‘ከይሖዋ ቀን’ በሕይወት መትረፍ
“የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል?”—ኢዩኤል 2:11
1. ‘አስፈሪው የይሖዋ ቀን’ የደስታ ወቅት መሆን ያለበት ለምንድን ነው?
“የሚያስፈራ”! ነቢዩ ኢዩኤል ‘የይሖዋን ቀን’ የገለጸው እንዲህ በማለት ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋን የምንወድና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ራሳችንን ለእርሱ የወሰንን ሁሉ የይሖዋ ቀን እየቀረበ ሲመጣ በፍርሃት መርበድበድ አይኖርብንም። ይህ ቀን አስፈሪ እንደሚሆን እሙን ነው። ሆኖም ታላቅ መዳን የሚገኝበትና በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጆችን ሲያሠቃይ ከኖረው ከዚህ የነገሮች ሥርዓት የምንገላገልበት ጊዜ ነው። ይህንን ቀን በማስመልከት ኢዩኤል ‘አምላክ ታላቅ ነገርን ስላደረገ የአምላክ ሕዝቦች ደስ እንዲላቸውና እልል እንዲሉ’ ጥሪ ካቀረበ በኋላ አክሎም ‘የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል’ በማለት ዋስትና ይሰጣል። ከዚያም በአምላክ መንግሥት ዝግጅት ውስጥ “መድኃኒት ይገኛል [“የሚድኑ ይገኛሉ፣” NW]። ደግሞም እግዚአብሔር የጠራቸው፣ የምሥራች የሚሰበክላቸው ይገኛሉ።”—ኢዩኤል 2:11, 21, 22, 32
2. በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ (ሀ) ‘በጌታ ቀን’ ውስጥ (ለ) ‘በይሖዋ ቀን’ ላይ ምን ነገሮች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ?
2 አስፈሪ የሆነው የይሖዋ ቀን በራእይ 1:10 ላይ ከተገለጸው ‘ከጌታ ቀን’ ጋር ሊምታታብን አይገባም። ‘የጌታ ቀን’ ከራእይ ምዕራፍ 1 እስከ 22 ድረስ ያሉትን የ16ቱን ራእዮች ፍጻሜ የሚያጠቃልል ነው። ይህ ጊዜ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና [“የመገኘትህና፣” NW] የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” በማለት ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ በሰጠበት ወቅት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ ይጨምራል። ዓለም ላይ የታየው አስከፊ ‘ጦረነቶች፣ ረሃብ፣ ጥላቻ፣ ቸነፈርና ዓመፅ’ ኢየሱስ በሰማያዊ ሥልጣን መገኘቱን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች ናቸው። እነዚህ አስከፊ ሁኔታዎች እየተበራከቱ በሄዱ መጠን ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህን የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ” እንዲሰብኩ ዘመናዊ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ ፈሪሃ አምላክ ላላቸው ሰዎች መጽናኛ የሚያገኙበትን መንገድ ከፍቶላቸዋል። ከዚያም የጌታ ቀን የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃው ላይ በሚደርስበት ጊዜ የዚህ የነገሮች ሥርዓት “መጨረሻው” ማለትም አስፈሪው የይሖዋ ቀን ይፈነዳል። (ማቴዎስ 24:3-14፤ ሉቃስ 21:11) ይህም ብልሹ በሆነው የሰይጣን ዓለም ላይ ይሖዋ ፈጣን የሆነ የጥፋት ፍርድ የሚያስፈጽምበት ቀን ይሆናል። “ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ . . . ይሆናል።”—ኢዩኤል 3:16
ይሖዋ በኖኅ ዘመን እርምጃ ወሰደ
3. በዛሬው ጊዜ ያለው ሁኔታ በኖኅ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንዴት ነው?
3 በዛሬው ጊዜ ያለው የዓለም ሁኔታ ከ4,000 ዓመት በፊት ‘በኖኅ ዘመን’ ከነበረው የዓለም ሁኔታ ጋር በብዙ መልኩ ይመሳሰላል። (ሉቃስ 17:26, 27) በዘፍጥረት 6:5 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደ ሆነ አየ።” በዛሬው ጊዜ ካለው ዓለም ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው! ክፋት፣ ስግብግብነትና ፍቅር የለሽነት በሁሉም ቦታ ተንሰራፍቶ ይገኛል። አንዳንድ ጊዜ የሰዎች የሥነ ምግባር ዝቀት ወደ መጨረሻ ደረጃው ላይ ደርሷል ብለን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የመጨረሻውን ቀን’ በማስመልከት የተናገረው “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” የሚለው ትንቢት መፈጸሙን ገና ይቀጥላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13
4. የሐሰት አምልኮ በቀድሞዎቹ ዘመናት ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?
