የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የኤርምያስ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
ኤርምያስ በገዛ ወገኖቹ ላይ ያወጀው ታላቅ ጥፋት በጣም አስደንጋጭ ሳይሆን አልቀረም! ከ300 ለሚበልጡ ዓመታት የአምልኮ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ዕጹብ ድንቅ ቤተ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ይወድማል። ኢየሩሳሌምና የይሁዳ ምድር ባድማ ይሆናሉ፤ ሕዝቦቻቸውም በግዞት ይወሰዳሉ። እነዚህም ሆኑ ሌሎች የፍርድ አዋጆች፣ ከቅዱሳን መጻሕፍት መካከል በትልቅነቱ ሁለተኛ ደረጃን በያዘው በኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ። በተጨማሪም ይህ መጽሐፍ፣ ኤርምያስ ለ67 ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግል ያሳለፈውን የግል ተሞክሮ ይዟል። በመጽሐፉ ላይ የሰፈረው መረጃ የቀረበው ታሪኮቹ በተፈጸሙበት የጊዜ ቅደም ተከተል ሳይሆን በርዕሰ ጉዳይ ተከፋፍሎ ነው።
የኤርምያስን መጽሐፍ መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ኤርምያስ በነቢይነት ያከናወነው ሥራም ሆነ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ለመልእክቱ የሰጡት ምላሽ በዘመናችን ካለው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ከዚህም በላይ ይሖዋ ከሕዝቦቹ ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጸው ታሪክ ባሕርያቱን አጉልቶ ያሳያል፤ በመሆኑም ዘገባው በሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል።—ዕብራውያን 4:12
“ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል”
ኤርምያስ የነቢይነት ሥራውን የጀመረው ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ በነገሠ በ13ኛው ዓመት ማለትም ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከመጥፋቷ ከ40 ዓመታት በፊት ነው። (ኤርምያስ 1:1, 2) በቀሪዎቹ የኢዮስያስ 18 የንግሥና ዓመታት፣ ኤርምያስ በአብዛኛው ስለ ይሁዳ ክፋትና ይሖዋ በእርሷ ላይ ስላስተላለፈው የፍርድ መልእክት አውጇል። ይሖዋ “ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣ . . . የይሁዳንም ከተሞች፣ ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኤርምያስ 9:11) ለምን? ይሖዋ ምክንያቱን ሲገልጽ “ሕዝቤ ሁለት ኀጢአት ፈጽመዋል” ብሏል።—ኤርምያስ 2:13
ከዚህም ባሻገር መልእክቱ ንስሐ የገቡት ቀሪዎች መልሰው እንደሚቋቋሙ ይናገራል። (ኤርምያስ 3:14-18፤ 12:14, 15፤ 16:14-21) ይሁንና መልእክተኛው ጥሩ ምላሽ አላገኘም። እንዲያውም “በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አለቃ የነበረው” ሰው ኤርምያስን መታው ሌሊቱን ሙሉም በእግር ግንድ ጠረቀው።—ኤርምያስ 20:1-3
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1:11, 12—ይሖዋ ቃሉን ለመጠበቅ መትጋቱ ‘ከለውዝ በትር’ ጋር ምን ግንኙነት አለው? የለውዝ ተክል በአይሁዳውያን አቆጣጠር ‘በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከሚያብቡት’ ዛፎች መካከል አንዱ ነው። (ቁጥር 12, አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከማጥኛ ጽሑፍ ጋር የግርጌ ማስታወሻ) ይሖዋ በምሳሌያዊ መንገድ ‘በየዕለቱ እየማለደ [ነቢያቱን] በመላክ’ ለሕዝቡ የፍርድ መልእክት እንደሚናገርና ቃሉም እስኪፈጸም ድረስ ‘እንደሚተጋ’ ተደርጎ ተገልጿል።—ኤርምያስ 7:25 የ1954 ትርጉም
