የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 26—ሕዝቅኤል
ጸሐፊው:- ሕዝቅኤል
የተጻፈበት ቦታ:- ባቢሎን
ተጽፎ ያለቀው:- 591 ከክ. ል. በፊት ገደማ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ613 ከክ. ል. በፊት እስከ 591 ከክ. ል. በፊት ገደማ
በ617 ከክርስቶስ ልደት በፊት የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን ኢየሩሳሌምን ለናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጠ። ናቡከደነፆርም በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸውን ሰዎች እንዲሁም በይሖዋ ቤትና በንጉሡ ቤት የነበሩትን ንብረቶች ወደ ባቢሎን አጋዘ። ከምርኮኞቹ መካከል የንጉሡ ቤተሰብና መሳፍንቱ፣ የጦር አለቆቹ፣ ተዋጊዎቹ፣ የእጅ ባለሙያዎችና ግንበኞች እንዲሁም የቡዝ ልጅ ካህኑ ሕዝቅኤል ይገኙበት ነበር። (2 ነገ. 24:11-17፤ ሕዝ. 1:1-3) ልባቸው በሐዘን የተሰበረው እነዚህ እስራኤላውያን ምርኮኞች ተራራማ ከሆነው፣ ምንጮች ከሞሉበትና ሸለቆዎች ካሉበት ምድራቸው ተነስተው አድካሚ ጉዞ በማድረግ ሜዳማ ወደሆነው መድረሻቸው ደረሱ። ከዚያም በኮቦር ወንዝ አጠገብ በአንድ ኃያል መንግሥት ሥር፣ እንግዳ ባህል ባላቸውና አረማዊ አምልኮ በሚያከናውኑ ሰዎች መካከል መኖር ጀመሩ። ናቡከደነፆር፣ እስራኤላውያኑ የራሳቸው ቤቶችና አገልጋዮች እንዲኖሯቸው እንዲሁም የራሳቸውን ሥራ እንዲያከናውኑ ፈቅዶላቸው ነበር። (ሕዝ. 8:1፤ ኤር. 29:5-7፤ ዕዝራ 2:65) ታታሪ ከሆኑ ሊበለጽጉ ይችሉ ነበር። እስራኤላውያን የባቢሎናውያንን ሃይማኖት ይከተሉ ወይም በፍቅረ ነዋይ ወጥመድ ይወድቁ ይሆን? በይሖዋ ላይ ማመፃቸውን ይገፉበት ይሆን? በምርኮ የተወሰዱት ይሖዋ ስለቀጣቸው መሆኑን ይገነዘቡ ይሆን? በግዞት በሚኖሩበት አገር ውስጥ አዳዲስ ፈተናዎች ይጠብቋቸው ነበር።
2 ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት አስቸጋሪ ዓመታት ይሖዋ ነቢያቶቹን ወደ እነርሱ መላኩን አላቋረጠም። ኤርምያስ እዚያው ኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፣ ዳንኤል በባቢሎን ቤተ መንግሥት የነበረ ሲሆን ሕዝቅኤል ደግሞ ባቢሎን ውስጥ በግዞት በነበሩት አይሁዶች መካከል ነቢይ ሆኖ ያገለግል ነበር። ሕዝቅኤል እንደ ኤርምያስ ካህንና ነቢይ የነበረ ሲሆን ዘካርያስም ከጊዜ በኋላ በነቢይነትና በካህንነት አገልግሏል። (ሕዝ. 1:3) የሕዝቅኤልን ትንቢት ስናጠና ሕዝቅኤል ከ90 ጊዜ በላይ “የሰው ልጅ” ተብሎ መጠራቱን ልብ ልንለው ይገባል፤ ምክንያቱም ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ኢየሱስ 80 ጊዜ ያህል “የሰው ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሕዝ. 2:1፤ ማቴ. 8:20) ሕዝቅኤል (በዕብራይስጥ ዬቼዝቄል) የሚለው ስሙ “አምላክ ያጠነክራል” ማለት ነው። ሕዝቅኤል የነቢይነት ተልዕኮውን ከይሖዋ የተቀበለው ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት ማለትም በ613 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። በግዞት ባሳለፉት በ27ኛው ዓመት ማለትም በነቢይነት ማገልገል ከጀመረ ከ22 ዓመት በኋላም ሕዝቅኤል በሥራው ላይ እንደነበረ እናነባለን። (ሕዝ. 1:1, 2፤ 29:17) ሕዝቅኤል አግብቶ የነበረ ቢሆንም ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ለመጨረሻ ጊዜ መክበብ በጀመረበት ቀን ሚስቱ ሞታለች። (24:2, 18) ነቢዩ የሞተበት ቀንና እንዴት እንደሞተ አይታወቅም።