4 ሃይማኖት በኖኅ ዘመን ለነበረው የሰው ዘር እፎይታ ማምጣት ችሎ ነበርን? ከዚህ በተቃራኒ በዚያን ጊዜ የነበረው ከሃዲ ሃይማኖት በጊዜው ለደረሰው ብልሽት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ‘ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለው የቀደመው እባብ’ ላቀረበው የሐሰት ትምህርት እጃቸውን ሰጡ። ከአዳም ሁለተኛ ትውልድ ላይ ስሙን ለማጉደፍ ሳይሆን አይቀርም “በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ስም መጠራት ተጀመረ።” (ራእይ 12:9፤ ዘፍጥረት 3:3-6፤ 4:26) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለአምላክ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ከማቅረብ ያፈነገጡት ዓመፀኛ መላእክት መልከ መልካም ከሆኑት ከሰው ሴቶች ልጆች ጋር ሕገ ወጥ የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ሥጋዊ አካል ለብሰው መጡ። እነዚህ ሴቶች ኔፍሊም የተባሉ ግዙፍ ዲቃሎችን ወለዱ። እነርሱም ሰዎችን የሚጨቁኑና የሚያሠቃዩ ጉልበተኞች ሆኑ። በእነዚህ አጋንንታዊ ተጽዕኖ ሥር የነበረው ‘ሥጋ የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር።’—ዘፍጥረት 6:1-12
5. ኢየሱስ በኖኅ ዘመን የተከናወኑ ነገሮችን በመጥቀስ ምን የማስጠንቀቂያ ምክሮች ሰጥቶናል?
5 ሆኖም አንድ ቤተሰብ ለይሖዋ የነበረውን የጸና አቋም ጠብቋል። በዚህም የተነሳ አምላክ “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ” አወረደ። (2 ጴጥሮስ 2:5) ይህ የጥፋት ውኃ ዛሬ ያለው የነገሮች ሥርዓት ለሚያበቃበት ለአስፈሪው የይሖዋ ቀን ጥላ ነው፤ ኢየሱስ ይህን በተመለከተ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል:- “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፣ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፣ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:36-39) በአሁኑ ጊዜ እኛም ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ ላይ ስለምንገኝ ኢየሱስ ‘ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድንችል ስንጸልይ ሁልጊዜ ትጉ እንድንሆን’ አጥብቆ አሳስቧል።—ሉቃስ 21:34-36
ይሖዋ በሰዶምና ጎሞራ ላይ ያስፈጸመው የቅጣት ፍርድ
6, 7. (ሀ) በሎጥ ዘመን የተከሰቱት ነገሮች ለምን ነገር ጥላ ናቸው? (ለ) ይህ ለእኛ ምን ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ይዞልናል?
6 የጥፋት ውኃው ከሆነ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ፣ የኖኅ ዝርያዎች በምድር ላይ በዝተው ሳሉ ታማኙ አብርሃምና የወንድሙ ልጅ ሎጥ በሌላ ጊዜ ደርሶ ለነበረው አስፈሪ የይሖዋ ቀን የዓይን ምሥክር ሆነው ነበር። ሎጥና ቤተሰቡ ሰዶም ተብላ በምትጠራ ከተማ ይኖሩ ነበር። ይህች ከተማና አጎራባቿ የሆነችው ገሞራ ጸያፍ በሆኑ የጾታ ብልግና ድርጊቶች ተበክለው ነበር። ፍቅረ ነዋይም አንዱ የሰዎችን ሕይወት የሚቆጣጠር ነገር ነበር። ሌላው ቀርቶ የሎጥን ሚስት ሕይወት ጭምር ነክቷል። ይሖዋ “የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፣ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና” በማለት ለአብርሃም ነገረው። (ዘፍጥረት 18:20) በከተሞቹ ውስጥ ለሚኖሩ ጻድቅ ሰዎች ሲል ከተሞቹን እንዳያጠፋቸው አብርሃም ይሖዋን ተማጸነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ አሥር ጻድቅ ሰዎች እንኳ በዚያ ሊያገኝ እንዳልቻለ ተናገረ። ከአምላክ የተላኩ መላእክት ሎጥና ሁለት ሴት ልጆቹ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ዞዓር ወደሚባል ከተማ ሸሽተው እንዲያመልጡ ረዷቸው።
