ወጣቶች ሆይ፤ ምን ነገር እየተከታተላችሁ ነው?
“ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፣ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አጥብቀህ ተከተል።” — 2 ጢሞቴዎስ 2:22
1. በመካከላችን ስለሚገኙት ወጣቶች ምን ተስፋ እናደርጋለን?
“የይሖዋ ምሥክሮች” ይላል ዳገን የተባለው በስዊድን የሚታተም የጰንጠቆስጤዎች ጋዜጣ “ከማንኛውም ቡድን የበለጠ በርካታ ቁጥር ያላቸው አባላት በየዓመቱ የሚያገኙና በርካታ የወጣት ጭፍራ ያላቸው ሕዝቦች ናቸው።” ምናልባት አንተም ከእነዚህ ንፁሕና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች አንዱ ትሆናለህ። ከሕጻንነትህ ጀምረህ በክርስትና መንገድ ያደግህ አለበለዚያም የመንግሥቱን ምሥራች ከሰማህ በኋላ ራስህ መልእክቱን ለመቀበል እርምጃ የወሰድህ ትሆን ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በመካከላችን በመሆንህ በጣም ደስ ይለናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ታማኝ ክርስቲያን ወጣቶችም የጽድቅ መንገድ እንደምትከተል ተስፋ እናደርጋለን። የሐዋርያው ዮሐንስ ቃል ለአንተም ሊሠራ ይችላል። “ብርቱዎች ስለሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር እጽፍላችኋለሁ” ብሎአል። — 1 ዮሐንስ 2:14
2. በአፍላ የጎልማሳነት ዕድሜ የጽድቅ መንገድ መከተል አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው በምን ምክንያቶች ነው?
2 በዘመናችን ያሉ ብዙ እንዲያውም አብዛኞቹ ክርስቲያን ወጣቶች የዚህን ዓለም ተጽዕኖዎች በመቋቋም ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ ይህን አካሄድ ጠብቆ መኖር ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝበህ ይሆናል። በአፍላ የጐልማሳነት ዕድሜ ላይ በምትሆንበት ጊዜ አዳዲስና ጠንካራ የሆኑ ስሜቶች ሊሰሙህ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:36) በዚህ ላይ ደግሞ በትምህርት ቤት፣ በቤትና በጉባኤ ያለብህ ኃላፊነት እየጨመረ በመሄዱ ሸክሙ እየከበደህ ሊመጣ ይችላል። ሰይጣን ዲያብሎስ ራሱ የሚያመጣብህ ተጽዕኖ ይኖራል። የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ለማሳት ቆርጦ የተነሳ ስለሆነ በኤደን አትክልት ሥፍራ እንዳደረገው በቀላሉ ሊሸነፉ የሚችሉ በሚመስሉ ሁሉ ላይ ጥቃቱን ይሰነዝራል። ያኔም መሰሪ ሽንገላውን ያቀረበው በዕድሜም በዕውቀትም ብልጫ ለነበረው ለአዳም ሳይሆን ከአዳም ጋር ስትወዳደር በዕድሜም በተሞክሮም ታናሽ ለሆነችው ለሔዋን ነበር። (ዘፍጥረት 3:1–5) ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላም ሰይጣን ይህንኑ የሚመስል ዘዴ በመንፈሳዊ ተዳክሞ በነበረው በቆሮንቶስ ክርስቲያን ጉባኤ ላይ ተጠቅሞአል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎአል:- “ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።” — 2 ቆሮንቶስ 11:3
3, 4. ሰይጣን ዲያብሎስ ወጣቶችን ለማሳት ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ምን ዓይነት ውጤትስ ሊያስከትሉ ይችላሉ?
