ምዕራፍ አሥራ ሁለት
ከአምላክ ዘንድ የመጣ መልእክተኛ አበረታው
1. ዳንኤል ስለ ይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ለማወቅ ጉጉት በማሳደሩ የተባረከው እንዴት ነው?
ዳንኤል ስለ ይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ለማወቅ ጉጉት በማሳደሩ ተባርኳል። መሲሑ ስለሚገለጥበት ጊዜ የሚገልጸውን የ70 ሳምንቱን ስሜት ቀስቃሽ ትንቢት ሊናገር ችሏል። ከዚህም በላይ ዳንኤል የታመኑት የአገሩ ልጆች ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ለማየት በቅቷል። ይህ የሆነው ‘በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ የመጀመሪያ ዓመት’ ማለቂያ ላይ ማለትም በ537 ከዘአበ ነው።—ዕዝራ 1:1-4
2, 3. ዳንኤል ከአይሁዳውያን ቀሪዎች ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ያልተመለሰው ለምን ሊሆን ይችላል?
2 ዳንኤል ወደ ይሁዳ ምድር ከተመለሱት ሰዎች ጋር አብሮ አልተመለሰም። ከዕድሜው አንጻር ይህን ጉዞ ማድረጉ አስቸጋሪ ሊሆንበት ይችላል። ያም ሆነ ይህ አምላክ በዚያው በባቢሎን ውስጥ አንድ ሌላ አገልግሎት እንዲያከናውን ይፈልግ ነበር። በመሐል ሁለት ዓመታት ካለፉ በኋላ ዘገባው እንዲህ ይለናል:- “በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፤ ነገሩም እውነት ነበረ፣ እርሱም ታላቅ ጦርነት ነው፤ ነገሩንም አስተዋለ፣ በራእዩም ውስጥ ማስተዋል ተሰጠው።”—ዳንኤል 10:1
3 ‘ሦስተኛው የቂሮስ ዓመት’ ያረፈው 536/535 ከዘአበ ላይ ነው። ዳንኤል ከሌሎች የይሁዳ የንጉሣዊ ቤተሰብ ልጆችና የመኳንንት ልጆች ጋር ወደ ባቢሎን ከመጣ ከ80 የሚበልጡ ዓመታት አልፈዋል። (ዳንኤል 1:3) መጀመሪያ ወደ ባቢሎን ሲመጣ ዕድሜው በአሥራዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ እንኳ ቢሆን አሁን ወደ 100 ዓመት ተጠግቶታል ማለት ነው። ዳንኤል ያከናወነው እንዴት ያለ ግሩም የታማኝነት አገልግሎት ነው!
4. ዳንኤል ዕድሜው ቢገፋም በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ገና ምን ቁልፍ ሚና ነበረው?
4 ዳንኤል ዕድሜው ቢገፋም በይሖዋ አገልግሎት ገና የሚያበረክተው ትልቅ ድርሻ ነበረው። አምላክ በእርሱ አማካኝነት የሚያስነግረው ሰፊ ተፈጻሚነት ያለው አንድ ሌላ ትንቢታዊ መልእክት ነበር። ይህ እስከ ዘመናችን ድረስ የሚደርስና ከዚያም አልፎ የሚሄድ ትንቢት ነው። ይሖዋ ዳንኤልን ለዚህ ተጨማሪ ሥራ ለማዘጋጀት ሲል ከፊቱ ለሚጠብቀው አገልግሎት የሚያበረታው አንድ ነገር ሊያደርግለት አስቧል።
ዳንኤልን ያስጨነቀው ነገር
5. ዳንኤልን ያስጨነቁት ምን ሪፖርቶች ሊሆኑ ይችላሉ?
5 ዳንኤል ከአይሁዳውያን ቀሪዎች ጋር አብሮ ወደ ይሁዳ ምድር ባይመለስም በተወደደችው ትውልድ አገሩ የሚከናወነው ነገር ከልብ ያሳስበው ነበር። ዳንኤል በኢየሩሳሌም ያለው ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ ከደረሱት ሪፖርቶች ተረድቷል። በኢየሩሳሌም መሠዊያው እንደገና የተሠራ ሲሆን የቤተ መቅደሱም መሠረት ተጥሎ ነበር። (ዕዝራ ምዕራፍ 3) ይሁን እንጂ አጎራባቾቹ ብሔራት የመልሶ ግንባታውን ፕሮጄክት በመቃወም በተመለሱት አይሁዳውያን ላይ እያሴሩ ነበር። (ዕዝራ 4:1-5) በእርግጥም ዳንኤልን ሊያስጨንቁት የሚችሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ።
6. በኢየሩሳሌም ያለው ሁኔታ ዳንኤልን የረበሸው ለምን ነበር?
