የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ታኅሣሥ 2020
ከታኅሣሥ 7-13
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 10–11
“ለይሖዋ ያለን ፍቅር ለቤተሰባችን ካለን ፍቅር ሊበልጥ ይገባል”
(ዘሌዋውያን 10:1, 2) በኋላም የአሮን ወንዶች ልጆች ናዳብና አቢሁ እያንዳንዳቸው የዕጣን ማጨሻቸውን አምጥተው በላዩ ላይ እሳት አደረጉበት፤ በእሳቱም ላይ ዕጣን ጨመሩበት። ከዚያም ይሖዋ እንዲያደርጉ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደ እሳት በፊቱ አቀረቡ። 2 በዚህ ጊዜ እሳት ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በላቸው፤ እነሱም በይሖዋ ፊት ሞቱ።
it-1 1174
ያልተፈቀደ
ያልተፈቀደ እሳትና ዕጣን። በዘሌዋውያን 10:1 ላይ “ያልተፈቀደ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ዛር (በአንስታይ ፆታ ሲቀመጥ ዛራ፤ ቃል በቃል እንግዳ የሚል ትርጉም አለው) የሚለው ነው፤ የአሮን ልጆች የሆኑት ናዳብና አቢሁ “ይሖዋ እንዲያደርጉ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደ እሳት” በማቅረባቸው ይሖዋ በእሳት እንዲጠፉ አድርጓል። (ዘሌ 10:1, 2፤ ዘኁ 3:4፤ 26:61) በኋላም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ስትገቡ አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ። ይህ ትእዛዝ ለትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላለማዊ ደንብ ነው። ይህም ቅዱስ የሆነውን ከረከሰው ነገር እንዲሁም ንጹሕ ያልሆነውን ንጹሕ ከሆነው ነገር ለመለየት እንዲሁም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸውን ሥርዓቶች በሙሉ ለእስራኤላውያን ለማስተማር ነው።” (ዘሌ 10:8-11) ይህ ጥቅስ፣ ናዳብና አቢሁ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥተው እንደነበር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ ምናልባትም ያልተፈቀደ እሳት ለማቅረብ የተደፋፈሩት በዚህ የተነሳ ይሆናል። እሳቱን ያልተፈቀደ ያደረገው የቀረበበት ጊዜ፣ ቦታ ወይም መንገድ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ዕጣኑ በዘፀአት 30:34, 35 ላይ በተገለጸው መሠረት ያልተቀመመ ሊሆን ይችላል። በመጠጥ ተገፋፍተው ይህን ማድረጋቸው የኃጢአቱን ክብደት አይቀንሰውም።
(ዘሌዋውያን 10:4, 5) ሙሴም የአሮን አጎት የዑዚኤል ልጆች የሆኑትን ሚሳኤልንና ኤሊጻፋንን ጠርቶ “ኑ፣ ወንድሞቻችሁን ከቅዱሱ ስፍራ ፊት ለፊት አንስታችሁ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ቦታ አውጧቸው” አላቸው። 5 ስለዚህ መጥተው ልክ ሙሴ በነገራቸው መሠረት ሟቾቹን ከነቀሚሳቸው ተሸክመው ከሰፈሩ ውጭ አወጧቸው።
(ዘሌዋውያን 10:6, 7) ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም ሌሎቹን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እንዳትሞቱ እንዲሁም አምላክ በመላው ማኅበረሰብ ላይ እንዳይቆጣ ፀጉራችሁን አታንጨብርሩ ወይም ልብሶቻችሁን አትቅደዱ። ሆኖም ወንድሞቻችሁ ይኸውም መላው የእስራኤል ቤት ይሖዋ በእሳት ለገደላቸው ያለቅሱላቸዋል። 7 የይሖዋ የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ላይ ስላለ ከመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ መራቅ የለባችሁም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ።” እነሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ።
ወደ አምላክ እረፍት ገብተሃል?
16 የሙሴ ወንድም አሮን ከሁለት ልጆቹ ጋር በተያያዘ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ናዳብና አብዩድ የተባሉት ልጆቹ በይሖዋ ፊት ያልተፈቀደ እሳት በማቅረባቸው በተቀሰፉ ጊዜ አሮን ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው። እርግጥ ነው፣ የአሮን ልጆች ስለሞቱ ከዚያ በኋላ ከወላጆቻቸው ጋር መነጋገር አይችሉም ነበር። ይሁንና ነገሩ በዚህ አላበቃም። ይሖዋ፣ ለአሮንና ታማኝ ለሆኑት ልጆቹ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ [ሐዘናችሁን ለመግለጽ] ጠጕራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ።” (ዘሌ. 10:1-6) ትምህርቱ ግልጽ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ ታማኝ ላልሆኑ የቤተሰባችን አባላት ካለን ፍቅር መብለጥ ይኖርበታል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 10:8-11) ከዚያም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ 9 “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ስትገቡ አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ። ይህ ትእዛዝ ለትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላለማዊ ደንብ ነው። 10 ይህም ቅዱስ የሆነውን ከረከሰው ነገር እንዲሁም ንጹሕ ያልሆነውን ንጹሕ ከሆነው ነገር ለመለየት 11 እንዲሁም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸውን ሥርዓቶች በሙሉ ለእስራኤላውያን ለማስተማር ነው።”
በምግባራችን ሁሉ ቅዱስ መሆን አለብን
18 ቅዱስ ለመሆን የአምላክን ቃል በጥልቀት መመርመርና እሱ የሚጠብቅብንን መፈጸም ይኖርብናል። “ያልተፈቀደውን እሳት” በማቅረባቸው የተቀሰፉትን ናዳብንና አብዩድን እንመልከት፤ እነዚህ የአሮን ልጆች ይህን ያደረጉት በአልኮል መጠጥ ተገፋፍተው ሳይሆን አይቀርም። (ዘሌ. 10:1, 2) ናዳብና አብዩድ ከሞቱ በኋላ አምላክ ለአሮን ምን እንዳለው አስተውለሃል? (ዘሌዋውያን 10:8-11ን አንብብ።) ይህ ታሪክ ወደ ክርስቲያን ስብሰባዎች ከመሄዳችን በፊት ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ መቅመስ እንደሌለብን የሚያሳይ ነው? እስቲ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ነጥቦች ልብ በል፦ እኛ በሙሴ ሕግ ሥር አይደለንም። (ሮም 10:4) በአንዳንድ አገሮች የእምነት ባልንጀሮቻችን ወደ ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ምግብ ሲመገቡ የአልኮል መጠጦችን በልኩ መውሰዳቸው የተለመደ ነው። በፋሲካ በዓል ላይ ወይን ጠጅ የያዙ አራት ጽዋዎች ይቀርቡ ነበር። ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ሐዋርያቱ ደሙን የሚወክለውን ወይን ጠጅ እንዲጠጡ አድርጓል። (ማቴ. 26:27) መጽሐፍ ቅዱስ ከመጠን በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (1 ቆሮ. 6:10፤ 1 ጢሞ. 3:8) በርካታ ክርስቲያኖች በማንኛውም ዓይነት ቅዱስ አገልግሎት ከመካፈላቸው በፊት የአልኮል መጠጥ ለመጠጣት ሕሊናቸው ስለማይፈቅድላቸው በዚህ ጊዜ ጨርሶ መጠጥ አይቀምሱም። ይሁንና ሁኔታዎች ከአገር አገር ይለያያሉ፤ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ክርስቲያኖች ‘የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን በመለየት’ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ቅዱስ ሆነው መመላለሳቸው ነው።