7 ከዚያስ ምን ነገር ተከተለ? እኛ ያለንበትን “የመጨረሻ ቀን” ከሎጥ ዘመን ጋር በማወዳደር ሉቃስ 17:28-30 “እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ። የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል” በማለት ይዘግባል። በዚያ አስፈሪ የይሖዋ ቀን በሰዶምና ገሞራ ላይ የደረሰው ከባድ ጥፋት በዚህ በኢየሱስ መገኘት ዘመን ለምንኖር ለእኛ ግልጽ የሆነ ማስጠንቀቂያ ያስተላልፋል። በጊዜያችን የሚኖረው የሰው ዘርም ‘ዝሙትን የሚያደርግና ሌላን ሥጋ የሚከተል’ ነው። (ይሁዳ 7) ከዚህም በላይ በጊዜያችን የሚፈጸመው ልቅ የጾታ ብልግና ኢየሱስ በዘመናችን እንደሚፈጸሙ አስቀድሞ ለተናገረው የተለያዩ ‘ቸነፈሮች’ መከሰት ምክንያት ሆኗል።—ሉቃስ 21:11
እስራኤል “ዐውሎ ነፋስን” ያጭዳል
8. እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን የጠበቁት እስከ ምን ድረስ ነበር?
8 የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ይሖዋ “ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት . . . የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ” እንዲሆኑት እስራኤላውያንን መረጠ። ሆኖም ይህ ሁኔታ ተጠብቆ የሚቆየው ‘ቃሉን በእውነት እስከ ሰሙና ኪዳኑንም እስከ ጠበቁ’ ድረስ ብቻ ነው። (ዘጸአት 19:5, 6) ይህን ታላቅ መብት አክብረው ይዘው ነበር? በፍጹም! እርግጥ ነው በሕዝቡ መካከል ይኖሩ የነበሩ እንደ ሙሴ፣ ሳሙኤል፣ ዳዊት፣ ኢዮሳፍጥ፣ ሕዝቅያስ፣ ኢዮስያስ እንዲሁም ራሳቸውን የወሰኑ ወንድና ሴት ታማኝ ነቢያትን የመሰሉ ግለሰቦች ከአቋማቸው ዝንፍ ሳይሉ ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ሕዝቡ ታማኝ ሳይሆን ቀርቷል። ውሎ አድሮ መንግሥቱ እስራኤልና ይሁዳ ተብሎ ለሁለት ተከፈለ። ሁለቱም ሕዝቦች አረመኔአዊ በሆነ አምልኮና በጎረቤት አገር ይፈጸሙ በነበሩ አምላክን በማያስከብሩ ልማዶች ተተበተቡ።—ሕዝቅኤል 23:49
9. ይሖዋ ዓመፀኛ በሆነው በአሥሩ ነገድ መንግሥት ላይ ፍርዱን ያስፈጸመው እንዴት ነበር?
9 ታዲያ ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውነው እንዴት ነው? ይሖዋ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ በዚያን ጊዜም ጥፋት ከማምጣቱ በፊት ማስጠንቀቂያ አስነግሯል። ይህም አሞጽ “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” በማለት ከገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። አሞጽ ራሱ “የእግዚአብሔርን ቀን ለምን ትፈልጋላችሁ? ጨለማ ነው እንጂ ብርሃን አይደለም” በማለት ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የሚደርስበትን ወዮታ አውጇል። (አሞጽ 3:7፤ 5:18) በተጨማሪም እንደ አሞጽ ነቢይ የነበረው ሆሴዕ “ነፋስን ዘርተዋል፣ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ” በማለት ተናግሯል። (ሆሴዕ 8:7) በ740 ከዘአበ ይሖዋ ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት የአሦራውያንን ጦር ተጠቅሟል።
ይሖዋ በከዳተኛዋ ይሁዳ ላይ የወሰደው የጥፋት እርምጃ
10, 11. (ሀ) ይሖዋ ይሁዳን ይቅር ለማለት ያልፈለገው ለምን ነበር? (ለ) ሕዝቡ በምን አጸያፊ ነገሮች ተበክሎ ነበር?
