የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ግንቦት 2017
ከግንቦት 1-7
it-1-E 105 አን. 2
አናቶት
የአናቶት ሰው የነበረው ኤርምያስ የገዛ አገሩ ሰዎች ክብር የማይሰጡት ነቢይ ነበር፤ እንዲያውም የይሖዋን የእውነት ቃል በመስበኩ ሊገድሉት ይዝቱበት ነበር። (ኤር 1:1፤ 11:21-23፤ 29:27) በዚህም ምክንያት ይሖዋ በከተማዋ ላይ ጥፋት እንደሚያመጣ ትንቢት ተናገረ፤ ይህም ባቢሎን ከተማዋን በወረረች ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ኤር 11:21-23) ኢየሩሳሌም ከመውደቋ በፊት ኤርምያስ የመቤዠት መብቱን በመጠቀም በአናቶት የሚገኘውን የአጎቱን ልጅ መሬት ገዛ፤ ይህም በግዞት የተወሰዱት አይሁዳውያን ተመልሰው እንደሚቋቋሙ የሚያሳይ ምልክት ነበር። (ኤር 32:7-9) ከዘሩባቤል ጋር ከግዞት ከተመለሱት የመጀመሪያው ቡድን አባላት ውስጥ 128 የአናቶት ሰዎች ይገኙበታል፤ ከዚህም በተጨማሪ አናቶት ኤርምያስ በትንቢት በተናገረው መሠረት ዳግመኛ የሰው መኖሪያ ከሆኑ ከተሞች አንዷ ነች።—ዕዝራ 2:23፤ ነህ 7:27፤ 11:32
jr-E 152 አን. 22-23
“እኔን ማወቅ ማለት ይህ አይደለም?”
22 አንድ ሰው ሳያስብ የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር ቅር ቢያሰኝህ የይሖዋን ምሳሌ ትከተላለህ? አምላክ የጥንቶቹን አይሁዳውያን አስመልክቶ ሲናገር በደላቸውን ይቅር ያላቸውን ሁሉ ‘እንደሚያነጻቸው’ ገልጿል። (ኤርምያስ 33:8ን አንብብ።) ይሖዋ በደልን ያነጻል ሲባል ንስሐ የገባውን ሰው በደል በመተው ግለሰቡ እንደገና እሱን ማገልገል እንዲጀምር አጋጣሚ ይሰጠዋል ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው የአምላክን ይቅርታ አግኝቷል ማለት ከወረሰው አለፍጽምና ተላቆ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ሆኗል ማለት አይደለም። ይሁንና አምላክ ሰዎችን እንደሚያነጻ ከተናገረው ሐሳብ የምናገኘው ትምህርት አለ። አንድ ሰው የፈጸመብንን በደል ለመተው በሌላ አባባል በውስጣችን ያደረውን ቅሬታ በማስወገድ ልባችንን ለማንጻት ጥረት ማድረግ አለብን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
23 አንድ ሰው የሚያምር የአበባ ማስቀመጫ ወይም ጌጥ ስጦታ አድርጎ ሰጠህ እንበል። ዕቃው ቢቆሽሽ ወዲያውኑ ትጥለዋለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ዕቃውን በጥንቃቄ ለማጽዳት ወይም ላዩ ላይ ያለውን ቆሻሻ ለማስለቀቅ ጥረት ታደርጋለህ። ዕቃው በተቻለ መጠን ውበቱን ጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ሲበድልህ የሚሰማህን ቅሬታ ወይም የብስጭት ስሜት ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። ግለሰቡ ያደረሰብህን ጉዳት ከማብሰልሰል ተቆጠብ። የፈጸመብህን በደል በመተው ግለሰቡን ይቅር ስትለው ለዚያ ሰው ያደረብህን አሉታዊ ስሜት ማስወገድና ልብህን ማንጻት ትችላለህ። እንዲህ ስታደርግ ተቋርጦ የነበረው ወዳጅነታችሁ ሊታደስ ይችላል።
jr-E 173 አን. 10
ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጥቅም ማግኘት ትችላለህ