(ዘሌዋውያን 11:8) የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ ወይም በድናቸውን አትንኩ። እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው።
it-1 111 አን. 5
እንስሳት
ከሚበሉና ከማይበሉ ነገሮች ጋር በተያያዘ የተሰጡት መመሪያዎች የሚሠሩት በሙሴ ሕግ ሥር ላሉት ብቻ ነው፤ ምክንያቱም በዘሌዋውያን 11:8 ላይ “እነዚህ ለእናንተ ርኩስ ናቸው” የተባሉት እስራኤላውያን ናቸው። በክርስቶስ ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት አማካኝነት ሕጉ ሲሻር በሕጉ ውስጥ የነበሩት እነዚህ እገዳዎች ተነስተዋል፤ ከዚያ በኋላ ሁሉም የሰው ዘር ከጥፋት ውኃ በኋላ ለኖኅ ወደተሰጠው ሰፋ ያለ ደንብ ተመልሷል ሊባል ይችላል።—ቆላ 2:13-17፤ ዘፍ 9:3, 4
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 10:1-15) በኋላም የአሮን ወንዶች ልጆች ናዳብና አቢሁ እያንዳንዳቸው የዕጣን ማጨሻቸውን አምጥተው በላዩ ላይ እሳት አደረጉበት፤ በእሳቱም ላይ ዕጣን ጨመሩበት። ከዚያም ይሖዋ እንዲያደርጉ ያላዘዛቸውን ያልተፈቀደ እሳት በፊቱ አቀረቡ። 2 በዚህ ጊዜ እሳት ከይሖዋ ፊት ወጥቶ በላቸው፤ እነሱም በይሖዋ ፊት ሞቱ። 3 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡ ሰዎች መካከል እቀደሳለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከበራለሁ’ ብሏል።” አሮንም ዝም አለ። 4 ሙሴም የአሮን አጎት የዑዚኤል ልጆች የሆኑትን ሚሳኤልንና ኤሊጻፋንን ጠርቶ “ኑ፣ ወንድሞቻችሁን ከቅዱሱ ስፍራ ፊት ለፊት አንስታችሁ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ቦታ አውጧቸው” አላቸው። 5 ስለዚህ መጥተው ልክ ሙሴ በነገራቸው መሠረት ሟቾቹን ከነቀሚሳቸው ተሸክመው ከሰፈሩ ውጭ አወጧቸው። 6 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም ሌሎቹን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “እንዳትሞቱ እንዲሁም አምላክ በመላው ማኅበረሰብ ላይ እንዳይቆጣ ፀጉራችሁን አታንጨብርሩ ወይም ልብሶቻችሁን አትቅደዱ። ሆኖም ወንድሞቻችሁ ይኸውም መላው የእስራኤል ቤት ይሖዋ በእሳት ለገደላቸው ያለቅሱላቸዋል። 7 የይሖዋ የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ላይ ስላለ ከመገናኛ ድንኳኑ ደጃፍ መራቅ የለባችሁም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ።” እነሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ። 8 ከዚያም ይሖዋ አሮንን እንዲህ አለው፦ 9 “እንዳትሞቱ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ስትገቡ አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶች ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ። ይህ ትእዛዝ ለትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላለማዊ ደንብ ነው። 10 ይህም ቅዱስ የሆነውን ከረከሰው ነገር እንዲሁም ንጹሕ ያልሆነውን ንጹሕ ከሆነው ነገር ለመለየት 11 እንዲሁም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸውን ሥርዓቶች በሙሉ ለእስራኤላውያን ለማስተማር ነው።” 12 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲሁም የተረፉትን የአሮን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፦ “ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች የተረፈውን የእህል መባ ወስዳችሁ ያለእርሾ በማዘጋጀት በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤ ምክንያቱም ይህ እጅግ ቅዱስ ነገር ነው። 13 ለይሖዋ በእሳት ከሚቀርቡት መባዎች ላይ ይህ የአንተ ድርሻና የወንዶች ልጆችህ ድርሻ ስለሆነ ቅዱስ በሆነ ስፍራ ብሉት፤ ምክንያቱም እንዲህ እንዳደርግ ታዝዣለሁ። 14 እንዲሁም የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባና የቅዱሱን ድርሻ እግር አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያሉት ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ንጹሕ በሆነ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች እስራኤላውያን ከሚያቀርቧቸው የኅብረት መሥዋዕቶች ላይ የአንተ ድርሻና የወንዶች ልጆችህ ድርሻ ሆነው የተሰጡ ናቸው። 15 እነሱም የቅዱሱን ድርሻ እግርና የሚወዘወዘውን መባ ፍርምባ በእሳት ከሚቀርቡት የስብ መባዎች ጋር ያመጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የሚወዘወዘውን መባ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ለመወዝወዝ ነው፤ ልክ ይሖዋ ባዘዘው መሠረትም ይህ ለአንተና ከአንተ ጋር ላሉት ወንዶች ልጆችህ ዘላለማዊ ድርሻ ሆኖ ያገለግላል።”
ከታኅሣሥ 14-20
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 12–13
“የሥጋ ደዌን በተመለከተ ከተሰጡት ሕጎች የምናገኘው ትምህርት”
(ዘሌዋውያን 13:4, 5) ሆኖም በቆዳው ላይ ያለው ቋቁቻ ነጭ ከሆነና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ካልተለወጠ ካህኑ ቁስል የወጣበትን ሰው ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል። 5 ከዚያም በሰባተኛው ቀን ካህኑ ሰውየውን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ባለበት ከቆመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ ካህኑ ሰውየውን ለተጨማሪ ሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል።
ዘመን ያለፈበት ወይስ ከዘመኑ የቀደመ?