10 በተጨማሪም ይሖዋ ወደ ደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ነቢያቱን ልኳል። ይሖዋ ይህን ቢያደርግም እንኳ እንደ ምናሴና በእርሱ እግር እንደተተካው እንደ አሞን የመሳሰሉ የይሁዳ ነገሥታት ‘ብዙ ንጹሕ ደም በማፍሰስ፣ ጣዖታትን በማምለክና ለጣዖታት በመስገድ’ በይሖዋ ፊት ክፉ ነገር ማድረጋቸውን ቀጥለው ነበር። ምንም እንኳ የአሞጽ ልጅ የነበረው ኢዮስያስ በይሖዋ ፊት ቅን ነገር ያደረገ ቢሆንም ከእርሱ በኋላ የነገሡት ነገሥታትም ሆኑ ሕዝቡ እንደገና ክፉ ነገር ማድረጋቸውን በመቀጠላቸው የተነሳ “እግዚአብሔር ይራራ ዘንድ አልወደደም።”—2 ነገሥት 21:16-21፤ 24:3, 4
11 ይሖዋ በነቢዩ ኤርምያስ በኩል “የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤ ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፣ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፣ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?” በማለት ተናግሯል። የይሁዳ ብሔር ከመጠን በላይ የደም ባለ ዕዳ ሆኖ ነበር፤ እንዲሁም ሕዝቡ በሥርቆት፣ በነፍስ ግድያ፣ በጾታ ብልግና፣ በሐሰት በመማል፣ ባዕድ አማልክትን በማምለክና በሌሎች አጸያፊ ተግባሮች ቆሽሸው ነበር። የአምላክ ቤተ መቅደስ “የሌቦች ዋሻ” ሆኖ ነበር።—ኤርምያስ 2:34፤ 5:30, 31፤ 7:8-12
12. ይሖዋ ከዳተኛይቱን ኢየሩሳሌምን የቀጣው እንዴት ነበር?
12 ይሖዋ “ከሰሜን [ከከለዳውያን] ክፉ ነገርንና ጽኑ ጥፋትን አመጣለሁ” በማለት ገለጸ። (ኤርምያስ 4:6) ልክ እንዳለውም ከዳተኛ የሆነችውን ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን ለመደምሰስ በጊዜው “የምድር ሁሉ መዶሻ” የነበረውን ባቢሎናዊውን የዓለም ኃያል መንግሥት አመጣባቸው። (ኤርምያስ 50:23) በ607 ከዘአበ ከተማዋ በጽኑ ከተከበበች በኋላ ኃያል በሆነው የናቡከደነፆር ሠራዊት እጅ ወደቀች። “የባቢሎንም ንጉሥ [የንጉሥ] ሴዴቅያስን ልጆች በዓይኑ ፊት በሪብላ ገደላቸው፤ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን ከበርቴዎች ሁሉ ገደለ። የሴዴቅያስንም ዓይን አወጣ፣ ወደ ባቢሎንም ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው። ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፣ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ ወደ እርሱም የኮበለሉትን ሰዎች የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማረካቸው።”—ኤርምያስ 39:6-9
13. በ607 ከዘአበ ከደረሰው የይሖዋ ቀን የዳኑት እነማን ናቸው? ለምንስ?
13 በእርግጥም እጅግ አስፈሪ ቀን ነበር! ሆኖም ከዚያ አስፈሪ የጥፋት ፍርድ ከዳኑት ሰዎች መካከል ለይሖዋ ታዛዥ የነበሩ ጥቂት ነፍሳት ይገኙበታል። ከእነርሱም መካከል ከአይሁዳውያን በተለየ መንገድ የትሕትናና የታዛዥነት መንፈስ ያሳዩት እስራኤላዊ ያልነበሩት ሬካባውያን ይገኙበታል። እንዲሁም ኤርምያስን ጭቃ ከሞላበት ጉድጓድ በማውጣት ከሞት ያዳነው ታማኙ ጃንደረባ አቤሜሌክና የኤርምያስ ታማኝ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ድነዋል። (ኤርምያስ 35:18, 19፤ 38:7-13፤ 39:15-18፤ 45:1-5) ይሖዋ “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” በማለት የተናገረው እንደነዚህ ላሉት ሰዎች ነበር። ንጉሥ ቂሮስ በ539 ከዘአበ ባቢሎናውያንን ድል በማድረግ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸውን አይሁዳውያን ነፃ ባወጣና የኢየሩሳሌምን ከተማና ቤተ መቅደስ ለመገንባት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባደረገ ጊዜ ይህ የተስፋ ቃል የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቶ ነበር። በዛሬው ጊዜም ባቢሎናዊ ከሆነ ሃይማኖት ወጥተው ወደ ይሖዋ ንጹህ አምልኮ የተመለሱ ሰዎች ይሖዋ መልሶ በሚያቋቁመው ገነት ውስጥ የሚኖረውን ሰላም የሰፈነበትን ክብራማ የወደፊት ተስፋ አሻግረው ሊመለከቱ ይችላሉ።—ኤርምያስ 29:11፤ መዝሙር 37:34፤ ራእይ 18:2, 4
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የደረሰው “ታላቅ መከራ”
14. ይሖዋ እስራኤልን ለዘለቄታው የተወው ለምንድን ነው?