10 ኤርምያስ፣ ይመጣል ተብሎ የተነገረለት መሲሕ ለዳዊት የሚነሳ “ቀንበጥ” እንደሆነ ገልጿል። ይህ ተስማሚ መግለጫ ነው። ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ ያገለግል በነበረበት ጊዜም እንኳ የዳዊትን ንጉሣዊ የዘር ሐረግ የሚወክለው ዛፍ ተቆርጦ ነበር። ሆኖም ጉቶው አልሞተም ነበር። በመሆኑም ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከንጉሥ ዳዊት ዘር ተወለደ። ኢየሱስ “ይሖዋ ጽድቃችን ነው” ተብሎ ሊጠራ ይችላል፤ ይህም አምላክ ለዚህ ባሕርይ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ያሳያል። (ኤርምያስ 23:5, 6ን አንብብ።) ይሖዋ አንድያ ልጁ በምድር ላይ ሥቃይ እንዲደርስበትና እንዲሞት ፈቅዷል። በመሆኑም ይሖዋ ከፍትሕ መሥፈርቱ ጋር በሚስማማ መንገድ የሰው ልጆችን ኃጢአት ይቅር ለማለት ለዳዊት የተነሳው “ቀንበጥ” የከፈለውን ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ መጠቀም ይችላል። (ኤር. 33:15) ይህም የተወሰኑ ሰዎች “ጻድቃን ናችሁ ተብለው ለሕይወት እንዲበቁ” እና በመንፈስ ቅዱስ እንዲቀቡ እንዲሁም በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንዲታቀፉ አስችሏል። አምላክ ለጽድቅ ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጥ የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ደግሞ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ በቀጥታ ያልታቀፉ ሌሎች ሰዎችም ከቃል ኪዳኑ ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉ መሆኑ ነው።—ሮም 5:18
ግንቦት 8-14
it-2-E 1228 አን. 3
ሴዴቅያስ
መኳንንቱ ኤርምያስ የሕዝቡን ወኔ እያዳከመ በመሆኑ እንዲገደል ጥያቄ ባቀረቡለት ጊዜ ሴዴቅያስ ያደረገው ነገር ጠንካራ አቋም የሌለው ሰው እንደነበረ ያሳያል፤ ሴዴቅያስ “እነሆ፣ እሱ በእጃችሁ ነው፤ ንጉሡ እናንተን ለማስቆም ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልምና” ብሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሴዴቅያስ ከጊዜ በኋላ ኤቤድሜሌክ ኤርምያስን ለማዳን ያቀረበውን ጥያቄ የተቀበለ ሲሆን 30 ሰዎችን ይዞ በመሄድ ኤርምያስን ከጉድጓድ እንዲያወጡት አዞታል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ሴዴቅያስ ኤርምያስን ብቻውን አነጋግሮታል። ነቢዩን እንደማይገድለውና ሕይወቱን ለማጥፋት ለሚሹት ሰዎች አሳልፎ እንደማይሰጠው አረጋግጦለታል። ይሁንና ሴዴቅያስ ወደ ከለዳውያን የኮበለሉት አይሁዳውያን እንዳይበቀሉት ፈራ፤ በመሆኑም ለባቢሎን መኳንንት እጁን እንዲሰጥ ኤርምያስ በመንፈስ ተመርቶ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ሳያደርግ ቀረ። ንጉሡ በድብቅ ያደረጉትን ውይይት፣ በጥርጣሬ ዓይን ለሚያዩት መኳንንት እንዳይናገር ኤርምያስን ማሳሰቡ ፈርቶ እንደነበረ ያሳያል።—ኤር 38:1-28
it-2-E 759
ሬካባውያን
ይሖዋ ሬካባውያን ባሳዩት አክብሮት የተሞላበት ታዛዥነት ተደስቶ ነበር። ሬካባውያን፣ ለፈጣሪያቸው ታዛዥ ካልነበሩት አይሁዳውያን በተቃራኒ ለሰብዓዊ አባታቸው ምንጊዜም ታዛዥ እንደነበሩ አሳይተዋል። (ኤር 35:12-16) አምላክ “ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ዘር በፊቴ የሚያገለግል ሰው ፈጽሞ አይታጣም” በማለት ሬካባውያንን እንደሚባርክ ቃል ገብቷል።—ኤር 35:19