• የታመሙ ሰዎች ከጤነኞች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግ
የሙሴ ሕግ የሥጋ ደዌ የያዛቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ያዝዝ ነበር። ሆኖም ሐኪሞች በመካከለኛው ዘመን ወረርሽኝ እስከተከሰተበት ጊዜ ድረስ ይህን መመሪያ ተግባራዊ የማድረግን ጥቅም አልተገነዘቡም፤ ይህ ዘዴ ውጤታማ መሆኑ በዘመናችንም ቢሆን ተቀባይነት አለው።—ዘሌዋውያን ምዕራፍ 13 እና 14
(ዘሌዋውያን 13:45, 46) የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው ልብሶቹ የተቀዳደዱ ይሁኑ፤ ፀጉሩም ይንጨብረር፤ አፍንጫው ሥር እስካለው ጢም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ፣ ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46 ሰውየው ደዌው በላዩ ላይ ባለበት ጊዜ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። ርኩስ ስለሆነም ከሰዎች ተገልሎ መኖር አለበት። መኖሪያውም ከሰፈሩ ውጭ ይሆናል።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
የጥንቶቹ አይሁዳውያን በወቅቱ በነበረው የሥጋ ደዌ እንዳይያዙ ይፈሩ ነበር። አስፈሪ የሆነው ይህ ተላላፊ በሽታ የታማሚውን የነርቭ ጫፎች በማጥቃት ዘላቂ ጉዳትና የመልክ መበላሸት ያስከትል ነበር። በወቅቱ የሥጋ ደዌ መድኃኒት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ከሰዎች ተገልለው እንዲኖሩ የሚደረግ ከመሆኑም ሌላ ይህ በሽታ እንዳለባቸው ለሌሎች የማሳወቅ ግዴታ ነበረባቸው።—ዘሌዋውያን 13:45, 46
(ዘሌዋውያን 13:52) እሱም ደዌው ያለበትን ልብስ ወይም የሱፍም ሆነ የበፍታ ድር ወይም ማግ አሊያም ደግሞ ከቆዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ ያቃጥል፤ ምክንያቱም ይህ አደገኛ ደዌ ነው። በእሳት መቃጠል ይኖርበታል።
(ዘሌዋውያን 13:57) ይሁንና ደዌው በልብሱ ወይም በድሩ አሊያም በማጉ ወይም ደግሞ ከቆዳ በተሠራው በማንኛውም ዕቃ ላይ በሌላ ቦታ አሁንም ከታየ ደዌው እየተስፋፋ ነው፤ ስለዚህ በደዌው የተበከለውን ማንኛውንም ዕቃ በእሳት አቃጥለው።
it-2 238 አን. 3
የሥጋ ደዌ
በአልባሳት እና በቤት ላይ። ደዌ በሱፍ ወይም በበፍታ በተሠራ ልብስ አሊያም በቆዳ በተሠራ ነገር ላይ ሊወጣ ይችላል። ደዌው በእጥበት ብቻ ሊለቅ ይችላል፤ የተበከለው ዕቃ ተለይቶ እንዲቆይ ይደረጋል። ወደ ቢጫነት ያደላ አረንጓዴ ወይም ቀላ ያለው ምልክት ካልጠፋ ግን ደዌው አደገኛ ስለሆነ ዕቃው ይቃጠል ነበር። (ዘሌ 13:47-59) በአንድ ቤት ግድግዳ ላይ ወደ ቢጫነት ያደላ አረንጓዴ ወይም ቀላ ያለ የተቦረቦረ ምልክት ከታየ ካህኑ ቤቱን ያሽገዋል። የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡና ቤቱ ከውስጥ በኩል እንዲፈቀፈቅ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል፤ ተሰርስረው የወጡት ድንጋዮችም ሆኑ ተፈቅፍቆ የተነሳው ልስን ከከተማዋ ውጭ በሚገኝ ርኩስ የሆነ ስፍራ ይደፋል። ደዌው እንደገና ተመልሶ በቤቱ ላይ ከታየ ካህኑ ቤቱ ርኩስ እንደሆነ ያስታውቃል፤ ከዚያም ቤቱ እንዲፈርስ የሚደረግ ሲሆን ፍርስራሹም ርኩስ በሆነ ቦታ ይጣላል። ቤቱ ንጹሕ ነው ከተባለ ግን የመንጻት ሥርዓት የሚካሄድበት ዝግጅት ይደረጋል። (ዘሌ 14:33-57) በአልባሳት ወይም በቤት ላይ የሚወጣው ደዌ የሻጋታ ዓይነት እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፤ ሆኖም ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 12:2) “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘አንዲት ሴት ብታረግዝና ወንድ ልጅ ብትወልድ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለሰባት ቀን ትረክሳለች።
(ዘሌዋውያን 12:5) “‘ሴት ልጅ ከወለደች ደግሞ በወር አበባዋ ወቅት እንደምትረክሰው ሁሉ ለ14 ቀን ትረክሳለች። ከደም ራሷን ለማንጻትም ለቀጣዮቹ 66 ቀናት ትቆያለች።
የዘሌዋውያን መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
12:2, 5—ልጅ መውለድ አንዲትን ሴት ‘የሚያረክሳት’ ለምንድን ነው? የመራቢያ አካላት የተፈጠሩት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት እንዲያስተላልፉ ተደርገው ነው። ይሁን እንጂ በውርስ በሚተላለፈው ኃጢአት ምክንያት ወደ ልጁ የሚተላለፈው ፍጹም ያልሆነና ኃጢአተኛ ሕይወት ነው። በወሊድ እንዲሁም በወር አበባ ጊዜ ወይም ከወንድ ዘር መፍሰስ ጋር በተያያዘ ለተወሰነ ጊዜ ‘ርኩስ’ መሆን እስራኤላውያን ይህንን በውርስ የሚተላለፍ ኃጢአተኝነት እንዲያስታውሱ ይረዳቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 15:16-24፤ መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) ከዚህ ርኩሰት ለመንጻት የሚደረገው ሥነ ሥርዓት የሰውን ልጅ ከኃጢአቱ ለመዋጀትና ፍጹም እንዲሆን ለማድረግ ቤዛዊ መሥዋዕት እንደሚያስፈልግ እስራኤላውያን እንዲገነዘቡ ይረዳቸው ነበር። በዚህ መንገድ ሕጉ ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርሳቸው ሞግዚታቸው ሆኗል።’—ገላትያ 3:24
(ዘሌዋውያን 12:3) ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ይገረዛል።
ዘመን ያለፈበት ወይስ ከዘመኑ የቀደመ?