3 ሕዝቅኤል በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ መጻፉንና መጽሐፉ ተቀባይነት ያገኙት ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን በተመለከተ የተነሳ ውዝግብ የለም። መጽሐፉ በቅዱሳን ጽሑፎች ዝርዝር ውስጥ የተጨመረው በዕዝራ ዘመን ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘመን በነበሩት በተለይም ኦሪጀን ባዘጋጀው የቅዱሳን ጽሑፎች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል። በተጨማሪም መጽሐፉ የሚጠቀምባቸው ምሳሌያዊ አገላለጾች በኤርምያስና በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ካሉት ጋር በሚያስገርም ሁኔታ መመሳሰላቸው የመጽሐፉን ትክክለኛነት ያረጋግጣል።—ሕዝ. 24:2-12—ኤር. 1:13-15፤ ሕዝ. 23:1-49—ኤር. 3:6-11፤ ሕዝ. 18:2-4—ኤር. 31:29, 30፤ ሕዝ. 1:5, 10—ራእይ 4:6, 7፤ ሕዝ. 5:17—ራእይ 6:8፤ ሕዝ. 9:4—ራእይ 7:3፤ ሕዝ. 2:9፤ 3:1—ራእይ 10:2, 8-10፤ ሕዝ. 23:22, 25, 26—ራእይ 17:16፤ 18:8፤ ሕዝ. 27:30, 36—ራእይ 18:9, 17-19፤ ሕዝ. 37:27—ራእይ 21:3፤ ሕዝ. 48:30-34—ራእይ 21:12, 13፤ ሕዝ. 47:1, 7, 12—ራእይ 22:1, 2
4 የመጽሐፉን ትክክለኛነት የሚያረጋግጠው ሌላኛው ማስረጃ ሕዝቅኤል እንደ ጢሮስ፣ ግብፅና ኤዶም ባሉ አጎራባች አገሮች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች አስገራሚ ፍጻሜ ነው። ለምሳሌ ጢሮስ እንደምትጠፋ ሕዝቅኤል ተንብዮ ነበር፤ ናቡከደነፆር ከተማዋን ለ13 ዓመታት ከከበባት በኋላ ሲይዛት ትንቢቱ በከፊል ተፈጽሟል። (ሕዝ. 26:2-21) ጢሮስ በዚህ ጦርነት ሙሉ በሙሉ አልጠፋችም። ይሖዋ የፈረደው ግን ሙሉ በሙሉ መጥፋት እንደሚገባት ነው። ይሖዋ በሕዝቅኤል አማካኝነት እንዲህ በማለት ተንብዮ ነበር:- “ዐፈሯን ከላይዋ ጠርጌ የተራቈተ ዐለት አደርጋታለሁ። . . . ድንጋይሽን፣ ዕንጨትሽንና የግንቦች ፍርስራሽ ወደ ባሕር ይጥላሉ።” (26:4, 12) ታላቁ እስክንድር ከ250 ዓመታት በኋላ የደሴት ከተማ በሆነችው በጢሮስ ላይ በዘመተበት ጊዜ ይህ ሁሉ ተፈጽሟል። የእስክንድር ወታደሮች በየብስ ላይ የሚገኘውን የወደመውን ከተማ ፍርስራሽ ጠርገው ባሕሩ ውስጥ በመደልደል በደሴት ላይ ወደምትገኘው ከተማ የሚወስድ 800 ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ሠሩ። ከዚያም ውስብስብ የሆነ ከበባ በማድረግ 46 ሜትር ርዝመት ባለው አጥሯ ላይ ወጥተው ወደ ከተማዋ በመግባት በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተቆጣጠሯት። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ብዛት ያላቸው ደግሞ በባርነት ተሸጡ። ሕዝቅኤል እንደተነበየው ጢሮስ ‘የተራቈተ ዐለት እንዲሁም የመረብ ማስጫ ቦታ’ ሆናለች። (26:14)a ከተስፋይቱ ምድር በሌላኛው አቅጣጫ የሚገኙት ከዳተኞቹ ኤዶማውያንም ሕዝቅኤል በተነበየው መሠረት ተደመሰሱ። (25:12, 13፤ 35:2-9)b በተጨማሪም ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋትና ስለ እስራኤል ተመልሶ መቋቋም የተናገራቸው ትንቢቶች ትክክል መሆናቸው ተረጋግጧል።—17:12-21፤ 36:7-14
