የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የዳንኤል መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
“የዳንኤል መጽሐፍ ትኩረት ከሚስቡት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ ነው። . . . መጽሐፉ ጊዜ የማይሽራቸውን እውነቶች ይዟል።” ይህ ሐሳብ የሚገኘው ሆልመን ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ በተባለው መጽሐፍ ላይ ነው። የዳንኤል ዘገባ፣ በ618 ከክርስቶስ ልደት በፊት የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከተማዋን እንደከበባት በመግለጽ ይጀምራል። ናቡከደነፆር ይሁዳን ከወረረ በኋላ አንዳንዶቹን “ወጣት ወንዶች” በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። (ዳንኤል 1:1-4) ከእነዚህ ወጣቶች አንዱ ዳንኤል ሲሆን በወቅቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፉ የሚደመደመው ዳንኤል በባቢሎን እያለ ነው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ፣ ወደ 100 ዓመት ገደማ ለሚሆነው ዳንኤል “አንተ . . . ታርፋለህ፤ በቀኖቹ መጨረሻም ተነሥተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ” በማለት ቃል ገባለት።—ዳንኤል 12:13
የዳንኤል መጽሐፍ የመጀመሪያ ክፍል የተጻፈው ድርጊቶቹ በተፈጸሙበት ቅደም ተከተል ከሦስተኛ ወገን አንጻር ሲሆን የመጨረሻውን ክፍል የሚተርከው ግን ዳንኤል ራሱ ነው። በዳንኤል የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ስለ ዓለም መንግሥታት መነሳትና መውደቅ፣ መሲሑ ስለሚመጣበት ጊዜ እንዲሁም በዘመናችን ስለሚፈጸሙ ክስተቶች የሚገልጹ ትንቢቶችን ይዟል።a ከዚህም በላይ አረጋዊው ነቢይ ያሳለፈውን ረጅም ሕይወት መለስ ብሎ በማስታወስ፣ ለአምላክ በታማኝነት የምንጸና ወንዶችና ሴቶች እንድንሆን የሚያበረታቱ ክንውኖችን ይተርክልናል። በእርግጥም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ሕያውና የሚሠራ ነው።—ዕብራውያን 4:12
በቅደም ተከተል ከተቀመጠው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
ወቅቱ 617 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ዳንኤል እንዲሁም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ የተባሉት ሦስት ወጣት ጓደኞቹ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ውስጥ ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ስለ ቤተ መንግሥት ሕይወት ለሦስት ዓመታት የዘለቀ ሥልጠና በተሰጣቸው ወቅት ለአምላክ ታማኝ ሆነው ቆይተዋል። ከስምንት ዓመታት በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር ግራ የሚያጋባ ሕልም ተመለከተ። ዳንኤል ሕልሙን ከገለጠለት በኋላ ፍቺውን ነገረው። ንጉሡም፣ ይሖዋ “የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ” መሆኑን አምኖ ተቀበለ። (ዳንኤል 2:47) ይሁን እንጂ ናቡከደነፆር ብዙም ሳይቆይ በዚህ ወቅት ያገኘውን ትምህርት የዘነጋው ይመስላል። የዳንኤል ሦስት ጓደኞች ለአንድ ግዙፍ ምስል ለመስገድ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ንጉሡ በሚንበለበል የእሳት እቶን ውስጥ እንዲጣሉ አደረገ። እውነተኛው አምላክ ሦስቱን ወጣቶች ከእሳቱ አዳናቸው፤ ናቡከደነፆርም “እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ [እንደሌለ]” ለመቀበል ተገደደ።—ዳንኤል 3:29