2:10, 11—የከሃዲዎቹ እስራኤላውያን ድርጊት እንግዳ ነገር የሆነው ለምንድን ነው? በስተ ምዕራብ በኬቲም እንዲሁም በስተ ምሥራቅ በቄዳር የሚኖሩት አረማውያን የሌሎች ብሔራትን አማልክት ሊያመልኩ ቢችሉም እንኳ አማልክቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ በባዕድ አገር አማልክት የመለወጡን ጉዳይ ፈጽሞ አያስቡትም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ይሖዋን በመተው ሕያው ለሆነው አምላክ ሊሰጠው የሚገባውን ክብር በድን ለሆኑት ጣዖታት አሳልፈው ሰጥተዋል።
3:11-22፤ 11:10-12, 17—ሰማርያ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት የጠፋች ቢሆንም ኤርምያስ በተናገረው የፍርድ መልእክት ውስጥ አሥሩን ነገድ ያቀፈውን የሰሜኑን መንግሥት የጨመረው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበት ምክንያት በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ጥፋት ይሖዋ በይሁዳ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የእስራኤል ብሔር ላይ መፍረዱን ስለሚያመለክት ነው። (ሕዝቅኤል 9:9, 10) ከዚህም በላይ የአምላክ ነቢያት መልእክት እስራኤላውያንንም ይጨምር ስለነበር አሥሩን ነገድ ያቀፈው መንግሥት ከወደቀ በኋላ ዳግም ወደ ምድራቸው የመመለስ ተስፋቸው ከኢየሩሳሌም ሕልውና ጋር የተያያዘ ነበር።
4:3, 4—የዚህ ትእዛዝ ትርጉም ምንድን ነው? ታማኝ ያልሆኑት አይሁዳውያን በመሬት የተመሰለውን ልባቸውን ማዘጋጀት፣ ማለስለስና ማጽዳት ይጠበቅባቸው ነበር። የልባቸውንም “ሸለፈት” መግረዝ፣ በሌላ አባባል መጥፎ የሆነውን አስተሳሰባቸውን፣ ስሜታቸውንና ዝንባሌያቸውን ማስወገድ ነበረባቸው። (ኤርምያስ 9:25, 26፤ የሐዋርያት ሥራ 7:51) ይህም ከክፉ መንገዳቸው ተመልሰው የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝላቸውን ነገር በማድረግ አኗኗራቸውን መቀየር ይጠይቅባቸዋል።
4:10፤ 15:18—ይሖዋ ዓመጸኛ የሆኑትን ሕዝቦቹን ያታለላቸው በምን መንገድ ነው? በኤርምያስ ዘመን ‘የሐሰት ትንቢት የሚናገሩ’ ነቢያት ነበሩ። (ኤርምያስ 5:31፤ 20:6፤ 23:16, 17, 25-28, 32) ይሖዋ እነዚህን የሐሰት ነቢያት አሳሳች የሆኑ መልእክቶች እንዳይናገሩ አልከለከላቸውም።
16:16—ይሖዋ “ብዙ ዓሣ አጥማጆችን” እና ‘ብዙ አዳኞችን መላኩ’ ምን ያመለክታል? ይሖዋ ከሃዲ በሆኑት አይሁዳውያን ላይ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም የጠላት ኃይሎችን እንደሚልክባቸው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ከኤርምያስ 16:15 አንጻር ስናየው ጥቅሱ ንስሐ የገቡ እስራኤላውያንን በመፈለግ ወደ ምድራቸው እንደሚመልሳቸው ሊያመለክት ይችላል።
20:7—ይሖዋ በኤርምያስ ላይ ‘የበረታውና’ ያታለለው በምን መንገድ ነው? ኤርምያስ የይሖዋን ፍርድ በሚያውጅበት ጊዜ የገጠመው የቸልተኝነት መንፈስ፣ ተቃውሞና ስደት፣ በሥራው ለመግፋት የሚያስችል ጥንካሬ እንዳነሰው ሆኖ እንዲሰማው አድርጎት ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ኤርምያስ ያደረበትን አሉታዊ አስተሳሰብ እንዲያስወግድና በሥራው እንዲቀጥል ብርታት ሰጥቶታል። ስለዚህ ይሖዋ ነቢዩ ሊወጣው እንደማይችለው የተሰማውን ሥራ እንዲያከናውን በማድረግ ኤርምያስን አታልሎታል ማለት ይቻላል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:8፦ በአንዳንድ ወቅቶች ይሖዋ ፍትሕ ወዳድ የሆኑ ዳኞችን በማስነሳት፣ ክፉ ባለ ሥልጣናትን ምክንያታዊ በሆኑት በመተካት ወይም ደግሞ ለአምላኪዎቹ ለመጽናት የሚያስችላቸውን ጥንካሬ በመስጠት ሕዝቦቹን ከስደት ሊታደጋቸው ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 10:13
