የይሖዋ አገልጋዮች እውነተኛ ተስፋ አላቸው
“የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል . . . የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል።”—ሚክያስ 5:7
1. መንፈሳዊ እስራኤላውያን ለአሕዛብ መንፈስ የሚያድሱ የሆኑት እንዴት ነው?
ይሖዋ የዝናብና የጠል ፈጣሪ ነው። ሰዎች ዝናብና ጠል ይሰጡናል ብሎ ተስፋ ማድረግ ሞኝነት ነው። ሚክያስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፣ በሣር ላይ እንደሚወርድ ካፊያ፤ ሰውንም እንደማይጠብቅ፣ የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል።” (ሚክያስ 5:7) በአሁኑ ጊዜ ያለው ‘የያዕቆብ ቅሬታ’ ማን ነው? የመንፈሳዊ እስራኤል አባል የሆኑት ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀሪዎች ናቸው። (ገላትያ 6:16) መንፈሳዊ እስራኤላውያን ‘ለአሕዛብ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ [መንፈስን የሚያድስ] ጠል’ እና “በሣር ላይ እንደሚወርድ ካፊያ” ናቸው። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች አምላክ ለአሕዛብ የሰጣቸው በረከት ናቸው። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናቸው ይሖዋ እውነተኛ ተስፋ የሚሰጠውን መልእክቱን ለሰዎች ለማዳረስ ይጠቀምባቸዋል።
2. የምንኖረው በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ ቢሆንም እውነተኛ ተስፋ ሊኖረን የቻለው ለምንድን ነው?
2 ከዚህ ዓለም እውነተኛ ተስፋ የሚገኝ አለመሆኑ ብዙም የሚያስደንቅ አይደለም። በሰይጣን ዲያብሎስ ከሚተዳደረው ከዚህ ዓለም የምንጠብቀው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሥነ ምግባር ዝቅጠት፣ ወንጀል፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ ሽብርተኝነት፣ ጦርነትና እነዚህን የመሰሉ ችግሮች ብቻ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ብዙ ሰዎች ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን እያሉ ይጨነቃሉ። እኛ የይሖዋ አምላኪዎች ግን ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ስላለን ምንም አንፈራም። ይህ ተስፋ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እውነተኛ ተስፋ ነው። ይሖዋ የሚናገረው ሁልጊዜ ፍጻሜውን ስለሚያገኝ በእርሱና በቃሉ ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን።
3. (ሀ) ይሖዋ በይሁዳና በእስራኤል ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ያስጠነቀቀው ለምንድን ነው? (ለ) የሚክያስ ትንቢት በዛሬው ጊዜም ተፈጻሚነት የሚኖረው ለምንድን ነው?
3 በይሖዋ አነሳሽነት የተነገረው የሚክያስ ትንቢት በስሙ እንድንሄድ የሚያበረታን ከመሆኑም በላይ እውነተኛ ተስፋ ይሰጠናል። ሚክያስ ትንቢት በተናገረበት በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች እስራኤልና ይሁዳ ተብለው በሁለት ብሔራት ተከፍለው ነበር። ሁለቱም የአምላክን ቃል ኪዳን ቸል ብለው ነበር። ይህም በሥነ ምግባር ዝቅጠት፣ በሃይማኖታዊ ክህደትና በፍቅረ ንዋይ እንዲዋጡ አድርጓቸዋል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ እርምጃ እንደሚወስድባቸው አስጠነቀቃቸው። የይሖዋ ማስጠንቀቂያ ያነጣጠረው በሚክያስ ዘመን ይኖሩ በነበሩ ሰዎች ላይ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ያለው ሁኔታ በሚክያስ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር በጣም ስለሚመሳሰል ሚክያስ የተናገራቸው ቃላት በዚህ ዘመንም ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል። በሚክያስ መጽሐፍ ሰባት ምዕራፎች ውስጥ የምናገኛቸውን አንዳንድ ጎላ ያሉ ነጥቦች በምንመረምርበት ጊዜ ይህንን በግልጽ መገንዘብ እንችላለን።
የሚክያስ መጽሐፍ አጠቃላይ ይዘት ምን ይመስላል?