6 ዳንኤል የኤርምያስን ትንቢት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። (ዳንኤል 9:2) በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ እንደገና መገንባትም ሆነ የእውነተኛው አምልኮ ተመልሶ መቋቋም ይሖዋ ለሕዝቡ ካለው ዓላማ ጋር በቀጥታ የተቆራኙ ነገሮች መሆናቸውን እንዲሁም ይህ ሁሉ ከመሲሑ መምጣት በፊት እንደሚከናወን ያውቅ ነበር። እንዲያውም ዳንኤል ‘የሰባ ሳምንቱን’ ትንቢት ከይሖዋ የመቀበል ልዩ መብት አግኝቷል። በዚህ ትንቢት መሠረት መሲሑ የኢየሩሳሌም መጠገንና መሠራት ትእዛዝ ከወጣ በኋላ 69 ‘ሳምንት’ ቆይቶ እንደሚመጣ ተረድቷል። (ዳንኤል 9:24-27) ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም ከነበረችበት የባድማነት ሁኔታና ቤተ መቅደሷ ሳይገነባ ከመዘግየቱ አንጻር ሲታይ ዳንኤል ለምን እንዳዘነና እንደተከዘ መረዳት አያስቸግረንም።
7. ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ምን አደረገ?
7 ዘገባው እንዲህ ይላል:- “በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፣ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፣ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም።” (ዳንኤል 10:2, 3) “ሦስት ሳምንት ሙሉ” ወይም 21 ቀናት ማዘንና መጾም ቀላል አይደለም። ጾሙና ሐዘኑ ያበቃው ‘በመጀመሪያው ወር በሃያ አራተኛው ቀን’ ይመስላል። (ዳንኤል 10:4) በመሆኑም ዳንኤል የጾመበት ወቅት በመጀመሪያው የኒሳን ወር 14ኛ ቀን የሚከበረውን የማለፍ በዓልና ከዚያ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የሰባት ቀናት የቂጣ በዓል የሚጨምር ነበር።
8. ቀደም ሲል ዳንኤል የይሖዋን መመሪያ አጥብቆ የፈለገበት አጋጣሚ የትኛው ነው? ውጤቱስ ምን ነበር?
8 ዳንኤል ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ነገር ገጥሞታል። በዚያ ጊዜ ይሖዋ ስለ ኢየሩሳሌም የ70 ዓመት ባድማነት የተናገረውን ትንቢት ፍጻሜ በሚመለከት ግራ ተጋብቶ ነበር። ታዲያ ዳንኤል ምን አደረገ? “ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ” ብሏል። ይሖዋ መልአኩ ገብርኤልን በእጅጉ የሚያበረታታ መልእክት አስይዞ ወደ ዳንኤል በመላክ ለጸሎቱ ምላሽ ሰጥቶታል። (ዳንኤል 9:3, 21, 22) አሁንስ ለዳንኤል በጣም የሚያስፈልገውን ማበረታቻ በመስጠት ይሖዋ ተመሳሳይ ነገር ያደርግለት ይሆን?