ናቡከደነፆር ሌላ ትኩረት የሚስብ ሕልም አለመ። አንድ ረጅም ዛፍ ሲቆረጥና እንደገና እንዳያቆጠቁጥ ጉቶው በብረት ሲታሰር ተመለከተ። ዳንኤል የሕልሙን ፍቺ ለንጉሡ አስታወቀው። ናቡከደነፆር ለተወሰነ ጊዜ አእምሮውን ስቶ ከቆየ በኋላ ጤናው ሲመለስለት ሕልሙ በከፊል ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ ከሆነ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ንጉሥ ቤልሻዛር ለመኳንንቱ ትልቅ ድግስ ያዘጋጀ ሲሆን በዚያም ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን መጠጫዎች አክብሮት በጎደለው መንገድ ተጠቀመባቸው። በዚያው ሌሊት ቤልሻዛር ተገደለ፤ መንግሥቱንም ሜዶናዊው ዳሪዮስ ወሰደው። (ዳንኤል 5:30, 31) በዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ዳንኤል ከ90 ዓመት በላይ ሆኖት ነበር፤ በዚህ ወቅት በአረጋዊው ነቢይ ቅናት ያደረባቸው ባለ ሥልጣናት እሱን ለመግደል አሴሩበት። ሆኖም ይሖዋ “ከአንበሶች አፍ” አዳነው።—ዳንኤል 6:27
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
1:11-15—አራቱ አይሁዳውያን ወጣቶች አምረው እንዲታዩ ያደረጋቸው አትክልት መመገባቸው ነበር? አልነበረም። በአሥር ቀናት ውስጥ ብቻ እንዲህ ዓይነት ለውጥ ሊያስገኝ የሚችል ምግብ የለም። የእነዚህ ዕብራውያን ወጣቶች መልክ ያማረው ይሖዋ፣ በእሱ በመታመናቸው ስለባረካቸው ነው።—ምሳሌ 10:22
2:1—ናቡከደነፆር ስለ ግዙፉ ምስል የሚገልጸውን ሕልም ያየው መቼ ነበር? ይህ የሆነው “ናቡከደነፆር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት” እንደሆነ ዘገባው ይገልጻል። ናቡከደነፆር በባቢሎን ላይ የነገሠው በ624 ከክርስቶስ ልደት በፊት በመሆኑ የግዛቱ ሁለተኛ ዓመት የጀመረው በ623 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው፤ ይህም ይሁዳን ከመውረሩ ከዓመታት በፊት ነበር። በዚያን ጊዜ ዳንኤል በባቢሎን ሆኖ ሕልሙን ሊተረጉምለት አይችልም። ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ‘ሁለተኛው ዓመት’ የተቆጠረው የባቢሎን ንጉሥ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌምን አጥፍቶ የዓለም ገዥ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ነው።
2:32, 39—በብር የተመሰለው መንግሥት ከወርቁ ራስ፣ በናስ የተመሰለው መንግሥት ደግሞ በብር ከተመሰለው መንግሥት ያነሰ የሆነው በምን መንገድ ነው? ምስሉ ላይ በብር የተመሰለው የሜዶ ፋርስ መንግሥት ይሁዳን የመጣል አጋጣሚ ባለማግኘቱ በወርቁ ራስ ከተመሰለው የባቢሎን መንግሥት ያነሰ ነበር። ከሜዶ ፋርስ ቀጥሎ የዓለም ኃያል የሆነው መንግሥት ግሪክ ሲሆን እሱም በናስ ተመስሏል። ናስ ከብር ያነሰ እንደሆነ ሁሉ የግሪክ መንግሥትም ከሜዶ ፋርስ ያነሰ ነበር። የግሪክ መንግሥት ሰፊ ግዛት የነበረው ቢሆንም እንደ ሜዶ ፋርስ መንግሥት የአምላክ ሕዝቦችን ከግዞት ነፃ የማውጣት አጋጣሚ አላገኘም።
4:10, 11, 20-22—ናቡከደነፆር በሕልሙ ያየው ረጅም ዛፍ ምን ያመለክታል? ዛፉ በመጀመሪያ የሚያመለክተው የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረችው የባቢሎን ገዥ የሆነውን ናቡከደነፆርን ነው። ሆኖም ግዛቱ “እስከ ምድር ዳርቻ” በመሆኑ ዛፉ ከዚህ የበለጠ ነገር የሚያመለክት መሆን አለበት። ዳንኤል 4:17 ሕልሙን፣ በሰው ዘር ላይ ከሚገዛው “ልዑል” አገዛዝ ጋር አያይዞታል። በመሆኑም ዛፉ የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትም (በተለይም ከምድር ጋር በተያያዘ) ያመለክታል። ስለዚህ ንጉሡ ያየው ሕልም ከናቡከደነፆር አገዛዝና ከይሖዋ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ሁለት ፍጻሜዎች አሉት።