3 ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ወላጆቻችሁ ሊፈሩላችሁ ይችላሉ። የሚፈሩላችሁ የክፋት ዝንባሌ እንዳላችሁ ስለሚያስቡ ሳይሆን በተለይ ወጣቶች ለሰይጣን ሽንገላ የተጋለጡ እንደሆኑ ከራሳቸው ተሞክሮ ስለሚያውቁ ነው። (ኤፌሶን 6:11 አዓት የግርጌ ማስታወሻ ) የሰይጣን ወጥመዶች አደገኛ ሆነው ከመታየት ይልቅ የሚያስጎመጁና የሚፈለጉ ሆነው ይታያሉ። ቴሌቪዥን ቁሳዊ ሀብት ማሳደድን፣ ሕገ ወጥ የፆታ ግንኙነትን፣ ዓመፅንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን በመዝናኛ መልክ አሳምሮ ያቀርባል። የወጣቶች አእምሮ ‘እውነት፣ ጭምትነት፣ ጽድቅ፣ ንጽሕናና ፍቅር’ በጎደላቸው ነገሮች ሊሞላ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:8) ሌላው የሰይጣን ጠንካራ መሣሪያ የዕድሜ እኩዮች ተጽዕኖ ነው። የዕድሜ ጓደኞችህ ከአኗኗራቸው፣ ከአለባበሳቸውና ከአጋጌጣቸው ጋር እንድትስማማ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 4:3, 4) የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የሆኑት ዊልያም ብራውን እንዲህ ብለዋል:- “በአሥራዎቹ ዓመታት የሚገኝ አንድ ወጣት የሚያመልከው ሰብአዊ አምላክ አለ ከተባለ ይህ አምላክ ከሌሎች ጋር የመስማማት አምላክ ነው። በአሥራዎች ዓመታት ለሚገኙ ወጣቶች ከእኩዮቻቸው የተለየ አቋም መያዝ ከሞት የከፋ ነገር ነው።” አንዲት በኢጣልያ የምትኖር ምሥክር ወጣት ሳትሸሽግ እንዲህ ብላለች:- “የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ለትምህርት ቤት ጓደኞቼ ማሳወቅ ያሳፍረኝ ነበር። ይሖዋ በዚህ እንደማይደሰትብኝ ስለማውቅ በጣም አዝናለሁ እንዲሁም እተክዛለሁ።”
4 አትሳት፣ ሰይጣን ወደ ጥፋት አዘቅት ሊያወርድህ ይፈልጋል። በዓለም ያሉ ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን ለስህተት ስላጋለጡ በታላቁ መከራ ወቅት ሕይወታቸውን ያጣሉ። (ሕዝቅኤል 9:6) ከጥፋት ለመትረፍ የሚቻለው ትክክል የሆነውን ነገር በመከታተል ብቻ ነው።
ከመጥፎ ባልንጀርነት ተጠበቁ
5, 6. (ሀ) ወጣቱ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ይኖር በነበረበት ጊዜ እንዴት ያለ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? (ለ) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ምን ምክር ሰጠው?
5 ሐዋርያው ጳውሎስ ለወጣቱ ጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር ፍሬ ሐሳብ ይህ ነበር። ጢሞቴዎስ ከአሥር ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በሚሲዮናዊ ጉዞው አብሮት ተጉዞ ነበር። ጢሞቴዎስ የአረማውያን ከተማ በሆነችው በኤፌሶን ያገለግል በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ የሚገደልበትን ጊዜ እየጠበቀ በሮማ እሥር ቤት ውስጥ ተቀምጦ ነበር። ጳውሎስ የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ ሲሄድ የጢሞቴዎስ ሁኔታና አኗኗር አሳስቦት እንደነበረ አያጠራጥርም። ኤፌሶን በብልጽግናዋ፣ በሥነ ምግባር እርኩሰትዋና፣ ከሥርዓት ውጭ በሆኑት መዝናኛዎችዋ በጣም እውቅ የሆነች ከተማ ነበረች። ከዚህም በላይ ጢሞቴዎስ የተወደደ መካሪው የነበረውን የጳውሎስን ድጋፍ ሊያጣ ነው።
6 በዚህ ምክንያት ጳውሎስ ‘ለተወዳጅ ልጁ’ የሚከተለውን ጻፈለት:- “በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፣ እኩሌቶቹም ለክብር፣ እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፤ እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ፣ ለክብር የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል። ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፣ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።” — 2 ጢሞቴዎስ 1:2፤ 2:20–22
7. (ሀ) ጳውሎስ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው ‘የውርደት ዕቃዎች’ ምንድን ናቸው? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ወጣቶች የጳውሎስን ምክር እንዴት ሥራ ላይ ሊያውሉ ይችላሉ?