አስፈሪ ራእይ
9, 10. (ሀ) ዳንኤል ራእዩ ሲመጣለት የት ነበር? (ለ) ዳንኤል በራእይ ያየው ነገር ምን እንደሆነ ግለጽ።
9 ዳንኤል በተስፋ መቁረጥ አልተዋጠም። ቀጥሎ ስለሆነው ነገር እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ጤግሮስ [“ሂዴኬል፣” NW] በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ሳለሁ፣ ዓይኔን አነሣሁ፣ እነሆም፣ በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ።” (ዳንኤል 10:4, 5) ሂዴኬል ከኤደን ገነት ይወጡ ከነበሩት አራት ወንዞች መካከል አንዱ ነው። (ዘፍጥረት 2:10-14) በጥንቷ ፋርስ ሂዴኬል የሚታወቀው ጤግራ በመባል ሲሆን ጤግሮስ ከሚለው የግሪክኛ ስም የተገኘ ነው። በሂዴኬልና በኤፍራጥስ ወንዝ መካከል ያለው ቦታ መሶጴጣሚያ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙም “በሁለት ወንዞች መካከል ያለ ቦታ” ማለት ነው። ይህም ዳንኤል ራእዩን ሲቀበል በባቢሎን ከተማ ላይሆን ቢችልም በባቢሎንያ ምድር እንደነበር ያረጋግጣል።
10 ዳንኤል የተመለከተው ራእይ እንዴት የሚያስገርም ነው! ዓይኑን ቀና አድርጎ ሲመለከት ያየው ተራ ሰው አልነበረም። ዳንኤል የሚከተለውን ሕያው መግለጫ ሰጥቷል:- “አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበረ፣ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፣ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ።”—ዳንኤል 10:6
11. ራእዩ በዳንኤልና አብረውት በነበሩት ሰዎች ላይ ምን ውጤት ነበረው?
11 ራእዩ እጅግ አንጸባራቂ ቢሆንም ዳንኤል ‘ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ራእዩን አላዩም’ ሲል ተናግሯል። ባልታወቀ ምክንያት ሰዎቹ “ጽኑ መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፣ ሊሸሸጉም ሸሹ።” ከዚያ በኋላ ዳንኤል በወንዙ ዳርቻ ብቻውን ቀረ። የዚህ “ታላቅ ራእይ” ትእይንት እጅግ አስገራሚ ከመሆኑ የተነሣ ዳንኤል እንደሚከተለው ሲል አምኗል:- “ኃይልም አልቀረልኝም፣ ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፣ ኃይልም አጣሁ።”—ዳንኤል 10:7, 8
12, 13. የመልእክተኛው (ሀ) ልብስ (ለ) ሰውነት ምን ይጠቁማል?
12 እስቲ ዳንኤልን ይህን ያህል ስላስፈራው ባለ ግርማ መልእክተኛ በጥልቀት እንመርምር። ‘በፍታ ለብሶ ወገቡን በጥሩ የአፌዝ ወርቅ ታጥቋል።’ በጥንቷ እስራኤል የነበረው ሊቀ ካህናት መታጠቂያው፣ ኤፉዱና የደረት ኪሱ እንዲሁም የቀሩት ካህናት የሚለብሱት ልብስ የሚዘጋጀው በብልሃት ከተሠራ በፍታ ሲሆን በወርቅ ይጌጥ ነበር። (ዘጸአት 28:4-8፤ 39:27-29) በመሆኑም የመልእክተኛው ልብስ ቅድስናንና የሥልጣን ክብር የሚያሳይ ነው።
13 ዳንኤል በመልክተኛውም ሰውነት ማለትም እንደ ከበረ ማዕድን ባለው የሰውነቱ አንጸባራቂ ክብር፣ ዓይን የሚያጥበረብረው የፊቱ ነፀብራቅ፣ እንደ ጦር በሚዋጉት ዓይኖቹና በሚያንጸባርቁት ፈርጣማ እጅና እግሮቹ በፍርሃት ተውጦ ነበር። ሌላው ቀርቶ እንደ ነጎድጓድ የሚያስገመግመው ድምፁም ራሱ አስፈሪ ነበር። ይህ ሁሉ ነገር ከሰው በላይ የሆነ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ነበር። ይህ ‘የበፍታ ልብስ የለበሰ ሰው’ በይሖዋ ፊት የሚያገለግል ከፍተኛ ሥልጣን ያለው መልአክ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። መልእክቱንም ያመጣው ከይሖዋ ነው።a
‘እጅግ የተወደደው ሰው’ ብርታት አገኘ
14. ዳንኤል መላእክታዊውን መልእክት ለመቀበል ምን እርዳታ አስፈልጎት ነበር?