4:16, 23, 25, 32, 33—‘ሰባቱ ዘመናት’ [የ1954 ትርጉም] ምን ያህል ርዝመት አላቸው? በንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ከተፈጸሙት ለውጦች አንጻር ‘ሰባቱ ዘመናት’ ከሰባት ቀናት የበለጠ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ከናቡከደነፆር ጋር በተያያዘ እነዚህ ዘመናት እያንዳንዳቸው 360 ቀናት ያላቸው ሰባት ዓመታትን ወይም 2,520 ቀናትን ያመለክታሉ። በትንቢቱ ታላቅ ፍጻሜ ላይ ደግሞ ‘ሰባቱ ዘመናት’ 2,520 ዓመታት ናቸው። (ሕዝቅኤል 4:6, 7) እነዚህ ዘመናት፣ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ጀምረው ኢየሱስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲሾም አብቅተዋል።—ሉቃስ 21:24
6:6-10—ወደ ይሖዋ ለመጸለይ አንድ ለየት ያለ አኳኋን የማያስፈልግ በመሆኑ ዳንኤል ለ30ዎቹ ቀናት በድብቅ ቢጸልይ የጥበብ አካሄድ አይሆንም ነበር? ዳንኤል በቀን ሦስት ጊዜ እንደሚጸልይ ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር። በእሱ ላይ ያሴሩት ሰዎች መጸለይን የሚከለክል ሕግ እንዲወጣ ሐሳብ ያቀረቡትም ለዚህ ነው። ዳንኤል የጸሎት ልማዱን በማንኛውም መንገድ ቢቀይረው ጠላቶቹ አቋሙን ያላላ ሊመስላቸው ይችላል፤ እንዲሁም ለይሖዋ ብቻ የሚያቀርበውን አምልኮ እንደተወው ሊያስመስልበት ይችል ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:3-8:- ዳንኤልም ሆነ ጓደኞቹ ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቆራጥ አቋም መያዛቸው ወላጆቻቸው የሰጧቸው ሥልጠና ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበር አጉልቶ ያሳያል። አምላክን የሚፈሩ ወላጆች በሕይወታቸው ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ሲሰጡና ልጆቻቸውም ይህን እንዲያድርጉ ሲያስተምሯቸው ልጆቹ በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ ቦታ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና እንዲሁም የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተሻለ አጋጣሚ ይኖራቸዋል።
1:10-12:- ዳንኤል፣ “የጃንደረቦቹ አለቃ” ንጉሡን ለምን እንደፈራ ስለተገነዘበ ግለሰቡን አልተጫነውም። ከዚህ ይልቅ ዳንኤል ቆየት ብሎ ‘መጋቢውን’ አነጋገረው፤ ይህ ሰው ያለው ቦታ ሁኔታውን ለመለወጥ ያስችለው ይሆናል። እኛም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ማስተዋልና ጥበብ ማሳየት ይገባናል።
2:29, 30:- እንደ ዳንኤል ሁሉ እኛም ይሖዋ ካቀረበልን መንፈሳዊ ዝግጅት ተጠቃሚ በመሆናችን ላገኘነው ማንኛውም እውቀት እንዲሁም ላዳበርነው ባሕርይና ችሎታ እሱን ልናወድሰው ይገባል።
3:16-18:- ሦስቱ ዕብራውያን ወጣቶች ቀደም ሲል ከምግብ ጋር በተያያዘ ፈተና ሲያጋጥማቸው አቋማቸውን አላልተው ቢሆን ኖሮ በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ ጠንካራ አቋም ኖሯቸው መልስ መስጠታቸው አጠራጣሪ ይሆን ነበር። እኛም ‘በነገር ሁሉ የታመንን ለመሆን’ መጣር ይገባናል።—1 ጢሞቴዎስ 3:11
4:24-27:- ዳንኤል፣ ናቡከደነፆር ምን እንደሚደርስበት እንዲሁም ‘በሰላም የሚኖርበት ዘመን እንዲራዘምለት’ ምን ማድረግ እንዳለበት ለመናገር እምነትና ድፍረት አስፈልጎታል፤ የአምላክን የጥፋት ፍርድ የሚጨምረውን የመንግሥቱን መልእክት ለማወጅም ተመሳሳይ እምነትና ድፍረት ያስፈልጋል።
5:30, 31:- ‘በባቢሎን ንጉሥ ላይ የተነሣው ምሳሌ’ [የ1954 ትርጉም] በትክክል ተፈጽሟል። (ኢሳይያስ 14:3, 4, 12-15) እንደ ባቢሎን ነገሥታት እብሪተኛ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስም እንዲሁ አሳፋሪ የሆነ ውደቀት ይደርስበታል።—ዳንኤል 4:30፤ 5:2-4, 23
ዳንኤል የተመለከታቸው ራእዮች ምን ያሳያሉ?