7 ስለዚህ ጳውሎስ በክርስቲያኖች መካከል እንኳን ‘የውርደት ዕቃዎች’ ማለትም በትክክለኛ መንገድ የማይመላለሱ ግለሶቦች እንደሚኖሩ ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆታል። ከአንዳንድ የተቀቡ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብ ጢሞቴዎስን ሊጎዳው የሚችል ከነበረ የዘመናችን ክርስቲያን ወጣቶች ከዓለማውያን ጋር ቢቀራረቡ የበለጠ መጥፎ ጉዳት አይደርስባቸውምን? (1 ቆሮንቶስ 15:33) እንዲህ ሲባል የትምህርት ቤት ጓደኞችህን ፊት መንሳት አለብህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንዳንድ ጊዜ ከሰው የተለየህ እንደሆንህ የሚያስመስልብህ ቢሆንም እንኳን ከሚገባው በላይ ከእነርሱ ጋር መቀራረብ የለብህም ማለት ነው። ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አንዲት ብራዚልያዊት ልጃገረድ እንዲህ ብላለች:- “በጣም አስቸጋሪ ነው። የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ሁልጊዜ ወደ ፓርቲዎችና ለክርስቲያን ወጣቶች ወደማይገቡ ቦታዎች አብሬያቸው እንድሄድ ይጋብዙኛል። ‘ምን! አትሄጅም? አብደሻል ማለት ነዋ!’ ይሉኛል።”
8, 9. (ሀ) ጥሩ መስለው ከሚታዩ ዓለማውያን ጋር እንኳን መቀራረብ ለአንድ ክርስቲያን አደገኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ጤናማ ባልንጀሮችን የት ማግኘት ይቻላል?
8 አንዳንድ ዓለማዊ ወጣቶች ስለማያጨሱ፣ በመጥፎ አነጋገር ስለማይጠቀሙ ወይም ዝሙት ስለማይፈጽሙ ብቻ ጥሩዎች የሆኑ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ጽድቅን የማይከታተሉ ከሆነ ሥጋዊ ዝንባሌያቸውና አስተሳሰባቸው በቀላሉ ወደ አንተ ሊጋባ ይችላል። ከዚህም በላይ ከማያምኑ ጋር ምን ያህል የጋራ ጉዳይ ሊኖርህ ይችላል? (2 ቆሮንቶስ 6:14–16) እንደ ውድ ነገር የምትቆጥራቸው መንፈሳዊ ነገሮች ለእነርሱ “ሞኝነት” ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 2:14) የምትመራበትን መሠረታዊ ሥርዓት ሳትጥስ ባልንጀሮች እንደሆናችሁ ልትኖሩ ትችላላችሁን?
9 ስለዚህ ጤናማ ካልሆነ ቅርርብ ራቅ። ቅርርብህን ይሖዋን ከልብ ከሚወዱና መንፈሳዊ አስተሳሰብ ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር ብቻ አድርግ። በጉባኤው ውስጥ ካሉ ስህተት ፈላጊ ከሆኑና የተቺነት መንፈስ ካላቸው ወጣቶች እንኳን ተጠንቀቅ። በመንፈሳዊ እያደግህ ስትሄድ የጓደኛ ምርጫህ እየተለወጠ ይሄድ ይሆናል። አንዲት በአሥራዎቹ ዓመታት የምትገኝ ምሥክር ልጃገረድ “ከተለያዩ ጉባኤዎች አዳዲስ ጓደኞች አግኝቻለሁ። ዓለማዊ ጓደኞች ምን ያህል የማያስፈልጉ እንደሆኑ እንድገነዘብ አስችሎኛል” ብላለች።
ከተሳሳቱ ምኞቶች ሽሽ
10, 11. (ሀ) “ከክፉ የጐልማሳነት ምኞት መሸሽ” ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) አንድ ሰው “ከዝሙት ሊሸሽ” የሚችለው እንዴት ነው?