4. ሚክያስ ምዕራፍ 1 እስከ 3 የሚናገረው ስለ ምንድን ነው?
4 በመጀመሪያ የሚክያስን መጽሐፍ ይዘት ባጭሩ እንመልከት። በምዕራፍ 1 ላይ ይሖዋ የእስራኤልንና የይሁዳን ዓመፀኝነት ያጋልጣል። በዚህ ዓመፀኝነታቸው ምክንያት እስራኤል የምትጠፋ ሲሆን የይሁዳ ቅጣት ደግሞ እስከ ኢየሩሳሌም ደጃፍ ይደርሳል። ምዕራፍ 2 ባለጠጎችና ጉልበተኞች ደካሞችንና ረዳት የሌላቸውን እንደሚጨቁኑ ያጋልጣል። ሆኖም መለኮታዊ የተስፋ ቃልም ይሰጣል። የአምላክ ሕዝቦች በአንድነት ይሰበሰባሉ። ምዕራፍ 3 ደግሞ ይሖዋ በብሔሩ መሪዎችና ምግባረ ብልሹ በሆኑት ነቢያት ላይ ስላስተላለፈው የፍርድ መልእክት ይናገራል። መሪዎቹ ፍርድ ያጣምማሉ፣ ነቢያቱም ሐሰት ይናገራሉ። ያም ሆኖ ሚክያስ ስለመጪው የይሖዋ ፍርድ እንዲናገር ከመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ሥልጣን ተሰጥቶታል።
5. የሚክያስ ምዕራፍ 4 እና 5 ፍሬ ነገር ምንድን ነው?
5 ምዕራፍ 4 በዘመኑ መጨረሻ ሁሉም ብሔራት ከይሖዋ ለመማር ከፍ ብሎ ወደሚታየው የይሖዋ ቤት ተራራ እንደሚመጡ ይተነብያል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን ይጋዛል። ይሖዋ ግን ሕዝቡን መልሶ ነጻ ያወጣል። ምዕራፍ 5 መሲሑ በቤተ ልሔም ይሁዳ እንደሚወለድ ይገልጻል። ሕዝቡን እንደ እረኛ ሆኖ የሚጠብቃቸው ከመሆኑም በላይ ከጨቋኝ ብሔራት ነጻ ያወጣቸዋል።
6, 7. በሚክያስ ትንቢት ምዕራፍ 6 እና 7 ላይ የሚገኘው ዋና ዋና ነጥብ ምንድን ነው?
6 ሚክያስ ምዕራፍ 6 ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ የመሠረተውን ክስ በአቤቱታ መልክ ያቀርባል። ይሖዋ ሕዝቡ እንዲያምፁበት የሚያደርግ ምን ነገር አድርጓል? ምንም አላደረገም። እንዲያውም ይሖዋ ከአምላኪዎቹ የሚፈልጋቸው ነገሮች በጣም ምክንያታዊ ናቸው። በመንገዱ ሲመላለሱ ፍትሕን እንዲያንጸባርቁ፣ ደግነትን እንዲያሳዩና ልካቸውን እንዲያውቁ ይፈልጋል። እስራኤልና ይሁዳ ይህን ከማድረግ ይልቅ የዓመፅ መንገድ ተከትለዋል። ይህ አካሄዳቸው የሚያስከትልባቸውን ውጤት ማጨዳቸው የማይቀር ነው።
7 ሚክያስ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች ክፋት ያወግዛል። ቢሆንም ተስፋ አይቆርጥም። ‘ይሖዋን ተስፋ ለማድረግ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። (ሚክያስ 7:7) መጽሐፉ ይሖዋ ለሕዝቡ ምሕረት ማድረጉ እንደማይቀር ያለውን እርግጠኝነት በመግለጽ ይደመድማል። ይህ ተስፋ መና ሆኖ እንዳልቀረና በትክክል እንደተፈጸመ ታሪክ ይመሰክራል። ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጠው ተግሣጽ በ537 ከዘአበ ሲያበቃ ለቀሪዎቹ ምሕረት በማሳየት ወደ ምድራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።
8. የሚክያስን መጽሐፍ ይዘት በአጭሩ ግለጽ።
8 ይሖዋ በሚክያስ በኩል የሰጠን መረጃ ምንኛ ጠቃሚ ነው! ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ አምላክ እርሱን እናገለግላለን እያሉ የክህደት አካሄድ በሚከተሉ ላይ ምን እንደሚያደርግ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሰጠናል። በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉ ሁኔታዎችን ይተነብያል። በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ተስፋችንን አጠንክረን ለመያዝ ምን ማድረግ እንደሚኖርብን መለኮታዊ ምክር ይሰጠናል።
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሲናገር እናዳምጥ
9. በሚክያስ 1:2 መሠረት ይሖዋ ምን ለማድረግ ቆርጧል?