ዳንኤል በ553 ከክርስቶስ ልደት በፊት የመጀመሪያውን ሕልም ሲያልምና ራእይ ሲመለከት በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ነበር። ዳንኤል ከእሱ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በተከታታይ የተነሱትን የዓለም ኃያል መንግሥታት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ አራዊት አየ። ዳንኤል በሰማይ ስላለው ሁኔታ ባየው ራእይ ላይ “የሰውን ልጅ የሚመስል” አካል የተመለከተ ሲሆን እሱም ‘ለዘላለም የማያልፍ ግዛት’ ተሰጠው። (ዳንኤል 7:13, 14) ከሁለት ዓመታት በኋላ ደግሞ ስለ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ እና ‘አስፈሪ ፊት ስላለው ንጉሥ’ የሚገልጽ ራእይ ተመለከተ።—ዳንኤል 8:23
ወቅቱ 539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ባቢሎን ወድቃለች፤ ሜዶናዊው ዳርዮስም በከለዳውያን መንግሥት ላይ ገዥ ሆኗል። ዳንኤል የትውልድ አገሩ እንደገና እንድትቋቋም እየጸለየ ሳለ ይሖዋ፣ ለነቢዩ ስለ መሲሑ መምጣት “ጥበብንና ማስተዋልን” እንዲሰጠው መልአኩን ገብርኤልን ላከው። (ዳንኤል 9:20-25) ቀን ቀንን እየወለደ 536/535 ከክርስቶስ ልደት በፊት ላይ ደርሰናል። ጥቂት አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። ሆኖም የቤተ መቅደሱ ግንባታ ተቃውሞ አጋጠመው። ይህ ደግሞ ዳንኤልን አስጨንቆታል። ዳንኤልም ስለዚህ ጉዳይ አጥብቆ በመጸለዩ ይሖዋ ከፍተኛ ቦታ ያለው መልአክ ላከለት። መልአኩም ነቢዩን ካበረታታው በኋላ የሰሜኑና የደቡቡ ንጉሥ የበላይ ለመሆን ስለሚያደርጉት ሽኩቻ የሚገልጽ ትንቢት ነገረው። በሁለቱ ነገሥታት መካከል የሚካሄደው ሽኩቻ የታላቁ እስክንድር መንግሥት ለአራት ጄኔራሎቹ ከተከፋፈለበት ጊዜ አንስቶ ታላቁ አለቃ ሚካኤል ‘እስከሚነሣበት’ ጊዜ ድረስ ይዘልቃል።—ዳንኤል 12:1
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-
8:9—“መልካሚቱ ምድር” ምን ታመለክታለች? እዚህ ላይ “መልካሚቱ ምድር” የሚለው አገላለጽ አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኖ በሚገዛበት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ የሚኖራቸውን ሁኔታ ያመለክታል።
8:25—‘የልዑላን ልዑል’ የተባለው ማን ነው? “ልዑል” ተብሎ የተተረጎመው ሳር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “አለቃ” ወይም “ራስ” የሚል ትርጉም አለው። ‘የልዑላን ልዑል’ የሚለው የማዕረግ ስም የሚያመለክተው፣ ‘ከዋነኞቹ አለቆች [ወይም ልዑላን] አንዱ የሆነውን ሚካኤልን’ ጨምሮ ልዑላን የሆኑት መላእክት ሁሉ አለቃ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ብቻ ነው።—ዳንኤል 10:13
9:21—ዳንኤል መልአኩ ገብርኤልን “ሰው” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው? ገብርኤል፣ ዳንኤል አስቀድሞ በተመለከተው ራእይ ላይ እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ሰብዓዊ አካል ለብሶ ስለመጣ ነው።—ዳንኤል 8:15-17
9:27—ሰባዎቹ የዓመታት ሳምንታት እስኪያበቁ ማለትም እስከ 36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ‘ከብዙ ሰዎች ጋር የጸናው ቃል ኪዳን’ የትኛው ነው?b በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሱስ ሲሰቀል የሕጉ ቃል ኪዳን ተወግዷል። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን እስከ 36 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ለሥጋዊ እስራኤላውያን እንዲጸና በመፍቀድ የአብርሃም ዘር ለሆኑት አይሁዳውያን ልዩ ሞገስ አሳይቷቸዋል። ‘ለአምላክ እስራኤል’ ግን ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን እንደጸና ነው።—ገላትያ 3:7-9, 14-18, 29፤ 6:16
ምን ትምህርት እናገኛለን?