2:13, 18፦ ታማኝ ያልሆኑት እስራኤላውያን ሁለት ክፉ ድርጊቶችን ፈጽመዋል። በረከት፣ መመሪያና ጥበቃ የሚያስገኝላቸውን አስተማማኝ ምንጭ ማለትም ይሖዋን ትተዋል። እንዲሁም ከግብፅና ከአሦር ጋር ወታደራዊ ጥምረት በመመሥረት በምሳሌያዊ አነጋገር ለራሳቸው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ቆፍረዋል። በዘመናችን እውነተኛውን አምላክ ትቶ ወደ ሰዎች ፍልስፍናና ጽንሰ ሐሳብ እንዲሁም ወደ ዓለም ፖለቲካ ዘወር ማለት ‘ሕያው የሆነውን የውሃ ምንጭ፣ ቀዳዳ በሆነ የውሃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ’ የመተካት ያህል ነው።
6:16፦ ይሖዋ ዓመጸኛ ሕዝቦቹ ቆም ብለው እንዲያስቡ፣ ራሳቸውን እንዲመረምሩና ታማኝ ቅድመ አያቶቻቸው ሲጓዙባት ወደነበረችው “መንገድ” እንዲመለሱ አሳስቧቸዋል። እኛስ ይሖዋ እንድንሄድበት በሚፈልግብን መንገድ እየሄድን መሆን አለመሆናችንን ለማወቅ በየጊዜው ራሳችንን መመርመር አይኖርብንም?
7:1-15፦ አይሁዳውያን አንዳች ምትኃታዊ ኃይል እንዳለው በማሰብ ጥበቃ ለማግኘት በቤተ መቅደሱ ቢታመኑም ከመጥፋት አልዳኑም። እኛም በእምነት እንጂ በማየት መመላለስ የለብንም።—2 ቆሮንቶስ 5:7
15:16, 17:- ልክ እንደ ኤርምያስ እኛም የተስፋ መቁረጥ ስሜትን መቋቋም እንችላለን። ትርጉም ያለው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በአገልግሎት የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ማድረግና ከክፉ ጓደኞች መራቅ ይህን እንድናደርግ ያስችለናል።
17:1, 2፦ የይሁዳ ሕዝቦች ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት የሚያቀርቡት መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ሆኗል። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችን ከጎደፈ የምናቀርበው የምስጋና መሥዋዕት ተቀባይነት አይኖረውም።
17:5-8፦ በሰዎችም ሆነ በሰብዓዊ ድርጅቶች እምነት የምንጥለው ከአምላክ ፈቃድና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እስከተመላለሱ ድረስ ብቻ ነው። እንደ መዳን፣ እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት ማስገኘት በመሳሰሉት ጉዳዮች ረገድ ግን የምንታመነው በይሖዋ ብቻ ነው።—መዝሙር 146:3
20:8-11፦ የሰዎች ቸልተኝነት፣ ተቃውሞና ስደት ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ ያለንን ቅንዓት እንዲያቀዘቅዝብን መፍቀድ አይኖርብንም።—ያዕቆብ 5:10, 11
“አንገታችሁን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዝቅ አድርጉ”
ኤርምያስ በመጨረሻዎቹ አራት የይሁዳ ነገሥታት፣ በሐሰተኛ ነቢያት፣ በክፉ እረኞችና ምግባረ ብልሹ በሆኑ ካህናት ላይ የፍርድ መልእክት አስተላልፏል። ይሖዋ በመልካም በለስ የመሰላቸውን ታማኝ ቀሪዎች አስመልክቶ “ዐይኔን ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ” ብሏል። (ኤርምያስ 24:5, 6) በምዕራፍ 25 ላይ የሚገኙ ሦስት ትንቢቶች፣ በሌሎቹ ምዕራፎች ላይ በሰፊው ስለሚብራሩ የፍርድ መልእክቶች በአጭሩ ይናገራሉ።