9 አሁን የሚክያስን ትንቢት ይበልጥ ዘርዘር አድርገን እንመርምር። ሚክያስ 1:2 እንዲህ ይላል:- “እናንተ አሕዛብ ሁሉ፣ ስሙ፤ ምድርም ሙላዋም ታድምጥ፤ ጌታ እግዚአብሔርም፣ እርሱም በቅዱስ መቅደሱ የሆነ ጌታ፣ ይመስክርባችሁ።” በሚክያስ ዘመን ኖረህ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ቃላት ትኩረትህን እንደሚስቡ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ይሖዋ የሚናገረው ከቅዱስ መቅደሱ ከመሆኑም በላይ ጥሪው የቀረበው ለእስራኤልና ለይሁዳ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሰው ዘር በመሆኑ ነው። በሚክያስ ዘመን ሰዎች ልዑሉን ጌታ ይሖዋን ለበርካታ ዘመናት ችላ ብለው ነበር። ይህ ሁኔታ ግን ብዙም ሳይቆይ ይለወጣል። ይሖዋ ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጧል።
10. በሚክያስ 1:2 ላይ ያሉት ቃላት ለእኛም ጠቃሚ የሆኑት ለምንድን ነው?
10 በዘመናችንም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ራእይ 14:18-20 ይሖዋ ከተቀደሰው መቅደሱ እንደሚናገር ይገልጻል። በቅርቡ ይሖዋ ወሳኝ እርምጃ ሲወስድ መላውን የሰው ልጅ የሚያናውጡ ክስተቶች ይፈጸማሉ። በዚህ ጊዜ ‘በምድር ላይ ካለው የወይን ዛፍ’ የተበላሸው ተቆርጦ ወደ ይሖዋ የቁጣ ወይን መጥመቂያ የሚጣል ሲሆን ይህም መላው የሰይጣን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠፋ ያሳያል።
11. የሚክያስ 1:3, 4 ትርጉም ምንድን ነው?
11 እስቲ ሚክያስ ይሖዋ የሚያደርገውን ሲናገር እናዳምጥ። ሚክያስ 1:3, 4 እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ እግዚአብሔር ከስፍራው ይወጣል፣ ወርዶም በምድር ከፍታዎች ላይ ይረግጣል። ተራሮችም በእሳት ፊት እንዳለ ሰም፣ በገደልም ወርዶ እንደሚፈስስ ውኃ በበታቹ ይቀልጣሉ፣ ሸለቆችም ይሰነጠቃሉ።” ይሖዋ ሰማያዊ መኖሪያውን ትቶ በመውረድ የተስፋይቱን ምድር ተራሮችና ሸለቆዎች ይረግጣል ማለት ነው? አይደለም። እንዲህ ማድረግ አያስፈልገውም። ፈቃዱ እንዲፈጸም ትኩረቱን ወደ ምድር ማድረግ ብቻ ይበቃዋል። ከዚህም በላይ የተነገሩት ጥፋቶች የሚደርሱት በነዋሪዎቹ ላይ እንጂ በግዑዛን ተራሮችና ሸለቆዎች ላይ አይደለም። ይሖዋ እርምጃ ሲወስድ ተራሮች እንደ ሰም እንደቀለጡ ወይም ሸለቆዎች በምድር መናወጥ እንደተሰነጠቁ ያህል በከሃዲዎች ላይ የሚደርሰው ጥፋትም በጣም አስከፊ ይሆናል።
12, 13. በ2 ጴጥሮስ 3:10-12 መሠረት የወደፊቱን ተስፋችንን አስተማማኝ የሚያደርገው ምንድን ነው?