14 እስቲ አሁን ትኩረታችንን ወደ መጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ዞር እናድርግ። በዚያን ጊዜ ወደ አገራቸው ተመልሰው የነበሩት አይሁዳውያን እንደገና ከዳተኞች ሆነው ነበር። ይሖዋ አንድያ ልጁን ወደ ምድር የላከው የእርሱ ቅቡዕ ወይም መሲህ እንዲሆን ነበር። ከ29 እስከ 33 እዘአ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ በእስራኤል ምድር ሁሉ ሰበከ። (ማቴዎስ 4:17) ከዚህም በተጨማሪ የመንግሥቱን ምሥራች በማወጁ ሥራ ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ ደቀ መዛሙርትን አሰባስቦ አሰለጠነ። ታዲያ የአይሁድ መሪዎች ለዚህ ምን ምላሽ ሰጡ? በኢየሱስ ላይ የሐሰት ወሬ ከነዙ በኋላ በመከራ እንጨት ላይ አሠቃቂ በሆነ መንገድ እንዲሞት በማድረግ ከሁሉ የከፋ ወንጀል ፈጸሙ። ይሖዋ አይሁዳውያንን እንደ ሕዝቦቹ አድርጎ መመልከቱን ተወ። በዚህ ጊዜ ግን ይህ ሕዝብ ተቀባይነት ያጣው ለዘለቄታው ነበር።
15. ከክፉ ሥራቸው ንስሐ የገቡት አይሁዳውያን ምን ነገር እንዲፈጽሙ መብት ተሰጣቸው?
15 ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን አፈሰሰ። ይህም ደቀ መዛሙርቱ ለአይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት ለተለወጡት ሰዎች በልሳን እንዲናገሩ ኃይል ሰጣቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ . . . እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ” በማለት ለተሰበሰበው ሕዝብ ተናገረ። ታዲያ ቅን የሆኑት አይሁዳውያን ምን ዓይነት ምላሽ ሰጡ? “ልባቸው ተነካ”፤ ከኃጢአታቸውም ንስሐ ገቡና ተጠመቁ። (ሥራ 2:32-41) የመንግሥቱ ስብከት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ሄዶ በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” ተዳረሰ።—ቆላስይስ 1:23
16. ይሖዋ በሥጋዊ እስራኤል ላይ ፍርዱን ለማስፈጸም ሲል ሁኔታዎችን ያቀነባበረው እንዴት ነው?
16 አሁን ይሖዋ በተዋቸው ሕዝቡ ማለትም በሥጋዊ እስራኤል ላይ የጥፋት ፍርዱን የሚያስፈጽምበት ጊዜ ደረሰ። በዚያን ጊዜ ይታወቅ ከነበረው ዓለም የተውጣጡ በሺህ የሚቆጠሩ ሕዝቦች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ በመጉረፍ መንፈሳዊ ‘የአምላክ እስራኤል’ እንዲሆኑ ተቀቡ። (ገላትያ 6:16) በዚያን ጊዜ የነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ ጥላቻ በተሞላበት አካሄድና በቡድን ዓመፅ ተውጦ ነበር። ጳውሎስ ‘በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣናት መገዛትን’ አስመልክቶ የጻፈውን በመቃረን በወቅቱ ይገዛ በነበረው የሮማ መንግሥት ላይ በይፋ ዓምፀዋል። (ሮሜ 13:1) ከዚያ በኋላ የደረሰውን ክንውን ይሖዋ ራሱ ያቀነባበረው ይመስላል። በ66 እዘአ በጄኔራል ጋለስ ይመራ የነበረው የሮማ የጦር ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ለመክበብ ወደፊት ገሰገሰ። ጥቃት የሰነዘሩት ሮማውያን ወደ ከተማዋ ዘልቀው ገብተው የቤተ መቅደሱን ግድግዳ እስከ መሰርሰር ደርሰው ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደዘገበው በእርግጥም በከተማውና በሕዝቡ ላይ መከራ ደርሶ ነበር።a ይሁን እንጂ በድንገት ጥቃት የሰነዘረው ሠራዊት ወደኋላ አፈገፈገ። ይህም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ማቴዎስ 24:15, 16 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው በኢየሱስ የማስጠንቀቂያ ትንቢት መሠረት ‘ወደ ተራራዎች’ ሸሽተው ማምለጥ እንዲችሉ አጋጣሚ ከፈተላቸው።
17, 18. (ሀ) ይሖዋ በአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ ፍትሃዊ የቅጣት ፍርዱን ያስፈጸመው የትኛውን መከራ በማምጣት ነው? (ለ) ‘የዳነው’ ሥጋ ምንድን ነው? ይህስ ለምን ነገር ጥላ ይሆናል?