14 የይሖዋ መልአክ ለዳንኤል ያመጣለት መልእክት ከበድ ያለና ውስብስብ ነበር። ዳንኤል ይህን መልእክት መቀበል እንዲችል ከገጠመው አካላዊና አእምሮአዊ መረበሽ እንዲያገግም እርዳታ ያስፈልገዋል። መልአኩ ይህንኑ በመገንዘብ ለዳንኤል በግል እርዳታና ማበረታቻ ሰጥቶታል። የተፈጸመውን ነገር ዳንኤል ራሱ ሲተርከው እንከታተል።
15. መልአኩ ዳንኤልን ለመርዳት ምን አደረገ?
15 “የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ።” ዳንኤል ክው ብሎ የቀረው በሥጋትና በጭንቀት ሳይሆን አይቀርም። መልአኩ ዳንኤልን ለመርዳት ምን አደረገ? ዳንኤል “እነሆም፣ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፣ በጉልበቴና በእጄም አቆመችኝ” ብሏል። በተጨማሪም መልአኩ በሚከተሉት ቃላት ነቢዩን አበረታትቶታል:- “እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፣ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፣ ቀጥ ብለህም ቁም።” የዳሰሰው እጅና የተነገሩት የሚያጽናኑ ቃላት ዳንኤልን አበረታተውታል። ዳንኤል ‘እየተንቀጠቀጠም’ ተነሥቶ ‘ቆመ’።—ዳንኤል 10:9-11
16. (ሀ) ይሖዋ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡት ጸሎት ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥ እንዴት መረዳት ይቻላል? (ለ) መልአኩ ዳንኤልን ለመርዳት ሲመጣ የዘገየው ለምን ነበር? (ሣጥኑን ጨምረህ መልስ።) (ሐ) መልአኩ ለዳንኤል ያመጣለት መልእክት ምን ነበር?
16 መልአኩ የመጣው በቀጥታ ዳንኤልን ለማበረታታት መሆኑን አመልክቷል። እንዲህ አለ:- “ዳንኤል ሆይ፣ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፣ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ።” ከዚያም መልአኩ የዘገየበትን ምክንያት አስረዳው። “የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም፣ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት” አለ። መልአኩ በሚካኤል እርዳታ ይህን በጣም አስቸኳይ መልእክት ለዳንኤል የማድረስ ተልእኮውን ለመፈጸም ችሏል:- “ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋላኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።”—ዳንኤል 10:12-14
17, 18. ዳንኤል ለሁለተኛ ጊዜ እርዳታ ያገኘው እንዴት ነው? ይህስ ምን እንዲያደርግ አስችሎታል?
17 ዳንኤል እንዲህ ያለ ስሜት ቀስቃሽ መልእክት ሊነገረው መሆኑን ሲሰማ ልቡ አልተንጠለጠለም። ይልቁንም የሰማው ነገር አስደነገጠው። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፣ ዲዳም ሆንሁ።” ነገር ግን ተልኮ የመጣው መልአክ ዳንኤልን ለሁለተኛ ጊዜ በፍቅር ሊረዳው ፈቃደኛ ነበር። ዳንኤል እንዲህ ይላል:- “እነሆም፣ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፤ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ።”b—ዳንኤል 10:15, 16ሀ
18 ዳንኤል መልአኩ ከንፈሩን ሲዳስስለት ብርታት አግኝቷል። (ከኢሳይያስ 6:7 ጋር አወዳድር።) የመናገር ችሎታው የተመለሰለት ዳንኤል ምን ያህል እንደተቸገረ ለተላከው መልአክ ማስረዳት ችሎ ነበር። ዳንኤል እንዲህ አለ:- “ጌታዬ ሆይ፣ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፣ ኃይልም አጣሁ። ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፣ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት።”—ዳንኤል 10:16ለ, 17
19. ዳንኤል ለሦስተኛ ጊዜ እርዳታ ያገኘው እንዴት ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
19 ዳንኤል የገጠመውን ችግር መግለጹ እንጂ ማጉረምረሙ ወይም ሰበብ መፍጠሩ አልነበረም። መልአኩም ሐሳቡን ተቀብሎታል። በመሆኑም የተላከው መልአክ ዳንኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ረዳው። ነቢዩ “ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፣ አበረታኝም” ብሏል። ዳበስ አድርጎት ኃይል ካገኘ በኋላ መልእክተኛው እነዚህን የሚያጽናኑ ቃላት ተናገረ:- “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፣ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፣ ጽና።” ዳንኤል የሚያስፈልገው ይህን በመሰለ ፍቅራዊ መንገድ ዳሰስ የሚያደርገውና በሚያጽናኑ ቃላት የሚናገረው ሰው የነበረ ይመስላል። ውጤቱስ ምን ሆነ? ዳንኤል እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና:- አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር አልሁ።” ከዚህ በኋላ ዳንኤል ከፊቱ ለሚጠብቀው ፈታኝ ኃላፊነት ተዘጋጅቶ ነበር።—ዳንኤል 10:18, 19
20. ተልኮ የመጣው መልአክ የተሰጠውን ሥራ መፈጸም ተጋድሎ ይጠይቅበት የነበረው ለምንድን ነው?