12 በሚክያስ 1:3, 4 ላይ የሚገኙት ትንቢታዊ ቃላት በምድር ላይ ስለሚደርስ ጥፋት የተነገረ ሌላ ትንቢት ያስታውሳችሁ ይሆናል። በ2 ጴጥሮስ 3:10 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” የጴጥሮስ ቃላትም እንደ ሚክያስ ትንቢት ሁሉ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው በግዑዛን ሰማያትና ምድር ላይ አይደለም። የሚናገሩት በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ስለሚመጣ ታላቅ መከራ ነው።
13 እንዲህ ያለ ጥፋት መምጣቱ የማይቀር ቢሆንም ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሚክያስ የወደፊቱን ጊዜ ያለአንዳች ፍርሃት ሊጠባበቁ ይችላሉ። እንዴት? በቀጣዮቹ የጴጥሮስ መልእክት ቁጥሮች ላይ የተገለጸውን ምክር በመከተል ነው። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” (2 ጴጥሮስ 3:11, 12) ታዛዥ ልብ እንዲኖረን የምንጥር፣ በቅዱስ አኗኗር የምንመላለስና ለአምላክ ማደራችንን በድርጊት የምናሳይ ከሆነ ስለወደፊቱ ጊዜ ያለን ተስፋ አስተማማኝ ይሆናል። ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲታየን የይሖዋ ቀን በእርግጥ እንደሚመጣ ማስታወስ ይኖርብናል።
14. እስራኤልና ይሁዳ ቅጣት የሚገባቸው ለምንድን ነው?
14 ይሖዋ በሚክያስ 1:5 ላይ የጥንት ሕዝቦቹ ቅጣት የሚገባቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን?” እስራኤልንና ይሁዳን ወደ ሕልውና ያመጣቸው ይሖዋ ራሱ ነው። ሆኖም በእርሱ ላይ ዓምፀዋል። ዓመፃቸው ደግሞ እስከ ዋና ከተሞቻቸው ማለትም እስከ ሰማርያና እስከ ኢየሩሳሌም ደርሷል።
የክፋት ድርጊቶች ተስፋፍተው ነበር
15, 16. በሚክያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ክፋት ምን ነበር?
15 በሚክያስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ክፋት በሚክያስ 2:1, 2 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። “በመኝታቸው ላይ በደልን ለሚያስቡ ክፋትንም ለሚያደርጉ ወዮላቸው! ኃይል በእጃቸው ነውና ሲነጋ ይፈጽሙታል። በእርሻው ላይ ይመኛሉ፣ በግዴታም ይይዙታል፤ በቤቶችም ላይ ይመኛሉ፣ ይወስዱአቸውማል፤ ሰውንና ቤቱን፣ ሰውንና ርስቱንም ይነጥቃሉ።”
16 ስግብግብ ሰዎች የጎረቤቶቻቸውን ርስትና ቤት እንዴት እንደሚቀሙ ሲያስቡ እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር ሌሊቱ ይነጋባቸዋል። እንደነጋም የተንኮል ዘዴያቸውን ሥራ ላይ ለማዋል ይጣደፋሉ። የይሖዋን ቃል ኪዳን ቢያስቡ ኖሮ እንዲህ ያለውን ክፋት አይሠሩም ነበር። የሙሴ ሕግ ድሆችን ለመጠበቅ የሚያስችሉ መመሪያዎች ነበሩት። በዚህ ሕግ መሠረት ማንኛውም ቤተሰብ ርስቱን እስከወዲያኛው አያጣም ነበር። እነዚህ ስግብግብ ሰዎች ግን ይህን ሁሉ ከቁምነገር አያስገቡም። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘውን ሕግ ችላ ብለዋል።
17. አምላክን እናገለግላለን እያሉ ቁሳዊ ጥቅሞችን የሚያስቀድሙ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?