5 ሕዝቅኤል በነቢይነት ባገለገለባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አምላክ በከዳተኛይቱ ኢየሩሳሌም ላይ ጥፋት ማምጣቱ እንደማይቀር ከማወጁም በተጨማሪ ምርኮኞቹ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ አስጠንቅቋል። (14:1-8፤ 17:12-21) ምርኮኞቹ አይሁዳውያን እውነተኛ የንስሐ ምልክት አላሳዩም ነበር። በመካከላቸው ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሕዝቅኤልን ቢያማክሩትም ለሚነግራቸው ከይሖዋ የመጡ መልእክቶች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ነበር። በጣዖት አምልኳቸውና በፍቅረ ንዋይ ላይ ባተኮረ አኗኗራቸው ገፉበት። ቤተ መቅደሳቸውን፣ ቅድስቲቱ ከተማቸውንና ሥርወ መንግሥታቸውን ማጣታቸው በጣም የሚያስደነግጥ ቢሆንም ይህ ሁኔታ ራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉና ንስሐ እንዲገቡ ያደረጋቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ነበሩ።—መዝ. 137:1-9
6 ሕዝቅኤል በመጨረሻዎቹ ዓመታት የተናገራቸው ትንቢቶች ተመልሶ በመቋቋም ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በተጨማሪም የይሁዳ አጎራባች ብሔራት ይሁዳ በመውደቋ ምክንያት መደሰታቸውን ይነቅፋል። እነዚህ ብሔራት የደረሰባቸው ውርደት ከእስራኤል መልሶ መቋቋም ጋር ተዳምሮ ይሖዋ እንዲቀደስ አድርጓል። እስራኤላውያን በምርኮው የመወሰዳቸውና እንደገና የመቋቋማቸው ዓላማ በአጭሩ ‘አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ይሖዋን እንዲያውቁት’ ማድረግ ነው። (ሕዝ. 39:7, 22) የይሖዋ ስም መቀደስ በመጽሐፉ ውስጥ ጎላ ተደርጎ የተገለጸ ሲሆን “እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ [ወይም፣ ያውቃሉ]” የሚለው አባባል በመጽሐፉ ውስጥ ከ60 ጊዜ በላይ ይገኛል።—6:7 NW የግርጌ ማስታወሻ
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
29 ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ያሳየውን ራእይ እንዲሁም ለሕዝቡ እንዲናገር ያዘዘውን አዋጅና የገባውን ቃል በሙሉ በግዞት ለነበሩት አይሁዶች በታማኝነት ተናግሯል። ብዙዎች በነቢዩ ላይ ቢያላግጡና ቢዘብቱበትም አንዳንዶች ግን የነገራቸውን አምነዋል። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በጣም ተጠቅመዋል። ተመልሶ ስለመቋቋም በሚናገረው ቃል ተበረታትተው ነበር። ተማርከው ከተወሰዱት ሌሎች ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ በብሔር ደረጃ ማንነታቸውን ጠብቀው የኖሩ ሲሆን ይሖዋም አስቀድሞ እንደተናገረው በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቀሪዎቹን እስራኤላውያን መልሶ አቋቁሟቸዋል። (ሕዝ. 28:25, 26፤ 39:21-28፤ ዕዝራ 2:1፤ 3:1) እነርሱም የይሖዋን ቤት አድሰው እውነተኛውን አምልኮ እንደገና አቋቋመዋል።
30 በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ የተዘረዘሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች ዛሬም ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው። ክህደት፣ የጣዖት አምልኮና ዓመጽ በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ሊያሳጣን ይችላል። (ሕዝ. 6:1-7፤ 12:2-4, 11-16) እያንዳንዱ ሰው ለሠራው ኃጢአት ተጠያቂ ቢሆንም ይሖዋ ከመጥፎ መንገዳቸው የሚመለሱ ሰዎችን ይቅር ይላል። እንደዚህ የሚያደርግ ሰው ምሕረት ከማግኘቱም በላይ በሕይወት ይቀጥላል። (18:20-22) የአምላክ አገልጋዮች በአስቸጋሪ የአገልግሎት ምድቦች ሲያገለግሉ እንዲሁም ሰዎች ሲያሾፉባቸውና ሲቃወሟቸውም ጭምር እንደ ሕዝቅኤል ታማኝ ጠባቂ መሆን አለባቸው። በኃጢአተኞች ደም እንዳንጠየቅ ከመሞታቸው በፊት ማስጠንቀቂያውን መንገር አለብን። (3:17፤ 33:1-9) የአምላክ ሕዝብ እረኞች መንጋውን የመንከባከብ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።—34:2-10