10 በተጨማሪም ጳውሎስ “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ” በማለት ጢሞቴዎስን መክሮታል። በወጣትነት ዕድሜህ ዝነኛ ለመሆን፣ ለመፈንጠዝ፣ ወይም የጾታ ፍላጎትህን ለማርካት ያለህ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ይህን ዓይነቱን ምኞት ካልተቆጣጠርከው ወደ ኃጢአት ሊመራህ ይችላል። በዚህ ምክንያት ጳውሎስ ከጎጂ ምኞቶች እንድትሸሽ ማለትም ሕይወትህን የሚያሳጣ አደጋ ያጋጠመህን ያህል ሮጠህ እንድታመልጥ መክሮአል።a
11 ለምሳሌ ያህል የጾታ ምኞት በብዙ ክርስቲያን ወጣቶች ላይ መንፈሳዊ ውድቀት አስከትሎአል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” ሲል የሚመክረን በቂ ምክንያት ስላለው ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:18) አንድ ወንድና ሴት ለጋብቻ ተሳስበው ለመጠናናት የሚቀጣጠሩና አብረው የሚውሉ ከሆነ በቤት ውስጥ ወይም በቆመ መኪና ውስጥ ብቻቸውን እንደመሆን ያለውን ፈታኝ ሁኔታ በማስወገድ ከዝሙት ሊሸሹ ይችላሉ። አንድ በሰል ያለ ሰው አብሮአቸው እንዲኖር ማድረግ ዘመኑ ያለፈበት ነገር መስሎ ቢታይም ከአደጋ ሊጠብቃቸው ይችላል። አንዳንድ የፍቅር መግለጫዎች ተገቢ ሊሆኑ የሚችሉ ቢሆንም ንጹሕ ካልሆነ ጠባይ ለመራቅ ሲባል እንደነዚህ ባሉት የፍቅር መግለጫዎች ላይ ምክንያታዊ ገደብ ማበጀት ያስፈልጋል። (1 ተሰሎንቄ 4:7) በተጨማሪም ከዝሙት መሸሽ መጥፎ ፍላጎቶችን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ማስወገድን ይጨምራል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ሳትፈልጉት ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ሐሳብ ወደ አእምሮአችሁ የሚመጣ ከሆነ ወዲያው የምታስቡትን ነገር ለውጡ። ወጣ ብላችሁ በእግር መሄድ፣ ማንበብ ወይም የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ጀምሩ። በዚህ ረገድ ጸሎት ከፍተኛ እርዳታ ያበረክታል። — መዝሙር 62:8b
12. መጥፎ የሆነውን ነገር መጥላትን መማር የሚቻለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
12 ከሁሉ በላይ ደግሞ መጥፎ የሆነውን ነገር መጥላትን ወይም መጸየፍ መማር ያስፈልግሃል። (መዝሙር 97:10) በመጀመሪያ ላይ ሊያስደስት የሚችልን ነገር መጥላት የሚቻለው እንዴት ነው? ስለሚያስከትላቸው ውጤቶች በማሰብ ነው። “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳል።” (ገላትያ 6:7, 8) በስሜትህ ለመሸነፍ በምትፈተንበት ጊዜ ከሁሉ በላይ ይህ ድርጊት ይሖዋን እንዴት እንደሚያሳዝነው አስብ። (ከመዝሙር 78:41 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም የማይፈለግ እርግዝና ሊመጣ ወይም እንደ ኤድስ ያለ መጥፎ በሽታ ሊይዝህ እንደሚችል አስብ። በዚህ ምክንያት የሚደርስብህን የስሜት ቀውስና ውርደት አመዛዝን። ከዚህም በተጨማሪ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል። አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ብላለች:- “እኔና ባለቤቴ ከመገናኘታችን በፊት ከሌሎች ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽመናል። ዛሬ ሁለታችንም ክርስቲያኖች ብንሆንም ይህ የቀድሞ ተግባራችን በጋብቻችን ውስጥ ጥልና መቀናናት እንዲኖር ምክንያት ሆኖአል።” ቲኦክራቲካዊ መብቶችን የሚያሳጣህና ከክርስቲያን ጉባኤ ሊያስወግድህ የሚችል መሆኑም መዘንጋት የለበትም። (1 ቆሮንቶስ 5:9–13) ለጊዜያዊ ደስታ ይህን ሲባል ያህል ውድ ዋጋ መክፈል ተገቢ ነውን?