17 ይህ ታሪክ አምላክን እናገለግላለን የሚሉ ሰዎች መንፈሳዊ ግቦችን ችላ ብለው ቁሳዊ ጥቅሞችን ማስቀደም ሲጀምሩ ምን እንደሚደርስባቸው ያሳያል። ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ክርስቲያኖች “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” ሲል አስጠንቅቋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9) አንድ ሰው ገንዘብ ማግኘትን የሕይወቱ ዋነኛ ግብ ካደረገ የሐሰት አምላክን ማለትም ብርን ወይም ሀብትን ማምለክ ጀምሯል ማለት ነው። ይህ የሐሰት አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ሊሰጠው አይችልም።—ማቴዎስ 6:24
18. በሚክያስ ዘመን ቁሳዊ ሃብት ያሳድዱ የነበሩ ሰዎች ምን እንደሚደርስባቸው ተነግሯቸዋል?
18 በሚክያስ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎች በቁሳዊ ነገሮች መታመን ከንቱ መሆኑን ከደረሰባቸው መከራ ተምረዋል። በሚክያስ 2:4 ላይ ይሖዋ “በዚያ ቀን በምሳሌ ይመስሉባችኋል፣ በጽኑ ልቅሶም ያለቅሱላችኋል፤ እነርሱም:- ፈጽመን ጠፍተናል፤ የሕዝቤን እድል ፈንታ ይሰፍራል፣ እርሱንም የሚከለክል የለም፤ እርሻችንን ለዓመፀኞች ይከፍላል ይላሉ” ሲል አስጠንቅቋል። አዎን፣ የሌሎችን ቤትና እርሻ የዘረፉ ሁሉ የገዛ ራሳቸውን ርስት ያጣሉ። ወደ ባዕድ አገር ይጋዙና ንብረታቸው ‘የዓመፀኞች’ ወይም የአሕዛብ ምርኮ ይሆናል። ሃብት አግኝተን ተደላድለን እንኖራለን የሚለው ተስፋቸው እንደ ጉም በኖ ይጠፋል።
19, 20. በይሖዋ የታመኑ አይሁዳውያን የትኛው ትንቢት ሲፈጸም አይተዋል?
19 በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች ተስፋ ግን ከንቱ ሆኖ አይቀርም። ይሖዋ ለአብርሃምና ለዳዊት የገባውን ቃል ኪዳን አይረሳም። እንደ ሚክያስ እርሱን ለሚወድዱና ሕዝቡ በሚፈጽመው ክህደት ለሚያዝኑት ምሕረት ያደርጋል። እንደነዚህ ላሉት ቅን ሰዎች ሲባል አምላክ በቀጠረው ቀን የተሃድሶ ዘመን ይመጣል።
20 ይህ የሆነው ከባቢሎን ውድቀት በኋላ አይሁዳውያን ቀሪዎች ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱበት በ537 ከዘአበ ነው። በዚያን ጊዜ የሚክያስ 2:12 ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን አገኘ። ይሖዋ እንዲህ ይላል:- “ያዕቆብ ሆይ፣ ሁለንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፣ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፤ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።” ይሖዋ ምንኛ አፍቃሪ አምላክ ነው! ሕዝቡን ከቀጣ በኋላ ቀሪዎች እንዲመለሱና ለአባቶቻቸው በሰጠው ምድር እንዲያገለግሉት ፈቅዷል።
ከዘመናችን ጋር ያለው ተመሳሳይነት
21. በጊዜያችን ያለው ሁኔታ በሚክያስ ዘመን ከነበረው ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
21 እነዚህን ሁለት ምዕራፎች ከተመለከትህ በኋላ ዛሬ ያለው ሁኔታ በዚያ ዘመን ከነበረው ጋር ምን ያህል እንደሚመሳሰል ስታውቅ መገረምህ አይቀርም። እንደ ሚክያስ ዘመን ሁሉ ዛሬም አምላክን እናገለግላለን የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። እንደ ይሁዳና እስራኤል ሁሉ እነርሱም እርስ በርሳቸው የተከፋፈሉ ከመሆኑም በላይ ጦር እስከመማዘዝ ደርሰዋል። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ባለጠጎች ድሆችን ይጨቁናሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የተወገዙ ድርጊቶችን አይተው እንዳላዩ የሚያልፉ ሃይማኖታዊ መሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ሕዝበ ክርስትና ከሌሎቹ ‘የታላቂቱ ባቢሎን’ አባላት ማለትም በዓለም ዙሪያ ካሉ የሐሰት ሃይማኖቶች ጋር በቅርቡ የምትጠፋ መሆኗ ሊያስደንቀን አይገባም። (ራእይ 18:1-5) በሚክያስ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ይሖዋ በምድር ላይ የሚቀሩ ታማኝ አገልጋዮች ይኖሩታል።
22. ተስፋቸውን በአምላክ መንግሥት ላይ ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች የትኞቹ ናቸው?
22 ታማኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 ከሕዝበ ክርስትና ጋር የነበራቸውን ንክኪ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቋርጠው የመንግሥቱን ምሥራች ለአሕዛብ የማወጁን ሥራ ተያያዙት። (ማቴዎስ 24:14) የመጀመሪያ ሥራቸው ቀሪዎቹን የአምላክ እስራኤል አባላት መሰብሰብ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች መጉረፍ ጀመሩና ሁለቱ ክፍሎች ‘በአንድ እረኛ የሚመሩ አንድ መንጋ’ ሆኑ። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ ታማኝ አምላኪዎች አምላክን የሚያገለግሉት በ234 አገሮች ቢሆንም እውነተኛ ‘አንድነት’ አላቸው። በአሁኑ ጊዜ በረቱ ሞልቶ ‘የሰዎች’ ማለትም የወንዶች፣ የሴቶችና የሕፃናት ‘ድምፅ’ የሚሰማበት ሆኗል። ተስፋቸውን ያደረጉት በዚህ ሥርዓት ላይ ሳይሆን በቅርቡ ምድርን ገነት በሚያደርገው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው።
23. ተስፋህ አስተማማኝ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?
23 ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎችን በማስመልከት የሚክያስ ምዕራፍ 2 የመጨረሻ ቁጥር “ንጉሣቸውም በፊታቸው አልፎአል፣ እግዚአብሔርም [“ይሖዋም፣” NW] በራሳቸው ላይ ነው” ይላል። አንተስ በዚህ ይሖዋ ግንባር ቀደም ሆኖ በሚመራው የድል ሰልፍ ንጉሥህን ኢየሱስ ክርስቶስን ተከትለህ ወደፊት ስትተም ይታይሃል? ከሆነ ድሉ የተረጋገጠ ተስፋህም አስተማማኝ እንደሆነ የጸና እምነት አለህ ማለት ነው። በሚክያስ ትንቢት ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ተጨማሪ ጎላ ያሉ ነጥቦችን ስንመረምር ይህ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልሃል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በሚክያስ ዘመን ይሖዋ በይሁዳና በእስራኤል ላይ እርምጃ ለመውሰድ የወሰነው ለምን ነበር?
• አምላክን እናገለግላለን እያሉ ቁሳዊ ጥቅሞችን የሚያስቀድሙ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል?
• ሚክያስ ምዕራፍ 1 እና 2 የወደፊቱ ተስፋህ አስተማማኝ መሆኑን ያረጋገጠልህ እንዴት ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሚክያስ ትንቢት በመንፈሳዊ ያበረታናል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ537 ከዘአበ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደተመለሱት አይሁዳውያን ቀሪዎች መንፈሳዊ እስራኤላውያንና አጋሮቻቸውም እውነተኛውን አምልኮ ያራምዳሉ