20 መልአኩ ዳንኤልን ካበረታውና አእምሮአዊና አካላዊ ችሎታውን መልሶ እንዲያገኝ ከረዳው በኋላ የተላከበትን ዓላማ በድጋሚ ገለጸለት። እንዲህ አለ:- “ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፣ ታውቃለህን? አሁንም ከፋርስ አለቃ ጋር እዋጋ ዘንድ እመለሳለሁ፤ እኔም ስወጣ፣ እነሆ፤ የግሪክ አለቃ ይመጣል። ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም።”—ዳንኤል 10:20, 21
21, 22. (ሀ) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በሚመለከት ከዳንኤል ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ዳንኤል ከዚህ በኋላ ምን ለማድረግ የሚያስችል ብርታት አግኝቷል?
21 ይሖዋ እንዴት ያለ አፍቃሪና አሳቢ አምላክ ነው! ሁልጊዜ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው እንደ ችሎታቸውና እንደ አቅማቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንዲሠሩ የሚሰጣቸው እንደሚያከናውኑት እርግጠኛ የሆነበትን ሥራ ነው። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ አገልጋዮቹ ሥራውን እንደሚችሉት ሆኖ አይሰማቸው ይሆናል። በአንጻሩ ደግሞ የሚናገሩትን ለማዳመጥና ከዚያም ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። እኛም ብንሆን ሁልጊዜ የእምነት አጋሮቻችንን በፍቅር በማበረታታትና በመደገፍ የሰማያዊ አባታችንን የይሖዋን ምሳሌ እንኮርጅ።—ዕብራውያን 10:24
22 መልአኩ ይዞት የመጣው አጽናኝ የሆነ መልእክት ዳንኤልን በእጅጉ አበረታትቶታል። ዳንኤል ዕድሜው ገፍቶ የነበረ ቢሆንም ለእኛ ጥቅም ሲባል ተጨማሪ ድንቅ ትንቢት መዝግቦ ለማቆየት የሚያስችለውን ብርታት አግኝቶና ተዘጋጅቶ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህ መልአክ በስም ባይጠቀስም ስላየው ራእይ ዳንኤልን ይረዳው ዘንድ ለገብርኤል መመሪያ ሲሰጥ ድምፁ የተሰማው መልአክ ይመስላል። (ዳንኤል 8:2, 15, 16ን ከዳን 12:7, 8 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል 10:13 ‘ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ’ የሆነው ሚካኤል ይህንን መልአክ ሊረዳው እንደመጣ ይገልጻል። በመሆኑም ይህ ስሙ ያልተገለጸው መልአክ ከገብርኤልና ከሚካኤል ጋር በቅርብ የመሥራት መብት ያለው መልአክ መሆን ይኖርበታል።
b የዳንኤልን አፍ የዳሰሰው ከዳንኤል ጋር ሲነጋገር የነበረው መልአክ ራሱ ሊሆን ቢችልም እዚህ ቁጥር ላይ ከገባው አገላለጽ አንጻር ሌላ መልአክ ምናልባትም ገብርኤል ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ተልኮ የመጣ አንድ መልአክ ዳንኤልን አበርትቶታል።
ምን አስተውለሃል?
• የይሖዋ መልአክ በ536/535 ከዘአበ ወደ ዳንኤል ሲሄድ የዘገየው ለምን ነበር?
• ከአምላክ ተልኮ የመጣው መልአክ የለበሰው ልብስና ሰውነቱ ስለ እርሱ ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?
• ዳንኤል ምን እርዳታ አስፈልጎት ነበር? መልአኩስ ሦስት ጊዜ የረዳው እንዴት ነው?