ከይሖዋ ጋር ያለንን የቅርብ ዝምድና መከታተል
13, 14. (ሀ) ከመጥፎ ነገር መሸሽ ብቻ በቂ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው ይሖዋን ማወቅን ሊከታተል የሚችለው እንዴት ነው?
13 ይሁን እንጂ ከክፉ መሸሽ ብቻውን በቂ አይሆንም። ጢሞቴዎስ “ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን” እንዲከታተል ጭምር ተመክሮአል። ይህም ጠንካራ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታል። ነቢዩ ሆሴዕ ከዳተኛ ለነበረው የእስራኤል ብሔር ተመሳሳይ ልመና አቅርቦአል። “ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እንመለስ፤ . . . እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] እንከተል።” (ሆሴዕ 6:1–3) አንተስ ይህን ተከታትለሃልን? በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ከወላጆችህ ጋር ወደ መስክ አገልግሎት መሄድ ብቻውን አይበቃም። አንዲት ክርስቲያን ሴት እንዲህ ብላለች:- “ወላጆቼ በእውነት ውስጥ አሳድገውኛል። የተጠመቅሁትም ገና በልጅነቴ ነው። . . . ከስብሰባ ቀርቼ አላውቅም፣ ሳላገለግል ያሳለፍኩት ወር የለም። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና ኖሮኝ አያውቅም።”
14 ሌላይቱ ወጣት ደግሞ ይሖዋን የምትመለከተው ተጨባጭ እንዳልሆነ መንፈስ አድርጋ እንጂ እንደ ወዳጅዋና እንደ አባትዋ አድርጋ እንደማታውቀው ተናግራለች። ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት ፈጽማ በ18 ዓመት ዕድሜዋ የዲቃላ እናት ሆነች። አንተም ይህን የመሰለ ስህተት አትሥራ። ሆሴዕ እንደመከረው “እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን [ይሖዋን አዓት] እንከተል።” በየቀኑ በመጸለይና አካሄድህን ከይሖዋ ጋር በማድረግ ይሖዋን የምሥጢር ወዳጅህ ለማድረግ ትችላለህ። (ከሚክያስ 6:8 ጋር አወዳድር፤ ኤርምያስ 3:4 አዓት) ከፈለግነው “እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም።” (ሥራ 17:27) ስለዚህ የማይቋረጥ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ያለው ጥናት የተንዛዛ ወይም ረዥም መሆን አያስፈልገውም። ሜለዲ የተባለች ወጣት ልጃገረድ “በየቀኑ ለ15 ደቂቃ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ አነባለሁ” ብላለች። እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ መጽሔት እትም የምታነብበትን ጊዜ መድብ። ሌሎችን ‘ለፍቅርና ለበጎ ሥራ ለማነቃቃት’ እንድትችል ለጉባኤ ስብሰባዎች ተዘጋጅ። — ዕብራውያን 10:24, 25
ልባችሁን ለወላጆቻችሁ ስጡ
15. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ ወላጆችን መታዘዝ አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አብዛኛውን ጊዜ መታዘዝ ለወጣቱ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?
