የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 29—ኢዩኤል
ጸሐፊው:- ኢዩኤል
የተጻፈበት ቦታ:- ይሁዳ
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት በ820 ገደማ (?)
የአንበጦች መንጋ ተመላልሶ በመምጣት ምድሪቱን ባድማ ያደርጋታል። ከአንበጦቹ መንጋ ፊት ያለው እሳትና ከበስተኋላቸው የሚከተለው ነበልባል የማያዳግም ጥፋት ያስከትላል። በሁሉም ቦታ ረሀብ ይኖራል። ታላቁና አስፈሪው የይሖዋ ቀን በጣም ስለቀረበ ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። ይሖዋ፣ ማጭዱን በመስደድ ብሔራትን ለጥፋት እንዲሰበስቡ ትእዛዝ ይሰጣል። ይሁን እንጂ ከዚህ ጥፋት ‘የሚድኑ’ ሰዎች ይኖራሉ። (ኢዩ. 2:32) የኢዩኤል ትንቢት እንደነዚህ ያሉ አስደናቂ ክስተቶች የተገለጹበት በመሆኑ ትኩረታችንን የሚስብና ከፍተኛ ጥቅም ያለው መጽሐፍ ነው።
2 መጽሐፉ “ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቃል” በማለት ይጀምራል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢዩኤል ከዚህ የበለጠ የሚናገረው ነገር የለም። በመጽሐፉ ውስጥ ትኩረት የተሰጠው ለትንቢታዊው መልእክት እንጂ ለጸሐፊው አይደለም። “ኢዩኤል” (በዕብራይስጥ ዮሄል) የሚለው ስም ትርጉሙ “ይሖዋ አምላክ ነው” ማለት እንደሆነ ይታመናል። ኢዩኤል ኢየሩሳሌምን፣ ቤተ መቅደሱንና ቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚከናወኑትን አገልግሎቶች በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን በሚገባ የሚያውቅ በመሆኑ ትንቢቱን የጻፈው በኢየሩሳሌም ወይም በይሁዳ ሊሆን ይችላል።—ኢዩ. 1:1, 9, 13, 14፤ 2:1, 15, 16, 32
3 የኢዩኤል መጽሐፍ የተጻፈው መቼ ነው? ይህን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ምሁራን የተለያዩ ጊዜዎችን የሚጠቅሱ ሲሆን ከ800 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 400 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት ዓመታት እንደተጻፈ ይናገራሉ። ይሖዋ በኢዮሣፍጥ ሸለቆ በብሔራት ላይ የቅጣት ፍርዱን እንዳስፈጸመባቸው የሚገልጸው መግለጫ፣ ኢዩኤል ትንቢቱን የጻፈው የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ኢዮሣፍጥ በአምላክ እርዳታ ታላቅ ድል ከተቀዳጀ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል፤ ይህም ትንቢቱ የተጻፈው ኢዮሣፍጥ ከነገሠበት ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ936 በኋላ እንደሆነ ያመለክታል። (ኢዩ. 3:2, 12፤ 2 ዜና 20:22-26) ነቢዩ አሞጽ ከኢዩኤል ጽሑፍ ሳይጠቅስ አልቀረም። ስለዚህ የኢዩኤል ትንቢት የተጻፈው ከአሞጽ ትንቢት በፊት ነበር ማለት ነው፤ አሞጽ ትንቢት መናገር የጀመረው በ829 እና በ804 ከክርስቶስ ልደት በፊት መካከል በነበሩት ዓመታት ነው። (ኢዩ. 3:16፤ አሞጽ 1:2) በተጨማሪም መጽሐፉ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ ከሆሴዕና ከአሞጽ መጻሕፍት መካከል መቀመጡ ቀደም ሲል የተጻፈ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ የኢዩኤል ትንቢት በ820 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ እንደተጻፈ ይገመታል።
4 የኢዩኤል ትንቢት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መጠቀሱ ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል። ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት ‘ነቢዩ ኢዩኤልን’ ከጠቀሰ በኋላ ከትንቢቶቹ አንዱ በዚያ ቀን ፍጻሜ እንዳገኘ ተናግሯል። ጳውሎስም ይህንኑ ትንቢት ከጠቀሰ በኋላ በአይሁዳውያንም ሆነ አይሁዳውያን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ገልጿል። (ኢዩ. 2:28-32፤ ሥራ 2:16-21፤ ሮሜ 10:13) ኢዩኤል በጎረቤት ብሔራት ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች በሙሉ በትክክል ተፈጽመዋል። ታላቋ የጢሮስ ከተማ በናቡከደነፆር የተወረረች ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ታላቁ እስክንድር የጢሮስን የደሴት ከተማ አውድሟል። ፍልስጥኤምም በተመሳሳይ ጠፍታለች። ኤዶም ምድረ በዳ ሆናለች። (ኢዩ. 3:4, 19) አይሁዳውያን የኢዩኤል መጽሐፍ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል መሆኑን ተጠራጥረው የማያውቁ ሲሆን በተለምዶ ንዑሳን ወይም ደቂቀ ነቢያት ከሚባሉት መጻሕፍት መካከል የሁለተኛነትን ቦታ ሰጥተውታል።