• መልአኩ ለዳንኤል ያመጣለት መልእክት ምን ነበር?
[በገጽ 204 እና 205 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መላእክታዊ ጠባቂዎች ወይስ አጋንንታዊ አለቆች?
የዳንኤል መጽሐፍ ስለ መላእክቱ ከሚናገረው ነገር ብዙ መማር እንችላለን። የይሖዋን ቃል በመፈጸም ረገድ ስለሚጫወቱት ሚናና የተሰጣቸውን ሥራ ለመፈጸም ስለሚያደርጉት ተጋድሎ ይነግረናል።
የአምላክ መልአክ ዳንኤልን ለማነጋገር ሲመጣ ‘የፋርስ መንግሥት አለቃ’ እንደገታው ተናግሯል። ከእርሱም ጋር ለ21 ቀናት ከታገለ በኋላ ጉዞውን መቀጠል የቻለው ‘ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ በሆነው በሚካኤል እርዳታ’ ነበር። በተጨማሪም መልአኩ ይህንኑ ጠላትና ምናልባትም ‘የግሪክን አለቃ’ መታገል እንዳለበት ተናግሯል። (ዳንኤል 10:13, 20) ለመልአክም ቢሆን ይህ ቀላል ሥራ አልነበረም! ይሁንና እነዚህ የፋርስና የግሪክ አለቆች እነማን ናቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ ሚካኤል ‘ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ’ እንዲሁም ‘የሕዝብህ አለቃ’ እንደተባለ እናስተውላለን። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሚካኤል ‘ስለ ሕዝብህ [ስለ ዳንኤል ሕዝብ] ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል’ ተብሏል። (ዳንኤል 10:21፤ 12:1) ይህም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይመራቸው ዘንድ ይሖዋ የመደበው መልአክ ሚካኤል እንደነበር ይጠቁመናል።—ዘጸአት 23:20-23፤ 32:34፤ 33:2
ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ‘የመላእክት አለቃ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር ስለ ሙሴ ሥጋ እንደተነጋገረ’ መግለጹ ይህንኑ መደምደሚያ የሚያጠናክር ነው። (ይሁዳ 9) ሚካኤል ያለው ማዕረግ፣ ኃይልና ሥልጣን በእርግጥም “የመላእክት አለቃ” ማለትም “ዋና መልአክ” እንዲሆን የሚያደርገው ነው። እንዲህ ያለው ከፍ ያለ ቦታ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊትና ከዚያ በኋላ ያለውን ሁኔታ የሚገልጽ እንጂ ሌላ ማንንም የሚያመለክት ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው።—1 ተሰሎንቄ 4:16፤ ራእይ 12:7-9
ይህ ማለት ግን ይሖዋ እንደ ፋርስና ግሪክ ያሉትን ብሔራት ለመምራት ሲል መልአክ ይሾምላቸዋል ማለት ነውን? የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል:- “የዚህ ዓለም ገዥ . . . በእኔ ላይም አንዳች የለውም።” በተጨማሪም ኢየሱስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:30፤ 18:36) ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዓለም በሞላው በክፉው እንደተያዘ’ ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 5:19) የዓለም መንግሥታት በአምላክ ወይም በክርስቶስ አመራር ወይም አገዛዝ ሥር ሆነው እንደማያውቁና ዛሬም እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ይሖዋ ‘የበላይ ባለ ሥልጣኖች’ እንዲኖሩና የምድርን መስተዳድራዊ ጉዳዮች እንዲቆጣጠሩ ቢፈቅድላቸውም መላእክቱን በእነርሱ ላይ አይሾምም። (ሮሜ 13:1-7) በእነርሱ ላይ የተሾሙ ‘አለቆች’ ወይም ‘ገዥዎች’ ካሉ “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ የሾመላቸው ናቸው። መላእክታዊ ጠባቂዎች ሳይሆኑ አጋንንታዊ አለቆች ናቸው። እንግዲያውስ በዓይን ከሚታዩት ገዥዎችና ብሔራዊ ግጭቶች በስተጀርባ ያሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በዓይን የማይታዩ አጋንንታዊ ኃይሎች ጭምር ናቸው ማለት ነው።
[በገጽ 199 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]
[በገጽ 207 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]