ግንቦት 15-21
it-2-E 1228 አን. 4
ሴዴቅያስ
የኢየሩሳሌም መውደቅ። በመጨረሻ (607 ዓ.ዓ.) “በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት በ11ኛው ዓመት፣ በአራተኛው ወር፣ ከወሩም በዘጠነኛው ቀን” የኢየሩሳሌም ቅጥር ተነደለ። ሴዴቅያስና ተዋጊዎቹ በሌሊት ሸሹ። ከለዳውያን ሴዴቅያስን በኢያሪኮ በረሃማ ሜዳ ላይ ደረሱበት፤ ከዚያም በሪብላ ወደነበረው ወደ ናቡከደነጾር ወሰዱት። የሴዴቅያስን ወንዶች ልጆች ዓይኑ እያየ አረዷቸው። በወቅቱ ሴዴቅያስ ዕድሜው ገና 32 ዓመት ገደማ ስለነበር ልጆቹ በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ሴዴቅያስ ልጆቹ ሲገደሉ ከተመለከተ በኋላ ዓይኑን አሳወሩት፤ በመዳብ የእግር ብረት አስረውም ወደ ባቢሎን ወሰዱት። እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ ታስሮ ቆየ።—2ነገ 25:2-7፤ ኤር 39:2-7፤ 44:30፤ 52:6-11፤ ከኤር 24:8-10፤ ከሕዝ 12:11-16 እና 21:25-27 ጋር አወዳድር።
it-2-E 482
ናቡዛራዳን
ናቡዛራዳን፣ ናቡከደነጾር በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ኤርምያስን ከእስር ለቆታል፤ መልካም መስሎ የታየውን ማድረግ እንደሚችል በመግለጽ በደግነት አነጋግሮታል፤ እንደሚንከባከበው የገለጸለት ከመሆኑም ሌላ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሰጥቶታል። በተጨማሪም ናቡከደነጾር ጎዶልያስን ገዢ አድርጎ በሾመበት ወቅት ናቡዛራዳን ለባቢሎን ንጉሥ ቃል አቀባይ ሆኖ አገልግሏል። (2ነገ 25:22፤ ኤር 39:11-14፤ 40:1-7፤ 41:10) ከአምስት ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ በ602 ዓ.ዓ. ናቡዛራዳን ሌሎች አይሁዳውያንን በግዞት ወስዷል፤ እነዚህ አይሁዳውያን በአካባቢው ወዳሉ ክልሎች ሸሽተው የነበሩ ሳይሆኑ አይቀሩም።—ኤር 52:30
it-1-E 463 አን. 4
የዘመናት ስሌት
ኢየሩሳሌም መጨረሻ ላይ የተከበበችው ሴዴቅያስ በነገሠ በ9ኛው ዓመት (609 ዓ.ዓ.) ሲሆን ከተማዋ የወደቀችው በ11ኛው ዓመት (607 ዓ.ዓ.) የንግሥና ዘመኑ ነው። ይህ የሆነው ናቡከደነጾር መግዛት በጀመረ በ19ኛው ዓመት (በ625 ዓ.ዓ. ሥልጣን ላይ ከወጣበት ዓመት ጀምሮ ሲቆጠር) ነው ማለት ነው። (2 ነገ 25:1-8) በዚሁ ዓመት አምስተኛ ወር (ከሐምሌ አጋማሽ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ያለውን ጊዜ በሚሸፍነው አብ በተባለው ወር) ላይ ከተማዋ በእሳት ጋየች፤ ቅጥሮቿ ፈረሱ፤ ከነዋሪዎቿም መካከል አብዛኞቹ በግዞት ተወሰዱ። ይሁንና “በምድሪቱ ከነበሩት ያጡ የነጡ ድሆች መካከል አንዳንዶቹ” ናቡከደነጾር በምድሪቱ ላይ የሾመው ጎዶልያስ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ እዚያው በከተማዋ ውስጥ እንዲቆዩ ተፈቅዶላቸው ነበር፤ እሱ ሲገደል ወዲያውኑ ወደ ግብፅ ሸሹ፤ በመሆኑም ይሁዳ ሙሉ በሙሉ ባድማ ሆነች። (2 ነገ 25:9-12, 22-26) ይህ የሆነው ኤታኒም ወይም ቲሽሪ በተባለው በሰባተኛው ወር ነው (ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ያለውን ጊዜ ይሸፍናል)። ስለዚህ ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና የምትቆይባቸው 70 ዓመታት መቆጠር የሚጀምሩት ጥቅምት 1, 607 ዓ.ዓ. ሲሆን የሚያበቁት ደግሞ 537 ዓ.ዓ. ነው። ከግዞት የተመለሱት የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን በ537 ዓ.ዓ. በሰባተኛው ወር ይሁዳ ደረሱ፤ ይህ የሆነው ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ባድማ ከሆነች ከ70 ዓመት በኋላ ነው።—2 ዜና 36:21-23፤ ዕዝራ 3:1