ካህናቱና ነቢያቱ ኤርምያስን ለመግደል አሴሩ። ኤርምያስ የባቢሎንን ንጉሥ ማገልገል እንዳለባቸው የሚገልጽ መልእክት ይናገር ነበር። እንዲያውም ለንጉሥ ሴዴቅያስ “አንገታችሁን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች ዝቅ አድርጉ” ብሎታል። (ኤርምያስ 27:12) ይሁንና “እስራኤልን የበተነ እርሱ [እስራኤልን] ይሰበስበዋል።” (ኤርምያስ 31:10) ለሬካባውያን ተስፋ መሰጠቱ ተገቢ ነው። ኤርምያስ “በዘብ ጠባቂዎች አደባባይ እንዲቀመጥ” ተደረገ። (ኤርምያስ 37:21) ኢየሩሳሌም የጠፋች ሲሆን አብዛኞቹ ነዋሪዎቿም በምርኮ ተወሰዱ። በምርኮ ሳይወሰዱ ከቀሩት የተወሰኑ ሰዎች መካከል ኤርምያስና ጸሐፊው ባሮክ ይገኙበታል። ኤርምያስ እንዳይሄዱ ቢያስጠነቅቃቸውም አንዳንድ ፍርሃት ያሸነፋቸው ሰዎች ወደ ግብፅ ሸሹ። ከምዕራፍ 46 እስከ ምዕራፍ 51 ላይ የሚገኙት ቃላት ኤርምያስ ለአሕዛብ የተናገረውን መልእክት ይዘዋል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
22:30—ይህ አዋጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊትን ዙፋን የመውረስ መብቱን ያሳጣዋል? (ማቴዎስ 1:1, 11) በፍጹም አያሳጣውም። አዋጁ ማንኛውም የኢዮአቄም ዘር ‘በዳዊት ዙፋን ተቀምጦ በይሁዳ ላይ እንዳይገዛ’ የሚከለክል ነው። ኢየሱስ የሚገዛው በይሁዳ ባለው ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳይሆን በሰማይ ሆኖ ነው።
23:33—“የእግዚአብሔር ሸክም” ምንድን ነው? በኤርምያስ ዘመን ነቢዩ ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ያወጀው ክብደት ያለው የፍርድ መልእክት ለወገኖቹ ሸክም ሆኖባቸው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ እርሱን የማይሰሙት ሰዎች ሸክም ስለሆኑበት ይወረውራቸዋል። በተመሳሳይም በሕዝበ ክርስትና ላይ ስለሚመጣው ጥፋት የሚናገረው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት ለሕዝበ ክርስትና ሸክም ሆኖባታል። ይህን መልእክት ሰምተው እርምጃ የማይወስዱ ሰዎች ደግሞ ለአምላክ ከባድ ሸክም ሆነውበታል።
31:33—የአምላክ ሕግ በልብ ላይ የሚጻፈው እንዴት ነው? አንድ ሰው የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ልባዊ ፍላጎት እስኪያድርበት ድረስ የአምላክን ሕግ በጥልቅ የሚወድ ከሆነ ሕጉ በልቡ ላይ ተጽፏል ሊባል ይችላል።
32:10-15—ለአንድ የግዢ ውል ሁለት ሰነዶች ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዓላማ ምንድን ነው? ያልታሸገው የውል ሰነድ ለማስረጃነት የሚቀመጥ ሲሆን የታሸገው ደግሞ ያልታሸገውን ሰነድ ትክክለኛነት ማጣራት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለማመሳከሪያነት የሚያገለግል ነው። ኤርምያስ ከሥጋ ዘመድም ይሁን ከእምነት ባልደረባ ጋር በሚደረጉ ውሎች እንኳ ምክንያታዊ የሆኑ ሕጋዊ ሂደቶችን መከተል እንዳለብን የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል።
33:23, 24—እዚህ ላይ ‘ሁለት መንግሥታት [“ቤተሰብ፣” NW]’ ተብለው የተጠሩት እነማን ናቸው? አንደኛው በንጉሥ ዳዊት በኩል የመጣው ንጉሣዊ ቤተሰብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በአሮን ዘር በኩል የመጣው የካህናት ቤተሰብ ነው። ኢየሩሳሌምና የይሖዋ ቤተ መቅደስ መጥፋታቸው ይሖዋ እነዚህን ሁለት ቤተሰቦች እንደተዋቸውና ከዚያ በኋላም በምድር ላይ እርሱን የሚወክል መንግሥት እንደማይኖረው ወይም አምልኮው እንደገና እንደማይቋቋም የሚያሳይ ይመስል ነበር።