17 ይሁን እንጂ በመከራው መደምደሚያ ላይ የሚፈጸመው የመጨረሻው የይሖዋ የጥፋት ፍርድ ገና ወደፊት የሚመጣ ነበር። በ70 እዘአ የሮማ የጦር ሠራዊት በጄኔራል ቲቶ እየተመራ ጥቃት ለመሰንዘር ተመልሶ መጣ። በዚህ ጊዜ የተካሄደው ፍልሚያ የማያዳግም ነበር! እርስ በርሳቸው ሳይቀር ይዋጉ የነበሩት አይሁዳውያን ሮማውያንን ለመቋቋም የማይችሉ ነበሩ። ከተማዋና የከተማዋ ቤተ መቅደስ ፍርስርሳቸው ወጣ። ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ረሃብ ያመነመናቸው አይሁዳውያን ተሠቃይተው ሞቱ። ወደ 600,000 የሚጠጋ አስከሬን ከከተማው ውጪ ተጣለ። ከተማዋ ከወደቀች በኋላ 97,000 አይሁዳውያን በምርኮ ተወሰዱ። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በግላዲያተር የትርዒት ማሳያ ሥፍራ ሕይወታቸው አልፏል። ከእነዚያ የመከራ ዓመታት በሕይወት የዳኑ ሥጋ ለባሾች ቢኖሩ ከዮርዳኖስ ባሻገር ወዳሉት ተራራዎች የሸሹ ታዛዥ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው።—ማቴዎስ 24:21, 22፤ ሉቃስ 21:20-22
18 ስለዚህ ኢየሱስ ስለ “ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” የተናገረው ታላቅ ትንቢት በይሖዋ ቀን ማለትም ከ66-70 እዘአ በዓመፀኛው የአይሁድ ብሔር ላይ በተወሰደው ፍትሃዊ እርምጃ የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ማቴዎስ 24:3-22) ሆኖም ይህ በአሁኑ ጊዜ ባለው ዓለም ላይ ለሚደርሰው የመጨረሻ መከራ ማለትም ‘ለታላቁና ለሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን’ እንደ ጥላ ሆኖ የሚያገለግል ብቻ ነው። (ኢዩኤል 2:31) ታዲያ ከዚህ ቀን ‘መዳን’ የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይነግረናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከተማዋን የከበበው አጥቂው የሮማ ሠራዊት ቅጥሩን በከፊል ከሰረሰሩ በኋላ በይሖዋ ቤተ መቅደስ በር እሳት ለመለኮስ ተቃርበው እንደነበር ጆሴፈስ ዘግቧል። እዚያው እንዳሉ የተከበቡት ብዙዎቹ አይሁዶች ይህን ሁኔታ ሲመለከቱ ከባድ እልቂት እንደሚጠብቃቸው በመገንዘብ ታላቅ ፍርሃት ወደቀባቸው።—ዎርስ ኦቭ ዘ ጁውስ፣ ሁለተኛ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 19
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ “የጌታ ቀን” ‘ከይሖዋ ቀን’ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
◻ የኖኅን ዘመን መለስ ብለን በመመልከት የትኛውን ማስጠንቀቂያ መከተል ይኖርብናል?
◻ የሰዶምና ገሞራ ሁኔታ ኃይለኛ ትምህርት የያዘው እንዴት ነው?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከደረሰው “ታላቅ መከራ” የዳኑት እነማን ናቸው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋ ለኖኅና ለሎጥ ቤተሰቦች እንዲሁም በ607 ከዘአበ እና በ70 እዘአ ለነበሩት ሰዎች መዳን የሚያገኙበትን መንገድ አዘጋጅቷል