• ሕፃናት የሚገረዙበት ጊዜ
የአምላክ ሕግ ወንድ ልጅ በተወለደ በስምንተኛው ቀን መገረዝ እንዳለበት አዟል። (ዘሌዋውያን 12:3) አራስ ሕፃናት ሰውነታቸው ሲቆረጥ፣ ደማቸው ቶሎ መቆም የሚችልበት ደረጃ ላይ የሚደርሰው ከተወለዱ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሆነ ይታመናል። ከዚህ አንጻር ዘመናዊ ሕክምና ባልነበረበት በጥንት ዘመን አንድ ሕፃን ከመገረዙ በፊት አንድ ሳምንት እንዲያልፍ የሚያዘው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጥበብ ያዘለ እንደሆነ መመልከት ይቻላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 13:9-28) “አንድ ሰው የሥጋ ደዌ ቢይዘው ወደ ካህኑ እንዲቀርብ ይደረግ፤ 10 ካህኑም ይመረምረዋል። በቆዳው ላይ ነጭ እብጠት ካለና በዚያ ቦታ ላይ ያለውን ፀጉር ወደ ነጭነት ከለወጠው እንዲሁም በእብጠቱ ላይ አፉን የከፈተ ቁስል ካለ 11 ይህ በቆዳው ላይ የወጣ ሥር የሰደደ የሥጋ ደዌ ነው፤ ካህኑም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ሰውየው ርኩስ ስለሆነም ለተወሰነ ጊዜ ተገልሎ እንዲቆይ ማድረግ አያስፈልገውም። 12 የሥጋ ደዌው በቆዳው ሁሉ ላይ ቢወጣና የሥጋ ደዌው ካህኑ ሊያየው እስከሚችለው ድረስ ግለሰቡን ከራሱ አንስቶ እስከ እግሮቹ ድረስ ቢያለብሰው 13 እንዲሁም ካህኑ ሲመረምረው የሥጋ ደዌው ቆዳውን ሁሉ አልብሶት ቢያይ ቁስሉ የወጣበት ግለሰብ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል። ቆዳው ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭነት ተለውጧል፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው። 14 ሆኖም በቆዳው ላይ አፉን የከፈተ ቁስል በወጣበት በማንኛውም ጊዜ ሰውየው ርኩስ ይሆናል። 15 ካህኑ አፉን የከፈተ ቁስል ካየ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። አፉን የከፈተው ቁስል ርኩስ ነው። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 16 ሆኖም አፉን የከፈተው ቁስል እንደገና ወደ ነጭነት ከተለወጠ ሰውየው ወደ ካህኑ ይመጣል። 17 ካህኑም ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ወደ ነጭነት ከተለወጠ ካህኑ ቁስሉ የወጣበት ግለሰብ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል። ሰውየው ንጹሕ ነው። 18 “አንድ ሰው በቆዳው ላይ እባጭ ቢወጣበትና ቢድን 19 ሆኖም እባጩ በነበረበት ቦታ ላይ ነጭ እብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቁቻ ቢወጣ ሰውየው ራሱን ለካህን ያሳይ። 20 ካህኑም ቁስሉን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነና በዚያ ቦታ ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ በእባጩ ላይ የወጣ የሥጋ ደዌ ነው። 21 ይሁንና ካህኑ ቁስሉን ሲመረምረው በላዩ ላይ ነጭ ፀጉር ከሌለና ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም እየከሰመ ከሆነ ካህኑ ሰውየውን ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል። 22 ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ ደዌ ነው። 23 ይሁን እንጂ ቋቁቻው ባለበት ከቆመና ካልተስፋፋ ይህ እባጩ ያስከተለው ቁስል ነው፤ ካህኑም ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል። 24 “ወይም አንድ ሰው እሳት አቃጥሎት በሰውነቱ ቆዳ ላይ ጠባሳ ቢተውና ጠባሳው ላይ ያለው ያልሻረ ቁስል ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቁቻ ቢሆን 25 ካህኑ ቁስሉን ይመረምረዋል። በቋቁቻው ላይ ያለው ፀጉር ወደ ነጭነት ከተለወጠና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ከሆነ ይህ በጠባሳው ላይ የወጣ የሥጋ ደዌ ነው፤ ካህኑም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 26 ይሁንና ካህኑ ሲመረምረው በቋቁቻው ላይ ነጭ ፀጉር ከሌለና ቁስሉ ከቆዳው ዘልቆ የገባ ካልሆነ እንዲሁም እየከሰመ ከሆነ ካህኑ ሰውየውን ለሰባት ቀን ተገልሎ እንዲቆይ ያደርገዋል። 27 ካህኑም በሰባተኛው ቀን ሰውየውን ይመረምረዋል፤ ቁስሉ በቆዳው ላይ እየተስፋፋ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቃል። ይህ የሥጋ ደዌ ነው። 28 ይሁንና ቋቁቻው ባለበት ከቆመና በቆዳው ላይ ካልተስፋፋ እንዲሁም ከከሰመ ይህ ጠባሳው ያስከተለው እብጠት ነው፤ ይህ የጠባሳው ቁስል ስለሆነ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል።
ከታኅሣሥ 21-27
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 14–15
“ለይሖዋ የምናቀርበው አምልኮ ንጹሕ መሆንን ይጠይቃል”
(ዘሌዋውያን 15:13-15) “‘እንግዲህ ፈሳሹ ቢቆምና ሰውየው ከፈሳሹ ቢነጻ ንጹሕ ለመሆን ሰባት ቀን ይቁጠር፤ ልብሶቹን ይጠብ፤ ገላውንም በምንጭ ውኃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 14 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ይውሰድ፤ እነዚህንም ይዞ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ። 15 ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ ያቀርባቸዋል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሹ ለሰውየው በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።
it-1 263
መታጠብ
እስራኤላውያን የመንጻት ሥርዓት ለመፈጸም ሲሉ ሰውነታቸውን መታጠብ ይጠበቅባቸው ነበር፤ እንዲህ ማድረግ የሚጠይቁ የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ። ራሱን ከሥጋ ደዌ የሚያነጻ ወይም “ፈሳሽ የሚወጣው ሰው” የነካቸውን ነገሮች የነካ ሰው፣ ዘር የሚፈሰው ወንድ፣ የወር አበባ የታያት ወይም ደም የሚፈሳት ሴት አሊያም የፆታ ግንኙነት የፈጸመ ማንኛውም ሰው “ርኩስ” ተደርጎ ስለሚቆጠር ገላውን መታጠብ ነበረበት። (ዘሌ 14:8, 9፤ 15:4-27) የሰው አስከሬን ወደተቀመጠበት ድንኳን የገባ ወይም አስከሬኑን የነካ ሰው “ርኩስ” ተደርጎ ይቆጠራል፤ ስለዚህ በሚያነጻ ውኃ መንጻት ያስፈልገው ነበር። ይህን ደንብ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው “የይሖዋን መቅደስ ስላረከሰ . . . ከጉባኤው መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ መደረግ” ነበረበት። (ዘኁ 19:20) ከዚህ አንጻር መታጠብ፣ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም ማግኘትን ለማመልከት የተሠራበት መሆኑ ተገቢ ነው። (መዝ 26:6፤ 73:13፤ ኢሳ 1:16፤ ሕዝ 16:9) በውኃ በተመሰለው የእውነት ቃል መታጠብ የማንጻት ኃይል አለው።—ኤፌ 5:26