46:22—የግብፅ ድምፅ በእባብ ፉጨት የተመሰለው ለምንድን ነው? ይህ አባባል የግብፅን መሸሽ ለማመልከት አሊያም ብሔሩ ከደረሰበት ጥፋት የተነሳ ኀፍረት መከናነቡን ለመግለጽ የተነገረ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ይህ አባባል የግብፅ ፈርዖኖች ኡአትችት የተባለችው እንስት የእባብ አምላክ ጥበቃ እንደምታደርግላቸው በማመን የቅዱስ እባብ ምስል በዘውዳቸው ላይ ማድረጋቸው ምን ያህል ከንቱ እንደሆነም ያሳያል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
21:8, 9፤ 38:19፦ ይሖዋ ንስሐ ለመግባት እምቢተኞች በመሆናቸው ምክንያት ሞት ይገባቸው ለነበሩት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሊጠፉ በተቃረቡበት በመጨረሻው ሰዓት እንኳ ምርጫ አቅርቦላቸው ነበር። አዎን፣ ይሖዋ ‘ምሕረቱ ታላቅ ነው።’—2 ሳሙኤል 24:14፤ መዝሙር 119:156
31:34፦ ይሖዋ ይቅር ያላቸውን ሰዎች ኃጢአት በማስታወስ እንደገና እንደማይቀጣቸው ማወቅ እንዴት ያጽናናል!
38:7-13፤ 39:15-18፦ ይሖዋ ‘ቅዱሳንን መርዳትን’ ጨምሮ በታማኝነት የምናቀርበውን አገልግሎት አይረሳም።—ዕብራውያን 6:10
45:4, 5፦ የአይሁዳውያን ሥርዓት ሊያከትም በተቃረበበት ጊዜ እንደነበረው ሁሉ የዚህ ዓለም ‘የመጨረሻ ዘመንም’ “ታላቅ ነገር” የምንሻበት ማለትም ሀብት፣ ታዋቂነትና አስተማማኝ ቁሳዊ ንብረት ለማግኘት የምንሯሯጥበት ጊዜ አይደለም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ 1 ዮሐንስ 2:17
ኢየሩሳሌም በእሳት ጋየች
ወቅቱ 607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን ሴዴቅያስ ንግሥናውን ከያዘ 11ኛ ዓመቱ ነው። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ለአንድ ዓመት ተኩል ከብቧታል። ናቡከደነፆር በነገሠ በ19ኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የክብር ዘብ ሰራዊት አዛዥ የሆነው ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም “መጣ።” (2 ነገሥት 25:8) ምናልባትም ናቡዘረዳን ከከተማዋ ቅጥር ውጪ ባለው የጦር ሰፈሩ ሆኖ ሁኔታውን ሳያጠናና ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት እቅድ ሳያወጣ አልቀረም። ከሦስት ቀን በኋላም ማለትም ወሩ በገባ በአሥረኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም “መጣ [“ገባ፣” የ1980 ትርጉም]።” ከዚያም ከተማይቱን በእሳት አጋያት።—ኤርምያስ 52:12, 13
ኤርምያስ የኢየሩሳሌምን አወዳደቅ በተመለከተ ዝርዝር ዘገባ አስፍሯል። ሁኔታውን የገለጸበት መንገድ የሐዘን እንጉርጉሮ ለመጻፍ መሠረት ጥሏል። እነዚህ የሐዘን እንጉርጉሮዎች ሰቆቃወ ኤርምያስ በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ሰፍረዋል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤርምያስ ያስተላለፈው አዋጅ ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ የሚያመጣውን የፍርድ መልእክት ያካተተ ነው
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በኤርምያስ ላይ ‘የበረታበት’ እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፣ የይሁዳን ምርኮ በመልካም አስበዋለሁ።’—ኤርምያስ 24:5