15 ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆች ከፍተኛ እርዳታና ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንተ ሊኖርህ የሚገባውን ድርሻ መዘንጋት የለብህም። “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትዕዛዝ ናት።” (ኤፌሶን 6:1–3) እርግጥ ዕድሜህ እየጨመረ በመሄዱ ተጨማሪ ነፃነት ለማግኘት ትፈልግ ይሆናል። በተጨማሪም የወላጆችህን የአቅም ውስንነት በይበልጥ እየተገነዘብህ መጥተህ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋችን አባቶች . . . መልካም ሆኖ እንደታያቸው” የሚቻላቸውን ያህል እንዳደረጉልን ተናግሮአል። (ዕብራውያን 12:10) ቢሆንም በአጠቃላይ ሲታይ እነርሱን ብትታዘዝ የኋላ ኋላ ትጠቀማለህ። ወላጆችህ ከማንም ይበልጥ ይወዱሃል፤ ያውቁህማል። ሁልጊዜ በሐሳባቸው የማትስማማ ብትሆንም እንኳን ከልባቸው የሚያስቡት ለአንተ የሚበጀውን ነው። አንተን “በጌታ [በይሖዋ አዓት] ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ለምን ትቃወማለህ? (ኤፌሶን 6:4) በእውነትም “የአባቱን ተግሣጽ የሚንቅ” ሞኝ ሰው ብቻ ነው። (ምሳሌ 15:5) ጠቢብ የሆነ ወጣት የወላጆቹን ሥልጣን ይቀበላል፤ ተገቢ አክብሮትም ይሰጣል። — ምሳሌ 1:8
16. (ሀ) ወጣቶች ችግራቸውን ከወላጆቻቸው ቢደብቁ ጥበብ የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ወጣት ከወላጆቹ ጋር ያለውን የሐሳብ ግንኙነት እንዴት ሊያሻሽል ይችላል?
16 ይህም ለወላጆች እውነቱን መናገርን፣ ስለ እውነት እንድትጠራጠር የሚያደርግህ ጥያቄ ቢኖርህ ወይም አጠያያቂ ድርጊት ብትፈጽም ወይም ይህን የመሰለ ሌላ ችግር ቢያጋጥምህ ወላጆችህ እንዲያውቁት ማድረግን ይጨምራል። (ኤፌሶን 4:25) እንደነዚህ ያሉትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከወላጆች መሸሸግ ሌሎች ተጨማሪ ችግሮችን ይፈጥራል። (መዝሙር 26:4) አንዳንድ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ለማድረግ እምብዛም ጥረት የማያደርጉ መሆናቸው አይካድም። አንዲት ወጣት ልጃገረድ “እናቴ አረፍ ብላ አነጋግራኝ አታውቅም። ትነቅፈኛለች ብዬ ስለምፈራ የሚሰማኝን ለመናገር ድፍረት አግኝቼ አላውቅም” ስትል አማርራለች። አንተም ይህን የሚመስል ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ተስማሚ የሆነውን ጊዜ በጥበብ ምረጥና ምን እንደሚሰማህ ለወላጆችህ ግለጥ። ምሳሌ 23:26 “ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ” በማለት ይመክራል። ችግሮች አድገው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት የሚያሳስብህን ነገር ከወላጆችህ ጋር ተወያይ።
ጽድቅን በመከታተል ቀጥል!
17, 18. አንድ ወጣት ጽድቅን በመከታተል እንዲቀጥል የሚረዳው ምንድን ነው?