ግንቦት 22-28
jr-E 104-105 አን. 4-6
“ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን” አትፈልግ
4 ባሮክን ያሳሰበው ነገር ዝና ወይም ክብር የማግኘት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ባሮክ የኤርምያስ ጸሐፊ ሆኖ አገልግሏል ሲባል የኤርምያስ የግል ጸሐፊ ብቻ እንደነበረ አድርገን ልናስብ አይገባም። ኤርምያስ 36:32 ላይ ባሮክ “ጸሐፊው” ተብሎ ተጠርቷል። የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ባሮክ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ነበር። ከይሁዳ መኳንንት አንዱ የሆነው ‘ጸሐፊው ኤሊሻማም’ በዚሁ የማዕረግ ስም ተጠርቷል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ባሮክ ከኤሊሻማ የሥራ ባልደረቦች አንዱ እንደመሆኑ መጠን ‘በንጉሡ ቤት’ ወደሚገኘው “ወደ ጸሐፊው ክፍል” መግባት ይችል ነበር። (ኤር. 36:11, 12, 14) በመሆኑም ባሮክ በቤተ መንግሥት ውስጥ የሚያገለግል የተማረ ባለሥልጣን ነበር ማለት ነው። ወንድሙ ሰራያህ በንጉሥ ሴዴቅያስ ቤተ መንግሥት ውስጥ አስተዳዳሪ የነበረ ሲሆን ንጉሡ አንድ አስፈላጊ ጉዳይ ለማከናወን ወደ ባቢሎን በተጓዘበት ወቅት አብሮ ሄዶ ነበር። (ኤርምያስ 51:59ን አንብብ።) ሰራያህ የቤተ መንግሥት አስተዳዳሪ እንደመሆኑ መጠን ንጉሡ ወደተለያዩ ቦታዎች በሚጓዝበት ወቅት የሚያስፈልጉትን ነገሮች የማቅረብና ማረፊያ የማዘጋጀት ኃላፊነት ነበረበት፤ ይህ ደግሞ ትልቅ ቦታ እንደነበረው ያሳያል።
5 ከፍ ባለ የኃላፊነት ቦታ ላይ መሥራት የለመደ ሰው በይሁዳ ላይ የተላለፉ የፍርድ መልእክቶችን በየጊዜው መጻፍ አሰልቺ ሊሆንበት ይችላል። እንዲያውም ባሮክ የአምላክን ነቢይ መርዳቱ ሥልጣኑንና ሥራውን ሊያሳጣው ይችል ነበር። ከዚህም ሌላ ኤርምያስ 45:4 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ የገነባውን ቢያፈርስ ምን ሊከሰት እንደሚችል አስብ። ባሮክ ይፈልገው የነበረው ‘ታላቅ ነገር’ በቤተ መንግሥት ውስጥ የተሻለ ቦታ ማግኘትም ይሁን ቁሳዊ ብልጽግና ከንቱ መሆኑ አይቀርም። ባሮክ ጥፋት በተደቀነበት የአይሁድ ሥርዓት ውስጥ አስተማማኝ ቦታ ለማግኘት እየጣረ ከነበረ አምላክ ይህን ዝንባሌ እንዲያስወግድ መምከሩ ተገቢ ነበር።
6 በሌላ በኩል ደግሞ ባሮክ ይፈልጋቸው ከነበሩት “ታላላቅ ነገሮች” መካከል አንዱ ቁሳዊ ብልጽግና ሊሆን ይችላል። በይሁዳ ዙሪያ የነበሩት ብሔራት የሚመኩት በቁሳዊ ነገሮችና በሀብት ነበር። ሞዓብ የታመነችው ‘በሥራዋና ውድ በሆነ ሀብቷ’ ነበር። አሞንም እንዲሁ አድርጋለች። በተጨማሪም ይሖዋ በኤርምያስ በኩል እንደተናገረው ባቢሎን ‘በሀብት የበለጸገች’ ነበረች። (ኤር. 48:1, 7፤ 49:1, 4፤ 51:1, 13) ይሁን እንጂ አምላክ እነዚህን ብሔራት አውግዟቸዋል።
jr-E 103 አን. 2
“ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን” አትፈልግ
