይሖዋ ወዴት አለ?’ ብለን የምንጠይቅበት ዓላማ ምን መሆን ይኖርበታል?
• ‘ይሖዋ ወዴት አለ?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
• አንዳንዶች መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ያቀረቧቸው ጸሎቶች መልስ ሳያገኙ የቀሩት ለምንድን ነው?
• ‘ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን መመርመር’ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳዩ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ይሖዋን የፈለገው እንዴት ነበር?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሳኦል ወደ መናፍስት ጠሪ የሄደው ለምን ነበር?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ ጸልይ፣ አጥና እንዲሁም አሰላስል