17 ጳውሎስ በሁለተኛ ደብዳቤው መደምደሚያ አካባቢ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር” በማለት ጢሞቴዎስን መክሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14) አንተም እንዲሁ ማድረግ ይኖርብሃል። ማንም ሆነ ምንም ነገር ጽድቅን ከመከታተል መንገድ አስቶ እንዲያስወጣህ አትፍቀድ። የሰይጣን ዓለም በርካታ ማታለያዎች ያሉት ቢሆንም በክፋት የተሞላ ነው። በቅርቡ ይህ ዓለምና የዓለም ክፍል የሆኑ ሁሉ ፈጽመው ይወድማሉ። (መዝሙር 92:7) ከሰይጣን ጭፍሮች ጋር እንዳትጠፋ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
18 ይህንንም ለማድረግ እንዲቻልህ ዘወትር ግቦችህን፣ ፍላጎቶችህንና ምኞቶችህን መመርመር ይኖርብሃል። ራስህን ‘ወላጆቼና የጉባኤ አባሎች በሌሉበት ቦታ ስሆን ከፍተኛ የሆነ የአነጋገርና የሥነ ምግባር ደረጃ እጠብቃለሁን? የምመርጣቸው ጓደኞች እንዴት ያሉ ናቸው? አለባበሴና አጋጌጤ የሚወሰነው በዕድሜ እኩዮቼ አለባበስ ነውን? ለራሴ ምን ዓይነት ግብ አውጥቼአለሁ? ልቤ ያተኮረው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ነው ወይስ በሚሞተው የሰይጣን ዓለም ውስጥ በሚገኝ ከፍተኛ ሥራና ቦታ?’ ብለህ ጠይቅ።
19, 20. (ሀ) አንድ ወጣት ይሖዋ ያወጣቸው ብቃቶች በጣም ከባድ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ወጣቶች በየትኞቹ ዝግጅቶች ሊጠቀሙ ይችላሉ?
19 ምናልባት በአስተሳሰብህ ረገድ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልገህ ትገነዘብ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ይህ በጣም ከባድ እንደሆነ አድርገህ በማሰብ አትደናገጥ። ይሖዋ ምክንያታዊ ያልሆነ ነገር እንደማይጠብቅብህ አስታውስ። ነቢዩ ሚክያስ “እግዚአብሔርም [ይሖዋም አዓት] ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትህትና [ቦታህን አውቀህ አዓት] ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ሲል ጠይቆአል። (ሚክያስ 6:8) ይሖዋ አንተን ለመርዳት ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች የምትጠቀም ከሆነ ይህን ማድረግ አስቸጋሪ አይሆንብህም። ከወላጆችህ ጋር ተቀራረብ። ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ዘወትር ግንኙነት አድርግ። በተለይ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በቅርብ ለመተዋወቅ ጥረት አድርግ። ስለደህንነትህ አጥብቀው ስለሚያስቡ የድጋፍና የመጽናናት ምንጭ ሊሆኑልህ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2) ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ አምላክ ጋር የተቀራረበና ሞቅ ያለ ዝምድና እንዲኖርህ ጥረት አድርግ። እርሱም ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለመከታተል የሚያስችልህን ኃይልና ፍላጎት ይሰጥሃል።
20 ይሁን እንጂ አንዳንድ ወጣቶች ጤናማ ያልሆነ ሙዚቃ በመስማት መንፈሳዊ ዕድገት ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት አደጋ ላይ ይጥላሉ። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኩራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ሽሽ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ማርያምና ዮሴፍ ከሄሮድስ የግድያ ሴራ ለማምለጥ ወደ ግብጽ እንዲሸሹ በተነገረበት በማቴዎስ 2:13 ላይ ተሠርቶበታል። — ከማቴዎስ 10:23 ጋር አወዳድር።
b የጾታ ፍላጎትን ስለመቆጣጠር የወጣቶች ጥያቄዎችና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው በተባለው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በሚዘጋጀው መጽሐፍ በምዕራፍ 26 ላይ በርካታ ሐሳቦችን ለማግኘት ትችላለህ።
ታስታውሳለህን?
◻ በተለይ ወጣቶች ለሰይጣን የተንኮል ዘዴዎች የተጋለጡ የሆኑት ለምንድን ነው?
◻ ከዓለማዊ ወጣቶች ጋር በጣም መቀራረብ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?
◻ ከጾታ ርኩሰት ለመሸሽ የሚቻለው እንዴት ነው?
◻ ከይሖዋ ጋር ያለህን የተቀራረበ ዝምድና ለመከታተል የምትችለው እንዴት ነው?
◻ ከወላጆችህ ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለጋብቻ ተሳስበው ለመጠናናት የሚፈልጉ ወንዶችና ሴቶች ራሳቸውን ከሌሎች በማያገል አካባቢ ሆነው ጥበብ ባለበት ሁኔታ እርስ በርስ ይተዋወቃሉ