2 ባሮክ “ወዮልኝ፣ ይሖዋ በሥቃዬ ላይ ሐዘን ጨምሮብኛልና! ከማሰማው ሲቃ የተነሳ ዝያለሁ” ሲል የተሰማውን ብሶት ገልጿል። አንተም በውስጥህ እንዲህ ያለ ስሜት አድሮብህ አሊያም የተሰማህን ብሶት በግልጽ ተናግረህ ታውቅ ይሆናል። ባሮክ ብሶቱን የገለጸው በየትኛውም መንገድ ቢሆን ይሖዋ ሰምቶታል። የሰውን ልብ የሚመረምረው አምላክ ባሮክ እንዲህ እንዲመረር ያደረገው ምን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር፤ ስለሆነም በኤርምያስ አማካኝነት በደግነት ምክር ሰጥቶታል። (ኤርምያስ 45:1-5ን አንብብ።) ይሁንና ‘ባሮክ እንዲህ እንዲሰማው ያደረገው ምንድን ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። እንዲህ እንዲሰማው ያደረገው የተሰጠው ኃላፊነት ነው ወይስ ሥራውን ያከናውን የነበረበት ሁኔታ? ይህ ስሜቱ ከውስጥ ፈንቅሎ የወጣ ነው። ባሮክ “ታላላቅ ነገሮችን” ፈልጎ ነበር። እነዚህ ነገሮች ምን ነበሩ? ባሮክ የአምላክን ምክርና መመሪያ ተግባራዊ ካደረገ ይሖዋ ምን እንደሚያደርግለት ቃል ገብቶለት ነበር? ባሮክ ከገጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት እናገኛለን?
it-1-E 430
ከሞሽ
ነቢዩ ኤርምያስ በሞዓብ ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት ትንቢት ሲናገር ዋነኛ አምላኳ የሆነው ከሞሽም ሆነ ካህናቷና መኳንንቷ በግዞት እንደሚወሰዱ ገልጿል። በአሥሩ ነገድ መንግሥት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት እስራኤላውያን በቤቴል ይካሄድ ከነበረው የጥጃ አምልኮ ጋር በተያያዘ በከተማዋ እንዳፈሩ ሁሉ ሞዓባውያንም አምላካቸው አቅመ ቢስ በመሆኑ ያፍራሉ።—ኤር 48:7, 13, 46
it-2-E 422 አን. 2
ሞዓብ
ሞዓብን በተመለከተ የተነገሩት ትንቢቶች በትክክል እንደተፈጸሙ ምንም ጥርጥር የለውም። ሞዓብ ተብሎ የሚጠራው ሕዝብ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ጠፍቷል። (ኤር 48:42) እንደ ነቦ፣ ሃሽቦን፣ አሮዔር፣ ቤትጋሙልና ቤትምዖን ያሉ የሞዓባውያን ከተሞች በዛሬው ጊዜ የፍርስራሽ ክምር ሆነዋል። ሌሎቹ በርካታ ከተሞቻቸው ደግሞ የት እንደነበሩ እንኳ አይታወቅም።
it-1-E 54
ባላጋራ
አምላክ ሕዝቦቹ ታማኝ ሳይሆኑ ሲቀሩ ባላጋራዎቻቸው ድል እንዲያደርጓቸውና እንዲበዘብዟቸው ይፈቅድ ነበር። (መዝ 89:42፤ ሰቆ 1:5, 7, 10, 17፤ 2:17፤ 4:12) ይሁን እንጂ ጠላቶቻቸው ድል የተቀዳጁት በራሳቸው ኃይልና በአማልክታቸው እርዳታ እንደሆነ አድርገው በማሰብ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ይደርሱ ነበር፤ በተጨማሪም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ በፈጸሙት ድርጊት ተጠያቂ እንደማይሆኑ ይሰማቸው ነበር። (ዘዳ 32:27፤ ኤር 50:7) በመሆኑም ይሖዋ እነዚህን ኩሩና ጉረኛ የሆኑ ባላጋራዎች አዋርዷቸዋል (ኢሳ 1:24፤ 26:11፤ 59:18፤ ናሆም 1:2)፤ ይህንንም ያደረገው ለቅዱስ ስሙ ሲል ነው።—ኢሳ 64:2፤ ሕዝ 36:21-24
jr 161-E አን. 15
“ይሖዋ ያሰበውን አድርጓል”