(ዘሌዋውያን 15:28-30) “‘ይሁን እንጂ ይፈሳት ከነበረው ፈሳሽ በምትነጻበት ጊዜ ለራሷ ሰባት ቀን ትቆጥራለች፤ ከዚያ በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። 29 በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ትውሰድ፤ እነዚህንም በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ወዳለው ወደ ካህኑ ታመጣቸዋለች። 30 ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ ለሚቃጠል መባ ያደርገዋል፤ ካህኑም የሚፈሳትን ርኩስ ፈሳሽ አስመልክቶ ለሴትየዋ በይሖዋ ፊት ያስተሰርይላታል።
it-2 372 አን. 2
የወር አበባ
በተጨማሪም አንዲት ሴት የወር አበባዋ ከሚመጣበት ከተለመደው ጊዜ ውጭ ደም ቢፈሳት ወይም “በወር አበባዋ ወቅት ከወትሮው ረዘም ላለ ጊዜ ደም ቢፈሳት” ርኩስ ትሆናለች፤ በዚህ ወቅት የተኛችባቸው ወይም የተቀመጠችባቸው ነገሮች እንዲሁም እነዚህን ነገሮች የነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል። ከተለመደው ውጭ የሚፈሳት ደም ከቆመበት ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ትቆጥራለች፤ ከዚያ በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። በስምንተኛው ቀን ሴትየዋ ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን ይዛ ወደ ካህኑ ትሄዳለች፤ ካህኑም አንዱን የኃጢአት መባ ሌላኛውን ደግሞ የሚቃጠል መባ አድርጎ ለይሖዋ በማቅረብ ያስተሰርይላታል።—ዘሌ 15:19-30
(ዘሌዋውያን 15:31) “‘በመካከላቸው ያለውን የማደሪያ ድንኳኔን በማርከስ በርኩሰታቸው እንዳይሞቱ በዚህ መንገድ እስራኤላውያንን ከርኩሰታቸው ለዩአቸው።
it-1 1133
ቅዱስ ስፍራ
2. የመገናኛ ድንኳኑ እና በኋላ ቤተ መቅደሱ። የማደሪያ ድንኳኑን ግቢና የቤተ መቅደሱን ግቢ ጨምሮ አምልኮ የሚካሄድበት ቦታ በአጠቃላይ ቅዱስ ስፍራ ነው። (ዘፀ 38:24፤ 2ዜና 29:5፤ ሥራ 21:28) በዋነኝነት ግቢው ውስጥ የሚገኙት መሠዊያውና የመዳብ ገንዳው ናቸው። እነዚህ ቅዱስ ነገሮች ናቸው። በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ግቢ መግባት የሚችሉት በሥርዓቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፤ በተመሳሳይም ንጹሕ ያልሆነ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ መግባት አይችልም። ለምሳሌ ያህል፣ ንጹሕ ያልሆነች ሴት ቅዱስ የሆነን ማንኛውም ነገር መንካት ወይም ወደ ቅዱሱ ስፍራ መግባት አትችልም። (ዘሌ 12:2-4) ሌላው ቀርቶ እስራኤላውያን ለተወሰነ ጊዜ ቅድስናቸውን አለመጠበቃቸው የማደሪያ ድንኳኑን እንዳረከሰው ተቆጥሯል። (ዘሌ 15:31) ከሥጋ ደዌ ለመንጻት መባ የሚያቀርቡ ሰዎች፣ መሥዋዕታቸውን ይዘው መምጣት የሚችሉት እስከ መገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ድረስ ብቻ ነበር። (ዘሌ 14:11) ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በማደሪያ ድንኳኑ ወይም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከሚቀርበው የኅብረት መሥዋዕት መብላት አይችልም፤ ይህን ማድረግ በሞት ያስቀጣ ነበር።—ዘሌ 7:20, 21
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 14:14) “ካህኑም ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ይወስዳል፤ ከዚያም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል።
(ዘሌዋውያን 14:17) በእጁም መዳፍ ላይ ከቀረው ዘይት ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል፤ በበደል መባው ደም ላይ ደርቦ ይቀባዋል።
(ዘሌዋውያን 14:25) ከዚያም ለበደል መባ እንዲሆን የቀረበውን የበግ ጠቦት ያርዳል፤ ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል።
(ዘሌዋውያን 14:28) በእጁ መዳፍ ላይ ካለው ዘይት የተወሰነውን ወስዶ የበደል መባውን ደም በቀባበት ቦታ ላይ ማለትም ራሱን በሚያነጻው ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ በቀኝ እጁ አውራ ጣት እንዲሁም በቀኝ እግሩ አውራ ጣት ላይ ይቀባል።
it-1 665 አን. 5
ጆሮ
በእስራኤል የክህነት ሹመት ሥርዓት በተካሄደበት ወቅት ሙሴ ለክህነት ሹመት ሥርዓት የሚቀርበውን አውራ በግ ደም ወስዶ የአሮንንና የልጆቹን የቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጅ አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግር አውራ ጣት እንዲቀባ ታዝዞ ነበር፤ ይህም የሚሰሙት ነገር፣ የሚሠሩት ሥራ እንዲሁም አካሄዳቸው በዚያ ከሚከናወነው ነገር ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበት የሚጠቁም ነበር። (ዘሌ 8:22-24) ራሱን ከሥጋ ደዌ ከሚያነጻ ሰው ጋር በተያያዘም ካህኑ ለበደል መባ ከቀረበው አውራ በግ ደም እንዲሁም ከዘይቱ ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ እንዲቀባ ሕጉ ያዝዝ ነበር። (ዘሌ 14:14, 17, 25, 28) ለጌታው ዕድሜ ልኩን ባሪያ ሆኖ ለመኖር ከሚፈልግ ሰው ጋር በተያያዘ የሚከናወነው ሥርዓትም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር አለው። በዚህ ሥርዓት መሠረት ጌታው ባሪያውን ወደ በሩ መቃን አምጥቶ ጆሮውን በወስፌ ይበሳዋል። ለመስማት በሚያገለግለው የአካል ክፍል ላይ ይህ ጉልህ ምልክት መደረጉ ባሪያው ጌታው የሚለውን እየታዘዘ ለመኖር ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም።—ዘፀ 21:5, 6
(ዘሌዋውያን 14:43-45) “ድንጋዮቹ ተሰርስረው ከወጡና ቤቱ ተፈቅፍቆ ዳግመኛ ከተለሰነ በኋላ ብክለቱ እንደገና ተመልሶ በቤቱ ላይ ከታየ 44 ካህኑ ገብቶ ይመረምረዋል። ብክለቱ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከሆነ ይህ በቤቱ ላይ የወጣ አደገኛ ደዌ ነው። ቤቱ ርኩስ ነው። 45 ቤቱ ይኸውም ድንጋዮቹ፣ እንጨቶቹ፣ ልስኑና ምርጊቱ እንዲፈርስ ያደርጋል፤ ከከተማዋ ውጭ በሚገኝ ርኩስ የሆነ ስፍራም እንዲጣል ያደርጋል።
g 1/06 14 ሣጥን
ወዳጃችንም ጠላታችንም የሆነው ሻጋታ!
ሻጋታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል?
መጽሐፍ ቅዱስ “የለምጽ ደዌ . . . በአንድ ቤት” ማለትም በሕንፃው ላይ ስለመኖሩ ይጠቅሳል። (ዘሌዋውያን 14:34-48 የ1954 ትርጉም) ይህ ደዌ “እየፋገ የሚሄድ ለምጽ” ተብሎም የተጠራ ሲሆን አንድ ዓይነት ሻጋታ ሊሆን እንደሚችል ሐሳብ ተሰንዝሯል፤ ሆኖም ይህን ሐሳብ በተመለከተ ጥርጣሬዎች አሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን የአምላክ ሕግ የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡ፣ በውስጥ በኩል ያለው የቤቱ ግድግዳ በሙሉ እንዲፋቅና እንደተበከለ የሚጠረጠረውን ነገር በሙሉ ከከተማው ውጭ ባለ ‘ርኩስ ስፍራ’ እንዲጥሉት ያዝዝ ነበር። ከዚህም በኋላ ይህ ደዌ እንደገና ከታየ ቤቱ እንዳለ እንደ ርኩስ ተቆጥሮ ይፈርስና ቁሳቁሶቹ ይጣላሉ። ይሖዋ የሰጠው ዝርዝር መመሪያ ለሕዝቡ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ስለ ደኅንነታቸው የሚያስብ መሆኑን ያሳያል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 14:1-18) ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “የሥጋ ደዌ ያለበት አንድ ሰው መንጻቱን ለማረጋገጥ ካህኑ ፊት እንዲቀርብ በሚደረግበት ዕለት የሚኖረው ሕግ ይህ ነው። 3 ካህኑ ከሰፈሩ ውጭ ወጥቶ ሰውየውን ይመረምረዋል። የሥጋ ደዌ ይዞት የነበረው ሰው ከሥጋ ደዌው ከዳነ 4 ካህኑ ሰውየው ራሱን ለማንጻት በሕይወት ያሉ ሁለት ንጹሕ ወፎችን፣ የአርዘ ሊባኖስ እንጨት፣ ደማቅ ቀይ ማግና ሂሶጵ እንዲያመጣ ያዘዋል። 5 እንዲሁም ካህኑ አንደኛዋ ወፍ ከወራጅ ውኃ የተቀዳ ውኃ ባለበት የሸክላ ዕቃ ውስጥ እንድትታረድ ትእዛዝ ይሰጣል። 6 በሕይወት ያለችውን ወፍ ደግሞ ከአርዘ ሊባኖስ እንጨቱ፣ ከደማቁ ቀይ ማግና ከሂሶጱ ጋር ወስዶ ከወራጅ ውኃ በተቀዳው ውኃ ላይ በታረደችው ወፍ ደም ውስጥ ይንከራቸው። 7 ከዚያም ራሱን ከሥጋ ደዌ በሚያነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል፤ ሰውየውም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቃል፤ በሕይወት ያለችውንም ወፍ ሜዳ ላይ ይለቃታል። 8 “ራሱን የሚያነጻውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ፤ ፀጉሩንም በሙሉ ይላጭ፤ ገላውንም በውኃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። ይህን ካደረገ በኋላ ወደ ሰፈሩ መግባት ይችላል፤ ሆኖም ለሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቀመጣል። 9 በሰባተኛው ቀን በራሱ ላይ ያለውን ፀጉር፣ ጺሙንና ቅንድቡን በሙሉ ይላጭ። ፀጉሩን በሙሉ ከተላጨ በኋላ ልብሶቹን ያጥባል እንዲሁም ገላውን በውኃ ይታጠባል፤ ከዚያም ንጹሕ ይሆናል። 10 “በስምንተኛው ቀን እንከን የሌለባቸውን ሁለት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ዓመት ገደማ የሆናትን እንከን የሌለባት አንዲት እንስት የበግ ጠቦት፣ የእህል መባ እንዲሆን በዘይት የተለወሰ ሦስት አሥረኛ ኢፍ የላመ ዱቄትና አንድ የሎግ መስፈሪያ ዘይት ያመጣል፤ 11 ሰውየው ንጹሕ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህንም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ከመባዎቹ ጋር በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት ያቀርበዋል። 12 ካህኑም አንደኛውን የበግ ጠቦት ወስዶ ከአንዱ የሎግ መስፈሪያ ዘይት ጋር በማድረግ የበደል መባ እንዲሆን ያቀርበዋል፤ እነዚህንም የሚወዘወዝ መባ አድርጎ በይሖዋ ፊት ወዲያና ወዲህ ይወዘውዛቸዋል። 13 ከዚያም የበግ ጠቦቱን የኃጢአት መባውና የሚቃጠል መባው ዘወትር በሚታረዱበት ቦታ ይኸውም ቅዱስ በሆነ ስፍራ ያርደዋል፤ ምክንያቱም እንደ ኃጢአት መባው ሁሉ የበደል መባውም የካህኑ ድርሻ ነው። ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው። 14 “ካህኑም ከበደል መባው ደም ላይ የተወሰነውን ይወስዳል፤ ከዚያም ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል። 15 ካህኑም ከአንዱ የሎግ መስፈሪያ ዘይት ላይ የተወሰነውን በራሱ የግራ እጅ መዳፍ ላይ ያንቆረቁረዋል። 16 ከዚያም የቀኝ እጁን ጣት በግራ እጁ መዳፍ ላይ ባለው ዘይት ውስጥ ይነክራል፤ ከዘይቱም የተወሰነውን በይሖዋ ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጨዋል። 17 በእጁም መዳፍ ላይ ከቀረው ዘይት ላይ የተወሰነውን ወስዶ ራሱን የሚያነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣት እንዲሁም የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ይቀባል፤ በበደል መባው ደም ላይ ደርቦ ይቀባዋል። 18 ካህኑም በእጁ መዳፍ ላይ የቀረውን ዘይት ራሱን በሚያነጻው ሰው ራስ ላይ ያፈሰዋል፤ ለሰውየውም በይሖዋ ፊት ያስተሰርይለታል።
ከታኅሣሥ 28–ጥር 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘሌዋውያን 16–17
“የስርየት ቀን ለአንተ ምን ትርጉም አለው?”