5 የኢዩኤል የአጻጻፍ ስልት ግልጽና ሥዕላዊ ነው። አንዳንድ ሐሳቦችን ጎላ ለማድረግ ሲል ይደጋግማል፤ እንዲሁም በተነጻጻሪ ዘይቤያዊ አነጋገር ይጠቀማል። አንበጦች ሰዎች፣ ሕዝብና ሠራዊት ተብለዋል። ጥርሳቸው የአንበሳ፣ መልካቸው የፈረስ ሲሆን ለጦርነት የሚዘምት ሠራዊት የሚነዳቸው ሠረገሎች ዓይነት ድምፅ ያሰማሉ። ዘ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል ስለ አንበጦች የሚገልጽ መጽሐፍን በመጥቀስ “ኢዩኤል ስለ አንበጦች ወረራ የሰጠው ዝርዝር መግለጫ በትክክለኛነቱ ተወዳዳሪ ሊገኝለት አልቻለም” ብሏል።a አሁን፣ ኢዩኤል አስፈሪ ስለሆነው የይሖዋ ቀን የሚናገረውን ትንቢት እናዳምጥ።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
12 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ኢዩኤል የሚያስተክዝ ነቢይ እንደሆነ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአምላክ ሕዝቦች አመለካከት ሲታይ ታላቅ የመዳን መልእክት አብሳሪ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 10:13 ላይ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ሲል ይህን ሐሳብ ጎላ አድርጎ ገልጾታል። (ኢዩ. 2:32) የኢዩኤል ትንቢት በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ በአስደናቂ ሁኔታ ተፈጽሟል። በዚያ ወቅት ጴጥሮስ የአምላክ መንፈስ በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ መፍሰሱ የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜ መሆኑን በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ ተናግሯል። (ሥራ 2:1-21፤ ኢዩ. 2:28, 29, 32) ጴጥሮስ “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል” የሚሉት የኢዩኤል ቃላት ትልቅ ትንቢታዊ ትርጉም ያላቸው መሆኑን አበክሮ ተናግሯል።—ሥራ 2:21, 39, 40
13 ኢዩኤል የገለጸው የአንበጦች መቅሰፍት ራእይ ምዕራፍ 9 ላይ ከተገለጸው መቅሰፍት ጋር በጣም እንደሚመሳሰል መመልከት ይቻላል። በዚህ መቅሰፍትም ላይ ፀሐይ እንደ ጨለመች ተነግሯል። አንበጦቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስላሉ፣ የብዙ ሠረገሎች ድምፅ የሚመስል ድምፅ ያሰማሉ እንዲሁም ጥርሳቸው የአንበሳ ጥርስ ይመስላል። (ኢዩ. 2:4, 5, 10፤ 1:6፤ ራእይ 9:2, 7-9) በኢዩኤል 2:31 ላይ ፀሐይ እንደምትጨልም ከተነገረው ትንቢት ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ በኢሳይያስ 13:9, 10 እና ራእይ 6:12-17 ላይ ይገኛል፤ ከዚህም በላይ ኢየሱስ ይህ ትንቢት የሚፈጸመው የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በሚመጣበት ጊዜ እንደሆነ ባመለከተበት በማቴዎስ 24:29, 30 ላይም ይኸው መግለጫ ሰፍሯል። በኢዩኤል 2:11 ላይ የሚገኘው “የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ፣ እጅግም የሚያስፈራ ነው” የሚለውም ጥቅስ ሚልክያስ 4:5 ላይ ይገኛል። ስለዚህ “የጨለማና . . . የድቅድቅ ጭጋግ ቀን” የሚገልጽ ተመሳሳይ ሐሳብ በኢዩኤል 2:2 እና በሶፎንያስ 1:14, 15 ላይም እናገኛለን።
14 የራእይ ትንቢት ‘ታላቁን’ የመለኮታዊ ቁጣ ‘ቀን’ ያመላክታል። (ራእይ 6:17) ኢዩኤልም ስለዚህ ቀን ትንቢት ከመናገሩም በላይ ታላቁ ‘የይሖዋ ቀን’ በብሔራት ላይ ሲመጣ ከለላ ለማግኘትና ለመዳን የአምላክን ስም የሚጠሩ ሁሉ ‘እንደሚድኑ’ ይገልጻል። ይሖዋ ለሕዝቡ “መሸሸጊያ” ይሆናል። በኤደን የነበረው ብልጽግና ይመለሳል:- “በዚያ ጊዜ ተራሮች፣ አዲስ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤ ኰረብቶችም ወተት ያፈሳሉ፤ በይሁዳ ያሉ ሸለቆዎች ሁሉ ውሃ ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ቤት ምንጭ ይፈልቃል።” ኢዩኤል እንደገና ስለመቋቋም የሚገልጹትን እነዚህን አስደናቂ ተስፋዎች ሲናገር የይሖዋ አምላክን ሉዓላዊነት ከፍ አድርጓል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችም በይሖዋ ታላቅ ምሕረት ተጠቅመው እንዲመለሱ ተማጽኗል። “ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ተመለሱ፤ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ . . . ነውና” ብሏል። ይህን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተነገረ ጥሪ የተቀበሉ ሁሉ ዘላለማዊ በረከት ያገኛሉ።—ኢዩ. 2:1, 32፤ 3:16, 18፤ 2:13
[የግርጌ ማስታወሻ]
a 1956 ጥራዝ 6፣ ገጽ 733