15 ኤርምያስ ግብፅን ድል ያደረገችው ባቢሎን ስለሚደርስባት ጥፋትም ትንቢት ተናግሯል። ኤርምያስ ትንቢቱ ከመፈጸሙ ከመቶ ዓመት በፊት ባቢሎን በድንገት እንደምትወድቅ በትክክል ተንብዮአል። ይህ የአምላክ ነቢይ ከተማዋን ከጥቃት ይከላከሉ የነበሩት በዙሪያዋ ያሉት ውኃዎች ‘እንደሚደርቁ’ እንዲሁም የባቢሎን ኃያላን እንደማይዋጉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኤር. 50:38፤ 51:30) ሜዶናውያንና ፋርሳውያን የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ አስቀይረው ውኃው እንዲጎድል ካደረጉ በኋላ ወንዙን ተሻግረው ባቢሎናውያኑ ባልጠበቁት ሁኔታ ከተማዋን በተቆጣጠሩ ጊዜ ትንቢቱ አንድ በአንድ ተፈጽሟል። ከተማዋ ሰው የማይኖርባት ባድማ እንደምትሆን የተነገረው ትንቢትም ትኩረት የሚስብ ነው። (ኤር. 50:39፤ 51:26) በአንድ ወቅት ኃያል የነበረችው ባቢሎን አሁንም ድረስ ባድማ መሆኗ አምላክ የተናገረው ትንቢት በትክክል እንደሚፈጸም የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
it-1-E 94 አን. 6
አሞናውያን
ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ሳልሳዊ ቴልጌልቴልፌልሶርም ሆነ ከእሱ በኋላ የነገሠው ንጉሥ በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የሚኖሩትን ሰዎች በግዞት ወደ አሦር ከወሰዱ በኋላ (2ነገ 15:29፤ 17:6)፣ አሞናውያን የጋድን ነገድ ክልል መውረር የጀመሩ ሲሆን ከዮፍታሔ ጋር ባደረጉት ውጊያ ድል ተመተዋል። (ከመዝሙር 83:4-8 ጋር አወዳድር።) በዚህ የተነሳ ይሖዋ በኤርምያስ በኩል ባስተላለፈው ትንቢታዊ መልእክት፣ አሞናውያን የጋድን ነገድ መሬት በመያዛቸው የገሠጻቸው ከመሆኑም ሌላ በአሞንና የአሞናውያን አምላክ በሆነው በማልካም (ሚልኮም) ላይ ጥፋት እንደሚመጣ ማስጠንቀቂያ ተናግሯል። (ኤር 49:1-5) ይሁንና አሞናውያን በዚህ ብቻ አላበቁም፤ የይሁዳ መንግሥት የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ በነበረበት ወቅት በንጉሥ ኢዮዓቄም ዘመነ መንግሥት ወራሪ ቡድኖችን በመላክ በይሁዳ ላይ ጥቃት ይፈጽሙ ነበር።—2ነገ 24:2, 3
jr 163 አን. 18
“ይሖዋ ያሰበውን አድርጓል”
18 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. አንድ ሌላ ትንቢትም ተፈጽሟል። አምላክ ባቢሎናውያን ከሚወሯቸው አገሮች መካከል ኤዶምም እንደምትገኝበት በኤርምያስ በኩል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኤር. 25:15-17, 21፤ 27:1-7) ትንቢቱ ኤዶም የሚደርስባትን ነገር በተመለከተ ተጨማሪ መግለጫ ይዟል። ኤዶም እንደ ሰዶምና ገሞራ እንደምትሆን ይገልጻል። ይህም ከሕልውና ውጭ እንደምትሆንና ዳግመኛ ሰው እንደማይኖርባት የሚያሳይ ነው። (ኤር. 49:7-10, 17, 18) የሆነውም ይኸው ነው። ኤዶምና ኤዶማውያን የሚሉት ስሞች በዛሬው ጊዜ ባሉ ካርታዎች ላይ የሚገኙ ይመስልሃል? በፍጹም። እነዚህ ስሞች በአብዛኛው የሚገኙት በጥንታዊ መጻሕፍትና በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ወይም በዚያን ጊዜ የነበረውን ዓለም በሚያሳዩ ካርታዎች ላይ ነው። በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ኤዶማውያን የአይሁድን እምነት በግድ እንዲቀበሉ ተደርገው እንደነበር ፍላቪየስ ጆሴፈስ ዘግቧል። ከዚያ በኋላ ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. ስትደመሰስ ኤዶም ተብሎ የሚጠራው ሕዝብ ጠፍቷል።