(ዘሌዋውያን 16:12) “በይሖዋ ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የተወሰደ ፍም የሞላበትን ዕጣን ማጨሻና ሁለት እፍኝ ሙሉ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን ይወስዳል፤ እነዚህንም ይዞ ወደ መጋረጃው ውስጥ ይገባል።
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
4 ዘሌዋውያን 16:12, 13ን አንብብ። በስርየት ቀን የሚከናወነውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፦ ሊቀ ካህናቱ ወደ ማደሪያው ድንኳን ይገባል። ሊቀ ካህናቱ በዚህ ዕለት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ሦስት ጊዜ የሚገባ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገባው በዚህ ወቅት ነው። በአንድ እጁ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን፣ በሌላኛው እጁ ደግሞ ፍም የሞላበትን ከወርቅ የተሠራ ዕጣን ማጨሻ ይይዛል። የቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ጋ ሲደርስ ቆም ይላል። ከዚያም በጥልቅ አክብሮት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ከገባ በኋላ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ይቆማል። በምሳሌያዊ ሁኔታ በይሖዋ አምላክ ፊት የቆመ ያህል ነው! ቀጥሎም ቅዱሱን ዕጣን በጥንቃቄ ፍሙ ላይ ይጨምረዋል፤ በዚህ ጊዜ ክፍሉ ደስ በሚል መዓዛ ይታወዳል። በኋላ ላይ፣ ሊቀ ካህናቱ የኃጢአት መባውን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ተመልሶ ይገባል። ሊቀ ካህናቱ ዕጣኑን የሚያጨሰው የኃጢአት መባውን ደም ከማቅረቡ በፊት እንደሆነ ልብ በል።
(ዘሌዋውያን 16:13) እንዳይሞትም ዕጣኑን በይሖዋ ፊት ባለው እሳት ላይ ይጨምረዋል፤ የዕጣኑም ጭስ ከምሥክሩ በላይ ያለውን የታቦቱን መክደኛ ይሸፍነዋል።
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
5 በስርየት ቀን ዕጣን የሚጨስ መሆኑ ምን ያስተምረናል? መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚያቀርቡት ጸሎት እንደ ዕጣን እንደሆነ ይገልጻል። (መዝ. 141:2፤ ራእይ 5:8) ሊቀ ካህናቱ፣ ዕጣኑን ይዞ ወደ ይሖዋ ፊት የሚገባው በታላቅ አክብሮት እንደሆነ እናስታውስ። እኛም በተመሳሳይ በጸሎት ወደ ይሖዋ የምንቀርበው በጥልቅ አክብሮት ሊሆን ይገባል። የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ፣ አንድ ልጅ አባቱን የሚቀርበውን ያህል ወደ እሱ እንድንቀርብና በጸሎት እንድናነጋግረው ስለፈቀደልን በጣም አመስጋኝ ነን። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከተናል! (መዝ. 25:14) ይህን መብት በጣም ከፍ አድርገን ስለምንመለከተው ፈጽሞ እሱን ማሳዘን አንፈልግም።
(ዘሌዋውያን 16:14, 15) “ከወይፈኑም ደም የተወሰነውን ወስዶ ከመክደኛው ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ በኩል በጣቱ ይረጨዋል፤ የተወሰነውን ደም ደግሞ ከመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 15 “ከዚያም ለሕዝቡ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ፍየል ያርደዋል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ በመግባት ልክ በወይፈኑ ደም እንዳደረገው በዚህኛውም ደም ያደርጋል፤ ደሙንም ወደ መክደኛውና በመክደኛው ፊት ይረጨዋል።
ከዘሌዋውያን መጽሐፍ የምናገኛቸው ትምህርቶች
6 ሊቀ ካህናቱ መሥዋዕቶቹን ከማቅረቡ በፊት ዕጣኑን ማጨስ እንደነበረበት እናስታውስ። ይህን ማድረጉ፣ መሥዋዕቱን ከማቅረቡ በፊት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ያስችለዋል። ከዚህ ምን እንማራለን? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረቡ በፊት ሊያከናውነው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር፤ ይህም ለሰው ልጆች መዳን ከማስገኘት ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ታዲያ ሊያከናውነው የሚገባው ነገር ምን ነበር? በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት በሙሉ ንጹሕ አቋሙን መጠበቅና በታማኝነት መመላለስ ነበረበት፤ የሚያቀርበው መሥዋዕት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው እንዲህ ካደረገ ነው። ኢየሱስ ይህን በማድረግ፣ ሕይወታችንን ልንመራበት የሚገባው ትክክለኛው አካሄድ የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል እንደሆነ አሳይቷል። ኢየሱስ፣ የአባቱ ሉዓላዊነት ማለትም አገዛዙ ትክክለኛና ፍትሐዊ መሆኑን አረጋግጧል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘሌዋውያን 16:10) ለአዛዜል እንዲሆን ዕጣ የወጣበት ፍየል ግን በእሱ አማካኝነት ስርየት እንዲፈጸምበት ከነሕይወቱ መጥቶ በይሖዋ ፊት እንዲቆም ይደረግ፤ ከዚያም ለአዛዜል እንዲሆን ወደ ምድረ በዳ ይለቀቃል።
it-1 226 አን. 3
አዛዜል
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳብራራው ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሲል ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም” ሊያስገኝ ከሚችለው እጅግ የላቀ ነገር አስገኝቷል። (ዕብ 10:4, 11, 12) ከዚህ አንጻር ‘ስለ መተላለፋችን የተወጋው’ ኢየሱስ ‘ሕመማችንን የተሸከመ’ የአዛዜል ፍየል ሆኖልናል። (ኢሳ 53:4, 5፤ ማቴ 8:17፤ 1ጴጥ 2:24) በቤዛዊ መሥዋዕቱ የሚያምኑ ሰዎችን ኃጢአት በሙሉ ‘ተሸክሞ’ ሄዷል። ይሖዋ ኃጢአታችንን እስከ ወዲያኛው ከእኛ ለማራቅ ያደረገው ዝግጅት እውን የሆነው በኢየሱስ አማካኝነት ነው። በዚህ መንገድ ‘የአዛዜል’ ፍየል ለኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ምሳሌ ይሆናል።