31 ስለ መሲሑ የሚናገሩት ትንቢቶች በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ ጎላ ብለው ይታያሉ። መሲሑ በዳዊት ዙፋን ላይ ለመቀመጥ “የሚገባው ባለ መብት” እንደሆነና ዙፋኑ ለእርሱ መሰጠት እንዳለበት ተገልጿል። መሲሑ ሁለት ቦታዎች ላይ “ባሪያዬ ዳዊት” ተብሎ የተጠራ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ “እረኛ፣” ‘ንጉሥ’ እና “ገዥ” ተብሏል። (21:27 34:23, 24፤ 37:24, 25) ዳዊት ከሞተ ረጅም ጊዜ ስለሆነው ሕዝቅኤል እየተናገረ ያለው የዳዊት ልጅና ጌታ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ነው። (መዝ. 110:1፤ ማቴ. 22:42-45) ሕዝቅኤል ከኢሳይያስ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አንድ ቀንበጥ እንደተተከለና ይሖዋ ከፍ ከፍ እንደሚያደርገው ተናግሯል።—ሕዝ. 17:22-24፤ ኢሳ. 11:1-3
32 ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደስ የተመለከተውን ራእይ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለ “ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም” ከተገለጸው ራእይ ጋር ማወዳደሩ ጥሩ ነው። (ራእይ 21:10) በሁለቱ ራእዮች መካከል ልዩነቶች አሉ፤ ለምሳሌ ሕዝቅኤል የተመለከተው መቅደስ የሚገኘው ነጠል ብሎ በከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰችው ከተማ መቅደስ ግን ይሖዋ ራሱ ነው። ሆኖም ሁለቱም ስለሚፈስሰው የሕይወት ወንዝ፣ በየወሩ ስለሚያፈሩትና ቅጠሎቻቸው ለመፈወሻነት ስለሚያገለግሉት ዛፎች እንዲሁም የይሖዋ ክብር በዚያ ስለመኖሩ ተናግረዋል። ሁለቱም ራእዮች ለይሖዋ ንግሥና እንዲሁም ለእርሱ ቅዱስ አገልግሎት ለሚያቀርቡለት ሰዎች ላደረገው የመዳን ዝግጅት አድናቆት እንዲኖረን የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—ሕዝ. 43:4, 5—ራእይ 21:11፤ ሕዝ. 47:1, 8, 9, 12—ራእይ 22:1-3
33 የሕዝቅኤል መጽሐፍ ይሖዋ ቅዱስ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል። የይሖዋ ስም መቀደስ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ አንገብጋቢ መሆኑን ያስታውቃል። “የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ . . . አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]።” ትንቢቱ እንደሚያሳየው የማጎጉን ጎግ ጨምሮ ስሙን የሚያረክሱትን በጠቅላላ በማጥፋት ስሙን ይቀድሳል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ እርሱ የሚፈልግባቸውን ብቃቶች በማሟላት በአሁኑ ጊዜ በአኗኗራቸው ይሖዋን የሚቀድሱ ሰዎች ጥበበኞች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ መቅደስ በሚፈስሰው ወንዝ አማካኝነት ፈውስና የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። “እግዚአብሔር በዚያ አለ” ተብላ የምትጠራው ከተማ የላቀ ክብርና ፍጹም ውበት አላት!—ሕዝ. 36:23፤ 38:16፤ 48:35
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 531, 1136
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 681-682