9:1-23፤ 10:11:- ዳንኤል ትሑትና ለአምላክ ያደረ ከመሆኑም በላይ በትጋት ያጠና እንዲሁም አዘውትሮ ይጸልይ ስለነበር በይሖዋ ዘንድ “እጅግ የተወደድህ” ተብሏል። እንዲህ ዓይነት ሰው መሆኑ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለአምላክ ታማኝ እንዲሆን ረድቶታል። እኛም የዳንኤልን ምሳሌ ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
9:17-19:- “ጽድቅ የሚኖርበት” የአምላክ አዲስ ዓለም እንዲመጣ ስንጸልይም እንኳ በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው የግል ችግራችንና ሥቃያችን መወገዱ ሳይሆን የይሖዋ ስም መቀደሱና ሉዓላዊነቱ መረጋገጡ ሊሆን አይገባም?—2 ጴጥሮስ 3:13
10:9-11, 18, 19:- ወደ ዳንኤል የመጣው መልአክ እንዳደረገው ሁሉ እኛም እርስ በርስ በመረዳዳትና የሚያጽናኑ ቃላት በመለዋወጥ አንዳችን ሌላውን ማበረታታት ይገባናል።
12:3:- በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ “ጥበበኞች” የተባሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘እንደ ከዋክብት በማብራት’ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ጨምሮ ‘ብዙዎችን ወደ ጽድቅ መልሰዋል።’ (ፊልጵስዩስ 2:15፤ ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከእሱ ጋር ሆነው፣ ታዛዥ የሰው ዘሮች ከቤዛዊው መሥዋዕት የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ በማድረጉ ሥራ በመካፈል ሙሉ በሙሉ “እንደ ከዋክብት . . . ይደምቃሉ።” “ሌሎች በጎች” ደግሞ ቅቡዓኑን በሙሉ ልብ በመደገፍ ከእነሱ ጎን በታማኝነት መቆም አለባቸው።
ይሖዋ ‘የሚፈሩትን ይባርካል’
የዳንኤል መጽሐፍ ስለምናመልከው አምላክ ምን ያስተምረናል? በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙት ፍጻሜያቸውን ያገኙና ገና ወደፊት የሚፈጸሙ ትንቢቶች ይሖዋ ቃሉን የሚፈጽም አምላክ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ!—ኢሳይያስ 55:11
በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ስለ አምላካችን ምን ይገልጹልናል? የባቢሎናውያንን የቤተ መንግሥት ሕይወት ሙሉ በሙሉ ለመቀበል ፈቃደኞች ላልሆኑት አራት ዕብራውያን ወጣቶች ይሖዋ “ትምህርት ዕውቀትንና ማስተዋልን” ሰጥቷቸዋል። (ዳንኤል 1:17) እውነተኛው አምላክ መልአኩን በመላክ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብድናጎን ከሚንበለበል የእሳት እቶን ዳንኤልን ደግሞ ከአንበሶች ጉድጓድ አድኗቸዋል። ይሖዋ ‘በእርሱ ለሚታመኑት ረዳታቸውና ጋሻቸው ነው’፤ እንዲሁም ‘የሚፈሩትን ይባርካል።’—መዝሙር 115:9, 13
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስለ ዳንኤል መጽሐፍ የበለጠ ለማወቅ የመጽሐፉ ምዕራፎች ቁጥር በቁጥር የተብራሩበትን የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የሚለውን መጽሐፍ ተመልከት።
b ስለ 70ዎቹ የዓመታት ሳምንታት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 197-199 ተመልከት።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳንኤል “እጅግ የተወደደህ” የተባለው ለምንድን ነው?