(ዘሌዋውያን 17:10, 11) “‘ከእስራኤል ቤት የሆነ ማንኛውም ሰው ወይም በመካከላችሁ የሚኖር የትኛውም የባዕድ አገር ሰው ምንም ዓይነት ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው ሰው ላይ በእርግጥ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 11 ምክንያቱም የሥጋ ሕይወት ያለው በደሙ ውስጥ ነው፤ ለራሳችሁም ማስተሰረያ እንዲሆን እኔ ራሴ ደሙን ለእናንተ ስል ለመሠዊያው ሰጥቼዋለሁ፤ ምክንያቱም በውስጡ ባለው ሕይወት አማካኝነት የሚያስተሰርየው ደሙ ነው።
ቅዱስ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
10 ዘሌዋውያን 17:10, 14ን አንብብ። እስራኤላውያን “የማንኛውንም ፍጡር ደም” እንዳይበሉ ይሖዋ አዟቸው ነበር። ክርስቲያኖችም ቢሆኑ የእንስሳም ሆነ የሰው ደም ከመጠቀም መራቅ ይኖርባቸዋል። (ሥራ 15:28, 29) አምላክ ፊቱን እንደሚያከብድብንና ከጉባኤው እንደሚያስወግደን ማሰቡ እንኳ ያስፈራናል። ይሖዋን ስለምንወደው እሱን መታዘዝ እንፈልጋለን። ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ቢያጋጥመንም እንኳ ይሖዋን የማያውቁና የእሱን ሕጎች መታዘዝ የማይፈልጉ ሰዎች በሚያሳድሩብን ተጽዕኖ ላለመሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። ከደም በመራቃችን ሌሎች ሊያፌዙብን እንደሚችሉ ብናውቅም አምላክን ለመታዘዝ መርጠናል። (ይሁዳ 17, 18) ታዲያ ደምን እንዳንበላ ወይም እንዳንወስድ ‘ለመጠንቀቅ’ ያደረግነውን ውሳኔ የሚያጠናክርልን ምን ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ነው?—ዘዳ. 12:23
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘሌዋውያን 16:1-17) ሁለቱ የአሮን ወንዶች ልጆች ይሖዋ ፊት በመቅረባቸው የተነሳ ከሞቱ በኋላ ይሖዋ ሙሴን አነጋገረው። 2 ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “እኔ ከመክደኛው በላይ በደመና ውስጥ ስለምገለጥ በመጋረጃው ውስጥ ወዳለው ቅዱስ ስፍራ ይኸውም በታቦቱ ላይ ወዳለው መክደኛ ፊት በፈለገው ጊዜ እንዳይገባና በዚህም የተነሳ እንዳይሞት ለወንድምህ ለአሮን ንገረው። 3 “አሮን ወደተቀደሰው ስፍራ በሚገባበት ጊዜ ለኃጢአት መባ የሚሆን አንድ ወይፈንና ለሚቃጠል መባ የሚሆን አንድ አውራ በግ ይዞ ይምጣ። 4 ቅዱሱን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፤ በበፍታ ቁምጣዎቹም ሰውነቱን ይሸፍን፤ የበፍታ መቀነቱንም ይታጠቅ፤ ራሱም ላይ የበፍታ ጥምጥሙን ይጠምጥም። እነዚህ ቅዱስ ልብሶች ናቸው። እሱም ገላውን በውኃ ታጥቦ ይለብሳቸዋል። 5 “ከእስራኤል ማኅበረሰብም ሁለት ተባዕት የፍየል ጠቦቶችን ለኃጢአት መባ፣ አንድ አውራ በግ ደግሞ ለሚቃጠል መባ ይውሰድ። 6 “ከዚያም አሮን ለራሱ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ፤ ለራሱም ሆነ ለቤቱ ያስተሰርያል። 7 “ሁለቱን ፍየሎች ወስዶ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ በይሖዋ ፊት እንዲቆሙ ያደርጋል። 8 አሮንም በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጥላል፤ አንደኛው ዕጣ ለይሖዋ ሌላኛው ዕጣ ደግሞ ለአዛዜል ይሆናል። 9 አሮንም ለይሖዋ እንዲሆን ዕጣ የወጣበትን ፍየል ያቀርባል፤ የኃጢአትም መባ ያደርገዋል። 10 ለአዛዜል እንዲሆን ዕጣ የወጣበት ፍየል ግን በእሱ አማካኝነት ስርየት እንዲፈጸምበት ከነሕይወቱ መጥቶ በይሖዋ ፊት እንዲቆም ይደረግ፤ ከዚያም ለአዛዜል እንዲሆን ወደ ምድረ በዳ ይለቀቃል። 11 “አሮንም ለራሱ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ወይፈን ያቀርባል፤ ለራሱም ሆነ ለቤቱ ያስተሰርያል፤ ከዚያም ለራሱ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ወይፈን ያርዳል። 12 “በይሖዋ ፊት ካለው መሠዊያ ላይ የተወሰደ ፍም የሞላበትን ዕጣን ማጨሻና ሁለት እፍኝ ሙሉ ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን ይወስዳል፤ እነዚህንም ይዞ ወደ መጋረጃው ውስጥ ይገባል። 13 እንዳይሞትም ዕጣኑን በይሖዋ ፊት ባለው እሳት ላይ ይጨምረዋል፤ የዕጣኑም ጭስ ከምሥክሩ በላይ ያለውን የታቦቱን መክደኛ ይሸፍነዋል። 14 “ከወይፈኑም ደም የተወሰነውን ወስዶ ከመክደኛው ፊት ለፊት በስተ ምሥራቅ በኩል በጣቱ ይረጨዋል፤ የተወሰነውን ደም ደግሞ ከመክደኛው ፊት በጣቱ ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 15 “ከዚያም ለሕዝቡ የኃጢአት መባ የሚሆነውን ፍየል ያርደዋል፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ በመግባት ልክ በወይፈኑ ደም እንዳደረገው በዚህኛውም ደም ያደርጋል፤ ደሙንም ወደ መክደኛውና በመክደኛው ፊት ይረጨዋል። 16 “እስራኤላውያን ስለፈጸሙት ርኩሰት፣ ስለ መተላለፋቸውና ስለ ኃጢአታቸው ለቅዱሱ ስፍራ ያስተሰርይ፤ በእነሱ ዘንድ በርኩሰታቸው መካከል ለሚገኘው ለመገናኛ ድንኳኑም ይህንኑ ያድርግ። 17 “ለማስተሰረይ ወደ ቅዱሱ ስፍራ ገብቶ እስኪወጣ ድረስ ሌላ ማንም ሰው በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ መገኘት የለበትም። እሱም ለራሱ፣ ለቤቱና ለመላው የእስራኤል ጉባኤ ያስተሰርያል።